Thursday, February 22, 2024

የአያልነሽ ወጎች

ጸሐፊ: አፈንዲ ሙተቂ

-------

ከሰው ቤት ትቼው የሄድኩትን የመጽሐፍ መደርደሪያዬን ስበረብር “መስታወት” የተሰኘ የድሮ መጽሔት ምዝዝ ብሎ ወጣ፡፡ እንደ ዋዛ ዐይኔን ከመፅሔቱ ላይ ጣል ሳደርግም የ“አያልነሽ” ፎቶ ታየኝ፡፡ ከፎቶው አጠገብም እንዲህ የሚል ጽሑፍ ሰፍሮ አነበብኩኝ፡፡


“አቶ መለስ የራሷ ድርጅት የላትም፤ እራሷ ድርጅት ትሆን እንጂ” ያሉት ሳያውቁ ቀርተው ነው ብሎ ማመን ያዳግተኛል”፡፡


አቶ መለስ ዜናዊ እንዲህ ማለታቸው የተነገረው ገና ጫካ ሳሉ ከሲ.አይ.ኤው ፖል ሂንዝ ጋር ባደረጉት ውይይት እንደሆነ ተዘግቧል (በርግጥ አቶ መለስ ያሉት “ራሷ ድርጅት ናት” ሳይሆን “እርሷ በራሷ የምትታገል ታጋይ ናት እንጂ ከየትኛውም ድርጅት ጋር የወገነች አይመስለኝም” ነው፡፡ ፖል ሄንዝ የውይይቱን ጭማቂ በአሜሪካ ይፋ ካደረገ በኋላ በተለያዩ መጽሔቶች ላይ ታትሞ ነበር)፡፡


ወይ “አያልነሽ”! ስንቱን ያንቀጠቀጠች ጀግና መሰለቻችሁ?! ለደርግ ራስ ምታት ሆና በጎንደር እና በጎጃም እንደፈለገችው ትንሸራሸር ነበር፡፡ በርሷ ጀግንነት የተመሰጠው የጎጃም ህዝብ “አያልነሽ….ክላሽ ልግዛልሽ” እያለ በሰርግ ላይ የሚዘፈን የአጀብ ዜማ እስከ መውጣት ደርሷል፡፡ በደርግ እግር የተተካው ኢህአዴግም በርሷ ምክንያት ክፉኛ ታውኮ ነበር፡፡ እርሷ ስትያዝ ደግሞ ኢህአዴጎች በየስፍራው የደስታ መድፍ መተኮሳቸው በሰፊው ተወርቷል፡፡


የ“አያልነሽ” ነገር በጊዜ ሰረገላ ወደ ኋላ እያበረረኝ የድሮ ትዝታዬን ቀሰቀሰው፡፡ ስለ“አያልነሽ” አመጸኛነት ሳስብ የያኔው ትውልድ የዓላማ ጽናት ከፊቴ እየመጣ በሃሳብ አስተከዘኝ፡፡ “የኔ ትውልድስ እንደዚያ ዓይነት ጀግኖችን ያወጣ ይሆን?” እያልኩ ደጋግሜ ራሴን ጠየቅኩኝ፡፡


ከሀገር ጭምር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ለመሆን የበቃችው ያቺ ሴት ዛሬ በትግሉ ውስጥ የለችም፡፡ ወደ ሰላማዊ ኑሮ ገብታ የልጆች እናት ሆናለች፡፡ ሆኖም የታሪካችን አካል ነችና በወቅቱ ስለርሷ ላልሰሙት ታሪኳን የማድረስ ግዴታ አለብን፡፡ እነሆ አያልነሽን ከብዙ በጥቂቱ ልናስቃኛችሁ ነው፡፡ 

*****

የደርግ መንግሥት በግንቦት 20/1983 ሲገረሰስ ኢሕአዴግ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመጣመር የሽግግር መንግሥት እንዲመሰርት ተወስኖ ነበር፡፡ ኢሕአዴግም በለንደኑ ኮንፈረንስ የተወሰነውን ውሳኔ ተቀብሎ ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ለልዩ ልዩ ድርጅቶችም የጉባኤ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ በዚህም መሰረት በርካታ ድርጅቶች ወደ አዲስ አበባ መጉረፍ ጀመረ፡፡ ይሁንና በዚያ ዘመን ከኢህአዴግና ከኦነግ ቀጥሎ ከፍተኛ ስም የነበረው የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሀይሎች ቅንጅት (ኢ.ዲ.ሀ.ቅ) በጉባኤው እንዳይሳተፍ ተከለከለ (ኢዲሀቅ የኢህአፓ፣ የመኢሶን፣ የኢፒዲኤ እና የኢዲዩ ጥምረት ነበር)፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ጊዜያዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ኢዴሀቅ በጉባኤው ላይ እንዳይሳተፍ የተከለከለበትን ምክንያት በሰኔ ወር አጋማሽ ለጋዜጠኞች ሲያብራሩ እንዲህ ብለው ነበር።


“ኢዴሀቅ በጊዜያዊ መንግሥቱ ላይ ጦርነት አውጇል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ያወጀውን የጦርነት አዋጅ አላነሳም፤ ይህም የጦርነት አዋጅ ድርጅቱ በሰላምና በዲሞክራሲ ጉዳይ ላይ በሚመክር በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እንደሌለው ያሳያል”። 


አቶ መለስ እንዲህ በማለት የገለጹት ኢዴሀቅ የተመሰረተው በመጋቢት 1983 ነበር፡፡ ይሁንና ይህ ድርጅት በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በጊዜያዊ መንግሥቱ ላይ ጦርነት አውጇል መባሉ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኖ ነበር (ጊዜያዊ መንግሥቱ በግንቦት ወር 1983 የደርግ ውድቀትን ተከትሎ ነበር የተመሰረተው)፡፡ ኢዴሀቅ የደርግ ብሔራዊ ሸንጎ በመጨረሻ ጉባኤው ያስተላለፈውን ውሳኔ በመደገፍ ሚያዚያ 16/1983 መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡ በመሆኑም አቶ መለስ “ኢዴሀቅ ጦርነት አውጇል” ያሉት ያንን መግለጫ ተንተርሰው እንደሆነ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች በወቅቱ የተናገሩት ጉዳይ ነው፡፡

*****

ከጥቂት ጊዜ በኋላ አቶ መለስ የተናገሩት የጦርነት ወሬ ውሸት እንዳልሆነ የሚያረጋግጥ ጭምጭምታ ተሰማ፡፡ ከወደ ጎንደርና ጎጃም አካባቢ የጦርነት ዜና መናፈስ ጀመረ፡፡ ኢህአዴግ እና አንድ ያልታወቀ ሀይል ብርቱ ውጊያ ላይ መሆናቸው ተነገረ፡፡ የዚያ ያልታወቀ ሀይል ኮማንደርም ሴት ናት መባሉ ደግሞ የብዙዎችን ቀልብ ሳበ፡፡ ያ ሀይል ማን ነው? ሴቲቷስ ማን ናት?

ኢህአዴግ በወቅቱ ስለውጊያው ትንፍሽ አላለም፡፡ ከአሜሪካና ከአውሮፓ የሚተላለፉ የተቃዋሚ ሬድዮዎችና አንዳንድ በራሪ ወረቀቶች ነበሩ ዜናውን ሲያስተላልፉ የነበሩት፤ የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮም ወሬውን አልፎ አልፎ ይነካካ ነበር፡፡ ከነዚያ ምንጮች ለማወቅ እንደተቻለው በወቅቱ ከኢህአዴግ ጋር ሲዋጋ የነበረው የኢህአፓ ሰራዊት ነው፡፡ የሰራዊቱ ኮማንደርም “አያልነሽ” ነበረች፡፡ በርሷ የሚመራው ጦር ከ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በምዕራብ ጎንደር ቆላማ ክፍል (ወገራ፣ ጭልጋ፣ ቋራ ወዘተ…) እና በመተከል አውራጃ ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡ (“መተከል” በዘመኑ የጎጃም ክፍለ ሀገር ትልቁ አውራጃ ሲሆን በደርግ የመጨረሻ ዓመታት ራሱን ችሎ “የመተከል አስተዳደር አካባቢ” ተብሎ ተሰይሞ ነበር፡፡ “መተከል” በአሁኑ ዘመን የቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል አካል ሆኗል)፡፡


አያልነሽ ደርግን ስትዋጋ ለብዙዎች ተራ ሽፍታ ትመስል ነበር፡፡ ይህም የደርግ ፕሮፓጋንዳ ክፍል የኢህአፓን መኖር ለህዝቡ ለማሳወቅ ባለመፈለጉ ምክንያት የመጣ ነው፡፡ ደርግ “ኢህአፓ ተደምስሷል” ብሎ በይፋ አውጆ ስለነበር አያልነሽ የኢህአፓ ኮማንደር መሆኗ ከተገለጸ “ኢህአፓ” አሁንም አለ እንዴ?” የሚል ጥያቄ ከህዝቡ ይነሳብኛል የሚል ፍርሃት ነበረው፡፡ ለዚህም ነበር የደርግ ሰዎች ኢህአፓን ትተው “ አያልነሽ… አያልነሽ..” ሲሉ የነበሩት፡፡ እንደ ደርግ ሰዎች አባባል “አያልነሽ ቀኛዝማች ስሜነህ የሚባሉ ጎንደሬ ልጅ ናት፡፡ የምትዋጋውም አባቷ በአብዮት ሀይሎች ስለተገደለባት የአባቷን ደም ለመበቀል” ነው፡፡


ነገሩ ግን እውነት አልነበረም፡፡ አያልነሽ የኢህአፓ ሰራዊት የምዕራብ ክፍል ኮማንደር ነበረች፡፡ ከሰራዊቱ ጋር የተቀላቀለችውም በቂም በቀል ተነሳስታ ሳይሆን ድርጅቱ የከተማ የትጥቅ ትግሉን ትቶ ወደ ገጠር ባፈገፈገበት ጊዜ ነው፡፡ ታዲያ አያልነሽ የኢህአፓ አባል የሆነችው በልጅነቷ (በአስራ አንድ ዓመቷ) ነው፡፡ ይህች ሴት የተወለደችው በጎንደር ከተማ ሲሆን እውነተኛ ስሟ “የዓለም ገዥ ከበደ” ነው፡፡ “አያልነሽ” በኢህአፓ አባልነቷ የተሰጣት የትግል ስሟ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ የምትታወሰውም በዚህ ስም ነው፡፡

*****

አያልነሽ በዘመነ ደርግ ሰራዊቷን በቆራጥነት መምራት ቀጠለች፡፡ በተለይ ጎጃምና ጎንደር የራሷ ነጻ ግዛት እስኪመስል ድረስ በህዝቡ ዘንድ ስሟ ተደጋግሞ ይወሳ ነበር፡፡ በ1980 መጨረሻ ገደማ በእርዳታ ሰራተኛነት ሽፋን የመተከል አውራጃ ዋና ከተማ የነበረችውን ፓዌን የጎበኘው የሲ.አይ.ኤው ዝነኛ ሰላይ ፖል ሄንዝ የአካባቢው ሰው ለአያልነሽ የነበረውን አድናቆት ልብ ብሎ አስተዋለ፡፡ እናም ከዓመት በኋላ ወደ ሰሜን አሜሪካ ለጉብኝት የጋበዘውን ወጣቱን የህወሐትና የኢህአዴግ መሪ አቶ መለስ ዜናዊን ስለአያልነሽ ጠየቀው፡፡ ታዲያ አቶ መለስም ልክ እንደ ደርግ ሰዎች የኢህአፓን ስም ላለማንሳት ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረበት፡፡ በወቅቱ የኢህዴን (የአሁኑ ብአዴን) ስም እንጂ የኢህአፓ ስም ተጋንኖ እንዲወራ አይፈለግም ነበርና “አያልነሽ በራሷ የምትታገል ታጋይ ናት እንጂ በድርጅት የታቀፈች አይመስለኝም” በማለት ጉዳዩን አድበስብሶት አለፈው፡፡


ደርግ ተደመሰሰ፡፡ ኢህአዴግም በርሱ ቦታ መንግሥት ሆነ፡፡ የአያልነሽ ቀጣይ ትግልም ከአዲሱ መንግሥት ጋር ሆነ፡፡ ሁለቱ ሀይሎች ከአሲምባ ጀምሮ ይተዋወቃሉ፡፡ ሁለቱም ከፍተኛ ግጭቶችን አድርገዋል፡፡ ይሁንና ኢህአዴግ በጎንደርና በጎጃም የነበረው የኢህአፓ ሰራዊት በገበሬው ልብ የገባ ሰላልመሰለው አያልነሽና ጦሯን በቀላሉ የሚያባርራቸው ፋኖዎች አድርጎ ነበር የገመተው፡፡ በአማራው ምድር ሲገባ ግን ሁኔታው እርሱ ከጠበቀው ውጪ ሆኖ አገኘው፡፡ እርሱ ሞቷል ብሎ የገመተው ኢህአፓ የተሰኘው ታሪካዊ ጠላቱ ለቀጣይ ትግሉ አደጋ ሊሆን እንደሚችል ተረዳ፡፡ ስለዚህ እርሱም እንደ ደርግ “ኢህአፓ መጥፋት ያለበት ድርጅት ነው” በማለት ወሰነ፡፡ በወቅቱ ተጠራርጎ ሊወድቅ የሚንገታተውን የደርግ መንግሥት በአንድ ዙር ካጠናቀቀው በኋላ በኢህአፓ ላይ ለመዝመት ቆረጠ፡፡


ከላይ እንደገለጽኩትም በሰኔ 1983 መጀመሪያ ላይ ከኢህአፓ ጋር የሚደረገው ጦርነት በጎጃምና በጎንደር ተጀመረ፡፡ ሚዲያው “ደርግ ወድቆ ሰላም ሰፍኗል” በሚልበት ሰዓት ጎጃምና ጎንደር በጦርነት እሳት እየተለበለቡ መሆናቸው ታወቀ፡፡ ኢህአዴጎች ስም ያልሰጡት የዚያ ዘመቻ ዓላማ “ኢህአፓ”ን ማጥፋት ሊሆን እንደሚችልም በስፋት ተወራ፡፡

ጦርነቱ ቀጠለ፡፡ በደርግ ላይ በተጎናጸፈው ድል ከፍተኛ ሞራል የሰነቀው የኢህአዴግ ጦር በኢህአፓ ላይ ተረባረበ፡፡ በቁጥሩ አነስተኛ በዓላማ ጽናቱ ግን ከፍተኛ የነበረውና በአያልነሽ የሚመራው የኢህአፓ ጦር በበኩሉ የኢህአዴግን ዘመቻ ለመመከት ጥረት ማድረጉን ቀጠለ፡፡ በጦርነቱ ሳቢያ ጎጃምና ጎንደር ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ ሆኑ፡፡ በተለይ ደርግ ከወደቀ በኋላ አዲሱን የኢህአዴግ መንግሥት በገፍ ለመቀላቀል ይጠባበቁ የነበሩ ቀደምት የኢህአዴግ ታጋዮች፣ ስደተኛ ምሁራንና ሌሎች የድል አጥቢያ አርበኞች ከሱዳን ወደ አዲስ አበባ ለመንቀሳቀስ ክፉ ፈተና ገጠማቸው (በወቅቱ የአውሮፕላን ጉዞ ተቋርጦ ስለነበር ከሱዳን ወደ አዲስ አበባ የሚኬደው በመኪና ነው)፡፡


የኢህአዴግ ሰዎች ጦርነቱን በቀላሉ የሚያጠናቅቁበትን መላ ዘየዱ፡፡ በዚህም መሰረት ዋናው ጦርነት የኢህአፓ ተዋጊዎች የቆራጥነት ምልክትና የጽናት አብነት በሆነችው ጀግና ኮማንደር ላይ ማተኮር እንዳለበት ወሰኑ፡፡ በመሆኑም ኮማንደር አያልነሽን ማሳደድ ጀመሩ፡፡ እርሷን ለመግደል ወይንም ከነነፍሷ ለመያዝ እንዲቻል በርካታ ልምድ ያለውን “አሉላ ክፍለ ጦር” ወደ ስፍራው ላኩ፡፡ አያልነሽና ጓዶቿም ለዘመናት ሲታገሉበት የነበረውን የኢህአፓን እስትንፋስ ለማስቀጠል የሞት ሽረት ትግል ማካሄዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ከሰኔ 1983 እስከ መስከረም 1984 ድረስ በልዩ ልዩ ስፍራዎች ከባድ ውጊያዎች ተካሄዱ፡፡ ይሁንና በብዙ እጥፍ ከሚበልጠው የኢህአዴግ ሰራዊት ጋር የተጋጠመው የኢህአፓ ሰራዊት በለስ ሳይቀናው ቀረ፡፡ በነሐሴ 1983 በጎንደር ክፍለ ሀገር ቋራ አውራጃ በተካሄደው ጦርነት እውቋ ኮማንደር አያልነሽ ከእልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ በኢሕአዴግ ተዋጊዎች እጅ ወደቀች፡፡ በመስከረም ወር አጋማሽ የኢህአፓ መስራች አባልና ለረጅም ጊዜ የጦሩ አዛዥ የነበረው ጸጋዬ ገብረመድህን (ደብተራው) ከጥቂት ጓዶቹ ጋር ተያዘ፡፡ ከጥቅምት እስከ ህዳር 1984 በነበረው ጊዜ ሁሉም ነገር አበቃለት፡፡ የአህአፓ ጦር ለረጅም ዘመናት ሲታገልበት ከነበረው የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሙሉ በሙሉ ተደመሰሰ፡፡


ኢህአዴግ ከጎጃምና ጎንደር የማረካቸውን የኢህአፓ ሰዎች ወደ መቀሌ እስር ቤት ወሰዳቸው፡፡ ከአራት ወራት እስር በኋላ አያልነሽና ጥቂት ሰዎች የተሐድሶ ስልጠና ተሰጥቷቸው ተለቀቁ፡፡ እነ ጸጋዬ ገብረመድህን ግን በዚያው ቀሩ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ያሉበት ሁኔታ በግልጽ አይታወቅም፡፡

*****

አያልነሽ በእስር ላይ እያለች ለአንድ ቀን በቴሌቪዥን መስኮት ታይታ ነበር፡፡ ታዲያ በወቅቱ እርሷን ያዩዋት ሰዎች መልኳ ቀደም ሲል ስለርሷ ያስቡት ከነበረው ውጪ ሲሆንባቸው በጣም ነበር የተደነቁት፡፡ “አያልነሽ” ሲባል ብዙዎች የጠበቁት በጣም ግዙፍ፤ ግድንግድ፤ ጨካኝ ፊት ያላት፤ መልከ ጥፉና አስፈሪ፣ ጎፈሬዋን ያንጨባረረች፣ ዕድሜዋ ከአርባዎቹ የሚበልጥ፣ የወታደር ልብስ የለበሰች ሴት ነበር፡፡ ሆኖም በቴሌቪዥን የታየችው አያልነሽ በግልባጩ የቀይ ዳማ፣ መለሎ፣ ዐይኖቿ እንደ ኮከብ የሚያበሩ፣ ጸጉሯ በስርዓቱ የተበጠረ፣ ሸንቃጣ ሰውነት ያላት፤ በጣም ቆንጆ የ27 ዓመት ወጣት ነበረች፡፡


አያልነሽ ከእስር ከተለቀቀች በኋላ ለጥቂት ጊዜ በአዲስ አበባ ቆየች፡፡ በ1985 መጀመሪያ ላይ ወደ አውሮፓ ተሻግራ ሀገረ ስዊዘርላንድ ገባች፡፡ እዚያም ትዳር ከመሰረተች በኋላ የልጆች እናት ሆናለች፡፡


አያልነሽ በዚያ ዘመን ስመ ገናና ነበረች፡፡ አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለችው? በኔ በኩል ወሬው የለኝም፡፡ እርሷን የሚያውቋት ሰዎች ያላቸውን መረጃ ቢያካፍሉን መልካም ነው፡፡ በነገራችን ላይ ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረአብ ውጪ ሄዶ ማስታወሻዎቹን ሲጽፍ ስለርሷ አንድ ነገር ይናገራል ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ ነገር ግን በአንድ ቦታ እንኳ የርሷን ስም አላነሳም፡፡ ከርሱ ይልቅ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አያልነሽን በመጠኑ አስታውሰዋታል፡፡ በወቅቱ ኢህአዴግን ለመቀላቀል በሱዳን በኩል ወደ ሀገር ቤት የገቡት ዶ/ር ነጋሶ በጎንደር-አዲስ አበባ መስመር የነበረው የአያልነሽ ሰራዊት ወደ አዲስ አበባ ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ እንዳስተጓጎለባቸው መስክረዋል (ለማስረጃው “ዳንዲ” የሚለውን መጽሐፍ አንብቡት)፡፡

*****

አያልነሽ በአጭሩ ይህቺ ነበረች፡፡ ስለርሷ የበለጠ የምታውቁ ሰዎች ያላችሁን መረጃ ልታካፍሉን ትችላላችሁ፡፡ በነገራችን ላይ ብዙዎቻችሁ የጠየቃችሁኝ የአያልነሽ የረጅም ጊዜ የትግል ጓደኛ የነበረው ገብረ እግዚአብሄር ወልደሚካኤል (ጋይም) ከአያልነሽ ጋር አልተማረከም፡፡ በ1985 አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተደብቆ በነበረበት ወቅት አንድ ውስጠ-አዋቂ ለኢህአዴግ የጸጥታ ሀይሎች ጠቆመበት፡፡ ኢህአዴጎችም እርሱን የሚይዝ አዳኝ ጦር ላኩበት፡፡ ሆኖም “ጋይም” እጁን መስጠት ስላልፈለገ ተኩስ ተከፈተ፡፡ ከ30 ደቂቃ የተኩስ ልውውጥ በኋላ ሞተ፡፡ (ስለዚህ ጉዳይ በዝርዝር ለማወቅ ካሻችሁ ሚያዚያ 1985 የታተመውን እፎይታ መጽሔት አፈላልጉ፡፡ “የኢህአፓው ኮማንደር በአዲስ አበባ” የሚል ጽሑፍ አውጥቶ ነበር)፡፡

*****

አፈንዲ ሙተቂ

ሸገር-አዲስ አበባ

ጥቅምት 10/2006

-------------

የቴሌግራም ቻናሌ የሚከተለው ነው።

You may join my telegram channel here


https://t.me/afandishaHarar

-----

ተማም። እናመሰግናለን። 


No comments:

Post a Comment