ጸሐፊ: አፈንዲ ሙተቂ
---
ወቅቱ የሰባተኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ነው። ስፍራው ሒጃዝ በሚባለው የዐረቢያ ምዕራባዊ ግዛት ውስጥ የምትገኘው የመካ ከተማ ናት። በዚህች ከተማ በተጧጧፈው ንግድ ገናና ስም ካፈሩት ነጋዴዎች አንዱ ኡመያ ኢብን ኸለፍ ይባላል።
ኡመያ በንግድ ተሰማርቶ ላሳየው ስኬት መንስኤው ከአያቶቹና ቅመ-አያቶቹ የወረሰውን የጣኦት አምልኮ በአጽንኦት መተግበሩ እንደሆነ የሚያምን ሰው ነበር። በሀብቱና በኑሮ ደረጃው ከብዙዎች የሚበልጥ በመሆኑም በእጅጉ ይኩራራ ነበር። በባርነት የሚያሰራቸውን አቅመ ደካሞችንም እንደ እንስሳ የሚመለከት የድንቁርና ሊቅ ነበር።
የኡመያ ድንቁርና በአምልኮውም ይንጸባረቅ ነበር። "እኔ ከባሮችና ከዝቅተኛ ሰዎች የበለጥኩ ነኝ። የማመልከው ጣኦትም ባሮቼ ከሚያመልኩት የእንጨት ጣኦት የበለጠ መሆን አለበት" የሚል አስተርዮ ነበረው። በመሆኑም እንደ አምላክ የሚሰግድለትን ጣኦት ከወርቅ አሰርቷል።
ኡመያ በባርነት ገዝቶአቸው ሌት ከቀን ይገለገልባቸው ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዱ "ቢላል ኢብን ረባህ" ይባላል። ቢላል በመካ ከተማ የተወለደ ሳተና ነበር። ወላጆቹ በተለያዩ ወቅቶች ተፈንግለው ለባርነት የተዳረጉ ግለሰቦች ሲሆኑ ከሁለቱ አንደኛቸው ከኢትዮጵያ የተወሰዱ ናቸው። ቢላል ወደ ኡመያ ቤት የተወሰደው በባርነት ተገዝቶ ነው።
ቢላል ወደ ኡመያ ቤት ከመጣ ወዲህ የጌታውን ትእዛዛት እየተቀበለ ከማገልገል አልቦዘነም። ኡመያ በቤቱ ሳሎን ውስጥ ከቁሬይሽ ባላባቶች ጋር የመወያየት ልማድ ያለው ቢሆንም ቢላል ጭውውታቸውን ከቁም ነገር ሳይቆጥር ስራውን ብቻ ይሰራ ነበር። አንድ ቀን ግን ቢላል ውይይታቸውን እንዲከታተል ያስገደደው ነገር ተከሰተ።
****
በዚያች ቀን ኡመያ እና ጓዶቹ በሳሎን ውስጥ ሆነው በመካ ስለተነሳው አዲሱ ሃይማኖት እና ሃይማኖቱን ስለሚያስተምረው ነቢይ ይወያዩ ነበር። አዲሱን እምነት የሚያስተምረው ሙሐመድ (ሰዐወ) የሚባል የበኒ ሃሺም ጎሳ ተወላጅ መሆኑን ተናገሩ። የሙሐመድ (ሰዐወ) መልእክት ዋና ጭብጥም "ጣኦት ማምለክን ተዉ፣ አንዱን አምላክ ብቻ ተገዙ" የሚል እንደሆነም አሰመሩበት። በዚህም ንዴታቸውንና ቁጭታቸውን ገለጹ።
****
በዚያች ቀን ኡመያ እና ጓዶቹ በሳሎን ውስጥ ሆነው በመካ ስለተነሳው አዲሱ ሃይማኖት እና ሃይማኖቱን ስለሚያስተምረው ነቢይ ይወያዩ ነበር። አዲሱን እምነት የሚያስተምረው ሙሐመድ (ሰዐወ) የሚባል የበኒ ሃሺም ጎሳ ተወላጅ መሆኑን ተናገሩ። የሙሐመድ (ሰዐወ) መልእክት ዋና ጭብጥም "ጣኦት ማምለክን ተዉ፣ አንዱን አምላክ ብቻ ተገዙ" የሚል እንደሆነም አሰመሩበት። በዚህም ንዴታቸውንና ቁጭታቸውን ገለጹ።
ታዲያ ተወያዮቹ በዚህ እሳቤ የተናደዱት በእኩል ደረጃ አልነበረም። ከእነርሱ መካከል ንዴቱ ጣሪያ ላይ የደረሰበት የቤቱ ባለቤት የሆነው ኡመያ ኢብን ኸለፍ ነበር። ኡመያ ንዴቱን የገለጸው እንደዚህ እያለ ነው፡፡
"ሙሐመድ "አንዱን አምላክ ብቻ ተገዙ" አለ። ይህ ምን ማለት ነው? እኔ እና ባሪያዬ የሆነው ቢላል አንድ አምላክ ልንገዛ ነው ማለት አይደለምን? እስቲ ይታያችሁ። እኔ የምገዛው ጣኦት ከወርቅ ነው የተሰራው። ቢላል የሚሰግድለት ጣኦት ግን ከእንጨት ነው የተሰራው። ሙሐመድ "ይህንን ተውትና አንዱን አምላክ ተገዙ" ሲል እኔና ባሪያዬን በእኩል ደረጃ ላይ ማስቀመጡ አይደለምን? ይህንን አንቀበልም። ሙሐመድን እስከመጨረሻው ድረስ እንታገለዋለን"
የቁሬይሽ ባላባቶች ይህንን ሲነጋገሩ ቢላል በወዲያኛው ክፍል ሆኖ በአትኩሮት ያዳምጣቸው ነበር። እነርሱ ውይይታቸውን አገባድደው ሲወጡ አሳዳሪው የሰጠውን ስራ በሙሉ ልቡ መስራት አልሆነለትም። በተለይም "ሙሐመድ የሚፈልገው እኔና የኔ ባሪያ የሆነው ቢላል እኩል ሆነን ለአንድ አምላክ እንድንሰገድ ነው" የሚለው የኡመያ ኢብን ኸለፍ ንግግር ሊያስቀምጠው አልቻለም። በመሆኑም ወደ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሄዶ ስለአዲሱ እምነት ሊጠይቃቸው ወሰነ።
ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ቢላልን በአክብሮት ተቀበሉት። ስለዲነል ኢስላም ዘርዘር አድርገው አስተማሩት። በዘሩም ሆነ በባርነቱ የማንም የበታች እንዳልሆነ ነገሩት። የሰው ልጆች ሁሉ በፈጣሪ ፊት እኩል መሆናቸውንና ለፈጣሪ ባላቸው ፍራቻ ብቻ እንደሚበላለጡም አስረዱት።
ቢላል ከነቢዩ (ሰዐወ) በተማረው ሁሉ ረካ። በድንቁርና በተዋጠው የያኔዋ የመካ ከተማ ማኅበረሰብ መካከል በባርነቱ የማይጠየፉት ቅን አሳቢዎች በመኖራቸውም ተደነቀ። የነቢዩ መንገድ ተበዳዮችን ከጭቆና ነፃ ሊያወጣ የመጣ የአርነት ፍኖት ስለመሆኑም ደመደመ። በዚያችው ቅጽበት "አሽሀዱ አን-ላኢላሀ ኢለላህ፣ ወ አሽሀዱ አንነ ሙሐመዱን ረሱሉሏህ" በማለት ሙስሊምነቱን አወጀ።
----
ቢላል እስልምናን በተቀበለበት ወቅት ነቢዩ (ሰዐወ) እምነቱን የሚያስተምሩት በሚስጢር ነው። የሙስሊሞችን ማንነት ለማወቅም አስቸጋሪ ነበር። ቢላልም እምነቱን በሚስጢር ጠብቆት ነበር። ይሁንና አንድ ቀን ሙስሊምነቱ እንዲታወቅበት ያደረገበትን ድርጊት ሲከውን ተገኘ።
----
ቢላል እስልምናን በተቀበለበት ወቅት ነቢዩ (ሰዐወ) እምነቱን የሚያስተምሩት በሚስጢር ነው። የሙስሊሞችን ማንነት ለማወቅም አስቸጋሪ ነበር። ቢላልም እምነቱን በሚስጢር ጠብቆት ነበር። ይሁንና አንድ ቀን ሙስሊምነቱ እንዲታወቅበት ያደረገበትን ድርጊት ሲከውን ተገኘ።
በዚያች ቀን ቢላል በነቢዩ (ሰዐወ) ዘንድ የነበረውን ቆይታ አገባድዶ ወደ ቤቱ ሲመለስ "አንድ ጊዜ ወደ ካዕባ ጎራ ብለህ በዚያ ዙሪያ የተኮለኮሉትን ጣኦቶች አዋርድ" የሚል ስሜት መጣበት። ይህንኑ ተከትሎም ወደ ካዕባው ጥብቅ ስፍራ ጎራ አለ። "የመካ ጣኦቶች! እናንተ ድንዙዞች! መናገርም ሆነ መስማት የምትችሉ ዱዳዎች! እስቲ አንድ ጉዳት አድርሱብኝ" እያለ ደነፋባቸው። በእጁ እየመታቸው ለእነርሰ ያላቸውን ጣላቻ አሳያቸው። ምራቁንም ተፍቶባቸው አዋረዳቸው።
ቢላል ይህንን ሲያደርግ አንዱ የመካ ነዋሪ ከኋላው ተደብቆ ያየው ነበር። ይህ ሰውዬ ቢላል ጣኦታቱን እንዲያዋርድ መነሻ የሆነው ነቢዩ ሙሐመድ የሚያስተምሩት እምነት ስለመሆኑ አልተጠራጠረም። በመሆኑም ጊዜ ሳያጠፋ ወደ ኡመያ ኢብን ኸለፍ ሄዶ ያየውን ሁሉ በዝርዝር ነገረው።
ኡመያ በሰማው ነገር በንዴት ጦፈ። በተለይም "ቢላል በጣኦቶቹ ላይ ተፍቶ ነበር" የሚለው ነገር እንደ እሳት ነው ያቃጠለው። በመሆኑም ቢላልን አሳማሚ ቅጣት ሊቀጣው ወደ ቤቱ ሄደ። ቤት እንደገባም ቢላልን ጠርቶት "አንተ የማትረባ ባሪያ! በጣኦቶቻችን ላይ ተፍተሃል የሚባለው ነገር እውነት ነው?" በማለት ጠየቀው።
"እውነት ነው። የማይጠቅሙና የማይጎዱ ዱዳዎች ናቸው። ከአንዱ አምላክ በስተቀር አምልኮ የሚገባው ምንም ነገር የለም"
"እንዲህ አልክ? አንተም የሙሐመድ ተከታይ ሆንክ"
"አዎን! ነቢዩ ከአላህ የተላኩ እውነተኛ መልእክተኛ ናቸው"
"ይህንን ነገር በቶሎ አስተባብል። ቶሎ ብለህ "ሙሐመድ ባመጣው መልእክት አላምንም፣ መካዎች ከአያት ቅድመ አያታቸው የወረሱት ሃይማኖት ትክክል ነው" በል። እምቢ ካልክ አሳማሚ ቅጣት ይከተልሃል። ዋ! ቶሎ አስተባብል"
"ላኢላሀ ኢለላህ፣ ሙሐመዱን ረሱሉሏህ"
ኡመያ በንዴት ጨሰ። በቤቱ ውስጥ ያሉት ሌሎች ባሮች ቢላልን እንዲያስሩት አዘዘ። ከዚያም በአለንጋ ይገርፈው ጀመር። ባለ በሌለ ሃይሉ ለጠለጠው። በሰውነቱ ላይ ሰንበር እስኪወጣ ድረስ ወገረው። በመሃሉም "ቶሎ ብለህ የሙሐመድን እምነት አስተባብል" እያለ ጠየቀው። የቢላል መልስ ግን "አሓዱን አሓድ" የሚል ነበር። ኡመያ በአለንጋ ላይ አለንጋ ቢቀያይር የሚፈልገውን መልስ ማግኘት አቃተው።
ኡመያ ለጥቂት ቀናት ቢላልን እንዲህ ካሰቃየው በኋላ ፍላጎቱን ለማስፈጸም ሌላ ብልሃት ቀየሰ። ይህም ቢላልን እንደ እሳት በሚለበልበው የዐረቢያ አሸዋ ላይ ራቁቱን ማስተኛት ነበር። ይሁን እንጂ ቢላል የሚበገር አልሆነም። ሰውነቱ በአሸዋው ረመጥ በሚተኮስበት ወቅት ሁሉ ከአንደበቱ የሚወጣው "አሓዱን አሐድ" የሚል ሐረግ ነበር።
ኡመያ እልሁን ሊተው አልፈቀደም። በልቡ በባሪያው ላይ የሚፈጽመውን ስቃይ በማጠናከር ወደ ድሮ እምነቱ ሊመልሰው ቆርጧል። በዚህም መሠረት ባሮቹ በበረሃው የአሸዋ ንዳድ በሚሰቃየው የቢላል ደረት ላይ ትልቅ ድንጋይ እንዲጭኑበት አዘዛቸው። ባሮቹም የተባሉትን ፈጸሙ። ቢላል በሕይወቱ አይቶት የማያውቀውን ስቃይ ተቀበለ። ይሁን እንጂ በስቃዩ ተሸንፎ እጁን አልሰጠም። ስቃዩ ቢለበልበውም ወኔው አልከዳውም። ባሮቹ በኡመያ የታዘዘውን ሁሉ በሚፈጽሙበት ወቅት ከአንደበቱ የሚወጣው "አሐዱን አሐድ" የሚል ሐረግ ነበር።
----
ኡመያ ኢብን ኸለፍ ባሪያውን ወደ ድሮ ሃይማኖቱ ማስመለስ እንደማይችል ተገንዝቧል። ይሁን እንጂ በባርነቱ የሚጸየፈው ቢላል "መከራውን ሁሉ የተቋቋመ" ተብሎ እንዲወደስ አልፈቀደም። ስለዚህ ገድሎት ሊገላገል ወስኗል። ታዲያ በዚህ መሃል በቢላል እና በሌሎች ተከታዮቻቸው የሚደርሰውን ስቃይ የሚመለከት ዜና ለነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ይደርሳቸዋል። ነቢዩም የምንጊዜም ታማኝ ወዳጃቸው የነበሩት አቡበክር አስ-ሲዲቅ በቢላልና በሌሎች ቀደምት ሙስሊሞች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ለማስቀረት የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ ሃሳብ ያቀርባሉ። አቡበክርም ባሮቹን በገንዘባቸው ሊገዙ ይወስናሉ።
----
ኡመያ ኢብን ኸለፍ ባሪያውን ወደ ድሮ ሃይማኖቱ ማስመለስ እንደማይችል ተገንዝቧል። ይሁን እንጂ በባርነቱ የሚጸየፈው ቢላል "መከራውን ሁሉ የተቋቋመ" ተብሎ እንዲወደስ አልፈቀደም። ስለዚህ ገድሎት ሊገላገል ወስኗል። ታዲያ በዚህ መሃል በቢላል እና በሌሎች ተከታዮቻቸው የሚደርሰውን ስቃይ የሚመለከት ዜና ለነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ይደርሳቸዋል። ነቢዩም የምንጊዜም ታማኝ ወዳጃቸው የነበሩት አቡበክር አስ-ሲዲቅ በቢላልና በሌሎች ቀደምት ሙስሊሞች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ለማስቀረት የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ ሃሳብ ያቀርባሉ። አቡበክርም ባሮቹን በገንዘባቸው ሊገዙ ይወስናሉ።
በዚሁ መሰረት አቡበክር ወደ ኡመያ ኢብን ኸለፍ ቤት ሄደው ቢላልን እንዲሸጡላቸው ጠየቁ። ኡመያ "በስንት ትገዛዋለህ?" አላቸው። አቡበክርም "አስር ዲናር እሰጥሃለሁ" አሉት። አስር ዲናር ትልቅ ገንዘብ ነው። በያኔዋ የመካ ገበያ የትኛውም ባሪያ ለሽያጭ ቀርቦ በዚህ ዋጋ አይሸጥም። በመሆኑም ኡመያ ቢላልን ለመግደል የደረሰበትን ውሳኔ ሰረዘው። ባሪያውን ለአቡበክር አስረክቦ ገንዘቡን ተቀበላቸው።
አቡበክር ቢላልን ይዘው ሊሄዱ መንገዳቸውን ሲጀምሩ ኡመያ ከኋላቸው እንዲህ አለ። "ይገርማል። አስር ዲናር ይቅርና በአንድ ዲናር ሽጥልኝ ቢለኝ እንኳ እቀበለው ነበር"። አበቡክር ይህንን ሲሰሙ እንዲህ አሉት።
"ወላሂ! ዋጋው መቶ ዲናር ነው ብትለኝ እንኳ እገዛህ ነበር"
አቡበክር ያን ያህል ገንዘብ ከፍለው ቢላልን የገዙት ከስቃዩ ሊገላግሉት እንጂ በባሪያነት ሊያሰሩት አልነበረም። በመሆኑም ወዲያውኑ ነፃነቱን አውጀውለት ከሌላው የመካ ነዋሪ ጋር እኩል እንዲሆን አደረጉት። ቢላል ለአኺራው መድኅን እንዲሆነው የተቀበለው እስላማዊ እምነት በአዱንያ አይቶት የማያውቀውን ነፃነት እንዲጎናጸፍ ምክንያት ሆነለት።
----
ጊዜ ነጎደ። ብዙ ትእይንቶችም ተስተናገዱ። በመካ ከተማ ሳሉ እምነታቸውን መተግበር ያቃታቸው ቀደምት ሙስሊሞችም ወደ መዲና ተሰደው የነፃነት አየር ማጣጣም ጀመሩ። የመዲና ነዋሪ የነበሩት አንሷር የሚባሉት ሙስሊሞችም ከመካ የመጡ ወንድሞቻቸውን በእውነተኛ ፍቅር ማስተናገድ ከጀመሩ ሰነበቱ። ቢላልም ከመካ ወደ መዲና ከተሰደደ ወራት ተቆጠሩ። ከአጭር ቆይታ በኋላም ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) እና አቡበክር አስሲዲቅ ከመካ ወደ መዲና መጥተው በማበብ ላይ የነበረውን የሙስሊሞች ጀመዓ ተቀላቀሉ።
----
ጊዜ ነጎደ። ብዙ ትእይንቶችም ተስተናገዱ። በመካ ከተማ ሳሉ እምነታቸውን መተግበር ያቃታቸው ቀደምት ሙስሊሞችም ወደ መዲና ተሰደው የነፃነት አየር ማጣጣም ጀመሩ። የመዲና ነዋሪ የነበሩት አንሷር የሚባሉት ሙስሊሞችም ከመካ የመጡ ወንድሞቻቸውን በእውነተኛ ፍቅር ማስተናገድ ከጀመሩ ሰነበቱ። ቢላልም ከመካ ወደ መዲና ከተሰደደ ወራት ተቆጠሩ። ከአጭር ቆይታ በኋላም ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) እና አቡበክር አስሲዲቅ ከመካ ወደ መዲና መጥተው በማበብ ላይ የነበረውን የሙስሊሞች ጀመዓ ተቀላቀሉ።
ነቢዩ ሙሐመድ ባወጡት እቅድ መሠረት የከተማዋ ዐይን የሆነው ትልቁ መስጂድ ተገነባ። ሰላት በጀመዓ እንዲሰገድም አዋጅ ወጣ። በቀን አምስት ጊዜ ምእመናን ወደ ሶላት እንዲመጡ የሚያስገንዘብ ጥሪ እንዲደረግም ደንብ ወጣ። ቢላል ኢብን ረባህም ይህንን ጥሪ የሚያደርግ "ሙአዚን" ሆኖ ተሾመ።
ነቢዩ ወደ መዲና ከተሰደዱ ከዓመት በኋላ ደግሞ ቁረይሾች ሙስሊሞችን ሊያጠፉ እየፎከሩና እየደነፉ መጡ። ነቢዩ ሙሐመድና ተከታዮቻቸውም "በድር" በሚባለው አምባ ላይ ተዘጋጅተው ጠበቋቸው። በሁለቱ መካከል ውጊያው ተጀመረ። ሰይፎች አፏጩ። ጦሮች ተወረወሩ። ቀስቶች ተፈናጠሩ።
የተሻለ ቦታ የያዙትና በዲሲፕሊን የሚዋጉት የነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ተከታዮች የመካ ባላንጣዎቻቸውን አላላውስ አሉ። ሶስት መቶ ሆነው በሶስት እጥፍ የሚበልጧቸውን ጠላቶቻቸውን አርበደበዱ። እንደ አቡ ጀህል፣ ሸይባ፣ ዑትባ፣ ወሊድ አል-ሙጊራ የመሳሰሉት የመካ ከበርቴዎች ተገደሉ።
በውጊያው መሃል የነበረው ቢላል ኢብን ረባህ አንድ ሁነኛ ጠላቱን ይፈልግ ጀመር። ወደ ግራና ወደ ቀኝ አማተረ። ወደ መሬት እያጎነበሰም የተገደሉትን አየ። የቁረይሽ ፊታውራሪዎችንም ሆነ ከጀርባ ሆነው የሚዋጉትን ተመለከተ። በስተመጨረሻም የሚፈልገው ሰው "ዐብዱራሕማን ኢብን አውፍ" የሚባለው የነቢዩ ሰሓባ ነፍሱን እንዲያተርፋት ሲለማመጠው አገኘው።
ቢላል ሰውዬውን ሲያየው ጥቂት ሰዎችን በማስከተል ወደ ስፍራው ደረሰ። ከመቅጽበትም ሰይፉን አሳረፈበት። ሌሎቹም ቢላልን ተከትለው ሰውዬውን በሰይፋቸው ወጉት። እነሆ ቢላልን ሲያሰቃይ የነበረው ኡመያ ኢብን ኸለፍ በዚህ መንገድ ከምድራዊ ሕይወቱ ተሰናበተ።
----
አሁንም ጊዜ ነጎደ።
----
አሁንም ጊዜ ነጎደ።
ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) በመዲና ለአስር አመታት እስልምናን ካስተማሩ በኋላ ተልእኮአቸውን አጠናቅቀው ወደ አኺራ ሄዱ። የነቢዩ መሰናበት የስሜት መዘባረቅንና የሃሳብ መደበላለቅን አስከተለ። በተለይም ከነቢዩ ጋር የጠበቀ ግንኙነት የነበራቸው ቀዳሚዎቹ ሰሓባዎች መሪር ሐዘን ተሰማቸው። በዚህ ረገድ የቢላልን ያህል በሐዘን የተጎዳ አልነበረም።
ቢላል በአቡበከር አማካኝነት ነፃነቱን ከተቀዳጀበት ጊዜ ጀምሮ ከነቢዩ ጋር ነበር የኖረው። በጉዞም ሆነ በስራ ተለይቶአቸው አያውቅም። በዒባዳ ወቅትም ከነቢዩ አይርቅም። ነቢዩ ኢማም ሆነው በሚያሰግዱበት ወቅት እርሱ ሙአዚን ሆኖ ሙስሊሞችን ወደ ሰላት ይጠራል። በአዛንም በቀን ለአምስት ጊዜ "አሽሀዱ አንነ ሙሐመደን ረሱሉላህ" እያለ ስማቸውን ያነሳል። እንዲህ የተሳሰራቸው ነቢይ (ሰዐወ) ወደ አኺራ ሲሄዱበት ሰብር ማድረግ ነው ያቃተው።
አቡበክር ሲዲቅ በነቢዩ ቦታ ተተክተው መንግስቱን መምራት ሲጀምሩ ቢላልም የሙአዚንነት ስራውን እንዲቀጥል ግዳጅ ተሰጥቶታል። ቢላል አዛን ማድረጉን ለጥቂት ቀናት ቀጠለበት። ከዚያ በኋላ ግን ሊያቆመው ወሰነ።
ታዲያ ለዚህ ውሳኔ የተዳረገው የአቡበክር አመራር ስላስከፋው አይደለም። አዛኑን ሲያደርግ "አሽሀዱ አንነ ሙሐመደን..." የሚለው ቦታ ጋ ሲደርስ የሚቀሰቀስበትን የሐዘን ትኩሳት መቋቋም ስላቃተው ነው የሙአዚንነት ስልጣኑን ሊተው የወሰነው። በአቡበክር ዘመን በሙአዚንነት በቆየባቸው ጥቂት ቀናት እንኳ እንባውን በጉንጮቹ ላይ እያፈሰሰ ነው አዛኑን የቋጨው።
ኸሊፋ አቡበክር ሲዲቅ የቢላልን ውሳኔ አልተቀበሉትም። በእስልምና ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው ሙአዚን በእርሳቸው ዘመንም አገልግሎት መስጠቱ ለኡማው ግርማ ሞገስ እንደሆነ ያምኑ ነበር። በመሆኑም ቢላል ሙአዚን ሆኖ እንዲያገለግል ማግባባት ጀመሩ። ይሁንና ቢላል ውሳኔውን የሚቀለብስ አልሆነም። በቀሪው ዘመኑ ከሙአዚንነት ርቆ መቆየትን ነው የመረጠው።
ከአቡበክር በኋላ ኸሊፋ የሆኑት ዑመር ኢብን ኸጣብ የቢላልን ውሳኔ ሲሰሙ እንዲህ አሉት።
"አቡበክር ሲዲቅ ገንዘቡን ከፍሎ ከባርነት ነፃ ያወጣህ ሰው ነው። የእርሱን ሃሳብ አለመቀበልህ ያስተዛዝባል"
ቢላል በምላሹ እንዲህ አላቸው።
"አቡበክር ነፃ ያወጣኝ በግሉ ሊጠቀምብኝ ፈልጎ ከሆነ ላገለግለው ዝግጁ ነኝ። ለአላህ ብሎ ነፃ ያወጣኝ ከሆነ ግን ፍላጎቴን ማክበር አለበት"
አቡበክርም ውሳኔው የማይቀለበስ ሲሆንባቸው እንዳሻው እንዲኖር ፈቀዱለት። ቢላል ከዚያ በኋላ በመዲና አልቆየም። ወደ ሶሪያ ሄዶ ራሱን ዝቅ አድርጎ ይኖር ጀመር። የተለያዩ ሰዎች እየተጠጉት "ድምጽህ ናፈቀን! እባክህ አንድ ጊዜ አዛን አድርግልን" ሲሉት አይቀበላቸውም ነበር።
ከብዙ ዓመታት በኋላ ኸሊፋ ዑመር ኢብን ኸጣብ ወደ ሶሪያ ወጡ። ቢላል ኢብን ረባህንም ዘየሩት። በነቢዩ (ሰዐወ) ዘመን በህይወት የነበሩት ሰሓባዎች አጋጣሚውን በመጠቀም ቢላል አዛን እንዲያድርግላቸው እንዲለምኑት ኸሊፋ ዑመርን ጠየቋቸው። ዑመር ኢብን ኸጣብም ልመናውን ለቢላል አቀረቡ።
ቢላል ቅር እያለው ልመናውን ተቀበለ። ሐዘኑን ችሎም አዛን ማድረግ ጀመረ። በነቢዩ (ሰዐወ) ዘመን ድምጹን የሚያውቁት ሁሉ አዛኑን ሲሰሙ እንባቸውን በጉንጮቻቸው ላይ አፈሰሱ።
----
አፈንዲ ሙተቂ
ረመዳን 19/1441 (ግንቦት 4/2020)
ገለምሶ-ምዕራብ ሀረርጌ
----
አፈንዲ ሙተቂ
ረመዳን 19/1441 (ግንቦት 4/2020)
ገለምሶ-ምዕራብ ሀረርጌ