ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
ክርስቲያን ወንድሞቻችን የጥምቀት በዓልን በሚያከብሩበት ዋዜማ ላይ እንገኛለን፡፡ ከዚህ ቀደም በዓሉ በመጣ
ቁጥር ትዝ የሚሉኝን መምሬ ሙላቱን የተመለከተ ትዝታዬን አካፍዬአችሁ ነበር፡፡ በዛሬው እለት ደግሞ በከተማችን ቀደምት አዛውንት
ዘወትር የሚታወሱትን መምሬ ይፍሩን ላስተዋውቃችሁ ፈቀድኩ፡፡
----
መምሬ ይፍሩ በሸዋ ክፍለ ሀገር ነበር የተወለዱት፡፡ በ1940ዎቹ የቀድሞው የጨርጨር አውራጃ (የአሁኑ የምዕራብ
ሀረርጌ ዞን) በአዲስ ሁኔታ ሲደራጅ የሀብሮ ወረዳ አጥቢያ ዳኛ ሆነው ወደ ገለምሶ መጡ፡፡ መምሬ ወደ ገለምሶ በመጡበት ዘመን ህዝቡ
በፍትሕ እጦት በከፍተኛ ሁኔታ ይማረር ነበር፡፡ መምሬው ህዝቡ በተነገፈው ፍትሕ በጣም አዘኑ፡፡ በመሆኑም ለማንም ሳይወግኑና ፍርድ
ሳያዛቡ የዳኝነት ስራቸውን ለመስራት ወሰኑ፡፡
በዘመኑ በመላው ኢትዮጵያ በጣም ይበደል የነበረው ጭሰኛው ገበሬ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም መምሬ ይፍሩ
ጭሰኛው አርሶ አደር ምርቱንና ጉልበቱን የሚበዘብዙትን ባላባቶች በፍርድ ቤት እንዲፋረዳቸው አደፋፈሩት፡፡ ባላባቶች በጭሰኞቻቸው
እንዳይከሰሱ ለመከላከል ተብሎ የተዘረጋውንና “በፍርድ ቤት የሚያስዘው ቋሚ ንብረት የሌለው ሰው ክስ መመሥረት አይችልም” የሚል
ይዘት የነበረውን የዘልማድ አሰራር በመነቃቀል አስወገዱትና ጭሰኛው ባላባቶችን እንዲፋለማቸው መንገዱን ከፈቱለት፡፡
መምሬ ይፍሩ ለክስና ለምስክርነት የሚመጡትንም የሩቅ ሀገር ሰዎች በራሳቸው ቤት እየመገቡ ያሳድሯቸው ነበር
ይባላል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በጭሰኞቹ ገላ ላይ በሚያዩት የነተበ ጨርቅ ያዝኑና የተለያዩ አልባሳትን ገዝተው ያለብሷቸው ነበር፡፡
ከሩቅ የመጡ ባለጉዳዮችን በቀጠሮ ከማጉላላትም ይቆጡ እንደነበረም ይነገራል፡፡
የዘመኑ ባላባቶች በመምሬ ይፍሩ አድራጎት በጣም ነበር የተደናገጡት፡፡ በመሆኑም “ይህ ሰውዬ ጭሰኞቻችን በኛ
ላይ እንዲፈነጩ እያደረጋቸው ነው” የሚል ክስ በጭሮ (አሰበ ተፈሪ) እና በሀረር ለሚገኙት የበላዮቻቸው አቅርበዋል፡፡ ይሁንና መምሬው
የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት እየጠቀሱ ባለስልጣኖቹ እንዲገሰጹ አድርገዋቸዋል፡፡ ከዚህም አልፎ የዘመኑ የሀረርጌ ጠቅላይ ግዛት
ሹማምንት መምሬ ይፍሩ ፍትሕን ለማስፈን ያደረጉትን ጥረት በአዎንታዊነቱ በመውሰድ የወረዳ ገዥነት ሹመት እንደሰጧቸው ሽማግሌዎች
ይናገራሉ፡፡
መምሬ ይፍሩ ከመንግሥት የተሰጣቸውንም መሬት ከፋፍለው ለጭሰኞች ያስረከቡት ከባላባቶቹ በተለየ መንገድ ነው፡፡
ለምሳሌ የመሬት ከበርቴዎቹ እንደሚያደርጉት አርሶ አደሩ ካመረተው ምርት 75% በመሻማት ፈንታ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ምርቱን ከጭሰኛው
ጋር እኩል ይካፈሉ ነበር፡፡ ታዲያ ይህንን ከማድረጋቸው በፊት ከጠቅላላው ምርት ገበሬው ለዓመት የሚሆነውን ቀለብ እንዲወስድ ይፈቅዱለታል፡፡
ገበሬው ከሚፍለው ግብርም ግማሹን ይከፍሉለታል፡፡
መምሬው እንደ ዘመኑ ባለባቶች ጭሰኛው የጉልበት ስራ እንዲሰራላቸውም አያስገድዱም፡፡ በዚህ ፈንታ ገበሬዎች
የእርሻ ስራቸውን አጠንክረው እንዲሰሩ ይገፋፉአቸው ነበር፡፡ በህይወት ዘመናቸው መጨረሻ ገደማም አራት ጋሻ ከሚሆን መሬታቸው ከአምስት
ሄክታር ያልበለጠውን ብቻ አስቀርተው ሌላውን ለጭሰኞች፣ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለመስጊድና ለታዋቂ የሙስሊም ዑለማ ሰጥተዋል፡፡
------
መምሬ ይፍሩ በሃይማኖት ረገድ ያላቸው እይታም በብዙዎች ዘንድ ተደንቆላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ሙስሊሞች መስጊድ በሚሰሩበት
ጊዜ የገንዘብ መዋጮ በማድረግ ይደግፏቸዋል፡፡ ከመንግሥት መሬትም ለአጣናና ለወራጅ የሚሆን ዛፍ እንዲወስዱ ይፈቅዱላቸው ነበር፡፡
በርሳቸው ድርጊት ልቡ ይነካ የነበረው ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በበኩሉ በተለያዩ ጊዜያት ብድሩን በመመለስ ተባብሮአቸዋል፡፡ ለምሳሌ መምሬ
ይፍሩ ኮሚቴ አዋቅረው “ደረኩ” እና “ቦኬ” በሚባሉት ከተሞች ቤተ ክርስቲያን ባስገነቡበት ወቅት በርካታ ሙስሊሞች ለግንባታው የገንዘብ
ድጋፍ አድርገው ነበር (ወላጅ አባቴ ለደረኩ ቤተክርስቲያን ግንባታ 200 ብር ለግሷል፡፡ የያኔው ሁለት መቶ ብር በመግዛት አቅሙ
ከአሁኑ ሃያ ሺህ ብር እንደሚበልጥ ልብ በሉ)፡፡ በነገራችን ላይ “ደረኩ” እና “ቦኬ” የሚባሉትን ከተሞች የቆረቆሩት መምሬ ይፍሩ
ራሳቸው ናቸው፡፡
-----
ስለመምሬ ይፍሩ የሚነገሩ አንዳንድ ወጎች “ideal” የሚባሉ ዓይነት በመሆናቸው “እውን በዚያ ዘመን ይህ
ተፈጽሞ ነበርን?” ያሰኛሉ፡፡ ለምሳሌ መምሬ ይፍሩ የዐረብኛውን ቅዱስ ቁርኣን ማንበብ እንደሚችሉ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም
ቁርኣን መማርና ማስተማር የሀይማኖቱን መሠረቶች ከመረዳት ባሻገር ፊደልን የማጥናት አካል እንደሆነ ያምኑ ነበር ይባላል፡፡ ስለዚህ
ለርሳቸው የተማረ ሰው ማለት መደበኛ ትምህርትና የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ያጠናው ብቻ ሳይሆን የእስልምና የእውቀት ዘርፎችን ያጠናው
ጭምር ነው፡፡
መምሬ ይፍሩ የመንግሥት ስራቸውን በሚሰሩበት ወቅት በቤተ ክርስቲያን የሚሰጡትን አገልግሎት አላቋረጡም፡፡ ከዚሁ
ጎን ለጎን በትርፍ ጊዜአቸው ህፃናትን ፊደል ያስጠኑ ነበር፡፡ በህይወታቸው መጨረሻ ላይ ደግሞ በገለምሶ ከተማ ምሥራቃዊ ጫፍ ላይ
በሚገኘው ቤታቸው አጠገብ ያሰሩትን አንድ ክፍል የጸሎት ቤት ለዚሁ አገልግሎት በመመደብ ብዙ ህፃናት “ሀ ሁ”ን እንዲያጠኑ ረድተዋቸዋል
(ለረጅም ጊዜ በዚህ ቤት ህፃናትን ፊደል ያስተማሩት “ጋሽ ሸዋንግዛው” የሚባሉትና በኛ ዘመን በጡረታ ላይ የነበሩት የድሮ መምህር
ነበሩ፡፡ እርሳቸውም ህፃናትን በነፃ ያስተምሩ እንደመሆናቸው ውለታቸው የማይዘነጋ ነው)፡፡
በነገራችን ላይ እኔ ጸሐፊው የአማርኛን ፊደል ማጥናት የጀመርኩት መምሬ ይፍሩ ባሰሩት ጸሎት ቤት ነበር (በዘመኑ
“ቄስ ትምህርት ቤት” ብለን ነበር የምንጠራው)፡፡ በርካታ የሙስሊም ልጆችም ጠዋት የቁርአን ትምህርታቸውን ከተማሩ በኋላ ከሰዓት
የአማርኛ ፊደል ለማጥናት ወደ ቄስ ትምህርት ቤት ይሄዱ ነበር፡፡ ይሁንና ትምህርት ቤቱ ከመኖሪያ ቤታችን ባለው ርቀትና በመንገዱ
ላይ የሚጫወቱ ህፃናት በሚያሳርፉብን ምት ወዲያውኑ ነበር የተማረርኩት፡፡ በመሆኑም በአስራ አምስት ቀኔ ትምህርቱን አቋርጬ ወጣሁና
በመድረሳዬ ብቻ ተወሰንኩ፡፡
----
መምሬ ይፍሩ እኔ ከመወለዴ በፊት ነው ያረፉት፡፡ በዚያ ዘመን ሀገሪቱን ይገዛ የነበረው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ
መንግሥት በኦፊሴል በሚከተለው ፖሊሲና በሚፈጽማቸው ተግባራት ከርሳቸው ጋር ይራራቃል፡፡ የወቅቱ መንግሥት በጊዜ ነቅቶ እርሳቸው
ያንፀባረቁትን ተራማጅነት በግማሹ እንኳ ቢከተል ኖሮ ሀገራችን ዛሬ በተሻለ ደረጃ ላይ በተገኘች ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ለሁሉም
ብዙዎች በጫቷ ብቻ የሚያውቋት ገለምሶ መምሬ ይፍሩን የመሰሉ አርቆ አስተዋይ ስብዕናዎች ታሪክ የሰሩባት መድረክ እንደሆነች እወቁልን
እላችኋለሁ፡፡
----
አፈንዲ ሙተቂ
ጥር 9/2010
በሸገር ተጻፈ፡፡
No comments:
Post a Comment