Pages

Wednesday, September 23, 2015

“ዐረፋ” እና “ዒድ አል-አድሐ”

ፀሐፊ ፡ አፈንዲ ሙተቂ
---
በ1982 ነው፡፡ ባልሳሳት ዕለቱ ሰኔ 26 ይመስለኛል፡፡ የኢድ አል አድሐን በዓል ለማክበር በገለምሶው የሼኽ ዑመር ዓሊይ ሐድራ ተሰብስበናል፡፡ የዕለቱ የክብር እንግዳ የሐብሮ አውራጃ ኢሠፓ ኮሚቴ አንደኛ ጸሐፊ የነበሩት ጓድ ዓለሙ መንገሻ ነበሩ፡፡ የመድረክ መሪው ጓድ ዓለሙን ንግግር እንዲያደርጉ ጋበዛቸው፡፡ እሳቸውም ንግግራቸውን እንዲህ በማለት ጀመሩ፡፡

“የአረፋ በዓል ታላቅ በዓል ነው፡፡ የእስልምና እምነት እንደሚያስተምረው ዐረፋ የሚለው ቃል በዐረብኛ “አወቀ” እንደማለት ነው፡፡ ይህም ታሪክ አለው፡፡ አዳምና ሔዋን ወይንም አደምና ሀዋ ከጀንነት ወደ ምድር ከወረዱ በኋላ ለብዙ ዘመናት ተጠፋፍተው ነበር፡፡ ለረጅም ጊዜ ሲፈላለጉ ከቆዩ በኋላ በዚህ ዕለት በሳዑዲ ዐረቢያ ባለው የአረፋ ተራራ ላይ ተገናኙ፡፡ እዚያም “ዐረፍቱከ… ዐረፍቱኪ” ተባባሉ፡፡ “አወቅኩህ! አወቅኩሽ” ማለታቸው ነው፡፡ ይህንን ታሪክ ለመዘከር ሲባል ነው የዐረፋን በዓል ማክበር የተጀመረው”

ጓድ ዓለሙ የገለጹት ታሪክ የሚመለከተው የዙልሒጃን ወር ዘጠነኛ ቀን ነው እንጂ አስረኛውን ቀን አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህንን ታሪክ ከሙስሊም ዓሊሞች ሳልሰማው ከእሳቸው አንደበት መስማቴ በጣም ደንቆኛል፡፡ ለዚያውም የሳቸው ፓርቲ በይፋ “ኤቲይዝምን” የሚሰብክ ሆኖ እያለ ነው እሳቸው ታሪኩን ያወጉን፡፡

እውነት ነው፡፡ ሐጅ በሚባለው አምስተኛው የእስልምና ማዕዘን (አርካን) ውስጥ ከሚፈጸሙት መንፈሳዊ ስርዓቶች መካከል በዙልሒጃ ወር ዘጠነኛ ቀን የሚከናወነው “አል-ዉቁፍ ቢዐረፋት” (በዐረፋ ቆሞ ጸሎት ማድረግ) ቀዳሚው መሰረቱ ከነቢዩ አደም ጋር የተገናኘው ታሪኩ ነው፡፡ ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ሐጃጆች ብሄር፣ ጾታ፣ ቀለም፣ አህጉር፣ ሀገር፣ ክፍለ ሀገር፣ መደብ፣ ስልጣን፣ የስራ መደብ፣ ወዘቱ ሳይገድባቸው በአንድ ቦታ ቆመው ሁላቸውም የአዳም ልጆች መሆናቸውን ያስመሰክራሉ፡፡

ታዲያ በዚሁ ቀን ሁለት ትልቅ ድርጊቶች ተከናውነዋል፡፡ ከነዚህም መካከል አንዱ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በታሪክ ገጾች The Masterpiece Sermon of Mohammed እየተባለ የሚጠራውን ታላቅ ዲስኩራቸውን ያሰሙበት እለት መሆኑ ነው፡፡ ነቢዩ ንግግራቸውን የጀመሩት “ሰዎች ሆይ! ከዚህ በኋላ በናንተ መካከል ላልገኝ እችላለሁ፤ ስለዚህ ልብ ብላችሁ አድምጡኝ” በሚል ዐረፍተ ነገር ነው፡፡ በርግጥም ነቢዩ ከዚህ የመሰናበቻ ንግግራቸው በኋላ በህይወት ብዙም አልቆዩም፡፡ ቢሆንም ከነቢዩ ንግግሮች መካከል በደንብ የተመዘገበው ይህ ንግግራቸው ነው፡፡ በሐዲስ ምሁራን ዘንድ የቃላትና የሐረጋት ልዩነት ሳይደረግበትና በእውነተኛነቱ ላይ ጥርጣሬ ሳይጣልበት (“ሰሒሕ” እና “ደዒፍ” ሳይባል) ተቀባይነትን ያገኘው ይህ የሐጀቱል ወዳዕ ንግግራቸው ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ንግግሩ በመቶ ሺህ ህዝብ የተሰማ መሆኑ ነው፡፡
   
ይህ ቀን የሚታወስበት ሁለተኛው ታላቅ ክስተት የቅዱስ ቁርአን የመጨረሻው አያህ (አንቀጽ) የወረደበት ዕለት መሆኑ ነው፡፡ አዎን!! “ኢቅራእ” በሚለው መለኮታዊ ቃል የጀመረው መጽሐፍ በዚህ ዕለት በሱረቱል ማኢዳ ውስጥ በሚገኘው ሶስተኛው አንቀጽ ተጠናቅቋል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ውስጥ እስላማዊውን ርእዮት ለዓለም የማዳረሱ ተልዕኮ በከፍተኛ ስኬት መጠናቀቁን የሚገልጸው ዐረፍተ ነገር ይገኛል፡፡ እንዲህም ይላል፡፡
“ዛሬ ለናንተ ሃይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ፤ ጸጋዬንም በናንተ ላይ ፈጸምኩ፤ እስልምናንም በሃይማኖትነት ወደድኩላችሁ”
(ሱረቱል ማኢዳ፤ 3)
---
ነቢዩ ሙሐመድ እንዲህ ብለዋል
“በዐረፋ ቀን ለጾመ ሰው አላህ ያለፈውን ዓመትና የቀጣዩን ዓመት ሐጢአቱን ይቅር ይለዋል”

በኛ ሀገር በተለምዶ ዐረፋ የሚባለው የኢድ አል አድሓን በዓል የምናከብርበት አስረኛው እለት ነው፡፡ በሸሪዓው እይታ ግን ዐረፋ የሚባለው የዙልሒጃ ወር ዘጠነኛው ቀን ነው፡፡
--
የዒድ አል-አድሓ ታሪካዊ ዳራ ደግሞ ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ለአላህ ለመሰዋት ያደረጉት ቁርጠኝነት የተመላበት ውሳኔ እና ለመስዋዕትነት የቀረበው ልጅ ያሳየው የተለየ ጽናት ነው፡፡ ነቢዩ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) የበኩር ልጃቸው የሆነውን ዒስማኢልን (ዐ.ሰ.) ያገኙት በእርጅና ዘመናቸው ነው፡፡ ታላቅ ሚስታቸው ሳራ ለፍሬ ባለመብቃቷ “ያ አላህ ያለ ዘር አታስቀረኝ፤ እኔን የሚተካ ሷሊህ የሆነ ልጅ ስጠኝ” በማለት ዱዓ አደረጉ፡፡ በዚሁ መሰረት በሳራ ፈቃደኝነት ሐጀራ የምትባለውን የቤት ሰራተኛቸውን አገቡ፡፡ ሐጀራም ዒስማኢል የተባለ ልጃቸውን ወለደችላቸው፡፡ ይህ ልጅ በአላህ ፈቃድ በመካ ከተማ እንዲያድግ የተወሰነ ስለነበረ ኢብራሂም ሐጀራን እና ዒስማኢልን ወደ ዐረቢያ ከተማ ወሰዷቸው፡፡

ዒስማኢል ካደገ በኋላ ደግሞ አላህ “ልጅህን እንድትሰዋ ታዘሃል” የሚል ትዕይንት በህልማቸው አሳያቸው፡፡ የነቢያት ህልም ደግሞ ከራዕይ የሚቆጠር ነው፡፡ ስለዚህ ኢብራሂም በህልማቸው ያዩትን በዝምታ አላለፉትም፡፡ በወቅቱ የሆነውን ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ይተርካል፡፡

“ከርሱ ጋር ለስራ በደረሰ ጊዜም “ልጄ ሆይ! እኔ በህልሜ የማርድህ ሆኜ አይቻለሁ፤ (እስቲ አንተም ነገሩን) ተመልከት፡፡ “ምን ይታይሃል” አለው፡፡ (ልጁም) አባቴ ሆይ! የታዘዝከውን ፈጽም፤ አላህ ቢሻ ከታጋሾቹ ሆኜ ታገኘኛለህ አለ”
(ሱረቱ -ሷፍፋት፤ 102)

አባትና ልጅ በዚህ መንገድ ከአላህ የተላለፈውን ትዕዛዝ ሊፈጽሙ ተነሱ፤ ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸውን እንዲሰው የታዘዙት ከዐረፋት መሬት ብዙም ባልራቀ ቦታ ላይ ስለነበረ ወደዚያው ጉዞ ጀመሩ፡፡ በመንገዳቸው ግን ኢብሊስ በሰው ተመስሎ በጣም ተፈታተናቸው፤ ሶስት ጊዜ ያህል እየወጣ “ከስንት ዓመት በኋላ ያገኘኸውን አንድዬ ልጅህን ስትሰዋ ምንም አይጸጽትም?… እንዴት ጅል ትሆናለህ” እያለ ሞገታቸው፡፡ ከአላህ ትዕዛዝ ፍንክች የማይሉት ኢብራሂም ግን ድንጋይ ከመሬት በማንሳት “አዑዙቢላሂ ሚነ-ሸይጣኒ ረጂም” እያሉ ኢብሊስን ወገሩት፡፡

ኢብራሂም ዒስማኢልን ሊያርዱት አጋደሙት፡፡ ልጁም ምንም ሳያንገራግር ከመሬቱ ላይ ተኛ፡፡ ኢብራሂም ልጁን ሊያርዱት ሲሞክሩ ግን ቢላዋው አላርድ አላቸው፡፡ ኢብራሂም እንደገና ቢላዋውን ገዘገዙት፡፡ ነገር ግን ቢላዋው ፈጽሞ ዶለዶመ፡፡ ልጁ የሆነው ነገር አልገባውም፡፡ አባቱ ቶሎ ስላላረደው ተገረመና “አባዬ! ፣ ምናልባት የአባትነት ፍቅር ይዞህ ይሆናል በቶሎ ያላረድከኝ፤ እስቲ ዐይኔን በጨርቅ ሸፍነውና እርዱን ሞክር” የሚል አስተያየት ሰጠ፡፡

በዚህን ጊዜ ግን ከወደ ሰማይ ጥሪ መጣ፡፡ የአላህ መልአክ “ኢብራሂም ታላቅነትህን አስመስክረሃልና እርዱን አቆየው” በማለት አወጀ፡፡ በምትኩም መልአኩ ከገነት ያመጣውን በግ እንዲያርድና ልጁን ወደቤቱ እንዲወስደው ነገረው፡፡ በዚህም መሰረት በጉ ታረደ፡፡ ኢብራሂምና ዒስማኢልም ወደ መካ ከተማ ተመለሱ፡፡ ሁለቱ ሰዎች ለፈጣሪ መታዘዝን በግልጽ ያሳዩባት ያቺ ዕለት የዒድ አል-አድሓ በዓል ሆና እንድትከበርም ተወሰነ፡፡ ዒስማኢል ለመስዋእትነት የቀረበበት ድርጊት ደግሞ በዚሁ ዕለት የሚታረደው “ኡድሒያ” መነሻ ሆነ፡፡
----
ዒድ አል-አድሐ የመስዋዕትነትና የመዳን በዓል ነው፡፡ የሐጅ ጸሎት የሚፈጽም ሰው በዚህ ዕለት “ኡድሒያ” የማረድ ግዴታ አለበት፡፡ እኛም ወደ ሐጅ ያልሄድነው ደግሞ ከተቻለ በዚሁ ዕለት በየቤታችን እንስሳት እያረድን ለ“ኡድሒያ” እንድናቀርብ ታዘናል፡፡ ታዲያ ኡድሒያው “ኡድሒያ” ተብሎ የሚመዘገብልን እርዱም ሆነ አጠቃቀሙ ነቢዩ ያስተማሩትን መንገድ የተከተለ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች ፍየሉን ያርዱና ለበዓል የሚሆናቸውን ያህል ካስቀሩለት በኋላ ሌላውን ወደ ፍሪጅ ውስጥ ይከቱታል፡፡ ይህ ግን ራስን መጋበዝ ነው እንጂ ኡድሒያ ተብሎ አይመዘገብም፡፡

ነቢዩ እንዳስተማሩት ለኡድሒያ ከታረደው ስጋ አንድ ሶስተኛው በቀጥታ ለድሆች መከፋፈል አለበት፡፡ አንድ ሶስተኛው ለዘመድና ለወዳጅ ነው የሚሰጠው፡፡ የተቀረው አንድ ሶስተኛ ብቻ ነው ለቤተሰቡ አገልግሎት የሚውለው፡፡ ስለዚህ በዚህ እለት የሚፈጸመው መስዋእት “ኡድሒያ” ሆኖ እንዲመዘገብልን ካሻን ትክክለኛውን መንገድ መከተል አለብን፡፡ በተለይ ከታረደው ስጋ የድሆች ድርሻ የሆነውን “ሡሉሥ” ከሁሉም አስቀድመን ለባለቤቶቹ እናስረክብ ዘንድ የአደራ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

ዒድ ሙባረክ
አፈንዲ ሙተቂ
----
መስከረም 12/2008
ሀረር-ምስራቅ ኢትዮጵያ
----


No comments:

Post a Comment