Pages

Tuesday, June 23, 2015

ተሰውፍ ምንድነው?


ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
---
   “ተሰውፍ” (Sufism) ሁለት ፍቺዎች አሉት፡፡ አንደኛው “ሱፍ መልበስ” የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው “ራስን ማጽዳት” ማለት ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የምንዳስሰው “ተሰውፍ” በሁለተኛ ፍቺው ፈለግ የሚሄድ ነው፡፡ ይህም በተገቢ መንገድ ሲቀመጥ የልብ ጥራት” እንደማለት ነው፡፡ ሙስሊም የሆነ ሰው ልቡ በአካሉ ከሚያደርገው ኢባዳ ጋር በእኩል ሁኔታ እንድትራመድለት ሲፈልግ ልዩ ልዩ ጥበባዊ ዘዴዎችን የሚማርበት መንገድ ነው- “ተሰውፍ፡፡ ይህም ሲባል ልብን ከልዩ ልዩ የልብ በሽታዎች ማጥራትማለት ነው፡፡

   በቁርአንና በሀዲስ በስፋት እንደተገለጸው ሰዎች ከፈጣሪ ጋር ያላቸውን ትስስር የምታበላሽባቸው አንዲት አካል አለች፡፡ እርሷም ልብ ናት፡፡ ሙእሚኖች ቁርኣናዊ ግዳጃቸውን በተገቢው መንገድ ለመወጣት ከፈለጉ ልባቸውን ከበሽታ ማጥራት አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል ፈጣሪያችን አላህ (..) ለምንሰራቸው መልካም ስራዎች የሚከፍለንን ምንዳ (አጅር) የሚወስነው የልባችንን ጥራት በመመዘን ነው፡፡ በከፍተኛ የልብ ጥራት የአንድ ብር ሰደቃ የሰጠ ሰው ከፍተኛ ሽልማት አለው፡፡ ሰውየው መካከለኛ የልብ ጥራት ካለው ሽልማቱ ያንስበታል፡፡ የልብ ንጽህናው በጣም የጎደፈ ሰው ደግሞ ሽልማቱ እጅግ ዝቅተኛ ነው (ሰውዬው መቶ ብር ቢሰጥ እንኳ በንጹህ ልብ አንድ ብር የሰጠውን ሰው ያህል ሽልማት አያገኝም)፡፡ ልቡ ሙሉ በሙሉ የቆሸሸ ሰው ግን ከአላህ ዘንድ ምንም ሽልማት አያገኝም፡፡

  እንግዲህ ይህንን የልብ ጥራት ማምጣት የሚቻለው እንዴት ነው? ኡለማ ለዚህ ጥያቄ የሚሆን ምላሽ ሲፈልጉ ነውተሰውፍየሚባለው አስገራሚ (አንዳንድ ጊዜ አወዛጋቢ) ኢስላማዊ የትምህርት ዘርፍ የተወለደው፡፡
  ተሰውፍን እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ አድርጎ ማስተማር መቼ እንደተጀመረ በትክክል አይታወቅም፡፡ በርካታ ምንጮች ታዋቂዎቹን የበስራ ምሁራን ሐሰን አል-በስሪንና ራቢአቱል አደዊያን እንደ ጀማሪዎች ይጠቅሳሉ፡፡ ለመጀመሩ ሰበብ የሆነውም በጊዜው የነገሰው የልዩ ልዩ ፊርቃዎች (ዓ፤ ኻዋሪጅ፤ ሙርጂአ፤ ጀሀሚያ፤ ሙእተዚላ፤ ቀደሪያ፤ ጀብሪያ ወዘተ…) ሽኩቻ እንደሆነ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡

   በተሰውፍ ላይ የሚያተኩሩ መጽሀፍት መጻፉንም ማን እንደጀመረው በርግጥ አይታወቅም፡፡ እንደሚመስለኝ ከሆነ የተሰውፍ መጽሀፍት መጻፍ የጀመሩት ከሂጅራ በኋላ 4ኛው መቶ አመት ገደማ፤ ማለትም እንደ አውሮፓ አቆጣጠር 900 .. በኋላ ሳይሆን አይቀርም፡፡ 10ኛው፤ 11ኛውና 12ኛው ክፍለ ዘመናት ፈሪዱዲን አጣር፤ አቡ ሀሚድ አል-ገዛሊ፤ አህመድ አል-ሪፋኢ፤ አብዱልቃዲር አል-ጁይላኒ ወዘተየመሳሰሉ ምሁራን በተሰውፍ ላይ ያተኮሩ በርካታ መጽሀፍትን አበርክተዋል፡፡

ተሰውፍና የልብ በሽታዎች
   ልባችን የሚቆሽሸው በተለያዩ በሽታዎች ነው፡፡ እነዚህ የልብ በሽታዎች ያሉበት ሰው ኢባዳውን በወጉ አያደርግም፡፡ ውሎውና ድርጊቶቹ ከኢስላማዊ አዳብ ጋር አይገጥሙለትም፡፡ ከግለሰቦችና ከማህበረሰቡ ጋር ያለው ግንኙነትም የተስተካከለ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ በዚህች አለም ብቻ ሳይሆን በወዲያኛውም አለም ታላቅ አደጋን ያስከትልበታል፡፡ ስለዚህ ከአደጋው ለመዳን ልቡን ከበሽታ ማጥራት ይጠበቅበታል፡፡

   የሰውን ልብ ከሚያደርቁትና ኢማንን ከሚያጎድሉት በሽታዎች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡
·        ኒፋቅ፡- የሙናፊቅነት ስሜት
·        ጡግያን፡- ጥመት
·        ኪብሪያእ፡-ኩራት
·        ጁብር፡ ትዕቢት
·        ሪኣእ፡- ልታይ ልታይ ማለት
·        ዘን፡- ከንቱ ጥርጣሬ
·        ገፍላን፡- መሰላቸት
·        ሻህዋእ፡- ከገደብ ያለፈ ስጋዊ ፍላጎት
·        ወዘተ

   አላህና መልዕክተኛው (..) ከነዚህ በሽታዎች እንድንጠነቀቅ አስተምረውናል፡፡ የተሰውፍ ሰዎች ለነዚህ በሽታዎች የሚሆኑ መድሃኒቶችን ነው የሚያስተምሩት፡፡ የነዚህ መድሃኒቶች ምንጭ ቁርአንና ሱንና ነው፡፡ ልቡን ከነዚህ በሽታዎች ያጠራ ሰው ዒባዳውን በታላቅ ኹሹእ (የአላህ ፍራቻ) ማከናወን ይችላል፡፡ በተሰውፍ ከምንታከምባቸው መድሀኒቶች መካከል ከሁሉም የሚበልጠውዚክር” (አላህን ማስታወስ ) ነው፡፡ ቁርኣን ልቦች በዚክር ይረጥባሉ በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷልና!!

   እንግዲህሱፊየሚባል ሰው ልቡን ከበሽታ ለመጠበቅ ሲል የተሰውፍን ጥበብ የሚከተል ማለት ነው፡፡ ይህ የተሰውፍ ጥበብ ደግሞ ከቁርአንና ከሀዲስ ጋር የማይጋጭ መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም ሰውየው ሌላውን ኢባዳ ትቶ ተሰውፍን ብቻ የሙጥኝ ብሎ መያዝ አይችልም፡፡ተሰውፍሰውዬው በኢባዳ ላይ ብርቱ ሆኖ እንዲቆይ የሚረዱትን ጥበባዊ ዘዴዎች ያስተምረዋል እንጂ በራሱ የቆመ ለየት ያለ ኢስላማዊ ጎዳና ወይም የሸሪኣ ዘርፍ አይደለም፡፡

   ማንም ሰው የተሰውፍ ዘዴዎችን ሳይማር ኢባዳውን ማድረግ ይችላል፡፡ልቤ በትእቢትና በኩራት ተወጥራለችና ምን ይበጀኛል?” ብሎ የሚጨነቅ ከሆነ መድሃኒቱን ከተሰውፍ መንገድ መፈለግ ይፈቀድለታል፡፡

   እዚህ ላይ የታዋቂውን የሱፊ ጥበብ አዋቂ የሼኽ ብዱልቃዲር አል-ጄይላኒን ምሳሌዎች ልጥቀስ፡፡ ሼይኽ አል-ጄይላኒአል-ጉንያ ሊጣሊብ ጠሪቀል ሀቅበተባለ መጽሀፋቸው ውስጥ እንዲህ ይላሉ፡፡
·        መቼም ቢሆን አትማል፤ መማል ካስፈገለ ግን በአላህ ስም ብቻ ማል!
·        በምላስህ አትዋሽ! ጥሩ ነገር ብቻ ተናገር!
·        በመንገድህ ላይ በእድሜው ካንተ የሚያንስ ሰው ቢያጋጥምህከርሱ የተሻልኩነኝ ብለህ አታስብ፡፡ ከዚህ ይልቅ በልብህይህ ልጅ በምድር ላይ የኖረበት ዘመን ከኔ እድሜ ያንሳል፡፡ ስለዚህ ሀጢአቱም ከኔ ያነሰ ነውበል፡፡
·        በእድሜው ካንተ የሚበልጥ ሰው ከገጠመህ ደግሞይህ ሰው በዚህች ምድር ላይ ከኔ እድሜ ለሚበልጥ ጊዜ ኖሯል፤ ስለዚህ ለአላህ ባደረገው ኢባዳ ከኔ ይበልጣልበል እንጂ በመጥፎ ነገር አትጠርጥረወ፡፡

   ደስ ይላል አይደል? ከማስደሰቱ ጋር መጠየቅ ያለበት ጥያቄሼኽ አብዱልቃዲር የተናገሯቸው ነገሮች ከኢስላማዊው ሸሪዓ ጋር ይቃረናሉ ወይ?” የሚለው ነው፡፡
   ሼኽ አብዱልቃዲር የጻፉት ነገር ከኢስላማዊ ሸሪዓ ውጪ አይደለም፡፡ ይልቅ ኢስላማዊ ሸሪዓን በትክክል ለመተግበር ያግዛል፡፡ ተሰውፍ ማለትም እንዲህ ነው፡፡ 
   በዚህ መሰረት ነው ሙስሊሞች ልባቸውን ከበሽታ የሚፈውሱባቸውን ልዩ ልዩ ምክሮች የሚሰጡ መጽሀፍት መጻፍ የተጀመሩት፡፡ አንዳንድ መምህራንም ሙሉ ጊዜያቸውን ለዚሁ ሰጥተው የማስተማሪያ ማእከላትን ያቋቋሙት ለዚሁ አላማ ነው፡፡

(ይቀጥላል)

-----
አፈንዲ ሙተቂ

ጥቅምት 2004

No comments:

Post a Comment