Pages

Saturday, January 10, 2015

ጽንፈኝነት፣ ምዕራባዊያንና ሚዲያ


ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
ከዚህ በፊት “እስልምና ጂሃድ እና ሰሞነኛው የኢራቅ ሚሊሻ” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ጽሑፍ የእስልምና ሃይማኖት በጽንፈኝነት ላይ ያለውን አቋም በሰፊው ገልጫለሁ (ጽሑፉ የኔ ብሎግ ላይ ስላለ ከዚያ ማንበብ ይቻላል)፡፡ በጽሑፉ ለማስረዳት እንደሞከርኩት በእስልምና የሚያምነው የዓለም ህዝብ ጽንፈኝነትና ጽንፈኞችን በጣም ያወግዛል፡፡ ከብዙሃን ጋር የማይጣጣሙት ጥቂት ጽንፈኞች እስልምናንም ሆነ ሙስሊሞችን አይወክሉትም፡፡

  ይሁንና ምዕራባዊያንና ሚዲያዎቻቸው ጽንፈኝነትን ለአንዱ ሃይማኖት በጅምላ ያሸከሙ ነው የሚመስሉት፡፡ ታላቋ ሶቪየት ህብረት ከፈራረሰች ወዲህ ከሚዲያ ኢንዱስትሪው ወሬ ማሟሟቂያዎች እና ከተንታኞቻቸው የአስተሳሰብ ምጡቅነት ማሳያ ዋነኛ አርዕስተ ጉዳዮች አንዱ ስለ“እስልምና አክራሪነት” መፍተልና መተርተር ሆኗል፡፡ እንግዲህ የ“እስልምና አክራሪነት” የሚል ርዕስ ከመጠቀም ጀምሮ የዓለም ማህበረሰቦች አትኩሮት በርሱ ላይ ብቻ እንዲሆን መጣሩ ከጀርባው ሌላ ነገር ያለ ነው የሚመስለው፡፡

“ጽንፈኝነት”ም ሆነ “አክራሪነት” በሀይማኖት ያልተገደቡ ናቸው፡፡ ጽንፈኛ ቡድኖች ከየትኛውም ሀይማኖት ሊመነጩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በጥንት ዘመን “Masada” የተሰኘ የአይሁዳዊያን ጽንፈኛ ቡድን ነበር፡፡ ዛሬም በእስራኤል ውስጥ በመቶ የሚቆጠሩ እጅግ ጽንፈኛ ቡድኖች አሉ፡፡ በ7ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ “ኸዋሪጃ” የሚባሉት ጽንፈኞች ከሙስሊሙ ዓለም ተነስተዋል፡፡ በዘመናችንም አል-ሸባብ፣ አል-ቃኢዳ፣ ቦኮ ሀራም የመሳሰሉት ተፈጥረዋል፡፡ ከክርስትናው ዓለምም በ“መስቀል ጦርነት” የሚያምኑ ጽንፈኛ ቡድኖች በተለያዩ ዘመናት ተነስተዋል፡፡ በዘመናችን በሰሜን ኡጋንዳ ጫካዎች ውስጥ መሽጎ ልዩ ልዩ ሰቆቃዎችን የሚፈጽመው Lords Resistance Army የተባለው ሚሊሺያ “ኡጋንዳን በወንጌልና በአስርቱ ትዕዛዛት እመራታለሁ” እያለ የሚለፍፍ ጽንፈኛ ቡድን ነው፡፡ ከሶስት ዓመታት በፊት ከሰማኒያ የሚበልጡ ንጹሃንን የጨፈጨፈው የኖርዌይ ጽንፈኛ ግለሰብም በሃይማኖቱ ክርስቲያን ነው፡፡ በጃፓን ሜትሮ (የምድር ውስጥ ባቡር) ውስጥ የመርዝ ጋዝ በመርጨት ንጹሃንን የፈጀው የኡም-ሺኖሮኪዮ ሀይማኖታዊ ቡድን “የፈጣሪን ትዕዛዝ እተገብራለሁ” የሚል ጽንፈኛ ነው፡፡ በሀይማኖት የማያምኑ (ማቴሪያሊስቶች፣ ኮሚንስቶች ወዘተ…) ጽንፈኛ ቡድኖችም በልዩ ልዩ ዘመናት ተነስተዋል፡፡የሚዲያው አካሄድ ግን ይህንን ሐቅ የተከተለ አይደለም፡፡ በአያያዙ ወደ አንዱ አቅጣጫ የተንጋደደ ነው፡፡ ይህ አድልኦ በግልጽ እየታየ ጽንፈኝነት ይጠፋል ማለት ዘበት ነው፡፡

ሌላኛው ደግሞ ሚዲያው ወሬ በማጋጋል ረገድ የሚጫወተው ሚና ነው፡፡ በልዩ ልዩ እምነቶችና ማህረበሰቦች ዘንድ እንደ ጸያፍ የሚታዩ ድርጊቶች በአንድ የዓለም ክፍል ሲፈጸሙ ሚዲያው ሽፋን የሚሰጣቸው አስቀድሞ በተቀመጠለት እቅድ ሳይሆን እንደማይቀር እገምታለሁ፡፡ እነዚህ ድርጊቶች መከሰታቸው እንዲታወቁ ሚዲያው ቶሎ ብሎ ወሬ ማራገብ ይጀምራል፡፡ ከሰዓታት ወይንም ከአንድ ቀን በኋላ ድርጊቱ ቁጣን ቀሰቀሰ ተብሎ ሌላ ወሬ ይራገባል፡፡ በሶስተኛው ቀን በቁጣው የተነሳሱ ጽንፈኞች ሰላማዊ ሰዎችን ገደሉ ተብሎ ይራገባል፡፡ በዚህ እርግብግቦሽ መሃከል ሌላ ቁጣ ይቀሰቀሳል፡፡ ሚዲያው እርሱንም ያራግባል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ይቀጥላል፡፡

እንደዚህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች ቀድሞውኑ የሚዲያ ሽፋን እንዲኖራቸው ባይደረግ ኖሮ የሚጠፋ ህይወትም ሆነ የሚበላሽ ንብረት ባልኖረ ነበረ፡፡ ነገር ግን ሚዲያው በሰዎች ስነ-ልቦና እየተጫወተ ድብቅ ተልዕኮውን ይፈጽማል፡፡ እግረ መንገዱንም ለራሱ ከፍተኛ ገቢ ይሸቅላል፡፡

 ይህንን ስጽፍ “International Qur’an Burning” ብሎ ዓለምን ለመጥበጥ የሞከረው ፓስተር ትዝ አለኝ፡፡ ሰውዬው የሚመራው Church መቶ አባላት እንኳ አልነበሩትም፡፡ ነገር ግን ሰውዬው እንዲያ አደርጋለሁ ብሎ ሲነሳ ሚዲያው ወሬውን እየተቀባበለ በዓለም ዙሪያ አዳረሰው፡፡ ዓለምም ለአስራ አምስት ቀን ተንጫጫ፡፡ ከዚያ ሰውዬው እቅዱን ሰረዘው ተብሎ ተነገረን፡፡ ሰውዬው የሰጠው ምክንያትም “በኒውዮርክ መንትያ ህንጻዎች ፊት ለፊት የሚሰራው መስጊድ ከተከለከለ እኔም እቅዴን እተወዋለሁ” የሚል ነበር፡፡እንግዲህ የሰውዬው ፍላጎት ቁርኣኑን ማቃጠል ሳይሆን የመስጊዱ ግንባታ እንዲቆም ማድረግ ነበር ማለት ነው፡፡ ሚዲያው ወሬውን እያጋነነው በዓለም ዙሪያ አዳረሰውና የልቡ እንዲደርስለት አደረገ፡፡ የሚዲያው ጫጫታ በጥርጣሬ መታየት አለበት የምለው ይህንን የመሳሰሉ በርካታ ታሪኮች ስላሉ ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ሌላው ነገር በዲሞክራሲ ስም የሌሎች እምነት ተከታዮችን ስነ-ልቦና የሚጎዱ አድራጎቶችን መፈጸሙ ነው፡፡ እነዚህ ተንኳሾች ሌሎች እንዲነኩባቸው የማይፈቅዷቸውን ነቢያት፣ ቅዱሳት እና መጻሕፍት በወረደ አኳሃን ይነካካሉ፡፡ የእምነቱ ተከታዮች ስለመብታቸው ሲጮኹ ደግሞ “በእገሌም እኮ ይቀለዳል” የሚል ምላሽ ይሰጣቸዋል፡፡ ይሁንና እነዚህ ቧልተኞች የማይደፍሯቸው ጥቂት ክፍሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ““Holocaust is a lie” ከተባለ በህግ ይጠየቃሉ፡፡ በነቢዩ ሙሐመድ እና በእየሱስ ክርስቶስ ሲቀልዱ ግን የዲሞክራሲ መብታቸው ነው ይባላል፡፡ “እንስሳት እኩል ናቸው፤ አንዳንዶቹ ግን በጣም እኩል ናቸው” የሚለው የጆርጅ ኦርዌል አባባል በሁሉም ቦታ ይሰራል ማለት ነው፡፡ ይሁንና እንዲህ ዐይነቱ ዓይን ያወጣ አድልኦ እየተደረገ ጽንፈኝነት በጭራሽ አይጠፋም፡፡ ስለዚህ ጽንፈኝነትን ለማጥፋት ከተፈለገ መከባበርን እንደ መርህ መያዝ ይገባል፡
*****
  ጽንፈኝነት ምንጊዜም ቢሆን አደገኛ ነው፡፡ የዓለምን ሰላምና የህዝቦችን አብሮ የመኖር ተስፋ ይገድላል፡፡ ስለዚህ የዓለም ህዝቦች ሁሉ በጋራ ሊታገሉት ይገባል፡፡ በተለይም በየሀገሩ ያሉ የየሃይማኖት ምሁራን እርስ በራሳቸው ሃሳቦችን የሚለዋወጡባቸው የ“Inter-faith” ፎረሞች ሊጠናከሩ ይገባል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ሚዲያው አድሎአዊነቱንና ድብቅ ተልዕኮ ፈጻሚነቱን ትቶ ሁሉንም ህዝቦች እኩል የማየትን ልማድ ማምጣት አለበት፡፡ እኛ አድማጮችና ተመልካቾችም ሚዲያው የሚዘበዝበውን ወሬ እንዳለ ከመቀበላችን በፊት ነገሮችን ከሁሉም አቅጣጫ መመልከት አለብን እላለሁ፡፡
---
አፈንዲ ሙተቂ
ጥር 2/2007 ተጻፈ፡፡

------

No comments:

Post a Comment