አፈንዲ
ሙተቂ
-----
የህንድ ፊልም ማየት የጀመርኩት በ1978 ይመስለኛል፡፡ በዘመኑ ቶማስ የሚባል
የህንድ ክልስ ነበር፡፡ ይህ ሰው ፊልሞቹን ከድሬ ዳዋ ያስመጣና በሌሎች የሀረርጌ ከተሞች እያዞረ በፕሮጀክተር ያሳያል፡፡ በዘመኑ
“የአሜሪካ ፊልም ውሸት ነው፤ የህንድ ፊልም እውነት ነው” የሚል አስተሳሰብ ስለነበረ የሰዎች ምርጫ በአብዛኛው የህንድ ፊልም ነበር፡፡
በመሆኑም ቶማስ ከሚያሳያቸው ፈልሞች መካከል ከመቶ ዘጠና የሚሆኑት የህንድ ፊልሞች ነበሩ፡፡
በዚህም መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት የህንድ ፊልም “T.D” የሚል ርዕስ
የነበረው ሲሆን አክተሩም “ጄተንድራ” ነው (በኋላ ላይ እንደተረዳሁት ያ ፊልም First Blood ከሚባለው የራምቦ ፊልም የተቀዳ ነው)፡፡ ቶማስ ፊልሙን የሚያሳየው በሁለት
ብርና በሶስት ብር ነው፡፡ በቶማስ ሲኒማ ስር ካየኋቸው ሌሎች የህንድ ፊልሞች መካከል Disco Dancer, Jimmy and
His Elephant, Mard የተሰኙት ይታወሱኛል፡፡
በ1981
የአውራጃችን አኢወማ ቪዲዮ ሲያስመጣ ግን የቶማስ ሲኒማ “በጣም ውድ ነው” በሚል ተረሳ፡፡ ቶማስም ወደኛ መምጣቱን ተወ፡፡ በዚህም
መሰረት Mister India, Ashanti, Kassam Paeda, Love Story, የመሳሰሉ ፊልሞችን በአኢወማ አየን፡፡ ከጥቂት
ጊዜ በኋላ ደግሞ “ፎቶ ማወርዲ” የሚባለው ፎቶ ቤት ሌላ ቪዲዮ ማሳያ ከፈተና ከአኢወማ ጋር ፉክክር ውስጥ ገቡ፡፡ ሁለቱም በርካታ
ፊልሞችን አስኮመኮሙን፡፡ በፎቶ ማወርዲ ካየኋቸው ፊልሞች መካከል “Ter Kassam”, “Maa Kassam”, “Numberi
Admi”, “Khoj”, “Marry Kassam”, “My Name is Lakan”, “Tarzan”, “Coolie”, የሚባሉትን ከነ
ስሞቻቸው አስታውሳቸዋለሁ፡፡ የብዙዎቹን ስም ግን አላስታውስም፡፡
***** *****
*****
በህንድ
ፊልሞች የምናውቃቸው አክተሮች በከተማችን በትክክለኛ ስማቸው አልነበረም የሚጠሩት፡፡ አንዳንዶቹ እኛ ባወጣንላቸው ስሞች ነው ይበልጥ
የሚታወቁት፡፡ ለምሳሌ “ሚቱን ቻካርቦርቲ” የሚባለው አክተር “ጂሚ” በሚለው ስም ነው የሚታወቀው፡፡ “ዳርሜንድራም” በኛ አጠራር
“ሻንካር” ነው የሚባለው፡፡ “ሪሽ ካፑር” ደግሞ “ኮጅ” እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡ እውነተኛ ስሙ “ሰኒ” የሆነው አክተር ደግሞ
በኛ አጠራር “ገባር” ነው የሚባለው፡፡ “አጄይ ኩማር”ም “ላቭ ስቶሪ” ተብሎ ነበር የሚጠራው፡፡ ከነዚህ ስሞች መካከል አንዳንዶቹ
(እንደ “ጂሚ” እና “ሻንካር” ያሉት) አክተሩ ታዋቂ በሆነበት ፊልም ውስጥ ከሚጠራበት ስም ነው የተወሰዱት፡፡ እንደ “ኮጅ” እና
“ላቭ ስቶሪ” የመሳሰሉት ደግሞ አክተሮቹ የተወኑባቸው ፊልሞች አርዕስት ናቸው፡፡
ከዚህ ሌላ
አክተሩ በፊልሙ ውስጥ ሲያንጸባርቀው የነበረውን ድርጊት በመመልከት የተሰጡ ስሞችም አሉ፡፡ ለምሳሌ “አኒል ካፑር” የሚባለው አክተር
በአንድ ፊልም ውስጥ ያለ ማቋረጥ “ማስቲካ” ያኝክ ስለነበረ “ማስቲካ” ተብሎ ተሰይሟል፡፡ “ቆሮንዴ” ደግሞ “Sholay” በተሰኘው
የአሚታብ ባችቻን ፊልም ውስጥ በአፍ የሚታኘክ ትምባሆ ስለሚጠቀም ነው እንዲህ ተብሎ የተጠራው (“ቆሮንዴ” በአፍ የሚታኘክ የትምባሆ
ዐይነት ነው)፡፡ እንደ ከማል ሐሰን፣ ነስሩዲን፣ አሚታብ ባችቻን፣ ሻሽ ካፑር፣ ጄክ ሸሪፍ፣ ጎቪንዳ፣ ሳንጃይ የመሳሰሉትን ግን
በትክክለኛ ስማቸው ነው የምንጠራቸው፡፡
ታዲያ በጣም ያስገረመኝ ይህ በኛ ከተማ የምንጠቀምበት የስም አጠራር ዘይቤ
ድሬ ዳዋና ሀረርን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችም በስፋት የሚታወቅ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ያደረግኩት ጥናት እንደሚያመለክተው ከስሞቹ
መካከል አንዳንዶቹን እኛ መፍጠራችን ትክክል ቢሆንም ሌሎቹ ስሞች ከድሬ ዳዋ ልጆች የተኮረጁ ናቸው፡፡
በድሮው
ዘመን “አክተር” የምንለው በፊልሙ ውስጥ መልካም ስብዕና የሚያሳየውን ብቻ ነው፡፡ እኩይ ባህሪ ተላብሶ የሚተውነው በኛ ቋንቋ
“ሙጅሪም” ነው የሚባለው፡፡ በአንደኛ ደረጃ ከሚነሱ ሙጅሪሞች መካከል “አሻንቲ”፣ “ሻክቲ”፣ “ጃሉ”፣ “ሼራ”፣ “ቆሮንዴ”፣
“ፋሩቅ” የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ (ፋሩቅ Disco Dancer በተሰኘው ዝነኛ የጂሚ ፊልም ውስጥ የተወነው ወፍራም ሙጅሪም ነው፤ አስታወሳችሁት
አይደል?)፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ከሚመደቡ ሙጅሪሞች መካከል ደግሞ “ሳምሶን መላጣ” እና “መለኪያ” የተባሉት ይጠቀሳሉ:: እነዚህኛዎቹ
ሙጅሪሞች በአብዛኛው በታላላቆቹ ሙጅሪሞች እየታዘዙ ጥፋት የሚፈጽሙ ናቸው፡፡ ከማል ሐሰንም ሲያሻው ከነዚህ ጋር ይደመርና ሙጅሪም
ይሆናል፡፡
በህንድ ፊልም ውስጥ ዘወትር የሚታይ ሶስተኛ አክተር አለ፡፡ ይህ ሰው በፊልሙ
ውስጥ የሚሰጠው ሚና እንደ ቤተሰብ አጫዋች ሆኖ ሰዎችን ማሳቅ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አስቂኝ ገጸ-ባህሪ በያኔው አጠራር “ማህሙዴ”
ይባላል፡፡ እጅግ ዝነኛ ከሆኑ ማህሙዴዎች መካከል “ሻክቲ” ተጠቃሽ ነው (“ሻክቲ” ሲፈልግ “ሙጅሪም”፤ ሲያሻው ደግሞ ማሕሙዴ ይሆናል)፡፡
***** *****
*****
የህንድ ፊልም ልዩ ገጽታው በርካታ ዘውጎችን አንድ ላይ የሚደበላልቅ መሆኑ
ነው፡፡ የአክሽን ፊልም ውስጥ ኮሜዲ አለ፣ አስማት አለ፣ ሮማንስ አለ፤ ዳንስ አለ፤ በአንዱ ፊልም ውስጥ ሁሉም ነገር ይገኛል፡፡
ደግሞም አክተሮቹ ሲደንሱ ድምጻቸው አንድ ዓይነት መሆኑ በጣም ያደናግራል፡፡ የሴትም ሆነ የወንድ ድምጽ ለመለየት ያስቸግራል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የህንድ ፊልም ውስጥ የሚታየው ግነት ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ
Mard በተሰኘው ፊልም ውስጥ አሚታብ ለመብረር የሚያኮበኩበውን ሂሊኮፕተር በገመድ ጠልፎ እንዳይበር ያደረገበት ትዕይንት ዘወትር
አይረሳኝም፡፡ በልጅነታችን ያንን ትዕይንት እንደ ጉድ ነበር ያጨበጨብንለት፤ አሁን ቢሆን ግን “አንተ ውሸታም! ሞኝህን ፈልግ
” ብዬ ቪዲዮውን የምዘጋው ይመስለኛል፡፡
የህንድ
ፊልም ሲነሳ ዘወትር የሚታወሱኝ ሁለት ልጆች አሉ፡፡ አንደኛው ታገል ዲሪብሳ ይባላል፡፡ ሌላኛውን ልጅ ግን ስላላስፈቀድኩት ስሙን
አልነግራችሁም፡፡ ታገል ምን አደረገ መሰላችሁ?.
የጄተንድራን ፊልም እያየን ነበር፡፡ በፊልሙ መሀል ላይ ሻክቲ የተባለው ሙጅሪም
የጄተንድራን እህት በመኪና ካሯሯጣት በኋላ ይገድላታል፡፡ ትዕይንቱ በጣም ያሳዝናል፡፡ በተለይ ልጅቷ በደም አበላ ተነክራ ላያት
ሰው ልብ ትሰብራለች፡፡ ይሁን እንጂ ብዙዎቻችን ፊልም መሆኑን አልሳትንም፡፡ ታገል ግን ከመመሰጡ ብዛት የእውነት ትዕይንት መሰለው፡፡
እናም ጮክ ብሎ “ህግ የለም እንዴ?” አለ፡፡ በቪዲዮ ቤቱ የነበረው ሰው ሁሉ በሳቅ ፍርስ አለ፡፡
የሁለተኛው ሰው ማስታወሻዬ ግን ከዚህ ይብሳል፡፡ በጊዜው ከነበሩት
የሀብታም ልጆች ነን ባዮች መካከል አንዳንዶቹ የለየላቸው ጅላጅሎች ነበሩ፡፡ አሪፍ መኪና ሲያዩ “የዘመዳችን ናት” ማለት ይቀናቸዋል፡፡
“ነዋይ ደበበ ቤታችን ሊመጣ ነው” የሚሉም ነበሩ፡፡ እኛም ለነዚህ ጅሎች ነገር እያሟሟቅን ብራቸውን እናጫርሳቸው ነበር፡፡ ከነዚያ
ልጆች አንዱ “አሚታብ ዘመዳችን ነው” እያለ ያወራልን ነበር፡፡ እኛም እያወቅን እንሞኝለታን:: አብዛኛውን ጊዜ የፊልም መግቢያ
ዋጋውን የሚከፍልልን እርሱ ስለሆነ ለርሱ መሞኘታችን የግድ ነበር፡፡
ታዲያ በብዙ ፊልሞች ውስጥ ሲሞት የማይታየው “ጀግናው” አሚታብ ባችቻን ሲያቀብጠው
Sholay በተሰኘው ፊልም መጨረሻ ላይ ሞተ፡፡ ነገሩ በጭራሽ ያልተገመተ በመሆኑ ብዙዎች ተገረሙ፡፡ “ጉድ ነው! አሚታብም ይሞታል
እንዴ?”… ተባባልን፡፡ እኛ እንዲህ ያልነው “አሚታብ ወክሎት የሚጫወተው ገጸ-ባህሪ ዘወትር አይሞትም” ከሚል መነሻ ነበር፡፡ ያ
የኛ ስፖንሰር የሆነው ልጅ ግን እየየውን አቀለጠው፡፡ “ዘመዴ ሞቶ የት አባቴ ነው የምገባው?” እያለ አነባ፡፡ ፊልም ለመመልከት
የሄደው ሰው ግራ ተጋባ፡፡ ለምን እንደሚያለቅስ ብንነግራቸው ሁላችንንም እንደ ጅል ይቆጥሩናል ብለን ፈራን፡፡ ስለዚህ ቶሎ ብለን
ልጁን ደጋግፈን ወደ ውጪ ካወጣነው በኋላ እያባበልነው ከቤታቸው ወሰድነው፡፡
ይህ ትዕይንት በአሁኑ ዘመን ይከሰታል ተብሎ የማይታሰብ ነው መቼስ! ከዛሬ
ሀያ አመት በፊት ግን ተመሳሳይ ድርጊቶችን ማየት የተለመደ ነው፡፡
-----
የህንድ ፊልም ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት በ1995 ይመስለኛል፡፡ በወቅቱ
ያየሁት Kabi Ghushi Kabi Gham የሚል የሻህሩኽ ኻን እና አሚታብ ፊልምን ነው፡፡ ያየሁበት ስፍራ አዲስ አበባ በመሆኑ
ግን እኛ ስናደርግ እንደነበረው “ማህሙዴ፣ ሙጅሪም፣ ወዘተ…” እያለ ስለ ፊልሙ የሚተርክ ሰው አላጋጠመኝም፡፡ ከዚያ ወዲህ እኔና
የህንድ ፊልም አንተዋወቅም፡፡ ለመሆኑ አሁን ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?… እስቲ ስለ ህንድ ፊልም ያላችሁን ትዝታችሁ አካፍሉን፡፡
ሰላም!
የካቲት 17/2006
ሸገር
Wow! Amazing. I remember watching very few Indian movies. There was a translator who seats in front and keeps translating everything. Then, translation goes to VCD lately. I really enjoyed the names you guys gave to different roles. Thanks for sharing Afendi!
ReplyDelete