Pages

Tuesday, December 9, 2014

አንጋፋው ሻዕቢያ



ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-------
   


 አትሳሳቱ! በምስሉ ላይ የምትመለከቱት ሰው ዐረብ አይደለም፡፡ ኢራናዊም አይደለም፡፡ ህንዳዊም አይደለም፡፡ በቀዳሚ ዘመኑ የኢትዮጵያ ፖስፖርት ነበረው፡፡ በኋላ ላይ ግን “ኤርትራ ነጸ መውጣት አለባት” ብሎ ኤርትራዊነትን ሰብኳል፡፡ ለዚህም በረሃ ወርዶ ብረት አንስቷል፡፡ በውጪ መዲናዎች “ሓርነት” እያለ ጮኋል፡፡ ይሁንና ያሰበው ከግቡ ሳይደርስለት ይህቺን ዓለም ተሰናብቷል፡፡ በአንድ ወቅት እርሱ ይመራቸው የነበሩ ወጣቶች ግን ዓላማውን አሳክተዋል፡፡
                                                                          *****
     “ጀብሃ” እና “ሻዕቢያ” በሚል ርዕስ የቀረበውን ተከታታይ ጽሑፍ ተከታትላችኋልን? እንዲያ ከሆነ “ሻዕቢያ” የተሰኘው ድርጅት ከጀብሃ ተገንጥሎ በሁለት እግሩ እንዲቆም የረዳው አንድ አደገኛ “ዲፕሎማት” እንደሆነ ተረድታችኋል ማለት ነው፡፡ ያ “ዲፕሎማት” በምስሉ ላይ የምትመለከቱት ሰው ነው፡፡ የዚህ ሰው ልደት የተበሰረው በሞቃት አየሯ በምትታወቀው ውቢቷ የምጽዋ ከተማ አጠገብ ባለችው “ሀርጊጎ” በተሰኘች ባህረ-ገብ መንደር ነው፡፡ ወላጆቹ በምሥራቅ ኤርትራ ከሚኖሩት የአሳውርታ (ሳሆ) ብሄረሰብ ነው የተገኙት:: የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በምጽዋ ካገባደደ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ከተማ አጠናቋል፡፡ በ1950ዎቹ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በመምህርነት ተመርቋል፡፡ በስራው ዓለም ወደ ምጽዋ ከተማ ተመልሶ በትምህርት ቤት ዳይሬክተርነት አገልግሏል፡፡ በዚህ ሙያ ላይ እያለም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል ሲደረግ እርምጃውን የተቃወመው “ማህበር ሸውአተ” (ሀረካ) አባል ሆኗል፡፡ በ1961 “ተጋድሎ ሐርነት ኤርትራ” (ጀብሐ) ሲመሰረት ደግሞ ከሀረካ ወጥቶ ጀብሃን ተቀላቅሏል፡፡ ድርጅቱንም ለረጅም ጊዜ በውጪ ጉዳይ ኃላፊነት አገልግሏል፡፡ ድርጅቱ እስከ አሁን ድረስ የሚታወቅበትን “ሰውራ” የተሰኘ መጽሔት መስርቷል፡፡ ከ1970 በኋላ ግን የድርጅቱን አካሄድ በመቃወም “ህዝባዊ ሀይሊ” የተሰኘ ንቅናቄ ጀምሯል፡፡ ይህንን ቡድን “ሰልፊ ነጻነት” ከተሰኘው የደገኛ ኤርትራዊያን ቡድን ጋር በማዋሃድ በታሪክ ገጾች “ህዝባዊ ሓርነት ሀይልታት” ወይንም “ሻዕቢያ” የተሰኘውን ጥምረት መስርቷል፡፡ ጥምረቱንም እንደ “ውስጠ ዘ” (defacto) ሊቀመንበር እና እንደ ውጪ ጉዳይ ሃላፊ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በስተመጨረሻው ግን ከወጣቶቹ ጋር መግባባት ስላልቻለ በልዩነት ተሰናብቷል፡፡

     ይህ ሰው እ.ኤ.አ. በ1978 ከጀብሃ ጋር በጋራ አብሮ የመስራት ስምምነት የተፈራረመ ሲሆን በ1980 ገደማም የርሱን መስመር ከሚከተሉ ሌሎች ታጋዮች ጋር “ህዝባዊ ሓርነት ሀይልታት ሰውራዊ ባይቶ” የተሰኘ ድርጅት መስርቶ ነበር፡፡ ሆኖም በወቅቱ “ሻዕቢያ” የተሰኘው ግንባር ከርሱ ጋር በሀሳብ የተለዩትን ድርጅቶች እያሳደደ ይመታ ስለነበር ወደ ሀገር ቤት ገብቶ የትጥቅ ትግል ለመጀመር አልቻለም፡፡ ቢሆንም ሰውዬው በፖለቲካው መስክ አልሰነፈም፡፡ በውጪው ዓለም ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ትግል ማድረጉን ቀጥሏል፡፡ በ1987 ግን ይህችን ዓለም ተሰናብቷል፡፡
                                                                          *****
  ሰውየውን አውቃችሁታል አይደል? አዎን! ዑስማን ሳልህ ሳቤ ነው፡፡ ዛሬ በኢሳያስ የሚመራውን ህዝባዊ ግንባር (ሻዕቢያ) የመሰረተው እርሱ ነው፡፡ ይህ ሰው በታሪክ ምሁራን እጅግ ከፍተኛ ችሎታ ያለው ፖለቲከኛ ተብሎ ነው የሚጠቀሰው፡፡ በርካታ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች በጨቅላነታቸው ዘመን የርሱ እርዳታ በእጅጉ አስፈልጎአቸዋል፡፡ የኢህአፓ ታጋዮች የትጥቅ ትግል እንዲጀምሩ ያበቃቸውን ስልጠና ያገኙት በርሱ አማካኝነት ነው፡፡ ከአስር የማያንሱ ጠመንዣዎችንም ያስገኘላቸው እርሱ ነው፡፡ የኦነግ ጠንሳሾች የሚባሉት እነ ጃራ አባገዳ በመሳሪያ ተደራጅተው ትግሉን ለመጀመር የበቁት እርሱ ባደረገላቸው እርዳታ ታግዘው ነው፡፡ ለሌሎችም እንዲሁ የእርዳታ እጁን ዘርግቷል፡፡

  “ሻዕቢያዎች” ከዑስማን ሳልህ ሳቤ ጋር መጣላታቸው እሙን ነው፡፡ በአንድ ዘመን ሀይለኛ የፕሮፓጋንዳ ጦርነት አካሂደውበታል፡፡ ከነጻነት በኋላ ግን በትግሉ ላበረከተው አስተዋጽኦ እውቅና ሰጥተዋል፡፡ በርሱ ስም ትምህርት ቤትና ጎዳና ሰይመዋል፡፡ ይህም ከጀብሃ ጋር ንክኪ የነበረው ማንኛውም ግለሰብ ያላገኘው እድል ነው፡፡ ከርሱ ጋር ይህንን እድል በጥቂቱ ለመጋራት የቻለው አንጋፋው የጀብሃ ታጋይ ኢድሪስ ገላውዴዎስ ብቻ ነው፡፡
 -----
አፈንዲ ሙተቂ
ታሕሳስ 1/2006

2 comments:

  1. Another mistake Afendi. there is no school or street named after Osman Saleh Sabbe. And Sabbe hasnt ever been discussed officially in governement or party mouthpieces since independence. To get more infos about Sabbe please refer Pro. Bereket Habte Selassie's "The Crown and the Pen".
    Secondly Idris Gelawdios surrendered to EPLF after independence in 1992, and has worked in the Commission of Referendum and Commisiion of Constitution Drafting. Later he died in Saudi Arabia.
    All comments are just for corrections. Besides, u deserve big respect and admiration for the wonderful job you are doing.

    ReplyDelete
  2. Thank you bro for your correction. I wrote this article last year. I latter realized that there is no school or street in the name of Sabbe. The new thing you told me today is that Sabbe has never been a subject in state media, press or other out lets. It is very sad to know this.

    ReplyDelete