ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
ዕለቱ መስከረም 2/1977 ነበር፡፡ በዚያች ዕለት ደርግ ከአጼ ኃይለሥላሤ መንግሥት ስልጣን የተረከበበት 10ኛው የአብዮት በዓል ይከበር ነበር፡፡ ያ በዓል ከቀደሙት በዓላት ለየት የሚልበት አንድ ነገር ታይቶበታል፡፡ ይህም የስመገናናው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ምስረታ በይፋ መታወጅ ነው፡፡ ይህንን ድርብ ደስታ ለማድመቅ ተብሎ የተዘጋጀው ክብረ በዓል በሀገራችን ታሪክ በድጋሚ አልታየም፡፡ ለዚህ በዓል ማክበሪያ በትንሹ አንድ መቶ ሚሊዮን ብር ወጪ ሆኗል (ያ ገንዘብ በአሁኑ ስሌት ሁለት ቢሊዮን ብር ሊሆን ይችላል)፡፡
በዚያን ጊዜ ነው በአስራ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር የተሰራው ታላቁ የኢሠፓ የጉባኤ
አዳራሽ ተመርቆ የተከፈተው፡፡ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ፊት ለፊት ያለው የ“ትግላችን” ሀውልትም በዚህ በዓል ወቅት ነው የተመረቀው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ለበዓሉ የታጨችው አዲስ አበባ በደማቅ መብራቶችና በልዩ ልዩ መፈክሮች ተጥለቅልቃ ነበር፡፡ እንግዶች በሚንቀሳቀሱባቸው
ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ያሉ አሮጌ ቤቶች በግንብ አጥርና በትላልቅ የጨርቅ ሽፋኖች እንዲከለሉ ተደርገዋል፡፡ የክፍለ ሀገር ዋና
ከተሞችና የአውራጃ ከተሞችም በመፈክሮችና በማጭድና መዶሻ ምስሎች አሸብርቀዋል፡፡ በዋና ዋና መንገዶች ላይ ያሉ የንግድ ድርጅቶችና
የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በሶስት ቀለማት (አረንጓዴ፤ ቢጫ፤ ቀይ) የተዘጋጁ አምፖሎችን እንዲያበሩ ታዘዋል፡፡ በየቀበሌው የተቋቋሙ
የኪነት ቡድኖችም ኢሠፓን የሚያወድሱ መዝሙሮችን አፍልቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የነጭና ጥቁር ስርጭቱን ትቶ ወደ ሙሉ የቀለም
ስርጭት የተሸጋገረው በዚያች ታሪካዊ ዕለት ነው፡፡
በዚያ ታላቅ ክብረ በዓል ላይ የምስራቅ ጀርመን ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ፀሐፊና
የሀገሪቱ መሪ የነበሩትን ጓድ ኤሪኽ ሆኔከርንና የየመን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ (ደቡብ የመን) መሪ ጓድ ዓሊ ናስር አል-ሐሰንን ጨምሮ
በርካታ የሶሻሊስት ሀገራት ልዑካን ተገኝተዋል፡፡ ከአፍሪቃም የዛምቢያው ኬኔት ካውንዳ፤ የዚምባብዌው ሮበርት ሙጋቤና የሞዛምቢኩ
ጓድ ሳሞራ ማሼል የበዓሉ ታዳሚ ነበሩ፡፡ ዋናው የበዓሉ አከባበር ስነ-ስርዓት በኢሠፓ ጉባኤ አዳራሽና በአብዮት አደባባይ የተካሄደ
ሲሆን በተለይም በአብዮት አደባባይ የተካሄደው ልዩ ትርዒትና ወታደራዊ ሰልፍ በሀገሪቱ ታሪክ ተወዳዳሪ አልተገኘለትም፡፡
*****
“ኢሠፓ” የሚባለው ዝነኛ ፓርቲ የተመሰረተው ለአምስት ዓመታት የዘለቀ መጠነ
ሰፊ ዝግጅት ከተደረገ በኋላ ነው፡፡ ለፓርቲው ምስረታ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን እንዲያቀላጥፍና ህዝቡን በሶሻሊስታዊ ስርዓት እንዲያደራጅ
በሚል “የኢትዮጵያ ሰርቶ አደሮች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን” (ኢሠፓአኮ) የተባለ ከፍተኛ የአስፈጻሚ አካል በመስከረም 1972 ተመስርቶ
ነበር፡፡ ይህንን ኮሚሽን ማቋቋሙ ያስፈለገው “የሰርቶ አደሩን ፓርቲ ለመመስረት የሚቻለው ህዝቡን በማንቃትና በማደራጀት በአንድ
ማዕከል ዙሪያ ካሰባሰቡ በኋላ ነው ” በሚለው የኮሚኒስቶች ርዕዮተ-ዓለማዊ መርህ መሰረት ነው፡፡ የዚህ ኮሚሽን ተጠሪ በመሆን በየክፍለ
ሀገሩ የተመደቡ ወኪሎች የየአካባቢው የበላይ ውሳኔ ሰጪዎች ነበሩ፡፡ የኮሚሽኑን ዓላማ የሚገልጸው “የኢሠፓአኮ ተልዕኮ ይሳካል”
የተሰኘ መፈክር በመላው ኢትዮጵያ ተደጋግሞ ይሰማ ነበር፡፡
ኢሠፓ የተመሰረተው
ለአምስት ቀናት በተካሄደ መስራች ጉባዔ ነው፡፡ በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ በድርጅታዊ አሰራር የተዘጋጀ ምርጫ ተደረገ፡፡ ጓድ መንግሥቱ
ኃይለማሪያም የፓርቲው ዋና ጸሐፊ ሆነው መመረጣቸውም ተነገረ፡፡ ከርሳቸው ጋርም መቶ ሰማኒያ ሶስት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተመረጡ፡፡
*****
የኢሠፓ አወቃቀርና አሠራር በሌሎች የሶሻሊስት ሀገራት ከታዩት ኮሚኒስት ፓርቲዎች
ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ፓርቲው የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት የበላይ ነው፡፡ የፓርቲውና የአስፈጻሚ አካላቱ ግንኙነት የጎንዮሽ ሳይሆን
ከላይ ወደታች የተዘረጋ መዋቅራዊ መልክ ነበረው፡፡ በመሆኑም ኢሠፓ በየትኛውም እርከን ላይ ላሉት አስፈጻሚ አካላት የበላይና አመራር
ሰጪ ነው፡፡ ይህ አወቃቀር በሀገር አቀፍ፣ በክፍለ ሀገርና በአውራጃ ደረጃ የተዘረጋ ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የነበሩት የሚኒስቴር
መስሪያ ቤቶች አመራር የሚቀበሉት ከኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት ነው፡፡ በክፍለ ሀገርና በአውራጃ ደረጃ ያሉ መስሪያ ቤቶችም ከኢሠፓ
ጽ/ቤት ነው አመራር የሚሰጣቸው፡፡ በመሆኑም የአውራጃና የክፍለ ሀገር የኢሠፓ ኮሚቴ አንደኛ ፀሐፊ ሆኖ የተመደበ ሰው በፕሮቶኮልም
ሆነ በስልጣኑ ከሌሎች ተሿሚዎች ሁሉ ይበልጣል፡፡
የኢሠፓ መዋቅር
በኢ-መደበኛ ሁኔታ ሁሉንም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች አዳርሷል፡፡ በያንዳንዱ የመንግሥት መስሪያ ቤት፣ በማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅቶችና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ “የኢሠፓ
መሰረታዊ ድርጅት ጽ/ቤት” የሚባል መምሪያ ነበረ፡፡ የዚህ መሰረታዊ ድርጅት ዓላማ የኢሠፓን ርዕዮተ ዓለም ማስተማርና ከበላይ አካል
የመጡ መመሪያዎች ተፈጻሚ መሆናቸውን መቆጣጠር ነው፡፡ ለፓርቲ አባልነት ብቁ የሆኑ ጓዶችን መልምሎ የአባልነት መታወቂያ የሚሰጠውም
እርሱ ነው፡፡
ኢሠፓ በፕሮፓጋንዳው ዘርፍ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያደርግ ነበር፡፡ የፓርቲው ልሳን
“ሠርቶ አደር” የሚባለው ሳምንታዊ ጋዜጣ ነው፡፡ መስከረም ደግሞ
የፓርቲው የርዕዮተ ዓለም መጽሔት ነው፡፡ የፓርቲው አባላት በሁለቱ ህትመቶች በወጡ ጽሑፎች ላይ የመወያየት ግዴታ አለባቸው፡፡
ኢሠፓ የደርግ
መንግሥት ከስልጣን እስከተወገደበት ጊዜ ድረስ ቆይቷል፡፡ በስልጣን ላይ በነበረባቸው ሰባት ዓመታት በጠቅላላው ከ100, 000 ያላነሱ
አባላትን አፍርቷል፡፡ አባላቱ ከሲቪልም ሆነ ከጦር ሀይሉ ክፍል የተመለመሉ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ የፓርቲ አባል በስራ ቀናት ከካኪ
የተሰፋ ሱሪና ኮት የመልበስ ግዴታ አለበት (ይህ መመሪያ የወጣው “የሀገር ውስጥ ምርቶችን ማበረታታት አለብን” በሚል መነሻ ነው፤
ካኪው በቃሊቲ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ነው የሚመረተው)፡፡
ከላይ እንደገለጽኩት የኢሠፓ ዋና ፀሐፊ ጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ነበሩ፡፡
ፓርቲው ምክትል ዋና ፀሐፊ በይፋ ባይሰይምም የጓድ መንግሥቱ ተከታይ ሆነው ሲሰሩ የነበሩት ጓድ ፍቅረ ሥላሤ ወግደረስ ናቸው፡፡
የርዕዮተ-ዓለም መምሪያ ሃላፊው ጓድ ሽመልስ ማዘንጊያ ሲሆኑ ጓድ ብርሃኑ ባይህ የውጭ ግንኙነት መምሪያ ሃላፊ ነበሩ፡፡ ጓድ ሸዋንዳኝ
በለጠ የኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ሃላፊ፤ ጓድ ተካ ቱሉ የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ሃላፊ፣ ጓድ ደበላ ዲንሳ የማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ
ሃላፊ፣ ጓድ ሜጀር ጄኔራል ገብረየስ ወልደሃና የወታደራዊ ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ ነበሩ፡፡ ከሁሉም በላይ ስልጣናቸው ገንኖ የነበረው ግን የድርጅት መምሪያ ሃላፊው ጓድ ለገሠ አስፋው ናቸው፡፡
*****
ኢሠፓ የምስረታ ጉባኤውን በሚያካሄድበት ወቅት (ጳጉሜ1-ጳጉሜ 5/1976)
ሀገሪቱ በከፍተኛ ድርቅ ተጠቅታ ነበር፡፡ ከአምስት ሚሊዮን የማያንሱ ዜጎች በትግራይ፣ በወሎ፣ በጎንደር፣ በኤርትራ፣ በሀረርጌና
በባሌ ክፍላተ ሀገር በቸነፈር ተጠብሰው በሞት አፋፍ ላይ ነበሩ፡፡ አንዳንድ የሀገር ተቆርቋሪዎች መንግሥት የፓርቲ ምስረታ ጉባኤውን
ለሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፍና የ10ኛ አብዮት በዓልን እንዲያስቀር ቢወተውቱም ሰሚ አላገኙም፡፡ የወቅቱ መንግሥት የድርቁ መኖር ከታወቀ
በአብዮት በዓል አከባበሩ ላይ ጥላውን ያጠላል በማለት የምዕራብ ሀገራት የዜና አውታሮች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ከልክሎአቸው
ነበር፡፡ ይሁንና አንዳንድ ሚዲያዎች የዜና ዘጋቢዎቻቸውንና የቪዲዮ ሪፖርተሮቻቸውን በድብቅ ወደ ሀገር ውስጥ በማስረግ የዓለም ህዝብ
አስከፊውን ድርቅ እንዲያየው አድርገዋል፡፡ በነዚያ ሪፖርተሮች የተቀረጹ ምስሎችን የተመለከቱ የዓለም ህዝቦች ለድርቅ የተጋለጠውን
ኢትዮጵያዊ ረሀብተኛ ለመታደግ በተንቀሳቅሰዋል (በሰር ቦብ ጊልዶፍ አስተባባሪነት የተሰባሰቡ የዓለማችን እውቅ አርቲስቶች Live
Aid የተባለውን የሙዚቃ ዝግጅት ያቀረቡት ያኔ ነው፡፡ አርቲስቶቹ በዝግጅቱ ላይ በጋራ ያዜሙት We are the world የተሰኘው
ዜማ ከምንጊዜም ምርጥ ዜማዎች መካከል አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል)፡፡
የደርግ መንግሥት
በህጋዊ መንገድ ፈቅዶላቸው የመጡ ጥቂት የሶሻሊስት ሀገራት ዘጋቢዎች ደግሞ “ድርቅ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ እየቀጠፈ ለዚህ በዓል
ከፍተኛ በጀት መመደብ አግባብ ነውን?” የሚል ጥያቄ በይፋ በማቅረብ የሀገሪቱን ከፍተኛ ባለስልጣናት አጨናንቀዋል፡፡ በመሆኑም የአብዮት
በዓሉ ሲፈጸም መንግሥት በድርቅ የተጎዳውን ህዝብ ለመታደግ መንቀሳቀሱ ግድ ሆኖበታል፡፡ ሆኖም የመንግሥት እርምጃ በጣም የዘገየ
በመሆኑ አምስት መቶ ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን በዚያ አስከፊ ድርቅ አልቀዋል፡፡
-----
አፈንዲ ሙተቂ
መስከረም 2/2007
No comments:
Post a Comment