Monday, August 11, 2014

“አንድ በላተኛ” ጠመንጃዎች በኢትዮጵያ


ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
---------
በዲሞትፈር፣ አርገው ገፍተር
በወጨፎ፣ አርገው ቀፎ
በሰናድር፣ አርገው ክንችር
በምንሽር፣ ያዘው አብሽር
ባጭር አልቤን፣ ደረት ልቤን፡፡

(ወዳጄ ካሳሁን አለማየሁ ከጻፈው ሀገርኛ ግጥም የተወሰደ)
*****
ጠመንዣ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሀገራችን የገባው በ16ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ከሰለሞናዊ አጼ ንጉሠ ነገሥቶች ጋር ሲፋለሙ የነበሩት የአዳል ሱልጣኔት ገዥዎች ናቸው ጠመንዣን ወደ ሀገራችን ያስገቡት፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ የሰለሞናዊ ነገሥታት ወታደሮችም ጠመንዣን ለመታጠቅ ችለዋል፡፡ ወታደሮች ሙሉ በሙሉ በጠመንዣ መዋጋት የጀመሩት ግን በአድዋው ጦርነት ማግስት ነው፡፡ እስከ አድዋው ጦርነት ድረስ ጦርና ጎራዴን ከጠመንጃ ጋር በማፈራረቅ ይጠቀሙ ነበር፡፡

    እንደዚህም ሆኖ ግን የያንዳንዱ ዘመን የቴክኖሎጂ ውጤት የሆነ ጠመንዣ ወደ ኢትዮጵያ ይገባ እንደነበረ ይታመናል፡፡ የውጪ መንግሥታት ለኢትዮጵያ ነገሥታት ከሚያቀርቧቸው ገጸ-በረከቶች መካከል አንዱ ጠመንዣ ስለመሆኑም በስፋት ተጽፏል፡፡ ከነዚያ የጠመንዣ ዓይነቶች መካከል አንዳንዶቹ እስከዚህ ዘመን ድረስ ይደነቃሉ፡፡ ለምሳሌ በጅማ ከተማ በሚገኘው የአባጅፋር ሙዚየም ውስጥ አነስተኛ ከዘራ የሚመስል አንድ ጠመንዣ አለ፡፡ ያ መሳሪያ ጠመንዣ መሆኑን የምትረዱት አስጎብኚው አተኳኮሱን ሲያሳችሁ ብቻ ነው፡፡ በሌላ ቦታ ብታዩት ትንሽዬ ከዘራ ነው ብላችሁ የምታልፉት ይመስለኛል (ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማሪያም እንደዚያ ዓይነት የከዘራ ጠመንዣ እንደነበራቸው አንድ የቀድሞ ጦር አባል ጥቅምት 1985 በታተመው በእፎይታ መጽሔት ላይ አስነብበውን ነበረ)፡፡

   ጠመንዣ በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የተሰራጨው በሀያኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡ ከነዚያ ጠመንዣዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ዛሬም ድረስ ያገለግላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ግን የአገልግሎት ዘመናቸው አብቅቶ ስሞቻቸው ብቻ ቀርተውናል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በጥቅሉ “አንድ በላተኛ” የሚባሉትን ጠመንጃዎች በጥቂቱ እንቃኛለን፡፡
*****
“አንድ በላተኛ” ኦቶማቲክ ያልሆኑ ጠመንዣዎች በወል የሚጠሩበት የአማርኛ ስም ነው፡፡ እነዚህ ጠመንዣዎች በኦሮምኛ “ተከ ኛቴ” (takka nyaattee) ይባላሉ፡፡ ጠመንዣዎቹ እንዲህ እየተባሉ የሚጠሩት አንድ ጥይት ብቻ ስለሚጎርሱ ሳይሆን የጎረሱትን ጥይት አንድ በአንድ የሚተኩሱ በመሆናቸው ነው፡፡ ይህም ማለት ጠመንዣው ተቀባብሎ አንዴ ከተተኮሰበት በኋላ እንደገና ማቀባበልን ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም “አንድ በላተኛ” ከተሰኘው ስያሜ በተጨማሪ “ቆመህ ጠብቀኝ” የሚል የፉገራና የስላቅ ስያሜም ወጥቶላቸዋል፡፡

    “አንድ በላተኛ” የሆኑ ጠመንዣዎች በአብዣኛው አምስት ያህል ጥይቶችን ነው የሚጎርሱት፡፡ እነዚህም ጥይቶች ትልልቆች ናቸው፡፡ ጥይቱ ከተተኮሰ በኋላ በርቀት ላይ የሚገኝን ነገር መትቶ የመጣል ሀይሉም ከፍተኛ ነው ይባላል፡፡ በመሆኑም “አንድ በላተኛ” ጠመንዣዎች በተለይ ለአደን ስራ በጣም ተመራጭ ናቸው፡፡

  በድሮው ዘመን ለውጊያ ይፈለጉ የነበሩት እነዚህ “አንድ በላተኛ”ዎች በሰለጠነው ዓለም እምብዛም አያገለግሉም፡፡ በኛ ሀገር ግን አስከ አሁን ድረስ በጥበቃ ስራ ላይ የተሰማሩ ዘበኞችና የአካባቢ ሚሊሻዎች በብዛት የሚያነግቱት “አንድ በላተኛ” ጠመንጃዎችን ነው፡፡  

   በሀገራችን ውስጥ የብዙ ሀገራት ስሪት የሆኑ “አንድ በላተኛ” ጠመንዣዎች አሉ፡፡ እነዚህን ጠመንዣዎች የምንጠራባቸው የተለምዶ ስያሜዎች በፋብሪካ የተሰጧቸው የሞዴል ስሞች ናቸው ብሎ ለመናገር ይከብዳል፡፡ የሆነው ሆኖ በኛ ሀገር ሲያገለግሉ ከነበሩት የጠመንዣ ዓይነቶች መካከል ጥቂቶቹን እንተዋወቃቸው፡፡  

1.      ምንሽር፡

“ምንሽር” ጣሊያን ሰራሽ ጠመንዣ ነው፡፡ በሀገራችን ውስጥ በስፋት ያገለግል ነበር፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ አርበኞች የጣሊያን ወራሪዎችን የተፋለሙበት ዓይነተኛው የጠመንዣ ዓይነት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ጠረፎችና በትግራይ ገጠሮች በአገልግሎት ላይ ያለ መሆኑ ይነገራል፡፡ በሌሎች ክልሎች ግን እምብዛም አይታይም፡፡  

2.     አልቤን:

የአልባኒያ ስሪት የሆነ የጠመንጃ ዐይነት ነው፡፡ በዚህ ዘመን ብዙም የማይታየው ይህ ጠመንጃ በኢጣሊያ ወረራ ዘመን ከፍተኛ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡

3.     ውጅግራ፡

ይህኛው ጠመንዣ ድምጹ ብራቅ ነው ይባልለታል፡፡ እንደ ከርከሮ እና ጅግራ ያሉት እንስሳት ወደ ሰብል ማሳ እንዳይጠጉ ለመከላከል ከተፈለገ አንድ የውጅግራ ጥይት ይበቃቸዋል፡፡

4.     ረሽ፡

ብዙ ጊዜ ለአደን ስራ የሚያገለግል ነው፡፡ ለዚህም ያግዝ ዘንድ በጠመንዣው ላይ የማነጣጠሪያ “ቴሌስኮፕ ተገጥሞለታል፡፡ ብዙ ሰዎች “መተሬ” (sniper) እያሉ የሚጠሩት ጠመንዣ እርሱ ሳይሆን ይመስለኛል፡፡

 ይህ ጠመንዣ ጥይት በሚጎርስበት ጊዜ ከሰደፉ በኩል ሰበር ብሎ ይቆለመማል፡፡ በተጨማሪም ሁለት አፈሙዝ ነው ያለው፡፡ ጥይቱ ከተተኮሰ በኋላ በአየር ላይ ስለሚበተን እንደ ጅግራ፣ ቆቅና ዳክዬ መሳሰሉ አዕዋፋት በመንጋ በሚበሩበት ወቅት ለማደን ተመራጭ ነው፡፡ ረሽ በሰሜን ኢትዮጵያ ገጠሮች “ግንጥል” የሚል ስያሜ እንዳለው “እንዳላማው አበራ” የሚባል የፌስቡክ ጓደኛዬ አጫውቶኛል፡፡

5.     ዲሞትፈር

በኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት የተሰራጨ የጠመንጃ ዓይነቶች አንዱ ነው፡፡ የዘንጉ ርዝማኔ ይለያያል፡፡ ከዚህ ጠመንዣ ጋር በተያያዘ በሀገራችን ውስጥ ታሪካዊ እና አወዛጋቢ የሆነ አንድ አባባል ተፈጥሯል፤ “ዲሞን በዲሞትፈር” የሚል፡፡ አባባሉ የተፈጠረው በዘመነ ቀይ ሽብር ነው፡፡ “ዲሞ” እየተባሉ የተጠሩት የኢህአፓ አባላትና ደጋፊዎች ናቸው፡፡ (“ዲሞ” የኢህአፓ ልሳን ከነበረችው “ዲሞክራሲያ” ጋዜጣ ስያሜ ላይ የተቀነጨበ ነው)፡፡

   ይህ አባባል ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማው ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ጥር 26 ቀን 1969 በተቀናቃኝ የደርግ አባላት ላይ  የወሰዱትን እርምጃ ለመደገፍ በሚል በቀጣዩ ቀን በተዘጋጀው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ነው፡፡ ብዙ ጸሐፍት እንደሚሉት “ዲሞን በዲሞትፈር” የሚለውን አባባል ፈጥረው ወደ አደባባይ ያወጡት የመኢሶን አመራሮች ናቸው፡፡ መኢሶን ግን ነገሩን ያስተባብላል፡፡ ያም ሆነ ይህ አባባሉ “ዲሞትፈር” ጠመንዣ በቀይ ሽብር አፈጻጸም ውስጥ የነበረውን ሚና የሚያስረዳ ይመስለኛል፡፡

ዲሞትፈር በሀገራችን ውስጥ አሁንም በስፋት ያገለግላል፡፡ ይሁንና በጎንደርና ጎጃም ክፍለ ሀገራት ይበልጥ የሚታወቀው “ጓንዴ” በሚለው ስም ነው፡፡
  
6.     ቺኮዝ


በደርግ ዘመን የመጨረሻ ዓመታት በቀበሌ ደረጃ የተደራጁ የአብዮት ጥበቃ ጓዶች ሲታጠቁ የነበሩት ጠመንዣ ነው፡፡ ከስያሜው ለመረዳት እንደሚቻለው ጠመንጃው የተሰራው በቼኮዝሎቫኪያ ነው፡፡ ቼኮዝ ግራጫ ቀለም ያለው ጠመንዣ ነው፡፡

ቺኮዝ በጣም አደገኛ መሳሪያ ነው፡፡ ጥይቱ ወደ ሰውነት ሲገባ ቀዳዳው ትንሽ ነው፡፡ ሲወጣ ግን አካልን በሰፊው ቦድሶ ነው የሚወጣው፡፡ አንድ ሰው በቺኮዝ መመታቱን ለማወቅ ጥይቱ የገባበትንና የወጣበትን ቦታ ብቻ መመልከት ይበቃል፡፡

7.     ቤንቶቭ

“አንድ በላተኛ” ጠመንዣዎች ሁሉ ለመሸከም የማይከብደው ይህኛው ነው፡፡ የጠመንዣው እንጨትም ጥቁር ቡናማ መልክ አለው፡፡ በደርግ ዘመን የቀበሌ ጥበቃ ጓዶች ከቺኮዝ ቀጥሎ በብዛት ይታጠቁ የነበሩት ቤንቶቭን ነው፡፡
*****

እላይ ከዘረዘርናቸው መሳሪያዎች ሌላ ወጨፎ፣ ቤልጅግ፣ መውዜር፣ ሰናድር፣ ናስማሰር፣ ጉንጮ፣ ስኩዌር ወዘተ… የሚባሉ “አንድ በላተኛ” ጠመንዣዎች በሀገራችን ውስጥ በስፋት ያገለግሉ እንደነበረ መዛግብትና የቃል ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ ከላይ እንደገለጽኩት በውጪው ዓለም በከፍተኛ ፍጥነት እየተለወጠ በመሄድ ላይ የሚገኘው የመሳሪያና የወታደራዊ ምህንድስና ቴክኖሎጂ እነዚህን አንድ በላተኛ ጠመንጃዎች ከአገልግሎት ውጪ አድርጎአቸዋል፡፡ በሀገራችንም ውስጥ ብዙዎቹ ለጥበቃ ስራ ቢያገለግሉም በቅርብ ዓመታት አገልግሎታቸውን ማቋረጣቸው እንደማይቀር ይታመናል፡፡ ቢሆንም አባቶቻችን ታሪክ ሲሰሩ የነበሩት በነርሱ ነውና የያንዳንዱን መሳሪያ ስርጭትና የአገልግሎት አድማስ መዝግቦ ለመጪው ትውልድ ማቆየት ይገባል፡፡ ሰላም!!

No comments:

Post a Comment