Pages

Tuesday, May 13, 2014

“ጄኔራል ፋንታ በላይ” እና “የግንቦት 8/1981 የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ”



ጸሓፊ፡- አፈንዲ ሙተቂ
---------
ይህንን ጽሑፍ ልክ የዛሬ ዓመት ገደማ ፖስት አድርጌው ነበር፡፡ ዛሬም ታሪካዊነቱ ጎልቶ ስለታየኝ ልደግመው ወሰንኩ፡፡ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው በተካሄደበት ግንቦት 8/2006 ቀን ሌላ ጽሑፍ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
-------
በዚህ የሁለት ደቂቃ ቪዲዮ ላይ የሚታዩት ሜጀር ጄኔራል ፋንታ በላይ ናቸው። ጄኔራል ፋንታ ግንቦት 8/1981 ተሞክሮ የከሸፈውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በማቀነባበር ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ በሰፊው ተነግሯል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወጡት የህትመት ውጤቶችም ይህንኑ አረጋግጠዋል ( ቪዲዮውን ለማየት ይህንን ሊንክ ይክፈቱ http://www.youtube.com/watch?v=GDjRkfq-toM )፡፡

ጄኔራል ፋንታ መፈንቅለ መንግሥቱን የጠነሰሱት በ1977 ዓ.ል. ክረምት ላይ በተካሄደው “ዘመቻ ባህረ ነጋሽ” ወቅት እንደሆነ በሰጡት የምርመራ ቃል አረጋግጠዋል። ዘመቻው ምዕራባዊውን የኤርትራ አውራጃዎች ከሻዕቢያ (EPLF) ነጻ የማውጣት ዓላማ ነበረው። በዘመቻው የኢትዮጵያ ጦር ድል ቢቀዳጅም የተከፈለው መስዋእትነት ከተጠበቀው በላይ ሆኖ ተገኘ። በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወጣቶች (በተለይም በአንደኛው የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ፕሮግራም የዘመቱ) አለቁ። የዚህ አሳዛኝ ትራጄዲ መንስኤ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም በሀገራቸው የጦር መኮንኖች የተወጠነውን የዘመቻ ስትራቴጂ በመግፋት ከሶቪየት ህብረት አማካሪዎቻቸው የተሰጣቸውን እቅድ መተግበራቸው ነው። በወቅቱ የኢትዮጵያ አየር ሀይል ዋና አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ፋንታ በላይ የዘመቻ ባህረ ነጋሽን ውጤት ሲሰሙ “ይህ ሰውዬ ዘወትር እኛን እየገፋን የሀገራችንን ወጣቶች እንደ ማገዶ እንጨት የሚቆጥሩትን የሶቪየት አማካሪዎችን ሃሳብ የሚተገብረው ለምንድነው? በዚህ ዓይነትስ እስከ መቼ ልንዘልቅ ነው?” እያሉ ማሳላሰል ጀመሩ። ብዙ አውጥተው ካወረዱ በኋላ መፍትሄው ሰውዬውን ማስወገድ ብቻ እንደሆነ አመኑ። “ለዚህም ዓይነተኛው ዘዴ በከፍተኛ መኮንኖች የሚመራ መፈንቅለ መንግሥት ነው” ከሚል መደምደሚያ ላይ ደረሱ።

ጄኔራል ፋንታ ኩዴታውን በጸነሱበት ማግስት ሶስት ከፍተኛ መኮንኖችን በጉዳዩ ላይ በማወያየት ስምምነታቸውን አገኙ። እነርሱም ሜ/ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ (የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም)፣ ሜ/ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ (የሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት ዋና አዛዥ) እና ሜ/ጄኔራል አበራ አበበ (በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የዘመቻ መምሪያ ሃላፊ) ነበሩ። አራቱ ጄኔራሎች እቅዳቸውን ለተወሰነ ጊዜ በሚስጢር ይዘውት ቆዩ። ይሁንና ሁለት አደገኛ ሀይሎች ሚስጢሩን አገኙት። እነርሱም KGB የተሰኘው የሶቪየት ህብረት የስለላ ተቋም እና የደህንነት ሚኒስትሩ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ ናቸው።

ለኮሎኔል ተስፋዬ ሚስጢሩን የነገሩት ጄኔራሎቹ ራሳቸው ናቸው። ይህም በጄኔራል ፋንታ የምርመራ ቃል ተረጋግጧል። እነ ጄኔራል ፋንታ ለደህንነት ሚኒስትሩ የነገሩት ነገር ለሶቪየቱ KGB እንደሚደርሰው አያውቁትም ነበር ለማለት ይከብዳል። ይሁንና ጄኔራሎቹ በወቅቱ ነገሩን የረሱት ይመስላል (ወይንም ነገሩን አቃለው አይተውታል)። ታዲያ ምትሀተኛው KGB ሞስኮ ቁጭ ብሎ ያገኘውን ሚስጢር ሳያባክን ከከፍተኛ ትዕዛዝ ጋር አዲስ አበባ ለሚገኙት የሶቪየት አምባሳደር አስተላለፈው። አምባሳደሩም በከፍተኛ ፍጥነት እየበረሩ ወደ ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ቢሮ ደረሱና ሚስጢሩን ነገሯቸው።

ኮ/ል መንግሥቱ ከሶቪየቱ አምባሳደር የሰሙትን በመጠራጠር የደህንነት ሚኒስትሩን አስጠሩና ስለጉዳዩ የሚያውቁት ነገር እንዳለ ጠየቋቸው። ኮ/ል ተስፋዬ ከመንጌ በሰሙት ነገር ተደናገጡ። ሙሉ ሰውነታቸው ተርበተበተ። ኮ/ል መንግሥቱ ዛሬ ላይ ቆመው እንደሚያስታውሱት “ኮ/ል ተስፋዬ መናገር አቅቷቸው ቡ..ቡ…ቡ..” አሉ።  ኮሎኔሉ ከመንጌ ጥያቄ ለማምለጥ ያህል “ይህንን ነገር አልሰማሁትም፤ ከዛሬ ጀምሮ በቅርበት እከታተለውና የምደርስበትን ውጤት እነግርዎታለሁ” አሉ። መንጌም በነገሩ ተስማምተው ተለያዩ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ በመፈንቅለ መንግሥቱ ደጋፊነት የሚታወቁት ኮሎኔል ተስፋዬ በመንጌ ፍጥጫ (እና ምናልባትም በኬጂቢ ፍራቻ) ወደ ተቃዋሚነት ተለወጡ። ጄኔራሎቹ በስልክ የሚነጋገሩትን እየጠለፉ ማዳመጥና በየጦር ክፍላቸው የሚያደርጉትን ሁሉ በአይነ ቁራኛ መከታተል ጀመሩ። መንጌም ኩዴታው ጎላ ብሎ ባይታያቸውም እንኳ “እንዲያው ለምናልባቱ” በሚል ጄኔራል ፋንታ በላይን ከአየር ሀይል አዛዥነታቸው አንስተው “የኢንዱስትሪ ሚኒስትር” አድርገው ሾሟቸው። 
*****
ማክሰኞ ግንቦት 8/1981 የቁርጥ ቀን ሆነ። ጄኔራሎቹ በመጋረጃ ጀርባ ለአራት ዓመታት ሲያንከባልሉት የነበረውን የመፈንቅለ መንግሥት ሀሳብ በዚህ ቀን ወደ ድርጊት ሊቀይሩት ተነሱ። በእለቱ ወደ ጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ (ምስራቅ ጀርመን) የሚጓዙትን ኮ/ል መንግሥቱ ሀይለማሪያምን ከሸኙ በኋላ እኩለ ቀን ላይ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ተገናኙ። በወቅቱ በአዲስ አበባ ይገኙ የነበሩትን ዋና ዋና የጦር መኮንኖች ሰበሰቡና ስለመፈንቅለ መንግሥቱ ነገሯቸው።

    ከነዚያ ጄኔራሎች በስተቀር በየትኛውም የስልጣን እርከን ላይ የነበረ የደርግ ሰው ስለስብሰባው ያወቀው ነገር አልነበረም። ይሁንና ከጥቂት ጊዜ ወዲህ የጄኔራሎቹን ጉዳይ ስራዬ ብሎ መከታተል የጀመረው  የደህንነት ሚኒስትሩ ስብሰባው “የመፈንቅለ መንግሥት አድማ” እንደሆነ ወዲያውኑ ነበር ያወቀው። ለዚህም የረዱት ሶስት ነገሮች ናቸው። አንደኛ ጄኔራል መርእድ ንጉሤ (ኤታማዦር ሹሙ) በጠዋቱ የፕሬዚዳንት መንግሥቱ አሸኛኘት ፕሮግራም ላይ መገኘት ሲኖርባቸው አልተገኙም። ሁለተኛ የመከላከያ ሚኒስትሩ ሜጀር ጄኔራል ሀይለ ጊዮርጊስ ሀብተ ማሪያም በስብሰባው ቦታ አልነበሩም። በመሆኑም መከላከያ ሚኒስትሩ ያልተሳተፉበት ስብሰባ የርሳቸው እውቅና እንዳልነበረው ለደህንነት ሚ/ሩ ታይቶታል። ሶስተኛ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር የነበረው ጄኔራል ፋንታ በላይ በስብሰባው ላይ ተገኝቷል። በወቅቱ ሲቪል የነበረው ጄኔራል ፋንታ በዚያ ቦታ መገኘቱ ለደህንነት ሚኒስትሩ አንድ ፍንጭ ሰጥቷል። 
*****
የደህንነት ሚኒስትሩ እነዚህን ነገሮች ካገናዘበ በኋላ በቀጥታ ወደ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት በረረና የደረሰበትን ሁሉ የፕሬዚዳንቱ ልዩ ረዳት ለነበረው ሻምበል መንግሥቱ ገመቹ ነገረው። ሁለቱ ሰዎች በነገሩ ላይ ለጥቂት ደቂቃዎች ከተማከሩ በኋላ የመከላከያ ሚኒስትሩን አስጠርቶ መጠየቅ እንደሚበጅ ከስምምነት ላይ ደረሱ። በዚሁ መሰረት ሚኒስትሩ ተጠርተው ሲጠየቁ  ስለስብሰባው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናገሩ። ሁለቱ ሰዎችም (ሻምበል መንግሥቱና ኮ/ል ተስፋዬ) እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ሚኒስትሩ ወደ መከላከያ ሄደው ተሰብሳቢዎቹን ቢያነጋግሩ የተሻለ እንደሚሆን ሀሳብ አቀረቡ። ሚኒስትሩም ከአንዴም ሁለቴ መኪናቸውን ወደ መከላከያ ሚኒስቴር እየነዱ ተሰብሳቢዎቹን ለማነጋገር ሞከሩ። ይሁንና በሁለቱም ጊዜያት ከተሰብሳቢዎቹ ዘንድ ለመድረስ አልቻሉም። ይባስ ብሎም የመፈንቅለ መንግሥቱ የዘመቻ መኮንን ተብሎ በተመደበው ጄኔራል አበራ አበበ ተገደሉ።

 የጄኔራል ሀይለ ጊዮርጊስ (መከላከያ ሚኒስትሩ) መገደል መፈንቅለ መንግሥቱ ጥርጣሬ ብቻ እንዳልሆነ የሚያረጋግጥ ድርጊት ሆነ። በአንጻሩም መፈንቅለ መንግሥቱን ለውድቀት ያበቃው ይኸው ድርጊት ሆኖ ተገኘ። ከዚህ ክስተት በኋላ ጄኔራል አበራ ከቢሮ ውስጥ ለተሰበሰቡት ጄኔራሎች አድራሻውን ሳያሳውቅ ከግቢው ወጥቶ ተሰወረ። ቤተ መንግሥቱን የሚጠብቀው የልዩ ጥበቃ ብርጌድም (በተለምዶ አጠራር “ቅልብ ጦር”) ሳይታሰብ የመከላከያን ግቢ በታንክና በብረት ለበስ ከበበው። ከአስመራ ጄነራሎቹን ለመርዳት የተላከው የአየር ወለድ ጦርም መሪው ጄኔራል ቁምላቸው ደጀኔ ጥርት ያለ አመራር ስላልሰጡት በነመንግሥቱ ገመቹና ተስፋዬ ወ/ሥላሴ ተጠለፈ። ይሄኔ በመከላከያ ግቢ “ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ” ሆነ። ለጥበቃቸው አንድ ሻምበል ተጠባባቂ ጦር እንኳ ያላዘጋጁት ጄኔራሎች ተዋከቡ።  እዚያው ቡድን አበጅተው መጣላት ጀመሩ። “የህጻን እቅድ አውጥታችሁ እንድናንቦጫርቅ አደረጋችሁን” ተባባሉ።

   የአድማው መሪ ሆነው የዋሉት ጀኔራል መርዕድ ንጉሤ ግን ተስፋ ሳይቆርጡ እስከ ምሽት ድረስ ዕድላቸውን ሞከሩ። በተለይ ደብረ ዘይት ላይ የከተመው አየር ሀይል ጄቶቹን አንቀሳቅሶ በመከላከያ ሚ/ር ዙሪያ የተኮለኮሉትን ታንኮች እንዲደበድብላቸው ብዙ ወተወቱ። ሆኖም ምንም ምላሽ አላገኙም።

  ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ሁሉም ነገር ያበቃለት መሰለ። ለግማሽ ቀን ያህል መከላከያን ከበው የዋሉት የቅልብ ጦር ኮማንዶዎች ወደ ግቢው መግባት ጀመሩ። በዋናው ህንጻ ላይ ወዳለው የሚኒስትሩ ቢሮ ሲደርሱ አስራ ሁለት ጄኔራሎች ተቀምጠው በስጋት ዓይናቸውን ሲያቁለጨልጩ አገኟቸው። ሁሉንም አውጥተው ለሻምበል መንግሥቱ ገመቹ አስረከቧቸው።

  ሻምበል መንግሥቱ የተያዙትን ሰዎች ትክ ብሎ ሲያይ አራት መኮንኖች ከጄኔራሎቹ ቁጥር መጉደላቸውን አረጋገጠ። ለኮማንዶዎቹም “እያንዳንዱን ክፍል እየከፈታችሁ ፈትሹ” የሚል ትዕዛዝ ሰጣቸው። ኮማንዶዎቹም በተባሉት መሰረት ክፍሎችን መፈተሽ ሲጀምሩ ከዋናው ህንጻ ምዕራባዊ ጥግ አካባቢ “ድው” የሚል የተኩስ ድምጽ ሰሙ። ድምጹ ወደተሰማበት አቅጣጫ በዝግታ እያማተሩ ሲጓዙም “ድው” የሚል ሌላ ድምጽ ተሰማ። በዚህን ጊዜ ወታደሮቹ ሁለት ረድፍ ሰርተው በጥንቃቄ እያዘገሙ ከቦታው ደረሱ። ሁለት ከፍተኛ ጄኔራሎች ሽጉጣቸውን ጠጥተው ተገኙ። ሜጀር ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ- የኢህዲሪ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም፣ እና ሜጀር ጄኔራል አምሐ ደስታ- የኢህዲሪ አየር ሀይል ዋና አዛዥ….
*****
   ግንቦት 8/1981። ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት። የኢትዮጵያ ድምጽ ብሔራዊ አገልግሎት (የአሁኑ የኢትዮጵያ ሬዲዮ) እንዲህ የሚል ዜና አስተላለፈ።
“በጥቂት ከሀዲ ጄኔራሎች የተካሄደው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሙሉ በሙሉ መክሸፉን የኢህዲሪ የመንግሥት ምክር ቤት ቃል አቀባይ አስታወቁ”
*****
  በዚያች ምሽት ሁለት ጄኔራል መኮንኖች የገቡበት ሳይታወቅ ጠፍተዋል። ከአስር ቀናት በኋላ ግን አንደኛው ጄኔራል የነበረበት ቦታ በውስጠ አዋቂ ተደረሰበትና አዳኝ ጦር ተላከበት። ጄኔራሉ በጦር እንደተከበበ ሲያውቅ ጣሪያ ለጣሪያ እየሮጠ ለማምለጥ ሞከረ። ግን አልቻለም። ሰፈሩን በድርብርብ ክብ ያጠረው አዳኝ ጦር የጀኔራሉን የማምለጥ እድል አጨናጎለው። ጄኔራሉም ልክ እንደ ጓደኞቹ ወደቀ። ሜጀር ጄኔራል አበራ አበበ- የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የዘመቻ መምሪያ ሃላፊ።

   ይህ ከመሆኑ ከአንድ ሳምንት በፊት ሁለተኛው ጄኔራል በራሳቸው ፍላጎት ከተደበቁበት ቦታ ወጥተው ለመከላከያ ሚኒስቴር የጥበቃ ዘቦች እጃቸውን ሰጥተዋል። ጄኔራል ፋንታ በላይ- የቀድሞው የኢህዲሪ አየር ሀይል ዋና አዛዥ፣ በወቅቱ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር……

 ጄኔራል ፋንታ ለሶስት ቀናት ያህል በኮንቴነር ውስጥ ተደብቀው መቆየታቸውን ገልጸዋል። ጄኔራሉ ለሶስት ቀናት ያለ ምግብና ውሃ መቆየታቸው ያስደነቀው የአዲስ አበባ ህዝብ በወቅቱ እንዲህ የሚል ስንኝ ቋጥሮ ነበር።
     “ፔፕሲ ኮካ ኮላው ከከተማው ጠፍቶ
       ፋንታ ተገኘ አሉ በኮንቴነር ሞልቶ”

በመፈንቅለ መንግሥቱ ጦስ ከተያዙት ጄኔራሎች መካከል ነገሩን ከውጥኑ ጀምሮ የሚያውቁት ጄኔራል ፋንታ በላይ ብቻ ነበሩ። ይሁንና ምርመራ ሲደረግባቸው አጠቃላይ ነገሮችን ከመናገር ውጪ ዝርዝር የሆኑ ጉዳዮችን ከማውጋት ተቆጥበዋል። ጄኔራል ፋንታ የተናገሩት አንድ ትልቅ ሚስጢር ቢኖር የደህንነት ሚኒስትሩ ከሃዲነት ነው። በማዕከላዊ ምርመራ ላነጋገሩዋቸው ኦፊሰሮች “ሚኒስትሩ ‘ከናንተ ጋር ነኝ’ ብሎን ነበር፤ እኛም አምነነው በእርምጃችን ቀጠልንበት። በኋላ ላይ ግን ከዳን” በማለት ገልጸዋል። ታዲያ የደህንነት ሚኒስትሩ ይህንን ሲሰሙ እጅግ በጣም በመደናገጣቸው መናገር ሁላ አቅቷቸው እንደነበር በወቅቱ በቦታው የነበሩት መርማሪዎች ተናግረዋል። በመሆኑም ሚኒስትሩ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ሳይቀደሙ ለመቅደም ተነሱ። ጄኔራል ፋንታ ከሁለት ወር የእስር ቆይታ በኋላ ከነሚስጢራቸው ተገደሉ። ሀምሌ 13/1981 ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ የኢትዮጵያ ድምጽ ብሔራዊ አገልግሎት እንዲህ የሚል ዜና አስተላለፈ።

“በግንቦት 8/1981 ተካሂዶ የከሸፈውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ያቀናበሩት ከሀዲው ጄኔራል ፋንታ በላይ ጠባቂያቸውን በካራቴ መትተው ለማምለጥ ሲሞክሩ በሌሎች ዘቦች ተገደሉ”
     ******************************************
አፈንዲ ሙተቂ
ግንቦት 7/2005
ሀረር
http://www.youtube.com/watch?v=GDjRkfq-toM

No comments:

Post a Comment