Wednesday, September 4, 2013

==የሀረላ ወግ==



ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
----------

ከታችኛው አዋሽ አካባቢ ተነስታችሁ እስከ ጅጅጋ ድረስ በተዘረጋው መሬት ባሉት መንደሮች ውስጥ ስትጓዙ የጥንታዊ ግንባታ ፍርስራሾች በብዛት ያጋጥሟችኋል። የየመንደሮቹን ነዋሪዎች ስለግንባታዎቹ እንዲነግሯችሁ ብትጠይቋቸው ሀረላ የሚባል ጥንታዊ ነገድ መኖሪያዎች እንደነበሩ ያወጓችኋል። ስለዚያ ጥንታዊ ነገድ የበለጠ ማወቅ አምሯችሁ ወግ ቢጤ ብትጀምሩ ደግሞ በጣም የሚነሽጡ ወጎችን ያጫውቱአቸዋል፡፡ እስቲ የሀረላ ወጎችን በጥቂቱ ልጻፍላችሁ፡፡
*****     *****   *****
     የሀረላ ነገድ ሰዎች ቁመተ ረጃጅም ነበሩ፡፡ አንድ የሀረላ ሰው በቁመቱ የዘመናችንን ሰው ስድስት ጊዜ ያህል ይበልጠዋል፡፡ ግዝፈቱ ደግሞ ለከት የለውም። ትከሻው በጣም ሰፊ ነው። እጅግ በጣም ጠንካራ በመሆኑ ትልልቅ ቋጥኞችን በቀላሉ እየፈነቀለ ይወረውራል። ቤቱን የሚገነባውም ከተራራ ላይ ቋጥኝ እየፈነቀለ ነው። በሸለቆ ውስጥ የሚፈሱ ወንዞችን እየጠለፈ ሽቅብ እንዲፈሱ በማድረግ ውሃው ወደ እርሻው እንዲደርስ የሚያደርግበትን ብልሀት ተክኗል።
 
    ሀረላ ገበሬ መኖሪያ ቤቱ በልበሌቲ (ምዕራብ ሀረርጌ) ቢሆን እርሻው አሰቦት ያህል ሊሆን ይችላል። በየቀኑም ከበልበሌቲ ተነስቶ እርሻው ወዳለበት አሰቦት አካባቢ ይሰማራል። ሚስቱ ሆጃ እና ላቀን (ምሳ) እዚያ ድረስ ትወስድለታለች። ከዚያም ሲመሽ ሀረላው በሬዎቹን እየነዳ ወደቤቱ ያዘግማል። ሀረላው ይህንን ረጅም ርቀት (በደርሶ መልስ 250 ኪ.ሜ. የሚሆን) የሚጓዘው ዘና ብሎ ነው።

     ሀረላ ገበሬ ምሽት ላይ ወደ ቤቱ የሚመለሰው ባዶውን አይደለም፤ በእጁ የአትክልትና ፍራፍሬ መአት ተሸክሞ ነው እንጂ። ይህም ድርጊት ዓመቱን በሙሉ ዘላቂ ሆኖ ይቆያል። ምክንያቱም እርሻው ውሃ አያጣምና። በክረምት ጊዜ ዝናብ አለ፡፡ በበጋ ጊዜ ሀረላው ተራራውን እየሰረሰረ ውሃ ያወጣል፡፡ ስለዚህ እርሻው ለዘወትር በመስኖ ውሃ እንደረጠበ ነው የሚቆየው፡፡

    ታዲያ የሀረላ ነገድ በሚኖርበት ዘመን የኛን ዓይነት ሰዎችም (የኛ ቅድመ አያቶች) ይኖሩ ነበር፡፡ እነዚያ ቅድመ አያቶቻችን ከሀረላ ጋር በአንድ መሬት ላይ ቢኖሩም ከሀረላ ጋር ብዙም ቀረቤታ አልነበራቸውም። ሀረላዎች ዘራችንን ያበላሻሉ በማለት ከነርሱ ጋር አይቀራረቡም፤ አይጋቡምም፡፡ ሀረላዎች በቅድመ አያቶቻችን አጭር ሰውነት እየተገረሙ በሽምብራ ጥላ ስር የሚጋደሙ ድንክዬዎች ይሏቸው ነበር፡፡ የኛ ቅድመ አያቶች እንደጥላ የሚያርፉባቸው ዛፎች በቁመታቸው የሀረላ ገበሬ ከሚዘራው ሽንብራ ስለማይበልጡ ነው ሀረላዎቹ ቅድመ አያቶቻችንን እንዲያ ብለው የሚያናንቁት፡፡

   አንድ የኛ ቅድመ አያት ወደ ሀረላ እርሻ ተደብቆ በመግባት ስርቆት ከፈጸመ ብዙም የሚያጎድለው ነገር ስለሌለ ሀረላዎች እርሻቸው መሰረቁ አይታወቃቸውም፡፡ ሰውየው እሰርቃለሁ ቢል ከአንድ ቲማቲም በላይ መሸከም አይችልምና፡፡ ይህ ሰው በእርሻው ውስጥ ሳለ ሀረላ ድንገት ከያዘው ለቅጣቱ ብዙም አይጨነቅም፡፡ ከሽምብራው ዛፍ ላይ ትንሽ ቅርንጫፍ ይቆርጥና ሌባውን ቅድመ አያታችንን ሶስት ጊዜ ያህል ሾጥ ሾጥ ያደርገዋል፡፡ ሌባው ወዲያውኑ ከዚህች ዓለም ይሰናበታል፡፡
   
   ቅድመ አያቶቻችን የሟቹን ደም ለመበቀል በርከት ብለው ጦርነት ሲያውጁ ደግሞ ሰባት ሀረላ ብቻ ይመረጥና ይላክባቸዋል፡፡ እነዚያም ሰባት ሀረላዎች ለጦርነቱ ቀስትም ሆነ ደጋን አይታጠቁም፡፡ አምስት ያህል ድንጋይ ብቻ ይይዙና ለውጊያ ይሰለፋሉ፡፡ ቅድመ አያቶቻችን ውጊያውን ሲጀምሩ ሀረላዎቹ ለጥቂት ጊዜ ቆም ብለው ያዩዋቸዋል፡፡ ቅድመ አያቶቻችን በአንድ ቦታ በርከት ሲሉላቸው ሀረላዎቹ አንዳንድ ድንጋይ ይወረውሩባቸዋል፡፡ አንዱ የሀረላ ድንጋይም አንድ ሻምበል ጦር (100 ሰው) ይገድላል፤ (ምክንያቱም የሀረላው ድንጋይ በኛና በቅድመ አያቶቻችን ስሌት መሰረት  የተራራ ቋጥኝ ነውና)፡፡ ቀሪው ጦርም ይህንን ሲያይ በፍርሃት ይበተናል፡፡
*****     *****   *****
      ሀረላ በጣም ሀብታም ነው፡፡ እያንዳንዱ ሀረላ ለመቶ ዓመት የሚሆነውን ቀለብ ቀደም ብሎ አጠራቅሟል፡፡ በየዓመቱ የሚያገኘውን አዲስ ምርት ለፈንጠዚያና ለፌሽታ ነው የሚያውለው፡፡ ሁሉም ያሰኘውን ነገር ስለሚያገኝ ገበያ ሄዶ መሸጥና መግዛት የለም፡፡
 
      ታዲያ የሀረላ ፌሽታ የዋዛ እንዳይመስላችሁ! በተለይ ሰርግ ሲሰረግ ከሙሽራው ቤት አንስቶ እስከ ሙሽሪት ቤት ድረስ እንጀራ ይነጠፍና ሰርገኞች በዚያ ላይ እንዲሄዱ ይደረጋል። የሰርጉ ታዳሚዎች እጃቸውን የሚታጠቡትም በወተት ነው።  ማርና ቅቤው ሀያ አራት ሰዓት ይበላል፡፡ ጭፈራና ዳንኪራው ይቀልጣል፡፡ በአጠገባቸው የሚኖሩትን አጫጭር ሰዎች (የኛ ቅድመ አያቶች) ሲመጡ ወደ ድግሳቸው አያስጠጓቸውም፡፡ በረሀብ ቢሞቱ እንኳ ዞር ብለው አያዩዋቸውም፡፡ በተለይ በአንድ ወቅት ሀይለኛ ረሀብ በሀገሩ ገብቶ አጫጭሬዎቹ ለእርዳታ ቢማጸኗቸው ሀረላዎች የሜሪ አንቷኔትን ለምን ኬክ አይበሉም? ዓይነት መልስ ሰጧቸው፡፡ እንዲያውም ጥርግ ብትሉንና ያለ አንዳች ቀለዋጭ በደስታ በኖርን! አሏቸው፡፡
 
   ቅድመ-አያቶቻችን በሀረላ ጭካኔ አዘኑ፡፡ እምባ ለእምባ ተራጩ! ወደ ፈጣሪ ጮሁ፡፡ ፍርድህን በቶሎ አሳየን! አሉት፡፡ ፈጣሪም ጸሎታቸውን ሰማቸው፡፡ ፍርዱንም እንደሚከተለው በየነ፡፡
   
       ሁሉም ሀረላዎች ለትልቅ ጉባኤ በመተሀራ ተሰበቡ፡፡ ጉባኤውንም አደረጉ፡፡ ከጉባኤው በኋላም እንደለመዱት ፌሽታቸውን ጀመሩ፡፡ በዚህን ጊዜም ከየት መጣህ የማይሉት እሳተ ጎመራ ፈነዳ፡፡ ምድር ተቀወጠች፡፡ ሀረላዎች ነደዱ፡፡ ለወሬ ነጋሪ እንኳ አንድ ሰው ሳይተርፍላቸው ሁሉም አለቁ፡፡
 
   በሀረላ ከርሰ መቃብርም ላይ የአሁኑ የመተሀራ (በሰቃ) ሀይቅ ፈለቀ፡፡ አንድ ጥቅም የሌለው መርዝ የሆነ ውሃ! ጥም የማይቆርጥ ለእርሻ የማይሆን ግም ውሃ!! ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ ግን? ሀረላዎች ያኔ ሲፈነጥዙ የሸኑት ሽንት እኮ ነው!! ግም አሲዳም ውሃ! ሽንተ ርጉማን ዘኮነ ዘብሄረ ሀረላ!! ወዘተ...ጂንኒ ጀቡቲ.......
  
------
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 30/2005

No comments:

Post a Comment