Saturday, August 24, 2013

የኒያላ እና የግሥላ ካርቶን ንግድ (1983)


ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----------
ወቅቱ የደርግ መንግሥት ፍጻሜ ዋዜማ ነው፡፡ ዕለተ ማክሰኞ፡፡ ገለምሶ እንደ ሁል ጊዜዋ የማክሰኞ ገበያተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ነበረች፡፡ እኔም “አው ሰኢድ” ከሚባለው ሰፈር ካለው የአባቴ መኖሪያ (ድሮ የታወቀ ሱቅ ነበር) ወርጄ ወደ መኖሪያ ቤታችን እየተመለስኩ ነው፡፡ ታዲያ “ኒብራ” ከሚባለው የከተማችን አውራ ጎዳና ላይ ያልጠበቅኩት ነገር ገጠመኝ፡፡
 
  “ናሲሮ ሰኢዶ” የሚባለው አብሮ አደግ ጓደኛዬ በየሱቁ እየገባ “የኒያላ ወይም የግሥላ ካርቶን አላችሁ?” እያለ ይጠይቃል፡፡ በእጁ ከሶስት ያላነሱ ካርቶኖችን ይዞ ሌላ ካርቶን መጠየቁ ትንሽ ገረሜታን ፈጠረብኝ፡፡ ምክንያቱም ካርቶን ከአዲስ አበባና ከድሬ ዳዋ የሚመጡ ዕቃዎች ታሽገውበት ወደኛ ከተማ (ገለምሶ) ከመጣ በኋላ አገልግሎቱን እንዳበቃ ነው የሚቆጠረው፡፡ ወደ ሌላ አካባቢ የሚሄድ ጭነት (ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቡና፣ እህል ወዘተ…) የሚታሸገው በጆንያ እንጂ በካርቶን አልነበረም፡፡ ባዶውን ካርቶን የሚፈልጉት “ኩሊ” የሚባሉት የቀን ሰራተኞች አሊያም የቤታቸውን ግማሽ ከፍለው የጥናት ክፍል ሊሰሩበት የሚፈልጉ ተማሪዎች (በተለይ ወደ ሀይስኩል የገቡ)፤ ወይም በካርቶኖ ጊዜያዊ ኮርኒስ ለመስራት የሚፈልጉ አንዳንድ አባወራዎች ናቸው፡፡ “ናሲሮ” ግን ከሶስቱም አልነበረም (ልጁ በወቅቱ ቆንጆ የሆነ የጥናት ቤት ነበረው)፡፡ በዚያ ላይ በእጁ የተመነዘረ ረብጣ ብር ይዟል፡፡ እናም ነገሩን ከርሱ ጠይቄ መረዳት አማረኝና “ለምንድነው ካርቶን የምትገዛው?” አልኩት፡፡
“በጣም ይፈለጋል፤ ወደ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ተወስዶ ይሸጣል”
“ባዶ ካርቶን?”
“አዎን”
“በስንት ነው የምትገዛው?”
“የአንዱ ዋጋ አምስት ብር ነው”
“አምስት ብር ሙሉ?”
“አዎን”
“ሁሉም ዓይነት ካርቶን ይሆናል?”
“አይሆንም፤ የኒያላና የግሥላ ሲጋራዎች ብቻ ነው የሚፈለገው”

ናሲሮ በስራው እንዳግዘው ጠየቀኝ፡፡ “ስንት ትሰጠኛለህ?” አልኩት፡፡ አራት ብር ሊሰጠኝ ቃል ገባልኝ፡፡ እኔም ግብዣውን በደስታ ተቀበልኩት (አራት ብር ዶሮ ከተገዛለት በኋላ እንኳ አንድ ብር ያህል የሚተርፍለት ገንዘብ መሆኑን እያስታወሳችሁ)፡፡
ከናሲሮ ጋር በ“ኒብራ” ጎዳና አንድ ክንፍ ላይ ያሉትን ሱቆች አዳረስን፡፡ አሁን በትክክል የማላስታውሰውን ያህል የኒያላና የግሥላ ካርቶኖችንም ገዛን፡፡ ወደ አስር ሰዓት ገደማም “ፎቶ ማወርዲ” ከሚባለው ፎቶ ቤት አጠገብ ወደሚገኝ መጋዘን ወሰድናቸው፡፡ ከዚያም አራት ብሬን ይዤ ወደ ማክሰኞ ገደማ ላፍ አልኩ፡፡ ዘይቱናና ሸንኮራ እየበላሁ ከናስሮ ጋር የሰራሁትን ገድል ለጓደኞቼ እየቀደድኩላቸው ከቆየሁ በኋላ መሸ፡፡
  *****  *****  *****
በማግስቱ ትምህርት ቤት ሄጄ ስመለስ ከተማው “የኒያላ ካርቶን ያላችሁ….የግሥላ ካርቶን ሽልጡልን” በሚሉ ደላላዎች ተወረሮ አገኘሁት፡፡ “ምን መጣ?” አልኩኝ ለራሴ፡፡ “የሲጋራ ካርቶን ምን ይሰራበታል? ይህንን ያህል ይፈለጋል ማለት ነው?” እያልኩ አሰላሰልኩ፡፡ ነገሩ ይበልጥ የገረመኝ የመግዣ ዋጋው አስር ብር መግባቱን ስሰማ ነው፡፡
“ናሲሮ አታለለኝ ማለት ነው? ለምንድነው የደበቀኝ? እኔ አራት ብሬን ብቻ ከሰጠኝ ከዋጋው ጉዳይ የለኝ! ዋጋውን ለሌላ ሰው እንዳልናገርበት ጠርጥሮኛል ልበል?” እያልኩ በጓደኛዬ አድራጎት ስለፈላሰፍ አንዱ ደላላ ዋጋው በአንድ ቀን ከእጥፍ እንደጨመረ አስረዳኝ፡፡
“እንዴ! ባዶ ካርቶን?”
“አዎን”
“ምን ይሰራበታል ግን?”
“እኔ እንጃ! በጣም ይፈለጋል”

ነገሩ ሀገሬውን በሙሉ ነበር ያስደመመው፡፡ ታዲያ የዕሮብለቱ ሲገርመኝ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዋጋው በእጥፍ ጨመረ፡፡ ባዶ ካርቶን በሀያ ብር! ምክንያቱ ግን ለማንም ግልጽ አልነበረም፡፡

በዚህን ጊዜ ነው ከተሜው በሙሉ ካርቶንን ከያለበት ማሰስ የጀመረው፡፡ “ኩሊዎች” ለንጣፍ የሚጠቀሙበትን አሮጌ ካርቶን ለገበያ አወጡ፡፡ ተማሪዎች ከፍራሽ ስር የሚያነጥፉትን የእርጥበትና የአዋራ መከላከያ ካርቶን እያወጡ የሳምንት በርጫ መግዣ አደረጉት፡፡ ወሬው በየሰፈሩ ተዛመተ፡፡ የጎረምሳና የጎልማሳው የመወያያ ርዕስ “የኒያላ ካርቶን” እና “የግሥላ ካርቶን” ሆነ፡፡

ከጥቂት ቀናት በኋላ የካርቶን መግዣ ዋጋው ሀምሳ ብር ደረሰ፡፡ ካርቶንን እንደ ኮርኒስ የሚጠቀመው ቤተሰብ “ኮርኒስ በአፍንጫዬ ይውጣ” እያለ የቤቱን የጣሪያውን መከለያ ፈነቃቀለው፡፡ ዋጋው ወደ ስድሳና ሰባ ብር ሲያሻቅብ የካርቶን ግድግዳዎች ተደረመሱ፡፡ መቶ ብር ሲገባማ በርካታ ነጋዴዎች ቋሚ የካርቶን ገዥዎችና ጫኞች ሆኑ፡፡ ደላሎች እስከ ገጠር እየዘለቁ በየቤቱ የተደበቁትን የኒያላና የግሥላ ካርቶኖች እየገዙ በከፍተኛ ዋጋ ለነጋዴዎች ያቀርቡ ጀመር፡፡

ዋጋው እስከ መቶ ሀያ ብር ደረሰ… ገበያው ጦፈ፡፡ ምድርና ሰው ሁሉ “ካርቶን….ካርቶን” እያለ ቃላት የመላለስ ገባ ይመላለስ ገባ፡፡ የእናቶቸ የቡና ወሬ ካርቶን ሆነ፡፡ ወሬው ከከተማዋ አልፎ በየገጠሩ ተዛመተ፡፡ ጥቂት ነጋዴዎች በካርቶን ንግድ እስከ መቶ ሺህ ብር የሚደርስ ትርፍ እንደዛቁበት ይወራ ጀመር፡፡
  *****  *****  *****
ይህ ኩነት ከሁለት ወራት በላይ የቆየ አይመስለኝም (ምናልባት ሶስት ወር ያህል ቆይቶ ይሆናል)፡፡ ከሚያዚያ ወር መግቢያ በኋላ የከተማችን ነዋሪዎች የመወያያ አጀንዳ ተቀይሮ ከሰሜን ወደ መሀል ሀገር እየገፋ በመጣው የጦርነት ዜና ላይ ሆነ፡፡ የካርቶን ገበያ ሙሉ በሙሉ ባይደርቅም እጅግ በጣም እየቀዘዘ ሄደ፡፡ በሚያዚያ ማብቂያ ገደማ ከነአካቴው ጠፋ፡፡ ከዚያ ወዲህ ስለርሱ ያነሳ ሰው የለም፡፡

 “ስንቶች በዚህ ንግድ ከበሩ? ስንቶች በኪሳራ ተሸመደመዱ?” የሚለው እስከ አሁን ድረስ በትክክል የማይታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ መልስ ያልተገኘለት ጥያቄ ግን “የኒያላ እና የግሥላ ካርቶኖች እስከ መቶ ሀያ ብር በሚደርስ ሂሣብ የተቸበቸቡበት ምክንያት ምንድነው?” የሚለው ነው፡፡
 
   ለዚህ ጥያቄ የሚሆን ትክክለኛ ምላሽ እስከ አሁን አላገኘሁም፡፡ የተወሰኑ ሰዎች “በወቅቱ በምስራቅ ኢትዮጵያ በኮንትሮባንድ የሚገቡትን ሲጋራዎች በግሥላና በኒያላ ካርቶኖች እየደበቁ ወደ አዲስ አበባ ለማስተላለፍ ጥረት በሚደረግበት ጊዜ የካርቶኖቹ ፍላጎት ጨመረ፡፡ በድሬዳዋ አካባቢ ካሉት ገበያዎች የተገዙት የኮንትሮባንዲስቶቹን ፍላጎት ማሟላት አልቻሉም፡፡ ስለዚህም ነው ገበያው እስከ ገለምሶና መቻራ ድረስ የዘለቀው” ብለውኛል፡፡ እንዲያ ከሆነ በውጪ የተመረቱ ሲጃራዎችን እንደ ሀገር ውስጥ ሲጋራ በማድረግ  የፋይናንስ ፖሊሶች አይን እንዳያርፋበቸው ለማድረግ ተችሎ ነበር ማለት ነው፡፡ ግን ሲጃራው በብዛት ወደ አዲስ አበባ ሲጎርፍ የፋይናንስ ፖሊሶቹ በቀላሉ ይነቁ አልነበረም እንዴ? ወይስ ፋይናንሶችን በሙስና በመሸበብ ነበር የሚታለፈው?
 አንድ ሰው ግን “የሀገር ውስጥ ሲጋራዎች በድብቅ ኤክስፖርት ይደረጉ ነበር፤ ለዚህም ነው የካርቶን ንግድ የተጀመረው” ብሎኛል፡፡ ይህኛውን አባባል በምክንያትነት መቀበል የሚቻል ይመስላል፤ ምክንያቱም በዘመኑ አንዳንድ የመንግሥት ባለስልጣናት ከነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር እንደዚህ አይነቱን ንግድ ያካሄዱ እንደነበረ በስፋት ሲነገር ኖሯልና፡፡ ነገር ግን በዚህ አንጻር ሲኬድም “የሲጋራ ፋብሪካው ሲጋራ የሚያመርተው ያለ ካርቶን ነው እንዴ?” ከሚል ሙግት መፋጠጥ ግድ ይላል፡፡

    በበኩሌ እርግጠኛውን ነገር አልደረስኩበትም-ከላይ እንደጠቀስኩት፡፡ ወደፊት የምደርስበትን ጀባ እንደምላችሁ ቃል ልግባላችሁና የኔን ፈንታ በዚሁ ላብቃ፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ነገሩን የምታውቁ ጓዶቻችን ያላችሁን መረጃ እንድታካፍሉን በአክብሮት እንጠይቃችኋለን፡፡ ሰላም!
  አፈንዲ ሙተቂ

No comments:

Post a Comment