ጸሓፊ፡ ረሺድ ቢላል
--------------------------------------
በሰባተኛው
ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በዐረባይቱ የመካ ከተማ ይኖር የነበረውን “አል-አሚን”ን ብዙዎች ይወዱታል። ይህ ሰው አደራን
ጠበቅ አድርጎ ስለሚይዝና የሰዎችን ገንዘብ የሚያምታታ ባለመሆኑ ነበር “አል-አሚን” የተሰኘውን ቅጽል ያገኘው። “አል-አሚን” ከጥንት
ጀምሮ ሐኒፍ ነበር። ራዕይ (ወሕይ) ባይገለጽለትም ዓለምንና
ፍጥረቱን ሁሉ የሰራ አንድ ሀያል አምላክ እንዳለ በልቦናው ያውቀዋል። በመሆኑም እንደ ዘመኑ ህዝቦች ለጣኦታት በጭራሽ ሰግዶ አያውቅም። የሞተ እንስሳ ስጋ አይበላም። ፍትህ አዋቂነቱ በጣም ያስመካል። አራጣ በማበደር ሰዎችን አያማርርም። በሐሰት አይምልም። የዕድሌን ዳራ በጥንቆላና በመተት
ልፈልግ አይልም።
አል-አሚን በዚህ መልካም ባህሪው ከልጅነት እስከ
እውቀት ዘልቋል። በተፈጥሮው ብሩህ የሆነ አዕምሮ ነበረው። ይሁንና ማንበብና መጻፍ በጭራሽ አያውቅም።
ታሪካዊው የሂራ ዋሻ |
ታዲያ አል-አሚን ዘወትር በረመዳን ወር ከሰው
ተገልሎ እውነትን የመተንተንና የማስተንተን ልማድ ነበረው። ለዚህም የመረጠው ሂራ የሚባለውንና ከመካ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የነበረውን
ዋሻ ነው። አል-አሚን አርባ ዓመት እስኪሞላው ድረስ በዚህ ባህሪው ተጓዘ። በአርባኛው ዓመቱ በወርሃ ረመዳን እንደ ልማዱ ስንቁን
ሰንቆ ወደ ሂራ ዋሻ በመግባት ነገረ-ፈጣሪንና ነገረ ዓለምን በመተንተን (ተፈኩር በማድረግ) ላይ ሳለ ግን ያልጠበቀው አስገራሚ
ፍጡር ከፊቱ ተደቀነ።
***** ***** *****
ያ አስገራሚ ፍጡር እንደ ወተት የነጣ ልብስ ለብሷል። ውበቱ ለጉድ ነው።
ግርማ ሞገሱ በጣም ያስፈራል። በዚያ ላይ ሰውነቱ ብርሃን በብርሃን ሆኗል። ፍጥረቱ በትክለ ሰውነቱ ከሰው ልጅ ጋር ይመሳሰላል።
ግዝፈቱ ግን ሌላ ነው። በዚያ ላይ ትልልቅ ክንፎች አሉት። አል አሚን ባየው ፍጥረት ቢረበሽም በድንጋጤ አቅሉን አልሳተም።
ግዙፉ ፍጡር ወደ አል-አሚን ተጠጋና ከሐር በተሰራ
ወረቀት መሳይ ቅጠል ላይ የተጻፈ ጽሑፍ እያቀረበለት “አንብብ” አለው። አል-አሚን ግን “እኔ ማንበብ አልችልም” አለው። እንግዳው
ፍጡርም አል-አሚንን በመዳፎቹ ውስጥ አስገብቶ ላብ በላብ እስኪሆን ድረስ ወደ መሬት ተጫነው። ከዚያም በድጋሚ ጽሑፉን እያቀረበለት
“አንብብ” አለው። አል-አሚንም እንደ በፊቱ “እኔ ማንበብ አልችልም” የሚል መልስ ሰጠው። ግዙፉ ፍጡር አል-አሚንን በድጋሚ አፈፍ
አድርጎት ወደ መሬት ተጫነው (የሀጂ ሙሐመድ ሣኒ ሀቢብን ቋንቋ ልዋስና “ሰውነቱን ጭቁን” አደረገው)።
እንግዳው ፍጡር ለሶስተኛ ጊዜ ጽሑፉን እያሳየው
“አንብብ” አለው። በዚህ ጊዜ አል-አሚን “እኔ ማንበብ አልችልም፤ ቢሆንም የትኛውን ነው የማነበው?” የሚል ጥያቄ አዘል ምላሽ
ሰጠ። እንግዳውም ጽሑፉን ወደ ራሱ አስጠግቶ የሚከተሉትን አናቅጽ አነበበለት።
“አንብብ፣ በዚያ (ዓለምን) በፈጠረው ጌታህ ስም።
ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው።
አንብብ ጌታህ በጣም ቸር ነውና።
ያ በብዕር (መጻፍን) ባስተማረው።
የሰውን ልጅ የማያውቀውን ሁሉ ያሳወቀው።”
(አል-ዐለቅ፣ 1-5)
(አል-ዐለቅ፣ 1-5)
አል-አሚን የተነበበለትን በብሩህ አዕምሮው ከቀረጸ
በኋላ አንድም ፊደልና ቃል ሳያጓድል ለእንግዳው ፍጡር አነበበለት። በዚህን ጊዜም ግዙፉ ፍጡር “ከአንድ አላህ በስተቀር ሌላ አምላክ
የለም፤ አንተን ባሪያውና መልዕክተኛው እንድትሆን መርጦሃል፣ እኔም የፈጣሪዬን መልዕክት ወደ ደጋግ ባሮቹ የማደርሰው ጂብሪል ነኝ”
አለው። ከዚያች ቅጽበት በኋላም ከቦታው ተሰወረ።
አል-አሚን በድንጋጤ ወባ እንደያዘው ሰው ተንቀጠቀጠ። ከዚያም ከዋሻው ወጣና
ለአፍታ እንኳ ወደ ኋላው ሳይገላመጥ በከፍተኛ ፍጥነት እየገሰገሰ ከቤቱ ደረሰ። ከቤቱ ውስጥ የነበረችው ባለቤቱ የአል-አሚንን ሁኔታ
ስታይ አንጀቷ ተላወሰ። ወደ ባለቤቷ ተጠግታ “የቃሲም አባት ሆይ! ምን አጋጥሞህ ነው?” በማለት ጠየቀችው (ቃሲም የመጀመሪያ ወንድ
ልጃቸው ነው)። እርሱ ግን ለጥያቄው መልስ ሳይሰጣት “እባክሽን መተኛት እፈልጋለሁ፤ ልብሶችን ደራርቢልኝ” አላት። ሚስቱ “ምን
ሆንክ ውዴ!” እያለች ልታወጣጣው ብትሞክርም ምንም አልተነፈሰም። በመሆኑም ባለቤቱ በጥያቄዋ መግፋቱን ተወችውና በተጠየቀችው መሰረት
ልብሶችን ደራረበችለት። የአል-አሚንን ሁኔታ ለማወቅ ብትጓጓም ከመኝታው እስኪነቃ ድረስ መጠበቁን መረጠች።
ታዲያ አል-አሚን ገና ከመጋደሙ በዋሻው የተገናኘው ግዙፍ ፍጡር መልኩን በሰው
አስመስሎ መጣበትና “አንተ ተከናናቢው ሆይ! ከሌሊቱ የሚበዛውን ክፍል በስግደት አሳልፍ። ወይም ግማሹን፣ አሊያም ከዚህ ላላነሰ
ጊዜም ቢሆን ለአምላክህ በመስገድ አሳልፍ፤” የሚሉ ውብ ቃላትን አነበበለት (አል-ሙዘሚል 1-3)። እነዚያም ቃላት በአል-አሚን
ልቦና ላይ ታትመው ቀሩ።
አል-አሚን
ለተወሰነ ጊዜ ከተኛ በኋላ ሚስቱን “አሁን ቀለል ብሎኛልና የሆንኩትን ሁሉ ልነግርሽ እችላለሁ” አላት። ከዚያም ያጋጠመውን ሁሉ
አንድ በአንድ ተረከላት። ባለቤቱም “አይዞህ! አንተ ደግነት እንጂ ክፋት የለብህም። ዘመዶችህን ካሉበት ሄደህ ትጠይቃቸዋለህ። ለተቸገረ
ሰው ፈጥነህ ትደርሳለህ። የሌሎችን ገንዘብ አትመዘብርም። አደራ የተባልከውን ነገር ከልብህ ትጠብቃለህ። ውሸት ታይቶብህ አይታወቅም።
ጌታችን በአንተ ላይ ደጉን እንጂ ክፉውን እንደማያመጣብህ እርግጠኛ ነኝ” እያለች አበረታታችው። “ለማንኛውም ግን” አለች የአል-አሚን
ባለቤት በማስከተል “ለማንኛውም ወረቃ ኢብን ነውፈል የሚባለው የአጎቴ ልጅ ተውራትና ኢንጂል የሚባሉትን ቀደምት መጻሕፍት በደንብ
ያጠና በመሆኑ ወደርሱ እንሂድና የተፈጠረውን ሁሉ እንንገረው” አለችው። አል-አሚንም በባለቤቱ ሃሳብ ተስማማ።
ሁለቱ ሰዎች ወደ “ወረቃ” ዘንድ ሄዱና የሆነውን ሁሉ ነገሩት። ወረቃም
ነገሩን ካዳመጠ በኋላ “ይህማ ነቢዩ ሙሳን የገጠመው ቢጤ ነው። በዋሻው የተገናኘህ አስገራሚ ፍጡር መልዐኩ ጂብሪል ነው። እነሆ
ሲጠበቅ የነበረው የመጨረሻው ነቢይ ወደ ዓለም የሚላክበት ቀን ደረሰ። ዋ! ዕድሜ ሰጥቶኝ ወገኖችህ ከዚህ ከተማ በሚያባርሩህ ጊዜ
ያንተ ረዳትና ጋሻ መከታ በሆንኩ!” አለ። አል-አሚን ወረቃ የተናገረውን በደንብ ከሰማ በኋላ “በእርግጥ ወገኖቼ ከዚህ ከተማ ያባርሩኛል?”
በማለት ጠየቀ። ወረቃም “በትክክል!” የሚል ማረጋገጫ ከሰጠው በኋላ “ነቢይ ሆኖ ችግርና መከራ ያልደረሰበት የለም። ችግሩን ሁሉ
ችለህ ካሳለፍክና መከራውን መቋቋም ከቻልክ አሸናፊነቱ ያንተ መሆኑ አይቀርም” የሚል ምክር አዘል መልዕክት ጣለለት። ሆኖም ወረቃ
በጣም አርጅቶ ነበርና የአል-አሚንን የታሪክ ጉዞ ለማየት ሳይታደል ቀረ። ይህንን ከተናገረ ከጥቂት ወራት በኋላም አረፈ። አል-አሚን
ግን ታሪካዊውን ግዳጅ ለመፈጸም ተነሳ።
እነሆ በወረቃ
ኢብን ነውፈል አንደበት እንደተመሰከረው አል-አሚንና ያ እንግዳ ፍጡር በሂራ ዋሻ ያደረጓት አጭር የቃላት ምልልስ
(dialogue) እና በጋራ የከወኑት አቻ-የለሽ ኪናዊ ገቢር የሰው ልጆች ወደ ሐቅ እንዲመጡና ከዘላለም ቅጣት ይድኑ ዘንድ ታላቁ
አዋጅ የታወጀባት ታላቅ ቅጽበት ሆና በዓለም ታሪክ ተመዘገበች። እጅግ አስገራሚ የሆነው የአል-አሚን የ23 ዓመታት የህይወት ጉዞም
በዚያች ቅጽበት “አሐዱ” ተብሎ ተጀመረ።
***** ***** *****
አል-አሚን ከዚህ ስም በተጨማሪ “አስ-ሷዲቅ” የሚል ቅጽልም ነበረው።
“እውነተኛው” ወይንም “ዋሽቶ የማያውቀው” እንደ ማለት ነው። በእርግጥም ይህ ሰው በቀልድ እንኳ ዋሽቶ አያውቅም። ድሮ በነበረው
መልካም ጸባይ ላይ ነቢይነትን ሲደርብ ራሱን ብቻ ሳይሆን የዓለም ታሪክን ለመቀየር በቅቷል። Michael Hart የሚባለው አሜሪካዊ
በሚሊዮን ኮፒዎች በተሸጠለት “100 Influential
Persons in History” በተሰኘው መጽሐፉ በዓለም ታሪክ ላይ ከባድ ተጽእኖ መፍጠር የቻሉ 100 ሰዎችን የህይወት ተመክሮ
ሲተርክ አል-አሚንን በአንደኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጠዋል። በእርግጥም ህላዌአቸውን በብዙ ሺህ ክፍለ ዘመናት ከሚቆጥሩት ቀደምት ህዝቦች
መካከል በሚመደቡትና ነገር ግን እስከ 7ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የረባ ቁምነገር ማስመዝገብ ባልቻሉት ኋላቀር የዐረቢያ ጎሳዎች መካከል
ተወልዶ ቢሊዮኖችን በደቀ መዛሙርትነት ማሰለፍ እንዲህ በቀላሉ የሚነገር ተአምር አይደለም። የርሱ አስተምህሮ ዘመን አይሽሬ በመሆኑ
ዛሬም ድረስ እየተተገበረ ነው። ዛሬም ድረስ እየተሰበከ ነው። በነገው እለትም ይቀጥላል።
ይህ ሰው “ኢቅረእ” የሚለውን አዋጅ ማሰማት ሲጀምር
ከማንም ቀድማ አዋጁን በይሁንታ የተቀበለችው ከላይ የተጠቀሰችውና በተጸውኦ ስሟ “ኸዲጃህ ቢንት ኹወይሊድ” የምትባለው ውድ ባለቤቱ
ነበረች (ረ.ዐ.)። ዛሬ ግን ከዓለም ህዝብ ሩብ ያህሉ እርሱ በለኮሰው መንፈሳዊ ጎዳና ላይ እየተጓዘ ነው። የርሱ ተከታይ ካልሆኑትም
የሚበዙቱ በክፉም ሆነ በደጉ ስሙን ያነሱታል።
አል-አሚን የነቢይነቱንና የመልዕከተኝነቱን ካባ ከደራረበ በኋላ የርሱን
ምትክ የለሽነት የሚገልጹ በርካታ ቅጽሎችን ተጎናጽፏል። “ሲራጅ” (ጸሐዩ ወይንም እንደ ጸሐይ የሚያበራው” ማለት ነው) “ሙኒር”
(“አብሪው” ወይም “ብርሃኑ” ለማለት ነው) “አል-ሙኽታር (“ምርጡ” ወይም “የተመረጠው” እንደማለት ነው) “አል-ሙስጠፋ”
(“ተመራጩ” ማለት ነው) ወዘተ… እያልን መዘርዘር እንችላለን። እንደርሱ “ሐኒፍ” (ለአንዱ አምላክ እንጂ ለጣኦታት የማይሰግድ)
የነበረው ዐብዱል ሙጠሊብ የሚባለው አያቱ ያወጣለት ስም ግን “ሙሐመድ ነው” (ሰ.ዐ.ወ) ነው። ይሁንና እኛ በዚህ የተጸውኦ ስሙ
ከምንጠራው “ነቢዩ” ወይንም የአላህ መልዕክተኛ” ማለቱን እንመርጣለን (ሰ.ዐ.ወ)።
***** ***** *****
አዎን! ረመዳን የመዳኛ ወር ነው። የሀጢአት ጭቅቅታችንን በተውባ (ንስሓ)
እና በኢስቲግፋር (ማርታ) ለማጠብ የምንተጋበት የዓመቱ ታላቅ ድግሳችን ነው። ስግብግብነትና ግለኝነት የሚፈታተኑትን ደካማ ስሜታችንን
የምናገራበት የተግባር ትምህርት ቤታችን ነው። ከዚህ ባሻገር ረመዳንን የምንዘክረው ግን የመጨረሻው ነቢይ (ሰ.ዐ.ወ) ለዓለም ህዝብ
የተላኩበት ታላቅ ወር በመሆኑ ነው። ይህ ብስራት የተነገረውም ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከጂብሪል ጋር በሂራ ዋሻ በተገናኙባትና “ኢቅራእ”
የሚለው የፈጣሪያችን አዋጅ በተነበበባት በዚያች ውብ ተአምረኛ ቅጽበት ነው። ያች አዋጅም ረመዳንን “የቁርኣን ወር” አሰኝታዋለች።
በእርግጥም ጌታችን “እንድትጾሙ የተደገነነው ቅዱስ ቁርኣን በወረደበት የረመዳን ወር ነው” በማለት ወርሃ-ረመዳንን ባርኮታል (አል-በቀራህ፣
185)።
እንኳን
አላህ የነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ተከታዮች አደረገን። እንኳንም አል-ሙስጠፋን (ሰ.ዐ.ወ) አስነሳልን። እንኳን ለወርሃ ረመዷን አደረሰን።
ረሺድ ቢላል
ረመዷን 3/1431
--------------------------------------
ማስታወሻ፡
1.
አንዳንድ ምንጮች “ጂብሪል አላህ የመጨረሻ መልዕክተኛ እንድትሆን መርጦሃል” የሚለውን ቃል ያሰማው ነቢዩ ከዋሻው ወጥተው
በሩጫ ወደ ቤት በመመለስ ላይ እያሉ ነው” የሚል ዘገባ አሰምተዋል። እኔ እዚህ ያቀረብኩት ትረካ ግን በኢብኑ ሒሻም የተዘገበውን
ነው። ሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብም የነቢዩን ታሪክ በአማርኛ በጻፉበት ወቅት ይህንኑ ትረካ መዝግበውታል።
በሁለቱም አቀራረብ የረመዳንን ልቅና ያገዘፈውን ገቢር ማስመሰከር ይቻላል።
ሁለቱም “ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) የመጨረሻው መልዕክተኛ መሆናቸው በረመዳን ወር ታወጀ” ከሚለው አባባል ጋር ይጣጣማሉ።
2.
“ነቢዩ በሂራ ዋሻ ሳሉ ጂብሪል በሰው መልክ ተመስሎ መጣባቸው” የሚሉ ምሁራን አሉ። ነገር ግን ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጂብሪልን
ሁለት ጊዜ በትክክለኛ ቁመናው እንዳዩት በቁርአንም ሆነ በሐዲስ ተረጋግጧል። እነርሱም የመጀመሪያውን ወህይ (ራዕይ) ያዩባት ምሽት
እና ወደ ሰማይ ያረጉባት ሌሊት ናቸው (“ሱረቱን-ነጅም” የሚባለው የቁርኣን ምዕራፍ የመጀመሪያ አንቀጾች ስለሁለቱ ኩነቶች ነው
የሚተርኩት)።
3.
ነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) “እርሱ” እያልኩ የጠራሁት ወጋችን እንዲጣፍጥልን በማለት ነው (እናንተ ደስ ካላችሁ “አንቱ” እያላችሁ
አንብቡት”)።
*****
***** *****
የትረካ ምንጮች
- አል-ቁርአኑል ከሪም፡ (ቅዱስ ቁርኣን በዐረብኛ)
- ቅዱስ ቁርአን፡ የአማርኛ ትርጉም በሰይድ መሀመድ ሳዲቅና በሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ፣ አዲስ አበባ፣ 1963
- Holy Qur'an፡ English Translation By Abdullah Yusuf Ali, London, 1945
- ሰሒሕ አል-ቡኻሪ፣ ቅጽ 1፣ አንደኛ መጽሐፍ፣ ሐዲስ ቁጥር 3
- ዐብዱል መሊክ ኢብኑ ሒሻም፣ “ሲረቱ ረሱሉላህ” (የአላህ መልዕክተኛ የህይወት ታሪክ)፣
- ሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ፡ እስልምና እና የታላቁ ነቢይ የሙሐመድ ታሪክ፣ አዲስ አበባ፣ 1988
No comments:
Post a Comment