Pages

Wednesday, March 20, 2013

የገለምሶው “አቦ ደርጂ” ጨዋታዎች (ክፍል ሁለት)


ጸሓፊ- አፈንዲ ሙተቂ 

አቦ ደርጂ ዘወትር የሚታወሱበት አንዱ ባህሪ ድፍረታቸው ነው። አንደበታቸው እንደ ብዙዎቻችን በይሉኝታ ገመድ የተሸበበ ስላልሆነ ያልጣማቸውን ነገር ፊት ለፊት ከመቃወም ወደኋላ አይሉም። ታዲያ እምቢ ባይነታቸው በደረቅ ቃላት የተደረተ አይደለም። እውነትን በሰፊው ይገልጻል። አንዳንዴ ደግሞ በአዝናኝነቱ የሁል ጊዜ ተጠቃሽ ሆኖ ይኖራል። ለዚህም ሁለት አብነቶችን ልስጣችሁ።

ኢሕአዴግ ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ነው። ስለ አዲሱ ስርዓት አካሄድና ስለዜጎች መብት በሚል በየቀበሌው ህዝባዊ ስብሰባ ይካሄድ ነበር። አቦ ደርጂ በታደሙበት አንድ ስብሰባ ደግሞ የመድረኩ መሪ አደም አብደላ (በቅጽል ስሙ “ጉመ ከፈል”) የሚባል የምዕራብ ሀረርጌ ዞን አስተዳዳሪ ነው። ታዲያ “ጉመ ከፈል” ስብሰባውን እየመራ ሳለ በአዳራሹ የመጀመሪያ ረድፍ ላይ ወደ ተቀመጡት አቦ ደርጂ እያየ እንዲህ አላቸው።
“አባቴ፣ እርስዎ ትልቅ ሰው ነዎት፤ ቢያንስ ሶስት መንግስታትን አይተዋል። እስቲ የኃይለ ስላሴን፣ የደርግንና የአሁኑን መንግስት በማነጻጸር ሀሳብዎትን ይስጡኝ።”
አቦ ደርጂም “የእውነት መልስ ነው የምትፈልገው ወይስ ውሸት እንድናገር ነው የምትፈልገው?”
ጉመ-ከፈልም “እውነት ነው እንጂ ውሸት ምን ይሰራልኛል?” አላቸው።
አባ ደርጂም “ጥሩ! ኃይለስላሴ በድንቁርና ፈጀን። ከባላባት ልጆች በስተቀር የኛ ልጆች መማር አይችሉም ነበር። ደርግ ደግሞ “ቀይ ሽብር” እና አብዮታዊ ዘመቻ እያለ ልጆቻችንን ጨረሰብን። ስለአሁኑ መንግስት ግን ከወረደ በኋላ ብትጠይቀኝ ይሻላል” በማለት የዞኑን አስተዳዳሪና በአዳራሹ የነበረውን ህዝብ በሳቅ አፈረሱ።
******************
ዝናብ በጠፋበት በአንድ ወቅት ደግሞ ህዝቡ በመስጊድ ውስጥ ከሰላት (ስግደት) በኋላ ፈጣሪውን ይለማምናል። የመስጊዱ ኢማምም ከተቀመጡበት ተነስተው ህዝቡ ቀንም ሆነ ማታ ፈጣሪውን መማጸኑን እንዳይተው አሳሰቡ። በመስጊዱ የነበረውም መላው ህዝብ ይሁንታውን ገለጸ። አቦ ደርጂ ግን “የምን ዝናብ ነው የምታወሩት? አይሆንም! እስቲ ይዝነብ!” በማለት ተቃውሞአቸውን አሰሙ። በዚህም የተነሳ በመስጊዱ የነበረው ህዝብ ተደናገጠ። ኢማሙ ግን “ቆዩ! ረጋ በሉ!” ካለ በኋላ አቦ ደርጂ እንደዚያ ያሉበትን ምክንያት እንዲያስረዱ ጠየቃቸው። እርሳቸውም “አምና የነፈሰው ሀይለኛ ነፋስ የቤቴን ጣሪያ ነቃቅሎት እንዳልነበረ አድርጎታል። ዘንድሮ ዝናቡ ከደገመኝ ደግሞ እኔና ልጆቼ የምንደርስበት ቦታ አጣን ማለት ነው። ስለዚህም ነው አይዝነብ ያልኩት” በማለት ተናገሩ።
ይህንን የሰማው ኢማም ወደ ህዝቡ ዞሮ “አያችሁ ሰዎች! ፈጣሪ የሚቀጣን እኮ ሀጢአታችን ስለበዛ ነው። እንደ አቦ ደርጂ ያሉ ሽማግሌዎችን ስለማናስታውስ ዝናቡም ይጠፋብናል። አሁን በአስቸኳይ ለአቦ ደርጂ ጣሪያ ጉዳይ መፍትሔ መፈለግ አለብን” አለ። ወዲያው በመስጊዱ የነበረው አንድ ነጋዴ “የአቦ ደርጂን ጣሪያ እኔ ራሴ ነገውኑ አሰራዋለሁ” በማለት ሀላፊነት ወሰደ። ቃሉንም በሚቀጥለው ቀን ተግባራዊ አደረገ።

እንግዲህ የአቦ ደርጂ ድፍረት እንዲህ ነው። በመስጊድም ውስጥ ቢሆን የተሰማቸውን ከመናገር ወደ ኋላ አይሉም። ሌላ ሰው ቢሆን ኖሮ ይሉኝታ ይዞት በዝምታው ይጸናል። ነገር ግን ይሉኝታ በሁሉም ቦታ አይሰራም። በተለይ መጠለያን በመሰለ መሰረታዊ ነገር ላይ አደጋ የሚጋርጥ ሁኔታ ሲፈጠር በዝምታ ማለፍ አግባብነት የለውም።

******************

አንድ ጊዜ አቦ ደርጂ ታመሙ። በአካባቢው የነበርን ሰዎች ተሰባስበን ወደ ሀኪም ቤት ወሰድናቸው። ተረኛ ሀኪሙም ከመረመራቸው በኋላ መርፌ አዘዘላቸው። መርፌውን የሚወጋቸው ነርስም መጣ። መድኃኒቱንም ከሲሪንጅ ውስጥ ጨምሮ በታፋቸው ላይ ሰካ። መርፌው ግን በጣም ስላሳመማቸው አቦ ደርጂ በሀይለኛ ሁኔታ ተቆጡ፤ ነርሱንም እንዲህ አሉት፣ “አንተ! በኔ ላይ እየተለማመድክ ነው እንዴ?”
ከአሁን አሁን አንድ ነገር ይናገሩ ይሆናል ብለን የምንጠብቀው ሰዎችም ሀኪም ቤቱን በሳቅ ሞላነው።

******************
የአቦ ደርጂ ልጅ ካገባ አንድ ሶስት ወር ሆኖታል። በዚያው ሰሞን የተወሰንን ሰዎች ከርሳቸው ጋር በመንገድ ላይ ተገናኘን። አንዱ ጓደኛችንም ወሬ ለመጀመር ያህል “አቦ ደርጂ! ልጅዎት እኮ አገባ!” አላቸው። እርሳቸውም ቀድመው የሰሙት ነገር በመሆኑ ቀዝቀዝ ያለ መልስ ሰጡት።  ሌላው ጓዳችን ደግሞ “ኧረ! እኔ እንዲያውም ወለደ ሲሉ ነው የሰማሁት” አላቸው። ይሄኔ አቦ ደርጂ “Mucaan khiyya baatii sadii kheessatti yoo dhale intalti inni fuudhe “Bukkurii” jechuudha gaa!” (“ልጄ በሶስት ወሩ የሚወልድ ከሆነ “ቡኩሪ” ነው ያገባው ማለት ነዋ!” በማለት ማንም ያልጠበቀውን ንግግር ተናገሩ። አቤት የዚያኔ የሳቅነው ሳቅ! እስካሁን ድረስ አይረሳኝም።

(ማስታወሻ፡- ቡኩሪ የሀረርጌ ገበሬዎች በበልግ ወቅት የሚዘሩት የበቆሎ ዝርያ ነው። ይህ የበቆሎ ዓይነት ከሶስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለምግብነት ይደርሳል። አቦ ደርጂም “ልጄ ያገባት ሚስት በሶስት ወራት ውስጥ ከወለደች ልክ እንደ ቡኩሪ በአጭሩ የምታፈራ ዘር መሆን አለባት” ማለታቸው ነው።)
******************
የሀብታም ቤተሰብ ተብለው ከሚጠቀሱት አንዱ ነው። የዚህ ቤተሰብ ሰዎች ልጃቸውን ለመዳር ያስቡና በአካባቢው በሚታወቀው ባህል መሰረት “ጂማ” (የሽምግልና ጫት”) ለማስገባት ይወስናሉ። አቦ ደርጂንም ለሽምግልና ወደ ልጅቷ ቤት በሚላከው ቡድን ውስጥ ለማካተት በማሰብ ያማክሯቸዋል። አቦ ደርጂ ግን በነገሩ ከት ብለው በመሳቅ “እኛ ዘወትር ጫታችንን እየቃምን ነው፤ አልሐምዱሊላህ! ፈጣሪ ለበርጫ የሚሆነን ያህል ነፍጎን አያውቅም። ባይሆን እኛን ድኩማኑን መጥራት ያለባችሁ ሰንጋ ተጥሎ ጥብስና ክትፎው በሚደረደርበት ቀን ነው፤ አደራ ያኔ እንዳትረሱኝ!” አሏቸው። እውነትና ብስለት የሞላበት ንግግር ! በድህነት የሚኖሩትን ወገኖች ”ሀጃ” (ጉዳይ) ሲይዛቸው ብቻ ለሚያስታውሱት የሀብታም ከንቱዎች የሚገባ መልስ ነው።  
   በአንድ ወቅት እንዲህ ዓይነቱ ነገር በከተማችን ውስጥ በስፋት ይታይ ነበር። ሀብታም የሚባል ሰው ድሃውን የሚያስታውሰው ጉዳይ ሲይዘው ብቻ ነው። በሀብታም ሰርግ ላይ የሚታደሙትም ሀብት ያላቸው ወገኖች ብቻ ናቸው። አባ ደርጂም በጊዜው የተቃወሙት እንዲህ አይነቱን ኢ-ሞራላዊ ድርጊት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የድሮው ብልሹ ስርዓት እየቀረ ነው። ወደፊት የበለጠ መሻሻል ይታያል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
 ******************
 የገለምሶው አቦ ደርጂ ጨዋታዎች ብዙ ናቸው። እኔ ያልሰማኋቸው በርካታ ወጎች እንዳሉም አምናለሁ። ለወደፊቱ ሁሉንም በማሰባሰብ ለአንባቢያን ለማቅረብ እሞክራለሁ። ለአሁኑ ግን በዚሁ ይብቃኝ። ፈጣሪ የአቦ ደርጂንም ነፍስ በጀንነት ያኑራት!
ሰላም!
አፈንዲ ሙተቂ
መጋቢት 11/2005 ዓ.ል.

No comments:

Post a Comment