Thursday, July 16, 2015

በዒድ ዋዜማ ምሽት


ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
----
ነገ የዒድ አል-ፈጥር በዓልን ልናከብር ነው፡፡ ድሮ ልጆች ሳለን በዚህ የዋዜማ ምሽት በየቤቱ ላይ እየዞርን የምንዘምረው ህብረ ዜማ ነበረን፡፡ ይህ ዝማሬ አሁንም ድረስ አለ፡፡ ይሁንና የአሁኖቹ ልጆች በኛ ጊዜ ያልነበሩ ግጥሞችንም ጨመርመር እንዳደረጉ ተነግሮኛል፡፡ ለምሳሌ ህጻናቱ ጠቀም ያለ ጉርሻ ከተሰጣቸው “ያ ቢጢ ቢጢ… ጀንነተ ሊጢ” (“አንተ የቤቱ ባለቤት ጀንነት ግባ” ለማለት ነው) የሚል ምርቃት ያወርዳሉ ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ምንም ነገር ሳይሰጣቸው የሚያሰናብታቸውንም ሰው “ያ ቢጢ ቢጢ… አዛባ ሊጢ” (“የቤቱ ባለቤት ሆይ ጀሀነም ግባ” ለማለት ነው) እያሉ ይረግሙታል የሚል መረጃ ተሰጥቶኛል (“ቢጢ” የሚለው ቃል ለግጥሙ ማሳመሪያ ሲባል የገባ ነው፤ ጠበቅ ተደርጎ ሲነበብ “እንጎቻ” እንደማለት ነው፤ ላላ ተደርጎ ሲነበብ ግን ምንም ትርጉም የለውም፤ ህጻናቱ “ላላ” በማድረግ ነው በግጥሙ ውስጥ ያስገቡት)፡፡

  በኛ ዘመን እንዲህ የሚል ግጥም አልነበረም፡፡ ከዚህ ወልካፋ ግጥም በስተቀር ዜማው እንዳለ የያኔው ነው፡፡ ያ ህብረ ዝማሬ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር ነው ለኛ የደረሰው፡፡ ለዜማው ለየት ያለ መጠሪያ አላበጀንለትም፡፡ በጥቅሉ የምንጠራው “ሙሐመዶ” በሚል ስያሜ ነው፡፡

“ሙሐመዶ” የዝማሬው የመጀመሪያ ቃል ነው፡፡ ይህንን ዝማሬ የምንዘምረው በአንድ ልጅ መሪነት ነው፡፡ ልጁ የግጥሙን ስንኞች እያከታተለ ሲያወርድልን ሌሎች ጓደኞቹ “ሙሐመድ ሰይዲና ሙሐመድ” እያልን እንቀበለዋለን፡፡ የህብረ-ዜማው ሙሉ ግጥም የሚከተለው ነው (ግጥሙ በኦሮምኛ ነው የተገጠመው፤ በቅንፍ ውስጥ በአማርኛ ተርጉሜዋለሁ)፡፡

ሙሐመዶ (ሙሐመድ ሆይ)
ሙሐመድ ጄንኔ (ሙሐመድ እያልን)
ነቢ ፋርሲኔ (ነቢዩን እናወድሳለን)
ያ ነቢ ባህሩ (አንተ እንደ ባህር የሆንከው ነቢዩ)
ዛሂድ ኢኒ ሂንአሩ (አላግባብ የማትናደድ ነህ)
ፋጢማ ነቢ ኢልኬን ቲሚራ (የነቢ ልጅ የሆነችው ፋጢማ ጥርሷ እንደ ቴምር ነው)
ዲና ነቢዳ ኢልኬን ዲጊራ (የነቢዩ ጠላት ጥርሱ እንደ “ድግር” ነው)
ሶመንኒ ገሌ  (ረመዳን ሄዷል)
ሲዲስቶ መሌ (ከስድስቶ/ሸዋል በስተቀር)
ያ ሀደ ዲራ (የቤቱ ባለቤት ሆይ)
ገድ ደርቢ ሊራ (እስቲ ሊራ ወርወር አድርጊልን)
ሊራ አፉሪ (አራት ሊራ ሰጥተሽን)
ሉብቡን ኑፉሪ (ከልባችን አስደስቺን)፡፡
ሙሐመድ ሰለላሁ ዐላ
ሙሐመድ ሰለላሁ ዐላ ሙሐመድ፡፡
-----
“ሙሐመዶ” በበርካታ ከተሞች የታወቀ ህብረ-ዜማ ነው፡፡ በልጅነቱ እርሱን ሳይዘምር ያደገ ልጅ የለም፡፡ የክርስቲያን ልጆች እንኳ ከኛ ጋር ተቀላቅለው “ሙሐመዶ”ን ይዘምሩ ነበር፡፡ ይሁንና በርሱ ብቻ መቆየቱ ስለማይበቃን ሌሎች ዜማዎችንም እንጨምር ነበር፡፡ እነዚህ ተጭማሪ ህብረ ዝማሬዎች ግን አንድ ወጥ አይደሉም፡፡ በአንድ ከተማ ውስጥ ባሉ ሁለት ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ ልጆች እንኳ የተለያዩ ዜማዎችን ሊዘምሩ ይችላሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን “ጀማሉል ዓለም” የተሰኘው ህብረ-ዝማሬ ከመሐመዶ ቀጥሎ በሌሎችም አካባቢዎች በደንብ የሚታወቅ ይመስለኛል፡፡ “ሙሐመዶ”ን የማይዘምሩት የሶማሊ ልጆች እንኳ “ጀማሉል ዓለም”ን ሲዘምሩት በአንድ የነሺዳ ሲዲ ውስጥ አይቼአቸው ነበር፡፡ የ“ጀማሉል ዓለም” አዝማች የሚከተለው ነው፡፡

ጀማሉል ዓለም (ሸሊላ)
ጀማሉል ዓለም (ሸሊላ)
ባህረ ሙስጠፋ (ሸሊላ)
ያ ባህረ ጁህዲ ጁንዲላ

“ጀማሉል ዓለም” ማለት “አንተ የዓለም ውብ የሆንከው” እንደማለት ነው፡፡ እንዲህ የተባሉት ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ናቸው፡፡ ታዲያ ከአዝማቹ ቀጥሎ የሚዜሙት አንዳንድ ግጥሞች ከአዝማቹ ጋር የማይሄዱ (“አንታራም” ግጥሞች) መሆናቸውን ሳስብ ድንቅ ይለኛል፡፡ ለምሳሌ በዝማሬው ውስጥ እንዲህ የሚል ግጥም ነበር፡፡

“ጋረራ ያና ቦሮፋ ካፍና
ጆልሌ ኑቲ ካቲ ዱኬ ኢቲ ካፍና
ዱኬ ማል ካስና ጋረራ ባፍና”

የአማርኛው ትርጉም የሚከተለው ነው፡፡

“ጋራ ላይ እንሄዳለን ድኩላ እናባርራለን
የሚተናኮሉንን ልጆች እናርበደብዳቸዋለን
የምን ማርበድበድ ብቻ! ጋራው ላይ እንነዳቸዋለን”

በተለምዶ እንዲህ ዓይነት ግጥሞች የሚገጠሙት የሁለት ሰፈር ልጆች በሚጣሉበት ጊዜ ነው፡፡ የተጣሉ ልጆች በዱላ እየተመካከቱ የሚበሻሸቁበት ግጥም መሆኑን ካደግን በኋላ ነው የተረዳነው፡፡ እኛ ግን ምኑም ሳይገባን የዒድ ማድመቂያ አደረግነው፡፡ አይ ልጅነት ደጉ!!

የገንደ ሀድራ ልጆች ደግሞ አሉ! አንዱን ዝማሬ ለነርሱ ብቻ በሞኖፖል የተሰጠ አድርገው የሚያስቡ፡፡ ያንን ዝማሬ የኛ ሰፈር ልጆች ካዜሙት የቃል ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ ይለቁብናል፡፡ ዝማሬውን ከደገምነው ግን በዱላ ጭምር ያዋክቡን ነበር፡፡ የዝማሬው አዝማች የሚከተለው ነበር፡፡

“አወይ ነቢ ሰላም ዐላ (አንተ ነቢ ሰላም ላንተ ይሁን)
ኑር ሐቢቢ ሶላት ዐላ (አንተ ነቢ ሶላት ላንተ ይሁን)

ከዚህ አዝማች ጋር ብዙ ግጥሞችን ይደረድራሉ፡፡ በመሃሉም እንዲህ የሚል ባለሁለት መስመር ግጥም አለ፡፡

“አክካ አዱ ጎላ ባቱ (ከጎሬዋ እንደምትወጣ ጮራ)
ከን ዱራ ዱብኒ አዳቱ” (ፊቱም ኋላውም የሚያበራ)

የሀድራ ልጆች በጣም ብዙ ነበሩ፡፡ ብዛታቸውን ተመክተው ነው “አወይ ነቢ ሰላምን አትዘምሩት” እያሉ የሚጫኑን፡፡ እኛም በምሽቱ መጀመሪያ ላይ ትዕዛዛቸውን እናከብርና “ሙሐመዶ”ን ወይንም “ጀማሉል ዓለም”ን ብቻ እንዘምራለን፡፡ በሶስት ሰዓት ገደማ ግን የሀድራ ልጆች ለሚያደርጉብን ጭቆና ብድሩን እንከፍላለን በማለት ከላይ የጻፍኩትን ግጥም እንዲህ እያበላሸን እንዘምራለን፡፡

አክከ አዱ ጎላ ባቱ (ከጎሬዋ እንደምትወጣ ጮራ)
ሚጪዮ ፉልሊ አዳቱ  (የልጅቷ ፊት ሲያበራ)

እንዲህ እያልን የምንዘምረው የሀድራ ልጆች እንዲሰሙን ድምጻችንን ከፍ በማድረግ ነው፡፡ ሀድራዎች በንዴት ዱላቸውን እየወዘወዙ በሩጫ ሲመጡብን በጨለማው ውስጥ እንበታተንና ወደቤታችን እንመርሻለን!! አይ ልጅነት ደጉ!!

እኛ ነቢዩን አልነካንም!! ሐድራዎች ዝማሬው የኛ ብቻ ነው እያሉ ስለሚጫኑን እነርሱን ለመበቀል የነበረን አማራጭ መንገድ ይኸው ብቻ ነው፡፡ ቢሆንም ለነቢዩ የተገጠመን ግጥም ማጣመም ልክ አልነበረም፡፡ በመሆኑም ሐራምና ሐላሉን በደንብ ስንረዳ “አስተግፊሩላህ” ብለናል!! አሁንም አስተግፊሩላህ!! ወደፊትም አስተግፊሩላህ!!
----
እንኳን ለዒድ አል-ፈጥር በዓል አደረሰን!!
ዒድ ሙባረክ!!

Saturday, June 27, 2015

የ“ዐጀም” አጻጻፍ ስርዓት በኢትዮጵያ


ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
“ዐጀም” በጥንተ ማንነቱ ዐረባዊ ያልሆነ ህዝብና ሀገር ማለት ነው፡፡ ይሁንና “ዐጀም” የሚለው ቃል በዐረብኛ ስነ-ጽሑፍ ውስጥ በስፋት የሚያገለግለው ዐረብ ያልሆኑ ሙስሊሞችን ለማመልከት ነው፡፡ በዚህም መሰረት ኢራን፣ ቱርክ፣ ህንድ፤ ኢንዶኔዥያ፣ ማሌዥያ፣ ፓኪስታን፣ ባንግላዲሽ ወዘተ…. የሙስሊም ሀገራት ቢሆኑም “ዐጀም” ናቸው ማለት ነው፡፡ 
   
ወደ ሀገራችን ስንመጣ ግን “ዐጀም” ሌላ ተልዕኮ ያለው ቃል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህም የሀገራችን ቋንቋዎች በዐረብኛ ሆሄያት የሚጻፉበትን ስርዓተ-ፊደላት ነው የሚያመለክተው፡፡ ኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ ሀረሪ፣ አፋርኛና ሶማሊኛ በዚህ ስርዓተ ጽሑፍ ይጻፉ ነበር፡፡ ዛሬም በርካታ የእስልምና ሊቃውንት በዐጀም አጻጻፍ ስርዓት ይጠቀማሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ ሁሉ ቋንቋዎች የሚጻፉበት “ስርዓተ ፊደላት” በወል “ዐጀም” ተብለው ቢጠሩም በሚይዟቸው የሆሄያት ብዛት ይለያያሉ፡፡ ይህም ከቋንቋዎቹ የስነ-ድምጽ ባህሪ ጋር በቀጥታ ይዛመዳል፡፡ ለምሳሌ ኦሮምኛ የሚጻፍበት የ“ዐጀም” ስርዓት ሶማሊኛ በሚጻፍበት “ዐጀም” ውስጥ የሌሉ (“ጨ”፣ “ኘ”፣ ጰ የተሰኙትን ድምጾች የሚወክሉ) ሶሰት ፊደላት አሉት፡፡ የአማርኛው ዐጀምም በኦሮምኛው “ዐጀም” ውስጥ የሌሉ ሁለት ፊደላት (“ዠ” እና “ጸ”) አሉት፡፡

    ለመሆኑ የዐጀም አጻጻፍ ስርዓት ሲሰራበት የነበረው እንዴት ነው?….. ትምህርቱስ እንዴት ነበር የሚሰጠው? በልጅነቴ የተማርኩትን የኦሮምኛውን “ዐጀም” እንደምሳሌ ልውሰድና ለማስረዳት ልሞክር፡፡
 *****
  በአንድ ጽሑፌ እንደገለጽኩት በምስራቁ የኢትዮጵያ ክልል ለረጅም ዘመናት ፊደል የማስጠናት ተግባር ሲፈጽሙ የኖሩት “ቁርኣን ጌይ” የሚባሉ የትምህርት ማዕከላት ናቸው፡፡ በነዚህ ማዕከላት የሚሰጠው ትምህርት ዋነኛ ዓላማ ህጻናት ቅዱስ ቁርኣንን በራሳቸው ብቻ ( ያለምንም ረዳት) የማንበብ ችሎታ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም ወደ ቁርኣን ጌይ ለትምህርት የመጣ ተማሪ በቅድሚያ የዐረብኛ ፊደላትን እንዲለይ እና የተማራቸውን ፊደላት መልሶ እንዲጽፍ ይደረጋል፡፡ ከዚያም ወደ ቁርኣን ምንባብ ትምህርት ይሸጋገራል፡፡

   ታዲያ የቁርኣን ጌይ ተማሪ የሚማረው የቁርአን ምንባብ ትምህርትን ብቻ አይደለም፡፡ ከቁርኣን ትምህርት በተጨማሪ የዐቂዳ (ስነ-መለኮት)፣ የፊቂህ (እስላማዊ ድንጋጌ)፣ የሂሳብ እና የኸጥ (የዐረብኛ ፊደላት አጣጣል) ትምህርቶችም ይሰጣሉ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በትምህርታቸው ጎበዝ የሆኑ ልጆች እየተመረጡ የ“ዐጀም” ስርዓተ ጽሕፈትን እንዲማሩ ይደረጋል፡፡ የዚህ ስርዓተ ጽሕፈት ዓላማ ተማሪው የአፍ መፍቻ ቋንቋው የሆነውን ኦሮምኛን በዐረብኛ ፊደላት መጻፍ እንዲችል ማድረግ ነው፡፡

    የዐጀም ስርዓተ ፊደላት መነሻ የዐረብኛው የፊደል ገበታ ነው፡፡ በዐረብኛው የፊደል ገበታ ላይ ያሉት ሀያ ስምንት ፊደላት በሙሉ የኦሮምኛው “ዐጀም” አካላት ናቸው፡፡ በተጨማሪም በዐረብኛ ውስጥ የማይገኙ ስድስት የኦሮምኛ ድምጾችን  የሚወክሉ “ውልድ” ፊደላት ተቀርጸው የስርዓተ ጽሑፉ አካላት ተደርገዋል፡፡ በዐረብኛ ውስጥ የሌሉት ስድስት የኦሮምኛ ድምጾች ከዐረብኛ ሆሄያት በተራቡ “ውልድ” ፊደላት ሲወከሉ የሚከተለውን ይመስላሉ፡፡

ዸ/Dh= ڎ
ገ/G= ݞ
ጨ/C= ڟ
ጰ/Ph= ٻ
ኘ/Ny= ٿ
ቸ/Ch= ݜ

  እነዚህ ውልድ ፊደላት የተቀረጹት በድምጽ የሚቀርቧቸውን የዐረብኛ ፊደላት መነሻ በማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ “ገ” በድምጹ ለዐረብኛው “” ይቀርባል፡፡ በመሆኑም በዚሁ ፊደል ላይ ሁለት ነጥቦች ተጨምረው የ“ገ” ወኪል ሆኖ የሚያገለግል ڠ  የሚባል ውልድ ፊደል ተፈጥሯል፡፡

   ከላይ እንደጠቆምኩት የኦሮምኛው የ“ዐጀም” ስርዓተ ፊደላት በዐረብኛው የፊደል ገበታ ላይ የሌሉትንና “ዸገ”፣ “ጨ”፣ “ጰ”፣ “ኘ” እና “ቸ” የተሰኙ ስድስት የኦሮምኛ ድምጾችን የሚወክሉ ውልድ ፊደላትን በመቅረጽ የተፈጠረ ነው፡፡ ታዲያ ተማሪዎች እነዚህን ፊደላት በቀላሉ እንዲያስታውሷቸው ለመርዳት ሲባል የሀረርጌ ዑለማ “ዸጋ ጨጳ ኛቹ” የሚል ሐረግ ፈጥረዋል፡፡ በአማርኛ “የተሰበረ ድንጋይ መብላት” እንደማለት ነው፡፡ በዚህ ዐረፍተ ነገር ውስጥ ያሉት ድምጾች በሙሉ በዐረብኛ ውስጥ የሉም (በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታዬ “ሁሉንም የእንግሊዝኛ ፊደላት የያዘው ዐረፍተ ነገር የትኛው ነው” እየተባልን ስንጠየቅ ከነበረው ፎርሙላ በፊት “ዸጋ ጨጳ ኛቹ”ን ነው የማውቀው)፡፡

     የኦሮምኛው የዐጀም ስርዓተ ፊደላት የኦሮምኛ ተናጋሪ ሙስሊሞች መኖሪያ በሆኑት ሀረርጌ፣ ባሌ፣ አርሲ፣ ጅማ፣ ደቡብ ወሎ (ከሚሴ ዙሪያ) ወዘተ… ይታወቃል፡፡ አንዳንድ ምንጮች “የአሮምኛው ዐጀም አጻጻፍ የተፈጠረው በሀረርጌ ምድር ነው” ይላሉ፡፡ ለዚህም በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተጻፉ ልዩ ልዩ ድርሳናትን እንደ ማስረጃ ይጠቅሳሉ፡፡ አንዳንዶች ግን “ዐጀም በወሎ ክፍለ ሀገር ውስጥ ባለው የ“ደዌ” ወረዳ (ከሚሴ) የተፈጠረ ነው፤ በደዌ የተማሩ ቀደምት ዑለማ ናቸው ወደ ሀረርጌ ያመጡት” የሚል ሐሳብ አላቸው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ “በባሌው የሼኽ ሁሴን መስጊድ ዙሪያ የሚያስተምሩ ዑለማ ያስገኙት ነው” የሚል ክርክር ያቀርባሉ፡፡ በዚህ ረገድ የተጨበጠ ማስረጃ የለኝም፡፡ ስለዚህ ጥናትና ምርምር ያሻዋል፡፡
*****
በመግቢያዬ እንደገለጽኩት የዐጀም ስርዓተ ፊደላት በሌሎች የሀገራችን ቋንቋዎችም ልዩ ልዩ ጽሑፎችን ለመጻፍ አገልግሏል፡፡ በዚህ ረገድ በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ሀረሪና አማርኛ ናቸው፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የሀረሪ ቋንቋ በዐጀም የአጻጻፍ ስርዓት መጻፍ የጀመረው በመካከለኛው ዘመን ነው፡፡ በመሆኑም የሀረሪ የዐጀም አጻጻፍ በሌሎች ቋንቋዎች ከምናውቃቸው የዐጀም ስነ-ጽሑፎች በሙሉ ይቀድማል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃ የሚሻ ሰው በዶ/ር ኤንሪኮ ቼሩሊ የታተሙ የጥንት ድርሳናትን መመልከት ይችላል፤ ከ1648-1875 በቆየው የሀረር አሚሬት ዘመን የተመዘገቡ ድርሳናትንም መመልከት ይቻላል፡፡
 
 አማርኛ በዐጀም መጻፍ የጀመረበትን ዘመን በትክክል ማመልከት ባይቻልም ጅምሩ በወሎ ክፍለ ሀገር እንደተጸነሰ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ይህ የአማርኛው የዐጀም አጻጻፍ በስፋት ጥቅም ላይ ሲውል የነበረውም በወሎ ነው፡፡ እነ ሼኽ ዑመር ቡሽራን የመሳሰሉ የወሎ ታዋቂ ዑለማ የገጠሟቸው የመንዙማ ግጥሞች ሙሉ በሙሉ በዐጀም የተጻፉ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሼኽ ሑሴን ጂብሪል ትንቢታዊ ግጥሞች በቅድሚያ የተጻፉት በዐጀም አጻጻፍ ነው ይባላል፡፡
*****
  ኢትዮጵያችን በዐጀም ስርዓተ ጽሕፈት የተጻፉ የበርካታ ድርሳናት ባለቤት ናት፡፡ የጥንቱ ሙስሊም ዑለማ የመንዙማ ግጥሞችን ከመጻፍና የዕለት ተዕለት ሁኔታን ከመመዝገብ በተጨማሪ በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በግብርና፣ በአስትሮኖሚ፣ በህክምና፣ በስነ-ማዕድንና በሌሎችም የህይወት ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ድርሳናትን በዐጀም የአጻጻፍ ስርዓት ጽፈዋል፡፡ ይሁንና ከነዚህ ድርሳናት መካከል በጣም የሚበዙት ተሰብስበው በህዝብ ሀብትነት አልተመዘገቡም፡፡ በርካቶቹ በግለሰቦች እጅ ተይዘው ብልና ምስጥ እየበላቸው ነው፡፡
 
  የ“ዐጀም” አጻጻፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደከመ መምጣቱ ደግሞ ሌላው ጉዳት ነው፡፡ ድርሳናቱ በጥቂቱ ተሰብሰበው በሚገኙባቸው አካባቢዎች እንኳ የዐጀም አጻጻፍ እየተረሳ ነው፡፡ ድርሳናቱን ማንበብ የሚቻልበት ስርዓት ተጠብቆ ካልቆየ ቀጣዩ ትውልድ እነርሱን አንብቦ መረዳት ሊያቅተው ይችላል፡፡ ስለዚህ ሁለቱም ጉዳዮች ሊተኮርባቸው ይገባል፡፡ አንደኛ የዐጀም ድርሳናት ተሰብስበው የተሻለ እንክብካቤ በሚያገኙባቸው ስፍራዎች መቀመጥ አለባቸው፤ ሁለተኛ የዐጀም አጻጻፍ ስርዓታችን ተመዝግቦ ለትውልድ መተላለፍ አለበት፡፡ በዚህ ረገድ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር ያለው የፊሎሎጂ ዲፓርትመንት ቀዳሚ ሆኖ መንቀሳቀስ ይኖርበታል እላለሁ፡፡
-------
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 2006
ገለምሶ-ሀረርጌ



Tuesday, June 23, 2015

ተሰውፍ ምንድነው?


ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
---
   “ተሰውፍ” (Sufism) ሁለት ፍቺዎች አሉት፡፡ አንደኛው “ሱፍ መልበስ” የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው “ራስን ማጽዳት” ማለት ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የምንዳስሰው “ተሰውፍ” በሁለተኛ ፍቺው ፈለግ የሚሄድ ነው፡፡ ይህም በተገቢ መንገድ ሲቀመጥ የልብ ጥራት” እንደማለት ነው፡፡ ሙስሊም የሆነ ሰው ልቡ በአካሉ ከሚያደርገው ኢባዳ ጋር በእኩል ሁኔታ እንድትራመድለት ሲፈልግ ልዩ ልዩ ጥበባዊ ዘዴዎችን የሚማርበት መንገድ ነው- “ተሰውፍ፡፡ ይህም ሲባል ልብን ከልዩ ልዩ የልብ በሽታዎች ማጥራትማለት ነው፡፡

   በቁርአንና በሀዲስ በስፋት እንደተገለጸው ሰዎች ከፈጣሪ ጋር ያላቸውን ትስስር የምታበላሽባቸው አንዲት አካል አለች፡፡ እርሷም ልብ ናት፡፡ ሙእሚኖች ቁርኣናዊ ግዳጃቸውን በተገቢው መንገድ ለመወጣት ከፈለጉ ልባቸውን ከበሽታ ማጥራት አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል ፈጣሪያችን አላህ (..) ለምንሰራቸው መልካም ስራዎች የሚከፍለንን ምንዳ (አጅር) የሚወስነው የልባችንን ጥራት በመመዘን ነው፡፡ በከፍተኛ የልብ ጥራት የአንድ ብር ሰደቃ የሰጠ ሰው ከፍተኛ ሽልማት አለው፡፡ ሰውየው መካከለኛ የልብ ጥራት ካለው ሽልማቱ ያንስበታል፡፡ የልብ ንጽህናው በጣም የጎደፈ ሰው ደግሞ ሽልማቱ እጅግ ዝቅተኛ ነው (ሰውዬው መቶ ብር ቢሰጥ እንኳ በንጹህ ልብ አንድ ብር የሰጠውን ሰው ያህል ሽልማት አያገኝም)፡፡ ልቡ ሙሉ በሙሉ የቆሸሸ ሰው ግን ከአላህ ዘንድ ምንም ሽልማት አያገኝም፡፡

  እንግዲህ ይህንን የልብ ጥራት ማምጣት የሚቻለው እንዴት ነው? ኡለማ ለዚህ ጥያቄ የሚሆን ምላሽ ሲፈልጉ ነውተሰውፍየሚባለው አስገራሚ (አንዳንድ ጊዜ አወዛጋቢ) ኢስላማዊ የትምህርት ዘርፍ የተወለደው፡፡
  ተሰውፍን እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ አድርጎ ማስተማር መቼ እንደተጀመረ በትክክል አይታወቅም፡፡ በርካታ ምንጮች ታዋቂዎቹን የበስራ ምሁራን ሐሰን አል-በስሪንና ራቢአቱል አደዊያን እንደ ጀማሪዎች ይጠቅሳሉ፡፡ ለመጀመሩ ሰበብ የሆነውም በጊዜው የነገሰው የልዩ ልዩ ፊርቃዎች (ዓ፤ ኻዋሪጅ፤ ሙርጂአ፤ ጀሀሚያ፤ ሙእተዚላ፤ ቀደሪያ፤ ጀብሪያ ወዘተ…) ሽኩቻ እንደሆነ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡

   በተሰውፍ ላይ የሚያተኩሩ መጽሀፍት መጻፉንም ማን እንደጀመረው በርግጥ አይታወቅም፡፡ እንደሚመስለኝ ከሆነ የተሰውፍ መጽሀፍት መጻፍ የጀመሩት ከሂጅራ በኋላ 4ኛው መቶ አመት ገደማ፤ ማለትም እንደ አውሮፓ አቆጣጠር 900 .. በኋላ ሳይሆን አይቀርም፡፡ 10ኛው፤ 11ኛውና 12ኛው ክፍለ ዘመናት ፈሪዱዲን አጣር፤ አቡ ሀሚድ አል-ገዛሊ፤ አህመድ አል-ሪፋኢ፤ አብዱልቃዲር አል-ጁይላኒ ወዘተየመሳሰሉ ምሁራን በተሰውፍ ላይ ያተኮሩ በርካታ መጽሀፍትን አበርክተዋል፡፡

ተሰውፍና የልብ በሽታዎች
   ልባችን የሚቆሽሸው በተለያዩ በሽታዎች ነው፡፡ እነዚህ የልብ በሽታዎች ያሉበት ሰው ኢባዳውን በወጉ አያደርግም፡፡ ውሎውና ድርጊቶቹ ከኢስላማዊ አዳብ ጋር አይገጥሙለትም፡፡ ከግለሰቦችና ከማህበረሰቡ ጋር ያለው ግንኙነትም የተስተካከለ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ በዚህች አለም ብቻ ሳይሆን በወዲያኛውም አለም ታላቅ አደጋን ያስከትልበታል፡፡ ስለዚህ ከአደጋው ለመዳን ልቡን ከበሽታ ማጥራት ይጠበቅበታል፡፡

   የሰውን ልብ ከሚያደርቁትና ኢማንን ከሚያጎድሉት በሽታዎች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡
·        ኒፋቅ፡- የሙናፊቅነት ስሜት
·        ጡግያን፡- ጥመት
·        ኪብሪያእ፡-ኩራት
·        ጁብር፡ ትዕቢት
·        ሪኣእ፡- ልታይ ልታይ ማለት
·        ዘን፡- ከንቱ ጥርጣሬ
·        ገፍላን፡- መሰላቸት
·        ሻህዋእ፡- ከገደብ ያለፈ ስጋዊ ፍላጎት
·        ወዘተ

   አላህና መልዕክተኛው (..) ከነዚህ በሽታዎች እንድንጠነቀቅ አስተምረውናል፡፡ የተሰውፍ ሰዎች ለነዚህ በሽታዎች የሚሆኑ መድሃኒቶችን ነው የሚያስተምሩት፡፡ የነዚህ መድሃኒቶች ምንጭ ቁርአንና ሱንና ነው፡፡ ልቡን ከነዚህ በሽታዎች ያጠራ ሰው ዒባዳውን በታላቅ ኹሹእ (የአላህ ፍራቻ) ማከናወን ይችላል፡፡ በተሰውፍ ከምንታከምባቸው መድሀኒቶች መካከል ከሁሉም የሚበልጠውዚክር” (አላህን ማስታወስ ) ነው፡፡ ቁርኣን ልቦች በዚክር ይረጥባሉ በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷልና!!

   እንግዲህሱፊየሚባል ሰው ልቡን ከበሽታ ለመጠበቅ ሲል የተሰውፍን ጥበብ የሚከተል ማለት ነው፡፡ ይህ የተሰውፍ ጥበብ ደግሞ ከቁርአንና ከሀዲስ ጋር የማይጋጭ መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም ሰውየው ሌላውን ኢባዳ ትቶ ተሰውፍን ብቻ የሙጥኝ ብሎ መያዝ አይችልም፡፡ተሰውፍሰውዬው በኢባዳ ላይ ብርቱ ሆኖ እንዲቆይ የሚረዱትን ጥበባዊ ዘዴዎች ያስተምረዋል እንጂ በራሱ የቆመ ለየት ያለ ኢስላማዊ ጎዳና ወይም የሸሪኣ ዘርፍ አይደለም፡፡

   ማንም ሰው የተሰውፍ ዘዴዎችን ሳይማር ኢባዳውን ማድረግ ይችላል፡፡ልቤ በትእቢትና በኩራት ተወጥራለችና ምን ይበጀኛል?” ብሎ የሚጨነቅ ከሆነ መድሃኒቱን ከተሰውፍ መንገድ መፈለግ ይፈቀድለታል፡፡

   እዚህ ላይ የታዋቂውን የሱፊ ጥበብ አዋቂ የሼኽ ብዱልቃዲር አል-ጄይላኒን ምሳሌዎች ልጥቀስ፡፡ ሼይኽ አል-ጄይላኒአል-ጉንያ ሊጣሊብ ጠሪቀል ሀቅበተባለ መጽሀፋቸው ውስጥ እንዲህ ይላሉ፡፡
·        መቼም ቢሆን አትማል፤ መማል ካስፈገለ ግን በአላህ ስም ብቻ ማል!
·        በምላስህ አትዋሽ! ጥሩ ነገር ብቻ ተናገር!
·        በመንገድህ ላይ በእድሜው ካንተ የሚያንስ ሰው ቢያጋጥምህከርሱ የተሻልኩነኝ ብለህ አታስብ፡፡ ከዚህ ይልቅ በልብህይህ ልጅ በምድር ላይ የኖረበት ዘመን ከኔ እድሜ ያንሳል፡፡ ስለዚህ ሀጢአቱም ከኔ ያነሰ ነውበል፡፡
·        በእድሜው ካንተ የሚበልጥ ሰው ከገጠመህ ደግሞይህ ሰው በዚህች ምድር ላይ ከኔ እድሜ ለሚበልጥ ጊዜ ኖሯል፤ ስለዚህ ለአላህ ባደረገው ኢባዳ ከኔ ይበልጣልበል እንጂ በመጥፎ ነገር አትጠርጥረወ፡፡

   ደስ ይላል አይደል? ከማስደሰቱ ጋር መጠየቅ ያለበት ጥያቄሼኽ አብዱልቃዲር የተናገሯቸው ነገሮች ከኢስላማዊው ሸሪዓ ጋር ይቃረናሉ ወይ?” የሚለው ነው፡፡
   ሼኽ አብዱልቃዲር የጻፉት ነገር ከኢስላማዊ ሸሪዓ ውጪ አይደለም፡፡ ይልቅ ኢስላማዊ ሸሪዓን በትክክል ለመተግበር ያግዛል፡፡ ተሰውፍ ማለትም እንዲህ ነው፡፡ 
   በዚህ መሰረት ነው ሙስሊሞች ልባቸውን ከበሽታ የሚፈውሱባቸውን ልዩ ልዩ ምክሮች የሚሰጡ መጽሀፍት መጻፍ የተጀመሩት፡፡ አንዳንድ መምህራንም ሙሉ ጊዜያቸውን ለዚሁ ሰጥተው የማስተማሪያ ማእከላትን ያቋቋሙት ለዚሁ አላማ ነው፡፡

(ይቀጥላል)

-----
አፈንዲ ሙተቂ

ጥቅምት 2004