Wednesday, June 26, 2013

አንድ ሰው አየሁኝ


አፈንዲ ሙተቂ (ስነ ግጥም)
ጥንት እንደሰማሁት
በመድረሳ እንደተማርኩት
ነቢዩ እንደሰበኩት
በኮሌጅ እንዳጠናሁት
ፈላስፎች እንደጻፉት።
ጀግና ሰው ማለት
ጠላቱን ደምስሶ
ከመሬት ደባላቂ
የወደዱትን አቅርቦ
የጠሉትን አስጨናቂ
የናቁትን አድቃቂ
ማለት እኮ አልነበረም
ጦር አዝማች በዓለም።
ጀግናማ ማለት
እንደ ኮንፉሺየስ
ነጻነትን አስተማሪ
እንደ ሶቅራጥስ
እውነትን መስካሪ
እንደ ሀሩን አል-ረሺድ
እውቀትን አጥማቂ
እንደ ህንዱ ጋንዲ
ፍቅርን አድማቂ
እንደ ቶልስቶይ
ህላዌን ተንታኝ
እንደ ፐርሺያው ሩሚ
ጥላቻን አምካኝ።
እንደዚያ ነው ጀግና
የሚኖር በዝና
በማይጠፋ ጉብዝና
በማያረጅ ስብዕና።
ታዲያ በዚህ ዘመን
በዓለም ስሙ የገነነው
በሚዲያ የሚዘምረው
በቴቪ የሚንጎማለለው
በፕሬስ የሚመላለሰው
ሁሉም ቢሆንብኝ አረመኔ
አውደልዳይ ወመኔ
አሽቃባጭ ቦዞኔ።
እተክዝ ጀመርኩኝ
የጥንቶቹን እየዘከርኩኝ
በድርሰት ያወቅኳቸውን
ግን በአካል ያላየኋቸውን
እነርሱን እያሰብኩኝ
ለራሴ እንዲህ አልኩኝ
“ጀግና ሳላይ ነው የምሞተው?
ወደ አፈር የምመለሰው
ይሄስ ክፉ እድል ነው
እንዲያውም እርግማን ነው”
ሆኖም በትካዜዬ መሀል
አንድ ሰው ውልብ ብሎብኝ
“የዘመንህ ጀግና እኔ ነኝ
እኔ ነኝ ተመልከተኝ”
በማለት ደስኩሮብኝ
ፈገግታውን አልብሶኝ
ሓሳቤን አቃለለልኝ
ድብቱን አባረረልኝ
እኔም አልኩ ተመስገን
ተመስገን ያ አላህ ተመስገን
ተመስገን ጌታዬ ተመስገን።
ይህንን ጀግና የሰጠኸን
እንካችሁ ብለህ የሸለምከን
በትግሉ ጽናትን ያስተማርከን
በእስሩ ቻይነትን ያሳየኸን
በመሐሪነቱ ፍቅርን ያስዘመርከን
በአባትነቱ ብስለትን ያስጨበጥከን።
ተመስገን ያረቢ ተመስገን
ተመስገን አምላኬ ተመስገን
ማዲባን የሰጠኸን
መምህሩን ያነሳህልን።”
ከሐሳቤ ስመለስ
ልቤን ሞልቶት ኩራት
መፈንሴ በርቶ በብስራት
ሰውነቴ ጠንክሮ በጽናት
ራሴን ድኖ አገኘሁት።
(ለኔልሰን ማንዴላ ክብር የተገጠመ)

------ግጥም፡ አፈንዲ ሙተቂ፣
ሰኔ 19/2005 ዓ.ል.
ሀረር/ ምስራቅ ኢትዮጵያ

Tuesday, June 25, 2013

የምስራች!


 የሼኽ ሑሴን ጂብሪልን ሙሉ ግጥሞች እንድሰጣችሁ በጠየቃችሁኝ መሰረት በዶ/ር ጌቴ ገላዬ የተዘጋጀው ባለ 36 ገጽ ጥናታዊ ጽሁፍ በዘልዓለም ክብረት ብሎግ ላይ ተጭኖ አግኝቼዋለሁ። ስለዚህ ከታች ያለውን ሊንክ ተከትላችሁ ዳውንሎድ ማድረግ ትችላላችሁ።
-----------
ማስታወሻ፡-
1. የሼኽ ሑሴን ጂብሪል ግጥሞችን በዚህ ፔጅ ላይ ሳቀርብ የነበረው ስለኢትዮጵያ ቀደምት ዑለማ ስጽፍ ያዩኝ አንዳንድ የፔጁ ተከታታዮች "ስለወሎው ሼኽ ሑሴን ጂብሪልም ንገረን" የሚል ጥያቄ ስላቀረቡልኝ ነው፤ እንጂ ግጥሞቹ የወደፊቱን ጠቋሚ ትክክለኛ ትንቢቶች ናቸው በማለት አይደለም (ይህንን የሚያውቀው አላህ ብቻ ነውና)። ስለዚህ ግጥሞቹ ከማንኛችንም እምነት ጋር መያያዝ የለባቸውም።

2. እስከ አሁን post ያደረግኳቸው ግጥሞች ለራሴ ምርጫ የተስማሙት ብቻ  ናቸው። ከእኔም ሆነ ከብዙዎች እምነት ጋር የማይሄዱ ግጥሞችም በድርሳኑ ውስጥ አሉ። ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ተቃርኖ ያሉባቸውን ግጥሞች እየዘለላችኋቸው ደስ የሚሉትን ብቻ እንድታዩአቸው ማስገንዘቢያ ቢጤ ጣል ላደርግላችሁ እፈልጋለሁ።

3. ሼኽ ሑሴን ጂብሪል ስለሚባሉት ሰው ማንነትም ሙሉ በሙሉ የሚታወቅ ነገር የለም። ስለዚህ የሼኹ የህይወት ታሪክ ተብሎ የተነገረው ጸሐፊው/ጸሓፊያኑ በአፈታሪክ ሲነገር የሰሙት ብቻ መሆኑን እንድታውቁት ይፈለጋል።

ለሁሉም ጽሁፉን ዳውንሎድ አድርጋችሁ ውሰዱት።
------አፈንዲ ሙተቂ
ሰኔ 20/2005
ሀረር- ምስራቅ ኢትዮጵያ
ሊንኩ ይኸውና http://zelalemkibret.files.wordpress.com/2011/03/gelaye4.pdf


N.B. ግጥሞቹ የታተሙበትን መጽሐፍ ብሔራዊ ቲያትር አካባቢ ወዳለው ደስታ መጻሕፍት መደብር ሄዳችሁ ጠይቁ። እኔም ከዚያ ነው የገዛሁት (ሽፋኑ ሰማያዊ ነው)።

Tuesday, May 28, 2013

የህዝብ ፍቅር ይስጠን- እንደ ሙሐመድ ረሻድ-!!


ጸሓፊ፡- አፈንዲ ሙተቂ
 

   ትዝታን እንደ መግቢያ
የዛሬ ሃያ ዓመታት ገደማ ነው። ወሩን በትክክል ባላስታውሰውም መስከረም ወይም ጥቅምት 1985 ይመስለኛል። በተወለድኩባት የገለምሶ ከተማ እምብርት ላይ ከነበረው “ፎቶ ማወርዲ” አጠገብ ከጓደኞቼ ጋር እየተጨዋወትኩ ነበር። ታዲያ ከተማችንን ከሁለት ከፍሎ ከሚያልፈው ዋነኛ ጎዳና ላይ ዓይኔን በድንገት ስወረውር አንድ ቁመናው ያማረ ባለ ግርማ ሞገስ “ ሼኽ” እና አንድ ሌላ ሰው በኛ ትይዩ ሲያልፉ ተመለከትኩ። “ሼኹ” ለአካባቢያችን እንግዳ ነው። ከሰውነቱ ላይ የሚያበረቀርቀው ብርሃንና የጀለቢያው ንጣት የተመልካችን ቀልብ ይስባል። በራሱ ላይ ያደረገው ኮፍያም የአካባቢያችን ሼኾች ከሚያደርጉት የተለየ ነው። ሁለመናው ለአካባቢያችን አዲስ ሰው መሆኑን ያሳብቅበታል።
   ከጓደኞቼ መካከል አንደኛው ወደ ሼኹ እያመለከተ “ይህንን ሰውዬ አውቃችሁታል?” የሚል ጥያቄ አቀረበልን። በስፍራው የነበርነው  ባልንጀራሞች አሉታዊ ምላሽ ሰጠነው። “ይህ ሰውዬ እኮ ሙፍቲ ነው። ቁርአንን በኦሮምኛ ተርጉሟል። ካሴቱን ሰምቼለታለሁ። በጣም ደስ ይላል” አለን። ጓደኛዬ የነገረንን ወሬ በመረጃ ደረጃ ብንበቀበለውም የተለየ አትኩሮት አልሰጠነውም። ምክንያቱም ሙፍቲ መሆንም ሆነ የቁርአንን ተፍሲር በካሴት አስቀድቶ ማስደመጥ በወቅቱ ለኛ አዲስ ነገር ስላልነበረ ነው። ይሁንና ጓደኛችን ሊነግረን የፈለገን የቁርአን ተፍሲር ድሮ ከምናውቀው የተለየ ነው። በወቅቱ በደንብ ስላላብራራልን ነው ለነገሩ ትኩረት ሳንሰጥ በዝምታ የተለያየነው።
*****  *****  *****
      ይህ ነገር ከተከሰተ ከሁለት ቀናት በኋላ በዘመኑ የነበረው የከተማው አስተዳዳሪ (አሊሹ ሙሳ ይባላል) መላው የገለምሶ ህዝብ በከተማዋ ሁለገብ አዳራሽ እንዲሰበሰብ አዘዘ። ህዝቡም ትእዛዙን አክብሮ በቦታው ተገኘ። እኔም ጥሪው ባይመለከተኝም “እንዲያው ለጨዋታ የሚሆን ነገር ከሰማሁ” በሚል ከጓደኞቼ ጋር በአዳራሹ ተገኘሁ። ምክንያቱ ደግሞ ምን መሰላችሁ? አሊሹ ሙሳ ከዚያ ዘመን ካድሬዎች በጣም የተለየ ነው። መድረክ ላይ ወጥቶ ንግግር ሲያደርግ ህዝቡን በደረቅ ፕሮፓጋንዳ አያደነቁርም። አነጋገሩ በድሬ ዳዋ ልጆች ስልት የተቃኘ በመሆኑ በጣም ያዝናናል። በመድረክ ላይ የሚደሰኩረው ሁሉ በጆክና በኩመካ የተሞላ በመሆኑ እርሱ ሲናገር አዳራሹ በሳቅ የሚደረመስ ነው የሚመስለው። ደግሞም መላ ቅጡ የጠፋ ተረትና ምሳሌ ይፈጥርና ለሳምንት የሚበቃ የሳቅ ስንቅ ያሸክማችኋል። በዚህም የተነሳ የከተማው ህዝብ ከስብሰባ አይቀርም ነበር።

የስብሰባው ሰዓት ደርሶ አሊሹ ወደ መድረክ ላይ ወጣ። ይሁንና ከወትሮው በተለየ ሁኔታ “ዛሬ ታላቅ እንግዳ በመሀከላችን አሉ። የዛሬውን ንግግር የሚያደርጉልን እሳቸው ናቸው” በማለት ተናገሮ መድረኩን ሲለቅ የአሊሹን ወግ የለመደነው ሰዎች ኩምሽሽ አልን። ሳቅ እንሸምታለን ብለን ተቻኩለን ገብተን ባልጠበቅነው የፕሮፓጋንዳ ድግስ ላይ መገኘታችን አንገበገበን። በተለይ በቀበሌ በሚካሄድ ስብሰባ ላይ የመገኘት ግዴታ ያልነበረብን እድሜያችን አስራ ስምንት ዓመት ያልሞላው ታዳጊዎች ከስብሰባው መጠናቀቂያ በፊት መውጣት ከማይቻልበት አዳራሽ በመግባታችን ተንጨረጨርን። አንደኛው ወደ ሌላኛው ጠጋ በማለት “ዛሬስ አሊሹ ጉድ ሰራን! አንድ የዞን ካድሬ አምጥቶ ሊያንባርቅብን ነው። መቻል ነው መቼስ!” እያልን በለሆሳስ ተነጋገርን። ይህንን የጨፈገገ ስሜት ይዘን አሊሹ የነገረንን እንግዳ ለአስር ደቂቃዎች ያህል ጠበቅን።
 
 እንግዳው ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ገደማ ከአዳራሹ ተገኘ። ታዲያ የዞን ካድሬ ነው ብለን የጠበቅነው እንግዳ ማን ይሆናል መሰላችሁ? ከላይ በመነሻዬ ላይ የጠቆምኳችሁ ሼኽ!! “እዚህ ደግሞ ምን ሊሰራ መጣ?” አልኩ በልቤ።
     የከተማችን ህዝብ የእንግዳውን ማንነት አላወቀም። ሆኖም የስብሰባው አጀንዳ ከወትሮው የተለየ እንደሚሆን ተረድቷል። ስለዚህ በተሰላቸ ስሜት ከየወንበሩ ላይ የሚቁነጠነጠው አብዛኛው ታዳሚ አደብ ገዝቶ የሚሆነውን ወደ መጠበቁ አዘነበለ። ልዩ ልዩ ምክንያት እየፈጠሩ ከስብሰባ የመጥፋት ልማድ የነበራቸው አንዳንድ የከተማችን ታዋቂ እናቶችም በእንግዳው ሁኔታ ተማርከው በጸጥታ ወደርሱ መመልከት ያዙ። እኔና መሰሎቼም የእንግዳው በስፍራው መገኘት ስላስደነቀን የመሰላቸት ጸባያችንን በአንድ አፍታ አሽቀንጥረን ጣልነው። ሙሉ ሰውነታችንን ጆሮ አድርገን ከርሱ የሚወጡትን ቃላት ለመስማት በጉጉት መጠባበቅ ጀመርን።
    ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እንግዳው እጅግ በተዋበ ድምጽ መናገር ጀመሩ። “ለብዙ ዓመታት የተለየኋትን ሀገሬን ለማየት በመብቃቴ ፈጣሪዬን አመሰግነዋለሁ። እኔ ወንድማችሁ ሼኽ ሙሐመድ ረሻድ ከቢር አብዱላሂ እባላለሁ። ታውቁኛላችሁ አይደል?” የሚሉ ዐረፍተ ነገሮች ከአንደበቱ ወጡ። እንግዳው ይህችን ታህል በመናገሩ ብቻ በአዳራሹ የነበረው ድባብ በአንድ ጊዜ ተቀየረ። ጎልማሶች እንባቸውን በጉንጮቻቸው ላይ ማፍሰስ ጀመሩ። እናቶች እዬዬውን አቀለጡት። በርካቶች ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ድምጻቸውን ከፍ እያደረጉ መጯጯህ ጀመሩ። ከደቂቃ በፊት ኮሽታ ያልነበረበት አዳራሽ ከህዝቡ በተፈነቀለው ስሜት ድብልቅልቁ ወጣ።
    
   የሆነው ሁሉ ህልም ነበር የመሰለኝ። ህልም አለመሆኑን የተረዳሁት ከኔ በጥቂት እርምጃዎች ርቀት ላይ ቆሞ የነበረው አቻዬ ማልቀስ ሲጀምር ነው። “ታላላቆቹ አለቀሱ፤ እርሱስ ምን አስለቀሰው?” እያልኩ በአትኩሮት አየሁት። አንድ አፍታ ደግሞ ወደ ህዝቡ ተመለከትኩ። ለቅሶና ሁካታው ቀጥሏል። እንግዳው የሚናገርበት ፋታ አላገኘም። ይብሱኑ እርሱም ከህዝቡ ጋር ያለቅሳል። የአሊሹን የሳቅ ድግስ ለመኮምኮም አቅደን በአዳራሹ የተገኘነው ታዳጊዎች በለቅሶ በመዋጣችን በጣም ግራ ተጋብተናል። ከህዝቡ ጋር እንዳናለቅስ የሚለቀስበትን ምክንያት አላወቅነውም። ሁኔታው እፍረት ቢጤ ጫረብኝ። ግና የ14 ዓመት ታዳጊ መሆኔን ሳስታውስ ማፈሩን ተውኩትና የለቅሶውን ምክንያት ከሚያለቅሰው እኩያዬ ለመረዳት ወሰንኩኝ። ይሁንና እርሱንም ከማድረግ አሊሹ ገላገኝ።
“አንድ ጊዜ ጸጥታ!” በሚል ህዝቡ ለቅሶውን እንዲተው ትእዛዝ ሰጠ። አዳራሹ ጸጥ ሲል እንግዳው ማይኩን አነሳና ንግግሩን ካቆመበት ቀጠለ። ስላሳለፈው የህይወት ውጣ ውረድ፣ ስለገጠሙት ፈተናዎች፣ ስላከናወናቸው ድርጊቶች፣ በህይወት ስለተለዩት የትግል ጓዶቹ ወዘተ… ተናገረ። ህዝቡም ንግግሩን በእንባ እያወራረደ አዳመጠው። እኔም በዚያ አዳራሽ የሆነውን ሁሉ በተመስጦ እየታዘብኩ አረፈድኩ። በእለቱ ከታዘብኩት ነገር በመነሳት ህዝቡን በእንባ ያራጨው እንግዳ ህዝቡ ከፈጠራቸው ጥቂት ጀግኖች መካከል እንደሚመደብ ለማወቅ ቻልኩኝ።
በዚያች እለቱ ከሆነው ሁሉ ሁለት ነገሮች እስከዛሬ ድረስ በልቤ ላይ ታትመው ቀርተዋል። ያ ህዝብ አሊሹ በሚናገርበት ስብሰባ ላይ የሚገኘው አጀንዳው ጥሞት ሳይሆን የአሊሹ አነጋገር በሚፈጥርለት ሳቅና ደስታ መዝናናት ስለሚፈልግ ነው። ሌሎች አሰልቺ ስብሰባዎችን የሚካፈለው ደግሞ “ከስብሰባ የቀረ ሰው ከቀበሌ ሱቅ ስኳርና ዘይት መግዛት አይችልም” ከሚለው የዘመኑ ቅጣት ለማምለጥ ሲል ነው።
በዚያች እለት የሆነው ግን ተቃራኒው ነው። ያ በአሊሹ ተረብ መዝናናት የለመደ ህዝብ ከእንግዳው ጋር በእንባ ሲራጭ ዋለ። እንግዳው ንግግሩን ካበቃ በኋላ ህዝቡ በመድረኩ ላይ ያደረገውን ወረራ በቃላት መግለጽ ያስቸግራል። “እርሱን አቅፎ የሳመ ዛሬ ማታ ጀንነት ይገባል” የተባለ ይመስል በርሱ ላይ ሲረባረብ ነበር የዋለው። እርሱን መሳም ያልቻለውም ሰውነቱን ለመዳሰስ ሲጋፋና ሲረጋገጥ ነበር ያረፈደው። የሚገርመው ነገር ይህ ሁሉ ሲሆን ህዝቡ ስቅስቅ ብሎ ማልቀሱን አላቆመም። ጸጥታ አስከብራለሁ በሚል ተፍተፍ ሲል የነበረው አሊሹ እንኳ ጸጥታ ማስከበሩን ትቶ ከህዝቡ ጋር ማልቀሱን ተያይዞታል። “የህዝብ ፍቅር ይስጥህ!” የሚል ምርቃት ስሰማ ያ ትእይንት ከፊቴ ድቅን ይላል። ህዝብ ለጀግናው ያለውን ፍቅር በዐይኔ ያየሁት በዚያች እለት ነውና።
    የእንግዳው ነገርም አስገርሞኛል። ለአርባ ዓመታት ከተለየው ህዝብ መሀል ሲገኝ ህዝቡ ይረሳኛል ብሎ ባያስብም እንኳ በዚያ አዳራሽ የተፈጠረውን ትዕይንት እንዳልጠበቀው ከግምት በላይ መናገር ይቻላል። ነገር ግን ህዝብ ህዝብ ነው። ማን እንደሰራለትና ማን እንደሰራበት አበጥሮ ያውቃል። ጀግኖቹ የዋሉለትን ውለታ ፈጽሞ አይረሳም። ለህዝብ የሰራና ለህዝብ የለፋ ሰው ከህዝብ የሚጠብቀው ሽልማት የማይነጥፍ ፍቅር ነው። ይህንን ሽልማት የተሸለሙ ጀግኖች እንዳሉ ሰምቻለሁ። በታሪክ መጻሕፍትም አንብቤአለሁ። በህዝብ የተሸለመ ጀግና በዐይኔ ለማየት የቻልኩት ግን በዚያች ዕለት በዚያ አዳራሽ ውስጥ ነው።
*****  *****  *****
 
የጀግናው ፍጻሜ
ግንቦት 17/2005 …ሀረር
 ከምሳ በኋላ አልጋዬ ላይ ጋደም እንዳልኩ እንቅልፍ ይዞኝ ጭልጥ አለ። ለተወሰነ ጊዜ ከለጠጥኩት በኋላ ነቃሁ። ሞባይሌን በዳበሳ ፈላልጌ አገኘሁትና ሰዓቱን አየሁት። አስር ሰዓት ተኩል መሆኑንም ተረዳሁ። እግረ መንገዴንም በተኛሁባቸው ሶስት ሰዓታት ዓለም እንዴት እንደቆየችኝ ማወቅ አማረኝና ኢንተርኔት ከፈትኩ። ቢቢሲና አል-ጀዚራ ለኔ የማይጥሙ ወሬዎችን በመረባቸው ላይ ለቀዉታል። “አንባቢ ያውጣላቸው” ብዬ አለፍኳቸውና ወደ ፌስቡክ ገባሁ። የፌስ ቡክ ቀንደኛ ዜና (top story) ሆኖ የተጻፈውን ሳይ ከዛሬ ሀያ ዓመት በፊት በህዝብ ሲሸለም ያየሁት ጀግና መሞቱን የሚያረዳ ሆኖ አገኘሁት።
ዐይኔ ተስቦ ሊጠበስ ደረሰ። ልቤም ተደናባብሮ ምቱን ቀየረው። “እውነት ነው ውሸት?” በሚል ይበልጥ ለማረጋገጥ ሞከርኩ። የተለየ ለውጥ የለውም። ለጥቂት ደቂቃዎች ስልኩን ዘጋሁትና “ፈጣሪዬ! ውሸት አድርገው ባክህ?” እያልኩ አጉተመተምኩ። ግን ዋጋ አልነበረውም። የሆነውን መቀበል ብቻ ነው የተረፈኝ….
ይገርማል! ሰው ሞተ ሲባል “ኢና ሊላህ የኢና ኢለይሂ ራጂዑን” ከማለት ውጪ ብዙም አልደነግጥም። በጣት የሚቆጠሩ ሰዎችን መርዶ ስሰማ ግን ከመደንገጥም አልፎ በቁሜ እንደ መቃዠት ብያለሁ። የትላንትናውም በዚሁ ምድብ ውስጥ ከሚካተቱት ነው።
በእርግጥ እላችኋለሁ። ድንጋጤዬ ለከት አልነበረውም። ደግሞም በንዴት እርር ብያለሁ።  ሞትን ባገኘሁት ኖሮ እንቅ አድርጌ በገደልኩት ነበር። “ተልካሻውን ለቃቅመህ ማጥፋት ሲገባህ ጀግናውን የምትለቅመው ለምንድነው?” ብዬ ባፋጠጥኩት ነበር። ግን አይቻልም። ሞት በፈጣሪ የተሰጠውን ግዳጅ ነው ያከናወነው። ፈጣሪ ያመጣውን መቀበል ግዴታ ነውና እየመረረኝም ቢሆን ዋጥኩት።
  አዎን! ያ ከሃያ ዓመታት በፊት በህዝብ ሲሸለም ያየሁት ጀግና ዳግም ላይመለስ ሄዷል። ጣፋጭ አንደበቱ ከእንግዲህ አንዲት ቃል ላይተነፍስ ተዘግቷል። የተባ ብዕሩ አንዲት አንቀጽ ላይጭር ነጥፏል። ጀግናው ከኛ ጋር እንዳልነበረ ሁሉ ዛሬ ለዘልዓለሙ ተለይቶናል። በመሆኑም የኔና የወገኔ ሀዘን ድርብርብ ነው።
እንጉርጉሮዬን በዚሁ ልቋጭ። ጀግናውን “አላህ ይርሐመክ” ልበለው!

አፈንዲ ሙተቂ
ግንቦት 26/2005
ሀረር