Tuesday, October 23, 2012

“ከቢር” እና “አርዳ ዊጅ"


(አፈንዲ ሙተቂ: “ሀረር ጌይ- የአስገራሚዋ ከተማ የኢትኖግራፊ ወጎች”: ገጽ 12-16)

ለዕድለኛ ሰው የህይወት ጥሪ ይደርሰዋልይባላል፡፡ እኔ ድሮ በዚህ አላምንም ነበር፡፡ ተኣምረኛዋ ከተማ ግን ተስፈንጣሪ አቋሜን ትቼ ከብዙሀኑ እምነት ጋር እንድታረቅ አስገድዳኛለች፡፡1 “እንዴት?” የምትሉኝ ከሆነ ነገሩን በጥቂቱ ላጫውታችሁ፡፡
የዚህችን ከተማ ስመ-ገናናነት ቀድሞውንም ቢሆን እመሰክራለሁ። በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪቃ በጥንታዊነታቸው ከሚጠቀሱ ጥቂት ማዕከላት መካከል እንደምትመደብም ተጠራጥሬ አላውቅም፡፡ እርሷን በአካል ካወቅኳት በኋላ ግን በመጠነ ሰፊ ተአምራት የተሞላች ባለትንግርት (mystique) መዲና መሆኗ አነቃቃኝና በትንግርቶቿ ላይ አሰሳ ማድረግ ጀመርኩ፡፡
በዚሁ መሰረት በንባብ (reading) በምልከታ (observation) በመጠይቅ (interrogation) በፍተሻ (survey) እና በውይይት (discussion/ dialogue) የማገኘውን ሁሉ ከማስታወሻ ደብተሬ ላይ ማስፈሩን ተያያዝኩት፡፡ አንዳንድ መረጃዎችን ደግሞ እንደኔው ለከተማዋ አዲስ ለሆኑ ወገኖች ማስተላለፍ ጀመርኩ። ይህንን ሁሉ ሳደርግ ታዲያራሴን ላረጋጋበት” 2 ከማለት ያለፈ ሐሳብ መጥቶብኝ አያውቅም፡፡
ጥቂት እንደሰነባበትኩ ግን ከአስገራሚ እውነታዎች ጋር መናበብ ግድ ሆነብኝ፡፡ ለምሳሌም ከተማዋየምስራቅ አፍሪቃ ቲምቡክቱ” 3 የተሰኘችበትን ወርቃማ ዘመን ማሳለፏ፣ 1750ዎቹ መጨረሻ እስከ 1850ዎቹ መጀመሪያ በዘለቀው ዘመን እርሷን ለማየት ከፍተኛ ጉጉት የነበራቸው የአውሮጳ ምሁራን ከተማዋ ያለበችን ቦታ ማወቅ ተስኗቸው መላውን የአፍሪቃ ምድር ሲያስሱት መክረማቸው ወዘተ... ድሮ የማላውቃቸው እውነታዎች ናቸው፡፡ 4
በዚህን ጊዜም ነበርእኔ ተራ ሚኒባስ እየጋለብኩ የገባሁባት ከተማ ዓለምን እንዲህ ጉድ አሰኝታ ነበርን? እንደዚያ ከሆነ ምክንያቱ ምንድነው?” የሚል ሙግት በአዕምሮዬ የተከሰተው፡፡ የዚህን ጥያቄ ምላሸ ሳፈላልግም ዕድለኛ መሆኔ ታወቀኝናራሴን ላረጋጋማለቱን ከነአካቴው ትቼ ይህንን ድርሳን ለመቀመርኒያ” (ልባዊ ውሳኔ) አደረግኩኝ፡፡
***** ***** *******
አዎን! ከታላቋ ከተማ ጋር የተዋወቅኩበት አጋጣሚ የህይወት ጥሪ ከደረሳቸው እድለኞች ጎራ አሰልፎኛል። በዕድለኛነቴም ስለርሷ ላወጋችሁ ነው:: ስለ ትንግርተኛዋ የጥበብ መንደር!
ሀረር! የዕውቀት ሰፈር!.......
ሀረር የተወለድኩባትን ከተማ ገለምሶን ትመስላለች፤ አዲስ አበባን ትመስላለች፤ ድሬ ዳዋን ትመስላለች፡፡ ጅማንና ደሴንም ትመስላለች፡፡ በስነ-ጽሁፍ ብቻ የማውቃቸውን ቃሂራን (ካይሮን) ዲመሽቅን (ደማስቆን) ሎንዶንን፣ሮማን፣ አቴናን፣ ፓሪስን፣ ኒውዮርክን ወዘተትመስላለች። ከአሰላም ሆነ ከነቀምቴ፣ ከጎንደርም ሆነ ከመቀሌ የተገኘ ሰው በሀረር ላይ ሲከትም ተመችቶት የሚኖረው ከተማዋ እንዲህ ሁሉንም መምሰል የምትችልበት በመሆኑ ነው።
መምሰልና መሆን ግን ለየቅል ናቸው። ሀረር ሌሎችን ብትመስልም ራሷን ብቻ ነች፡፡ በሌሎች አካባቢዎች የምታውቋቸውን ነገሮች በሙሉ በሀረርም ለማየት አይቸግራችሁም፡፡ በሀረር የሚገጥማችሁን ተአምር ግን ወዴትም ብትሄዱ ላታገኙት ትችላላችሁ፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ሀረርን የረገጠ ሰው ሁለመናው ወደ አዲስ ሰውነት የሚቀየረው፡፡
***** ***** *******
ሁሉንም እየመሰሉ ራሳቸውን ብቻ ሆነው መገኘት የሚችሉ ከተሞችን ጥሩ!” ብትባሉ በቶሎ የሚታወሷችሁ እነማን ናቸው? የናንተን ምላሽ አላውቅም፡፡ እኔ ግን ሁለት ከተሞችን ልጠራላችሁ እችላለሁ፡፡ አንደኛዋ በጽሁፍ ብቻ የማውቃት በጝዳድ ናት፡፡ ሌላኛዋ ከተማ አሁን የምኖርባት ሀረር ናት፡፡ የሁለቱ መመሳሰል ደግሞ በእጅጉ ይደንቃል፡፡
አዎን! በጝዳድና ሀረር በጣም ይመሳሰላሉ፡፡ በዚህም የተነሳ እህትማማች ከተሞች መሆናቸው በሰፊው ይነገርላቸዋል።5 ይህንንም በጥቂት አብነቶች ላስረዳ፡፡
በጝዳድ የኸሊፋዎች መንበር ነበረች - ሃሩን አል-ረሺድን 6 ያስታውሱ፡፡ ሀረር ደግሞ የአሚሮች መንደር ነበረች - አሚር ኑርን ያስታውሱ። በሌላ በኩል ሁለቱም ከተሞችየአባዲር ከተማበመባል ይታወቃሉ። የሼኽ አባዲር ስም በሁለቱም ከተሞች የተከበረ ነው።7
ሶስተኛው አብነት ደግሞ (ከተሞቹን የሚያመሳስላቸው) ከዓለም አቀፉ አሳሽና ደራሲ ከሰር ሪቻርድ በርተን ጋር ይያያዛል። በርተን በአፍላ የወጣትነት ዘመኑ ላይ ጀብድ የመስራት ስሜት ቢወጥረው አጭቤነትተዳረገና ከርሱ በፊት ያልተሞከሩ አደገኛ ማጭበርበርድርጊቶችን ለመዳፈር ቆረጠ።
በቅድሚያምአፍጋናዊ ሼኽ ነኝየሚል ካባ ደርቦ ወደ መካና መዲና በመግባት 8 እዚያ ያየውን ነገር ሁሉ ለዓለም ህዝብ አስነበበ፡፡ በዚያው እግሩ ወደ አፍሪቃ ምድርም ተሻገረ፡፡የመናዊ ሼኽ ነኝበሚል የማጭበርበሪያ ስልት ወደ ሀረርም ገባና ጓዳዋን መረመረ፡፡ የምርመራውንም ውጤት “First Footsteps in East Africa or the Exploration of Harar” በሚል ርዕስ ስር ለአንባቢያን ላከ።
ሪቻርድ በርተን በሕይወቱ መጨረሻ ላይ በጝዳድንም ጎበኛትና ዝነኛውን “The Book of Thousand Nights and a Night” (ወይንም ደግሞ The Arabian Nights) ለዓለም ህዝብ አበረከተ፡፡ 9 ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሁለቱን መጽሀፍት የሚያነብ ሰው ሀረርና በጝዳድን በደንብ ያውቃቸዋል።
***** ***** *******
ሀረር በነዚህና በሌሎችም ትንግርቶች የተመላች ናት፡፡ እኔም ላለፉት ሶስት ዓመታትዚሸርቂ ኢፍሪቂያ ታዕሊም መርከዝ” 10 ከምትባለው ከዚህች የታሪክና የስልጣኔ አምባ ጋር ከቢርእና አርዳ ዊጅጥምረት መስርቼ አስገራሚዒልሚስሸምት ከርሜአለሁ፡፡ 11
ሀረር የምታስተምረውንማድዲሙሉ በሙሉ ከማጠናቅቅበት ደረጃ ላይ ገና ላይ አልደረስኩም። ስለዚህአርዳ ዊጅሆኜ መሰንበት ግድ ይለኛል። ለአሁኑጢት ከቢርእንድሆን በተፈቀደልኝ መሰረትከቢርካስተማረችኝዒልሚበጥቂቱ እየቆነጠርኩ ላቀብላችሁ ተዘጋጅቻለሁ፡፡ቀለም መስበርደረጃ ላይ ስደርስ የሚሆነውን ደግሞ በጊዜው አጫውታችኋለሁ። ዕድሜና ጤና ይስጠንና!
አፈንዲ ሙተቂ
ሀረር ጌይ
ጥር 2012

የግርጌ ማስታወሻዎች

1. ከርሷ ጋር የተዋወቅኩበት አጋጣሚ ራሱ ያስደንቀኛል፡፡ እርሱን ግን አሁን አላወጋችሁም። በህይወቴ የማልረሳው ትልቅ ምዕራፍ ነው ብዬ ማለፉን እመርጣለሁ::
2. “ራሴን ላረጋጋስል አንዳንድ ጊዜ የሚነሳብኝን የጽሁፍሐራራላስታግስበት ማለቴ ነው፡፡
3. Richard F. Burton First Foot Steps in East Africa, 1856, pp 1
4. ለምሳሌ 19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የታላቋ ብሪታኒያ ምሁራንን ለአዳዲስ አሰሳዎች ሲያሰማራ የነበረው The Royal Geographical Society ሀረር የምትገኝበትን ትክክለኛ ቦታ ለማወቅ የተደረጉ ጥናቶችን በማጠቃለል Extract Report on the Probable Location of Harar በሚል ርዕስ አንድ ጽሁፍ አሳትሞ ነበር:: (The Journal of Royal Geographical Society, Volume 12, 1842) ከላይ በጠቀስኩት የሪቻርድ በርተን መጽሀፍ ውስጥም በሰር ዊሊያም ባርከር የተመራ የብሪታኒያ አገር አሳሾች ቡድን ከአንኮበር ወደ ሀረር ለመድረስ ያደረገው ትግል በባርከር አንደበት ተተርኳል። (Richard F. Burton: ibid pp. 597)
5. አቶ ሑሴን አብዱሰታር፣ ህዳር 2009 ሀረር አቶ አብዱሰመድ ኢድሪስ፣ ታህሳስ 2009 ሀረር አቶ ኢድ ባሻ፣ ጥር 2009 ሀረር
6. ኸሊፋ ሃሩን አል-ረሺድን ከናንተ ጋር ለማስተዋወቅ አልቃጣም፡፡ በርሱና በሀረር አሚሮች መካከል የነበረውን መመሳሰል የሚያስረዳ አንድ አብነት ግን ይኸውላችሁ፡፡
ሃሩን አል-ረሺድ ህዝቡ በአስተዳደሩ ላይ ያለውን አስተያየት ለመስማት ሲፈልግ ምሽት ላይ እንደ በደዊ (የባላገር ዐረብ) ይለባብስና በጝዳድን ከዳር እስከ ዳር ያስሳታል:: የሀረር አሚሮችም እንደ ሃሩን አል-ረሺድ ማንነታቸውን በመደበቅ በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ በምሽት የመዘዋወር ልማድ ነበራቸው፡፡ ለምሳሌ አሚር አህመድና አባቱ አሚር አቡበከር ከተማዋን በምሽት ያስሷት እንደነበር ሪቻርድ በርተን ነግሮናል። (Richard F. Burton: ibid: 335)
7. ሼኽ አባዲር በከተማዋ ህዝብ ዘንድ በጣም የሚታወቁበትን ገድል በዚሁ መጽሀፍ ውስጥ ታገኙታላችሁ።
8. በርተን በጉብኝቱ ማግስት የጻፈው Personal Narrative of a Pilgrimage to Al-Madinah and Meccah (1850) ከፍተኛ እውቅናን አትርፎለት ነበር፡፡ እርሱ ግን በአውሮጳ አደባባዮች ያገኘውን ዝና ከማጣጣም ይልቅ ሌላኛዋን አስደናቂ ከተማ ለመጎብኘት ወደ ሀገራችን ምድር አቀና፡፡ ከዚያም በለመደው የማጭበርበሪያ ስልት ወደ ሀረር ገብቶ ያየውንና የሰማውን ሁሉ “First Footsteps in East Africa” በሚባለው መጽሀፍ ውስጥ ጻፈው፡፡ ታዲያ አሁን የምታነቡትን መጽሀፍ ሳዘጋጅ የመጀመሪያ ደረጃ ምንጭ ሆነው ከረዱኝ ሰነዶች መካከል አንዱ ይህ የበርተን መጽሀፍ እንደሆነ ወደፊት ታዩታላችሁ፡፡
9. “አልፍ ለይላ ለይላየሚለውን የመጽሀፉን የዐረብኛ ስም ነው “The Book of Thousand Nights and a Night” በማለት የተረጎመው፡፡ አንባቢያን መጽሀፉን በደንብ የሚያውቁት ግን The Arabian Nights በሚለው ስሙ ነው፡፡ የዚህ መጽሐፍ የአማርኛ ትርጉም (“አንድ ሺህ አንድ ሌሊትየሚል ርእስ ያለው) ከእንግሊዝኛው የተቀዳ የትርጉም ትርጉም ቢሆንም በዐረብኛው መጽሐፍ የሚገኘውን ድባብ አልለቀቀም፡፡
10. “የምስራቅ አፍሪቃ የትምህርት ማዕከልማለት ነው-በጌይ ሲናን (የሀረሪ ቋንቋ)፡፡ ሀረር እንዲህ የተባለችው በወርቃማው ዘመኗ ነው፡፡ ሪቻርድ በርተን ይህንን ሲገልጽ “it shares with Zebid in Yemen, the reputation of being an Alma Mater” ብሎ ነበር (Richard F. Burton: ibid, pp-323).
11. በሀረር ባህላዊ ትምህርት ቤቶች መምህሩከቢርይባላል፡፡ ተማሪው ደግሞአርዳ ዊጅተብሎ ይጠራል፡፡ መምህሩ ሲያስተምር ከተማሪዎቹ ውስጥ ተመርጦ በሚሾምናጢት ከቢርበሚባል ረዳት መምህር ይታገዛል። በትምህርት የሚገኝ ማንኛውም ዕውቀትዒልሚይሰኛል፡፡ ትምህርት ቤቱቁርኣን ጌይተብሎ ይጠራል። ትምህርት የሚጠናቀቅበት (የምረቃ) ደረጃ ደግሞቀለም መስበርበመባል ይታወቃል።

የ“ሀረር ጌይ” መግቢያ- በረዳት ፕሮፌሰር አሕመድ ዘከሪያ


በረዳት ፕሮፌሰር አሕመድ ዘከሪያ
( አፈንዲ ሙተቂ: ሀረር ጌይ- የአስገራሚዋ ከተማ የኢትኖግራፊ ወጎች: ገጽ V )

ቀስ በቀስ መጣጥፍ ወደ መጽሐፍ በሚቀየርበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ መጣጥፍ እንደ አንድ የስነ-ጽሁፍ ዘውግ መታየትም ጀምሯል፡፡ መስፍን ሀብተማሪያም፣ ስብሐት ገ/እግዚአብሔር እና ሌሎችም አንጋፋ ደራሲያን ፍሬያማ የወግ መንገድን አሳይተውናል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ደራሲያንም በተለያየ አቅጣጫና ትኩረት የአንጋፋዎቹን ፈለግ በመከተል ላይ ናቸው፡፡
   ይህንን የወግ ዘውግ ከተከተሉት አንዱ አፈንዲ ሙተቂ ነው፡፡ ይህ ወጣት ደራሲ እጆቻቸውን በጋዜጣ ዓምድ እንዳፍታቱት ሌሎች በርካታ ጸሐፊዎቻችን እጅግ በሳል የሆነ የወግ ጸሀፊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
   አፈንዲ ስለሀረር ሲጽፍ በተወሰነ መልኩ የስብሐትን የአጻጻፍ ስልት የተከተለ ይመስላል፡፡ ሆኖም ይዞት የመጣው የራሱን የተለየ ዘይቤ (style) ነው፡፡ በተጨማሪም የአካባቢው ተወላጅ በመሆኑና በሀረር ከተማም ከስብሐት የአስራ አምስት ቀናት ቆይታ በላይ ስለኖረ የአካባቢውን ቋንቋ በላቀ ደረጃ እንድናጣጥም አድርጎናል፡፡ በተለይም የሰዓሊ ጥበበ ተርፋአጃዒብ ነው አባባል አፈንዲ ከደራሲ ስብሐት ገ/እግዚአብሄር በላይ ለኛ በሚሰማ መልኩ አስተላልፏል፡፡  እንደ ቀሽጢበዘበዛራሓ፣ ወዘተ የመሳሰሉትንም በማከል መጽሀፉን ሀረር ላይ ሆነን የምናነበውን ምናባዊ ፍስሐ ጨምሮልናል::
   በቅርብ ጊዜያት በሀረር ላይ ያተኮሩ ሶስት መጽሐፍት ወጥተዋል፡፡ አንደኛው መጽሐፍ አብዱላሂ ቡህ የጻፈው ሀረሪና የሀረር ከተማ ታሪክ ሲሆን በአማርኛ ቋንቋ የታዋጣለት የታሪክ፣ የባህልና የቋንቋ ቅኝት ነው፡፡ ደራሲው የጽሁፍና የቃል መረጃዎችን በተገቢ ሁኔታ አገናዝቦ የሀረርን ታላቅነት አስረድቶናል፡፡
  ሁለተኛው መጽሐፍ የመፍቱህ ዘከሪያ ሀረር ጁገል- የከተማ ባህል መፍለቂያ ነው፡፡ ይህም ስራ ስለሀረር ቅርሶች አስፈላጊውን መረጃ ያቀብለናል፡፡ መጽሐፉ በይዘቱ ማለፊያ ቢሆንም ሊታረሙ የሚገቡ ህጸጾች ይገኙበታል፡፡
   ሶስተኛው የሀረሪ አመጽ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በተለያዩ ደራሲያን የተጻፉ ጥናታዊ መጣጥፎችን ያካተተ ነው፡፡ በተወሰነ መልኩም ታሪክ ቀመስ ነው፡፡
   አሁን በእጃችን ላይ ያለው ድርሰት ከቀደሙት መጽሐፍት በአቀራረቡም ሆነ በይዘቱ በብዙ መልኩ የሚለይ ከመሆኑም በላይ ባለፉት መጽሐፍት ያላነበብናቸውን ተጨማሪ ግንዛቤዎችና መረጃዎች ይዞልን የቀረበ ነው፡፡ በጣም የሚገርሙና አዳዲስ የሆኑ የሀሳብ አቅጣጫዎችንም ያሳየናል፡፡ የአጭር የወግ አጻጻፍ ዘውግን የሚከተል በመሆኑም ብዙ ሳይደክመን የተለያዩ ቁም ነገሮችን ያስጨብጠናል፡፡
   አፈንዲ ያጠናው ኢኮኖሚክስ ነው፡፡ ከኢኮኖሚክሱ ዓለም ያገኘውን ልምድ ለታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ ጥናት በተገቢው መልኩ አውሎታል፡፡ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቁጥር ቀመስ እንደመሆኑ መጠን አፈንዲም empirical data ፍለጋ ውስጥ ይዞን ይነጉዳል፡፡ ያነባል፤ ይጠይቃል፤ ይመራመራል፤ በመጨረሻም አሳማኝ አማራጮቹን በተዋበ ቋንቋ ያቀርብልናል፡፡ እርግጠኛ ነኝ! ብዙ ምሽቶችን ያለ እንቅልፍ አሳልፏል፡፡ አማራጮችን ሲያወጣና ሲያወርድ፣ ሲያገናዝብ፣ ሲተነትን
  አፈንዲ ስራው የተዋጣለትና ይበል ብለን የምናደፋፍረው አፍለኛ ደራሲ ነው፡፡ ተከታይ ሥራዎቹንም እንድናጣጥም የነገ ሰው ይበለን፡፡
ረ/ፕሮፌሰር አሕመድ ዘከሪያ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም
Note:
1.     The Book will be on sale starting from May 1/2012. (Price 75 Birr in Ethiopia and 35 USD abroad)
2.    Harar Gey is the first book to be produced by Harar Ethnographic Research Project which focuses on the peoples of East Ethiopia (especially the city of Harar, the Harari people and the Oromo of Hararghe).