በረዳት ፕሮፌሰር አሕመድ ዘከሪያ
( አፈንዲ ሙተቂ: “ሀረር ጌይ- የአስገራሚዋ ከተማ የኢትኖግራፊ ወጎች” : ገጽ V )
ቀስ
በቀስ መጣጥፍ ወደ መጽሐፍ በሚቀየርበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ መጣጥፍ እንደ አንድ የስነ-ጽሁፍ ዘውግ መታየትም ጀምሯል፡፡ መስፍን ሀብተማሪያም፣ ስብሐት ገ/እግዚአብሔር እና ሌሎችም
አንጋፋ ደራሲያን ፍሬያማ የወግ መንገድን አሳይተውናል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ደራሲያንም በተለያየ አቅጣጫና ትኩረት የአንጋፋዎቹን
ፈለግ በመከተል ላይ ናቸው፡፡
ይህንን የወግ ዘውግ ከተከተሉት አንዱ አፈንዲ ሙተቂ ነው፡፡ ይህ ወጣት ደራሲ እጆቻቸውን በጋዜጣ ዓምድ እንዳፍታቱት ሌሎች በርካታ ጸሐፊዎቻችን
እጅግ በሳል የሆነ የወግ ጸሀፊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
አፈንዲ
ስለሀረር ሲጽፍ በተወሰነ መልኩ የስብሐትን የአጻጻፍ ስልት የተከተለ ይመስላል፡፡ ሆኖም ይዞት
የመጣው የራሱን የተለየ ዘይቤ (style) ነው፡፡ በተጨማሪም የአካባቢው ተወላጅ በመሆኑና በሀረር ከተማም ከስብሐት የአስራ አምስት
ቀናት ቆይታ በላይ ስለኖረ የአካባቢውን ቋንቋ በላቀ ደረጃ እንድናጣጥም አድርጎናል፡፡ በተለይም የሰዓሊ ጥበበ ተርፋን “አጃዒብ
ነው” አባባል አፈንዲ
ከደራሲ ስብሐት ገ/እግዚአብሄር በላይ ለኛ በሚሰማ መልኩ አስተላልፏል፡፡
እንደ “ቀሽጢ”፣ “በዘበዛ”፣ “ራሓ”፣
ወዘተ… የመሳሰሉትንም በማከል መጽሀፉን ሀረር ላይ ሆነን የምናነበውን ምናባዊ ፍስሐ ጨምሮልናል::
በቅርብ ጊዜያት በሀረር ላይ ያተኮሩ ሶስት መጽሐፍት ወጥተዋል፡፡ አንደኛው መጽሐፍ አብዱላሂ ቡህ የጻፈው “ሀረሪና የሀረር ከተማ ታሪክ” ሲሆን በአማርኛ ቋንቋ የታዋጣለት የታሪክ፣
የባህልና የቋንቋ ቅኝት ነው፡፡ ደራሲው የጽሁፍና የቃል መረጃዎችን በተገቢ ሁኔታ አገናዝቦ የሀረርን ታላቅነት አስረድቶናል፡፡
ሁለተኛው መጽሐፍ የመፍቱህ ዘከሪያ “ሀረር ጁገል- የከተማ ባህል መፍለቂያ” ነው፡፡ ይህም ስራ ስለሀረር ቅርሶች አስፈላጊውን መረጃ ያቀብለናል፡፡ መጽሐፉ በይዘቱ
ማለፊያ ቢሆንም ሊታረሙ የሚገቡ ህጸጾች ይገኙበታል፡፡
ሶስተኛው “የሀረሪ አመጽ”
ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በተለያዩ ደራሲያን የተጻፉ ጥናታዊ መጣጥፎችን ያካተተ ነው፡፡ በተወሰነ መልኩም ታሪክ ቀመስ ነው፡፡
አሁን በእጃችን ላይ ያለው ድርሰት ከቀደሙት መጽሐፍት በአቀራረቡም ሆነ
በይዘቱ በብዙ መልኩ የሚለይ ከመሆኑም በላይ ባለፉት መጽሐፍት ያላነበብናቸውን ተጨማሪ ግንዛቤዎችና መረጃዎች ይዞልን የቀረበ
ነው፡፡ በጣም የሚገርሙና አዳዲስ የሆኑ የሀሳብ አቅጣጫዎችንም ያሳየናል፡፡ የአጭር የወግ አጻጻፍ ዘውግን የሚከተል በመሆኑም
ብዙ ሳይደክመን የተለያዩ ቁም ነገሮችን ያስጨብጠናል፡፡
አፈንዲ ያጠናው
ኢኮኖሚክስ ነው፡፡ ከኢኮኖሚክሱ ዓለም ያገኘውን ልምድ ለታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ ጥናት በተገቢው መልኩ አውሎታል፡፡ የኢኮኖሚክስ
ትምህርት ቁጥር ቀመስ እንደመሆኑ መጠን አፈንዲም empirical data ፍለጋ ውስጥ ይዞን ይነጉዳል፡፡ ያነባል፤ ይጠይቃል፤
ይመራመራል፤ በመጨረሻም አሳማኝ አማራጮቹን በተዋበ ቋንቋ ያቀርብልናል፡፡ እርግጠኛ ነኝ! ብዙ ምሽቶችን ያለ እንቅልፍ
አሳልፏል፡፡ አማራጮችን ሲያወጣና ሲያወርድ፣ ሲያገናዝብ፣ ሲተነትን…
አፈንዲ
ስራው የተዋጣለትና ይበል ብለን የምናደፋፍረው አፍለኛ ደራሲ ነው፡፡ ተከታይ ሥራዎቹንም እንድናጣጥም የነገ ሰው ይበለን፡፡
ረ/ፕሮፌሰር አሕመድ ዘከሪያ
አዲስ
አበባ ዩኒቨርሲቲ
የኢትዮጵያ
ጥናትና ምርምር ተቋም
Note:
1.
The
Book will be on sale starting from May 1/2012. (Price 75 Birr in Ethiopia and
35 USD abroad)
2. “Harar Gey” is the first book to be
produced by “Harar Ethnographic Research Project” which focuses on the peoples of East Ethiopia (especially the
city of Harar, the Harari people and the Oromo of Hararghe).