ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
------
እነሆ ስለሒሳብና ስለ እውቁ የሒሳብ ጀግና በጥቂቱ ልናወጋችሁ ነው፡፡ ጀግናችን ፎቶግራፍ ከተፈጠረበት ዘመን አስቀድሞ የኖረ በመሆኑ ፎቶውን ልናሳያችሁ አንችልም መቼስ!…. በምስሉ ላይ የምትመለከቱት የሒሳቡ ጀግና የተወለደበት 1200ኛ ዓመት ሲከበር ታላቋ የሶቪየት ህብረት ያሳተመችውን የመታሰቢያ ቴምበር ነው፡፡ ሰውየውን ከሶቪየቶች ጋራ ምን አገናኘው? ከወደታች እንመጣበታለን፡፡ አሁን ወጋችንን በመሰረታዊ ጉዳዮች እንጀምር፡፡
*****
እስቲ ከዜሮ ጀምሩና በቅደም ተከተል የሚመጡትን ቁጥሮች ጻፉ፡፡ 1፣ 2፣ 3፣ ….. አስር ስትደርሱ ሌላ ቁጥር ለማግኘት አትችሉም አይደል?… አዎን! አስር ለማለት ከፈለጋችሁ አንድና ዜሮን ጎን ለጎን በማድረግ ትጽፋላችሁ፡፡ ሌሎቹንም ቁጥሮች ለመጻፍ ከፈለጋችሁ በነዚህ ቁጥሮች ትጠቀማላችሁ፡፡
በጥንት ዘመን ግን እንዲህ ዓይነት ነገር አልነበረም፡፡ የጥንት ግብጻዊያን ይገለገሉበት በነበረው የሄሮግሊፍ (hieroglyphic) አጻጻፍ ሁሉንም ነገር በተለየ ምስል ስለሚመስሉ የሚጠቀሙባቸው ቁጥሮች ብዛትም ማለቂያ አልነበረውም፡፡ ሮማዊያን በበኩላቸው ፊደልን እንደ ቁጥር ሲጠቀሙ ነው የኖሩት፡፡ ይህኛው የቁጥር ዘዴም ወጥ የሆነ ቀመር ስለሌለው ትልልቅ ቁጥሮችን ለመጻፍ ይቅርና በመቶና በአንድ ሺህ መካከል ያሉ ቁጥሮችን እንኳ ሳይደናግሩ ሊጽፉበት ይከብዳል፡፡ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ያሉ የቁጥር ዘዴዎችም (numeration systems) ተመሳሳይ ጉድለቶች አሏቸው፡፡ በመሆኑም ከጭንቀት ለመገላገል የሚፈልግ ሰው በመግቢያዬ ወደጠቀስኩት የአቆጣጠር ዘዴ መመለሱ የግድ ነው፡፡
ይህ ዘዴ “የሂንዱ-ዐረብ የቁጥር ዘዴ” (Indo-Arabic Numeration System) ይባላል:: ከስያሜው እንደምትረዱት “ህንድ”ና “ዐረቢያ” በጋራ በመሆን ለዓለም ህዝብ ያበረከቱት ታላቅ ገጸ-በረከት ነው፡፡ የቁጥሮቹ መሰረት የሆኑት ምልክቶች የተወጠኑት ከክርስቶት ልደት በፊት በሀገረ-ህንድ ነው፡፡ እነዚያ ምልክቶችም 1-እስከ 9 ያሉትን ቁጥሮች ብቻ የሚወክሉ ነበሩ፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመጀመሪያው ምእተ- ዓመት ምልክቶቹ ከህንድ ተሻግረው ወደ ፋርስ፣ ግብጽ፣ ሜሶጶጣሚያ፣ ሶሪያና ዐረቢያ ገቡ፡፡ በነዚህ ሀገራት የሂሳብ ሊቃውንትና በነጋዴዎች እጅ ሲሸከረከሩም ቆዩ፡፡ በ800 ዓ.ል. ገደማ ግን አንድ ሰው ከባግዳድ ተነሳና ምልክቶቹን በማሻሻል አሁን ያሉትን ቁጥሮች አስገኘ፡፡
ታዲያ ይህ ሰው ቁጥሮችን በማስገኘቱ ብቻ አላበቃም፡፡ ከዚያ በፊት የማይታወቁ የሂሳብ ጽንሰ-ሐሳቦችንም ለዓለም አስተዋውቋል፡፡ ከነዚያ ጽንሰ-ሐሳቦች መካከል የመጀመሪያው “the concept of Zero” ይባላል፡፡ ሰውዬው ዘጠኙ ቁጥሮች በትክክል ሊሰሩ የሚችሉት ዜሮ ከታከለችባቸው ብቻ መሆኑ ገብቶታል፡፡ በዚህም መሰረት ዜሮን በራሱ በመፈልሰፍ በአስሩ ቁጥሮች ሁሉንም ዐይነት “ህልቅ” (number) ለመጻፍ እንደሚቻል አሳይቷል፡፡ በተጨማሪም በቁጥሮቹ በትክክል ለመጠቀም ከተፈለገ የሂሳቡ ዓምድ “አስር” (base ten) መሆን እንዳለበት አስገንዘቧል (ከዚያ በፊት ሂሳቡ ወጥ ዓምድ አልነበረውም፡፡ ግሪኮች አስራ ሁለትን ወይንም “ደርዘን”ን ነበር እንደ ዓምድ የሚጠቀሙት፡፡ ለባቢሎኒያ እና ለአሶሪያ ሰዎች ደግሞ የሂሳቡ ዓምድ “ስድሳ” ቁጥር ነበረ)፡፡
*****
ለጥንት ሰዎች ሂሳብ ማለት ሁለት ነገር ነው፡፡ አንደኛው በየቀኑ ነገሮችንና የምንደምርበት፣ የምንቀንስበት፣ የምናባዛበትና የምንቀንስበት መሰረታዊው የሂሳብ ዘርፍ ነው፡፡ ይህም “አርቲሜቲክ” ይባላል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ስፋት፣ ርዝመት፣ ወርድ፣ መጠነ ዙሪያ፣ ቁመት ወዘተ የመሳሰሉትን ለመስፈር የምንጠቀምበት “ጂኦሜትሪ” ነው፡፡
ታዲያ ከላይ የጠቀስነው የባግዳዱ ሰውዬ ከሁለቱ የሂሳብ ዘርፎች ወጣ በማለት መመራመር ጀመረ፡፡ የምርምሩን ውጤትም “ሒሳቡል ጀብር ወል-ሙቃበላ” በሚል ርዕስ አሳተመ፡፡ መጽሐፉ በልዩ ልዩ ምሁራን እጅ ሲገባም ጥንት ያልነበሩ የሂሳብ ስልቶችን፣ ስሌቶችንና ዘዴዎችን አጭቆ የያዘ አዲስ የሂሳብ ዘርፍ እንደፈጠረ ታወቀለት፡፡ በመሆኑም አዲሱ የሒሳብ ዘርፍ በመጽሐፉ ስም “ሒሳቡል-ጀብር” ተብሎ ተሰየመ፡፡ መጽሐፉ ወደ ላቲን ሲተረጎም ደግሞ ስያሜው “አልጄብራ” ተብሎ ተቀየረ፡፡
*****
ያ የሒሳብ ሊቅ “ሙሐመድ ኢብን ሙሳ” ይባላል፡፡ የተወለደውና አብዛኛውን ዘመኑን ያሳለፈው በአሁኗ የኢራቅ መዲና በባግዳድ ውስጥ ነው፡፡ ይሁንና ወላጆቹ “ኸዋሪዝም” ከምትባለው የመካከለኛው እስያ ክፍለ ሀገር (በአሁኗ ኡዝቤኪስታን ውስጥ የምትገኝ) ወደ ባግዳድ የመጡ በመሆናቸው ራሱን ሲጠራ “አል-ኸዋሪዝሚ” በሚል ቅጥያ በስሙ ላይ ይጨምር ነበር፡፡ የዓለም ህዝብም እርሱን በደንብ የሚያውቀው በተጸውኦ ስሙ ሳይሆን በዚሁ ቅጥያ ነው፡፡ የሒሳብ ሊቃውንት በበኩላቸው ስራዎቹ ዘወትር ይታወሱ ዘንድ “አልጎሪዝም” (algorithm) የተባለውን የስሌት ዘዴ በስሙ ሰይመውለታል፡፡
አል-ኸዋሪዝሚ በመላው ዓለም የተከበረ ምሁር ነው፡፡ በዓለም ታሪክ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ ናቸው ከሚባሉት 100 ሳይንቲስቶች መካከልም ስሙ አለ፡፡ በዚህም የተነሳ እርሱ የተወለደባት ኢራቅ፣ ለተወሰነ ጊዜ የኖረባት ኢራን እና ወላጆቹ የተገኙባት ኡዝቤኪስታን “የኔ ነው” በሚል ይወዛገቡበታል፡፡ እንግዲህ የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት በምስሉ ላይ የምትመለከቱትን የመታሰቢያ ቴምብር ያሳተመችው “አል-ኸዋሪዝሚ የኔ ነው” በሚል መነሻ ነው (ኡዝቤኪስታን ከ1924 እስከ 1991 የሶቪየት ህብረት አካል እንደነበረች አስታውሱ)፡፡
ቢሆንም አል-ኸዋሪዝሚን የአንድ ሀገር ብሄራዊ ጀግና ብቻ አድርጎ ማየቱ ለዚህ ዘመን ሰው አይስማማም፡፡ ስራው መላውን ዓለም ያዳረሰ በመሆኑ የሁሉም ህዝቦች ብሄራዊ ሀብት ተደርጎ ቢታይ ነው የሚመረጠው፡፡
-----
አፈንዲ ሙተቂ
ህዳር 8/2007
በገለምሶ ከተማ ተጻፈ፡፡
---