ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
በ1988 የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና (ESLCE) እንደወሰድኩ ነው፡፡ ዕለቱ ከሚያዚያ ወር መአልት አንዱ
መሆኑ ይታወሰኛል፡፡ በዚያች ዕለት የጀርመን ድምጽ ራድዮ ከቀደሙት የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለየ ዓላማን ያነገበ ድርጅት መቋቋሙን
ዘገበ፡፡ የፓርቲው መስራች የሆኑት ግለሰብ የተናገሩትንም ቀንጨብ አድርጎ አስደመጠን፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ሐሳባቸውን የሰጡ ግለሰቦች “አዲሱን ድርጅት የመሠረቱት ግለሰብ
ለኦሮሞ ህዝብም ሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች አዲስ ራዕይ ያላቸው ናቸው” ማለታቸውንም ሰማን፡፡
በዚያች ዕለት ድምጻቸውን የሰማናቸው ግለሰብ የያኔው ረ/ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ የአሁኑ ዶክተር መረራ ጉዲና
ነበሩ፡፡ እርሳቸው የመሠረቱት ድርጅት ደግሞ “የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረስ” ይባል ነበር (ከ1998 ወዲህ “ኦህኮ” ተብሎ ነበር፤
ከጥቂት ዓመታት በፊት ደግሞ የቀድሞው ኦፌዴን እና “ኦህኮ” አንድ ላይ ተዋህደው “ኦፌኮ” የሚባል ድርጅት ፈጥረዋል)፡፡
በዕለቱ በተላለፈው የሬድዮ ዘገባ ዶ/ር መረራ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ነገር “መገንጠል ከኦሮሞ ህዝብ
ጥያቄ ጋር አይሄድም፤ የኦሮሞ ህዝብ በስፋቱና በብዛቱ ልክ በኢትዮጵያ ፖለቲካና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ውስጥ ሁነኛ ስፍራ እንዲኖረው
መታገል ነው የሚሻለው” የሚል ነበር፡፡ ይህ የዶ/ር መረራ የፖለቲካ አስተርዮ በርካታ ደጋፊ ያፈረላቸውን ያህል ብዙ ተቃዋሚዎችም
አስነስቶባቸዋል፡፡ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በ1990 እስኪቀሰቀስ ድረስም ለፖለቲካ የቀረቡ የሀገራችን ዜጎች የሚራኮቱበትና የሚቆራቆሱበት
ዋነኛ አጀንዳም እርሱ ነው፡፡ በወቅቱ ከፍተኛ አንባቢ የነበራቸው የግል ጋዜጦችና መጽሔቶችም ለዶ/ር መረራ ከፍተኛ ሽፋን ይሰጧቸው
ነበር፡፡
በዚያ ወቅት ዶ/ር መረራ ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠማቸው ከኦሮሞ ሊሂቃን እና መገንጠልን ከሚደግፉ የኦሮሞ የፖለቲካ
ድርጅቶች እንደነበረ ይታወቃል፡፡ በዘመኑ የኦሮሞን የፖለቲካ መድረክ (Spectrum) ተቆጣጥሮት የነበረው “የራስን ዕድል በራስ
መወሰን እስከ መገንጠል” የሚለው አማራጭ ነበር፡፡ ስለሆነም ከዚህ የተለየ አማራጭ ይዞ ወደ ኦሮሞ ፖለቲካ በሚቀላቀል ግለሰብም
ሆነ ድርጅት ላይ ተቃውሞ ይቀርብበት ነበር፡፡ በሂደት ግን በዶ/ር መረራ የተቋቋመው ፓርቲ የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር ከመታገል
ውጪ ሌላ አጀንዳ እንደሌለው በርካቶች ተረድተዋል፡፡ ዶ/ር መረራ የለኮሱት ርእዮት ለኦሮሞ ህዝብ መቅረብ ካለባቸው አማራጮች ቀዳሚው
እንደሆነም ተገንዝበዋል፡፡
----------
አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ዶ/ር መረራ ጉዲናን በመልክ ያወቃቸው የ1992 ሀገር አቀፍ ምርጫን በማስመልከት
የተዘጋጀው የፓርቲዎች ክርክር ተቀድቶ በቴሌቪዥን ሲተላለፍ ነው፡፡ ክርክሩ በሁለት ወቅቶች (በታሕሳስና ሚያዚያ 1992) ነበር
የተካሄደው፡፡ ዶ/ር መረራ አይረሴ (classic) ሆነው የተመዘገቡላቸውን “የሚበላውን ያጣ ህዝብ መሪዎቹን ይበላል” እና “የኢህአዴግን
ልብ እንኳን ሰው እግዚአብሄርም አያውቀውም” የተሰኙ ታዋቂ አባባሎችን የተናገሩት በነዚያ የክርክር መድረኮች ላይ ነበር፡፡
በኔ እይታ ዶ/ር መረራ እጅግ ውጤታማና ማራኪ ክርክር ያካሄዱት ያኔ ነው፡፡ በተለይም ዶ/ር መረራ በሚያዚያ-1992
በተካሄደው ክርክር ያሳዩት ብቃት የተለየ ነው፡፡ በውይይቱ ወቅት የገዥውን ፓርቲ ጥፋቶችና ድክመቶች እየነቀሱ በማውጣትም ሆነ የራሳቸው
ፓርቲ የሚያራምደውን ዓላማ በማብራራት ረገድ ከሁሉም ተከራካሪዎች በልጠው ታይተዋል፡፡ በንግግራቸው መሀል የሚወረውሯቸው ቀልዶችና
ሽሙጦችም ከመሬት ጠብ የማይሉ ነበሩ፡፡ በጥቂቱ ብናስታውሳቸው አይከፋም፡፡
በሚያዚያ-92 በተካሄደው ክርክር ገዥውን ፓርቲ ወክለው የተገኙት ወይዘሮ ገነት ዘውዴ ለአርባ ደቂቃ ያህል
“ኢህአዴግ ያስገኛቸው የልማት ውጤቶች” የሚል ይዘት ያለውን ንግግር አቀረቡ፡፡ ከርሳቸው በማስከተልም የመናገሩ ተራ የዶ/ር መረራ
ጉዲና ሆነ፡፡ ታዲያ ዶ/ር ንግግራቸውን የጀመሩት እንዲህ ነበር፡፡
“አፄ ኃይለ-ሥላሴ ‘የምንወደውና የሚወደን ህዝባችን’ እያሉ የኢትዮጵያን ዕድገት በ40 ዓመት ወደ ኋላ ጎተቱት፡፡
ደርግ ደግሞ ‘አስራ ሰባት የትግልና የድል ዓመታት’ እያለ ኢትዮጵያን ከሶስት ደሀ የዓለም አገሮች አንዷ አደረጋት፡፡ ኢህአዴግም
በተራው “አንጸባራቂ የልማት ድሎች” እያለን ኢትዮጵያን የዓለም ቁጥር አንድ ደሀ ሀገር አደረጋት”
(በአዳራሹ የነበረው የክርክሩ ታዳሚ ሳቀ፡፡ ዶ/ር መረራም ፈገግ አሉ፡፡ ትንፋሽ ከወሰዱ በኋላ ደግሞ ንግግራቸውን
እንዲህ በማለት ቀጠሉ)
“ቢሆንም ኢህአዴግ የወሰደው እርምጃ ደግ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም “ቀኝ ኋላ ዙር” በተባለ ጊዜ በኢኮኖሚያችን
ከዓለም አንደኛ እንሆናለን”
(አዳራሹ በድጋሚ በሳቅ ተናወጠ፡፡ ክርክሩን በዳኝነት ይመሩ የነበሩት ዶ/ር ገብሩ መርሻ እና በሀገር ሽማግሌነት
የተጋበዙት ደራሲ ማሞ ውድነህ ጭምር ይስቁ እንደነበረ አስታውሳለሁ)፡፡
-------
ዶ/ር መረራ በዚያ የክርክር መድረክ ላይ አጽንኦት የሰጡት አንዱ ጉዳይ “ብሄራዊ እርቅ” ነው፡፡ በወቅቱ የነበሩት
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብሄራዊ እርቅን የሚደግፉ ሲሆን እርቁን የሚገፋው ኢህአዴግ ብቻ ነበር፡፡ ይህንኑ በማስመልከት ዶ/ር መረራ በክርክሩ
ላይ የሚከተለውን ተናግረዋል፡፡
“አንድ የኦሮሞ ህዝብ ተረት “Waraabeessi balleessaa isaa waan beekuuf jecha
halkan dukkana deema” ይላል፡፡ “ጅብ ያጠፋውን ነገር ስለሚያውቅ በጭለማ ይጓዛል” ማለት ነው፡፡ ኢህአዴግም የብሄራዊ
እርቅ ጥሪን የሚገፋው ያጠፋውን ስለሚያውቅ ነው፡፡
(ሌላ ሳቅ አዳራሹን ደበላለቀው፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና የተናገሩት የኦሮምኛ ተረትም በሳምንቱ የወጡት ጋዜጦች
ዐቢይ ርእስ ለመሆን በቃ)፡፡
-------
በዚያ የECA አዳራሽ “ተቃዋሚዎች የሰነዘሩትን ሐሳብ እንዲሞግቱ” በሚል የኢህአዴግ ትልልቅ ካድሬዎች ለአምስት
ደቂቃ ያህል እንዲናገሩ ይፈቀድላቸው ነበር፡፡ ከነዚያ ካድሬዎች መካከልም አንዳንዶቹ ስሜታዊ ይሆኑና የተቃዋሚ መሪዎችን በኃይለ-ቃል
እስከ መወረፍ ይደርሱ ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ ፈርጅ የተከወነ አንድ ነገር ዘወትር አይረሳኝም፡፡ እንዲህ ነው፡፡
ኦህዴድን ወክለው በአስረጅነት ከተገኙት ባለስልጣናት አንዱ የነበረው አቶ ዮናታን ዲቢሳ “ድርጅታችን ያስገኘው
የልማት ውጤት” ያለውን መረጃ ስሜታዊ በሆነ መልኩ አቀረበ፡፡ በማስከተልም “ረ/ፕሮፌሰር መረራን የመሳሰሉ ሰዎች ግን ኦህዴድን
እንደተለጣፊ ድርጅት ነው የሚያዩት” የሚል ክስ ሰነዘረ፡፡ ዶ/ር መረራም ለአቶ ዮናታን መልስ ሲሰጡ እንዲህ በማለት ጀመሩ፡፡
“እኔ የኦሮሞን ልጅ ተለጣፊ ብዬ አላውቅም፡፡ ምናልባት አቶ ዮናታን ኦነግ የሚላቸውን ነገር ይዘው ይመስለኛል
በዚህ የሚከሱኝ”
በማስከተልም ዶ/ር መረራ ለአቶ ዮናታን የሚከተለውን ምላሽ ሰጡ፡፡
“ቢሆንም ግን የኦህዴድ ሰዎች ምስጋና አታብዙ! እባካችሁ ከአቶ ሐሰን ዓሊ ተማሩ!! እንደምታውቁት ከሐሰን
ዓሊ በላይ እኔ ነኝ ያለ የኦህዴድ ካድሬና የስርዓቱ ደጋፊ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ወደ አሜሪካ ኮብልሎ “እንኳንስ ህዝቡ እኔ
ራሴ ነፃነት አልነበረኝም” እያለ ነው፡፡ ስለዚህ ለነገው መንገዳችሁ ስትሉ ምስጋና አታብዙ”
ዶ/ር መረራ ይህንን ተናግረው ዓመት እንኳ ሳይሞላ ነበር አቶ ዮናታን ዲቢሳ መኮብለሉ የተሰማው፡፡ በሚያዚያ
1992 በተዘጋጀው የክርክር መድረክ ላይ በልበ ሙሉነት ሀገር ሲያስተዳድር እንደነበረ ለማስረገጥ ያልጣረውን ያህል ባለፉት 16
ዓመታት ግን “የኦህዴድ ገመና” ያለውን ሁሉ ሲዘከዝክ ከርሟል፡፡ ዶ/ር መረራ በመድረኩ ላይ የሰጡት መልስ አንቅቶት ከሀገር ጠፍቶ
ይሆን? ምክንያቱ አልታወቀም፡፡ አጋጣሚው ግን የሚረሳ አይደለም፡፡
------
ዶ/ር መረራ በምርጫ-97 ወቅት በተካሄዱት ክርክሮችም ከፍተኛ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ ዶክተሩ በነዚያ መድረኮች
ላይ ካሳዩት ገቢሮች መካከል ብዙዎች የሚያስታውሱት ከአባዱላ ገመዳ ጋር ያደረጉትን ፍጥጫ ነው፡፡ ዶ/ር መረራ በመድረኩ ላይ መናገር
የጀመሩት አባዱላን እንዲህ በመተረብ ነበር፡፡
“አቶ አባዱላ! መቼም “ጄኔራል” የሚል ማዕረግ ነበርዎት፡፡ ያ ማዕረግ ከብዙ ልፋት በኋላ የተሰጥዎት ስለሆነ
መከበር አለበት፡፡ ስለዚህ ጄኔራል ብዬ ብጠራዎት እንዳይከፋዎት”
(ሁሉም ተከራካሪ ሳቀ፡፡ በጣም የሳቁት ደግሞ አባዱላ ገመዳ ራሳቸው ናቸው)፡፡
በዚህ መድረክ ላይ አባዱላ ገመዳ “በዶ/ር መረራ የሚመራው “ኦብኮ” የቀድሞ ስርዓት ናፋቂዎች ተላላኪ ነው”
የሚል ክስ አቅርበው ነበር፡፡ ታዲያ ዶ/ር መረራ መልሱ አልከበዳቸውም፡፡ ወዲያውኑ ነበር የመልስ ምታቸውን እንዲህ በማለት የወረወሩት፡፡
“አባዱላ ገመዳ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ከየት ወደየት የሚል መጽሐፋቸውን ሲጽፉ የኔን መጻሕፍትና በመጽሔቶች ላይ
የወጡትን ጽሑፎቼን ከሰላሳ ጊዜ በላይ እንደ ምንጭ ጠቅሰዋል፤ አሁን ደግሞ ተላላኪ ነህ ይሉኛል፤ ተላላኪ ከሆንኩ ጽሑፎቼን በምንጭነት
ሲጠቀሙ እንዴት እምነት ሊጥሉብኝ ቻሉ? ይህ ሊገባኝ አልቻለም”
(ሳቅ እንደገና ትንሹን አዳራሽ ሞላው፡፡ በነገራችን ላይ ቅንጅትን ከወከሉት ተከራካሪዎች አንዱ የነበሩት አቶ
ሙሐመድ ዓሊ እዚሁ ፌስቡክ ላይ ስላሉ አሁን በጻፍኩት ላይ ማስተካከያ ሊሰጡን ይችላሉ፡፡ እኔ የጻፍኩት በአዕምሮዬ የማስታውሰውን
ብቻ ነው)
-------
መረራ ጉዲና በሚያስተምርበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለአራት ዓመታት (ከ1989-1992) ነበርኩ፡፡
ይሁንና በነዚያ ዓመታት ለአንድም ቀን እንኳ አይቼው አላውቅም፡፡ ከዚያ በኋላም እርሱን በአካል ያየሁት ለሶስት ወይንም ለአራት
ጊዜ ብቻ ቢሆን ነው፡፡ በማስሚዲያና በፕሬስ ግን ዘወትር እከታተለዋለሁ፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ድምጹን የሰማሁትና በቪዲዮም ያየሁት በአምናው
ክረምት እርሱ፣ ጌታቸው ረዳ፣ ነጃት ሀምዛ እና ፍጹም ብርሃነ በአል-ጀዚራ ቴሌቪዠን ለክርክር በቀረቡበት ጊዜ ነው፡፡ በቀደሙት
ዓመታት መጽሐፎቹንና መጣጥፎቹን አንብቤአቸው ነበር፡፡ ስለስብእናውና ስለግላዊ ህይወቱ በደንብ የተረዳሁት ግን በ2006 የታተመውን
ግለ-ታሪኩን ሳነብ ነው፡፡
በዚህ ዓመት (2009) መግቢያ ላይ ዶ/ር መረራ በሽብርተኝነት ተጠርጥረሀል ተብሎ መታሰሩ ይታወሳል፡፡ በብዙሀኑ
የሀገራችን ዜጎችም ሆነ በዓለም አቀፍ ተቋማት “አፋኝና ጨቋኝ” ተብሎ የተወገዘውን የጸረ-ሽብር ህግ ያጣቀሰ ክስም ተከፍቶበታል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ እጆቹ በካቴና ታስሮ ልብ በሚሰብር ሁኔታ ወደ ፍርድ ቤት ሲወሰድ የሚያሳይ ፎቶግራፍ በማህበራዊ ሚዲያዎች
ሲዘዋወር ነበር፡፡
አንዳንዶች “ፎቶው በሐሰት የተሰራ ነው” እያሉ ነው፡፡ ይሁንና ዋናው ነገር ፎቶው አይደለም፡፡ እጅግ በጣም
ልብ የሚያደማው ዋነኛ ነገር ከአበባ የወጣትነት ዘመኑ ስምንት ዓመታትን በከርቸሌና በማዕከላዊ ምርመራ ያሳለፈው፣ ደርግ ከወደቀ
በኋላም የሚበዛ ጊዜውን ለህዝብ መብት መከበር ሲታገል የነበረው፣ በዩኒቨርሲቲው በሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በማስተማር የአባትነት
ኃላፊነቱን የተወጣው፣ በዚህች ሀገር የተቃውሞ ፖለቲካን በሰለጠነ መንገድ ማካሄድን ሲያስተምር የቆየውና ይህ የተቃውሞ ፖለቲካ ባህል
ስር እንዲሰድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው ዶ/ር መረራን የመሰለ ጎምቱ ምሁር በመጦሪያው ወቅት “አሸባሪ” ተብሎ ወደ እስር ቤት
መወርወሩ ነው፡፡
የዶ/ር መረራ እጣ ፈንታ ያሳዝናል፡፡ በጣም ያስጨንቃል፡፡ ሰዎች የተለየ የፖለቲካ አመለካከት በመያዛቸውና
ለሀገርና ለህዝብ የማይበጁ አዝማሚያዎችን በመቃወማቸው ብቻ እንደ ጠላትና ሽብርተኛ ሲፈረጁ ማየት ሁላችንንም ያሳስበናል፡፡ ባለፉት
26 ዓመታት በዚሁ መንገድ ስንጓዝ ከርመናል፡፡ ገዥው ፓርቲው “በጥልቀት ታድሻለሁ” በሚልበት በዚህ ወቅት ቀዳሚው ትኩረቱ ዜጎች
ያለ አንዳች ስጋትና ፍርሐት የሚኖሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት መሆን ነበረበት፡፡
አሁንም ድምጻችንን ደግመን እናሰማለን!! ዶ/ር መረራን ጨምሮ በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ በየወህኒ ቤቱ የታሰሩት
ዜጎቻን ይፈቱልን!! አላግባብ የታሰሩ የፖለቲካ መሪዎች ይፈቱልን!! አላግባብ የታሰሩት የህዝበ-ሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ
አባላት ይፈቱልን!! አላግባብ የታሰሩት ጋዜጠኞች ይፈቱልን!! አላግባብ የታሰሩት ተማሪዎች ይፈቱልን! “ሽብርተኛ” እየተባሉ አላግባብ
የታሰሩት ሙስሊም ወጣቶች ይፈቱልን! ሁሉም ዜጋ በሀገሩ ላይ ያለ ፍርሐት የሚኖርበት ሁኔታ ይፈጠርልን!! የሰዎችን ነፃነት የሚተበትቡትና
ሀገሪቱን በዓለም ዙሪያ መሳለቂያ እያደረጉ ያሉት “የጸረ-ሽብር ህግ”ን የመሳሰሉ አፋኝ አዋጆች ይወገዱልን!!
አላህ ሀገራችንና ህዝቦቻችን በሰላምና በፍቅር ያኑርልን! አሚን!!
----
አፈንዲ ሙተቂ
ሀምሌ 25/2009
በአዳማ ከተማ ተጻፈ፡፡