Saturday, January 13, 2018

የገለምሶው ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብን በጨረፍታ

                                     
ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
---
በከተማችን ነዋሪዎችና በሌሎች አካባቢዎችም ዘንድ በጣም የሚከበሩት ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ በትናንትናው እለት አርፈዋል፡፡ ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ ዕድሜአቸው ወደ መቶ ዓመት ሆኖአቸው ነበር፡፡ አላህ ዕድሜ ሰጥቶአቸው ብዙ ማየት ቢችሉም የሄዱት ተመልሰው ወደማይመጡበት ዓለም ነውና እርሳቸውን በማጣታችን መሪር ሐዘን ተሰምቶናል፡፡

ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ በአንድ ዘመን በገለምሶና በመላው የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ፈክተው ይታዩ ከነበሩት እነ ሼኽ ሙሐመድ ጡልላብ (ጪሮ)፣ ሼኽ ሙሐመድ ረሺድ ሼኽ ቢላል (ጭረቲ)፣ ሐጂ ዑመር አርቦዬ (ደረኩ)፣ ሼኽ ኒብራስ ሙሐመድ (አሰቦት)፣ ሼኽ አሕመድ ሼኽ አቡበከር (ቡሶይቱ)፣ ሙፍቲ ሓጂ ዑስማን (ገርቢ ጎባ)፣ ሼኽ ሐሰን አነኖ፣ ሼኽ ሻቶ ሚኦ (ጉባ ቆርቻ)፣ ሼኽ ሙሐመድ ጀልዲ (ሂርና) የመሳሰሉትን ታላላቅ ዑለማ ያፈራው ወርቃማው ትውልድ አባል ነበሩ፡፡ ከነዚያ ዑለማ መካከል እስከ ለታሪክ ተርፈው ረጅም ዓመት መኖር የቻሉት እርሳቸውና የገለምሶው ሼኽ ሙሐመድ ሲራጅ ብቻ ናቸው፡፡ እርሳቸው አሁን አርፈዋል፡፡ ሼኽ ሙሐመድ ሲራጅ ብቻ ቀርተዋል (ዕድሜአቸውን ያርዝመውና)፡፡
*****
ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ የተጸውኦ ስማቸው “ሙሐመድ ሐቢብ” ነው፡፡ ሸሪፍ” ደግሞ የማዕረግ ስማቸው ነው፡፡ እኝህ ዓሊም እንደ ሌሎች ዑለማ ሼኽ ተብለው ያልተጠሩት በትውልዳቸው ሸሪፍ በመሆናቸው ነው (ሸሪፍ የዘር ሐረጋቸው ከነቢዩ ሙሐመድ (..) ቤተሰብ ለሚዘዝ ሰዎች የሚሰጥ ማዕረግ ነው፤ አንዳንድ ጊዜም “ሰይድ” ይባላሉ፤ ከነቢዩ ቤተሰብ የተወለዱ መሆናቸው የሚነገርላቸው ጎልማሶችና ዑለማ በአብዛኛው “ሸሪፍ” እየተባሉ ነው የሚጠሩት)፡፡

ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ የተወለዱት በቀድሞው የጨርጨር አውራጃ (በአሁኑ ምዕራብ ሀረርጌ ዞን) በዶባ ወረዳ፣ ቢዮ ኸራባ በሚባለው መንደር ነው፡፡ ይሁን እንጂ የዕድሜአቸውን ግማሽ ያህል የኖሩት ሎዴ በተሰኘውና በገለምሶ ከተማ ዳርቻ ላይ ባለው መንደር ነው (መንደሩ ከከተማው ሶስት ኪሎሜትር ያህል ወጣ ብሎ ይገኛል)፡፡ ሸሪፍ ሙሐመድ በዚህ የሎዴ መንደር የከተሙት 1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው፡፡
------
ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ በመምህርነት፣ በአባትነት እና በሀገር ሽማግሌነት ህዝቡን ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ታዲያ እኝህ ዓሊም ከሌሎች የገለምሶ ዑለማ በበለጠ ሁኔታ የሚታወሱበትና ስማቸውን የተከሉበት አንድ ቁምነገር አለ፡፡ ይኸውም ዘጠና ዘጠኙን የአላህ ስሞች (አስማኡላሂል ሑስና) እየጠሩ ዚክር ማድረግን ለአካባቢያችን ህዝብ በስፋት ያስተዋወቁ መሆናቸው ነው፡፡

የሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ ደረሳ ሆኖ አስማኡል ሑስና ያልሓፈዘ (በቃሉ ያልያዘ) የለም ለማለት ይቻላል፡፡ “ሐርፍ” መቁጠር (ፊደል ማጥናት) ከጀመረው ህፃን አንስቶ ኪታብ እስከሚቀራው ደረሳ ያለው የሸሪፍ ሙሐመድ ተማሪ “እስቲ የአላህ ስሞችን ቁጠርልኝ” ብትሉት አንድ በአንድ ይነግራችኋል፡፡ እሳቸው ከኖሩበት መንደር ነዋሪዎች መካከልም ብዙዎች አስማኡል ሑስናን በቃላቸው ይዘዋል፡፡

 ታዲያ ይህ የሸሪፍ ሙሐመድ አስማኡል ሑስና አብዮት በሒፍዝ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ደረሳዎቻቸው በልዩ ልዩ ወቅቶች የሚያዜሟቸው ዚክሪዎችም አስማኡል ሑስና መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ እነዚህ ዚክሮች በድቤ ታጅበው በዜማ የሚዘከሩ በመሆናቸው “መንዙማ” ይባሉ ይሆናል፡፡ በአካባቢያችን ልማድ መሠረት ግን “አስማኣ” ወይንም “አስማኡል ሑስና” ነው የሚባሉት፡፡

በኛ ዘንድ መንዙማ የሚባለው በግጥም እየተቀኘ የሚጻፈው ውዳሴ ነው፡፡ የሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ “ዚክሪ” ግን ከአላህ ስሞች በስተቀር ሌላ ግጥም የለውም፡፡ ሸሪፍ ሙሐመድ የሚገጥሙት አዝማቹን ብቻ ነው፡፡ ተከታዮቹ ግጥሞች ደግሞ ዘጠና ዘጠኙ የአላህ ስሞች ናቸው፡፡ እስቲ ለወግ ያህል ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ ዜማና አዝማች እያወጡላቸው ያቀናበሩዋቸውን አንዳንድ የአስማኣ ዚክሪዎችን ላካፍላችሁ፡፡
------
አንዱ የሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ ዚክሪ የሚከተለው አዝማች አለው(ተቀራራቢ ትርጉሙ በቅንፍ ውስጥ የተጻፈው ነው)፡፡

አላህ ቀሲሙን ዳኢሙ (አንተ የምትረዝቀው ሁሌም የምትኖረው አላህ ሆይ)
አላህ ቀሲሙን ዳኢሙ (አንተ የምትረዝቀው ሁሌም የምትኖረው አላህ ሆይ)
ሱብሓነከ ቃኢሙ (ከጉድለት ሁሉ የጠራኽ ነህ አንተ ዘወትር ያለኸው)

ጀመዓው ድቤ እየመታና በአንድ ሼኽ እየተመራ ይህንን ዚክሪ እየደጋገመ ያዜማል፡፡ በዚህ በኩል የሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ ዚክሪዎች በሌሎች አካባቢዎች ከምታውቋቸው መንዙማዎች ልዩነት የላቸውም፡፡ ሼኹ ዚክሪውን ሲመራው ግን የአላህ ስሞችን እንደሚከተለው ይጠራቸዋል፡፡

ራሕማን ረሒም አላህ (ጀመዓው አላህ ቀሲሙን ዳኢሙ እያለ ይቀበላል)
ደያኑን ቡርሓን አላህ (አሁንም ጀመዓው አላህ ቀሲሙን ዳኢሙ ይላል)
አወሉን አኺር አላህ 
ወሊዩን ከቢር አላህ
 (ሼኹ የመጨረሻዎቹን ሁለት ግጥሞች በአንድ ላይ ስለሚላቸው ጀመዓው በጸጥታ ያሳልፋል)፡፡

ሼኹ ይህንን ተናግሮ ፋታ ሲወስድ ጀመዓው እንደገና አላህ ቀሲሙን ዳኢሙ ይዘምራል፡፡ ከዚያም ሼኹ ሌሎች የአላህ ስሞችን ይጠራል፡፡ ጀመዓው እንደገና አላህ ቀሲሙን ዳኢሙ ያዜማል፡፡ እንደገና ሼኹ ሌሎች የአላህ ስሞችን ይጠራል፡፡ እንዲህ እንዲህ እየተባለ ሼኹ ሁሉንም የአላህ ስሞች ጠርቶ እስኪያበቃ ድረስ ዚክሪው ይሄዳል፡፡

ታዲያ ሼኹ ሁሉንም የአላህ ስሞች ጠርቶ ገቢሩን የሚዘጋው በነቢዩ ሙሐመድ ላይ ሰለዋት በማውረድ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ለሁሉም ዚክሪዎች የሚያገለግለው አንድ ባለ አራት መስመር ግጥም ነው፡፡ ግጥሙ እንዲህ ይሄዳል፡፡

መዐ-ስ-ሰላሚላህ መዐ-ስ-ሰላሚላህ (ከአላህ ሰላም ጋር፣ ከአላህ ሰላም ጋር)
ዐላ ሙሐመዲን ወ ኸይሩ ኸልቂላህ (የፍጡራን ሁሉ በላጭ በሆነው ሙሐመድ ላይ በሚወርደው)
ወል አህሊ ወሳህቢ ወማ ፊ ዲኒላህ (በቤተዘመዶቹ፣ በባልደረቦቹና በአላህ ዲን ውስጥ ባለው ሰው ሁሉ)
ዐላ ሙሐመዲን ወኩሊ ጁንዲላህ (በሙሐመድ እና በአላህ ሰራዊትም ላይ)

*****
ሸሪፍ ሙሐመድ “አስማኣዎቹ”ን በየጊዜው ነው የሚያወጡት፡፡ እነርሱን በቃል መያዝ ደግሞ በጣም ቀላል ነው፡፡ በሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ ከተደረሱት ዝነኛ የአስማኣ ዚክሮች መካከል የሚከተሉትን ማስታወስ ይቻላል፡፡

1.  ሐስቡነላህ ወኒዕመል ወኪሉ
ሐስቡነላህ ወኒዕመል ወኪሉ
ኒዕመል መውላ ወኒዕመ-ንነሲሩ

2.  ቢስሚላሂ ራሕማኒ-ረሒም
አልሐምዱሊላህ ወሱብሓነላህ
ረብቢ ሰልሊ ዐላ ሙሐመድ

3.  አላሁ አላህ አላሁ አላህ
ሱብሓነከ ያ ሳቲረል ዑዩብ
ጋፊረ ዙኑብ

4.  አላሁ አላሁ ሚንከል መደዱ
አላሁ አላሁ ሚንከል መደዱ
ጀማል ከውኒ አንተል አሐዱ

5.  አላሁ አላህ ያ አላህ
ራሕማን ያ ረሒም
ኢርሐምና ወል-ሙስሊሚና
በርሩ ያ ከሪም

*****
ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ በአንድ ወቅት የደረሱት “አስማኣ” በህብረተሰቡ ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ አስማኣ የሚከተለው አዝማች ነበረው፡፡ 

አላሁ አላህ አላህ ዘልፈረጂ
በሺር ረብበና ቢል ቢል-ኢማን ኩለል ፈረንጂ
የአማርኛ ትርጉሙ እንደሚከተለው ሊሆን ይችላል፡፡

አንተ የፈረጃ ባለቤት የሆንከው አላህ ሆይ
ፈረንጆችን ሁሉ በኢማን አብስራቸው (ኢማን ሙላባቸው)፡፡

ሸሪፍ ሙሐመድ ይህንን ዚክሪ ለምን እንደጻፉ ሲጠየቁ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡
እነኝህ ፈረንጆች ኢማን ባይኖራቸውም አብዛኞቹ ደግ ናቸው፡፡ የሚሰሩት ነገርም ደግ ነው፡፡ ከአውሮፕላን እስከ መኪና፣ ከመርከብ እስከ ባቡር የተሰሩት በእነርሱ ነው፡፡ እነርሱ በሰሯቸው መጓጓዣዎች ነው ወደ ሐጂ የምንሄደው፡፡ የምግብ ማብሰያ ቡታጋዝና ማታ የምናበራውን ፋኖስ የፈለሰፉት እነርሱ ናቸው፡፡ ሰዎች የሚለብሷቸው አልባሳትም በአብዛኛው በነርሱ የሚሰራው፡፡ ሌላው ይቅርና ድርቅ ሀገራችንን በሚያጠቃበት ወቅት የእርዳታ እህል የሚመጸውቱን እነርሱ ናቸው፡፡ በመሆኑም ነው እነዚህ ደጋግ ፈረንጆች ኢማን ኖሯቸው አላህ ጀንነት እንዲሰጣቸው የተመኘሁት” 
    
*****
እኝህ ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ አስማኣን ከመቀመር በተጨማሪ የሚታወቁባቸው አስገራሚ ጸባዮችም ነበራቸው፡፡ ለምሳሌ ጉዳይ ሲይዛቸው ከመንደራቸው እስከ ገለምሶ የሚመጡት በእግር ነው፡፡ የመልስ ጉዞውንም የሚያደርጉት በእግር ነው፡፡ በመንገዱ ላይ የሚዘዋወሩ መኪናዎች ሲቆሙላቸው በጭራሽ አይሳፈሩም፡፡ በእጃቸውም እንደ ሽማግሌ ከዘራ አይዙም፡፡ በተጨማሪም በሐድራቸው ከመቶ ከማያንሱ ደረሳዎቻቸውና ልጆቻቸው ጋር እየኖሩ አንድም ሰው በጉዞአቸው እንዲያጅባቸው አይፈቅዱም፡፡ ይህ በብዙ ሼኾች ዘንድ ያላየሁት ጸባያቸው ነው፡፡

ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብን ለመጨረሻ ጊዜ ያየኋቸው የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ነበር፡፡ አንድ ቀን ተመልሼ የሕይወት ታሪካቸውን በስፋት አጠናለሁ የሚል ሐሳብ ነበረኝ፡፡ ነገር ግን ሐሳቤ ሳይሞላልኝ እርሳቸው ቀድመውኝ ወደ አኺራ ሄዱ፡፡ አላህ በጀንነት ያብሽራቸው፡፡ መልካም ስራቸውን ይቀበላቸው፡፡
------
አፈንዲ ሙተቂ
መጀመሪያ ሐምሌ 10/2006 በገለምሶ ከተማ ተጻፈ፡፡
እንደገና ተሻሽሎ ጥር 5/2010 በሸገር ተጻፈ፡፡


Friday, January 12, 2018

አቡል ሚስክ፡ ግብጽን የገዛው ኢትዮጵያዊ ወዚር




አቡል ሚስክ፡ ግብጽን የገዛው ኢትዮጵያዊ ወዚር
ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
“የኢትዮጵያ ታሪክ ከተጻፈው ያልተጻፈው ይበዛል” ይባላል፡፡ እውነት ነው፡፡ የዚህ አባባል ሐቀኝነት የሚገባችሁ ወደ ታሪክና ኢትኖግራፊ ምርምር ስትገቡ ነው፡፡ ታዲያ ከተጻፈው የሀገራችን ታሪክ መካከል እንኳ ከኛ ከባለቤቶቹ ይልቅ በሌሎች ዘንድ በስፋት የሚታወቅ ታሪክም አለ፡፡ በዚህ ጽሑፍ በጨረፍታ የምዘክረውን ግለሰብ ታሪክ ያገኘሁት ከውጪ ምንጮች ነው፡፡
----
ባለታሪካችን “አቡል ሚስክ ካፉር” ይባላል፡፡ በአስረኛው ክፍለ ዘመን የኖረ ትውልደ-ኢትዮጵያዊ የግብጽ ገዥ ነው፡፡ አቡል-ሚስክ ወደ ግብጽ የተወሰደው በጉርምስና ዕድሜው ባርነት ተሸጦ ነው፡፡ በዘመኑ ባሮችን መሰለብ በሰፊው ይተገበር ነበር፡፡ በመሆኑም አቡል-ሚስክም ወደ ግብጽ የተወሰደው ጃንደረባ (eunuch) ሆኖ ነው፡፡

አቡልሚስክ በ923 በአንዱ ቀን ለገበያ ቀርቦ ሳለ “የኢኽሺዲ” ስርወ-መንግሥት መስራች የነበረው ሱልጣን ሙሐመድ ኢብን ቱግጅ በድንገት አየው፡፡ ኢብን ቱጊን በብላቴናው ወጣትነት ተማረከ፡፡ ወደ ነጋዴዎቹ ቀረብ ካለ በኋላም “ይሄ ወጣት ከየት ሀገር ነው የመጣው?”በማለት ጠየቃቸው፡፡ ነጋዴዎቹም “ከሐበሻ ነው” በማለት መለሱ፡፡

ኢብን ቱግጅ የነጋዴዎቹን ምላሽ ሲሰማ የጥንቱ ቢላል ኢብን ረባህ ትዝ አለው፡፡ በደም ፍላት መንፈስም “የሐበሻን ልጅ ነው እንዲህ አስራችሁ ለሽያጭ ያመጣችሁት? የነጃሺ ውለታ ተረስቶ ነው ሐበሻ በሀገሬ ምድር በባርነት የሚሸጠው?” በማለት በንዴት ወረደባቸው፡፡ ነዴዎቹም “እኛ እኮ አይደለንም የፈነገልነው! ከሀገሩ ነጋዴዎች ነው ገዝተን ያመጣነው” በማለት መለሱለት፡፡

ኢብን ቱግጅ “በሉ ቶሎ ለኔ ስጡኝ! ሁለተኛ የሐበሻ ተወላጅ የሆነን ሰው በባርነት እንዳትሸጡት” በማለት አቡልሚስክን ከነጋዴዎቹ እጅ ተረከበው፡፡ ወደ ቤተ መንግሥቱ ወስዶትም ልብሱን ከቀየረለት በኋላ እዚያው እንዲኖር ፈቀደለት፡፡ በዘመኑ በታወቀው ኒዛሚያ መድረሳ የካይሮ ቅርንጫፍ አስመዝግቦት ትምህርቱን እንዲማርም አደረገው፡፡

ወጣቱ አቡልሚስክ በትምህርት ቆይታው ዐጃኢበኛ ተማሪ ወጣው፡፡ በትምህርት መደቡ ከሁሉም ተማሪ መካከል አንደኛ እየወጣ ይሸለም ጀመር፡፡ ሌሎች ተማሪዎች ብዙ ዓመታት የሚወስድባቸውን የዒልም ጉዞ እርሱ በጥቂት ዓመታት ውስጥ አጠናቀቀው፡፡ ሱልጣን ሙሐመድ ኢብን ቱግጅ የአቡል ሚስክን ጉብዝና ሲያይ እርሱን ከነጋዴዎቹ እጅ መንጭቆ የወሰደበትን ቀን አወደሰው፡፡

የመድረሳው ኃላፊዎች አቡልሚስክን “ሙዓሊም” (ፕሮፌሰር) አድርገውት ሊቀጥሩት ፈልገው ነበር፡፡ ሱልጣን ሙሐመድ ግን “እርሱን ለከፍተኛ ስራ ስለምፈልገው አስተማሪ አይሆንም” በማለት ከለከላቸው፡፡ ወደ ቤተ መንግሥቱ ወስዶትም ዋና አማካሪው አድርጎ ሾመው፡፡ ልጆቹ እንደርሱ ጎበዝ እንዲሆኑለት ስለተመኘም ከስራ ሰዓት ውጪ የግል መምህራቸው ሆኖ እንዲያስተምራቸው መደበው፡፡ የአቡልሚስክ መኖሪያም እዚያው ያደገበት ቤተመንግስት ሆነ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ጄኔራሎቹ ሱልጣኑን ሊገለብጡት ሲሞክሩ ደግሞ አቡልሚስክ በፊት ከነበረው ሹመት በተጨማሪ የቤተመንግስቱ ጠባቂዎች አዛዥ ሆኖ ተመደበ፡፡
----
ይህ በእንዲህ እያለ በግብጹ ሱልጣን ስር ይገዙ በነበሩት ሶሪያና ሒጃዝ አመጽ ፈነዳ፡፡ ሱልጣን ሙሐመድ የመደባቸው ጄኔራሎች እየተሸነፉ ከግዛቶቹ ተባረሩ፡፡ ሱልጣኑ አመጹን ለመቆጣጠር እንዲመቸው አዲስ ጦር አዘጋጀ፡፡ አቡልሚስክንም የዚህ ጦር አዛዥ አድርጎ አዘመተው፡፡ አቡልሚስክ ወደ ሶሪያና ሒጃዝ ገብቶ አማጺዎቹን ድል በማድረግ ሱልጣኑ በግዛቶቹ ላይ የነበረውን የበላይነት አስከበረ፡፡

ታዲያ አቡልሚስክ ከድሉ በኋላ የሱልጣኑን ተቃዋሚዎች አልተበቀለም፡፡ ከዚያ ይልቅ የአመጹን መንስኤ ለማወቅ ነበር የሞከረው፡፡ ከህዝቡ ጋር ባደረገው ውይይትም የአመጹ መንስኤ ሀገሩን ያስተዳደሩ የነበሩት ገዥዎች በህዝቡ ላይ ሲፈጽሙት የነበረው በደልና የተዘፈቁበት የስልጣን ብልግና እንደሆነ ተረዳ፡፡ ይህንንም ለሱልጣኑ ግልጽ አድርጎ አስረዳው፡፡ ሱልጣኑም በግዛቶቹ የተፈጠሩትን ችግሮች ለመቅረፍ ሰፊ ስራ ሰራ፡፡
---
ሱልጣን ሙሐመድ ኢብን ቱግጅ ከልጆቹ መካከል እርሱን የሚተካ ወራሽ እንደሌለው በጊዜ ነበር ያወቀው፡፡ በመሆኑም “ጠላቶቼ በብዙ ልፋት ያስከበረውን የግዛቱን ሉዓላዊነት ሊደመስሱት ይችላሉ” በማለት ስጋት ገባው፡፡ በተለይም ከሁለት መቶ አመታት በፊት በሽንፈት የተባረሩት ሮማዊያን ግብጽን በድጋሚ ሊነጥቁ ማቆብቆባቸው አሳሰበው፡፡ ስለዚህ በበሽታ ተለክፎ አልጋ ላይ በዋለበት ጊዜ ቤተዘመዶቹን ሁሉ ጠርቶ “ንግሥናውን ለልጆቼ አውርሼአለሁ፡፡ ሀገሩን በበላይነት የማስተዳደሩን ስልጣን ግን ለአቡልሚስክ አስረክቤአለሁ፣ ማንም ሰው በስራው ጣልቃ እየገባ እንዳያስቸግረው” በማለት ተናዘዘ፡፡ አቡልሚስክም የሱልጣኑን አደራ በመረከብ የሀገሩ “ዋና ወዚር” (ጠቅላይ ሚኒስትር) ሆኖ መግዛት ጀመረ፡፡
----           
አቡልሚስክ በስልጣን ላይ ሳለ ከፈጸማቸው ዋና ተግባራት አንዱ ትምህርትን ማስፋፋቱ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በግብጽ ምድር በመቶ የሚቆጠሩ መድረሳዎችን ገነባ፡፡ ለትምህርት የሚሆን መደበኛ ፈንድም መሠረተ፡፡ ለአስተማሪዎች በቂ ክፍያ እንዲፈጸምም አደረገ፡፡ በዘመኑ ተዳክሞ የነበረው የአልኬሚ ምርምር እንዲጠናከር በትጋት ሠራ፡፡

አቡልሚስክ ኢኮኖሚውንም ለማንሰራራት ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ለነጋዴዎች የግብር ቅናሽ አደረገ፡፡ ከሀገር ሀገር እየተዘዋወሩ ለሚነግዱት ሲራራ ነጋዴዎች ጥበቃ እንዲደረግላቸውም አዘዘ፡፡ በዘመኑ ዋጋው ወድቆ የነበረውን የግብጽ ዲናር የሚተካ አዲስ የወርቅ ገንዘብ አሰራ (ፎቶውን ይመልከቱ)፡፡
-----
አቡልሚስክ በዘመኑ መለኪያ በቂ በሚባል ደረጃ የተማረ ሰው ቢሆንም እውቀትን ጠግቦ አያውቅም፡፡ በመሆኑም በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው እውቀት የመጠቁ ምሁራንን ወደ ቤተመንግሥቱ እየጠራ ያወያያቸው ነበር፡፡ ለገጣሚዎችም ፍቅርና ክብር ነበረው፡፡ በዚህ ሁኔታ ወደ ቤተመንግስቱ ከመጡት አንዱ ታዋቂው ገጣሚ “አል-ሙተነቢህ” ነው፡፡

አል-ሙተነቢህ ጎበዝ ገጣሚና ባለቅኔ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁንና ከገጣሚነቱ ባሻገር ስልጣንና ገንዘብም በብዛት ይወድ ነበር፡፡ ወደ ካይሮ ከተማ የመጣውም የሶሪያው ገዥ ስልጣን ስላልሰጠው “የርሱ የበላይ ከሆነው የግብጽ ሱልጣን ዘንድ ሄጄ ፍላጎቴን መፈጸም እችላለሁ” በሚል ምኞት ነበር፡፡

አቡልሚስክ የአልሙተነቢህን ቅኔዎች ቢያደንቅም ሌሎች ሰዎችን እየተነኮሰ መዘባበቻ እንደሚያደርጋቸውም ያውቅ ነበር፡፡ ስለዚህ ወደ ቤተመንግሥቱ በጣም እንዲቀርብ አልፈቀደለትም፡፡ በከተማዋ አንድ ቤት ሰጥቶት ለኑሮው መደገሚያ የሚሆን ተቆራጭ ብቻ ይልክለት ነበር፡፡ አልሙተነቢህ አቡልሚስክን በቅኔዎቹ እየደጋገመ ቢያሞግሰውም ወዚሩ ፊት አልሰጠውም፡፡ ገጣሚው አልሙተነቢህ ለሶስት ዓመታት (ከ957-960) የገዥውን ልብ ለማማለል ያደረገው ሙከራ ስላልተሳከለት ከግብጽ ወደ ኢራቅ ለመሰደድ ወሰነ፡፡ ታዲያ ወደ ባግዳድ ሲሄድ በልቡ የተደበቀውን በሽታ ይፋ ያወጣበትንም ድርጊት ፈጸመ፡፡ አቡልሚስክ በባርነት ተፈንግሎ ወደ ግብጽ የመጣ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ መሆኑን እየጠቀሰ አንድ ገጽ የሚሆን ቅኔ ጻፈበት፡፡
         
ይሁንና በዚህም በኩል የርሱ ምኞት አልተሳካለትም፡፡ ቅኔው አቡልሚስክን ሊያሳጣው ቀርቶ በተቃራኒው በአል-ሙተነቢህ ላይ ከባድ መዘዝ ነው ያስከተለበት፡፡ በሄደበት ሀገር ሁሉ ህዝቡ “የቢላልን ታሪክ ረስቶ በሐበሻው ብላቴና ላይ የተሳለቀ” እያለ ወረደበት፡፡ እርሱ ያነጋገራቸው የአውራጃና የክፍለ ግዛት ገዥዎች ድሮ በግጥሞቹ እንዳልተንሰፈሰፉለት ሁሉ በአቡልሚስክ ላይ በፈጸመው ድርጊት የተነሳ ሊያነጋገሩት እንኳ ተጠየፉ፡፡ አልሙተነቢህም ተስፋ ቆርጦ ከዐረቡ ዓለም ወደ ኢራን ተሰደደ፡፡ ታዲያ በዚያም ከዓመት በላይ ለመቆየት አልቻለም፡፡ የግዛቱ ገዥ ሊያቀርበው ስላልፈቀደ በተሸነፈ መንፈስ ወደ ኢራቅ ለመመለስ ወሰነ፡፡ ሆኖም ካሰበው ስፍራ ሳይደርስ በመንገድ ላይ ባደፈጡ ወንበዴዎች ተገደለ፡፡
-----
አቡልሚስክ ግብጽንና በርሷ ስር የነበሩትን ግዛቶች (ሂጃዝ፣ ሶሪያ፣ ፈለስጢን) ለሀያ ዓመታት ከገዛ በኋላ በ966 የገዥነቱን ስልጣን ዓሊ ለተባለው የሱልጣን ሙሐመድ ልጅ አስረከበ፡፡ ከመንግሥት ስራ ሙሉ በሙሉ ተገልሎም በዒባዳና ሌሎችን በማስተማር ህይወቱን መግፋት ጀመረ፡፡ በ968 ግን በተስቦ በሽታ ተለክፎ አረፈ፡፡

በትረ መንግሥቱን ከአቡልሚስክ የተረከበው የሱልጣን ሙሐመድ ልጅ አባቱ እንደገመተው ጠንካራ ገዥ ለመሆን አልቻለም፡፡ ለአንድ ዓመት ብቻ እንደነገሠ ከቱኒዚያ አካባቢ የመጡትና “የነቢዩ ሙሐመድ ቤተሰብ አባላት ነን” የሚሉ ጎሳዎች መንግሥቱን ገለበጡት፡፡ በዚህም ለሀምሳ ዓመታት በስልጣን ላይ የቆየው የኢኽሺድ ስርወ-መንግሥት ፍጻሜ ሆነ፡፡ አዲሶቹ መሪዎችም “ፋጢሚይ” የሚባለውን ስርወ መንግሥት መሠረቱ፡፡
------
አፈንዲ ሙተቂ
ጥር 3/2010

በሸገር ተጻፈ፡፡

Thursday, January 11, 2018

ከ“ሁለት ዶክተሮች ወግ” ጀርባ ያለ እውነታ


(አፈንዲ ሙተቂ)
-----
   መካከለኛው ምስራቅን የሚያምሰው የፍልስጥኤም-እስራኤል ችግር ረጅም ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የዚህ ችግር መነሻ በ1948 የተመሠረተችው እስራኤል አንድ ዓመት እንኳ ሳይሞላት ፍልስጥኤማዊያን የወደፊት ሀገራቸውን እንዲመሠርቱበት የተመደበላቸውን ግዛት መውረሯ ነው፡፡ የእስራኤል ጎረቤት የሆኑ የዐረብ ሀገራት እርምጃውን በመቃወም ሶስት ጊዜ ጦርነት ያወጁባት ቢሆንም እስራኤል በሶስቱም ድል አድርጋለች፡፡

   ታዲያ እስራኤል የድሉን ብስራት ያከበረችው በወታደራዊ ሰልፍና በርችት ሳይሆን ፍልስጥኤምን ሙሉ በሙሉ ወደ ግዛቷ በማካተት ነው፡፡ የሀገሩ ባለቤት ከሆኑት ፍልስጥኤማዊያን ደግሞ ከፊሉን እየገደለች አብዛኛውን ከመሬቱ አባርራለች፡፡ ዛሬ በሀገራቸው ላይ የቀሩት ፍልስጥኤማዊያን ከመላው የፍልስጥኤም ህዝብ ሃያ በመቶ ያህል ብቻ ናቸው፡፡

    አብዛኛው የዓለም ህዝብ የእስራኤልን ወረራ አውግዞአል፡፡ እስራኤልም  ፍልስጥኤምን ለቃ እንድትወጣ በተደጋጋሚ ጊዜያት ውሳኔ ተላልፎባታል፡፡ ሀገራችንም ባለፉት አርባ ዓመታት ይህንን አቋም በማራመድ ላይ ትገኛለች፡፡

    “ታዲያ ለመገናኛ ብዙኃን፣ ለቢሮክራሲውና ለትምህርቱ ዓለም ቅርብ የሆነው የሀገራችን ማኅበረሰብ የፍልስጥኤማዊያንን ትግል የሚመለከተው በአንድ ወጥ ሁኔታ አይደለም፡፡ ይህም ከፍተኛ የሆነ ግራ መጋባትን ፈጥሮአል፡፡
    በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መንግሥት እና ለገዥው መደብ የቀረቡ ኃይሎች  የእስራኤል ደጋፊ የነበሩ ሲሆን የተማረው ክፍል (ኢንተሌጀንሲያው) ደግሞ በአብዛኛው የፍልስጥኤሞችን ትግል ይደግፍ ነበር፡፡ በደርግ ዘመን ደግሞ የሀገራችን መንግሥት የፍልስጥኤማዊያን ትግል ደጋፊ ከመሆኑም በላይ በስደት ለተቋቋመው የፍልስጥኤማዊያን መንግሥት በኦፊሴል እውቅና በመስጠት ኤምባሲውን በአዲስ አበባ እንዲከፍት ፈቅዶለታል፡፡ የኢንተሌጀንሲያው ክፍልም በአመዛኙ የፍልስጥኤምን ትግል ይደግፍ ነበር፡፡
  
“ከደርግ ውድቀት በኋላ ግን ነገሩ ሁሉ ተገለባብጦ ማኅበረሰባችን በሃይማኖት እየተከፋፈለ ለፍልስጥኤም-እስራኤል ግጭት ድጋፉን የሚያሳይበት/ተቃውሞውን የሚገልጽበት አካሄድ ተከስቷል፡፡ በዚህም መሠረት “ሀማስ እስራኤል ላይ ሮኬት ተኮሰ” ወይንም “እስራኤል የጋዛ ከተማን በአውሮፕላን ደበደበች” የሚል ዜና የተላለፈ እንደሆነ ክርስቲያን የሆኑ የሚዲያ ተከታታዮች በአብዛኛው የእስራኤል ደጋፊ ሆነው ይሰለፋሉ፡፡ እስራኤል የክርስቲያን ሀገር ሆና ከሙስሊሞች ጋር ጦርነት የገጠመችም ይመስላቸዋል፡፡ ሙስሊሞቹ ደግሞ በተቃራኒው የፍልስጥኤም ደጋፊ ይሆናሉ፡፡ ፍልስጥኤማዊያን ክርስቲያኖች የሌሉና ትግሉ ሁሉ በሙስሊሞች ብቻ የሚካሄድ ይመስላቸዋል፡፡

   እንዲህ ዓይነት አሰላለፍ የተከሰተው የእስራኤል ፕሮፓጋንዲስቶች ለረጅም ዓመታት ግጭቱ የሃይማኖት ጦርነት እንደሆነ በማስመሰል ሲያናፍሱት በነበረው በውዥንብር የተሞላ ትርክት የተነሳ ነው፡፡ ይህ አሰላለፍ በውጪው ዓለም አልፎ አልፎ ነው የሚታየው፡፡ በሀገራችን ውስጥም ቢሆን በቀድሞ ዘመናት እንዲህ ዓይነት አረዳድ አልነበረም”

    የዐፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት የእስራኤል ደጋፊ የሆነው ከጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታዎች በመነሳት ነው፡፡ ለምሳሌ የዐጼ ኃይለ ሥላሤ መንግሥት የግብፁ መሪ ጀማል ዐብዱናስር የሚያካሄዱት “የፓን ዐረቢዝም ንቅናቄ” ስላሰጋው የእንቅስቃሴው ዋነኛ ተቃዋሚ ከነበሩት የኢራን፣ የእስራኤልና የቱርክ መንግስታት ጋር በወዳጅነት ቃል ኪዳን ተሳስሮ ነበር፡፡ በሌላ በኩል የፍልስጥኤም ነፃ አውጪ ድርጅቶች የኤርትራ ንቅናቄዎችን (ጀብሃን እና ሻዕቢያን) በመደገፋቸው የኃይለሥላሴ መንግሥትም በአፀፋው ከእስራኤል ጋር ወግኗል፡፡

   የደርግ መንግሥት ለፍልስጥኤም ትግል አጋርነቱን ለመግለጽ የወሰነበት ዋነኛ ምክንያት የሚከተለው የሶሻሊስት ርእዮተ ዓለም የብሄራዊ አርነት ንቅናቄዎችን እንዲደግፍ የሚያስገድደው መሆኑ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የዓለም ሀገራት በፍልስጥኤም ጥያቄ ፍትሐዊነት ላይ የጋራ መግባባት የነበራቸው በመሆኑ የደርግ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም አንፀባርቋል፡፡

   በሌላ በኩል የደርግ መንግሥት በርካታ የዐረብ ሀገራት የኤርትራ ንቅናቄዎች ደጋፊ በመሆናቸው ብቻ ተበሳጭቶ ፍልስጥኤማዊያን ድርጅቶችን አልገፋቸውም፡፡ የፍልስጥኤም ነፃ አውጪ ድርጅት በአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የታዛቢነት ወንበር እንዲያገኝም ታግሏል፡፡ እነዚህም ዘወትር ከሚደነቁለት ተግባሮቹ መካከል ይቆጠራሉ (እርግጥ የኩባው ፊደል ካስትሮ እና ደቡብ የመን በዚህ ላይ ሚና እንደነበራቸው ይታመናል)፡፡

   በቅርብ ዘመናት የምናየው የእስራኤል-ፍልስጥኤምን ግጭት በሃይማኖት መስመር የመረዳት አባዜ ግን ድሮ ያልነበረ እና አንዳች የርእዮተ ዓለም፣ የታሪክና የጂኦ-ፖለቲካ ትንተና መሠረት የሌለው የድንቁርና እሳቤ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ የኋላቀርነት አስተሳሰብ በአጭሩ መገታት አለበት፡፡ በርግጥም የፍልስጥኤማዊያን ትግል መደገፍ ያለበት ፍትሐዊና ህጋዊ መሠረት ያለው ተጋድሎ  በመሆኑ ብቻ ነው፡፡

   ታዲያ የተጠቀሰው የድንቁርና አመለካከት እይታችንን በእጅጉ የጋረደ መሆኑን የማስረዳት አጋጣሚ ቢኖረኝ ኖሮ እያልኩ ስመኝ ኖሬአለሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለሁም አጋጣሚው ዘንድሮ ተከሰተልኝና ይህንን አነስተኛ ድርሳን በመጻፍ በትንሹም ቢሆን የልቤን ለማድረስ ቻልኩ፡፡

አፈንዲ ሙተቂ
January 2018



Saturday, January 14, 2017

ከግብጻዊው ወጣት ጋር


(አፈንዲ ሙተቂ)
----
ወደ ዱባይ በመጣሁ በሁለተኛው ሳምንት ይመስለኛል። እኔና ባለቤቴ "ኮርኒች" ከሚባለው የቱሪስቶችና የዋናተኞች መናኸሪያ በሚገኝ ካፍቴሪያ ላይ ተሰየምን። ወዲያውኑ አንድ ልጅ እግር አስተናጋጅ እየተጣደፈ መጣ።

"ዐላ ኺድማቲኩም ሰይዳቲ" አለን በዐረብኛ። "ልታዘዛችሁ ዝግጁ ነኝ" ማለቱ ነው። ባለቤቴ ጭማቂ አዘዘች። እኔ ሳንድዊች መብላት አምሮኝ ስለነበረ "ሳንዱች መውጁድ?" አልኩት ("ሳንድዊች አላችሁ እንዴ" እንደማለት ነው)። "ኤይዋ መውጉድ" በማለት መለሰልኝ!! ልጁ ግብጻዊ እንደሆነ ገባኝና "አንት ሚን መስር?" አልኩት። "ኤይዋ! አነ ሚን መስር" (አዎ! ከግብጽ ነኝ!) ብሎኝ የታዘዘውን ሊያመጣ ሄደ። ያ ልጅ በጣም የሚጣደፍ ከመሆኑ የተነሳ ግብጻዊ መሆኑን እንዴት እንዳወቅኩ አልጠየቀኝም። ቢሆንም ፎርሙላውን ለናንተ ልጻፈው።

ከዐረብኛ በርካታ ዘዬዎች መካከል የግብጹ ዘዬ በአንድ ነገር ይለያል። ይኸውም "ጀ" የሚባል ድምጽ የሌለው መሆኑ ነው። በዋናው የአል-ፉስሐ ዐረብኛ (Classical Arabic) የተጻፈና "ጀ" የሚል ድምጽ ያለበት ቃል በግብጾች ዘዬ በ"ገ" ድምጸት ነው የሚነበበው። ለዚህም ነው ግብጾች ታዋቂ መሪያቸውን "ጀማል ዐብዱናስር" በማለት ፈንታ "ገማል ዐብዱናስር" እያሉ የሚጠሩት። ያ ግብጻዊ ወጣትም "መውጁድ" በማለት ፈንታ "መውጉድ" ብሎ የመለሰልኝ ለዚሁ ነው (ይህ "ጀ"ን ወደ "ገ" የመቀየር አካሄድ ለቅዱስ ቁርአን ብቻ አይሰራም። በቁርአን ምንባብ ወቅት ሁሉም ፊደል በትክክለኛው ድምጽ መነበብ አለበት)።

በሌላ ምሽት በዚያው ስፍራ በእግር እየተንሸራሸርን ነበር። ያ ግብጻዊ ወጣት ወደ አስፋልቱ ወጥቶ በመንገዱ ላይ የሚያልፈውን ሰው ሁሉ "ጥሩ እራት! ከጥሩ መስተንግዶ ጋር! ወደኛ ሬስቶራንት ይግቡ" እያለ ይለማመጣል። በመሃሉ አንድ ቆነን ያለ ወፍራም ወጣት "ወደዚያ ሂድልን ባክህ!! መንገዱን ትዘጋብናለህ እንዴ!!" በማለት ገፍትሮት አለፈ። ግብጻዊውም "አረ ባክህ ተወን! ለራስህ መለይካ እየመሰልክ ትረማመዳለህ፥ እኛም ሰርተን ይለፍልን እንጂ" እያለ ለፈለፈ።

ታዲያ አንድ ነገር ውልብ አለብኝ። በልቤ "በዚህ ግብጻዊ ላይ ሙድ መያዝ አለብኝ" አልኩ። እናም ተጠጋሁትና "ኸሊ ያ ጋሊ! ሃዳ መጅኑን" አልኩት (ወዳጄ ተወው! ይሄ እኮ እብድ ነው" እንደማለት ነው)። ታዲያ ልጁም በሰውዬው አድራጎት ቅጥል ብሎ ኖሮ ጠንከር ባለ አነጋገር "ኤይዋ ሃዳ መግኑን" አለኝ። ባሰብኩት መንገድ ስለመለሰልኝ ከልቤ ሳቅኩ። እርሱም ከጣሪያ በላይ እያንባረቀ ከኔ ጋር ሳቅ። ( እኔ የሳቅኩት "መጅኑን" የሚለውን ቃል በግብጻዊው ስልት "መግኑን" ብሎ ስለተናገረው ነው። እርሱ ግን በዚያ አውደልዳይ መንገደኛ የሳቅኩ ነበር የመሰለው)።

ግብጻዊው አቀራረቤ ስላማረው ነው መሰለኝ የመጣሁበትን ሀገር ጠየቀኝ። ከኢትዮጵያ መሆኔን ነገርኩት። እርሱም ለመሸኛ የሚሆነኝን ንግግር እንዲህ በማለት አሸከመኝ!
"ኢትዮጵያ በለድ ገሚል"
እኔም ደግሜ ሳቅ አከናነብኩት። እርሱም በሃይለኛው ከኔ ጋር ሳቀ!!
(ሚስኪን!! እርሱ እኮ "ኢትዮጵያ ቆንጆ ሀገር ናት" እያለኝ ነበር። እኔ ግን "ጀ"ን ወደ "ገ" ቀይሮት ሲናገረው  ልስማው ብዬ ነበር ያዋራሁት። አላህ ይቅር ይበለኝ እንግዲህ!!)
----
"አንተ ስለ ሰው አነጋገር ምን አሳሳበህ?" ትሉኝ ይሆናል። በኢትኖግራፊ ምርምር ውስጥ ስትገቡ እንዲህ ነው የሚያደርጋችሁ። ስለሰዎች አነጋገር፣ የቃላትና የዐረፍተ ነገር አሰካክ፣ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ ጌጣጌጦች፣ የጸጉር አሰራር፣ ልዩ ልዩ ልማዶች ወዘተ በሰፊው ለማወቅ ትጨነቃላችሁ። ታዲያ ይህ አመልና አምሮት ያለጊዜውና ያለቦታው መዋል የለበትም። ተወዳጁ ገጣሚ ጀላሉዲን ሩሚ ይህንኑ በአንድ ወግ አጫውቶን ነበር።

ሰውዬው የነህዊ (ሰዋስው) መምህር ናቸው። ማንኛውም ሰው የሰዋስው ህግን ጠብቆ ያናግረኝ ባይ ነበሩ። በአነጋገሩ ስህተት የፈጸመውን ሁሉ "ያንተ ሰዋስው ችግር አለበት" ይሉት ነበር። ታዲያ እኚህ ሰውዬ በአንድ ሰፈር ሲያቋርጡ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ። እዚያ ሆነው ቢጣሩ ማንም ሊደርስላቸው አልቻልም። ወደ ውሃው ለመስጠም ሲቃረቡ ግን በመንገዱ በማለፍ ላይ የነበረ ገበሬ በድንገት ድምጻቸውን ሰምቶ ሊረዳቸው መጣ። መምህሩ ነፍሳቸውን በማዳን ፈንታ የገበሬው አነጋገር አስጨነቃቸው። እናም "ወዳጄ! ስትናገር እኮ የሰዋስው ህግ ጥሰኻል" አሉት።

"ደግ ነው እንግዲህ!" አለ ገበሬው፡ "ሰዋስው ተምሬ እስክመጣ ድረስ እዚሁ ይቆዩኝ!"

ከእንደዚህ ዓይነቱ ይሰውረን!! መልካም ጊዜ ለሁላችሁም ተመኝተናል!!
-----
አፈንዲ ሙተቂ
ዱባይ፥ የተባበሩት ዐረብ ኢማራት
January 13/2017