Tuesday, June 23, 2015

ተሰውፍ ምንድነው?


ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
---
   “ተሰውፍ” (Sufism) ሁለት ፍቺዎች አሉት፡፡ አንደኛው “ሱፍ መልበስ” የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው “ራስን ማጽዳት” ማለት ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የምንዳስሰው “ተሰውፍ” በሁለተኛ ፍቺው ፈለግ የሚሄድ ነው፡፡ ይህም በተገቢ መንገድ ሲቀመጥ የልብ ጥራት” እንደማለት ነው፡፡ ሙስሊም የሆነ ሰው ልቡ በአካሉ ከሚያደርገው ኢባዳ ጋር በእኩል ሁኔታ እንድትራመድለት ሲፈልግ ልዩ ልዩ ጥበባዊ ዘዴዎችን የሚማርበት መንገድ ነው- “ተሰውፍ፡፡ ይህም ሲባል ልብን ከልዩ ልዩ የልብ በሽታዎች ማጥራትማለት ነው፡፡

   በቁርአንና በሀዲስ በስፋት እንደተገለጸው ሰዎች ከፈጣሪ ጋር ያላቸውን ትስስር የምታበላሽባቸው አንዲት አካል አለች፡፡ እርሷም ልብ ናት፡፡ ሙእሚኖች ቁርኣናዊ ግዳጃቸውን በተገቢው መንገድ ለመወጣት ከፈለጉ ልባቸውን ከበሽታ ማጥራት አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል ፈጣሪያችን አላህ (..) ለምንሰራቸው መልካም ስራዎች የሚከፍለንን ምንዳ (አጅር) የሚወስነው የልባችንን ጥራት በመመዘን ነው፡፡ በከፍተኛ የልብ ጥራት የአንድ ብር ሰደቃ የሰጠ ሰው ከፍተኛ ሽልማት አለው፡፡ ሰውየው መካከለኛ የልብ ጥራት ካለው ሽልማቱ ያንስበታል፡፡ የልብ ንጽህናው በጣም የጎደፈ ሰው ደግሞ ሽልማቱ እጅግ ዝቅተኛ ነው (ሰውዬው መቶ ብር ቢሰጥ እንኳ በንጹህ ልብ አንድ ብር የሰጠውን ሰው ያህል ሽልማት አያገኝም)፡፡ ልቡ ሙሉ በሙሉ የቆሸሸ ሰው ግን ከአላህ ዘንድ ምንም ሽልማት አያገኝም፡፡

  እንግዲህ ይህንን የልብ ጥራት ማምጣት የሚቻለው እንዴት ነው? ኡለማ ለዚህ ጥያቄ የሚሆን ምላሽ ሲፈልጉ ነውተሰውፍየሚባለው አስገራሚ (አንዳንድ ጊዜ አወዛጋቢ) ኢስላማዊ የትምህርት ዘርፍ የተወለደው፡፡
  ተሰውፍን እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ አድርጎ ማስተማር መቼ እንደተጀመረ በትክክል አይታወቅም፡፡ በርካታ ምንጮች ታዋቂዎቹን የበስራ ምሁራን ሐሰን አል-በስሪንና ራቢአቱል አደዊያን እንደ ጀማሪዎች ይጠቅሳሉ፡፡ ለመጀመሩ ሰበብ የሆነውም በጊዜው የነገሰው የልዩ ልዩ ፊርቃዎች (ዓ፤ ኻዋሪጅ፤ ሙርጂአ፤ ጀሀሚያ፤ ሙእተዚላ፤ ቀደሪያ፤ ጀብሪያ ወዘተ…) ሽኩቻ እንደሆነ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡

   በተሰውፍ ላይ የሚያተኩሩ መጽሀፍት መጻፉንም ማን እንደጀመረው በርግጥ አይታወቅም፡፡ እንደሚመስለኝ ከሆነ የተሰውፍ መጽሀፍት መጻፍ የጀመሩት ከሂጅራ በኋላ 4ኛው መቶ አመት ገደማ፤ ማለትም እንደ አውሮፓ አቆጣጠር 900 .. በኋላ ሳይሆን አይቀርም፡፡ 10ኛው፤ 11ኛውና 12ኛው ክፍለ ዘመናት ፈሪዱዲን አጣር፤ አቡ ሀሚድ አል-ገዛሊ፤ አህመድ አል-ሪፋኢ፤ አብዱልቃዲር አል-ጁይላኒ ወዘተየመሳሰሉ ምሁራን በተሰውፍ ላይ ያተኮሩ በርካታ መጽሀፍትን አበርክተዋል፡፡

ተሰውፍና የልብ በሽታዎች
   ልባችን የሚቆሽሸው በተለያዩ በሽታዎች ነው፡፡ እነዚህ የልብ በሽታዎች ያሉበት ሰው ኢባዳውን በወጉ አያደርግም፡፡ ውሎውና ድርጊቶቹ ከኢስላማዊ አዳብ ጋር አይገጥሙለትም፡፡ ከግለሰቦችና ከማህበረሰቡ ጋር ያለው ግንኙነትም የተስተካከለ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ በዚህች አለም ብቻ ሳይሆን በወዲያኛውም አለም ታላቅ አደጋን ያስከትልበታል፡፡ ስለዚህ ከአደጋው ለመዳን ልቡን ከበሽታ ማጥራት ይጠበቅበታል፡፡

   የሰውን ልብ ከሚያደርቁትና ኢማንን ከሚያጎድሉት በሽታዎች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡
·        ኒፋቅ፡- የሙናፊቅነት ስሜት
·        ጡግያን፡- ጥመት
·        ኪብሪያእ፡-ኩራት
·        ጁብር፡ ትዕቢት
·        ሪኣእ፡- ልታይ ልታይ ማለት
·        ዘን፡- ከንቱ ጥርጣሬ
·        ገፍላን፡- መሰላቸት
·        ሻህዋእ፡- ከገደብ ያለፈ ስጋዊ ፍላጎት
·        ወዘተ

   አላህና መልዕክተኛው (..) ከነዚህ በሽታዎች እንድንጠነቀቅ አስተምረውናል፡፡ የተሰውፍ ሰዎች ለነዚህ በሽታዎች የሚሆኑ መድሃኒቶችን ነው የሚያስተምሩት፡፡ የነዚህ መድሃኒቶች ምንጭ ቁርአንና ሱንና ነው፡፡ ልቡን ከነዚህ በሽታዎች ያጠራ ሰው ዒባዳውን በታላቅ ኹሹእ (የአላህ ፍራቻ) ማከናወን ይችላል፡፡ በተሰውፍ ከምንታከምባቸው መድሀኒቶች መካከል ከሁሉም የሚበልጠውዚክር” (አላህን ማስታወስ ) ነው፡፡ ቁርኣን ልቦች በዚክር ይረጥባሉ በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷልና!!

   እንግዲህሱፊየሚባል ሰው ልቡን ከበሽታ ለመጠበቅ ሲል የተሰውፍን ጥበብ የሚከተል ማለት ነው፡፡ ይህ የተሰውፍ ጥበብ ደግሞ ከቁርአንና ከሀዲስ ጋር የማይጋጭ መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም ሰውየው ሌላውን ኢባዳ ትቶ ተሰውፍን ብቻ የሙጥኝ ብሎ መያዝ አይችልም፡፡ተሰውፍሰውዬው በኢባዳ ላይ ብርቱ ሆኖ እንዲቆይ የሚረዱትን ጥበባዊ ዘዴዎች ያስተምረዋል እንጂ በራሱ የቆመ ለየት ያለ ኢስላማዊ ጎዳና ወይም የሸሪኣ ዘርፍ አይደለም፡፡

   ማንም ሰው የተሰውፍ ዘዴዎችን ሳይማር ኢባዳውን ማድረግ ይችላል፡፡ልቤ በትእቢትና በኩራት ተወጥራለችና ምን ይበጀኛል?” ብሎ የሚጨነቅ ከሆነ መድሃኒቱን ከተሰውፍ መንገድ መፈለግ ይፈቀድለታል፡፡

   እዚህ ላይ የታዋቂውን የሱፊ ጥበብ አዋቂ የሼኽ ብዱልቃዲር አል-ጄይላኒን ምሳሌዎች ልጥቀስ፡፡ ሼይኽ አል-ጄይላኒአል-ጉንያ ሊጣሊብ ጠሪቀል ሀቅበተባለ መጽሀፋቸው ውስጥ እንዲህ ይላሉ፡፡
·        መቼም ቢሆን አትማል፤ መማል ካስፈገለ ግን በአላህ ስም ብቻ ማል!
·        በምላስህ አትዋሽ! ጥሩ ነገር ብቻ ተናገር!
·        በመንገድህ ላይ በእድሜው ካንተ የሚያንስ ሰው ቢያጋጥምህከርሱ የተሻልኩነኝ ብለህ አታስብ፡፡ ከዚህ ይልቅ በልብህይህ ልጅ በምድር ላይ የኖረበት ዘመን ከኔ እድሜ ያንሳል፡፡ ስለዚህ ሀጢአቱም ከኔ ያነሰ ነውበል፡፡
·        በእድሜው ካንተ የሚበልጥ ሰው ከገጠመህ ደግሞይህ ሰው በዚህች ምድር ላይ ከኔ እድሜ ለሚበልጥ ጊዜ ኖሯል፤ ስለዚህ ለአላህ ባደረገው ኢባዳ ከኔ ይበልጣልበል እንጂ በመጥፎ ነገር አትጠርጥረወ፡፡

   ደስ ይላል አይደል? ከማስደሰቱ ጋር መጠየቅ ያለበት ጥያቄሼኽ አብዱልቃዲር የተናገሯቸው ነገሮች ከኢስላማዊው ሸሪዓ ጋር ይቃረናሉ ወይ?” የሚለው ነው፡፡
   ሼኽ አብዱልቃዲር የጻፉት ነገር ከኢስላማዊ ሸሪዓ ውጪ አይደለም፡፡ ይልቅ ኢስላማዊ ሸሪዓን በትክክል ለመተግበር ያግዛል፡፡ ተሰውፍ ማለትም እንዲህ ነው፡፡ 
   በዚህ መሰረት ነው ሙስሊሞች ልባቸውን ከበሽታ የሚፈውሱባቸውን ልዩ ልዩ ምክሮች የሚሰጡ መጽሀፍት መጻፍ የተጀመሩት፡፡ አንዳንድ መምህራንም ሙሉ ጊዜያቸውን ለዚሁ ሰጥተው የማስተማሪያ ማእከላትን ያቋቋሙት ለዚሁ አላማ ነው፡፡

(ይቀጥላል)

-----
አፈንዲ ሙተቂ

ጥቅምት 2004

Sunday, January 18, 2015

ነቢዩ እና ዘመናዊነት



ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
------
ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ያስተማሩት ትምህርት ዘመናዊነትን ይከለክላል?…. በዘመን አፈራሽ የቴክሎኖጂ ትሩፋቶችና በተቀላጠፉ አሰራሮች መጠቀምን እርም ያደርጋል?… መልሱ “አያደርግም” ነው፡፡ የነቢዩንና የተከታዮቻቸውን የህይወት ታሪክ በወጉ ከፈተሽን ነገሩን በቀላሉ መረዳት እንችላለን፡፡ እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንውሰድ፡፡

·        ነቢዩ በዘመናቸው ለነበሩት ነገሥታት ደብዳቤ መጻፍ አስፈለጋቸው፡፡ አንዱ ባልደረባቸው “ደብዳቤው ከርስዎ የተላከ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማኅተም ያስፈልግዎታል፤ ማኅተም ቢያስቀርጹ መልካም ይመስለኛል” አላቸው፡፡ ነቢዩ የማኅተም አስፈላጊነት ሲነገራቸው እምቢ አላሉም፡፡ ሃሳቡን ወዲያውኑ ተቀብለው አዲስ ማኅተም አስቀረጹ፡፡

·        ከሂጅራ በኋላ በስድስተኛው ዓመት የቁሬይሽ ተዋጊዎች በመዲና ከተማ ላይ ሶስተኛ ዙር ወረራ ሊፈጽሙ ተነሱ፡፡ ከቁሬይሾች ጋር በርካታ ማህበረሰቦች ማበራቸውም ተሰማ፡፡ ይህም ወሬ ለነቢዩ ደረሳቸው፡፡ ነቢዩም በጉዳዩ ላይ ከባልደረቦቻቸው ጋር መወያየት ጀመሩ፡፡ በውይይቱ ላይ ከነበሩት ባልደረቦቻቸው መካከል “ሳልማን አል-ፋርሲ” የሚባለው “በከተማችን ዙሪያ ምሽግ ብንቆፍር ጠላቶታችንን በቀላሉ መመለስ እንችላለን” አላቸው፡፡ ሳልማን የፋርስ (ኢራን) ተወላጅ ነው፡፡ በሀገሩ ሲደረግ ያየውን ነው ለነቢዩ የነገራቸው፡፡ እስከዚያ ጊዜ ድረስ “ምሽግ” በዐረቦች ዘንድ አይታወቅም ነበር፡፡


ነቢዩ ከሳልማን በሰሙት ምሽግ የመቆፈር ብልሃት ተገረሙ፡፡ በተግባር ላይ ሊያውሉትም ተነሱ፡፡ የመዲና ከተማን ከዳር እስከ ዳር በምሽግ ቁፋሮ አጠሯት፡፡ የመካ ቁረይሾች እየፎከሩ ወደ መዲና ሲመጡ ምሽጉ ገደባቸው፡፡ በፈረስና በእግር እየዘለሉ ምሽጉን ለማለፍ ቢሞክሩም ምንም አልተሳካላቸውም፡፡ ይህ ሁኔታ ሌሊቱን ከጣለው ከባድ ዝናብ ጋር ተዳምሮ በጣም አስፈራቸው፡፡ በመሆኑም እቃቸውን እንኳ በወጉ ሳይሰበስቡ ወደመጡበት ፈረጠጡ፡፡ ነቢዩ አንድም ጦር ሳይሰብቁ በእጥፍ የሚበልጣቸውን የጠላት ሃይል ከሳልማን አል-ፋርሲ በሰሙት ዘዴ አባረሩት፡፡

·        በዚያ ዘመን በርካታ መልዕክተኞች ወደ ነቢዩ ዘንድ ይመጡ ነበር፡፡ ታዲያ አንዱ የነቢዩ ባልደረባ “ንጉሦችና የጦር መሪዎች የውጪ መልዕክተኞችን በሚቀበሉበት ጊዜ የአዘቦት ልብሳቸውን አይለብሱም፤ ለየት ያለ ልብስ ለብሰው በርሱ ላይ ካባ ይደርባሉ” አላቸው፡፡ ነቢዩም ምክሩን ተቀብለው በተግባር ላይ አውለውታል፡፡

·        ነቢዩ አይጽፉም፤ አያነቡምም፡፡ ደብዳቤም ሆነ ሌላ ጽሑፍ የሚጽፉላቸው ተከታዮቻቸው ናቸው፡፡ ከጸሐፊዎቻቸው መካከል እጅግ በጣም የተከበረው ዘይድ ኢብን ሣቢት የሚባለው ወጣት ነው፡፡ ነቢዩ የላኳቸው ደብዳቤዎች በአብዛኛው በርሱ እጅ ነበር የተጻፉት፡፡

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) በደብዳቤ የሚገናኟቸው የማህበረሰብ መሪዎችና ነገሥታት በሙሉ ዐረብኛን ማንበብ የሚችሉ አልነበሩም፡፡ ዐረብኛን የሚያነቡት በዐረቢያ ልሳነ-ምድር (Arabian Peninsula) እና በዙሪያው ባሉት መሬት ላይ የነገሡ መሪዎች ብቻ ነበሩ፡፡ በመሆኑም ነቢዩ ከዐረብኛ በተጨማሪ በሌሎች ቋንቋዎችም ደብዳቤዎችን መጻፍ እንዳለባቸው ተገነዘቡ፡፡ ዘይድ ኢብን ሣቢትንም በዘመኑ ሰፊ ተናጋሪ የነበራቸውን የእብራይስጥ (Hebrew) እና የአረማይስጥ (Aramaic/ Syriac) አጻጻፍ እንዲያጠና በመዲና ይኖሩ ከነበሩት አይሁዶችና ክርስቲያኖች ዘንድ ላኩት፡፡ ዘይድም ሁለቱንም አጻጻፎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጥናት የጸሐፊነቱን ስራ በሶሥት ቋንቋዎች ቀጥሎበታል፡፡

·        ነቢዩ ለዕውቀት የነበራቸው ከበሬታ ሲወሳ በዓለም ከሚኖሩት ሙስሊሞች ግማሽ ያህሉ የሚያውቁት አንድ ሐዲስ አለ፡፡ ሐዲሱ እንዲህ ይላል፡፡

“ዕውቀትን ቻይና ድረስ እንኳ ቢሆን ሄዳችሁ ፈልጉት”

ከላይ ከተገለጹት ታሪኮች እንደምትረዱት ነቢዩ ጠቃሚ የሆነ ዕውቀትን ያበረታቱ ነበር፡፡ “የተቀላጠፈ አሰራር መጠቀም ሀገርን ያጠፋል” በማለት በተከታዮቻቸው ላይ በሩን አልዘጉም፡፡ የርሳቸው ተከታዮችስ?… ባልደረቦቻቸውም ቢሆኑ በዘመናዊነት ላይ በነበራቸው እይታ የነቢዩን ፈለግ ተከትለዋል፡፡ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንጥቀስ፡፡


·        ኸሊፋ ዑመር ቢን ኸጣብ (ረ.ዐ) ከነቢዩ የቅርብ ረዳቶች አንደኛው ነበሩ፡፡ ከነቢዩ ህልፈት በኋላ የሙስሊሙን ኸሊፋዊ መንግሥት ለአስር ዓመታት መርተዋል፡፡ የነቢዩን ሐዲሶችን ጨምሮ በርካታ ታሪኮችን መመዝገብ የተጀመረው በርሳቸው ጊዜ ነው፡፡ ታዲያ ታሪክ ሲመዘገብ የዘመን መቁጠሪያ መጠቀም የግድ ይላል፡፡ ይሁንና በዚያ ዘመን ራሱን የቻለ የቀን መቁጠሪያ በዐረቢያ ምድር አይታወቅም ነበረ፡፡ በመሆኑም ዑመር ነቢዩ ከመካ ወደ መዲና ያደረጉት ስደት (ሂጅራ) እንደ መነሻ ሆኖ እንዲያገለግል ውሳኔ አስተላለፉ፡፡ ይህም ተግባራዊ ሆኖ እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ እየተሰራበት ይገኛል፡፡

·        አምስተኛው ኸሊፋ ሙአዊያ ኢብን አቡ-ሱፍያን (ረ.ዐ) ደግሞ በተማከለ አሰራር ደብዳቤዎችን ከግለሰቦች ተቀብሎ የሚያከፋፍል ተቋም በመመስረት በዓለም ታሪክ አዲስ አሰራር አስተዋውቀል፡፡ ዛሬ “ፖስታ ቤት” የሚባለውን ተቋም የፈጠሩት ኸሊፋ ሙአዊያ ናቸው (ባለፈው ነሐሴ ወር ይህንን ጉዳይ በጻፍኩበት ወቅት በርካታ ሰዎች የግኝቱ ባለቤት ሙአዊያ መሆናቸውን እንደማያውቁት ተገንዝቤአለሁ፤ ሆኖም ነገሩ ሐቅ ነው፤ እውነትነቱን ለማረጋገጥ ካሻችሁ በመጽሐፍ፣ በኢንተርኔትም ሆነ በሲዲ የተሰራጨው “ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ” ስለሙአዊያ የጻፈውን ታሪክ አንብቡት፡፡ በሁሉም ቦታ እንዲህ የሚል ነገር ተጽፎ ታገኛላችሁ፡፡

“Early Arabic sources credit two dīwāns in particular to Muʿāwiyah: the dīwān al-khatam, or chancellery, and the barīd, or postal service, both of which were obviously intended to improve communications within the empire”

የኢንሳክሎፒዲያ ብሪታኒካን ጽሑፍ በኢንተርኔት ለማንበብ ካሻችሁ ይህንን ሊንክ ተጠቀሙ፡፡



·        በአሁኑ ወቅት የዓለም ህዝብ በሙሉ የሚጠቀምበት “የሂንዱ-ዐረብ” የቁጥር ዘዴ የመጨረሻ ቅርጹን ያገኘው በሙስሊሞች አማካኝነት ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ለሂሳብ አቆጣጠር የሚያመቸው “የዜሮ ጽንሰ ሃሳብ” የተፈለሰፈው በ8ኛው ክፍለ ዘመን በባግዳድ ከተማ ነው፡፡

·        የሳይንስና የምርምር ዘርፍ ከፍተኛ እመርታ እንዲሳይ ያደረጉትን አል-ጀብራ እና አልጎሪዝም የተሰኙ የሂሳብ ስልቶችን የፈጠረው ሙሐመድ ኢብን ሙሳ አል-ኸዋሪዝሚ የተባለ ሙስሊም ሳይንቲስት ነው (ዜሮንም የፈጠረው አል-ኸዋሪዝሚ ነው)፡፡

·        ሌላም ብዙ ብዙ መዘርዘር ይቻላል፡፡


ከነዚህ ምሳሌዎች ለመረዳት እንደሚቻለው የጥንቱ ሙስሊሞች በአዳዲስ ፈጠራዎች ከመጠቀም አልፈው ለራሳቸውም ልዩ ልዩ ፈጠራዎችን አስተዋውቀዋል፡፡ በአዳዲስ ፈጠራዎች መጠቀም “ውግዝ” ቢሆን ኖሮ ነቢዩና ባልደረቦቻቸው “እርም፤ ነው አትጠጉት” በማለት ክልከላ ያስቀምጡበት ነበር፡፡ ስለዚህ ዘመን ባስገኘልን ትሩፋት ከመጠቀም ወደኋላ ማለት የለብንም፡፡

ይሁንና ይህ በፈጠራዎች የመጠቀም ጉዳይ ሲነሳ አንድ ነገር መታወቅ አለበት፡፡ ይኸውም በጥቅም ላይ የሚውለው አዲስ ፈጠራና አሰራር የሰዎችን ኑሮ በማቃለል ረገድ አስፈላጊነቱ የሁሉም ተጠቃሚዎች ምስክርነት ሊኖረው የተገባ መሆኑ ነው፡፡ እስልምና ከጉዳት በስተቀር አንዳች ጥቅም የሌለውን ፈጠራ ይከለክላል፡፡

 በሌላ በኩል ደግሞ በፈጠራና በዘመናዊነት ስም አላህ እርም ያደረጋቸውን ድርጊቶች መፍቀድ አይቻልም፡፡ ለምሳሌ ማንኛውም የእስልምና ሙፍቲ “አስካሪ መጠጥ ለጤና ይጠቅማችኋል፣ ድንበር ሳታልፉ ጠጡ” በማለት ውሳኔ መስጠት አይችልም፡፡ ቁማርን ህጋዊ ማድረግም በፍጹም አይቻልም፡፡ በሰብዓዊ መብት ስም ግብረ-ሰዶምን ህጋዊ ማድረግም ተቀባይነት የለውም፡፡ እነዚህ ድርጊቶች የሰዎችን ኑሮ ከማቃወስ በስተቀር አንዳች ጠቀሜታ የላቸውም፡፡

ነቢዩ በዘመናዊ እውቀት መጠቀምን ከልክለዋል የሚል የተቀዣበረ ወሬ የሚነዙት ነቢዩን የማያውቁት ጠላቶቻቸው ብቻ አይደሉም፡፡ “የነቢዩን ትክክለኛ ትምህርት የምንከተለው እኛ ብቻ ነን” ማለት የሚቃጣቸውና ሰዎችን “አዛ” ማድረግ ልማዳቸው የሆነ ከሙስሊሙ ዓለም የበቀሉ አንዳንድ ጽንፈኛ አንጃዎችም ጭምር ናቸው፡፡ ለምሳሌ የ“ጣሊባን” አንጃ አፍጋኒስታንን በሚያስተዳድርበት ጊዜ “በእስልምና የተከለከሉ ናቸው” በሚል በርካታ የቴክኖሎጂ ትሩፋቶችን እርም አድርጎ ነበር፡፡ ይሁንና ነቢዩ እንዲህ ዓይነት ጽንፈኝነትን አላስተማሩም፡፡ አላህ ነቢዩን የላከለው ለራሕመት (እዝነት) ነው እንጂ ጽንፍ በወጣ አስተምህሮ ሰዎችን እግር ተወርች ቀፍድደው ለሰቀቀን ኑሮ እንዲዳርጓቸው በሚል አይደለም፡፡ ነቢዩም ተከታዮቻቸውን ሲያስተምሩ “አግራሩ፤ አታክርሩ” (“የሲሩ፤ ወላ ቱዐሲሩ”) ነበር ያሉት፡፡ በመሆኑም የነዚህን ጽንፈኞች አድራጎት በማየት የነቢዩን አስተምህሮ በተዛነፈ ሁኔታ መረዳት ተገቢ አይደለም፡፡

የአላህ ሶላትና ሰላም በነቢዩ ላይ ይስፈን (ሰልላሁ ዐለይሂ ወሰለም)
------
አፈንዲ ሙተቂ
ጥር 9/2015

-----

Saturday, January 10, 2015

ጽንፈኝነት፣ ምዕራባዊያንና ሚዲያ


ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
ከዚህ በፊት “እስልምና ጂሃድ እና ሰሞነኛው የኢራቅ ሚሊሻ” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ጽሑፍ የእስልምና ሃይማኖት በጽንፈኝነት ላይ ያለውን አቋም በሰፊው ገልጫለሁ (ጽሑፉ የኔ ብሎግ ላይ ስላለ ከዚያ ማንበብ ይቻላል)፡፡ በጽሑፉ ለማስረዳት እንደሞከርኩት በእስልምና የሚያምነው የዓለም ህዝብ ጽንፈኝነትና ጽንፈኞችን በጣም ያወግዛል፡፡ ከብዙሃን ጋር የማይጣጣሙት ጥቂት ጽንፈኞች እስልምናንም ሆነ ሙስሊሞችን አይወክሉትም፡፡

  ይሁንና ምዕራባዊያንና ሚዲያዎቻቸው ጽንፈኝነትን ለአንዱ ሃይማኖት በጅምላ ያሸከሙ ነው የሚመስሉት፡፡ ታላቋ ሶቪየት ህብረት ከፈራረሰች ወዲህ ከሚዲያ ኢንዱስትሪው ወሬ ማሟሟቂያዎች እና ከተንታኞቻቸው የአስተሳሰብ ምጡቅነት ማሳያ ዋነኛ አርዕስተ ጉዳዮች አንዱ ስለ“እስልምና አክራሪነት” መፍተልና መተርተር ሆኗል፡፡ እንግዲህ የ“እስልምና አክራሪነት” የሚል ርዕስ ከመጠቀም ጀምሮ የዓለም ማህበረሰቦች አትኩሮት በርሱ ላይ ብቻ እንዲሆን መጣሩ ከጀርባው ሌላ ነገር ያለ ነው የሚመስለው፡፡

“ጽንፈኝነት”ም ሆነ “አክራሪነት” በሀይማኖት ያልተገደቡ ናቸው፡፡ ጽንፈኛ ቡድኖች ከየትኛውም ሀይማኖት ሊመነጩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በጥንት ዘመን “Masada” የተሰኘ የአይሁዳዊያን ጽንፈኛ ቡድን ነበር፡፡ ዛሬም በእስራኤል ውስጥ በመቶ የሚቆጠሩ እጅግ ጽንፈኛ ቡድኖች አሉ፡፡ በ7ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ “ኸዋሪጃ” የሚባሉት ጽንፈኞች ከሙስሊሙ ዓለም ተነስተዋል፡፡ በዘመናችንም አል-ሸባብ፣ አል-ቃኢዳ፣ ቦኮ ሀራም የመሳሰሉት ተፈጥረዋል፡፡ ከክርስትናው ዓለምም በ“መስቀል ጦርነት” የሚያምኑ ጽንፈኛ ቡድኖች በተለያዩ ዘመናት ተነስተዋል፡፡ በዘመናችን በሰሜን ኡጋንዳ ጫካዎች ውስጥ መሽጎ ልዩ ልዩ ሰቆቃዎችን የሚፈጽመው Lords Resistance Army የተባለው ሚሊሺያ “ኡጋንዳን በወንጌልና በአስርቱ ትዕዛዛት እመራታለሁ” እያለ የሚለፍፍ ጽንፈኛ ቡድን ነው፡፡ ከሶስት ዓመታት በፊት ከሰማኒያ የሚበልጡ ንጹሃንን የጨፈጨፈው የኖርዌይ ጽንፈኛ ግለሰብም በሃይማኖቱ ክርስቲያን ነው፡፡ በጃፓን ሜትሮ (የምድር ውስጥ ባቡር) ውስጥ የመርዝ ጋዝ በመርጨት ንጹሃንን የፈጀው የኡም-ሺኖሮኪዮ ሀይማኖታዊ ቡድን “የፈጣሪን ትዕዛዝ እተገብራለሁ” የሚል ጽንፈኛ ነው፡፡ በሀይማኖት የማያምኑ (ማቴሪያሊስቶች፣ ኮሚንስቶች ወዘተ…) ጽንፈኛ ቡድኖችም በልዩ ልዩ ዘመናት ተነስተዋል፡፡የሚዲያው አካሄድ ግን ይህንን ሐቅ የተከተለ አይደለም፡፡ በአያያዙ ወደ አንዱ አቅጣጫ የተንጋደደ ነው፡፡ ይህ አድልኦ በግልጽ እየታየ ጽንፈኝነት ይጠፋል ማለት ዘበት ነው፡፡

ሌላኛው ደግሞ ሚዲያው ወሬ በማጋጋል ረገድ የሚጫወተው ሚና ነው፡፡ በልዩ ልዩ እምነቶችና ማህረበሰቦች ዘንድ እንደ ጸያፍ የሚታዩ ድርጊቶች በአንድ የዓለም ክፍል ሲፈጸሙ ሚዲያው ሽፋን የሚሰጣቸው አስቀድሞ በተቀመጠለት እቅድ ሳይሆን እንደማይቀር እገምታለሁ፡፡ እነዚህ ድርጊቶች መከሰታቸው እንዲታወቁ ሚዲያው ቶሎ ብሎ ወሬ ማራገብ ይጀምራል፡፡ ከሰዓታት ወይንም ከአንድ ቀን በኋላ ድርጊቱ ቁጣን ቀሰቀሰ ተብሎ ሌላ ወሬ ይራገባል፡፡ በሶስተኛው ቀን በቁጣው የተነሳሱ ጽንፈኞች ሰላማዊ ሰዎችን ገደሉ ተብሎ ይራገባል፡፡ በዚህ እርግብግቦሽ መሃከል ሌላ ቁጣ ይቀሰቀሳል፡፡ ሚዲያው እርሱንም ያራግባል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ይቀጥላል፡፡

እንደዚህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች ቀድሞውኑ የሚዲያ ሽፋን እንዲኖራቸው ባይደረግ ኖሮ የሚጠፋ ህይወትም ሆነ የሚበላሽ ንብረት ባልኖረ ነበረ፡፡ ነገር ግን ሚዲያው በሰዎች ስነ-ልቦና እየተጫወተ ድብቅ ተልዕኮውን ይፈጽማል፡፡ እግረ መንገዱንም ለራሱ ከፍተኛ ገቢ ይሸቅላል፡፡

 ይህንን ስጽፍ “International Qur’an Burning” ብሎ ዓለምን ለመጥበጥ የሞከረው ፓስተር ትዝ አለኝ፡፡ ሰውዬው የሚመራው Church መቶ አባላት እንኳ አልነበሩትም፡፡ ነገር ግን ሰውዬው እንዲያ አደርጋለሁ ብሎ ሲነሳ ሚዲያው ወሬውን እየተቀባበለ በዓለም ዙሪያ አዳረሰው፡፡ ዓለምም ለአስራ አምስት ቀን ተንጫጫ፡፡ ከዚያ ሰውዬው እቅዱን ሰረዘው ተብሎ ተነገረን፡፡ ሰውዬው የሰጠው ምክንያትም “በኒውዮርክ መንትያ ህንጻዎች ፊት ለፊት የሚሰራው መስጊድ ከተከለከለ እኔም እቅዴን እተወዋለሁ” የሚል ነበር፡፡እንግዲህ የሰውዬው ፍላጎት ቁርኣኑን ማቃጠል ሳይሆን የመስጊዱ ግንባታ እንዲቆም ማድረግ ነበር ማለት ነው፡፡ ሚዲያው ወሬውን እያጋነነው በዓለም ዙሪያ አዳረሰውና የልቡ እንዲደርስለት አደረገ፡፡ የሚዲያው ጫጫታ በጥርጣሬ መታየት አለበት የምለው ይህንን የመሳሰሉ በርካታ ታሪኮች ስላሉ ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ሌላው ነገር በዲሞክራሲ ስም የሌሎች እምነት ተከታዮችን ስነ-ልቦና የሚጎዱ አድራጎቶችን መፈጸሙ ነው፡፡ እነዚህ ተንኳሾች ሌሎች እንዲነኩባቸው የማይፈቅዷቸውን ነቢያት፣ ቅዱሳት እና መጻሕፍት በወረደ አኳሃን ይነካካሉ፡፡ የእምነቱ ተከታዮች ስለመብታቸው ሲጮኹ ደግሞ “በእገሌም እኮ ይቀለዳል” የሚል ምላሽ ይሰጣቸዋል፡፡ ይሁንና እነዚህ ቧልተኞች የማይደፍሯቸው ጥቂት ክፍሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ““Holocaust is a lie” ከተባለ በህግ ይጠየቃሉ፡፡ በነቢዩ ሙሐመድ እና በእየሱስ ክርስቶስ ሲቀልዱ ግን የዲሞክራሲ መብታቸው ነው ይባላል፡፡ “እንስሳት እኩል ናቸው፤ አንዳንዶቹ ግን በጣም እኩል ናቸው” የሚለው የጆርጅ ኦርዌል አባባል በሁሉም ቦታ ይሰራል ማለት ነው፡፡ ይሁንና እንዲህ ዐይነቱ ዓይን ያወጣ አድልኦ እየተደረገ ጽንፈኝነት በጭራሽ አይጠፋም፡፡ ስለዚህ ጽንፈኝነትን ለማጥፋት ከተፈለገ መከባበርን እንደ መርህ መያዝ ይገባል፡
*****
  ጽንፈኝነት ምንጊዜም ቢሆን አደገኛ ነው፡፡ የዓለምን ሰላምና የህዝቦችን አብሮ የመኖር ተስፋ ይገድላል፡፡ ስለዚህ የዓለም ህዝቦች ሁሉ በጋራ ሊታገሉት ይገባል፡፡ በተለይም በየሀገሩ ያሉ የየሃይማኖት ምሁራን እርስ በራሳቸው ሃሳቦችን የሚለዋወጡባቸው የ“Inter-faith” ፎረሞች ሊጠናከሩ ይገባል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ሚዲያው አድሎአዊነቱንና ድብቅ ተልዕኮ ፈጻሚነቱን ትቶ ሁሉንም ህዝቦች እኩል የማየትን ልማድ ማምጣት አለበት፡፡ እኛ አድማጮችና ተመልካቾችም ሚዲያው የሚዘበዝበውን ወሬ እንዳለ ከመቀበላችን በፊት ነገሮችን ከሁሉም አቅጣጫ መመልከት አለብን እላለሁ፡፡
---
አፈንዲ ሙተቂ
ጥር 2/2007 ተጻፈ፡፡

------

Monday, January 5, 2015

ቅዱስ ቁርኣን በአማርኛ ሲተረጎም




ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
ቅዱስ ቁርኣን በአማርኛ እንዲተረጎም ትዕዛዝ ያስተላለፉት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ነበሩ፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ትዕዛዙን የሰጡት ወዳጆቻቸው ከነበሩት የግብጹ መሪ ጀማል አብዱናሲር እና የሳዑዲ ዐረቢያው ንጉሥ ፈይሰል ቢን ዐብዱል አዚዝ “ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች እምነታቸውን በራሳቸው ቋንቋ እንዲማሩ ሊደረግ ይገባል” የሚል ጫና ስለመጣባቸው እንጂ በራሳቸው ተነሳሽነት አልነበረም፡፡ ቢሆንም ንጉሡ እንዲህ ዓይነት ስራዎች መፈጸማቸውን ቀርቶ መታሰባቸውን እንኳ እንደ ድፍረት ይቆጥሩ የነበሩትን የወግ አጥባቂ መኳንንትና መሳፍንትን ተቃውሞ ሳይፈሩ ስራው እንዲጀመር በመወሰናቸው ሊመሰገኑ ይገባል፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ትእዛዙን ያስተላለፉት ሐምሌ 18/1958 በተጻፈ ደብዳቤ ነበር፡፡ የንጉሡን ደብዳቤ በመንተራሰስ ስራው እንዲጀመር ያደረጉት ደግሞ በወቅቱ የትምህርት ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ምናሴ ሃይሌ ናቸው፡፡ ዶ/ር ምናሴ በተርጓሚነት የመረጡት ከአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው በማስታወቂያ ሚኒስቴር ስር የሚታተመው የ“አል-ዐለም” ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ በመሆን ይሰሩ የነበሩትን ሐጂ በሺር ዳውድን ነው (ሐጂ በሺር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ የተገነባው ትልቅ መስጂድ ኢማም እንደነበሩ አውቃለሁ፤ በሚዲያም አንድ ሁለቴ አይቼአቸኋለሁ፤ አሁን በህይወት ይኖሩ ይሆን?… እስቲ መረጃ ካላችሁ አቀብሉን)፡፡

ሐጂ በሽር ከዶ/ር ምናሴ የተሰጣቸውን አመራር በግርድፉ አልተቀበሉትም፡፡ “ቁርኣንን መተርጎም ሌሎች መጽሐፍትን እንደ መተርጎም ተደርጎ ሊታይ አይገባም፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ኮሚቴ ተዋቅሮ ኮሚቴው በሚሰጠው መመሪያ መሰረት ነው መሰራት ያለበት” የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት፡፡ አባባላቸው ተቀባይነት በማግኘቱም የቁርኣን ትርጉም ኮሚቴው ተዋቀረ፡፡ ከሀገር አቀፉ ኮሚቴ አባላት መካከል እንደርሳቸው የአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ የነበሩት ሼኽ ዓብዱል ከሪም ኑርሑሴን እና ሙሴ ሰሊም ቡሽቅራ ይጠቀሳሉ፡፡

  ኮሚቴው የትርጉሙን ስራ በብቃት ማከናወን የሚችሉ ዓሊሞችን ማፈላለግ ጀመረ፡፡ በወቅቱ ትልቁ ችግር የነበረው በእስላማዊ እውቀትም ሆነ በዓለማዊ ትምህርቱ ብቁ የሆነ ዓሊም ማግኘት ነበር፡፡ በተለይም አማርኛ ቋንቋን አስተካክሎ ከመጻፍ ጀምሮ የቋንቋውን የሰዋስው እና የስነ-ልሳን ህግጋትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ዓሊም ማግኘቱ አስፈላጊ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ዓሊሞቻችን የመጀመሪያውን መስፈርት ቢያሟሉም የኋለኛው ይጎድላቸው ነበር፡፡ ሆኖም ኮሚቴው በሓጂ በሺር ዳውድ ጠቋሚነት ሁለት ሰዎችን አገኘ፡፡ እነርሱም በጊዜው በደሴ ከተማ በሚገኘው የወይዘሮ ስሒን ትምህርት ቤት የሚያስተምሩት ሓጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ እና የሸሪዓ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩት ሼኽ ሰይድ ሙሐመድ ሳዲቅ ነበሩ፡፡ በዚህ መሰረት ሁለቱ ዓሊሞች ዋና ተርጓሚ ሆነው ስራቸውን ጀመሩ፡፡ ሓጂ በሺር ዳውድ እና ሼኽ ዐብዱል ከሪም ኑርሑሴን ደግሞ ተባባሪ ኤዲተሮች ሆነው እንዲሰሩ ተመደቡ፡፡

ተርጓሚዎቹ ከኤዲተሮቹ ጋር በቅርበት እየሰሩ በአስራ አምስት ወራት ውስጥ ስራቸውን አጠናቀቁት፡፡ ሆኖም ከየክፍለ ሀገሩ የተመረጡ ዑለማ የትርጉሙን ረቂቅ አንብበው የእርማትና የማሻሻያ ሓሳቦችን እንዲሰጡበት ያስፈልጋል የሚል ሃሳብ ተሰነዘረ፡፡ በዚሁ መሰረት የሚከተሉት ታላላቅ ዑለማ ወደ ኮሚቴው ቀርበው ረቂቅ ስራውን በማንበብ ሃሳባቸውን እንዲሰጡበት ተደረገ፡፡

ሼኽ ቡሽረል ከሪም ሙስጠፋ (ከወሎ)
ሓጂ ዩሱፍ ዐብዱራሕማን ገራድ (ከሀረርጌ)
ቃዲ ሙሐመድ ዐብዱራሕማን (ከትግራይ)
ሓጂ አሕመድ ዳለቲ (ከሸዋ)
ሓጂ መንዛረሁ ከቢር ሑሴን (ከአርሲ)

በመጨረሻም ተርጓሚዎቹ ከአምስቱ ዑለማዎች የተሰጡትን አስተያየቶችና ሌሎች የማሻሻያ ሃሳቦችን በመቀበል ረቂቁን አርመው አዘጋጁ፡፡ አሁን በእጃችን ላይ የሚገኘው የቅዱስ ቁርኣን የአማርኛ ትርጉምም በ1961 የመጀመሪያ ወራት ውስጥ ለህትመት በቃ፡፡
-----
ቅዱስ ቁርኣን በአማርኛ የተተረጎመበት ሂደት ከብዙ በጥቂቱ ይህንን ይመስላል፡፡ ይሁንና አንዳንድ ጸሐፊዎችና ደራሲዎች ይህንን ታሪክ እንዳሻቸው ሲጽፉት ተመልክተናል፡፡ ለምሳሌ ፕሮፌሰር ሃጋይ ኤልሪችን የመሳሰሉ ፀሐፍት የትርጉም ስራው ባለቤትና መሪ አድርገው የሚጠቅሱት ተርጓሚዎቹ ረቂቁን ከጨረሱ በኋላ በኮሚቴው ጋባዥነት ሃሳባቸውን ከሰጡት አምስት ዑለማ መካከል አንዱ የነበሩትን  ሓጂ ዩሱፍ ዐብዱራሕማንን ነው፡፡ ፕሮፌሰር ኤልሪች ዋነኞቹ ተርጓሚዎቹ ሓጂ ሙሐመድ ሣኒ እና ሼኽ ሰይድ ሙሐመድ ሳዲቅ መሆናቸውን አጥተውት አይደለም ይህንን የሚያደርጉት፡፡ እርሳቸው ዘወትር “አሕባሽ እና ወሃቢያ” እያሉ በሚያቀርቧቸው መጣጥፎች  ውስጥ ከፍተኛ የአትኩሮት ማዕከል አድርገው የቀረጿቸውን ሓጂ ዩሱፍ ዐብዱራሕማንን ለማጥቆር ሲሉ ነው እንዲህ ዓይነት ታሪክ የሚጽፉት፡፡ የሚገርመው ደግሞ ሌሎች ምሁራን ይህንኑ የሃጋይ ኤልሪችን ትረካ እንደ ወረደ ተቀብለው ማስተጋባታቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ፕሮፌሰር ፓትሪክ ዴስፕላት የሚባሉት ጀርመናዊ ምሁር በአንድ ጽሑፋቸው እንዲህ ይሉናል፡፡

“Hadj Yusuf became closer to the Ethiopian government and supervised the first official translation of the Quran into Amharic, published in 1961”.

(Patrick Desplat, The Articulation of Religious Identities and their Boundaries in Ethiopia: A Case Study on Harar, Journal of Religions in Africa, Lieden, 2005, pp 497)


  እርግጥ ሓጂ ዩሱፍ ቅዱስ ቁርኣንን የመተርጎም ብቃት ያላቸው ዓሊም ነበሩ፡፡ ከእዉቁ የመዲና ዩኒቨርሲቲ የተመረቁ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ከመሆናቸውም ባሻገር የአማርኛ ቋንቋ እውቀታቸውም ከፍተኛ ነበረ፡፡ በህይወት ሳሉም ለኢትዮጵያን ሙስሊሞች ብዙ ውለታዎችን ውለዋል (አንዳንዶቹን በቅርቡ እናያቸዋለን)፡፡ ፕሮፌሰር ሃጋይ ኤልሪች ይህንን የሐሰት ትረካ የፈጠሩት ግን መልካም ስራቸውን ለማውሳት አስበው ሳይሆን “ሓጂ ዩሱፍ የንጉሡ ቀኝ እጅ ነበሩ” የሚለውን የተቃዋሚዎቻቸውን ክስ ለማጠናከር በሚል ነው፡፡

ማንም ያሻውን ይበል፡፡ ቅዱስ ቁርኣን ወደ አማርኛ የተተረጎመበት ትክክለኛው ሂደት ከላይ የገለጽኩት ነው፡፡ በእኛ በኩል በትርጉም ስራው ላይ በተሳተፉት ዑለማዎቻችን መካከል አንዳች ልዩነት አናደርግም፡፡ ሁለቱ ተርጓሚዎች፤ ሁለቱ ኤዲተሮችና ከየክፍለ ሀገሩ የተመረጡት አምስቱ አራሚዎች በሙሉ ባለውለታዎቻችን በመሆናቸው ዘወትር እናስታውሳቸዋለን፡፡ አላህ የበጎ ስራቸውን ምንዳ በጀንነት ይክፈላቸው፡፡ አሚን!!
------
አፈንዲ ሙተቂ
ታሕሳስ 22/2007
ሀረር-ምሥራቅ ኢትዮጵያ
-------
ምንጮች
1.      ቅዱስ ቁርኣን፡ የአማርኛ ትርጉም በሰይድ ሙሐመድ ሳዲቅ እና ሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ፣ 1961፣ አዲስ አበባ
2.     “ቢላል መጽሔት”፡ ቅጽ 1፡ ቁጥር 9፡ ግንቦት 1985
3.     ቢላል መጽሔት፡ ቅጽ 1፡ ቁጥር 11፡ ሐምሌ 1985
4.      Patrick Desplat, The Articulation of Religious Identities and their Boundaries in Ethiopia: A Case Study on Harar, Journal of Religions in Africa, Lieden, 2005
5.     Haggai Elrich: Islam and Christianity in the Horn of Africa, Lynne Rienner Publishers, Inc, Boulder, 2010
6.    Haggai Elrich: Saudi Arabia and Ethiopia, 2003, London

------
Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history with special focus on the peoples of East Ethiopia. You may follow him on his blog and his facebook page by clicking the following links


Saturday, January 3, 2015

ሓጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብን ስናስታውሳቸው



 ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ

------

 

------
አንድን መጽሐፍ ከአንድ ጊዜ በላይ የማንበብ ልማድ የለኝም፡፡ አንዳንድ መጻሕፍትን ግን ሃያ፣ ሰላሣ እና አርባ ጊዜ ያህል እየደጋገምኩ አንብቤአቸዋለሁ፡፡ ከነዚያ መጻሕፍትም አንዱ “እስልምና እና የታላቁ ነቢይ የሙሐመድ ታሪክ” የሚል ርዕስ አለው፡፡ ደራሲው ደግሞ በፎቶግራፉ ላይ የምታዩዋቸው ሃጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ ናቸው፡፡

የሓጂ ሙሐመድ ሣኒን መጽሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበብኩት በታተመበት ዓመት ውስጥ (በ1980) ነው፡፡ መጽሐፉ ከአዕምሮ ሊጠፋ ያልቻለበት አንዱ ምክንያት በልጅነቴ ያነበብኩት መሆኑ ይመስለኛል፡፡ ከዚያ ወዲህም ለበርካታ ጊዜያት አንብቤዋለሁ፡፡ በሀገራችን ውስጥ እስከ 1980ዎቹ አጋማሽ ድረስ እስልምናን በተመለከተ እንደ መጣቀሻ ሆነው ይወሰዱ የነበሩት ከአማርኛው የቅዱስ ቁርኣን በተጨማሪ ይህ የሓጂ ሣኒ መጽሐፍ እና በአቶ አብዱልዋሲዕ መንዲዳ የተጻፈው “መልዕክተ እስላም” ነበሩ (በዘመነ ኃይለ ሥላሤ “ማዕሙን ማሕዲ” የሚባሉ ሰው “ተውሂድና ፊቅህ” የተባለ መጽሐፍ አሳትመው ነበር፤ ሐጂ ሣኒም “የሰላት መማሪያ” የሚባል መጽሐፍ በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ አሳትመዋል፤ ይሁንና እነዚህ ሁለት መጻሕፍት መኖራቸውን የሚያውቁት ጥቂቶች ናቸው)፡፡

  እንግዲህ ዛሬ በመጻሕፍት መሸጫ ሱቁና በየሼልፉ ለሞሉት እስላማዊ የአማርኛ መጻሕፍት ፋና ወጊ የሆኑት እነዚያ ሁለት መጻሕፍት ነበሩ፡፡ እኛንም በልጅነት ዕድሜአችን ኮትኩተው በማሳደግ የላቀ ሚና ነበራቸው፡፡
-------
ሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ከዚያች መጽሐፍ በፊት (በ1963) ከሼኽ ሰይድ ሙሐመድ ሳዲቅ ጋር በመሆን ቅዱስ ቁርኣንን ወደ አማርኛ ተርጉመዋል፡፡ ያ የቁርኣን ትርጉም በዚህ ዘመን እየወጡ ካሉት ትርጉሞች በብዙ መልኩ ይለያል፡፡ አንድ ሰው ከቁርኣን ፍቺ ከሚያገኘው መልዕክት በተጨማሪ የዐረብኛ ሰዋስውን ባህሪ ለማወቅ ካሻው ከዚያ የትርጉም ስራ ብዙ ቁም ነገሮችን ይማራል፡፡  ለምሳሌ እኔ አፈንዲ በዐረብኛ የሚታወቁትንና በአማርኛ ውስጥ የሌሉትን የአገናዛቢ አጸፋ ተውላጠ ስሞችን አጠቃቀም ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቅኩት ከዚያ የቁርኣን ትርጉም መሆኑን እመሰክራለሁ፡፡ ለዚህም አንድ አብነት ብቻ ልስጣችሁ፡፡ ዐረብኛው “ዛሊከ” ሲል “ይህ” ማለት ነው፤ ይህንኑ ተውላጠ ስም ወደ ብዙ ቁጥር ስንቀይረው “ዛሊኩም” ይሆናል፤ ይህም በአማርኛ ሲፈታ “ይሃችሁ” እንደማለት ነው፤ በትርጉም ስራው ውስጥም ይህንኑ የተውላጠ ስም አጠቃቀም በደንብ ታያላችሁ)፡፡

  በሌላ በኩል በአማርኛ “አጎት” ከተባለ የእናት ወይም የአባት ወንድም ማለት ነው፡፡ አክስት ከተባለ ደግሞ የእናት ወይም የአባት እህት ማለት ነው፡፡ በእንግሊዝኛም ሁለቱንም አጎቶች uncle እንላቸዋለን፡፡ ሁለቱን አክስቶች aunt ብለን እንጠራቸዋለን፡፡ በዐረብኛ፤ በኦሮምኛ፣ በሀረሪ እና በሶማሊኛ ቋንቋዎች ግን ሁለቱ አጎቶች እና ሁለቱ አክስቶች በተለያዩ ስሞች ነው የሚጠሩት፡፡ በዐረብኛ የእናት ወንድም የሆነው አጎት “ኻል” ነው የሚባለው፡፡ የእናት እህት ደግሞ “ኻላህ” ትባላለች፡፡ የአባት ወንድም “ዓም” የሚባል ሲሆን የአባት እህት “ዓምማህ” ትባላለች፡፡ እንግዲህ ቁርኣን በዐረብኛ የወረደ እንደመሆኑ ሁለቱን አጎቶች በዐረብኛው ስልት “ኻል” እና “ዓም” እያለ ነው የሚጠራቸው፡፡ ሁለቱ ሰዎች በአማርኛ ቋንቋ በአንድ ዘርፍ “አጎት” ተብለው ከተጠሩ የቁርኣን ፍቺ የተዛባ ሊሆን ነው (ለምሳሌ “ኻል” እና “ዓም” እኩል የወራሽነት ድርሻ የላቸውም፤ በመሆኑም ሁለቱ ሰዎች “አጎት” ተብለው ከተጠሩ ይህንን ልዩነት ማስገንዘብ ከባድ ሊሆን ይችላል)፡፡

እነ ሓጂ ሣኒ ይህንን ክፍተት ለመሙላት “አሪፍ” ቀመር ነው የተጠቀሙት፡፡ ይህም በወሎ ከሚነገረው የደዌ ኦሮምኛ ዘዬ ተጨማሪ ቃላትን መደበር ነው፡፡ በዚህም መሰረት እነ ሓጂ ሣኒ ባሳተሙት የቁርኣን ፍቺ ውስጥ “አጎት” ማለት የአባት ወንድም ብቻ ነው፡፡ የእናት ወንድም ደግሞ “የሹማ” ተብሎ ነው የተጠራው (የደዌ ኦሮሞዎች ናቸው እንዲህ የሚሉት፤ ሌላው ኦሮሞ “ኤሱማ” ነው የሚለው)፡፡ የአባት እህት “አክስት” የተባለች ስትሆን የእናት እህት ደግሞ “የሹሜ” ተብላ ተሰይማለች፡፡ በዚህ ዓይነት ዘዴ የቁርኣኑን የዐረብኛ መልዕክት ያለምንም ችግር ወደ አማርኛው ለመመለስ ተችሏል፡፡

በቅዱስ ቁርኣኑ ፍቺ ውስጥ አጽንኦት የተሰጠው ሌላው ጉዳይ ደግሞ የድምጾችና የፊደላት ውክልና ነው፡፡ እንደሚታወቀው በዐረብኛና በግዕዝ ቋንቋዎች ውስጥ ያሉ በርካታ ድምጾችን በአማርኛ ውስጥ አናገኛቸውም፡፡ በአማርኛ “አ” እና “ዐ” እየተባለ ቢጻፍም በንባብ ደረጃ ምንም ልዩነት አናደርግባቸውም፡፡ በግዕዝና በትግርኛ ቋንቋዎች ግን ሁለቱ ፊደላት የተለያዩ ድምጾችን ነው የሚወክሉት፡፡ ዐረብኛም “የአንድ ፊደል ለአንድ ድምጽ” መርህን የሚከተል ቋንቋ በመሆኑ በጽሑፍ ጊዜ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ እነ ሓጂ ሣኒ ቁርአኑን በአማርኛ ሲተረጉሙ በተለይ የተጸውኦ ስሞች በኦሪጂናሌው ድምጽ መጠራት እንዳለበት አምነዋል፡፡ በመሆኑም በትርጉም ስራው ውስጥ ያሉት የተጸውኦ ስሞች ይህንን መርህ በመከተል ነው የተጻፉት፡፡ ለምሳሌ በትርጉሙ ውስጥ “ያሕያ” እንጂ “ያህያ” የሚል ስም አታገኙም (“ሐ” ቀጭኑንና በጉረሮ የሚነገረውን የዐረብኛውን “ሐእ” ነው የሚወክለው፤ ሃሌታው “ሃ” ደግሞ “ዋው” ከተሠኘው የዐረብኛ ፊደል አጠገብ የሚገኘውን ወፍራሙን “ሀ” ነው የሚወክለው)፡፡  የመርየም ልጅም “ዒሳ” እንጂ “ኢሳ” ተብሎ አልተጠራም፡፡ “ዒስማኢል”፣ “ኢብራሂም”፣ “አዩብ”፣ “ኢስሓቅ”፣ “ያዕቁብ”፣ ወዘተ… አሁን በጻፍኩት መልኩ ነው የተጠሩት፡፡
 
  ከዚህ ሌላ እነ ሓጂ ሣኒ በጥንታዊው ዐረብኛ ያሉትን ቃላት ለመጥራት ሲሉ ከየገጠሩ የሰበሰቧቸው ጥንታዊ የአማርኛ ቃላት በጣም ያስድምማሉ፡፡ “ዘለበት”፣ “ቀንዘል”፣ “እንዛዝላ”፣ “ሰርክ”፣ “አጎበር” ወዘተ…. የመሳሰሉ ቃላትን ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቅኩት ከዚሁ የቅዱስ ቁርኣን ትርጉም ነው፡፡

  አንዳንድ ሰዎች የነ ሐጂ ሣኒ የቁርኣን ትርጉም ይከብደናል ይላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በመጽሐፉ መጀመሪያ ላይ ያለውን መቅድም ስለማያነቡት ይመስለኛል ፍቺው ከበደን የሚሉት፡፡ መቅድሙን በአትኩሮት ያነበበ ሰው ምንም ግራ የሚገባው አይመስለኝም፡፡

እንግዲህ ሓጂ ሙሐመድ ሣኒ ማለት ያንን የቁርኣን ትርጉም ካበረከቱልን ሁለት ብርቅዬ ዑለማእ አንዱ ናቸው (ሼኽ ሰይድ ሙሐመድ ሳዲቅም የሃጂ ሣኒን ያህል ትልቅ ገድል ያላቸው ዓሊም ናቸው፤ እርሳቸውንም ወደፊት እንዘክራቸዋለን፤ ኢንሻ አላህ)፡፡
-----
 ሓጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ የሚጠቀሱበት ሌላው ታሪክ የኢትዮጵያው መጅሊስ እንዲመሰረት ያደረጉት ተጋድሎ ነበር፡፡ በንጉሡ ዘመን መጅሊስ የሚባል ነገር አይታወቅም(“መጅሊስ” ይቅርና ዐረፋና ዒድ አልፈጥርም አይከበሩም ነበር)፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን መብትና ጥቅም በጋራ የሚያስከብር ተቋም አልነበረም፡፡ ሙስሊሞችን ወክሎ የሚናገር፣ የሃጂና ዑምራ ጉዞአቸውን የሚያቀላጥፍ፣ መስጂዶችንና አውቃፍን የሚገነባና የሚያስተዳድር ተቋም ያስፈልግ ነበር፡፡ ሓጂ ሙሐመድ ሣኒ ከሌሎች ዑለማ ጋር በመሆን ሙስሊሞች የራሳቸው ተቋም እንዲኖራቸው ለረጅም ጊዜ ይሟገቱ ነበር፡፡ የ1966ቱ አብዮት ሲፈነዳ ህዝበ ሙስሊሙ መብቱ እንዲከበርለት የሚጠይቀውን የሚያዚያ 20/1966 ታላቅ ህዝባዊ ሰልፍ አደረገ፡፡ ሃጂ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብም የመጅሊሱን ጉዳይ ይዘው ከመንግሥት ጋር መሟገታቸውን ቀጠሉ፡፡ በአላህ ፈቃድ ትግሉ ሰምሮ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በብሄራዊ ደረጃ ተቋቋመ፡፡ ሓጂ ሣኒም ይህንን ተቋም እስከ እለተ ሞታቸው ከመሩት በኋላ በ1981 አረፉ፡፡ አላህ ስራቸውን ይውደድላቸው፡፡
-----
------
Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history with special focus on the peoples of East Ethiopia. You may follow him on his blog and his facebook page by clicking the following links