Saturday, December 27, 2014

የቆምጬ አምባው- ቃለ-ምልልስ (ክፍል አንድ)




ከበአበባየሁ ገበያው
 -------
የሶሻሊዝምን ርዕዮተ ዓለም 1960ዎቹ ማብቂያ ላይ በአገራችን ያስተዋወቁት የደርግ ባለስልጣናት ሶሻሊዝምን የተረዱት 70 ዓመቱ አዛውንት የጐጃሙ ቆምጬ አምባው በተረዱት መንገድ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ ታሪክ አሁን ከምናየው ፍፁም የተለየ ይሆን ነበር፡፡ ለእሳቸው ሶሻሊዝም ማለት ሠርቶ ማሰራት ነበር፤ ሶሻሊዝም ሜዳ ተራራውን አረንጓዴ ማልበስ ነበር፤ ለእሳቸው ሶሻሊዝም ብዙ /ቤት፣ ክሊኒክ፣ ወፍጮ ቤት፣ መገንባት ሌባን ማጥፋት ነው፡፡ በደርግ ዘመን 13 ዓመት የተለያዩ ወረዳዎችን ያስተዳደሩት ቆምጬ፤ በሠሯቸው በርካታ የልማት ሥራዎችና ብልሃት በታከለበት የአመራር ችሎቻቸው ከመንግስትም ከህዝብም ተወዳጅነት እንዳገኙ ይናገራሉ፡፡ እሳቸው ያልተናገሯቸው ብዙ ነገሮች እየተፈጠሩ በስማቸው እንደሚነገሩ አዛውንቱ ቢናገሩም እራሳቸው በትክክል የፈፀሟቸውም ቢሆኑ ከፈጠራዎቹ የሚተናነሱ አይደሉም፡፡ በሃላፊነት በሚመሩት ወህኒ ቤት የነበሩትን በጣታቸው እየፈረሙ ደሞዝ የሚበሉ ያሏቸውን ፖሊሶች 60 ቀን ማንበብና መፃፍ እንዲማሩ የፈጠሩት ብልሃት ተጠቃሽ ነው፡፡ ኰሎኔል መንግስቱ /ማርያም በሥራቸው ተደስተው ሽጉጣቸውን ሲሸልሟቸው አልተቀበሉም - ከሽፍታ ያስፈታሁት 18 ሽጉጥ አለኝ በማለት፡፡ በምትኩ ግን ለህዝቡ መብራትና ውሃ እንዲገባለት ጠይቀዋል፡፡ በትውልድ አገራቸው በጐጃም ያገኘቻቸው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ሰፊ ቃለ-ምልልስ ያደረገችላቸው ሲሆን አንባቢያን የእኒህ መለኛ አብዮተኛ ታሪክ ከነለዛቸው ይደርሳቸው ዘንድ ቃለምልልሱን እንደወረደ አቅርበነዋል - ከአነጋገር ዘዬአቸው ጋር፡፡
------
የት ተወለዱ? መቼ?
የተወለድኩት በጠላት ወረራ ዘመን ነው፡፡ በጐዛምን ወረዳ ማያ አንገታም ቀበሌ ገበሬ ማህበር፣ አባላይ በተባለ ቦታ ሜዳ ላይ ተወለድኩ፡፡ እናቴም አባቴም አርበኛ ናቸው፡፡ ስወለድ ማን እንበለው እያሉ ሲመካከሩ ሳለ አንድ አውሮፕላን ትመጣና ክምር ስታቃጥል፣ አባቴ አነጣጥሮ ቢተኩስ ተንከታክታ ወረደች፡፡ ያን ጊዜ ቆምጬአምባው እንበለው፤ ይኼ ልጅ ገዳም ነው ተብሎ ነው ስም የወጣልኝ፡፡
ለትምህርት እንደደረስኩ እዚያው ቀበሌ አንገታም ጊዮርጊስ የቄስ ትምህርት ተምሬ፣ ዳዊት ፆመድጓ ጨርሼ ወደ ቅኔ ቤት ገባሁ፡፡ በሽታ እንደገባ አባቴ ከቅኔ ቤት አውጥተው ወሰዱኝ፡፡ 15 ዓመቴ የሰባት ደብር የጐበዝ አለቃ ሆንኩኝ፡፡
ቆምጬ ማለት ምን ማለት ነው?
ደፋር፣ ጠንካራ፣ ቆራጥ ማለት ነው፡፡
በሸዋ ግን ትርጉሙ ሌላ መሰለኝ. . .
አዎ፡፡ በእኔ በኩል ግን ቆምጬ ማለት ታይቶ የሚታለፈውን የሚያውቅ፣ ታይቶ የማይታለፈው ላይ ቆራጥ እርምጃ የሚወስድና ሩህሩህ፣ የዋህ ማለት ነው፡፡
ወጣትነትዎ እንዴት አለፈ?
በወጣትነቴ የቤተሰብ ተጽዕኖ ነበረብኝ. . . ሰው ፊት ጠላ መጠጣት አይፈቀድልኝም፤ ውሃ እንኳን ጭልጥ አድርጎ መጠጣት እንከለከላለን፡፡ ስንበላ አፋችሁን ገጥማችሁ አፋችሁን አታጩሁ፤ እየተባልን ነው ያደግነው፡፡ አባቴ ቅዳሴ አስቀድሼ ወጥቼ መሃራ አያስቀምጡኝም ነበር፡፡ ..መሃራ መብላት ያለበት አቅም ያጣ፣ ቤቱ የሚበላው የሌለው ነው፡፡ አንተ ሁሉ ነገር ቤትህ ሞልቶ የተረፈህ ስለሆንክ ምንም እንዳትቀምስ.. እባላለሁ፡፡ ሰርግ ስንሔድ የአባቴን መሣሪያ ይዤ ከበስተጀርባው ነበር የምቀመጠው፡፡ እህል በወሰክንባ(ሞሶብ) ነበር የሚመጣልኝ፡፡ ጨዋታ አምሮኝ ከጉብላሊቱ(ህጻናት) ጋር መደባለቅ አይፈቀድልኝም፡፡ ከፍተኛ ተጽዕኖ ነበረብኝ፡፡ በፆም ቀን ከስምንት ሰዓት በፊት ስንበላ ከተገኘን እንደበደባለን፡፡ የገና ጨዋታ፤ ፈረስ ግልቢያ፣ ዋና፣ አውሬ አደን ምን ልበልሽ ያልተሳተፍኩበት የለም ...ከሁሉም ግን ደስ የሚለኝ አደን ነበር፡፡
ምን አድነዋል?
ድኩላው፣ አሳማው፣ ሚዳቋው. . . በለሴ ሆኖ ወደ እኔ ይመጣል፡፡ በቃ እያልን አገሬ ይዤ እገባለሁ፡፡ ከሰው የተጣላሁ እንደሆን አባቴ አይለቀኝም ነበር፡፡
የደብር አለቃ ሳለሁ ሰው ሲጣላ ባውቀውም ባላውቀውም አስታርቅ ነበር፡፡ በዚያውም የስብሰባን ጥቅምና የአንዳንድ ነገሮችን ሁኔታ ማየት ጀመርኩ፡፡
ስለትዳርና ቤተሰብ ይንገሩኝ. . .
አስር ልጆች አሉኝ፡፡ ባለቤቴ አሁን ያለችት የልጆቼ እናት ናት፡፡ ለሷ የእኔ እና የእሷን ስምንት ስምንት የቀንድ ከብት አማተን ደርሰን ሃብታም ሆነን፤ ኋላ ገንዲ በሽታ መጣና ከብቱን ሲፈጀው ተበሳጨሁና ወደ ጐጃም ጠቅላይ ግዛት መጣሁ፡፡ የምክትል ፀሃፊነት ፈተና ተፈተንኩና አለፍኩ - ጃናቢት በተባለች ስፍራ፡፡
ደሞዙ ጥሩ ነበር?
25 ብር ነው፡፡ ማለፌን ከሰማሁ በኋላ አንድ አህያ ተልባ፣ አንድ አህያ ኑግ ጭኜ ወደ ደብረማርቆስ ገበያ ወጣሁና ቦጋለ በረዳ የሚባል ቦታ ሸጥኩት፡፡ ከዚያ ምክትል ፀሃፊነት አለፍኩ አልኩና ሁለት አዝማሪ ጥሩ ብዬ፣ ሹመቴን እያነሳሳ ሲዘፈን ሲጠጣ ሲበላ ታደረ፡፡ ጥቂት ብር ቀረችኝ፡፡ ማለዳ የሹመት ደብዳቤውን ልቀበል አውራጃ አስተዳደሩ ስሄድ የወረዳው ገዢ ቀኝ አዝማች ረታ ፈረደ ይባላሉ ..አንተ ነህ ምክትል ፀሃፊ የተሾምከው?.. አሉኝ፡፡ አለባበሴም ደህና ነው ያን ጊዜ፤ ንቁ ነኝ፡፡ ..አዎ.. አልኳቸው፡፡
..አንተማ የዋናው የከበርቴ ልጅ አይደለህ፤ ሰባት ጉልት እያሳረሳችሁ፤ አንተን አንቀጥርም! በል ውጣ ከቢሮዬ.. አሉኝ፡፡ ተበሳጨሁ ገንዘቤን ጨርሻለሁ፤ ሌላ አማራጭ ሳፈላልግ በደብረማርቆስ ወህኒ /ቤት ለወታደርነት ቅጥር የተለጠፈ ማስታወቂያ አየሁ፡፡ ወዲያው እለቱን ተመዝግቤ አለፍኩ፡፡ ሲያዩኝ በቁመትም በክብደትም እኩል መጣሁ፡፡ ወደ ማሰልጠኛ ላኩኝ፡፡ ከማረሚያ ቤት አስተዳደር ወታደሮች አስራ ሰባት፣ ከፖሊስ ሰባት ነበር የተመለመለው፡፡ እዚያ ተደባልቀን ስንማር በፀባይ፣ በተኩስ፣ ህግ በማወቅ አንደኛ ወጣሁ፡፡የዚያን ጊዜው አገረገዥ ደጅአዝማች ፀሃይ እንቁ ኃይለስላሴ፣ የምስክር ወረቀት ሲሰጡ ..በወታደራዊ አቋም፣ በፀባይና በተኩስ ወታደር ቆምጬአምባው ይልማ አንደኛ.. ብለው ሸለሙኝ፡፡ ኮሎኔል አሰፋ ወንድማገኘሁ ከሚባሉ ከወህኒ ቤቱ አዛዥ ጋር ጠሩኝና ..ከአስራ ሰባቱ ወታደር አንተ በጣም ጠንካራ ነህ፤ ወደፊትም እናሳድግሃለን.. አሉና ሃምሳ ብር በግሌ ሰጡኝ፡፡ የወህኒ ቤቱ /ቤት የእስረኞች የህግ አማካሪና የጠቅላይ ግዛቱ ወህኒ ቤት ጠበቃና ነገረ ፈጅ አደረጉኝ፡፡ ኮልት ሽጉጥም ሸለሙኝ፡፡
ከእስረኞች ጋር ስለነበርዎ ግንኙነት ያጫውቱኝ፡፡
እስረኛው አንዳንድ ጊዜ ..ምግብ ጠቆረ.. ይልና ያድማል፡፡ ..እኛ መነገጃ አይደለንም.. ይላል፡፡ የጐጃም ጠቅላይ ግዛት በሙሉ፣ 35 ወረዳና የሰባቱ አውራጃ እዚሁ ነበር የሚታሰረው - የመተከል፤ የቤንሻንጉል፤ የባህርዳር ሁሉ ማለት ነው፡፡ እስረኛው ሲያድም እኔ ሽጉጥ ታጥቄ በመሃላቸው እገባና ..እናንተን ያሰራችሁ ሰው አይደለም፤ ያሰራችሁ እግዚአብሔር ነው፡፡ እዚህ እኮ የምትፀልዩበት፣ የምትማፀኑበት፣ ፍርድ እናግኝ ብላችሁ የምትለማመኑበት ነው፡፡ የጐጃም ሰው ሆዳም አይደለም ምግብ አነሰኝ ብሎ አይናገርም፡፡ አናንተ ቆሎ፣ በሶ፣ በግም ፍየልም አሳርዳችሁ ትበላላችሁ፤ አገራችን ተሰደበ.. ብዬ ያንን ጠቆረ አንበላም ብለው የተውትን ጥቁር እንጀራ እነሱ መሃል ሆኜ ቆርሼ እበላዋለሁ፡፡ ያንዜ ያጨበጭባሉ፡፡ ከዛ በኋላ አድማው ይበተናል፡፡ ..አሁን ትፈታላችሁ ግማሻችሁ በአመክሮ፤ ግማሾቻችሁ ደግሞ ፀባያችሁ ጥሩ ከሆነ ሚያዚያ 27 በአርበኞች ድል በዓል ወይም ሐምሌ 16 በጃንሆይ ልደትና ጥቅምት 23 በጃንሆይ የዘውድ በአል ትፈታላችሁ፡፡ እንቢ ካላችሁ ግን ችግር ላይ ትወድቃላችሁ.. ስላቸው በጀ ይላሉ፡፡ የጣቢያው አዛዥ ንግግር ስለማያውቅበት ቀጠሮ ስጡኝ ብዬ እኔ ነበርኩ የማናግራቸው፡፡
ለእስረኛው ያወጡት ህግ ነበር ይባላል?
ህጉ እያንዳንዱ እስረኛ ሰውነቱን በሳምንት አንድ ቀን ፀጉሩን ዕለት ዕለት እንዲታጠብ የሚል ነው፤ አሽቶ የሚያጥበው በወር 1 ብር ከፍሎ ሰው ራሱ ይቀጥራል፡፡ እስረኛው ገንዘብ ነበረው፡፡ ሞልቶታል፡፡ ከዚያ አሰልፋቸውና ከኪሴ ነጭ መሀረብ አውጥቼ የአንዱን ደረት አሸት አድርጌ ..ይሄው እድፍ አለው ውጣ.. እለዋለሁ፡፡ ንፁህ ሆኖ ያገኘሁትን ደግሞ አንድ ብር አወጣና እሸልመዋለሁ፡፡ ያን ጊዜ እስረኛው ሁሉ ንፁህ ለመሆን መሯሯጥ ነው፡፡ የመኝታቸውን ዳትም ክፍላቸው እየገባሁ እፈትሽ ነበር፡፡ ይሄን አይተው ደጃዝማች ፀሃይ (1958) የደ/ማርቆስ ቤተመንግስት ሲሰራ ..ይሄ ጐበዝ ልጅ ነው፤ ጠንካራ ሰራተኛ ነው.. ብለው ወሰዱኝና እንደገና ተሸለምኩ፡፡
ንጽህናውን ያልጠበቀ እስረኛስ? ቅጣት አለው?
አዎ ይቀጣል፡፡ አስር የችግኝ ጉድጓድ አስቆፍረዋለሁ፤ በግቢው ውስጥ የፍራፍሬና የአትክልት ስፍራ ስለነበረ እሱንም አስቆፍራቸዋለሁ፡፡ ሰው ገድሎ የታሰረውን ግን ወታደሩ ስራ አናሰራም ብሎ ይቃወመኛል፤ መሳሪያ ነጥቆን ይሄዳል በሚል፡፡ ..በያዝከው መሳሪያ አጨማደህ አትጥለውም፤ እንግዲህ በእግር ብረት ታስሮ አይሞትም.. እልና፤ የገደለውን ሁሉ ሰብስቤ .. ተንቀሳቀሱ ይሄ ስራ የእናንተ ነው፣ አካልና አእምሮአችሁን አስተባብራችሁ በሞራል የጠነከራችሁ እንድትሆኑ ስሩ.. እላቸዋለሁ፡፡ በጣም ይወዱኛል፡፡ /ቤት ለስራ ስሄድ ባዶ ወረቀት ካገኘሁ ሰብስቤ አመጣና አንዳንዱን በሽልማት እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘመድና ለምሽት ደብዳቤ መጠጣፊያ፡፡ ከዚያ ፊደል ሠራዊት የሚባል መሰረተ ትምህርት ተቋቋመ፡፡ በደጃዝማች ፀሃይ ጊዜ፣ አቶ ሸዋቀና የተባሉ የትምህርት ሚኒስቴር ሃላፊ፣ የጠቅላይ ግዛቱን ወህኒ ቤት እሱ ነው ማስተባበር የሚችለው አሉና እኔን ሾሙኝ፡፡ ማንበብ መፃፍ የማይችል፤ በጣቱ እየፈረመ የሚበላ ፖሊስ ሞልቷል - ያኔ፡፡ አዳራሽ ላይ ሰበሰብኩና እስከ ስልሳ ቀን ድረስ ማንበብና መፃፍ ካልቻላችሁ ሚስጢር ነው የምነግራችሁ ..ትባረራላችሁ.. ተብሏል አልኳቸው፡፡ (ሳቅ) መንግስት አቋም ይዟል፤ ማታ ማታ ልጆቻችሁ ቤት ውስጥ ያስተምሯችሁ አልኳቸው፡፡ ማንበብ መፃፍ የማይችል ሠራዊት በፍፁም አይሆንም፤ እየተባለ ነው ስላቸው. . . ማታ ማታ ጥናት ነው፣ ማንበብ ነው፡፡ ሲፈተኑ ደህና ናቸው፡፡ ..ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘኢትዮጵያ.. ብዬ ብላክ ቦርዱ ላይ ፃፍኩና ገልብጡ አልኳቸው - እንዳለ ፃፉት፡፡ በዚህም ተሸለምኩ፡፡
አብዮቱ ሲፈነዳ በአንድ ቀበሌ ውስጥ ህዝቡ ስለሚያውቀኝ የአብዮት ጥበቃ የፍርድ ዳኛ ሸንጐ ውስጥ ገባሁ፡፡ በደብረማርቆስ በድሮው ቀበሌ 8 ዳኛ ሆንኩ፡፡ ስራዬ እርቅ ነበር - ይቅር ተባባሉ ማለት፡፡ ፍርድ የሚሻውን ደግሞ ፍርድ እያሰጠሁ እየቀጣሁ በሬድዮ አስነግራለሁ፡፡ ጉልታዊ አገዛዝን እየኮነንኩ፤ የሠራተኛውን መደብ ንቃ እያልኩ የተናገርኩ እንደሆነ መልእክቴ ሁሉ በሬድዮ ይሰማ ነበር፡፡
በአፄ ኃይለስላሴ ጊዜ ከሽፍቶች ጋር ተደራድረሃል ይባላል?
የገበሬው አመ በሚባልበት በነ ባምላኩ ጊዜ፣ እነ ደጃዝማች ፀሃይ ከደ/ማርቆስ ይነሱ በሚባል ጊዜ ከብፁዕ አቡነማርቆስ ጋር ደብረወርቅ ሄጃለሁ፡፡ ገበሬው ሰው ቆምጬን ያውቀዋል ብሎ ለከኝ፡፡ በኢሊኮፍተር ነበር የሄድነው፡፡ ከዛ ከኢሊኮፍተሩ ላይ ስንወርድ ከርቀት አነጣጥረው የብፁዕ አቡነ ማርቆስን ቆብ ይመቱታል፤ ..ጐንበስ ይበሉ ጐንበስ ይበሉ.. አልኳቸው፡፡ በኋላ እንደ ምንም ወጣን፡፡
በዚያን ወቅት እንግዲህ ሀገሩ ሁሉ ሸፍቶ ነበር፡፡ ወንበዴ በወንበዴ ሽፍታ በሽፍታ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ማነው አሁን እነሱ ሄዶ እርቅ የሚለምን ተብሎ አገር ይታመሳል ..እኔ እሄዳለሁ ምን ችግር አለው.. ብዬ ሽጉጡንም፣ ኡዚ አቶማቲክ ጠመንጃም ይዤ በመሃላቸው ገባሁና ..ደህና ዋላችሁ፤ ደህና ዋላችሁ.. ስል ሁሉም ተነስቶ ሰላም አለኝ፡፡
ሽፍቶቹ?
እህሳ! ሁሉ ሽፍታ እኮ ታስሮ የተፈታ ነው፡፡ በእስር ቤት ውስጥ ሁሉም ነበር የሚያውቀኝ፡፡ በኋላ ከፊታቸው ቆሜ ንግግር አደረኩ፡፡ ..እናንተ ብቻችሁን አትችሉም፡፡ ሃገር ልታስደበድቡ ነው፤ ክቡር ዘበኛ መጥቷል፡፡ ዛሬ ምላሻቸውን እንፈልጋለን መልሱን አምጣ ተብዬ ነው.. ስላቸው ..አንተማ የሀገራችን ልጅ ነህ ሌላ ቢሆን በጥሰን በጣልነው ነበር፡፡ በእስር እያለን ከሚስታችን ከዘመዳችን እያገናኘህ ብዙ የረዳኸን ነህ፡፡ አሁንም የምትለንን እንሰማለን፤ ጦርነት አንፈልግም፤ እኛ የምንፈለገው አንድ ብር ከሃምሳ ግብር እንዲነሳልንና ደጃዝማች ፀሃይ እንዲወርዱልን ነው.. አሉኝ፡፡ እዚያው ያሉትን ቁጭ ብዬ ፃፍኩና ..መልስ እስክናመጣላችሁ ወደ ቤታችሁ ግቡ፡፡ እርሻም እረሱ፤ የመጣውም ጦር ይመለስ፤ ጳጳሱም መጥተው ተኩሳችሁ ልትገሏቸው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ነው ያወጣቸው፡፡ አሁን እሳቸው ሊያስታርቁ ቢመጡ ሊያስተኩሱ እንደመጡ ሁሉ እንዲህ ታደርጉ? እኔም ደሞ የሀገር ሰው ነህ፤ ወንድም ነህ ተብዬ ተመርጬ ነው የመጣሁ፡፡ የተከበሩ አቶ መኮንን እውነቴን፤ የተከበሩ በከፋ የኔነህን ታውቋቸዋላችሁ አይደል? በአምስት አመት የጠላት ወረራ ዘመን ከደጃዝማች በላይ ዘለቀ ጋር አብረው የነበሩ፣ የደጃዝማች በላይ ዘለቀን ማህተም ይዘው ይፉ የነበሩ ናቸው. . . ጠላትን ያርበደበዱ የነበሩ፡፡ ዛሬ ደግሞ አስታራቂ ሆነው መጡ፡፡ በሉ እነሱ ይምጡና ሰላም በሏቸው.. አልኳቸው፡፡ ..በቃ እሺ...... ወታደር እንዳይመጣ እነሱ ይምጡ.. አሉ፡፡ ይዤአቸው ሄድኩ፡፡ ብቻ ወዲህ ወዲያ ብለን ደጃዝማች ፀሃይ ወረዱ፡፡ ሰላም ሰፈነ፡፡
የደርግ መንግሥት እንዴት ተቀበለህ?
በደርግ ሥርዓት ሌባ፣ ሴሰኛ፣ ገንዘብ የሚያታልለው፣ ጥቅም ፈላጊ ፓርቲውን አይቀላቀልም ነበር፡፡ እንጃ! በኋላ አበላሽተውት እንደሆነ አላውቅም፡፡ የመደብ ትግሉን ለመቀላቀል የሚፈልግ ሰው የግል ማህደሩ ይታያል፡፡ እኔ በመጀመርያ በሙሉ ፈቃደኝነት ማመልከቻ የፃፍኩት ..የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራምን ተቀብያለሁ፤ ከሰፊው ህዝብ ጥቅም ይልቅ የራሴን ጥቅም አላስቀድምም፤ ከራሴ ጥቅም ይልቅ የሰፊውን ህዝብ ጥቅም አስቀድማለሁ፣ እየተማርኩ ከአብዮቱ ጋር ለመቀላቀል ፈቃደኛ ነኝ.. ብዬ፡፡ ማመልከቻዬ ተመረመረ፤ ጀርባዬን አስጠኑኝ - በደህንነቶች፤ በጐረቤት፡፡ በኋላ በቀበሌ የጥናት ክበብ ውስጥ አስገቡኝ፡፡ በመንግሥት ሥራ ተወጥሮ የጥናት ክበቡ ላይ ያልተገኘ እንኳን ይሰረዛል፡፡ መማር ግድ ነበር፡፡
ትምህርቱ ምንድን ነው?
የካፒታሊስት ስርዓትና፤ የሶሻሊስት ስርዓት ምንድን ነው? ጠቃሚው የትኛው ነው? በሚል ነበር፡፡ ከዛም የሠራተኛው መደብ ንቅናቄ በጀርመን በአሜሪካ ምን ይመስላል የሚለውን. . . ከዛም የምትበይው፣ አረማመድሽ፣ ንቃትሽ፣ ንግግርሽ ሁሉ ይገመገማል፡፡ የገባው ሁሉ አይዘልቅም፡፡ ልክ መንገድ ላይ መኪና እንደሚጥለው ፌርማታ ላይ እየተራገፈ ይሄዳል፡፡ ከብዙ ምልምሎች ጥቂቶች ቀረን፡፡ . . . እኔ እዚህም ምስጉን ነበርኩ፡፡
ምስጉንነትህን ማን ነገረህ?
ጓድ መንግሥቱ ናቸዋ! አፍና ተግባር ይሉኝ ነበር፡፡ አንደዜ እሳቸው በምሠራበት አቸፈር አካባቢ መጥተው ሳለ. . . እኔ አላውቅም ነበር እንደሚመጡ፡፡ የከብቶችን አዛባ እዝቅ ነበር፡፡ ኮረኔል ዘለቀ .. ሰላም በል ሰላም በል.. አሉኝ፡፡ ሸሚዜን ወደ ላይ ሸበሸብኩና ስጨብጣቸው ..ጓድ ቆምጬ አስተዳድሩ ተባለ እንጂ አዛባ ይዛቁ ተባሉ.. አሉኝ፡፡ ..ጓድ መንግስቱ፤ እኔ ካልሠራሁ ሌላው ስለማይሰራ ነው.. አልኳቸው፤ ዞረው ሁሉን አዩ፡፡ በቆሎው፣ በርበሬው ደርሷል፡፡ በቆሎውን ሸለቀኩና አንዱን ወታደር እንካ ጥበስ አልኩት፡፡ በኋላ ጠብሶ ሲሰጠኝ እንኩ አልኳቸው፤ ሰበር አድርገው እሸቱን በሉ፡፡ ቀሪውን ለአጃቢው ሰጠሁት፡፡ ያሉት ሁሉ አንዳንድ በቆሎ በሉ፤ ቆሎ በኑግ ከመንደር መጣ፡፡ ጠላ በዋንጫ ቀዳሁና እኔ መጀመሪያ ..ፉት.. አልሁና ሰጠኋቸው፡፡ ..ለምን ነው? ለምን ነው? ዝም ብለው ያምጡት አሉኝ.. መቸም ኸዱ ብዬ አላማቸውም፡፡ ..ለምን ቀመሱት ጓድ ቆምጬ ያምጡት በሉ.. አሉኝ ..አይ የጎጃም ባህል ነው፡፡ ማንም እንዲህ ሲሰጥ ቀምሶ ነው ሚሰጥ፤ እንቆቆ ወገርት መድኃኒት ሲሰጥ እንኳን ቢሆን ቀምሶ ነው፤ የሀገሩን ባህል ለማንፀባረቅ ነው.. አልኳቸው፡፡ በኋላ በርበሬ ብሎ ደርሷል፤ ይዩት ብዬ እሱን አሳየኋቸው፡፡ ጓድ ካሣ ገብሬ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴሩ ወፍራም ነበሩ፤ እኔ አላውቃቸውም ነበር፡፡ እንደዛሬው ቴሌቪዥን የለም፡፡ ሳያቸው ሆዳቸው ቦርጫቸው ሌላ ነው ..እስዎም አሁን ኮሚኒስት ተብለው ነውን?.. አልኳቸው፡፡ መሀረባቸውን ከኪሳቸው አውጥተው እምባ በእምባ እስቲሆኑ ድረስ ከት ከት ከት ብለው ሳቁ፡፡
አንተስ ቀጭን ነበርክ?
በጣም፡፡ ይኸውልሽ ወንበዴ እየመጣ ሁልጊዜ ተኩስ ነው፡፡ ሀሳብ ነበረብኝ፡፡ በዚያ የተነሳ ሃሳቡ ነው መሰለኝ በጣም ቀጭን ነበርኩ፡፡ በኋላ ጓድ መንግሥቱ ..እስቲ የወረዳውን ተፈጥሯዊ ገታና አጠቃላይ ሁኔታ አምጣ.. አሉኝ፡፡ ..አውራጃ አስተዳዳሪው ጓድ መስፍን አለ አይደል.. አልኳቸው፡፡ ..ከወረዳው መስማት ነው የምንፈልግ.. አሉ - እሳቸው፡፡ ያለውን ነገር ሁሉ ቁጭ አደረኩላቸው፡፡ በመሠረተ ትምህርት ቅስቀሳው አንዳንዶች አትማሩ እያሉ እየቀሰቀሱብን ነው እንዲያውም አስራ ሁለተኛ ክፍል የጨረሰውን ሥራ ሳያሲዙ እያሉ እንደሚያሳምፁና ወረዳውም በከፍተኛ ሁኔታ ኋላ ቀር መሆኑን፣ የመብራትና የውሃ ችግር መኖሩን፣ የአቸፈር ልጅ ለአብዮቱ በየተራራው እንደሚዋጋ ሃቁን ስነግራቸው ..እነዚህ ወረበላዎች ምን እያሉ ነው የሚቀሰቅሱ.. አሉኝ፡፡ አይ ይሄን የነገርኩዎን ነው አልኳቸው፡፡ የወረዳውን ለእኛ ተውት፤ ግን ነገሩ በውይይት ቢፈታ አልኳቸው ..በውይይት ሲሉ ምን ዓይነት ነው?.. አሉኝ፡፡ ..ሰውን የሚያጣላው የስልጣን ጥያቄ ነው ጓድ ሊቀመንበር.. አልኳቸው፡፡ ..ለመሆኑ እርቅና ድርድር ቢጀመር ትኩረት ሰጥተው ይከታተሉታል.. አሉኝ፡፡ ..አዎ.. አልኳቸው፡፡ ..እንዴት.. አሉኝ፡፡ ..በክቡር አቶ አማኑኤል አምደሚካኤል የሚመራ ቡድን ሦስት ጊዜ ሂዶ እርቁ ከሸፈ፡፡ በሬዲዮ የሰማሁትም የኢትዮጵያ መንግሥት እምቢ አለ የሚል ነው.. አልኳቸው፡፡ ..ለማንኛውም ጥሩ ግንዛቤና የሀገር ፍቅር አለህ፡፡ አፍና ተግባር ትክክል ሆኖ ያየሁት ባንተ ነው.. አሉኝ፡፡ ተዚያም ሽጉጥ አውጥተው ..ገንዘብ የለኝም.. አሉና ሊሰጡኝ ሲሉ ..ኧረ እኔ ተሽፍታ ያስፈታሁት አስራ ስምንት ሽጉጥ አለ፡፡ እንደውም ከቸገራችሁ ውሰዱ አልፈልግም.. አልኳቸው፡፡ ..ታዲያ ምንድነው የሚፈልጉት.. ሲሉኝ ..መብራት እና ውሃ ለሰፊው ህዝብ.. አልኳቸው፡፡ ጓድ ፍቅረስላሴ ወግደረስ አብረው ነበሩ፡፡ ..ጓድ ፍቅረሥላሴ፤ ቀን ሰጥቼሀለሁ. . . በተገኘው ገንዘብ ሁሉ መብራትና ውሃ እንዲገባ.. ብለው መመሪያ ሰጡልኝ፡፡ ስልሳ ቀን ሳይሞላ መብራትና ውሃ ገባ፡፡
ለአስተዳዳሪነት የተመደብክበት የመጀመሪያ ቦታ የት ነበር?
ቢቡኝ ነበረ፡፡ ቢቡኝ ማለት እስታሁንም አረንጓዴ ትርዒት ማለት ነው፡፡ በሄድኩበት ወረዳ የተፈጥሮ ሀብት እንክብከቤ በማድረግ የደን መራቆት እንዳይኖር ሳልታክት እሠራ ነበር፡፡ ከዚያ ደግሞ ሁለት እጅ እነሴ ወረዳ ነው የሰራሁ፡፡ እዛም እንደዚያው ደብረ ወርቅ ተዛውሬ አበት አለፍ የሚባል ተራራ አለ፤ የሬዲዮ መገናኛ ያለበት ነው፡፡ እዚያ ወጥቼ ሳየው ተራራውን ገበሬው እህል ያበቅልበታል፡፡ አጠናሁና ..እዚህ ላይ ደን እንትከል.. አልኩ. . . ..ከብት ይበላዋል.. አሉ፡፡ ..በፍፁም! እኔ እዚው መሳሪያዬን ይዤ እተኛለሁ እጠብቀዋለሁ ግዴለም.. አልኩ፡፡ በበሬ አረስነ አስተከልነ፡፡ ከዚያ በስብሰባ ላይ ..እንግዲህ ልብ አድርጉ የብሔራዊ አብዮታዊ የምርት ዘመቻን ሳንይዝ መንግሥት ያወጣው መመሪያ ግቡን አይመታም፡፡ ሊመታ የሚችለው እኛ ስንሠራ ነው.. እንደ አሁኑ 5 ዓመት መርሃ ግብር እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ ..በሥራ ቀን ቤት ተቃጥሎብህ፣ ጥይት ተተኩሶብህ ካልሆነ በስተቀር እዚህ ከተማ ሲያወደለድል የሚገኝ ሰው ቢኖር ደን ተከላ ነው የምልከው.. ብዬ አወጅኩ፡፡ ሰው ሲመጣ ይያዛል፤ ደን ተከላ ይላካል፡፡
የዚያንዜ ያስተከልሁት ችግኝ ዛሬ አድጎ መብራት ኃይል ለመላው ኢትዮጵያ ከዚያ እየቆረጠ ነው ሚወስድ፡፡ ወደ 6 ማሊዮን ብር ተሸጧል፡፡ ምን እንደሰሩበት እንጃ! በኋላ / ገረመው ደበሌ ለጉብኝት መጥተው አይተው በጣም ተደሰቱ፡፡ ወደ 50 ብር የሚሆን ለግብርናው ሽልማት ሰጡ፡፡
የቀለም ትምህርት እስከ ስንት ዘልቀሃል?
ደብረ ኤልያስ እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምሬአለሁ፤ ደብረ ወርቅ እስከ ዘጠኝ ተምሬ በተልዕኮ 12 ጨረስኩ፡፡ ከዛም ፖለቲካ /ቤት አስገቡኝ፡፡ ..ይሄን የመሰለ ልማት እየሠራ በትምህርት ቢታገዝ የበለጠ ውጤት ያመጣል.. ተባለ፡፡ ተዚያ ቀደም ይከለክሉኝ ነበር፡፡ የሚልኩኝ ችግር ባለበት ወረዳ ነው፡፡ ችግር ሲኖር እሱ ይሂድ ነው የሚባል፡፡ እኔ ሄጄ እግሬ እንደደረሰ ህዝቡን ሰብስቤ ..ከመንግሥት ጋር ያለህ ፀብ ምንድነው? በል ተናገር.. እለዋለሁ . . . ..ጠባችን ከመንግሥት ጋር አይደለም፤ ከሊቀመንበሩ ጋር ነው.. ይላል፡፡ ..እሱ ነው ጠላትህ ይሄው አወረድኩልህ፤ ሌላ ምረጥ.. እለዋለሁ፡፡ ይኸነዜ አዳሜ ወክ ይላል፡፡ አንድ የማልረሳው ምሳሌ ብነግርሽ አንደዜ የገበሬዎችና አምራቾች የህብረት ሥራ ላይ መሬት ከልለው ገበሬውን ባዶ አስቀርተውት አገኘሁ፡፡ ..ምንድን ነው.. ስላቸው ..ዛሬማ ቅልጥ ያለ ተኩስ አለ.. አሉኝ፡፡ ..ለምን?.. አልኩ፡፡ ..አምራቾች የሚያበሉትን ሳር እናብላ ብለው.. አሉኝ፡፡ አንድ የሚበጠብጥ ካድሬ ነበር ይሄን ሁሉ የሚያደርገው፡፡ የራሴን እርምጃ ወስጄ ወደ ሌላ ቦታ አዛወርሁት፡፡
ሌባን ለማጥፋት ሸፍተህ ነበር ይባላል. . .
! እህሳ! ልክ ነው፡፡ አስር ዓመት ሙሉ የሸፈተ አንድ ኃይለኛ ሽፍታ ነበር፡፡ አንደኛውን በቃ ሃይለኛ ነበር፡፡ ..ግዴለህም ግን.. ብዬ አባብዬ ብልክበት ..እነ ደጃዝማች ደምስ ያልነኩኝ ማን ነው እሱ!.. ብሎ ናቀኝ፡፡ የወረዳውን ህዝብ ሰበሰብኩና ሳበቃ ..የምንሄድበት ቦታ አለ፡፡ ወታደር የሆንክ ወደ ኋላ ሁን.. አልኩ፡፡ ሽማግሌዎች ነበሩ፡፡ የሀገሩ ሰው ለእሱ አብሮ ይተኩስብናል፡፡ ብቻ ተጠንቅቀን ደረስን፡፡ ከሌቱ 1000 ሰዓት ቤቱን ከበብነው ..እታኮሳለሁ.. አለ፡፡ ጠመንጃውን አቀባብሎ ሁለት የጣሊያን ቦምብ ይዞ፤ በሁለት ወታደር ታጅቦ መጣ፡፡ ሰላምታ እየሰጠ. . . እንግዲህ ከበነዋል፡፡ ማምለጫ የለም. . . ሁሉንም እየጨበጠ ሲመጣ እኔ ሰላም እለውና ..ያዝ!.. ስላችሁ በላዩ ላይ ተከመሩ ብዬ ወታደሮችን መክሬያቸው ነበር፡፡ እኔ ደርሶ ሰላም ሲለኝ ..ያዘው.. ብዬ ስል ያዙት ..ወይኔ ወይኔ!.. አለ፡፡ እጅ እግሩን ጠፍረን አሰርነው፡፡ ..እንግደለው.. አሉ፡፡ ..የለም ይሄ አይደረግም፡፡ እንኳን ይሄንና ሶማሊያ፣ ግብፆች፣ ቱርኮች፣ ጣሊያንና እንግሊዞች አገራችንን ሲወሩ እንደዚህ አድርገው እጃቸውን ሲሰጡ አይገደሉም፡፡ ይሄማ ወንድማችን ነው፤ አስረን ነው የምናስተምረው፤ እሺ ብሎ አንደዜ እጁን ሰጥቷል.. አልኳቸው፡፡ ተዚያማ ምኑን ልንገርሽ፡፡ ሌላ ሆነ . . .ተፎከረ ተሸለለ. . .

Friday, December 26, 2014

ዶ/ር ተወልደን በጨረፍታ

ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
---
በኢህአዴግ ዘመን ሲያገለግሉ ከነበሩት የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት መካከል በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታና ተወዳጅነት ያላቸው በፎቶው ላይ የምትመለከቷቸው ዶ/ር ተወልደ-ብርሃን ገብረእግዚአብሄር ናቸው፡፡ ዶ/ር ተወልደብርሃን በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ላደረጉት ምርምርና በጉዳዩ ዙሪያ ከፍተኛ ግንዛቤ እንዲፈጠር ላደረጉት ጥረት በፈረንጆቹ 2000 ዓመት ዓለም አቀፉን የአቋራጭ ኖቤል ሽልማት (በትክክለኛ ስሙ Right Livlihood Award የሚባለውን) ተሸልመዋል፤ ይህንን ፎቶ የተነሱትም ሽልማቱን በተቀበሉበት ወቅት ነው፡፡ ዶ/ር ተወልደ በፈረንጆቹ 2006 ዓመትም የተባበሩት መንግሥታት በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሰዎች የሚሸልመውን Champions of the Earth ሽልማት አግኝተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በ1997 የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቶአቸዋል፡፡


እኚህ ሰው የሀገራችንን የብዝሀ-ህይወት ኢኒስቲትዩት ከማቋቋማቸውም በላይ ሀገር ዝርያቸው ለመጥፋት የተቃረበ ሀገር በቀል ዛፎችን በሰፊው በማጥናት ለዘራቸው ጥበቃ የሚደረግበት የኢትዮጵያ ጄኔቲክ ባንክ እንዲመሰረት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የሀገራችንን የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ የቀየሱትም እርሳቸው ናቸው፡፡ በተጨማሪም ዶ/ር ተወልደ የአፍሪቃ ሀገራት የአሜሪካና የአውሮጳ ኩባኒያዎች ወደ ከባቢ አየር በሚለቋቸው በካይ ጋሶች ለሚደርስባቸው ጉዳት ተመጣጣኝ የካሳ ክፍያ እንዲጠይቁ ካስተባበሩት መሪዎች አንዱ ናቸው፡፡
----
ዶ/ር ተወልደ ብርሃን በትግራይ ክልል በአድዋ ከተማ አቅራቢያ ባለችው “አዲ-እስላም” የተሰኘች የገጠር መንደር ነው የተወለዱት፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1955 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተቀበሉ በኋላ የማስትሬትና ዶክትሬት ዲግሬአቸውን ከዌልስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ ዶ/ር ተወልደ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋኩልቲ ዲን ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከ1975 እስከ 1982 በነበረው ዘመን ደግሞ የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው ሰርተዋል፡፡ አስመራ በህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) ስትከበብ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ መጥተው በያኔው ካቢኔ ውስጥ የባህል ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሆነው አገለገሉ፡፡ የደርግ መንግሥት ከተወገደ በኋላም ለብዙ ዓመታት በሚታወቁበት የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከመንግሥት ስራ በጡረታ ተገልለው በግል ሙያ ላይ ተሰማርተዋል፡፡

  ይህንን ካልን ዘንዳ ዶ/ሩ የሚተቹበትን አንድ ነጥብ መጠቆም እንፈልጋለን፡፡ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ከአውሮጳ የመጡ የአበባ አምራችና ላኪ ኩባኒያዎች ሀገራችንን አጥለቅልቀዋታል፡፡ እነዚህ አምራቾች አበባውን ወደ ውጪ ልከው የውጪ ምንዛሬ ማምጣታቸው ጥሩ ነገር ቢሆንም አበቦችን በማምረት ሂደቱ የሚጠቀሙባቸው ኬሚካሎች ከፍተኛ የአካባቢ ብክለትን የሚያስከትሉ መሆናቸው በልዩ ልዩ ምሁራን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች በመሬት ውስጥ የሚኖሩ ጠቃሚ ነፍሳትን (micro organisms) ይገድላሉ ይባላል፡፡ የውሃ ዑደትንም እንደሚያዛቡ ይነገራል፡፡ በትነት መልክ እየቦነኑ አየሩን እንደሚበክሉም በሰፊው ሲጻፍ ቆይቷል፡፡ በዚህም የተነሳ በአበቦቹ ማሳ ዙሪያ የሚኖረው አራሽ ማህበረሰብ ጤናማ የምግብ ስርዓት እንደማይኖረው ተገልጿል (አንዳንዶቹ  ኩባኒያዎች በአካባቢ ላይ ሲያደርሱት በነበረው ጉዳት ምክንያት ከኬኒያና ከኡጋንዳ ተባረው መምጣታቸው በሰፊው ሲጻፍ የቆየ ጉዳይ ነው)፡፡

   ታዲያ “ዶ/ር ተወልደ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣና ዳይሬክተር ሆነው እነዚህ ሀገር አጥፊ ኩባኒያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ እንዴት ፈቀዱ? ” የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች “ዶ/ር ተወልደ በሌሎች መድረኮች ሲያሰሙት የነበረውን ድምጽ በነዚህ ኩባኒያዎችም ላይ ማሰማት ነበረባቸው” ባይ ናቸው፡፡ ይሁንና ዶ/ር ተወልደ በአንድ ወቅት በጉዳዩ ዙሪያ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነገሩን በቸልታ እንዳላለፉትና ኩባኒያዎቹን መቆጣጠሩ ከስልጣናቸው በላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ እርሳቸውን ከሾመው መንግሥት ጋር ልዩነት እንደነበራቸውም አስታውቀዋል፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የኬሚካሎቹን አጥፊነት ከመናገር እንዳልተቆጠቡም ተናግረዋል፡፡
------
ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረእግዚአብሄር የታዋቂው ደራሲ የስብሐት ገብረእግዚአብሄር ታናሽ ወንድም ሲሆኑ ባለቤታቸው ደግሞ እንግሊዛዊት ናት፡፡ በፌስቡክ የምናውቃት ገጣሚ ሮማን ተወልደም የርሳቸው ልጅ ናት፡፡ ጋሼ ስብሐት “ማስታወሻ” የሚል ርዕስ ባለው የዘነበ ወላ መፅሐፍ “ከተወልደ የሰማሁት ተረት ነው” ብሎ የገለጸውን እንጋብዛችሁና እናብቃ፡፡

  በአንዲት የገጠር መንደር ነው፡፡ አንድ ሰውዬ ከሩቅ ቦታ የመጣ የለቅሶ ድምጽ ይሰማል፡፡ ከዚያው ገደማ የመጣ ገበሬ ያይና “አንተዬ! ያቺ ሴትዮ ምን ሆና ነው የምታለቅሰው” በማለት ጠየቀው፡፡ ገበሬውም “እባክህ ተዋት! እርሷ ልጇ ሞታ ነው የምታለቅሰው፤ እኔ አለሁ አይደለም እንዴ ማረሻዬ ጠፍቶብኝ በፍለጋ የምንከራተተው” በማለት ያልጠበቀውን መልስ ሰጠው (ቂቂቂቂቂ… በጣም ነበር የሳቅሁት፤ ጋሽ ስብሐት እንዳለው ይህቺ ተረት ለዶ/ር ተወልደ ማስተር ፒስ ናት)፡፡
------
አፈንዲ ሙተቂ
መስከረም 6/2007
------
The writer, Afendi Muteki, is a researcher and author of ethnography and history with special focus on the peoples of East Ethiopia. You may follow him on his facebook page. Just click this link





Tuesday, December 23, 2014

እስላማዊ ኪነ-ህንጻ እና “ሲናን”ን በጨረፍታ




ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ                                  
-----
በ7ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የተጠነሰሰው እስላማዊ ኪነ-ህንጻ በአስራ አራት ክፍለ ዘመናት ውስጥ እያደገ ብዙ ፈርጆች ያሉት የጥበብ  ዘይቤ ሊሆን በቅቷል፡፡ በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ አድናቆት የተቸራቸው ቋሚ ግንባታዎችንም አበርክቷል፡፡ በካይሮ ከተማ የሚገኘው የአል-አዝሃር መስጊድ፣ የደማስቆው “የበኑ ኡመያ” መስጊድ (the Omayyad Mosque)፣ የኢስታንቡል “ሱሌይማኒያ” መስጊድ፣ በኢስፋሓን የሚገኘው የኢማም አደባባይና መድረሳ (Midyyan-e-Imami)፣ የህንዱ ታጅማሃል፣ ታላቂ የቁርጡባ መስጊድ (Great Mosque of Cordoba)፣ የግሪናዳ ከተማ መከላከያ ግንብ (fortress) እና ልዩ ልዩ ግንባታዎች፤ የፌዝ ከተማ የመከላከያ ግንብና ጥንታዊው የቃራዊያን መስጊድ (ሞሮኮ)፣ ከጭቃ የተሰሩት የቲምቡክቱ መስጊዶች ወዘተ… ከተደናቂ እስላማዊ ግንባታዎች ጥቂቶች ናቸው፡፡




እስላማዊ ኪነ-ጥበብ ብዙ ፈርጆች እንዲኖሩት ያደረገው በባህሪው “ሆደ ሰፊ” በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ሲባል ከሙስሊሙ ዓለም የተገኙት የኪነ-ህንጻ ጠቢባን በየሀገራቸው የነበሩትን ጥንታዊ የንድፍ ዘይቤዎች ከእስልምና መርሆች ጋር በማጣጣም አዳዲስ የኪነ-ህንጻ ዘይቤዎችን ይፈጥሩ ነበር ለማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በኢስታንቡል ከተማ የሚገኙት ታላላቅ መስጊዶች የተሰሩት የጥንቱን የቤዛንታይን ኪነ-ህንጻ ከዐረቢያና ከፋርስ ኪነ-ህንጻ ጋር በማዋሃድ በተፈጠረው የቱርክ ኪነ-ህንጻ ዘይቤ ነው፡፡ የቲምቡክቱ መስጊዶችም የማሊን ጥንታዊ የኪነ-ህንጻ ጥበብ መሰረት በማድረግ ነው የተሰሩት፡፡

ጥንት ከተገነቡት እስላማዊ ቅርሶች መካከል ከፊሎቹ ጠፍተዋል፡፡ ግማሽ ያህሉ ግን ዛሬም ቋሚ ሆነው ታሪክን ይመሰክራሉ፡፡ በእስላማዊ ግንባታዎቻቸው በዓለም ዙሪያ የተደነቁት ከተሞች የሚከተሉት ናቸው፡፡

1.      መካ
2.     መዲና
3.     እየሩሳሌም
4.     ባግዳድ (ኢራቅ)
5.     ሰመራ (ኢራቅ)
6.     ቡኻራ (ኡዝቤኪስታን)
7.     ሰመርቀንድ (ኡዝቤኪስታን)
8.     ደማስቆ (ሶሪያ)
9.     ኢስታንቡል (ቱርክ)
10.    ሂራት (አፍጋኒስታን)
11.     መዘር-ኢ-ሸሪፍ (አፍጋኒስታን)
12.    ቁርጡባ (ስፔን)
13.    ግሪናዳ (ስፔን)
14.    ካይሮ (ግብጽ)
15.    ሰንዓ (የመን)
16.    ዘቢድ (የመን)
17.    ፌዝ (ሞሮኮ)
18.    መራኪሽ (ሞሮኮ)
19.    ቱኒስ (ቱኒዚያ)
20.   ቲምቡክቱ (ማሊ)
21.    ጄኔ (ማሊ)
22.   ሀረር (ኢትዮጵያ)
23.   ዛንዚባር (ታንዛኒያ)
24.   ኒሻፑር (ኢራን)
25.   ኢስፋሓን (ኢራን)
26.   ሺራዝ (ኢራን)
27.   ቴህራን (ኢራን)
28.   ጠብሪዝ (ኢራን)
29.   ዴልሂ (ህንድ)
30.   አግራ (ህንድ)
---
እስላማዊ ኪነ-ህንጻ ሲጠቀስ በቀዳሚነት ከሚወሱት ጠቢባን መካከል አንዱ ከ1489 እስከ 1588 የኖረው ቱርካዊው “ሲናን” ነው፡፡ ቱርኮች ይህንን ሰው ሲጠሩት “ኮጃ ሚማር ሲናን”፣ ማለትም “ታላቁ አርክቴክት ሲናን” ይሉታል፡፡ ችሎታውን ሲገልጹም “እርሱን የመሰለ የኪነ-ህንጻ ጠቢብ አልተፈጠረም” ነው የሚሉት፡፡ በርግጥም በመቶ የሚቆጠሩ “እጹብ ድንቅ” የተባሉ ስራዎቹን ያየ ሰው በከፊልም ቢሆን የቱርኮችን አባባል መጋራቱ የማይቀር ነው፡፡

 “ሲናን” የተወለደው “አጊርናዝ” በተባለች የቱርክ አነስተኛ ከተማ ነው፡፡ በልጅነቱ በአባቱ ስር የአናጺነትና ድንጋይ የማሳመር ጥበብን ተማረ፡፡ አንድ ቀን ግን ህይወቱን የቀየረ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ በዚያ ቀን (በ1521) የኦቶማን ቱርክ ወታደራዊ ኦፊሰሮች ወደ ሲናን መንደር ሄደው ለውትድርና የሚቀጠሩ ወጣቶችን ይመዘግቡ ነበር፡፡ የሲናን ወታደራዊ አቋም የሚያመረቃ ሆኖ ስለተገኘ እርሱንም መዘገቡትና ወደ ቁስጥንጥንያ (የአሁኗ ኢስታንቡል) ወሰዱት፡፡ እዚያም ልዩ ልዩ ትምህርቶችን እንዲያጠና አደረጉት፡፡

የሲናን የጥበብ ተሰጥኦ መታየት የጀመረው በ1530 ድልድዮችንና ልዩ ልዩ ወታደራዊ ግንባታዎችን መስራት ሲጀምር ነው፡፡ በ1539 ግን ከውትድርናው ዓለም ተሰናብቶ የሲቪል ግንባታዎችን ጀመረ፡፡ በቀጣዮቹ 40 ዓመታትም ቱርክን በዓለም ዙሪያ ያስጠሯትን የልዩ ልዩ ግንባታዎችን ንድፍ እየወጠነ በራሱ አመራር በማስገንባት ለአግልግሎት አበቃ፡፡

ሲናን በህይወት ዘመኑ 79 መስጊዶችን፣ 34 ቤተ መንግሥቶችን፣ 33 የህዝብ የመታጠቢያ ገንዳዎችን (በተለምዶ “Turkish bath የሚባሉት)፣ 19 የመቃብር ስፍራዎችን፣ 55 ትምህርት ቤቶችን፣ 16 የድኾች መኖሪያ ማዕከላትን፣ 7 የከፍተኛ ደረጃ መድረሳዎችን፣ 12 ታላላቅ ምግብ ቤቶችን ሰርቷል፡፡ የፍሳሽ መውረጃዎች፣ ፋውንቴኖች፣ ሆስፒታሎችና ሌሎችንም ገንብቷል፡፡ የሁሉንም ግንባታዎች ንድፍ (ዲዛይን) የሰራው ራሱ ሲሆን በመሃንዲስነት አስጀምሮ የሚጨርሰውም እርሱ ነበረ፡፡

ከሲናን ግንባታዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የሱሌይማኒያ መስጊድ (በፎቶው ላይ ያለው)፣ የሻሕ ዛድ መስጊድ እና የሰሊም መስጊድ ናቸው (የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ በኢስታንቡል ነው የሚገኙት፤ የሰሊም መስጊድ ግን በኢድሪን ከተማ ነው የተሰራው)፡፡ ሲናን የኔ ምርጥ ስራ ነው የሚለው “የሻህ ዛድ መስጊድ”ን ነው፡፡ የኪነ-ህንጻ ጠበብት በጣም የሚያደንቁት ግን የሱለይማኒያ መስጊድን ነው፡፡
----
አፈንዲ ሙተቂ
ህዳር 6/2007
----
The writer, Afendi Muteki, is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia.  You may like his facebook page and stay in touch with his articles and analysis: Just click the following link to go to his page.