Monday, December 22, 2014

ሁለት ትራጄዲ ተረቶች





ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ


-----
በህይወት እስካለን ድረስ ተረት መተረታችንን አናቆምም፡፡ እነሆ ለዛሬም በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል እየተደጋገሙ የሚነገሩ ሁለት ትራጄዲ ተረቶችን አዘጋጅተንላችኋል፡፡

===የተንኮል ገበቴ===

እናት አንድ ልጅ ብቻ ነበራት፡፡ ይህንንም ልጅ በብዙ ልፋት ካሳደገችው በኋላ ለአቅመ አዳም ሲደርስ ዳረችው፡፡ ታዲያ የልጁ ሚስት እናትዬውን የምትወድ አልነበረችም፡፡ በብዙ አድራጎቷ ትበድላታለች፡፡ ይብስ ብሎ ደግሞ እናትየዋ ታወረች፡፡ ሚስትም በደሏን አጠናከረች፡፡ በተለይም ሴትዮዋን በጣም የምትበድለው ለእናትዮዋ በምታቀርበው ምግብ ነው፡፡

 ለምሳሌ ለእራት ገንፎ ስታቀርብላት ባሏም ሆነ ሌላ ሰው ዐይኑን እንዳይጥልበት በገንፎው ላይ ቅቤ ትጨምርበታለች፡፡ ነገር ግን ቅቤው ወደ መሬት እንዲፈስ ገንፎው የሚቀርብበትን ገበቴ በአንድ በኩል በስታዋለች፡፡ ልጁ እናቱ ገንፎ በቅቤ የበላች ስለሚመስለው ሚስቱን አይናገራትም፡፡ ሆኖም ገንፎው ቀስ እያለ ወደ መሬት ስለሚፈስ እናትዮዋ አታገኘውም (እናትዮዋ ዐይነስውር መሆኗን አስታውሱ)፡፡

ዘመን አለፈ፡፡ የልጁ እናትም አረፈች፡፡ ልጅየውም ካገባት ሚስቱ አንድ ልጅ ወልዶ ሞተ፡፡ የትናንትናዋ ሚስት የአዲሱ ልጅ እናት ሆነችና ከልጇ ጋር መኖር ጀመረች፡፡ ልጇ ለአቅመ አዳም ሲደርስ እርሷም በተራዋ ከአንዲት ወጣት ጋር በጋብቻ እንዲጣመር አደረገችው፡፡ ሶስቱ ሰዎች በአንድ ላይ መኖር ጀመሩ፡፡ እናት ስታረጅ እንደ ትልቋ እናት (የሞተችው የቧላ እናት) ታወረች፡፡ አንድ ቀን ምግብ ሲቀርብላት ገንፎው ቅቤ የሌለው ሆነባት፡፡ ወዲያውኑ የሆነ ነገር ትዝ አላትና ገበቴውን መዳበስ ጀመረች፡፡ በርግጥም እንደጠረጠረችው ገበቴው በአንድ በኩል የተበሳ ሆኖ አገኘችው፡፡ እናም ድሮ ስትፈጽመው የነበረውን በደል በማስታወስ ከልቧ አዘነች፡፡ እንዲህም አለች፡፡

“አይ ገበቴ! አይ ገበቴዋ! ከምኔው ዞረሽ ወደኔ መጣሽ?!! ግድ የለም፡፡ የእጄን ነው ያገኘሁት፡፡ ያኔ የባሌን እናት ባልበድል ኖሮ ዛሬ ምግቤ እኔ በቀደድኩት ገበቴ ባልተሰጠኝ ነበር”

የሴትዮዋ ንግግር ከልጁ ሚስት ጆሮ ጥልቅ አለ፡፡ እናም ሚስት በሰማችው ነገር ሽምቅቅ አለች፡፡ “ለካስ የኔም የወደፊት እጣ በዚህች ገበቴ መብላት ነው?” እያለች አሰላሰለች፡፡ ወዲያውኑ የባሏን እናት ይቅርታ ጠይቃ ያቺን የተንኮል ገበቴ እንክትክት አድርጋ ሰባበረቻት፡፡ እናትም ምግባቸው በጤነኛ ገበቴ ይቀርብላቸው ጀመር፡፡

===ሁለቱ አባቶችና ሁለቱ ልጆች===

ልጅና አባት አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ አባት ልጁ ትዳር እንዲይዝ ካደረገው በኋላ ሁሉንም ነገር አስረከበው፡፡ ለራሱም ጡረተኛ ሆኖ ከልጁ ቤት ጀርባ ከነበረች አንዲት አነስተኛ ጎጆ መኖር ጀመረ፡፡ ይሁንና አባትዬው በጸባዩ ነጭናጫ ነው፡፡ በተለይ ልጅ ለስራ ወደሌላ ቦታ በሚሄድበት ጊዜ የልጁን ሚስት በሆነ ባልሆነው ይነዘንዛታል፡፡ ሚስትም በንጭንጩ ተማረረችና ባሏ ሲመጣ “ወይ አባትህን ከዚህ ቤት አርቅልኝ፤ ወይ ደግሞ ፍታኝ” አለችው፡፡

ልጁ ወደ አባቱ ሄደና “አባቴ! እዚህ ቤት ስትኖር አፍህን ዝጋልኝ!! ካልሆነ ግን ወደ ገደል እወረውርሃለው” በማለት አስጠነቀቀው፡፡ አባትም “አረ አትወርውረኝ! ከእንግዲህ አፌን እይዛለሁ” በማለት ተማፀነው፡፡ በመሆኑም አባት ከነርሱ ጋር መኖሩን ቀጠለ፡፡ ነገር ግን አባት ቃሉን ሊያከብር አልቻለም፡፡ ልጁ ከቤት እስኪወጣ ጠብቆ ሚስትዬውን ይጨቀጭቃት ገባ፡፡ በዚህ የተናደደችው ሚስት ወደ ባሏ ሄዳ “ነገ አባትህን ከዚህ ቤት ካላስወጣህልኝ እሄድልሃለሁ” አለችው፡፡ ባልም “ግድ የለም! ነገ ገደል ውስጥ እጥለዋለሁ” አላት፡፡

በንጋቱ ልጅየው ሽማግሌ አባቱን ወደ ገደል ሊወረውረው ተነሳ፡፡ ከገደሉ ጫፍ ላይ ካደረሰው በኋላም “አባቴ! ብትፈልግ ገደል ግባ! ብትፈልግ የፈለግከውን ሁን፡፡ አባቴ ስለሆንክ ግን በራሴ እጅ አልወረውርህም፡፡ ትዳሬንም እወዳለሁና ከቤቴ እንድትመለስ አልፈቅድልህም” አለው፡፡ አባትየውንም እዚያው ትቶት ሄደ፡፡

ዘመን አለፈ፡፡ የድሮው ልጅ በተራው አባት ሆነ፡፡ ልጁም አገባ፡፡ አባትም ከልጁ ጋር መኖር ጀመረ፡፡ ታዲያ እርጅና ሲመጣ ይህኛውም  አባት ልክ እንደ ድሮው አባት ጨቅጫቃ ሆነ፡፡ የልጁን ሚስት በረባ ባልረባው ይጨቀጭቃት ጀመር፡፡ ልጁም ጭቅጭቁ ሲሰለቸው አባትዬውን ወደ ገደል ሊወረውረው ተሸክሞት ተነሳ፡፡ ረጅም ርቀት ከተጓዙ በኋላ የታዘለው አባት ልጁን እንዲህ አለው፡፡
  “እዚሁ ጋ ብትተወኝ ይሻለኛል፤ እኔም ያኔ አባቴን ከዚህ አላሳለፍኩትም”፡፡
*****
  አያድርስ ነው ወገን! “ሁሉም የዘራውን ነው የሚያጭደው” የሚለው ምሳሌ አሁን ላይ የማይሰራ ቢመስልም ጊዜው ሲደርስ እውነት መሆኑ አይቀርም፡፡ አላህ ከእንዲህ ዓይነት ክፋት ይጠብቀን፡፡

በነገራችን ላይ የመጀመሪያውን ተረት የነገሩን ጎረቤቴ የነበሩት “ሀቦ ኑሪያ” ናቸው፡፡ ሁለተኛውን ተረት የአባቴ የቅርብ የስጋ ዘመድ ከሆኑት ሼኽ ሙሐመድ ሑሴን ቲርሞ የሰማሁት ነው (በኋላ ላይ ስብሐት ገብረእግዚአብሄር ጽፎት ባነበውም ተረቱን በቅድሚያ የሰማሁት ከሼኽ ሑሴን አንደበት ነው)፡፡
------
አፈንዲ ሙተቂ
ግንቦት 26/2006
አዳማ!!
-----
Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history with special focus on the peoples of East Ethiopia. You may follow him on his blog and his facebook page by clicking the following links



Sunday, December 21, 2014

ጂሚ እና ዲስኮ ዳንሰር





(አፈንዲ ሙተቂ)
----
   በምስሉ ላይ ያለውን ሰውዬ ታውቁታላችሁ አይደል?… ህንዳዊ የሲኒማ አክተር ነው፡፡ በትክክለኛ ስሙ “ሚቱን ቻክራቦርቲ” ይባላል፡፡ የሀገራችን የሲኒማ አፍቃሪዎች ግን “Disco Dancer” በሚባለው ፊልም ውስጥ በሚጠራበት ስሙ ነው የሚጠሩት፡፡






አዎን! “ጂሚ” ነው፡፡ ያ “እኔ እኮ የዲስኮ ዳንሰኛ ነኝ” እያለ የሚሞላቀቀው ጆሊ!!

  I am a disco dancer
 ዘንደኪ ሜራሃና!
 ሜንዲሽቲ ከቲቫና
ኮቹሞ ሀነቾ
ሀ ሜሪ ሰቲ ነቾ
 
  አዎን!!  እርሱ እኮ ነው፡፡ (ዲስኮ ዳንሰርን በዚህ ሊንክ ላይ ተመልከቱት https://www.youtube.com/watch?v=7JdEZoffm-Q   )

 “ጂሚ ጂሚ ጂሚ… አጃ.. አጃ” እያለች የምታለቅስለትን ልጅስ አስታወሳችኋት?… ወይ ስታዝን!… ጂሚ በኤሌክትሪክ ጊታር ተቃጥላ የሞተችበት የእናቱ ሐዘን ቅስሙን ሰብሮት ሙዚቃውን እርግፍ አድርጎ ስለተወ ሽልማቱን ሊያጣ ደርሶ ነበር፡፡ በመሆኑም ነው ልጅቷ  “ጂሚ.. ጂሚ.. አጃ.. አጃ.” እያለች የተለማመጠችው፡፡
---
በልጅነታችን Disco Dancer የሚባለውን ፊልም ሳናየው በፊት በቪዲዮው ውስጥ ያሉት ዘፈኖች የተሰበሰቡበት ካሴት በጣም ተወዳጅ ሆኖ ነበር፡፡ በመሆኑም በሰርግ ቤትም ሆነ በወላጆች ቀን በዓል ቀዳሚ ምርጫ ሆኖ ይከፈት የነበረው እርሱ ነው፡፡ እርሱ በደንብ ከተደመጠ በኋላ ነው የማይክል ጃክሰን “ትሪለር” በሁለተኛ ደረጃ የሚከፈተው (በሶስተኛ ደረጃ የ“ቦኒ ኤም” ዳዲ ኩል ነው የሚመረጠው)፡፡

   ታዲያ ዕድላችን ተቃንቶ የህንድ ሲኒማ በ1978 ወደ ከተማችን ሲመጣ ጂሚን በውኑ ያየነውን ያህል ነው የፈነጠዝነው፡፡ ጂሚን የማየት የዘመናት ጥማታችንን የተወጣንበት የመጀመሪያው ፊልም  “Jimmy and His Elephant” የሚል ርዕስ የነበረው ይመስለኛል (በአማርኛ “እኔና ዝሆኔ” ይሉት ነበር)፡፡ በርግጥም ጂሚ በፊልሙ ውስጥ ከዝሆን ጋር ጉደኛ ዳንስ ይደንሳል፡፡ ዝሆኑ እንደ ጥሩምቦንና እንደ ሳክስፎን “ፓፓፓ” እያለ ድምጽ አውጥቶ ይሞዝቃል፡፡

    ከሁለት ዓመት በኋላ (በ1980) ጂሚ በጣም የታወቀበት `Disco Dancer”  መጣ፡፡ ማን ይቻለን!! አቤት ፌሽታ!! የፊልሙ ፖስተር (በያኔው አጠራር “ሌክራም”) በከተማችን ማዕከላዊ ስፍራ ላይ በነበረው የአቶ ዋጋዬ ይደነቃል ሱቅ ግድግዳ ላይ ሲለጠፍ እርሱን ለማየት የነበረው ግርግር እስከ አሁን ድረስ ይታወሰኛል፡፡ ማታ በ12፡00 ሰዓት ለሚታየው ፊልም ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ነው የተሰለፍነው፡፡

   ፊልሙ ተጀመረ፡፡ ጂሚ በልጅነቱ Goron Ki Na kalon Ki እያለ ከሚዘፍነው ዘፈኑ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ ልባችን እየተሰቀለ አየነው፡፡ በርሱ ዳንስና እናቱን በገደለበት ተንኮለኛ ሙጅሪም (በኛ አጠራር “ፋሩቅ” የሚባል)መሀል እየተወዛወዝን አጣጣምነው፡፡ ፊልሙን ባየንበት ማግስት ወሬው እርሱ ብቻ ሆነ፡፡ በየሆቴሉ፣ በየሻይ ቤቱና በየጥናት ቤቱ የጂሚ ፖስተሮች ተለጠፉ!!
----
በ1981 ደግሞ ጂሚ ሌላ ተአምር ይዞ መጣ፡፡ Kassam Paida Karne Wale Ki (በአጭር አጠራር Kassam Paida) የሚባል ፊልም ውስጥ ያየነው ጂሚ ድሮ ከምናውቀው ጂሚ በእጥፍ ጨመረ፡፡ ይህኛው ጂሚ በሙዚቃው ብቻ ሳይሆን በአለባበሱም ከሌላ ፕላኔት የመጣ መልአክ መስሎ ነው የታየን፡፡ በዳንሱና በአለባበሱ በጣም ስላፈዘዘን “ከጂሚና ከማይክል ጃክሰን ማን ነው የሚበልጠው?” የሚል ውርርድም ተጀምሮ ነበር (በነገራችን ላይ Kassam Paida የሚባለው ፊልም በአማርኛ “ጂሚ እንደ ማይክል” ተብሎ ነው የሚጠራው፤ በፊልሙ ውስጥ ጂሚ የሚዘፍነው አንዱ ዘፈን ዜማው ከማይክል ዘፈን ስለተኮረጀ ይመስለኛል እንደዚያ የተባለው፤ ደግሞም ማይክል Thriller በተሰኘው ዘፈን እንዳደረገው ሁሉ ጂሚም ሙታንን ከመቃብር አስነስቶ አስደንሷል)፡፡

   ከሁሉም በላይ Kassam Paida ውስጥ የተወነው ጂሚ በጣም ያስደነቀን  በድራም አመታቱ ነው፡፡ በፊልሙ ውስጥ አብራው የተወነችው Salma Agha የተባለች ፓኪስታናዊት አክትረስ ናት፡፡ ይህቺ አክትረስ Joom Joom Joom Ba Bah እያለች የምትጫወተው ዘፈን አለ፡፡ በዚያ ዘፈን ላይ በሙዚቃ መሳሪያ ካጀቧት ሙዚቀኞች መካከል አንዱ ጂሚ ነው፡፡ ጂሚ ድራሙን ሲያተረማምሰው አፍ ያስከፍታል፡፡ በተለይም አንድ ቦታ ላይ “ሳልማ” (በፊልሙ ውስጥ የምትጠራበት ስም “ኒና” ነው) ዘፈኑን እያስኬደችው ታቆመውና ወደ ጂሚ ዞራ የዐይን ምልክት ትሰጠዋለች፡፡ ይሄኔ ጂሚ ድራሙን ይቀውጠዋል፤ እያርበደበደ ያንቀጠቅጠዋል፡፡ ዲም..ዲም ዲም.. ዲም….ተራራም.. ዲም…..ዳም ዳም…ኪሽ…ኪሽ…..!!  እንዲያው እኮ በኤሌክትሪክ የሚሰራ ማሽን ነው የሚመስለው!!
 
  ጂሚ ድራሙን እንደዚያ አተረማምሶ ሲወቃው በአዳራሹ የነበረው የከተማችን የሲኒማ ተመልካች በሙሉ ከመቀመጫው ተነስቶ በጭብጨባ አድናቆቱን ገልጾለታል፡፡ በሌሎች ከተሞችም ተመሳሳይ ነገር እንደተከሰተ ተነግሮኛል፡፡

 (ያንን የድራም ምት ለማየት ካሻችሁ ይህንን የዩቲዩብ ቪዲዮ ተመልከቱ፡፡ http://www.youtube.com/watch?v=IFjKnIgd9js  )
-------
“ጉድና ጅራት በስተመጨረሻ ነው” አሉ!! ሰሞኑን የሆነ ነገር ፈልጌ You Tubeን ስጎረጉር የጂሚን የቆዩ ቪዲዮዎች አገኘሁ፡፡ ያኔ በልጅነታችን ሲያስጨበጭቡን የነበሩት የዲስኮ ዳንሰር እና የKassam Paida ዘፈኖች በመደዳ ተደርድረዋል፡፡ “ወይ ጂሚ! ከየት ተገኘህ ደግሞ” አልኩኝና አንድ ሁለቱን ከፍቼ አየኋቸው፡፡ ጂሚ አሁን ያለበትንም ሁኔታ የማወቅ ጉጉት ስላደረብኝ ኢንተርኔቱን የበለጠ ጎረጎርኩት!!

መቼም ይህ ኢንተርኔት የሚባለው “የሸይጣን ድር” አቃጣሪም አይደል? የአሁኑን ጂሚ ብቻ ሳይሆን የያኔውን ጂሚ ጭምር ቁልጭ አድርጎ አሳየኝ፡፡ “ዳንሱም የውሸት፣ ሙዚቃውም የውሸት፣ ዘፈኑም የውሸት ነው፤ ጂሚ ሌላ ሰው በዘፈነው ሙዚቃ ነው እንደዚያ ሲያጭበረብራችሁ የነበረው”- ይላል ኢንተርኔቱ!!

ይገርማል!! ከዚህ በፊት “የህንድ ፊልም የእውነት ነው” ስንል እንደነበር ጽፌአለሁ፡፡ በሂደትም በፊልም ውስጥ የውሸትና የእውነት ትዕይንቶች ተቀላቅለው እንደሚቀናበሩ ማወቃችንንም ነግሬአችኋለሁ፡፡ በመሆኑም የህንድ ፊልምም የውሸትና የእውነት ቅንብር ነው ብዬ ነበር የማምነው፡፡ አሁን ግን ሁሉም ነገር የውሸት ሆኖ ቁጭ አለ! አይ እዳ!!

    ይህ ጂሚ አናደደኝ !! የምሬን ነው በጣም ነው ያቃጠለኝ!! በውሸት ምት እነ ሳምሶን መላጣን ከጣሪያ ወደ መሬት እያንከባለለ ሲያጭበረብረን የነበረው ሳያንሰው በውሸት ዘፈንና ዳንስ ያታልለናል እንዴ?!! አሁን ያቺ ምትሃተኛ ድራም የውሸት ናት?… በውሸት ነው እንደዚያ ከሳልማ ጋር እየተቀባበሉ “በዘበዛ” ሲያደርጉን የከረሙት?… እኛስ አስመሳዩን ሰውዬ ነው ከማይክል ጃክሰን ስናስበልጠው የነበረው?...

ይገርማል!! የሆሊውድ አክተሮችም በሙዚቀኛና በሙዚቀኛነት ህይወት ላይ ያተኮረ ፊልም ይሰራሉ፡፡ ነገፍ ግን ምዕራባዊያኑ በፊልም ውስጥ የሚዘፍኑት ዘፈንና የሚደንሱት ዳንስ በአብዛኛው የእውነት ነው (ለምሳሌ ጆን ትራ ቮልታን መጥቀስ እንችላለን)፡፡ ጂሚ ሆዬ በውሸት ዘፈንና በውሸት የሙዚቃ መሳሪያ አጨዋወት ስልት ሲያስለፈልፈን ከረመ!! ይኼ ቦንባ!! ይሄ ጉረኛ!!
----
ደግነቱ እኛ ብቻ አልነበርንም፡፡ “ጂሚ” በመካከለኛው ምስራቅ፣ በምስራቅ አውሮጳ ሀገራትና በሶቪየት ህብረትም ጭምር ነው ዝነኛ የሆነው፡፡( በዚያ ዘመን ከሆሊውድ የመጣ ፊልም በሶቪየት ህብረት አይታይም፤ የህንድ ፊልሞች ግን ይፈቀዳሉ፤ ምክንያቱ ደግሞ የህንድ ፊልሞች እንደ አሜሪካ ፊልሞች ሶቪየት ህብረትንና የሶሻሊዝም ስርዓትን ስለማያጥላሉና ስለማይተነኩሱ ነው)፡፡  በመሆኑም የኛ መሸወድ የተለየ የሚሆንበት ምክንያት የለም፡፡ ያ እንደዚያ ስናጨበጭብለት የነበረው ጂሚ እኛ ምኑንም ባላወቅነበት ወቅት በካሜራ ጥበብ ቢያታልለንም ዛሬም እናደንቀዋለን!!

ከመልከ መልካሙ ጂሚ ጋር ወደፊት!!
----
ጳጉሜ 5/2006

Saturday, December 20, 2014

ሁለቱ የጎንደር ነገሥታት



ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----

በጎንደር የነገሡት የኢትዮጵያ ነገሥታት በታሪካዊ ሚናቸው በእኩል ሚዛን ላይ አይቀመጡም፡፡ አንዳንዶቹ በሰሩት ስራ ስማቸው ዘመንን ተሻግሮ ይዘከራል፡፡ አንዳንዶቹ ግን ስልጣን አልባ ሆነው በስም ብቻ “ንጉሥ” እየተባሉ ይጠሩ ነበር፡፡ የሁላቸውንም ታሪክ መዘርዘር የኛ ዓላማ ባለመሆኑ እርሱን ለታሪክ መጻሕፍት እንተወው፡፡ ለበረካ ያህል ግን ሁለት ነገሥታትን በትንሹ እናውሳቸው፡፡

===ተረት መሳዩ ንጉሥ===
ከስሙ ጀምሮ ሁለመናው ይገርማል፡፡ ታሪኩ እንደ ተረት ያስደምማል፡፡ አንዳንዴ የሚሰራቸው ነገሮች ደግሞ ከባግዳዱ ኸሊፋ ሀሩን አል-ረሺድ ጋር ያመሳስሉታል፡፡

ይህ ንጉሥ “ባካፋ” ይባላል፡፡ አጼ ባካፋ የነገሠው በአድማ ነው፡፡ አጼ ዳዊት ሳልሳዊ በሚባለው ወንድሙ ላይ አምጾ ነው ስልጣንን የተቆጣጠረው፡፡ ታዲያ ለአመጽ ሲነሳ መጀመሪያ ላይ በለስ አልቀናውም፡፡ በውጊያ ስለተሸነፈ ራሱን ሸሽጎ ከአንድ ደብር ለመኖር ተገደደ፡፡ በዚያ ደብር እያለም በአንድ መምህር ስር ቅኔና ዜማ መማር ጀመረ፡፡ እያደር ከዚሁ መምህር ጋር ሚስጢረኛ ሆነ፡፡ ታሪኩንም አንድ በአንድ አጫወተው፡፡

  በአንድ ውድቅት ሌሊት እርሱና መምህሩ ለመጸዳዳት ይወጣሉ፡፡ እዚያ እያሉም ባካፋ ለመምህሩ “መሪጌታ! የኔን ነገር እንዴት ነው የሚያዩት?.. ይህንን ወንድሜን አሸንፌ መንገሥ የምችል ይመስልዎታል?” የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡ መምህሩም “የምትነግሥ ይመስለኛል፤ ነገር ግን ጸሎት ማብዛት አለብህ፣ በጸሎት ሀይል የማይቻል የለም፤ ታዲያ ቀኙ ያንተ ሆኖ አልጋውን በወሰድክ ጊዜ እኔን እንዳትረሳኝ” አለው፡፡ ባካፋም በፍጹም ላይረሳው ቃል ገባለት፡፡

   ዓመታት አለፉ፡፡ ባካፋም ወንድሙን ድል አድርጎ ነገሠ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ድሪቶ የለበሰ ባላገር መጥቶ ከቤተ መንግሥቱ ፊት ቆመ፡፡ ዘበኞቹንም እንዲህ የሚል መልዕክት ለባካፋ እንዲያደርሱለት ለመናቸው፡፡

“ታስታውሳለህ ባካፋ የተባባልነውን
እኔ የአብረሃምን አባት ሆኜ አንተ ሚስቱን”

   ዘበኞቹ የባላገሩን ንግግር እንደ እብድ ወሬ ቆጠሩትና ለባካፋ ላለመንገር ለገሙ፡፡ አንዱ “ነቄ” ዘበኛ ግን ሰውዬው ቅኔ የተናገረ ስለመሰለው “ንጉሡ መልዕክቱን መስማት አለባቸው” በማለት ወደ አጼ ባካፋ ሄዶ ተናገረ፡፡ ባካፋም “እንዴ?! የቅኔ መምህሬ ናቸው፤ በቶሎ አስገቡልኝ” በማለት ዘበኞቹን አዘዛቸው፡፡ በዚህ መንገድ ባካፋ ከጥንቱ መሪ ጌታ ጋር ተገናኘ፡፡ ያኔ የገባውንም ቃል ተግባራዊ አደረገ፡፡

  በነገራችን የቅኔውን ሚስጢር አግኝታችሁታል አይደለም?… የአብረሃም አባት “ታራ” ነው፡፡ የአብረሃም ሚስት ደግሞ “ሳራ” ናት፡፡ ስለዚህ መምህሩ ለማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት “እኔ ሳራ አንተ ታራ” የሚል ነው፡፡ ይህም ሁለቱ ሰዎች ሲጸዳዱ ያደረጉትን ውይይት የሚያስታውስ ነው፡፡
*****
    በሌላ ጊዜ ደግሞ ባካፋ እንደ ባግዳዱ ኸሊፋ “ሃሩን አል-ረሺድ” ማንነቱን ቀይሮ ሀገሩን ይጎበኝ ነበር፡፡ ከአንድ ምንጭ አጠገብ ሲደርስ አንድ እረኛ ገጠመውና “የዚህ ሀገር ንጉሥ እንዴት ነው?” አለው፡፡ እረኛውም “ጥሩ ነው፤ ተስማምቶናል፤ ሀገሩ ጥጋብ ነው፤ ደሀን አይበድልም” የሚል መልስ ሰጠው፡፡ ይሁንና ባካፋ ሆን ብሎ እረኛውን መተንኮስ ጀመረ፡፡ “ምን ጥጋብ ነው ትላለህ? እንዲህ ዓይነት ግፈኛ ንጉሥ ነግሦም አያውቅ፤ ደሀውንም እንደርሱ የሚበድል የለም” አለው፡፡ እረኛው “ሰውዬ! እኔ አልዋሸሁም፤ ይህንን ነገረኛነትን ተወኝ፤ ምላስህን ያዝልኝ” አለው፡፡ ባካፋ ግን ትንኮሳውን ቀጠለ፡፡ በዚህ ጊዜ እረኛው ሽመሉን መዝዞ “እምቢ ካልከኝ በዚህ ዝም ትላለህ” በማለት ባካፋን እስኪበቃው ድረስ ደበደበው፡፡

     ከሳምንት በኋላ እረኛው ወደ ቤተመንግሥት ተጠራ፡፡ “ለምን” ብሎ ቢጠይቅ መልስ አልተሰጠውም፡፡ በመሆኑም ፍርሃት ወረረው፡፡ “ምን አጥፍቼ ይሆን?” እያለ ተጨነቀ፡፡ እንዲሁ በጭንቀት እንደተወጠረ ቤተመንግሥት ሲደርስ ከሳምንት በፊት የደበደበው ሰውዬ በዙፋን ላይ ቁጭ ብሎ አገኘው፡፡ እረኛው የባሰውኑ ተርበተበተ፡፡ ይሁንና ንጉሡ የፈገግታ ምልክት ሲሰጠው ልቡ መለስ አለችለት፡፡ ንጉሡም እንዲህ አለው፡፡
  “ከሳምንት በፊት ላሳየሁ ሐቀኝነት አንድ መቶ ከብቶችን ተሸልመሃል”

===የቤተመንግሥቱ ጭውውትና ታሪክ ቀያሪው ፋኖ====

አሁን ደግሞ በጎንደር ቤተ-መንግሥት የተደረገ አንድ ጭውውት እንጥቀስላችሁ፡፡

1ኛ ተናጋሪ (እቴጌ መነን)
አረ ለመሆኑ ምን ይሆን አሳቡ
ሸፍቶ የሄደው ከነቤተሰቡ?
*****
2ኛ  ተናጋሪ (ራስ ዓሊ)
ሰውዬው ኩሩ ነው የተነፋ ልቡ
ይዞ ማዋረድ ነው ይበርዳል ጥጋቡ::
*****
3ኛ ተናጋሪ (አንድ መነኩሴ)
ሰውዬው ብርቱ ነው ስሙ የተጠራ
ጎበዝ እኔ ነኝ ባይ ሀይልን የማይፈራ
በዘዴ በትዕግስት ማባበል ይሻላል
በሀይል ብንለው በጣም ያውከናል፡፡
*****
4ኛ (እቴጌ መነን)
እንዲህ ስትሉ ነው ስሙ የገነነው
የፈራነው መስሎት አገር የሚያብጠው
ዘዴ መላ አታብዙ ጦር ይታዘዝና
ቢቻል ከነነፍሱ ይምጣ ይያዝና
እምቢ ካለም ይሙት በገዛ ጥፋቱ
ላንድ ወንበዴ ሽፍታ አይስጋ መንግሥቱ፡፡
*****
  ይህ ጭውውት በ1840ዎቹ በጎንደር ቤተመንግሥት እልፍኝ ከተደረገ ምክክር የተቀነጨበ ነው፡፡ ይህም “ቴዎድሮስ” በተሰኘው የደጃች ግርማቸው ተክለሃዋሪያት መጽሐፍ የመጀመሪያ ገጽ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ በጭውውቱ ውስጥ “ለምን ሸፈተ” ተብሎ እንደ አጀንዳ የቀረበው የያኔው ደጃች ካሳ ሀይሉ ጉዳይ ነው፡፡ በዚያን ወቅት ካሳ ሀይሉ ከተራ ቤተሰብ ተወልዶ በአስገራሚ ሁኔታ የቤተ መንግሥቱ አባል ሆኖ ነበር፡፡ ታሪክ አለው፡፡
  
ደጃች ካሳ በወጣትነቱ ሽፍታ ሆኖ በቋራና በደምቢያ ይዘዋወር ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያዊያን ሱዳንን ከሚቆጣጠሩት የቱርክ/ግብጽ ገዥዎች ጋር የድንበር ላይ ውጊያ ያካሄዱ ነበር፡፡ ታዲያ በአንዱ ውጊያ ላይ የዘመኑ ዋና መስፍን የነበሩት የራስ ዓሊ ልጅ የሆነችው ወይዘሪት ተዋበች ተማረከች፡፡ ይህም ወሬ ለካሳ ጆሮ ደረሰ፡፡ ካሳ በወቅቱ ሽፍታ ቢሆንም የኢትዮጵያዊያን መሸነፍና በምርኮ መጋዝ በጣም አበሳጨው፡፡ በመሆኑም በቱርኮች ላይ ድንገተኛ አደጋ ጥሎ አተረማመሳቸው፡፡

  ካሳ ይህንን ሲያደርግ ተዋበች ምርኮኛ መሆኗ በቁጭት ውስጥ ጥሎአት በመርዝ ጩቤ ሰውነቷን ወግታ ራሷን ለማጥፋት ሙከራ በማድረግ ላይ ነበረች፡፡ ይሁንና ካሳ በቦታው ደርሶ መርዙ ወደ ሰውነቷ ጠልቆ ሳይገባ ከደሟ ውስጥ መጥጦ ተፋው፡፡ በዚህም የተዋበች ህይወት ተረፈች፡፡ ካሳም ተዋበችን በጀርባው አዝሎ ከውጊያው ስፍራ እየሮጠ ወጣ፡፡ ወታደሮቹም በቶሎ እንዲያፈገፍጉ ትዕዛዝ ሰጣቸው፡፡

   ካሳ ነፍሲያዋን ያተረፈላትን ተዋበችን ለአባቷ ለራስ ዓሊ አስረከባት፡፡ ራስ ዓሊም በጀግንነቱ ተደስተው እሷኑ ዳሩለት፡፡ ሽፍትነቱን ትቶ በቤተመንግሥት እንዲኖርም አደረጉት፡፡ ይሁንና የቤተመንግሥቱ ህይወት በነጻነት መኖርን ለለመደው ካሳ የግዞት ያህል ሆነበት፡፡ በዚያ ላይ መኳንንቱ “የኮሶ ሻጭ ልጅ” እያሉ የሚያሳዩት ንቀት በጣም አቃጠለው፡፡ ተዋበችም በባሏ ላይ በሚደርሰው ንቀትና ማሽሟጠጥ በገነች፡፡ እናም በአንድ ውድቅት ላይ “አንተ ካሳ! ጎራዴህን ታጠቅና ተነሳ፤ ምንጊዜም ከጎንህ ነኝ” አለችው፡፡ ካሳም ሸፈተ፡፡
*****
  እንግዲህ ከላይ የቀረበው ጭውውት ካሳ በሸፈተ በማግስቱ የተደረገ ነው፡፡ በዚያ ቀን በተደረገው ምክክር ደጃች ወንድይራድ የካሳን እጅ ይዞ እንዲመጣ ታዘዘ፡፡ ወንድይራድም ከቤተመንግሥቱ ቀርቦ እየጎረነነ ትዕዛዝ መቀበሉን አረጋገጠላቸው፡፡ ይሁንና ከልክ ያለፈው የወንድይራድ ጉራ ያልጣማቸው ራስ ዓሊ “አንተ ወንድይራድ! ካሳ እንደ ሌላው ሽፍታ አይምሰልህ፤ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው አደገኛ ተዋጊ ነው” በማለት ምክር ቢጤ ቢወርውሩለት ዳጃች ወንድይራድ እንዲህ የሚል የንቀት መልስ ሰጣቸው፡፡
አይስሙ ጌታዬ ሰው የሚለውን
አያስፈራም ካሳ ይንዛ ጉራውን፡፡
ገና መጣ ሲሉት አገር ጥሎ ይሸሻል
ወይንም ካንዱ ደብር ገብቶ ይደውላል፡፡
እንኳን አንድ ሽፍታ ቀማኛ ወንበዴ
ብዙ እመልሳለሁ በጦር በጎራዴ፡፡
እኔ ነኝ ወንድይራድ ታማኝ አሽከርሽ
ያን የኮሶ ሻጭ ልጅ የምቀጣልሽ፡፡

    የወንድይራድ ፉከራና ድንፋታ ከካሳ ጆሮ ገባ፡፡ ካሳም “እናቴን እንዲህ የሰደበውን ባለጌ ባላሳየው እኔ ካሳ አይደለሁም” በማለት መሃላውን አስቀመጠ፡፡ ሁለቱ ሀይሎች ተገናኙ፡፡ ውጊያው ገና ከመጀመሩ የወንድይራድ ፉከራ የአሸዋ ላይ ቤት ሆኖ ፈረሰ፡፡ እቴጌ መነን (የራስ ዓሊ እናት) የተመኩበት ዳጃች ወንድይራድም ተማረከ፡፡ ካሳም መሃላውን ተግባራዊ አደረገ፡፡ ወንድይራድን ቀንና ማታ ኮሶ እያጠጣው ገደለው፡፡

   ከዚያ በኋላ ካሳ በሀገሩ ላይ ገነነ፡፡ ማን ይቻለው እንግዲህ? ደጃች ውቤም ሆኑ ራስ ዓሊ፣ ደጃች ተድላ ጓሉም ሆኑ ደጃች ጎሹ ሁሉም ተራ በተራ ተሸነፉ፡፡ ካሳን ያሸንፋሉ ተብለው የተጠበቁት እቴጌ መነንም በናቁት አማቻቸው እጅ ምርኮኛ ሆነው ወደቁ፡፡ የጥንቱ የቋራ ሽፍታም “ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ተብሎ ነገሠ፡፡ ንጉሥ ለስሙ ብቻ ቤተመንግሥት የሚቀመጥበት ዘመነ መሳፍንትም አበቃ፡፡ ኢትዮጵያም አዲስ ታሪካዊ ጉዞዋን ተያያዘችው፡፡
-----
አፈንዲ ሙተቂ
ግንቦት 23/2007
አዳማ
------
(ማስታወሻ፡ ይህ ጽሑፍ ከቀጣዩ መጽሐፌ የተቀነጨበ ነው፡፡ ጽሑፉን በኢንተርኔት ማውጣት ቢቻልም በየትኛውም የህትመት ሚዲያ ማተም ክልክል ነው)

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history with special focus on the peoples of East Ethiopia. You may follow him on his blog and his facebook page by clicking the following links