Monday, December 15, 2014

የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናትን በጨረፍታ




ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
----
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ሲጠቀሱ በቅድሚያ የሚታወሱት በላስታ አውራጃ፣ በ“ሮሃ” (ላሊበላ) ከተማ አጠገብ ከአንድ-ወጥ ድንጋይ ተፈልፍለው የተሰሩት አስራ አንድ ቤተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡ የአስራ አንዱ ቤተ ክርስቲያናት ስም እንደሚከተለው ነው፡፡

1.      ቤተ መድኃኒ-ዓለም
2.     ቤተ ማርያም
3.     ቤተ ደናግል
4.     ቤተ መስቀል
5.     ቤተ ሚካኤል
6.     ቤተ ጎለጎታ
7.     ቤተ አማኑኤል
8.     ቤተ ገብርኤል
9.     ቤተ አባ ሊባኖስ
10.    ቤተ መርቆሬዎስ
11.     ቤተ ጊዮርጊስ

እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙት በሦሥት የተለያዩ ስፍራዎች ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ስድስቱ በአንድ ስፍራ፣ ተከታዮቹ አራቱም በሌላ ስፍራ ላይ ነው የተሰሩት፡፡ ቤተ ጊዮርጊስ ግን ከሁሉም ተነጥሎ ለብቻው ቆሟል፡፡ ከአብያተ ክርስቲያናቱ ውስጥ ትልቁ “ቤተ መድኃኒ-ዓለም” ሲሆን በኪነ-ህንጻውና በዲዛይኑ በዓለም ዙሪያ የተደነቀው ግን በመስቀል ቅርጽ የተሰራው “ቤተ ጊዮርጊስ” ነው፡፡

እነዚህን ቤተ ክርስቲያናት ያሳነጸው ከ1181-1221 የነገሠው የዛግዌው ንጉሥ ገብረ መስቀል ሲሆን ይህ ንጉሥ በታሪክ ምዕራፎች በደንብ የሚታወቀው “ላሊበላ” በሚል ስም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ለንጉሥ ላሊበላ የቅድስና ማዕረግ መስጠቷ ይታወቃል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) በበኩሉ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን በዓለም ቅርስነት መዝገቦአቸዋል፡፡
       *****
በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ደንብና ትውፊት መሰረት አንድ ቤተ-ክርስቲያን የሚታነጸው ሦሥት ክፍሎች እንዲኖሩት ተደርጎ ነው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል “መቅደስ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ታቦት (ጽላት) በዚህ ክፍል ውስጥ ነው የሚቀመጠው፡፡ በመቅደሱ ውስጥ እንዲገቡ የሚፈቅድላቸውም ካህናት ብቻ ናቸው፡፡ ሁለተኛው ክፍል “ቅድስት” ይባላል፡፡ የ“ስጋ ወደሙ” ስርዓት የሚፈጸመው በዚህኛው ክፍል ውስጥ ነው፡፡ ሶስተኛው ክፍል “ቅኔ ማህሌት” ነው፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ በአንድ ወገን ደብተሮች ይዘምራሉ፡፡ በሌላ ወገን ቀሳውስት ሰዓታት ይቆማሉ፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የሚመጡት ምእመናንም ስርዓተ ቅዳሴውንና ልዩ ልዩ ስብከቶችን የሚከታተሉት በዚህ ክፍል ውስጥ ነው፡፡
       *****
በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክህነት ስር የሚተዳደሩት አብያተ-ክርስቲያናት በሶስት ይከፈላሉ፡፡ እነዚህም ገዳም፣ ደብር እና “ገጠር” (አጥቢያ) በመባል ይታወቃሉ፡፡ “ገዳም” የሚባለው መነኮሳት ከዓለማዊ ኑሮ ተገልገለው የምንኩስና ህይወት የሚኖሩበት ቤተ-ክርስቲያን ነው፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ገዳም የቆረቆሩት በ5ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሶሪያዊው “አቡነ-አረጋዊ” ሲሆኑ በርሳቸው የተቆረቆረውም በትግራይ የሚገኘው የ“ደብረ ዳሞ” ገዳም ነው፡፡ ሌሎች ታዋቂ ገዳማት ደግሞ “ደብረ-ሊባኖስ” (በሰሜን ሸዋ፣ ሰላሌ አውራጃ ውስጥ የሚገኝ፣ በአስራ ሦሥተኛው ክፍለ ዘመን በኖሩት “አቡነ ተክለ-ሃይማኖት” የተመሰረተ)፣ “ደብረ ቢዘን” (በደቡብ ኤርትራ፣ ሰራዬ አውራጃ ውስጥ የሚገኝ፣ በአስራ አራተኛው ክፍለ ዘመን በኖሩት “አባ ኤዎስጣቴዎስ” የተመሰረተ)፣ “ደብረ ወገግ” ወይንም የ“አሰቦት ገዳም” (በሀረርጌ ክፍለ ሀገር፣ በአሰቦት ተራራ ላይ የሚገኝ፤ “አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ” በተባሉት ታዋቂ መነኩሴና የብዙ መጻሕፍት ደራሲ እንደተመሰረተ የሚታመን) እና የ“ዋልድባ ገዳም” (በትግራይና ጎንደር ወሰን ላይ የሚገኝ፤ “አባ ሳሙኤል” በተባሉ መነኩሴ በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የተመሰረተ) የመሳሰሉት ናቸው፡፡ የገዳም አስተዳዳሪ ከመነኮሳቱ መካከል በዕድሜው፣ በስነ-ምግባሩ፣ በዕውቀቱ እና በገድሉ ተመርጦ “አባት” በሚል ማዕረግ ይሾማል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት “ደብር” ይባላሉ፡፡ እነዚህኛዎቹ በርከት ያለ ህዝብ በሚኖርበት ስፍራ የተሰሩ እና ሁለገብ የቤተ-ክርስቲያን አገልግሎት የሚሰጡ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡ ቆየት ባለው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ትውፊት መሰረት ደብሮች የሚሰሩት በኮረብታ ላይ ነው፡፡ ደብሮቹ የሚጠሩትም በክርስትና ታሪክ ቅዱስ መሆናቸው በተመሰከረላቸው ቀደምት የሃይማኖት አባቶች፣ በሰማእታትና በመላዕክት ስም ነው፡፡

   የደብር አስተዳዳሪ “አለቃ” ይባላል፡፡ ሆኖም እንደ አስፈላጊነቱ “ንቡረ እድ”፣ “ሊቀ-ስልጣናት”፣ “መልአከ ጸሐይ”፣ “መልአከ ገነት” ወዘተ… በመሳሰሉ ማዕረጎችም ሊጠራ ይችላል፡፡ አንዳንድ ደብሮች በየዓመቱ የሚከናወኑ ታላላቅ የንግሥ በዓላትን በማስተናገድ ይታወቃሉ፡፡ በዚህ ረገድ ጎላ ብለው የሚጠቀሱት የአክሱም ጽዮን ማሪያም ቤተ-ክርስቲያን፣ የግሸን ማሪያም ቤተ-ክርስቲያን እና የቁልቢ ገብርኤል ቤተ-ክርስቲያን ናቸው፡፡

“ገጠር” የሚባሉት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚሰሩ ቤተ-ክርስቲያናት ናቸው፡፡ እነዚህ ቤተ-ክርስቲያናት መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጡት  ቅዳሜና እሁድ ብቻ ነው፡፡ የገጠር ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ “መሪ ጌታ”፣ “ጎበዝ” እና “አለቃ” በሚሉ ማዕረጎች ይጠራል፡፡
       *****
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስርዓት መሰረት ዘጠኝ ዐቢይ በዓላት፣ ዘጠኝ ንዑሳን በዓላትና ሰባት አጽዋማት አሉ፡፡ ዐቢይ በዓላት የሚባሉት “ልደት” (ገና)፣ “ጥምቀት”፣ “ደብረ ታቦር”፣ “ሆሳዕና”፣ “ስቅለት”፣ “ትንሳኤ”፣ “ዕርገት” እና “ጰራቅሊጦስ” ናቸው፡፡ ንዑሳን በዓላት የሚባሉት ደግሞ “መስቀል”፣ “ስብከት”፣ “ብርሃን”፣ “ኖላዊ”፣ “ግዝረት”፣ “ልደተ ስምዖን”፣ “ቃና ዘገሊላ”፣ “ደብረ ዘይት” እና “ሁለተኛው መስቀል” (መጋቢት አስር ቀን የሚውል) ናቸው፡፡

ሰባቱ አጽዋማት “ዐቢይ ጾም” (ሁዳዴ)፣ “ጾመ ሐዋሪያት”፣ “ጾመ ፍልሰታ”፣ “ጾመ -ነቢያት”፣ “ገሃድ”፣ “ጾመ ነነዌ” እና የ“ረቡዕ እና ዐርብ” ጾም ናቸው፡፡ የእምነቱ ተከታዮች ከቻሉ ሁሉንም አጽዋማት ይጾማሉ፡፡ ካልቻሉ ግን “ዐቢይ ጾም”ን፣ “ጾመ-ፍልሰታ”ን እና ረቡዕና ዐርብን የመጾም ግዴታ አለባቸው፡፡
       *****
አፈንዲ ሙተቂ
ህዳር 5/2007
በገለምሶ ከተማ ተጻፈ፡፡
---
ምንጮች
1.      ሉሌ መልአኩ፡ “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ”፡ ትንሳኤ ብርሃን አሳታሚ ድርጅት፤ 1986

2.     ተክለ-ጻዲቅ መኩሪያ፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ከአጼ ልብነ-ድንግል እስከ አጼ ቴዎድሮስ፣ 1936

3.     Encyclopaedia Ethiopica: University of Hamburg: 2004: Volume 1-5

4.      የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ድረ-ገጽ (www.ethiopianorthodox.org )

Saturday, December 13, 2014

“ኦሮማይ” እና በዓሉ ግርማ





ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
--------
    ኦሮማይ ከልቡ መጽሐፍ ነው፡፡ በአማርኛ ልብ-ወለድ መጻሕፍት (Novel) ታሪክ በጣም አነጋጋሪውና አከራካሪው መጽሐፍ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ የህዝብ ፍቅር ካልተነፈጋቸው ጥቂት መጻሕፍት አንዱም ነው፡፡ በህይወቴ ብዙ ጊዜ እየደጋገምኩ ካነበብኳቸው መጻሕፍት መካከልም በመጀመሪያው ረድፍ ይሰለፋል፡፡ ይሁንና ሰዎች ለዚህ መጽሐፍ ያላቸው አድናቆት እንደየ አመለካከታቸው ይለያያል፡፡

  መጽሐፉ የብዙዎቹን አትኩሮት የሳበው ታሪኩ እውነት ነው ስለተባለ እና በመጽሐፉ ሳቢያም የደራሲው ህይወት ለአደጋ በመጋለጡ ይመስለኛል፡፡ ከመጽሐፉ ዐቢይ ገጸ-ባህሪያት አንዱ የሆኑት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ “የደም እምባ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ተመሳሳይ እይታ አንጸባርቀዋል፤ እንደ ሻለቃ ዳዊት አባባል ኦሮማይ ባይታገድ ኖሮ ተወዳጅነቱ ይሄን ያህል አይገዝፍም ነበር፡፡ ሆኖም እኔ በዚህ አባባል አልስማማም፡፡ ደራሲው ባይሞት እና ታሪኩ እውነተኛ ባይሆን እንኳ “ኦሮማይ” ተደናቂ የመሆንን እድል አያጣም ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህም በርካታ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
  
   “ኦሮማይ” በቅድሚያ ቀልብን የሚስበው በአጻጻፍ ብሂሉ ነው፡፡ ደራሲው ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው አጫጭር ዐረፍተ ነገሮችን ይጠቀማል፡፡ ይህም አንባቢው የመጽሐፉን የትረካ ቅደም ተከተል ሳይስት ድርሰቱን ያለድካም እንዲያጣጥም ያግዘዋል፡፡ ደራሲው ጠጣር ሃሳቦችን በቀላሉ ይዘረዝራል፡፡ የዘመኑ መንግሥት አሰራርን ለተደራሲው በሚገባው ቋንቋ ቀለል አድርጎ ያስረዳዋል፡፡ በሌላ በኩል መጽሐፉ ኪናዊ ውበቱን እንዳይስት ደራሲው በእጅጉ ተጠቧል፡፡ ዘይቤአዊ አባባሎችን ከዘመኑ የአነጋገር ፋሽን ጋር እየቀላቀለ አንባቢውን ያዝናናዋል፡፡ በተለይም “ኦሮማይ” ፈጠራ እየነጠፈ በዘመቻ ግርግር እና በንድፈ-ሓሳብ ዝብዘባ የሚፈበረኩ ቃላት የድርሰቱን ጎራ እያጠለሹ በመጡበት ዘመን አንባቢው በማይሰለቸው የቋንቋ ጥበብ የተጻፈ በመሆኑ የደራሲውን ልዩ ተሰጥኦ በጉልህ ያስረዳል፡፡ ሆኖም ኦሮማይ የዚያ ዘመን ድርሰት ብቻ አይደለም፡፡ በዚህ ዘመንም እንኳ ተደግመው ሊጻፉ ከማይችሉ ድርሰቶች መካከል ሊመደብ ይችላል፡፡ 

      ይበልጥ አስደናቂው ነገር ደግሞ ወዲህ ነው፡፡ ደራሲው ያንን ውብ መጽሐፍ የጻፈው በጥቂት ወራት ውስጥ ነው፡፡ ይገርማል! ሰውዬው በወቅቱ ምክትል የማስታወቂያ ሚኒስትር ነበር (በደንበኛ ስሙ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ ይባል ነበረ)፡፡ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ሆኖም ይሰራ ነበር፡፡ በአዲስ ዘመን እና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች ዝግጅትም ይሳተፋል፤ ዝግጅታቸውን በበላይነት ይቆጣጠራል፡፡ ቱባ ባለስልጣን በመሆኑ የብዙ ኮሚቴዎች አባል መሆኑም ይታመናል፡፡ በርካታ የቢሮክራሲ ስራዎችም ነበሩት፡፡ እና ከነዚህ ሁሉ የስራ ጋጋታዎች ጋር የሚታገል ሰው ያንን የመሰለ ውብ መጽሐፍ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዴት ብሎ ነው የጻፈው? ይህንን በቀላሉ ማመን ይቻላል? በትርፍ ጊዜው መጻፉ ይቅርና የሙሉ ጊዜ ደራሲ ቢሆን እንኳ አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርለትም፡፡ ሰውዬው ግን በዓሉ ነውና ቻለው! የስራ መደራረብ “ሳይበግረው” ኦሮማይን ከዘጠኝ ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንዲያ ከሽኖ አቀረበው (የቀይ ኮከብ ዘመቻ ያበቃው በየካቲት ወር 1974 ነው፤ ኦሮማይ የታተመው በታህሳስ ወር 1975 ነው)፡፡ ችሎታ ማለት እንዲህ ነው!!

 ለኦሮማይ ዘመን አይሽሬነት ሁለተኛ አብነት ሆኖ የሚጠቀሰው ደግሞ የመጽሐፉ ጭብጥ ነው፡፡ በዚህ ላይ በርካታ ሰዎች የተለያየ አስተያየት ነው ያላቸው፡፡ አንዳንዶች በዓሉ ኦሮማይን የጻፈው የቀይ ኮከብ ዘመቻ ውጥረትና ውድቀትን ለመግለጽ ስለፈለገ ነው ይላሉ፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ “የመጽሐፉ ጭብጥ በርዕሱና በመጨረሻው ዐረፍተ ነገር ላይ ነው የሚገኘው” ብለው ነገር፡፡ አቶ መለስ ንግግራቸውን ሲያሰፉም “በዓሉ በመጽሐፉ  “እናንተ ደርጎች በኤርትራ ላይ ሙዝዝ ካላችሁ በአዲስ አበባ ያላችሁንም ስልጣን ታጣላችሁ” የሚል መልዕክት ነው ያስተላለፈው” ብለዋል፡፡ አቶ መለስ ይህንን ትንተና የሰጡት ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የአልጀርሱን ስምምነት ፈርማ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ በምትጠባበቅበት ወቅት “የስምምነቱ አካሄድ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነው” የሚል ሃሳብ ለሰነዘሩ ተቃዋሚዎች መልስ በሚሰጡበት ጊዜ ነው (ባልሳሳት ጊዜው የካቲት 1994 ይመስለኛል)፡፡ ሆኖም የኦሮማይ ጭብጥ በእንዲህ ዓይነቱ የፖለቲካ ዘውግ ብቻ የታጠረ አይደለም፡፡ ኦሮማይ በዘመኑ “አይነኬ” (taboo) የነበሩ በርካታ ጉዳዮችን ይነካካል፡፡ ለማስረዳት ይፈቀድልኝ፡፡
   
   የደርግ መንግሥት በወቅቱ የሀገሪቱን ህዝብ ከአቅሙ በላይ እያሯሯጠው ነበር፡፡ ህዝቡ በየዓመቱ ከሚመጣበት የዘመቻ መአት ሳያገግም በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማያውቀው ግዙፉ የቀይ ኮከብ ሁለገብ ዘመቻ በጫንቃው ላይ ወረደ (ዘመቻው የጠየቀው የሰው ሀይልና ማቴሪያል ሳይደመር ሁለት ቢሊዮን ብር ወጥቶበታል፤ ይህም በወቅቱ ከሀገሪቷ በጀት ግማሽ ያህሉን ይሸፍናል)፡፡ ሆኖም በዘመኑ ወታደራዊው መንግሥት ያሻውን ቢያቅድና ቢፈጽም አይደፈሬ ነውና ማንም ሰው አፍ አውጥቶ አልተቃወመውም፡፡ በዓሉ ግርማ ግን ለመጪውም ዘመን ትምህርት በሚሆን መልኩ የቀይ ኮከብ ዘመቻን በግልጽ ቋንቋ ሄሶታል፡፡ ለምሳሌ በመጽሐፉ ውስጥ የጋዜጠኛ ጸጋዬ ኃይለማሪያም እጮኛ እንዲህ ትላለች፡፡
  
  “ኤጭ እቴ! ለሁሉም ነገር ቸኩሎ መሞት! ነጋ ጠባ ዘመቻ! እድገት በህብረት ብሎ ዘመቻ! ለጦርነት ዘመቻ፡፡ የኢኮኖሚ ግንባታ ዘመቻ፡፡ ማይምነትን ለማጥፋት ዘመቻ፡፡ የቁጥጥር ዘመቻ፡፡ አሁን ደግሞ የኤርትራን ችግር ለመፍታት ዘመቻ፡፡ የዘመቻ ባህል ፈጥረናል፡፡ ያለዘመቻ ኖረን የምንሞትበት ቀን መቼ ይሆን?”  (ኦሮማይ ፤ ገጽ 9)
 ጋዜጠኛው የመንግሥት ባለስልጣን ሆኖ ለእጮኛው ንግግር የሰጠው ምላሽ ይበልጥ የሚደንቅ ነው፡፡ “ጊዜ ያጥረናል፤ እብዶች ነን፤ ችኩል ትውልድ፤ ያበደ ትውልድ…” ወዘተ.. ይላታል (ኦሮማይ፤ ገጽ 10)

  በአንድ በኩል ጸሓፊው የዘመኑ ባለስልጣናት ለቀይ ኮከብ ዘመቻ መሳካት አኩሪ ገድል ሲፈጽሙ ያሳየናል፡፡ ወዲያው ዞር ይልና ደግሞ የመንግሥቱ የቀን ቅዠትና ሀገር አጥፊ ፖሊሲ ያስከተለውን ቀውስ በራሳቸው በባለስልጣናቱ አንደበት ይገልጽልናል፡፡ ለምሳሌ ከመጽሐፉ ዐቢይ ገጸ-ባህሪያት አንዱ የሆነው ኢኮኖሚስቱ መጽሐፈ ዳንኤል ዘመቻው በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ጫና በማስረዳት የዘመኑን አመራር እንዲህ ይሸረድደዋል፡፡

   “ይህንን የቆየ ችግር በዘመቻ እንፈታለን ብለን ስንረባረብ ከአሁኑ ሌላ ችግር እየፈጠርን ነው፤ 450 ከባድ የጭነት መኪናዎች፤ 250 ሼልቶ፣ 200 ከነተሳቢያቸው ወደ ሰሜን ማዞር ምን ማለት ነው? ባጭሩ ኢኮኖሚው ተናግቷል ማለት ነው፤ ደሞ አሁን የመኸር ጊዜ መሆኑን አትርሳ” (ኦሮማይ፤ ገጽ 75)

     ጋዜጠኛው በዚህ አባባል ተናዶ “ስብሰባው ላይ ምን ዘጋህ? ቅድም እንዲህ ብለህ አትናገርም ነበር፡፡ መድረኩ ለማንም ክፍት ነበር፡፡ማን ከለከለህ?” ሲለው መጽሐፈ ዳንኤል “ትቀልዳለህ ልበል?” በማለት በአጭሩ መልሶለታል፡፡ መጽሐፈ ልክ ነው፡፡ አንድ ሰው በሚፈልገው መንገድ ብቻ መደስኮር በሚፈቀድበት ስብሰባ ሐቁን እናገራለሁ ቢል የሚደርስበትን ቅጣት በደንብ ያውቀዋል፡፡ ለዚህም ነው በስብሰባና በጉባኤ ፊት እያስመሰሉ መለፍለፍ እና ለክፉ አሳልፎ የማይሰጥ ወዳጅ ሲገኝ ሐቁን መናገር የዘመኑ ወግ ሆኖ የቆየው፡፡
 
   በተመሳሳይ መልኩ ሰለሞን በትረ-ጊዮርጊስ የተባለው ገጸ-ባህሪ የያኔውን የፕሮፓጋንዳ አካሄድ እስኪበቃው ድረስ ሲወርፍ ይታያል፡፡ “እናንተ ጋዜጠኞች ጭንቀታችሁ ሁሉ ስታቲስቲክስ ነው፤ ይህን ያህል ሄክታር መሬት ታረሰ፤ ይህንን ያህል ህዝብ ተደራጀ፤ ይህን ያህል ሰዎች ከመሀይምነት ተላቀቁ፤ ነው የምትሉት፡፡ እንዲያው ወሬአችሁ ሁሉ ስታቲክቲክስ ነው፤ ዘገባችሁ ሰው ሰው አይሸትም፤ ስለ አሐዝ ስትጨነቁ ሰው ትረሳላችሁ” ይላል (ኦሮማይ፤ ገጽ 67)፡፡ እነኝህን የመሳሰሉ የስርዓቱን ጉድፍ የሚያሳዩ በርካታ አንቀጾችን መልቀም ይቻላል፡፡

    የቀይ ኮከብ ዘመቻ የመጨረሻ ግብ ናቅፋ የሚገኘውን የሻዕቢያ ዋና የዕዝ ማዕከል መቆጣጠር ተደርጎ ይታሰብ ነበር፡፡ ሆኖም ናቅፋ በቀላሉ የምትደፈር ሆና አልተገኘችም፡፡ ሺዎች እንደ ቅጠል ረግፈዋል፡፡ ሺዎች ቁስለኛና ምርኮኛ ሆነዋል፡፡ ሁኔታውን በቅርበት የታዘበው ጋዜጠኛ ጸጋዬ ኃይለማሪያም ጦርነቱ ከኪሳራ ውጪ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ተገንዝቧል፡፡ ከናቅፋ ወደ አፍአበት ሲመለስ “አይዞን! ገና ሺህ ናቅፋዎች ይጠብቁናል” ብሎ ለተናገረው የዘመኑ ከፍተኛ ባለስልጣን “እኔ አንድ ናቅፋ ከወዲሁ በቅቶኛል፤ የጦርነትን አስከፊ ገጽታ ከአሁን በኋላ ላለማየት ቆርጫለሁ” በማለት ተቃውሞውን ገልጿል (በዓሉ ጦርነቱን ከተቃወመባቸው ዐረፍተ ነገሮች መካከል ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ይህኛው ነው)፡፡
       *****
 “ኦሮማይ” ፈርጀ ብዙ የዕውቀት ድርሳን ነው፡፡ ረጅምና ውስብስብ የሆኑ እውነተኛ ታሪኮችን እጥር ምጥን አድርጎ በቀላሉ ያስነብበናል፡፡ ለምሳሌ የኤርትራ ችግር መሰረታዊ ምንጭ ምን እንደሆነ መረዳት የሚፈልግ ሰው ከሰለሞን በትረጊዮርጊስ ታሪካዊ ትንተና ብዙ ቁምነገሮችን ይጨብጣል (ኦሮማይ፡ ገጽ 78-86)፡፡ እንግሊዝ በኤርትራ ምድር የቀበረችው ፈንጂ፤ የኤርትራ ክፍለ ሀገርን ከኢትዮጵያ ጋር ለመቀላቀል የተደረገው ጥረት፤ የጀብሃና ሻዕቢያ አነሳስና በመካከላቸው የተፈጠረው ፍጭት፣ አብዮታዊ ሰራዊት ኤርትራን ከአማጺያን ለማጽዳት ያደረገው ዘመቻ ወዘተ… በሰለሞን አንደበት በሰፊው ተተንትነዋል (እርግጥ ትንተናው ሙሉ በሙሉ ትክክል ነው ለማለት አይቻልም፤ ግማሽ ያህሉ የደርግ መንግሥት በሚፈልገው መልክ የተቀናበረ ነው)፡፡
  
   የጎሪላ እና መደበኛ የውጊያ ስልትን በተነጻጻሪ ማወቅ የሚፈልግ ሰው ከኦሮማዩ ኮሎኔል ታሪኩ ወልዳይ ትንታኔ ብዙ ነገሮችን ይማራል፡፡ ኮሎኔል በትሩ ተሰማ እና አጋዥ ቡድኑ (እነ ተክላይ ዘድንግል ያሉበት) የዘመኑ የኢንተሊጀንስ ጥበብና ስልት ምን ይመስል እንደነበር በቃልና በድርጊት ያሳዩናል፡፡ ጋዜጠኛው ጸጋዬ ኃይለማሪያም አስቸጋሪውን የናቅፋ ተራሮች የመሬት አቀማመጥ ለዓይናችን ወለል ብሎ እስኪታየን ድረስ በማይሰለቸው ብዕሩ እያጣፈጠ ይተርክልናል፡፡ ስዕላይ ባራኺ እና ጓዶቹ ደግሞ የሚያስገርሙ ጀብዶችን እየተገበሩ ሻዕቢያ በሰርጎ ገቦቹ አማካኝነት አስመራን እንዴት ያሸብራት እንደነበር ያሳዩናል፡፡ የአስመራ ነዋሪዎች የአኗኗር ወግና ማሕበራዊ ህይወት፣ የከተማዋ ታዋቂ ሰፈሮችና ሆቴሎች፤ የመንገዶቹ ውበትና አቀማመጥ ወዘተ… በመጽሐፉ ዘርዘር ብለው ተጽፈዋል፡፡ በኔ እይታ አንድ ሰው ልብ ወለድ ተብሎ የተጻፈውን “ኦሮማይ”ን ቢያነብ ከአስር መጻሕፍት የሚያገኘውን ዕውቀት ሊገበይ ይችላል፡፡
        *****
     እንደዚያም ሆኖ ግን “ኦሮማይ” ሙሉ በሙሉ እውነተኛ ታሪክ አይደለም፡፡ ደራሲው የመጽሐፉን ተነባቢነት ለማጉላት ምናባዊ ገጸ-ባህሪዎችንና ታሪኮችን ጨማምሯል፡፡ ለምሳሌ ደራሲው የሁለት ሰዎችን ታሪክ አዳብሎ “ስዕላይ በራኺ” የተባለ ገጸ-ባህሪ ፈጥሮልናል፡፡ እንደዚሁ ደግሞ በመጽሐፉ ውስጥ የሻዕቢያ ሰዎች በዚሁ ስዕላይ በራኺ በተባለ ገጸ-ባህሪ መሪነት የሚያካሄዱት “ኦሮማይ” የተሰኘ ስውር ኦፕሬሽን የደራሲው ፈጠራ ነው (“ቢሮክራሲ” የተባለው የስለላ ኔትወርክ ግን ትክክለኛ ነው)፡፡
 
   ከኦሮማይ ገጸ-ባህሪያት መካከል ኮሎኔል መንግሥቱ ሀይለማሪያምና ኢሳያስ አፈወርቂን የመሳሰሉት በእውነተኛ ስማቸው ተጠቅሰዋል፡፡ አንዳንዶቹ ግን ስም የለሽ ሆነው በድርጊታቸው ብቻ ተገልጸዋል (ለምሳሌ “የቀይ ኮከብ ሁለገብ ዘመቻ ዋና ጸሐፊ” ተብለው በስራ መደባቸው ብቻ የተጠቀሱት ባለስልጣን አቶ አማኑኤል አምደሚካኤል ናቸው)፡፡ ከፊሎቹ ገጸ-ባህሪያት በእውነታው ዓለም የሚታወቁበት ስም በመጽሐፉ ውስጥ ተቀይሯል፡፡ ከነርሱ መካከል የጥቂቶቹ ትክክለኛ ስም እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

1.      ኮሎኔል በትሩ ተሰማ= ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ (በደርግ መንግሥት የህዝብ ደህንነት ጥበቃ ሚኒስትር፤ ሆኖም ኮሎኔሉ “የኔ ምክትል ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፤ እኔ በቀይ ኮከብ ዘመቻ አስመራ አልሄድኩም” በማለት አስተባብሏል)።

2.     ኮሎኔል ታሪኩ ወልዳይ= ኮሎኔል ተሻገር ይማም (የአንበሳው ሶስተኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ የነበረ፤ በ1974 በናቅፋ በተካሄደው አደገኛ ጦርነት ማብቂያ ላይ ራሱን የገደለ)።

3.     መጽሐፈ ዳንኤል= አቶ ፋሲካ ሲደልል (የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የማዕከላዊ ፕላን ሚኒስትር የነበረ)

4.     የሺጥላ ማስረሻ= አቶ ሽመልስ ማዘንጊያ (የኢሠፓ የፖሊት ቢሮ አባልና የርዕዮተ ዓለም ጉዳዮች ሃላፊ የነበረ)

5.     ጸጋዬ ሀይለማሪያም= የበዓሉ ግርማ ግርማ እና የቴሌቪዥን ጋዜጠኛው የጌታቸው ኃይለማሪያም ቅልቅል ይመስላል፡፡  

6.     ተድላ ረጋሳ= ሻለቃ ፍሰሓ ገዳ (የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደርግ መንግሥት የፕሮቶኮል ሹም)

7.     ሰለሞን በትረ ጊዮርጊስ= ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ (በቀይ ኮከብ ዘመን የኤርትራ ክፍለ ሀገር ኢሠፓአኮ ተጠሪ እና የክፍለ ሀገሩ የበላይ አስተዳዳሪ፣ በኋላም የእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ኮሚሽነር፤ በ1978 ከደርግ መንግሥት ተነጥሎ ወደ ውጪ ሀገር የኮበለለ)

8.     ስዕላይ ባራኺ= የሁለት ሰዎችን ታሪክ በመቀላቀል የተፈጠረ ነው፡፡ አንደኛው ተስፋሚካኤል ጆርጆ ነው (አቶ ተስፋሚካኤል በሀይለስላሴ ዘመን የደቀምሐረ ወረዳ ገዥ የነበረ ሲሆን በ1963 ኢሳያስ አፈወርቂን ከሲ.አይ.ኤ ጋር በማገናኘት ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፣ ይህ ሰው በ1984 መጨረሻ ላይ በሻዕቢያ አዳኝ ኮማንዶዎች አዲስ አበባ ውስጥ ቫቲካን በሚባለው ሰፈር ተገድሏል)። ሁለተኛው ሰው ተክላይ አደን ይባላል (ተክላይ አደን የሻዕቢያ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የድርጅቱ የፖለቲካ ትምህርት ቤት ሃላፊ ነበር፤ በኋላ እጁን ሰጥቶ በሀገር ውስጥ ሲኖር ከቆየ በኋላ ደርግ ሲደመሰስ ወደ አውሮጳ ሄዷል)፡፡

9.     “ቢሮክራሲ”= አፈወርቂ ተወልደ መድሕን (ደሴ የተማረ የሻዕቢያ የውስጥ አርበኛና ሰላይ፣ “ቢሮክራሲ” በሚል ስም የሚታወቀውን የስለላ ኔትወርክ የሚመራው እርሱ ነው፡፡ በኋላ ግን ድሬ ዳዋ ላይ ተይዞ ተረሽኗል)፡፡
       *****
ስለኦሮማይ ይህንን ብያለሁ፡፡ ወደፊት አዲስ ነገር ከተገኘ መመለሴ አይቀርም፡፡ እስከዚያው ሌሎቻችሁ የምታውቁትን ጨምሩበት፡፡
   ሰላም!
አፈንዲ ሙተቂ
ሸገር-አዲስ አበባ
ጥቅምት 13/2006



የኮማንደር “አያልነሽ” ወጎች



-----
ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
------
ከሰው ቤት ትቼው የሄድኩትን የመጽሐፍ መደርደሪያዬን ስበረብር “መስታወት” የተሰኘ የድሮ መጽሔት ምዝዝ ብሎ ወጣ፡፡ እንደ ዋዛ ዐይኔን ከመፅሔቱ ሽፈን ላይ ጣል ሳደርግም የ“አያልነሽ” ፎቶ ታየኝ፡፡ ከፎቶው አጠገብም እንዲህ የሚል ጽሑፍ ሰፍሮ አነበብኩኝ፡፡

   “አቶ መለስ የራሷ ድርጅት የላትም፤ እራሷ ድርጅት ትሆን እንጂ” ያሉት ሳያውቁ ቀርተው ነው ብሎ ማመን ያዳግተኛል”፡፡

    አቶ መለስ ዜናዊ እንዲህ ማለታቸው የተነገረው ገና ጫካ ሳሉ ከሲ.አይ.ኤው ፖል ሂንዝ ጋር ባደረጉት ውይይት እንደሆነ ተዘግቧል (በርግጥ አቶ መለስ ያሉት “ራሷ ድርጅት ናት” ሳይሆን “እርሷ በራሷ የምትታገል ታጋይ ናት እንጂ ከየትኛውም ድርጅት ጋር የወገነች አይመስለኝም” ነው፡፡ ፖል ሄንዝ የውይይቱን ጭማቂ በአሜሪካ ይፋ ካደረገ በኋላ በተለያዩ መጽሔቶች ላይ ታትሞ ነበር)፡፡

   ወይ “አያልነሽ”! ስንቱን ያንቀጠቀጠች ጀግና መሰለቻችሁ?! ለደርግ ራስ ምታት ሆና በጎንደር እና በጎጃም እንደፈለገችው ትንሸራሸር ነበር፡፡ በርሷ ጀግንነት የተመሰጠው የጎጃም ህዝብ “አያልነሽ!….ክላሽ ልግዛልሽ!” እያለ በሰርግ ላይ የሚዘፈን የአጀብ ዜማ እስከ መውጣት ደርሷል፡፡ በደርግ እግር የተተካው ኢህአዴግም በርሷ ምክንያት ክፉኛ ታውኮ ነበር፡፡ እርሷ ስትያዝ ደግሞ ኢህአዴጎች በየስፍራው የደስታ መድፍ መተኮሳቸው በሰፊው ተወርቷል፡፡ 

   የ“አያልነሽ” ነገር በጊዜ ሰረገላ ወደ ኋላ እያበረረኝ የድሮ ትዝታዬን ቀሰቀሰው፡፡ ስለ“አያልነሽ” አመጸኛነት ሳስብ የያኔው ትውልድ የዓላማ ጽናት ከፊቴ እየመጣ በሃሳብ አስተከዘኝ፡፡ “የኔ ትውልድስ እንደዚያ ዓይነት ፋኖዎችን ያወጣ ይሆን?” እያልኩ ደጋግሜ ራሴን ጠየቅኩኝ፡፡
  
    ከሀገር ጭምር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ለመሆን የበቃችው ያቺ ሴት ዛሬ በትግሉ ውስጥ የለችም፡፡ ወደ ሰላማዊ ኑሮ ገብታ የልጆች እናት ሆናለች፡፡ ሆኖም የታሪካችን አካል ነችና በወቅቱ ስለርሷ ላልሰሙት ታሪኳን የማድረስ ግዴታ አለብን፡፡ እነሆ የአያልነሽን ወግ ከብዙ በጥቂቱ ልናወጋችሁ ነው፡፡   
*****
   የደርግ መንግሥት በግንቦት 20/1983 ሲገረሰስ ኢሕአዴግ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመጣመር የሽግግር መንግሥት እንዲመሰርት ተወስኖ ነበር፡፡ ኢሕአዴግም በለንደኑ ኮንፈረንስ የተወሰነውን ውሳኔ ተቀብሎ ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ለልዩ ልዩ ድርጅቶችም የጉባኤ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ በዚህም መሰረት በርካታ ድርጅቶች ወደ አዲስ አበባ መጉረፍ ጀመረ፡፡ ይሁንና በዚያ ዘመን ከኢህአዴግና ከኦነግ ቀጥሎ ከፍተኛ ስም የነበረው የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሀይሎች ቅንጅት (ኢ.ዲ.ሀ.ቅ) በጉባኤው እንዳይሳተፍ ተከለከለ (ኢዲሀቅ የኢህአፓ፣ የመኢሶን፣ የኢፒዲኤ እና የኢዲዩ ጥምረት ነበር)፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ጊዜያዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ኢዴሀቅ በጉባኤው ላይ እንዳይሳተፍ የተከለከለበትን ምክንያት በሰኔ ወር አጋማሽ ለጋዜጠኞች ሲያብራሩ

  “ኢዴሀቅ በጊዜያዊ መንግሥቱ ላይ ጦርነት አውጇል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ያወጀውን የጦርነት አዋጅ አላነሳም፤ ይህም የጦርነት አዋጅ ድርጅቱ በሰላምና በዲሞክራሲ ጉዳይ ላይ በሚመክር በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እንደሌለው ያሳያል” ብለው ነበር፡፡
  
  አቶ መለስ እንዲህ በማለት የገለጹት ኢዴሀቅ የተመሰረተው በመጋቢት 1983 ነበር፡፡ ይሁንና ይህ ድርጅት በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በጊዜያዊ መንግሥቱ ላይ ጦርነት አውጇል መባሉ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኖ ነበር (ጊዜያዊ መንግሥቱ በግንቦት ወር 1983 የደርግ ውድቀትን ተከትሎ ነበር የተመሰረተው)፡፡ ኢዴሀቅ የደርግ ብሔራዊ ሸንጎ በመጨረሻ ጉባኤው ያስተላለፈውን ውሳኔ በመደገፍ ሚያዚያ 16/1983 መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡ በመሆኑም አቶ መለስ “ኢዴሀቅ ጦርነት አውጇል” ያሉት ያንን መግለጫ ተንተርሰው እንደሆነ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች በወቅቱ የተናገሩት ጉዳይ ነው፡፡
           *****
   ከጥቂት ጊዜ በኋላ አቶ መለስ የተናገሩት የጦርነት ወሬ ውሸት እንዳልሆነ የሚያረጋግጥ ጭምጭምታ ተሰማ፡፡ ከወደ ጎንደርና ጎጃም አካባቢ የጦርነት ዜና መናፈስ ጀመረ፡፡ ኢህአዴግ እና አንድ ያልታወቀ ሀይል ብርቱ ውጊያ ላይ መሆናቸው ተነገረ፡፡ የዚያ ያልታወቀ ሀይል ኮማንደርም ሴት ናት መባሉ ደግሞ የብዙዎችን ቀልብ ሳበ፡፡ ያ ሀይል ማን ነው? ሴቲቷስ ማን ናት?

   ኢህአዴግ በወቅቱ ስለውጊያው ትንፍሽ አላለም፡፡ ከአሜሪካና ከአውሮፓ የሚተላለፉ የተቃዋሚ ሬድዮዎችና አንዳንድ በራሪ ወረቀቶች ነበሩ ዜናውን ሲያስተላልፉ የነበሩት፤ የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮም ወሬውን አልፎ አልፎ ይነካካ ነበር፡፡ ከነዚያ ምንጮች ለማወቅ እንደተቻለው በወቅቱ ከኢህአዴግ ጋር ሲዋጋ የነበረው የኢህአፓ ሰራዊት ነው፡፡ የሰራዊቱ ኮማንደርም “አያልነሽ” ነበረች፡፡ በርሷ የሚመራው ጦር ከ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በምዕራብ ጎንደር ቆላማ ክፍል (ወገራ፣ ጭልጋ፣ ቋራ ወዘተ…) እና በመተከል አውራጃ ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡ (“መተከል” በዘመኑ የጎጃም ክፍለ ሀገር ትልቁ አውራጃ ሲሆን በደርግ የመጨረሻ ዓመታት ራሱን ችሎ “የመተከል አስተዳደር አካባቢ” ተብሎ ተሰይሞ ነበር፡፡ “መተከል” በአሁኑ ዘመን የቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል አካል ሆኗል)፡፡
 
    አያልነሽ ደርግን ስትዋጋ ለብዙዎች ተራ ሽፍታ ትመስል ነበር፡፡ ይህም የደርግ ፕሮፓጋንዳ ክፍል የኢህአፓን መኖር ለህዝቡ ለማሳወቅ ባለመፈለጉ ምክንያት የመጣ ነው፡፡ ደርግ “ኢህአፓ ተደምስሷል” ብሎ በይፋ አውጆ ስለነበር አያልነሽ የኢህአፓ ኮማንደር መሆኗ ከተገለጸ “ኢህአፓ” አሁንም አለ እንዴ?” የሚል ጥያቄ ከህዝቡ ይነሳብኛል የሚል ፍርሃት ነበረው፡፡ ለዚህም ነበር የደርግ ሰዎች ኢህአፓን ትተው “ አያልነሽ… አያልነሽ..” ሲሉ የነበሩት፡፡ እንደ ደርግ ሰዎች አባባል “አያልነሽ ቀኛዝማች ስሜነህ የሚባሉ ጎንደሬ ልጅ ናት፡፡ የምትዋጋውም አባቷ በአብዮት ሀይሎች ስለተገደለባት የአባቷን ደም ለመበቀል” ነው፡፡

   ነገሩ ግን እውነት አልነበረም፡፡ አያልነሽ የኢህአፓ ሰራዊት የምዕራብ ክፍል ኮማንደር ነበረች፡፡ ከሰራዊቱ ጋር የተቀላቀለችውም በቂም በቀል ተነሳስታ ሳይሆን ድርጅቱ የከተማ የትጥቅ ትግሉን ትቶ ወደ ገጠር ባፈገፈገበት ጊዜ ነው፡፡ ታዲያ አያልነሽ የኢህአፓ አባል የሆነችው በልጅነቷ (በአስራ አንድ ዓመቷ) ነው፡፡ ይህች ሴት የተወለደችው በጎንደር ከተማ ሲሆን እውነተኛ ስሟ “የዓለም ገዥ ከበደ” ነው፡፡ “አያልነሽ” በኢህአፓ አባልነቷ የተሰጣት የትግል ስሟ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ የምትታወሰውም በዚህ ስም ነው፡፡
           *****
   አያልነሽ በዘመነ ደርግ ሰራዊቷን በቆራጥነት መምራት ቀጠለች፡፡ በተለይ ጎጃምና ጎንደር የራሷ ነጻ ግዛት እስኪመስል ድረስ በህዝቡ ዘንድ ስሟ ተደጋግሞ ይወሳ ነበር፡፡ በ1980 መጨረሻ ገደማ በእርዳታ ሰራተኛነት ሽፋን የመተከል አውራጃ ዋና ከተማ የነበረችውን ፓዌን የጎበኘው የሲ.አይ.ኤው ዝነኛ ሰላይ ፖል ሄንዝ የአካባቢው ሰው ለአያልነሽ የነበረውን አድናቆት ልብ ብሎ አስተዋለ፡፡ እናም ከዓመት በኋላ ወደ ሰሜን አሜሪካ ለጉብኝት የጋበዘውን ወጣቱን የህወሐትና የኢህአዴግ መሪ አቶ መለስ ዜናዊን ስለአያልነሽ ጠየቀው፡፡ ታዲያ አቶ መለስም ልክ እንደ ደርግ ሰዎች የኢህአፓን ስም ላለማንሳት ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረበት፡፡ በወቅቱ የኢህዴን (የአሁኑ ብአዴን) ስም እንጂ የኢህአፓ ስም ተጋንኖ እንዲወራ አይፈለግም ነበርና “አያልነሽ በራሷ የምትታገል ታጋይ ናት እንጂ በድርጅት የታቀፈች አይመስለኝም” በማለት ጉዳዩን በደንብ ሳያወሳው አለፈው፡፡
  
   ደርግ ተደመሰሰ፡፡ ኢህአዴግም በርሱ ቦታ መንግሥት ሆነ፡፡ የአያልነሽ ቀጣይ ትግልም ከአዲሱ መንግሥት ጋር ሆነ፡፡ ሁለቱ ሀይሎች ከአሲምባ ጀምሮ ይተዋወቃሉ፡፡ ሁለቱም ከፍተኛ ግጭቶችን አድርገዋል፡፡ ይሁንና ኢህአዴግ በጎንደርና በጎጃም የነበረው የኢህአፓ ሰራዊት በገበሬው ልብ የገባ ሰላልመሰለው አያልነሽና ጦሯን በቀላሉ የሚያባርራቸው ፋኖዎች አድርጎ ነበር የገመተው፡፡ በአማራው ምድር ሲገባ ግን ሁኔታው እርሱ ከጠበቀው ውጪ ሆኖ አገኘው፡፡ እርሱ ሞቷል ብሎ የገመተው ኢህአፓ የተሰኘው ታሪካዊ ጠላቱ ለቀጣይ ትግሉ አደጋ ሊሆን እንደሚችል ተረዳ፡፡ ስለዚህ እርሱም እንደ ደርግ “ኢህአፓ መጥፋት ያለበት  ድርጅት ነው” በማለት ወሰነ፡፡ በወቅቱ ተጠራርጎ ሊወድቅ የሚንገታተውን የደርግ መንግሥት በአንድ ዙር ካጠናቀቀው በኋላ በኢህአፓ ላይ ለመዝመት ቆረጠ፡፡
   
    ከላይ እንደገለጽኩትም በሰኔ 1983 መጀመሪያ ላይ ከኢህአፓ ጋር የሚደረገው ጦርነት በጎጃምና በጎንደር ተጀመረ፡፡ ሚዲያው “ደርግ ወድቆ ሰላም ሰፍኗል” በሚልበት ሰዓት ጎጃምና ጎንደር በጦርነት እሳት እየተለበለቡ መሆናቸው ታወቀ፡፡ ኢህአዴጎች ስም ያልሰጡት የዚያ ዘመቻ ዓላማ “ኢህአፓ”ን ማጥፋት ሊሆን እንደሚችልም በስፋት ተወራ፡፡
   
  ጦርነቱ ቀጠለ፡፡  በደርግ ላይ በተጎናጸፈው ድል ከፍተኛ ሞራል የሰነቀው የኢህአዴግ ጦር በኢህአፓ ላይ ተረባረበ፡፡ በቁጥሩ አነስተኛ በዓላማ ጽናቱ ግን ከፍተኛ የነበረውና በአያልነሽ የሚመራው የኢህአፓ ጦር በበኩሉ የኢህአዴግን ዘመቻ ለመመከት ጥረት ማድረጉን ቀጠለ፡፡ በጦርነቱ ሳቢያ ጎጃምና ጎንደር ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ ሆኑ፡፡ በተለይ ደርግ ከወደቀ በኋላ አዲሱን የኢህአዴግ መንግሥት በገፍ ለመቀላቀል ይጠባበቁ የነበሩ ቀደምት የኢህአዴግ ታጋዮች፣ ከስደት ተመላሽ ምሁራንና ሌሎች የኢህአዴግ ደጋፊዎች ከሱዳን ወደ አዲስ አበባ ለመንቀሳቀስ ክፉ ፈተና ገጠማቸው (በወቅቱ የአውሮፕላን ጉዞ ተቋርጦ ስለነበር ከሱዳን ወደ አዲስ አበባ የሚኬደው በመኪና ነው)፡፡
   
    የኢህአዴግ ሰዎች ጦርነቱን በቀላሉ የሚያጠናቅቁበትን መላ ዘየዱ፡፡ በዚህም መሰረት ዋናው ጦርነት የኢህአፓ ተዋጊዎች የቆራጥነት ምልክትና የጽናት አብነት በሆነችው አያልነሽ ላይ ማተኮር እንዳለበት ወሰኑ፡፡ በመሆኑም ኮማንደር አያልነሽን ማሳደድ ጀመሩ፡፡ እርሷን ለመግደል ወይንም ከነነፍሷ ለመያዝ እንዲቻል በርካታ ልምድ ያለውን “አሉላ ክፍለ ጦር” ወደ ስፍራው ላኩ፡፡  አያልነሽና ጓዶቿም ለዘመናት ሲታገሉበት የነበረውን የኢህአፓን እስትንፋስ ለማስቀጠል የሞት ሽረት ትግል ማካሄዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ከሰኔ 1983 እስከ መስከረም 1984 ድረስ በልዩ ልዩ ስፍራዎች ከባድ ውጊያዎች ተካሄዱ፡፡ ይሁንና በብዙ እጥፍ ከሚበልጠው የኢህአዴግ ሰራዊት ጋር የተጋጠመው የኢህአፓ ሰራዊት በለስ ሳይቀናው ቀረ፡፡ በነሐሴ 1983 በጎንደር ክፍለ ሀገር ቋራ አውራጃ በተካሄደው ጦርነት እውቋ ኮማንደር አያልነሽ ከእልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ በኢሕአዴግ ተዋጊዎች እጅ ወደቀች፡፡ በመስከረም ወር አጋማሽ የኢህአፓ መስራች አባልና ለረጅም ጊዜ የጦሩ አዛዥ የነበረው ጸጋዬ ገብረመድህን (ደብተራው) ከጥቂት ጓዶቹ ጋር ተያዘ፡፡ ከጥቅምት እስከ  ህዳር 1984 በነበረው ጊዜ ሁሉም ነገር አበቃለት፡፡ የአህአፓ ጦር ለረጅም ዘመናት ሲታገልበት ከነበረው የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሙሉ በሙሉ ተደመሰሰ፡፡  

     ኢህአዴግ ከጎጃምና ጎንደር የማረካቸውን የኢህአፓ ሰዎች ወደ መቀሌ እስር ቤት ወሰዳቸው፡፡ ከአራት ወራት እስር በኋላ አያልነሽና ጥቂት ሰዎች የተሐድሶ ስልጠና ተሰጥቷቸው ተለቀቁ፡፡ እነ ጸጋዬ ገብረመድህን ግን በዚያው ቀሩ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ያሉበት ሁኔታ በግልጽ አይታወቅም፡፡
           *****
አያልነሽ በእስር ላይ እያለች ለአንድ ቀን በቴሌቪዥን መስኮት ታይታ ነበር፡፡ ታዲያ በወቅቱ እርሷን ያዩዋት ሰዎች መልኳ ቀደም ሲል ስለርሷ ያስቡት ከነበረው ውጪ ሲሆንባቸው በጣም ነበር የተደነቁት፡፡ “አያልነሽ” ሲባል ብዙዎች የጠበቁት ግዙፍ፤ ግድንግድ፤ ጨካኝ ፊት ያላት፤ መልከ ጥፉና አስፈሪ፣ ጎፈሬዋን ያንጨባረረች፣ ዕድሜዋ ከአርባዎቹ የሚበልጥ፣ የወታደር ልብስ የለበሰች ሴት ነበር፡፡ ሆኖም በቴሌቪዥን የታየችው አያልነሽ በግልባጩ የቀይ ዳማ፣ መለሎ፣ ዐይኖቿ እንደ ኮከብ የሚያበሩ፣ ጸጉሯ በስርዓቱ የተበጠረ፣ ሸንቃጣ ሰውነት ያላት፤ በጣም ቆንጆ የ27 ዓመት ወጣት ነበረች፡፡
                                                                                                   
  አያልነሽ ከእስር ከተለቀቀች በኋላ ለጥቂት ጊዜ በአዲስ አበባ ቆየች፡፡ በ1985 መጀመሪያ ላይ ወደ አውሮፓ ተሻግራ ሀገረ ስዊዘርላንድ ገባች፡፡ እዚያም ትዳር ከመሰረተች በኋላ የልጆች እናት ሆናለች፡፡
 
    አያልነሽ በዚያ ዘመን ስመ ገናና ነበረች፡፡ አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለችው? በኔ በኩል ወሬው የለኝም፡፡ እርሷን የሚያውቋት ሰዎች ያላቸውን መረጃ ቢያካፍሉን መልካም ነው፡፡ በነገራችን ላይ ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረአብ ውጪ ሄዶ ማስታወሻዎቹን ሲጽፍ ስለርሷ አንድ ነገር ይናገራል ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ ነገር ግን በአንድ ቦታ እንኳ የርሷን ስም አላነሳም፡፡ ከርሱ ይልቅ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አያልነሽን በመጠኑ አስታውሰዋታል፡፡ በወቅቱ ኢህአዴግን ለመቀላቀል በሱዳን በኩል ወደ ሀገር ቤት የገቡት ዶ/ር ነጋሶ በጎንደር-አዲስ አበባ መስመር የነበረው የአያልነሽ ሰራዊት ወደ አዲስ አበባ ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ እንዳስተጓጎለባቸው መስክረዋል (ለማስረጃው “ዳንዲ” የተሰኘውን መጽሐፍ አንብቡት)፡፡

           *****
አያልነሽ በአጭሩ ይህቺ ነበረች፡፡ ስለርሷ የበለጠ የምታውቁ ሰዎች ያላችሁን መረጃ ልታካፍሉን ትችላላችሁ፡፡ በነገራችን ላይ የአያልነሽ የረጅም ጊዜ የትግል ጓደኛ የነበረው ገብረ እግዚአብሄር ወልደሚካኤል (ጋይም) አንዳንዶች እንደሚሉት ከአያልነሽ ጋር አልተማረከም፡፡ “ጋይም” በ1985 አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተደብቆ በነበረበት ወቅት አንድ ውስጠ-አዋቂ ለኢህአዴግ የጸጥታ ሀይሎች ጠቆመበት፡፡ ኢህአዴጎችም እርሱን የሚይዝ አዳኝ ጦር ላኩበት፡፡ ሆኖም “ጋይም” እጁን መስጠት ስላልፈለገ ተኩስ ተከፈተ፡፡ ከ30 ደቂቃ የተኩስ ልውውጥ በኋላ ሞተ፡፡ (ስለዚህ ጉዳይ በዝርዝር ለማወቅ ካሻችሁ ሚያዚያ 1985 የታተመውን እፎይታ መጽሔት አፈላልጉ፡፡ “የኢህአፓው ኮማንደር በአዲስ አበባ” የሚል ጽሑፍ አውጥቶ ነበር)፡፡
           *****
 አፈንዲ ሙተቂ
ሸገር-አዲስ አበባ
ጥቅምት 10/2006
-------------
The writer, Afendi Muteki, is a researcher of the Ethnography and History of the peoples of East Ethiopia. He is an author of “Harar Gey”, an Ethnography book about the historical city of Harar. You can read some of his articles on his facebook page.
Facebook https://www.facebook.com/afendimutekiharar