Monday, December 8, 2014

“አሕመድ ያ ሐቢቢ”



ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-------
አንዳንዶች “ነቢዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ትጠላላችሁ፤ በነቢዩ ላይ ሰለዋት አታወርዱም” ይሉናል፡፡ ሐቁ ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ በነቢዩ ላይ ሰላምና ሰለዋት በማውረድ ከኛ የሚቀድም ማን ነው? እንዲያውም የነቢዩን ታላቅ ደረጃ በዜማ እየዘከርን እና ገድላቸውን እየተረክን ነው በርሳቸው ላይ ሰላምና ሰለዋት የምናወርደው:: ይህንን እውነታ ያስረዳልን ዘንድ የሱፊ ሼኾቻችን ትተውልን ያለፉትን አንድ “ነሺዳ” (የነቢዩ ውዳሴ”) እንጋብዛችሁ፡፡
  *****  *****  *****
    ነሺዳው መጠሪያ “አሕመድ ያ ሐቢቢ” ይሰኛል፡፡ “አሕመድ ወዳጄ ሆይ” እንደማለት ነው፡፡ እኛ ስናሰፋው “ አሕመድ የልቤ ወዳጅ”፤ “አሕመድ የነፍሴ ስር” ልንለው እንችላለን፡ (“አሕመድ” የነቢዩ ሙሐመድ -ሰ.ዐ.ወ- ሁለተኛ ስም ነው፡፡ ነቢዩ በመጨረሻው ቀን/የውመል ቂያማ የሚጠሩት አሕመድ በተሰኘው ስማቸው ነው)፡፡
    
   ይህንን “ነሺዳ” ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት በ1995 ዓ.ል. ይመስለኛል፡፡ ነሺዳውን በህብረት ሲዘምሩ የነበሩት መሰረቱን በኦምዱርማን ከተማ ባደረገውና “ፊርቀቱ-ሳሕዋ” በሚባለው ዝነኛ የሱዳን የነሺዳ ቡድን የታቀፉት ስድስት ወጣቶች ነበሩ፡፡ የቡድኑ አባላት የሚያዜሙት በአብዛኛው በታዋቂው ሼኽ ዐብዱረሒም አል-ቡረኢ የተጻፉትንና “መዲሕ” የሚባሉትን የነቢዩን ግጥማዊ መወድሶች በመሆኑ “አሕመድ ያ ሐቢቢ”ም የሼኽ አል-ቡረኢ ድርሰት ይመስለኝ ነበር፡፡ በ2001 ወደ ሀረር ከመጣሁ ወዲህ ግን “አሕመድ ያ ሐቢቢ” በአንድ ዘመንና በአንድ ስፍራ ያልተገደበ ውዳሴ እንደሆነ ለማወቅ ችያለሁ፡፡ ለዚህ ያበቃኝ ደግሞ በቀድሞ ዘመናት የተጻፈ አንድ “የመዲህ” ኪታብ (መጽሐፍ) በሀረር ለማየት መታደሌ ነው፡፡

     በርግጥም “የፊርቀቱ ሳሕዋ” ወጣቶች የሚዘምሩት “አሕመድ ያ ሐቢቢ” እና ከሀረር ያገኘሁት “አሕመድ ያ ሐቢቢ” አንድ መሰረት ያላቸው መሆኑን ከግጥሞቹ አሰካክ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ሆኖም በመካከላቸው መጠነኛ ልዩነቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሱዳናዊያኑ ወጣቶች “አሕመድ ያ ሐቢቢ” በሚል ሐረግ የሚጀምረውን ባለሁለት መስመር ግጥም እንደ አዝማች አድርገው ይደጋግሙታል፡፡ የሀረሩ “አሕመድ ያ ሐቢቢ” ግን አዝማች የለውም፤ በዚህኛው ስልት “አሕመድ ያ ሐቢቢ” የሚለው ሐረግ አንድ ጊዜ ከታየ በኋላ አይደገምም፡፡ በሁለተኛ ደረጃም ሁለቱ የ“አሕመድ ያ ሐቢቢ” ስልቶች በግጥሞቻቸው ብዛት ይለያያሉ፡፡ የሀረሩ ስልት በኦምዱርማኑ ስልት ውስጥ የሌሉ ግጥሞቹ አሉት፡፡ በመሆኑም በግጥሞቹ ብዛት ከኦምዱርማኑ ስልት ይበልጣል፡፡
  
   የሀረሩ ስልት በትርፍነት ከያዛቸው ግጥሞች ውጪ ባሉት ግጥሞቹ ከኦምዱርማኑ ስልት ጋር የመመሳሰል ነገር ይታይበታል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በሁለቱ ስልቶች ያሉት ግጥሞች መቶ በመቶ የሚመሳሰሉበት ሁኔታ የለም፡፡ ግጥሞቹ አንዳንዴ በሁለት ስንኞቻቸው ብቻ ይመሳሰሉና በሶስተኛው ስንኝ ይለያያሉ፡፡ ሲያሻቸው ደግሞ በተመሳሳይ ሁኔታ እየተጓዙ በቃላት ደረጃ ይለያያሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ሁሉም ስንኞች እኩል ርዝመት ነው ያላቸው፡፡ ሁላቸውም “ሰላም ዓለይከ” በሚል ሐረግ የሚጀምሩ መሆናቸው ደግሞ የነሺዳው ኪናዊ ውበት ምንጭ ሆኗል፡፡
 
   በዚህ መጣጥፍ የምጋብዛችሁ የኦምዱርማኑን “አሕመድ ያ ሐቢቢ” ነው፡፡ ከኔ ጋር ነሺዳውን በ“ፊርቀቱ ሳሕዋ” ዜማ ለመዘመር ተዘጋጁ! ዳይ!!!
(ዐረብኛውን ወደ አማርኛ መተርጎም ይከብዳል፡፡ ስለዚህ እንዳለ ልተተው ተገድጃለሁ)፡፡
  *****  *****  *****
አሕመድ ያ ሐቢቢ ሰላም ዓለይከ
ያ ሚስኪ ወጢቢ ሰላም ዓለይከ
---
ሰላም ዓለይከ ዜይነል አንቢያኢ
ሰላም ዓሌይከ አትቀል አትቂያኢ
ሰላም ዓለይከ አስፉል አስፊያኢ
ሰላም አለይከ ሚን ረብቢ-ሰማኢ
ሰላም ዓለይከ ዳኢመን ቢላ ኢንቲሃኢ
ሰላም ዓለይከ
----
ሰላም ዐለል ሙቀደም ሊል ኢማማ
ሰላም ዐለል ሙዘለል ቢል ጘማማ
ሰላም ዐለል ሙዘወጅ ሊል ከራማ
ሰላም ዐለል ሙሰቢህ ሊል ሰላማ
ሰላም ዐለል ኹላሳ ሚን ቱሐማ
ሰላም ዐለል ሙሸፍፊዕ ቢልቂያማ
ሰላም ዓለይከ
-----
ሰላም ዐለይከ ጣሃ ያ ሐቢቢ
ሰላም ዐለይከ ያ ሚስኪ ወጢቢ
ሰላም ዐለይከ ያ -ማሂ ዙኑቢ
ሰላም ዐለይከ ያ ጃሊል ኩሩቢ
ሰላም ዓለይከ
 -----
ሰላም ዐለይከ ያ ኸይረል አናሚ
ሰላም ዐለይከ ያ በድረ ተማሚ
ሰላም ዐለይከ ያ ኑረል ዘላሚ
ሰላም ዐለይከ ያ ኩለል ጉራም
ሰላም ዐለይከ
----
ሰላም ዐለይከ ያ ዘል ሙእጂዛቲ
ሰላም ዐለይከ ያ ዘል በይናቲ
ሰላም ዐለይከ ያ ሐቢቡ ዛቲ
ሰላም ዐለይከ ያ ሐሱነ-ስ-ሲፋቲ
ሰላም ዐለይከ ያ ዙኽረል ዑሳቲ
ሰላም ዐለይከ
----
ሰላም ዐለይከ አሕመድ ያ ሙሐመድ
ሰላም ዐለይከ ያ ጣሃ ያ ሙመጀድ
ሰላም ዐለይከ ዘል መንተፈረጅ
ሰላም ዐለይከ
---
ሰላም ዐለይከ ያ ሩክነ-ሰላሂ
ሰላም ዐለይከ ያ ዘይነል ኢላሂ
ሰላም ዐለይከ ያ ዳኢል ፈላሒ
ሰላም ዐለይከ
---
አሕመድ ያ ሐቢቢ ሰላም ዓለይከ
ያ ሚስኪ ወጢቢ ሰላም ዓለይከ
  *****  *****  *****
አፈንዲ ሙተቂ
ሸገር- አዲስ አበባ
ጥቅምት 2/2006

ተስፋዬ ደበሳይ- አንጋፋው ኢህአፓ





ፀሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
------
  ይህ ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ነው፡፡ ኢህአፓዎች ከማንም በላይ የሚያከብሩትና የሚያደንቁት አርበኛና የለውጥ ብስራት ነጋሪ ፋኖ! የጽናትና የቆራጥነት ተምሳሌት ሆኖ በየዓመቱ የሚዘከር የዚያ ትውልድ ታላቅ ሰው!





       በእርግጥም ተስፋዬ ደበሳይ ቆራጥ ነበር፡፡ ላመነበት ዓላማ ሺዎችን አንቀሳቅሷል፡፡ ለጠላቶቹ ሳይንበረከክ ህይወቱን ሰውቷል፡፡ በርሱ ሞት ያዘኑት ኢህአፓዎች “ተስፋዬን ከምናጣ ሌሎች የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቶቻችን በሙሉ ቢጠፉ ይሻለን ነበር” በማለት መሪር ሐዘናቸውን አሰምተዋል፡፡ የደርግ መንግሥት እርሱ በሞተበት ዕለት ባወጣው መግለጫ አንድ ክፍለ ጦር ሰራዊት የተደመሰሰ ያህል ነበር የፎከረው፡፡

    ተስፋዬ ደበሳይ ማን ነው? በኢህአፓ ውስጥ የነበረው ሚና ምን ይመስል ነበር?… ህይወቱ የተፈጸመው እንዴት ነው? እስቲ በጥቂቱ እንየው፡፡
                                                                          *****
    ኢሮብ በትግራይ ክፍለ ሀገር፣ አጋሜ አውራጃ ውስጥ የምትገኝ ወረዳ ናት (በአሁኑ የአስተዳደር አወቃቀር በትግራይ ክልል፣ ምስራቃዊ ዞን ውስጥ ነው የምትገኘው)፡፡ በዚህች ወረዳ ከትግርኛ ተናጋሪው ብሄረ-ትግራይ በተጨማሪ ኢሮብ የሚባለው አነስተኛ ብሄረሰብ ይኖራል፡፡ ይህ ህዝብ በውስጡ ሶስት ዐይነት ማህበረሰቦች አሉት፡፡ አንደኛው ደመክኒቶ ይባላል፡፡ የዚህ ማህበረሰብ አባላት የካቶሊክ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ሁለተኛው ማህበረሰብ “ሀሳበላ” የሚባል ሲሆን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ይበዙበታል፡፡ ሶስተኛው ማህበረሰብ “ዳልገዳ” ይባላል፡፡ እነዚህኛዎቹ ደግሞ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ እነዚህ ማህበረሰቦች የሚናገሩት ቋንቋ በኤርትራ ምድር ከሚነገረው የሳሆ ቋንቋ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ሆኖም ኢሮብ እና ሳሆ በኢኮኖሚ ስምሪታቸው ይለያያሉ፡፡ የሳሆ ህዝብ ሙሉ በሙሉ አርብቶ አደር ነው፡፡ ኢሮቦች ግን በእርሻ ስራና በአነስተኛ ዕደ-ጥበባት ነው የሚተዳደሩት፡፡ የኢሮብ ወረዳ ተራራና ሸንተረር ይበዛዋል፡፡ በአካባቢው ካሉት ተራሮች መካከል “አሲምባ” እና “አይጋ” ትልልቆቹ ናቸው፡፡ 
    
   በዚህች የኢሮብ ወረዳ ውስጥ አሊቴና የምትባል አነስተኛ መንደር አለች፡፡ ይህች መንደር የአጋሜ አውራጃ ርዕሰ ከተማ ከሆነችው አዲግራት 35 ኪሎ ሜትር ያህል ትርቃለች፡፡ የመንደሪቷ ነዋሪዎች በአብዛኛው ካቶሊክ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ተሰፋዬ ደበሳይ በዚያች አነስተኛ መንደር ውስጥ ነው በ1933 የተወለደው፡፡ ወላጅ አባቱ አቶ ደበሳይ ካህሳይ ይባላሉ፡፡ እናቱ ደግሞ ወ/ሮ ምህረታ ዓዶ-ዑማር ነበሩ፡፡ ተስፋዬ የቤተሰቡ የበኩር እና ብቸኛ ወንድ ልጅ ነው፡፡ ከርሱ በኋላ የተወለዱት ስድስት ልጆች በሙሉ ሴቶች ናቸው (ለዚህ ጽሑፍ የመረጃ ምንጭ ከሆነው የመጋቢት ወር/2005 የኢህአፓ ዘገባ ለመረዳት እንደተቻለው ከስድስት እህቶቹ መካከል አምስቱ በህይወት ይገኛሉ፤ ወላጅ አባቱም በህይወት አሉ)፡፡
  
     አሊቴና በዚያ ዘመን ትምህርት ቤት አልነበራትም፡፡ ስለዚህ ህጻኑ ተስፋዬ የትምህርት ጉጉት ቢኖረውም እድሜው አስር ዓመት እስኪሆነው ድረስ ትምህርት ቤት ለመግባት አልታደለም፡፡ በ1943 ግን አዲግራት ከሚኖሩት አክስቱ ዘንድ ሄደና ትምህርት ቤት እንዲያስገቡት ለመናቸው፡፡ አክስቱም በከተማዋ ከሚገኝ ታዋቂ የካቶሊክ ሚሽን ትምህርት ቤት አስገቡት፡፡ ተስፋዬም እስከ ስምንተኛ ክፍል በዚሁ ት/ቤት ከተማረ በኋላ ዘጠኛ ክፍልን መቀሌ በሚገኘው አጼ ዮሐንስ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቀቀ፡፡ ይሁንና በወቅቱ የትምህርት ወጪውን በራሱ ሸፍኖ መማር እንደማይችል በመረዳቱ ፊት ወደ ነበረበት የካቶሊክ ት/ቤት ተመለሰ፡፡ እዚያም እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ከተማረ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ጣሊያን ሀገር ተላከ፡፡ በሀገረ ኢጣሊያ ሮም ከተማ ካለው Urbaniana University በፍልስፍና ትምህርት የዶክትሬት ዲግሪውን ተቀበለ፡፡

    ተስፋዬ በስራው ዓለም ሲሰማራ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰራበት መስሪያ ቤት የማስታወቂያና መርሐ ብሄር ሚኒስቴር ነበር፡፡ በዚህ መስሪያ ቤት የምርምር ክፍል ሃላፊ ሆኖ እየሰራ በማታው ክፍል የአባዲና ፖሊስ ኮሌጅ አስተማሪ ለመሆን በቅቷል፡፡ በ1964 ለተጨማሪ ስልጠና ወደ አውሮጳ (ስዊዘርላንድ) ተልኳል፡፡ በዚያ እያለም በመቀጣጠል ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ልቡን ስለወሰደው ትምህርቱን ትቶ ሙሉ በሙሉ ወደዚያው ገብቷል፡፡
   
     ታዲያ እርሱ ወደ ስዊዘርላንድ በሄደበት ወቅት በአውሮጳው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር እና በአሜሪካው የተማሪዎች ማህበር መካከል ከፍተኛ ውዝግብ ይካሄድ ነበር፡፡ ሁለቱ ማህበሮች የተወዛገቡት የድርጅት ምስረታና አደረጃጀት፣ የኤርትራ ጥያቄ፣ የብሄረሰቦች መብት፣ የትጥቅ ትግል አስፈላጊነት በመሳሰሉ አርዕስተ ነገሮች ዙሪያ ነበር፡፡ በጊዜው የድርጅት አስኳል ለመመስረት ጥረት ያደርግ የነበረው የአልጄሪያው የስደተኛ ተማሪዎች ቡድን ከአሜሪካው ማህበር ጋር ተቀራራቢ አቋም አሳየ፡፡ የአውሮጳው ማህበር መሪዎች በሀገር ቤት ከነበሩ ጥቂት ተማሪዎች ጋር አንድ ዓይነት አቋም ላይ ደረሱ፡፡ ተስፋዬ ደበሳይ ግን የአውሮጳው ማህበር መሪዎችን ውሳኔ በመቃወም ከአልጄሪያው ቡድን ጋር ወገነ፡፡ በዚህም መሰረት የአልጄሪያው ቡድን፣ የአሜሪካው ቡድንና አውሮጳ የነበሩት ጥቂት ተማሪዎች በድርጅት ምስረታ ሂደት ላይ መነጋገር ጀመሩ፡፡ ውይይቱ ለወራት ሲብላላ ከቆየ በኋላ በዓለም ዙሪያ ተበታትነው የነበሩ ሌሎች ኢትዮጵያዊ ተማሪዎችንም ማካለል ጀመረ፡፡ በስተመጨረሻም በሚያዚያ ወር 1964 “የኢትዮጵያ ህዝቦች አርነት ድርጅት” (ኢህአድ) ተወለደ፡፡ ተስፋዬ ደበሳይም ለድርጅቱ አመራር ከተመረጡ ሰባት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አንዱ ሆነ፡፡
                                                                          *****
       ኢህአድ የተወለደው በውጪ ሀገር ነው፡፡ ከ1964-1966 በነበሩት ዓመታት ዋነኛ ስራው ድርጅቱን ማስተዋወቅና አባላትን ማሰባሰብ ነበር፡፡ ከፍልስጥኤም ነጻ አውጪ ድርጅትና ከኤርትራ ግንባሮች የተሰጠውን ድጋፍ በመጠቀም የትጥቅ ትግል የመጀመር እንቅስቃሴ ሲያደርግም ቆይቷል፡፡ የድርጅቱ ቀዳሚ ዓላማ ከገጠር በሚጀመር የትጥቅ ትግል በረጅም ጊዜ የስርዓት ለውጥ ማምጣት ነበር፡፡ የኢህአድ መሪዎችም ድርጅቱ ቀዳሚ ሰራዊቱን ሊያሰማራበት ወዳሰበው የአሲምባ ተራራ በመሄድ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራር እንዲሰጡ ለማድረግ ታስቧል፡፡ ይሁንና በ1966 የፈነዳው የኢትዮጵያ አብዮት የትግሉን አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ ቀየረው፡፡ የአሮጌው ስርዓት መውደቅ አይቀሬ እንደሆነ ሁሉም በየፊናው አወቀ፡፡ “በርሱ ቦታ ተተክቶ ሀገሪቱን የሚመራው ማን ነው?” የሚለው ጥያቄ ግን አነጋጋሪ ሆነ፡፡ በዚህም በተራማጅ አብዮተኞች መካከል ከፍተኛ ውይይት ተቀሰቀሰ፡፡ በመደምደሚያውም የፓርቲ ቅርጽ የነበራቸው ቡድኖች በከተሞች አካባቢ የፖለቲካ ትግል ቢያደርጉ ጠቀሜታው ከፍ ያለ እንደሚሆን ከስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ በመሆኑም በውጪ ሀገር የነበረው የኢህአድ አመራር ወደ ሀገሪቷ ለመግባት ወሰነ፡፡
   
     ከኢህአድ ከፍተኛ መሪዎች መካከል በቅድሚያ ወደ አዲስ አበባ የገባው ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ነው፡፡ ጊዜውም ሰኔ 1966 ነበር፡፡ በወቅቱ የወታደሮች ቡድን የሆነው ደርግ ተመስርቶ የአጼውን መንግሥት ለመጣል እያኮበኮበ ነበር፡፡ በሀምሌ ወር አጋማሽ ላይ ደርግ የልጅ እንዳልካቸውን ካቢኔ በመሻር ልጅ ሚካኤል እምሩ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ መረጣቸው፡፡ ልጅ ሚካኤልም ካቢኔአቸውን ሲያቋቁሙ በስዊዘርላንድ የሚያውቁትን ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይን የመሬት ይዞታ ሚኒስትር እንዲሆን ጠየቁት፡፡ እርሱ ግን ከውጪ የመጣው ለዚያ አልነበረምና አንዳች ምክንያት ፈጥሮ አሉታዊ መልስ ሰጣቸው፡፡ በምትኩ በመስሪያ ቤቱ በኤክስፐርትነት ቢቀጠር ለመስራት ፈቃደኛ እንደሆነ ገለጸላቸው፡፡ በዚህም መሰረት ከነሐሴ 1966 ጀምሮ የመስሪያ ቤቱ ሰራተኛ ሆነ፡፡
 
   ተስፋዬ ወደ ሀገር ቤት ከተመለሰ በኋላ ድርጅቱን በማስፋፋትና አባላትን በማደራጀት ስራ ላይ ነበር የተጠመደው፡፡ የድርጅቱ ልሳን የሆነችውን “ዲሞክራሲያ” ጋዜጣን ከሚያወጡ አርታኢያን መካከልም አንዱ ነበር፡፡ በድርጅቱ የመጀመሪያ ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሆኖ የተመረጠው ብርሃነ መስቀል ረዳ ከሰራዊቱ ጋር ስለነበር በርሱ ቦታ በጊዜያዊነት አመራር የሚሰጠውም ተስፋዬ ደበሳይ ነበር፡፡  በወቅቱ በድርጅቱ አመራር ላይ ከነበሩትም መካከል በዕድሜም ሆነ በትምህርት ደረጃ የሚበልጠው እርሱ ነበር፡፡
   
   ተስፋዬ እስከ ታህሳስ 1967 በአዲስ አበባ ከተማ ከቆየ በኋላ ከመሬት ይዞታ ጋር ለተያያዘ የመስክ ስራ ወደ ትግራይ ተጓዘ፡፡ እግረ መንገዱንም አሲምባ የሚገኘውን የድርጅቱን ጀማሪ ሰራዊት ለመጎብኘት ወደዚያው ጎራ አለ፡፡ በጊዜው የነበረውን የሀገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ ለሰራዊቱ ካብራራ በኋላ ግን ያልተጠበቀ ችግር ተከሰተ፡፡ ስምንት ያህል የሰራዊቱ አባላት ከጀማሪ ሰራዊቱ በመነጠል ለደርግ እጃቸውን ሰጡ (እጃቸውን የሰጡት ሰዎች ተስፋዬ መኮንን፣ ኃይለ እየሱስ ወልደ ሰንበት፣ አበበ በየነ፣ ዘከሪያ መሐመድ፣ አያሌው ከበደ፣ ጋሻው መንግሥቱ፣ ሀይሌ ወልደ ጊዮርጊስና ዳዊት አሰፋ ነበሩ፤ እነዚህ ሰዎች በ1968 መጀመሪያ ላይ “ማሌሪድ”፣ ማለትም “የማርክሲስት ሌኒኒስት ሪቮሉሽናሪ ድርጅት”ን መስርተዋል)፡፡ ታዲያ የነዚህ ሰዎች ከኢህአፓ አፈንግጦ መውጣት የዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይን ማንነት አጋለጠው፡፡ በመሆኑም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ህቡዕ ለመግባት ተገደደ፡፡
                                                                          *****
   ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ህቡዕ ከገባ በኋላ የሙሉ ጊዜ አብዮታዊ ሆኗል፡፡ ኢህአድን በሙሉ አቅሙ አገልግሏል፡፡ በነሃሴ ወር 1967 ድርጅቱ ስሙን ቀይሮ “ኢህአፓ” (የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ) የተሰኘውን ዝነኛ መጠሪያውን የያዘበትን ጉባኤ በዋናነት ያዘጋጀውም እርሱ ነው፡፡ የድርጅቱ የፍልስፍና ሊቅ (ideologue) ሆኖ የሚያገለግለውም እርሱ ነበር፡፡ በኢህአፓ መስራች ጉባኤ “ዋና ጸሐፊ” የሚባል የስልጣን ተዋረድ ሲሻር በቀዳሚነት የማዕከላዊ ኮሚቴ ጸሐፊ ሆኖ ማገልገል የጀመረው እርሱ ነበር (ይህ የጸሐፊነት ቦታ በየጊዜው ይለዋወጥ ነበር፤ ጸሐፊው የሚመረጠውም በፓርቲው ጉባኤ ሳይሆን በፖሊት ቢሮው ነው)፡፡

   እስከ 1968 አጋማሽ ድረስ በነበረው ጊዜ የኢህአፓ አመራሮች ማንነት በግልጽ አይታወቅም፡፡ በዚያን ጊዜ ህቡዕ ለመግባት የተገደዱት ብርሃነ መስቀል ረዳ እና ተስፋዬ ደበሳይ ብቻ ናቸው፡፡ በመሆኑም አብዛኛው የፓርቲው ስራ የሚከወነው በተስፋዬ ነበር (ብርሃነ መስቀል ለፖሊት ቢሮው ስላልተመረጠ ከፍተኛ ሃላፊነት አልተሰጠውም፤ በተጨማሪም ከሌሎች መሪዎች ጋር መነታረክ ጀምሮ ነበር) ፡፡
   
    የህዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ከተመሰረተ በኋላ ግን አመራሩን ለአደጋ የሚያጋልጥ ሁኔታ ተከሰተ፡፡ በጽ/ቤቱ የተመረጡት ከፍተኛ ካድሬዎች የኢህአፓ መሪዎችን ስለሚያውቋቸው ለደርግ አሳልፈው ይሰጡአቸዋል የሚል ስጋት ሰፈነ፡፡ በመሆኑም በ1968 መጨረሻ ገደማ ሁሉም መሪዎች ህቡዕ ለመግባት ተገደዱ፡፡ ታዲያ የኢህአፓ የትግል ስትራቴጂም መለወጥ የጀመረው ከዚህ ወቅት ጀምሮ ነው፡፡ ከ1968 ክረምት ወራት በፊት በከተሞች አካባቢ የፖለቲካ ትግል ብቻ ያደርግ የነበረው ኢህአፓ የደርግ ፋሺስትነትን ለመከላከል በሚል የከተማ ትጥቅ ትግል የጀመረው ያኔ ነው፡፡

      አንዳንድ ወገኖች የትጥቅ ትግሉ በዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ግፊት የመጣ ነው ይላሉ፡፡ ከሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማሪያም ጀምሮ መገደል ያለባቸውን ከፍተኛ የደርግና የመኢሶን ባለስልጣናት ዝርዝር እያዘጋጀ የሞት ፍርድ ያስወስን የነበረው ተስፋዬ ደበሳይ ነው በማለት ይሞግታሉ፡፡ ከዚህ እልፍ ሲል ደግሞ የተስፋዬን ትግሬነት በመጥቀስ ብቻ ሻዕቢያ በአዲስ አበባ ከተማ ሽብር ለመቀስቀስ የመደበው የጥፋት ወኪል ነው የሚል መረጃ የሚያስነብቡ ጽሁፎችን ማየት የተለመደ ሆኗል (ለነገሩ ተስፋዬ የኢሮብ ተወላጅ ነው እንጂ ትግሬ አልነበረም)፡፡ ይሁንና እንዲህ ዓይነቱን የተናጥል ክስ በተስፋዬ ላይ የሚያጠናክር ማስረጃ የለም፡፡ ኢህአፓ የከተማ ትጥቅ ትግል እንዲጀምር የወሰኑት ብዙሃኑ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ናቸው እንጂ ተስፋዬ ደበሳይ ብቻ አልነበረም፤ ውሳኔውን የተቃወሙት ጌታቸው ማሩ እና ብርሃነ መስቀል ረዳ ብቻ ነበሩ (በጊዜው የኢህአፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የነበሩት ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ፣ ዮሐንስ ብርሃኔ፣ ዮሴፍ አዳነ፣ ክፍሉ ታደሰ፣ ክፍሉ ተፈራ፣ ዘርዑ ክህሸን፣ ኢያሱ አለማየሁ፣ ሳሙኤል አለማየሁ፣ አበራ ዋቅጅራ፣ ፍቅሬ ዘርጋው፣ ጸጋዬ ገብረመድህን፣ ብርሃነ መስቀል ረዳ፣ ጌታቸው ማሩ እና ጸሎተ ህዝቅያስ ነበሩ)፡፡

                                                                          *****
  መስከረም 13 ቀን 1969፡፡ በዚህች ዕለት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያምን ለመግደል ያልተሳካ ሙከራ ተደረገ፡፡ በዚህም የተነሳ ኮሎኔሉ ኢህአፓን ለማጥፋት ቆርጠው ተነሱ፡፡ በስውር የሚያካሄዱትን ርሸና ይፋ ማውጣት ጀመሩ፡፡ በታህሳስ ወር የኮሎኔሉን እርምጃ የሚቃወሙ መኮንኖች በደርግ ውስጥ መዋቅራዊ ለውጥ አካሄዱ፡፡ ይሁን እንጂ ከአንድ ወር በኋላ (ጥር 25/1969) ኮሎኔል መንግስቱ ማንም ባላሰበው መንገድ ጠላቶቻቸውን በማጥፋት “ለምሳሌ ያሰቡንን ቁርስ አደረግናቸው” በማለት አወጁ፡፡ “አብዮቱ ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት ተሸጋግሯል” ተባለ፡፡ “ቀይ ሽብር” በይፋ ታወጀ፡፡ “ነጻ እርምጃ” ተፈቀደ፡፡
   
    በወቅቱ የኢህአፓው ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ አዲስ አበባ ውስጥ እንደነበረ ደርጎች ያውቁ ነበር፡፡ ነገር ግን አድራሻውን በትክክል ማወቅ አልቻሉም፡፡ ኢህአፓም ከጥር ወር መጨረሻ ጀምሮ እየተባባሰ በመሄድ ላይ የነበረውን የደርግ እርምጃ ለመቀልበስ እንደማይችል አውቆታል፡፡ ይሁንና የከተማውን የትጥቅ አመጽ አላቋረጠም፡፡ ደግሞም ዋና መሪውን ከደርግ አፍንጫ ስር አውጥቶ ከደህና ቦታ ለማድረስ አልሞከረም፡፡
  
   ታዲያ ኢህአፓዎች መሪአቸው ከከተማው ወጥቶ ለደህንነቱ አስተማማኝ በሆነ ቦታ ቢደበቅ ይፈልጉ ነበር፡፡ በተለይ በመጋቢት ወር አጋማሽ (1969) ከሚካሄደው የቤት ለቤት አሰሳ ነፍሱን እንዲታደግ ይመኙ ነበር፡፡ ይሁንና መሪው ከከተማው ለመውጣት ምንም ዓይነት ፍላጎት አልነበረውም፡፡ “በዚህ ክፉ ቀን ተከታዮቼን ጥዬ ከከተማ አልሰደድም” በማለት ቆርጧል፡፡ አሰሳው ከመጀመሩ አስቀድሞ በነበሩት ቀናት ራሱ ሸኝ ሆኖ በልዩ ልዩ እርከኖች ላይ ያሉ ኢህአፓዎችን ከከተማው ወደ ገጠር ይሸኝ ነበር፡፡ ለምሳሌ የቤት ለቤት አሰሳው ከሚካሄድበት ዕለት በፊት በነበሩት ቀናት (ከመጋቢት 10-13 ባሉት ቀናት) ተስፋዬ ደበሳይ በርካታ የኢህአፓ አባላትን ከከተማ እያስወጣ ወደ ገጠር መሸኘቱ ተመዝግቧል፡፡ በነዚያ ቀናት በርካቶች ወደ አሲምባና ሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ሄደዋል፡፡ እርሱ ግን እዚያው ሆኖ አሰሳው የሚያመጣውን ውጤት ለማየት ይጠባበቅ ነበር፡፡
                                                                          *****
   ዕለቱ መጋቢት አስራ 15/1969 ነው፡፡ ደርግ የቤት ለቤት አሰሳውን እያካሄደ ነው፡፡ እያንዳንዱ ቤት እየተከፈተ ይፈተሻል፡፡ “አናርኪስት” ተብሎ የተጠረጠረ ሰው እየተያዘ ወደ ማዕከላዊ ምርመራና የቀበሌ እስር ቤቶች ይጋዛል፡፡ ከእስራቱ ለማምለጥ የሞከረ ያለ ምንም ጥያቄ ይገደላል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ያረፈበት የበሪሁን ማሪዬ ቤትም እንደሚፈተሽ መረጃው ለኢህአፓ አሀዶች ደርሷል፡፡ በመሆኑም የተስፋዬን ህይወት ለመታደግ ቀኑን በመንግሥት ቢሮ ውስጥ ተደብቆ ማሳለፍ አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበታል (በወቅቱ ቢሮዎች አይፈተሹም ነበር)፡፡ በዚህ መሰረት ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይና በሪሁን ማሪዬ አምባሳደር ቴአትር አካባቢ ባለው ኪዳኔ በየነ ህንጻ ውስጥ በሚገኘው የበሪሁን ሚስት ቢሮ ለመደበቅ ወሰኑ፡፡ በበሪሁን ማሪዬ ሾፌርነትም ከመርካቶ አካባቢ ወደ አምባሳደር ቴአትር እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡ ተክለ ሀይማኖት አካባቢ ሲደርሱ ግን ተስፋዬን በሚያውቅ ሰው እይታ ውስጥ ገቡ፡፡ ያ ሰው ወዲያኑ ለደርግ ጸጥታ ሀይሎች በመደወል የተስፋዬን መገኘት አበሰራቸው፡፡ ለራሱ ደግሞ በቀስታ (እነርሱ ሳያዩት) ከኋላ እየነዳ ተከተላቸው፡፡ ደርጎች ለወራት ሲፈልጉት የነበረው አውራ ጠላታቸው ዱካ መገኘቱን ሲሰሙ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ተባለው ስፍራ አሳሽ ጦር ላኩ፡፡
  
    ተስፋዬ ደበሳይና በሪሁን ማሪዬ ወደ ኪዳኔ በየነ ህንጻ ገቡ፡፡ ሆኖም ህንጻው እንደጠበቁት ነጻ ሆኖ ስላላገኙት ወደ መጡበት ለመመለስ ወሰኑ፡፡ ፈጠን ባለ እርምጃ ከህንጻው መውጫ በር ላይ ሲደርሱ ግን ለነርሱ የተላከው አሳሽ ጦር ህንጻውን ከቦ አገኙት፡፡ በዚህን ጊዜም ወደ ህንጻው ለመመለስ ሩጫ ጀመሩ፡፡ ሆኖም በቅርብ ርቀት ላይ የነበሩት አሳሾች ተኮሱባቸው፡፡ በሪሁን ማሪዬ ወዲያውኑ ተገደለ፡፡ ተስፋዬ ደበሳይ ደግሞ ግንባሩ ላይ ቆሰለ፡፡ እርሱ ግን አልቆመም፡፡ የህንጻውን ፎቆች በትጋት ወጣ፡፡ ከስድስተኛው ፎቅ ላይ ሲደርስ አንድ ክፍት ቢሮ አየ፡፡ ከቢሮው በመግባት በመስኮቱ በኩል ወደ ውጪ ተወረወረ፡፡ ከሰከንዶች በኋላም መሬት ላይ ተፈጠፈጠ፡፡ የኢህአፓው መሪ እንዲህ ባለ አሳዛኝ ትራጄዲ ከምድር ላይ ተሰናበተ፡፡
                                                                          *****
      ስለዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ በኢህአፓ ወገን በይፋ የተጻፈው ታሪክ ይህ ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አንዳንድ ጸሐፊዎች አሟሟቱን በሚመለከት አወዛጋቢ ታሪኮችን ማስነበብ ጀምረዋል፡፡ ውዝግቡ ለጊዜው አይጠቅመንም፡፡ የታሪክ ጸሐፊዎች ሐቁን እስከሚያወጡት ድረስ አወዛጋቢውን ታሪክ ብንዘለው ይሻላል፡፡ በጣም የምንስማማበት ጉዳይ ቢኖር ሀይሌ ፊዳ የመኢሶን ግርማ እና ኩራት እንደነበረው ሁሉ ተስፋዬ ደበሳይም የኢህአፓ አውራ የነበረ መሆኑን ነው፡፡ መኢሶንን ያለ ሀይሌ ፊዳ፣ ኢህአፓንም ያለ ተስፋዬ ደበሳይ ማሰብ አይቻልም፡፡ ሁለቱም የአንድ ትውልድ ፈርጦች ነበሩ፡፡ ሁለቱም በተሳሳተ ስሌት እርስ በርስ ተዋጉ፡፡ ሁለቱም በጨካኙ ስርዓት ተበሉ፡፡

  የዶ/ር ተስፋዬ ታሪክን የማሳርገው በሚከተለው ታዋቂ የኢህአፓ መዝሙር ነው፡፡
“ቢወቀጥ አጥንቴ ቢንቆረቆር
አዲስ ሥርዓት ልምላሜ
ፍጹም ነው እምነቴ
ትግሉ ነው ሕይወቴ”
                                                                          *****
አፈንዲ ሙተቂ
መጋቢት 14/2006

(የትረካ ምንጮች)
1.      ባቢሌ ቶላ፣ የትውልድ እልቂት፣ 1985፣ አዲስ አበባ
2.     ክፍሉ ታደሰ፣ “ያ ትውልድ” ቅጽ 1፣ 1987፣ አዲስ አበባ
3.     ክፍሉ ታደሰ፣ “ያ ትውልድ” ቅጽ 2፣ 1990፣ አዲስ አበባ
4.     የያ ትውልድ ተቋም፣ “ዝክረ ተስፋዬ ደበሳይ”፣ መጋቢት 2005፣ ከኢንተርኔት የተገኘ
5.     ገነት አየለ አንበሴ፣ የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ትዝታዎች፣ 1994፣ አዲስ አበባ

The writer, Afendi Muteki, is a researcher of the Ethnography and History of the peoples of East Ethiopia. You can read some of his articles on his blog and his facebook page and his blog.
Facebook https://www.facebook.com/afendimutekiharar
Blog


Sunday, December 7, 2014

ብርሀነ መስቀል ረዳን በጨረፍታ




ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
----
    በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ (ከ1989-እስከ 1992 በነበረው ጊዜ) “ሐቄ” የምትባል ልጅ አውቃለሁ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የሴቶች ጉዳይ ሃላፊ የነበረችው (በኋላ በኮትዲቯር የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆነችው) ወ/ሮ ታደለች ሀይለሚካኤል የዚያች ልጅ እናት እንደነበረች ይወሳ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የባለስልጣን ልጅ መሆኗን በመፍራት ብቻ ብዙዎች አይጠጓትም ነበር፡፡ ከልጅቷ ጋር የሚቀራረበው ተወልደ መዝገቡ የሚባል የአዲግራት ልጅ ብቻ እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡
    
     የዩኒቨርሲቲው ትምህርት ከተጠናቀቀ ከጥቂት ወራት በኋላ መጽሔቶችን ሳገላብጥ ያቺ ልጅ ለምልክት ከሞት የተረፈች የፈጣሪ ተአምር እንደሆነች ተረዳሁ፡፡ አባቷ ነፍሲያውን ሊጠነቅ በተቃረበበት ወቅት ታሪኩን ትመሰክር ዘንድ የዘራት ብቸኛ ፍሬው ነበረች፡፡ ብዙዎች በእናቷ ሆድ የነበረችበትን ጊዜ በብዕራቸው ነካክተውታል፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም በበኩላቸው ያቺ ነፍስ በእናቷ ሆድ ውስጥ በመገኘቷ እናቷን ከሞት ያተረፈች መሆኗን መስክረውላታል፡፡ ለዚህም ይመስላል እናቷ “ሐቄ” የሚለውን ስም የሰጠቻት፡፡

ህይወት ተፈራ Tower in the sky የተባለውን መጽሐፍ ስትጽፍ ለዚያች ልጅ መጠነኛ ሽፋን ሰጥታለች፡፡ ከእናቷ ጋር የተነሳችውንም ፎቶግራፍ በመጽሐፉ ውስጥ አካተዋለች፡፡
                                                                          *****
   በፎቶግራፉ ላይ የምትመለከቱት የዚያች ልጅ አባት የነበረውን ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው ከታሪካዊው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ መሪዎች መካከል አንዱ የነበረውና የመጀመሪያው የኢህአፓ ዋና ጸሓፊ ሆኖ የተመረጠው ብርሀነ መስቀል ረዳ ነው፡፡ ለብዙሃን ህይወት መለወጥ በብርቱ የታገለ፣ ሁለቱን ጠንካራ ስርዓቶች ፊት ለፊት የተጋፈጠ፣ ላመነበት ዓላማ ትምህርቱን ሰውቶ መታገልን የመረጠ፣ ከሀገር ወጥቶ በሰው ሀገርና በበረሃ የተንከራተተ፣ በመጨረሻ ላይ ግን ከገዛ ጓዶቹ ጋር ተጣልቶ የራሱን መንገድ የመረጠ፣ በዚህም ከፍተኛ የውዝግብ ርዕስ ለመሆን የበቃ የዚያ ዘመን ፋኖ!...
 
  ብርሀነ መስቀል ማን ነው?… በኢትዮጵያ ህዝቦች የፖለቲካ ትግል ውስጥ ምን ሚና ነበረው?… የርሱ ህይወትና የትግል መንገድ እንዴት ይገመገማል?… እነኝህ በኔ አቅም የሚመለሱ ጥያቄዎች አይደሉም፡፡ ታሪኩ እስከ አሁን ድረስ እያወዛገበ ስለሆነ ሐቁን ከግርድፉ ማጣራቱ ከባድ ጥረት ይጠይቃል፡፡ ብርሀነ መስቀል በወዳጆቹም ሆነ በጠላቶቹ የሚከበርና የሚፈራ መሆኑን ግን ማንም አያስተባብልም፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም በእስር ቤት አናዝዘውት ከገደሉት በኋላ “የመርሐቤቴ ገበሬዎች ገደሉት” እያሉ ለመዋሸት ቢሞክሩም በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ የነበረውን ሚና በአዎንታዊ መልኩ ነው የገለጹት፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቅርብ ጓደኛው የነበሩት አንጋፋው ገጣሚና ባለቅኔ ኃይሉ ገብረ-ዮሐንስ (ገሞራው) “ችኩል እና ቁጡ ከመሆኑ በስተቀር ለሀገር መሪነት የሚበቃ ስብዕና ነበረው” በማለት መስክረውለታል፡፡

      ከሁሉም በላይ የብርሀነ መስቀልን ቆራጥነትና ልዩ ተሰጥኦ ሰፋ ባለ ሁኔታ የገለጹት የኢህአፓው ክፍሉ ታደሰ ነበሩ፡፡ አቶ ክፍሉ “ያ ትውልድ” በተሰኘውና በከፍተኛ ደረጃ ተነባቢ ለመሆን በበቃው መጽሐፋቸው “ብርሀነ መስቀል በኢህአፓ ውስጥ የራሱን አንጃ ፈጥሯል” የሚል ክስ እያቀረቡበት እንኳ ለትግሉ ያበረከተውን አስተዋጽኦ በተዋቡ ቃላት ገልጸዋል፡፡  ለምሳሌ ያህል የሚከተለውን መጥቀስ ይቻላል፡፡
    “በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተውና አንደበተ ርቱእ የሆነው ብርሃነ መስቀል፣ በእንቅስቃሴው ውስጥ ሲታሰርና ሲፈታ የኖረ ነው” (ክፍሉ ታደሰ፣ ያ ትውልድ፣ ገጽ- 144)
                                                                          *****
    ብርሀነ መስቀል ለደርግ መርማሪዎች የሰጠው ቃል ሰሞኑን በኢንተርኔት ተበትኖ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ እኔም ይህ 98 ገጾች ያሉት የምርመራ ቃል ከአንድ የፌስቡክ ጓደኛዬ ደርሶኝ እያነበብኩት ነው (ሙሉውን ዶክመንት www.debteraw.com ከተሰኘ ዌብሳይት ማግኘት ትችላላችሁ)፡፡ እስከ አሁን ድረስ 1/3ኛ ያህሉን አገባድጄዋለሁ፡፡ ይሁንና ፊት ከማውቀው የብርሀነ መስቀል ታሪክ የተለየ ነገር አላገኘሁበትም፡፡ በሚቀጥሉት ቀናት አትኩሮት የሚስቡ መረጃዎችን ካገኘሁበት ልመለስ እችላለሁ፡፡ እስከዚያው ግን ስለብርሀነ መስቀል በትንሹ ላውጋችሁ፡፡

   ብርሃነ መስቀል ረዳ ወልደ-ሩፋኤል በ1930ዎቹ አጋማሽ በትግራይ ገጠር ነው የተወለደው፡፡ ያደገው ግን በደሴ ከተማ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ በነበሩት አጎቱ ቤት ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደሴ በሚገኘው የወይዘሮ ስሒን ት/ቤት ካጠናቀቀ በኋላ በ1955 ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ትምህርቱን ከመከታተል ይልቅ ተማሪዎችን ለተቃውሞ በማንቀሳቀሱ ላይ ነበር ያተኮረው፡፡ በዚህም መሰረት ወደ ዩኒቨርሲቲው እንደገባ ከርሱ ቀደም ብለው “አዞዎቹ” በሚል ቡድን ዙሪያ የተሰባሰቡትን የስር-ነቀል ለውጥ ደጋፊ ተማሪዎችን ለመቀላቀል በቅቷል፡፡ ከዓመት በኋላ በ1956 በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች ህብረት ውስጥ የመረጃ ኦፊሰር ሆኖ ተመርጧል፡፡ በአመቱ ደግሞ የብሔራዊ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህብረት ዋና ጸሓፊ ሆኖ ነበር፡፡

Berhane Mesqel Redda
    
ብርሃነ መስቀል በ1957 የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች “መሬት ላራሹ” የሚል መፈክር አንግበው ድምጻቸውን ለፓርላማ ያሰሙበትን ታሪካዊ ሰልፍ ካደራጁት መካከልም ነበር፡፡ በዚያ ሰልፍ ሳቢያ ከትምህርታቸው ከተባረሩት ዘጠኝ ተማሪዎች መካከልም አንዱ ነው (በወቅቱ ከርሱ ጋር የተባረሩት ገብሩ ገብረወልድ፣ ሀይሉ ገብረዮሐንስ፣ ዮሐንስ ስብሐቱ፣ ታዬ ጉርሙ፣ ዘርዑ ክህሸን፣ ስዩም ወልደ ዮሐንስ፣ ሀብቴ ወልደ ጊዮርጊስና ሚካኤል አበበ ናቸው)፡፡ እነዚያ ተማሪዎች ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ዩኒቨርሲቲው ቢመለሱም በተረጋጋ ሁኔታ ትምህርታቸውን መከታተል አልቻሉም፡፡ በየጊዜው በሚካሄዱት ሰልፎችና የተቃውሞ ስብሰባዎች ግንባር ቀደም ተጠያቂ እየሆኑ ይታሰሩ ነበር፡፡ በስተመጨረሻ ግን የ“አዞዎቹ” ቡድን አባላት ከነአካቴው ከዩኒቨርሲቲው ተባረሩ፡፡ በመሆኑም በተደራጀ ሁኔታ ለመታገል ወሰኑ፡፡
   
   በዚህም መሰረት ብርሃነ መስቀልና አምስት ጓደኞቹ ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ የሚበር አንድ አውሮፕላን በመጥለፍ ወደ ካርቱም ኮበለሉ፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላም ወደ አልጄሪያ ተሻገሩ፡፡ በአልጀርስ ቆይታቸው እጅግ ቀስቃሸ የሆኑ ጽሑፎችን እያዘጋጁ ወደ ሀገር ቤት ይልኩ ጀመር (በዚያ ዘመን “ጥላሁን ታከለ” በሚል የብዕር ስም በመጠቀም አስደናቂ ጽሑፎችን ይጽፍ የነበረው ብርሃነ መስቀል ረዳ እንደሆነ ነው የሚታመነው)፡፡ በአልጄሪያ የነበሩት ስደተኛ አብዮተኞች በውጪው ዓለም ትምህርታቸውን ከሚከታተሉ ኢትዮጵያዊያን ጋር በሚያደርጓቸው ግንኙነቶች በተደራጀ መንገድ የሚታገሉበትን መንገድ ቀየሱ፡፡ እነዚያ ውይይቶች እያደጉ ሄደው በ1964 ኢህአድ (የኢትዮጵያ ህዝብ አርነት ድርጅት) የተሰኘ ህቡዕ ፓርቲ ተወለደ፡፡ ብርሀነ መስቀል ረዳም የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ሆኖ ተመረጠ (የድርጅቱ ስም በ1967 “የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ” በሚል ተለውጧል፤ ይህም በአህጽሮት “ኢህአፓ” የሚባለው ነው)፡፡

     ብርሀነ መስቀል የኢህአድ ዋና ጸሓፊ በነበረበት የመጀመሪያ ዓመት በአብዛኛው ፓርቲውን የማስተዋወቅና ድጋፍ የመፈለግ ስራዎችን ነበር የሰራው፡፡ በዚህም ከአውሮፓ እስከ መካከለኛው ምስራቅ ድረስ ተጉዟል፡፡ ከባለቤቱ ታደለች ሀይለሚካኤል ጋር የተዋወቀው በዚያን ጊዜ ነው፡፡ በ1966 ብርሃነ መስቀልና ጥቂት ሰዎች የድርጅቱን የትጥቅ ትግል እንዲጀምሩ ወደ ኤርትራ ተላኩ፡፡ ወታደራዊ ስልጠና ለመውሰድ ለአንድ ዓመት በኤርትራ ከቆዩ በኋላ በ1967 መጀመሪያ ላይ ትግራይ ውስጥ ወደሚገኘው አሲምባ ተራራ ተሻገሩ፡፡ ሆኖም የትጥቅ ትግሉን ሳይጀምሩ በአሲምባ ቤዛቸው ለስድስት ወራት ቆዩ፡፡ በዚህ መሀል ስምንት ያህል የቡድኑ አባላት ከብርሀነ መስቀል ጋር የነበራቸውን ቀየሜታ በማሳበብ ድርጅቱን ጥለው ለደርግ መንግሥት እጃቸውን ሰጡ፡፡ ብርሀነ መስቀል በፋኖዎቹ አድራጎት በመቆጣቱ በሌሉበት የሞት ፍርድ ፈረደባቸው፡፡ ሆኖም ይህ ውሳኔው ከሌሎች የኢህአፓ አባላት ተቃውሞ ገጠመው፡፡ የኢህአፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጉዳዩን ካጣራ በኋላ በሰዎቹ ላይ የተላለፈው የሞት ፍርድ እንዲነሳ ወሰነ፡፡ ብርሀነ መስቀልም ከሰራዊቱ ተነጥሎ ወደ አዲስ አበባ እንዲሄድ ተወሰነ፡፡ ይህም በብርሀነ መስቀልና በሌሎቹ የኢህአፓ መሪዎች መካከል ንትርክ ፈጠረ፡፡

     ይህ በእንዲህ እንዳለ በነሐሴ ወር 1967 አህአፓ ራሱን በአዲስ መልክና በአዲስ ስም ሲያደራጅ “ዋና ጸሐፊ” የሚባል የስልጣን እርከን ተሰረዘ፡፡ ድርጅቱ ሊቀመንበርም ሆነ ዋና ጸሐፊ የለውም ተብሎ ታወጀ፡፡ ብርሀነ መስቀል ይህንን እርምጃ እርሱን ከቦታው ለማንሳት የተሸረበ ሴራ አድርጎ ስለወሰደው ከፍተኛ ቅሬታ አደረበት፡፡ ከማዕከላዊ ኮሚቴው ጋር የሚያደርገውንም ግንኙነት ማቀዝቀዝ ጀመረ፡፡ የደርግ መንግሥት በሚያዚያ ወር 1968 በህቡዕ ለተደራጁ ድርጅቶች ሁሉ የግንባር ጥሪ ሲያደርግ ብዙሃኑ የኢህአፓ አመራር ጥሪውን በመሰረቱ እንደሚቀበል ከገለጸ በኋላ መሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አስቀመጠ፡፡  እነዚያ ሁኔታዎች ካልተሟሉ በስተቀር ከደርግ መንግሥት ጋር እንደማይሰራ ገለጸ፡፡ ብርሀነ መስቀል ግን “ቅድመ- ሁኔታ ማስቀመጡ ልክ አይደለም” በማለት ተከራከረ፡፡ በነሐሴ ወር 1968 የኢህአፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ “ራሳችንን ለመከላከል የከተማ ትጥቅ ትግል ማድረግ አለብን” በማለት ሲወስን ብርሀነ መስቀል “ውሳኔው አደገኛ ነው፤ ኢህአፓን ያስመታል፤ ደግሞም ደርግ ማርክሳዊ ነኝ ብሎ ያወጀ መንግሥት ስለሆነ ማርክሳዊ መንግሥትን በትጥቅ አመጽ መቃወም የአብዮታዊያን ጸባይ አይደለም” በማለት በብርቱ ተቃወመው፡፡ ይህም ታቃውሞ ከኢህአፓ አመራር ጋር እስከ ወዲያኛው አቆራረጠው፡፡
 
   የኢህአፓ አመራር ብርሀነ መስቀል ያሳያቸውን የአቋም ልዩነቶች ከገመገመ በኋላ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነቱ ሰረዘው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም “ብርሀነ መስቀል በፓርቲው ውስጥ የራሱን አንጃ ለመመስረት ጥረት እያደረገ ነው” የሚል ክስ አቀረበበት፡፡ በድርጅቱ ጋዜጦች ላይ ግለ-ሂስ እንዲያደርግም አዘዘው፡፡ ብርሀነ መስቀልም ሂሱን ካወረደ በኋላ በድርጅቱ ታጣቂዎች እንዲጠበቅ ተደረገ፡፡ በሚያዚያ 1969 ግን ለማንም ግልጽ ባልሆነ መንገድ ከአዲስ አበባ ከተማ ተሰውሮ ወደ መርሐቤቴ አውራጃ ገባ፡፡ እዚያም ከተወሰኑ ሰዎች ጋር የትጥቅ ትግል ለማድረግ ሞከረ፡፡ ይሁን እንጂ በእርምጃው ከጥቂት ወራት በላይ አልዘለቀም፡፡ የደርግ አዳኝ ሀይሎች በ1970 መጀመሪያ ላይ ይዘውት ወደ አዲስ አበባ አመጡት፡፡ ለአንድ ዓመት ከሰድስት ወራት ያህል በታላቁ ቤተ መንግሥት ከታሰረ በኋላ በሚስጢር ተገደለ፡፡
                                                                          *****
      የብርሀነ መስቀል አንጃ የመፍጠር ሙከራ በራሱም አንደበት የተረጋገጠ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ብርሀነ መስቀል “እኔ ያካሄድኩት የእርማት ንቅናቄ እንጂ ፓርቲውን ለማጥፋት ያለመ አንጃ አልፈጠርኩም” ባይ ነው፡፡ በተጨማሪም ባለቤቱ ወይዘሮ ታደለች ሀይለ ሚካኤል በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ ምልልስ ብርሀነ መስቀል የእርማት ንቅናቄ ለማካሄድ መሞከሩን ተናግረዋል፡፡ በዚያ ዘመን በርሱ ስም የተሰራጩትን ልዩ ልዩ ዶክመንቶች በሙሉ የርሱ ናቸው ለማለት ይከብዳል፡፡ አንደኛው ጽሑፍ ግን በርሱ እጅ ጽሑፍ የተጻፈ መሆኑ ስለሚታወቅ የርሱን እምነት ይገልጻል ተብሎ ይታመናል፡፡ ብርሀነ መስቀል በዚያ ጽሑፉ የኢህፓን አመራር ቢኮንንም ደርግንም በሚገባ ይቃወማል፡፡ እንዲሁም በርሱ ስም ድርጅቱን የበጠበጡ በርካታ ቅጥረኞች እንደነበሩም ያወሳል፡፡ ሆኖም የኢህአፓ አመራር እርሱ ያለውን አምኖ የተቀበለው አይመስልም፡፡ ኢህአፓዎች “ለድርጅቱ ብተና ፈር የቀደደ ከሀዲ ነው” ነው የሚሉት፡፡

   ማንም የማይክደው አንድ ሐቅ ግን አለ፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ሲነሳ ብርሀነ መስቀልን መርሳት በጭራሽ አይሞከርም፡፡ በርካታ የለውጥ ፈላጊው ትውልድ አባላት የርሱን አርአያ በመከተል ወደ ትግሉ ጎራ መቀላቀላቸውንም ማስተባበል አይቻልም፡፡ ስለዚህ ምሁራን በቅጡ ያልተመረመውን የዚህን ፋኖ ታሪክ ጎልጎለው በትግሉ ውስጥ የነበረውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ሚና ሳይሸፋፍኑ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
                                                                          *****
አፈንዲ ሙተቂ
ህዳር 28/2006