ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
ተነገወዲያ ህዳር ህዳር 29/2007 ዘጠነኛው የብሄርና ብሄረሰቦች ቀን ሊከበር
ነው፡፡ ይህ ቀን ለበዓሉ አከባበር የተመረጠው የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት የጸደቀበት ስለሆነ ነው ተብሏል፡፡ ታዲያ በዚሁ ቀን አንድ
ታላቅ አብዮታዊ ተገድሎ ነበር፡፡ የሚገርመው ደግሞ በዚያች ቀን የሞተው ሰውዬ በኢትዮጵያ ውስጥ የብሄርና ብሄረሰቦች መብት መከበር
አለበት በማለት ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ የጻፈ ሰው መሆኑ ነው፡፡
*****
ህዳር
29/1964፡፡ ረፋዱ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 708 ጄት አውሮፕላን ከአዲስ አበባ በአስመራ በኩል
ወደ አቴንስ ሊበር ነው፡፡ በአውሮፕላኑ የሚጓዙ መንገደኞች ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ ሰባት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም
ከአውሮፕላኑ ውስጥ ተሳፍረዋል፡፡ የበረራው ሰዓት ሲደርስ አውሮፕላኑ ከመሬት ተነሳ፡፡ ከሰማዩ ገብቶ መብረር ሲጀምር ግን ያልታሰበ
ሁኔታ ተከሰተ፡፡ እነዚያ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አውሮፕላኑን በቁጥጥራቸው ስር ማዋላቸውን አስታወቁ፡፡ እነርሱ ወደሚፈልጉት ሀገር እንዲበሩም አብራሪዎቹን አዘዟቸው፡፡ ተማሪዎቹ
የጠለፋ እወጃውን ካሰሙ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሌላ ያልታሰበ ነገር ተከሰተ፡፡ አውሮፕላኑን ከጠለፋ እንዲታደጉ የታዘዙ ኮማንዶዎች
በቀጥታ በጠላፊዎቹ ላይ በማነጣጠር ተኮሱባቸው፡፡ ስድስት ጠላፊዎች ተገደሉ፡፡ አንዲት ጓደኛቸው ደግሞ በከባድ ሁኔታ ቆሰለች፡፡
የአውሮፕላኑ ወለል በሙታኑ ደም ታጠበ፡፡
Walelign Mekoneen |
*****
በዚያች ዕለት የሞተው ታዋቂው የተማሪዎች ንቅናቄ መሪ ዋለልኝ መኮንን
ነበር፡፡ ከርሱ ጋር የተገደሉትም ማርታ መብራህቱ፣ ጌታቸው ሀብቴ፣ ተስፋዬ ቢረጋ፣ ዮሐንስ በፈቃዱ እና አማኑኤል ዮሐንስ ናቸው፡፡
እነዚያ ወጣቶች አውሮፕላኑን ለመጥለፍ የሞከሩት የስርዓቱ ክትትል መፈናፈኛ ስላሳጣቸው ነው፡፡ ዓላማቸው ወደ ውጪ ከኮበለሉት ጓደኞቻቸው
ጋር በመቀላቀል ለስር-ነቀል ለውጥ የሚታገል ድርጅት መመስረት ነበር፡፡ ከድርጅቱ ምስረታ በኋላም ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው ትግሉን
በየአቅጣጫው ለማፋፋም አስበዋል፡፡ ሆኖም እንደተመኙት አልሆነላቸውም፡፡ አውሮፕላን ለመጥለፍ ማቀዳቸው ቀደም ብሎ ተጠቁሞ ስለነበር
የጸጥታው ክፍል በአየር ላይ አፍኖ አስቀራቸው፡፡
*****
ከላይ በተገለጸው አሳዛኝ ገቢር (ትራጄዲ) ህይወቱ የተቋጨው ዋለልኝ መኮንን
በወሎ ክፍለ ሀገር የሳይንት (ቦረና) አውራጃ ተወላጅ ነው፡፡ የአንደኛና ደረጃ ትምህርቱን በደሴው ንጉሥ ሚካኤል ትምህርት ቤት
አጠናቀቀ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም እስከ አስረኛ ክፍል ድረስ ደሴ ከተማ በሚገኘው ታሪካዊው ወይዘሮ ስሒን ት/ቤት ተከታለለ፡፡
አስራ አንደኛና አስራ ሁለተኛ ክፍልን ደግሞ የዘመኑ ምርጥ ተማሪዎች መማሪያ በነበረው በአዲስ አበባው በዕደማሪያም ትምህርት ቤት
አገባደደ፡፡ በ1958 ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላም እጅግ የተለየ አብዮታዊ ሆነ፡፡
ዋለልኝ በ1959 በዩኒቨርሲቲው በተደረገው የግጥም
ውድድር “ሙት ወቃሽህ መጣው” በሚለው ግጥም አንደኛ ወጥቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲው
ተማሪዎች ህብረት ይዘጋጅ በነበረው የታገል መጽሔት ከማንም በላይ የነቃ ተሳትፎ ያደርግ ነበር፡፡ በህቡዕ የሚዘጋጁ ጽሑፎችንም እያዘጋጀ
ያሰራጭም ነበር፡፡ በተለይ “አዞዎቹ” የሚባለው የስር-ነቀል ለውጥ ደጋፊ የተማሪዎች ስብስብ በአቋም ደረጃ የተስማማባቸውን ሀሳቦች
በጽሑፍ እያቀናበረ የሚያዘጋጀው እርሱ እንደነበር በያኔው እንቅስቃሴ የተሳተፉትም ሆነ የዘመኑን ታሪክ ያጠኑ ምሁራን ይመሰክራሉ፡፡
ከዋለልኝ ጽሑፎች መካከል ዝነኛ የሆኑት ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው ከላይ የጠቀስኩትና ህዳር
10/1961 በታተመው “ታገል መጽሔት” ላይ የወጣው “የብሄረሰቦች ጥያቄ በኢትዮጵያ” የሚል ርዕስ ያለው ጽሑፍ ነው፡፡ ሁለተኛው
ደግሞ በ1962 የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት የነበረው ጥላሁን ግዛው ሲገደል የአጼው ስርዓት በተማሪዎቹ ላይ ያደረገውን ዛቻ በመቃወም
“ለአዋጁ አዋጅ” በሚል ርዕስ በህቡዕ ጽፎ የበተነው ጽሑፍ ነው፡፡ ዋለልኝ በጽሑፎቹ ሳቢያ በተደጋጋሚ ጊዜያት ታስሯል፡፡ በተለይ
“ለአዋጁ አዋጅ”ን የጻፈው እርሱ መሆኑ ሲታወቅ በችሎት ፊት ቀርቦ አምስት ዓመት እስራት ተፈርዶበታል (ሆኖም ተማሪዎች ባደረጉት
ከፍተኛ የተቃውሞ ጫና ከዓመት በኋላ ተፈትቷል)፡፡
ከ1962 በኋላ ሁለት ክስተቶች የተማሪውን ንቅናቄ አቅጣጫ ቀይረውታል፡፡
እነዚህም በስርዓቱ የሚደረገው አፈና መጠናከር እና የድርጅት ምስረታ ጥያቄ መቀስቀስ ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች
እንደ ቀድሞው ጊዜ የተቃውሞ ሰልፍ ከማድረግ ይልቅ የጥናት ክበቦችን እየመሰረቱ መወያየቱን መረጡ (የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በተቃውሞ
ቀጠሉ)፡፡ ዋለልኝም በውይይት ክበቡ በሚያደርገው ጥናት ላይ አተኮረ፡፡ ከሀገር ተሰደው በአልጄሪያ ከሚገኙት እነ ብርሀነ መስቀል
ረዳ ጋር በሚያደርገው የደብዳቤ ልውውጥ አማካኝነትም ሰፊ መሰረት ያለው ድርጅት ለመመስረት በሚደረገው ውይይትም ውስጥ ይሳተፍ ነበር፡፡
ህዳር 29/1964 በውጪ ካሉት ጓደኞቹ ጋር ለመቀላቀል ሲል አውሮፕላን ጠለፈ፡፡ ሆኖም ካሰበው ስፍራ ሳይደርስ በአውሮፕላኑ ውስጥ
ተገደለ፡፡
*****
ከያኔው የተማሪዎች ንቅናቄ መሪዎች መካከል ዋለልኝ መኮንን ልዩ የሚያደርገው
አንድ ነገር አለ፡፡ ይኸውም የተለያየ አመለካከት ባላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች እንደ ታላቅ ሰማዕት የሚታይ መሆኑ ነው፡፡ ደርግ፣
ኢህአፓ፣ ህወሐት፣ ኦነግ፣ ሻዕቢያ፣ መኢሶን፣ ወዘተ… ሁሉም ለርሱ በጎ አመለካከት ነው ያላቸው፡፡ ታዲያ በዋለልኝ ታሪክ ላይ የሚደረገው
ሽሚያም በጣም የጠነከረ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ታሪኩን ከራሳቸው ድርጅት ጋር ለማቆራኘት ይሞክራሉ፡፡ በወቅቱ የነበረው የርሱና የጓደኞቹ
አሰላለፍ ሲገመገም ግን ዋለልኝ ኢህአፓን ከመሰረቱ ወጣቶች ጋር ተመሳሳይ የፖለቲካ መስመር የነበረው ሆኖ ነው የሚታየው፡፡ ኢህአፓን
የመሰረቱትም የርሱ የቅርብ ጓደኞች ናቸው፡፡ በመሆኑም ዋለልኝ በህይወት ቢሰነብት ኖሮ የዚሁ ድርጅት አባል ይሆን ነበር ተብሎ ነው
የሚገመተው፡፡
*****
ዋለልኝ መኮንን ከብዙ በጥቂቱ ይህ ነበር፡፡ ወደፊት
ሰፋ ባለ ሁኔታ ስለርሱ እጽፋለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ እናንተም በበኩላችሁ የምታውቁትን እንድታጋሩን በአክብሮት እንጠይቃችኋለን፡፡
------
ሰላም
አፈንዲ ሙተቂ
ህዳር 29/2006