Sunday, April 6, 2014

የማይረሱ አባባሎች (ቆየት ካሉ ምንጮች የተገኙ)





ጥንቅር፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
 “ኢዴሐቅን ከለንደኑ ኮንፈረንስ ለማስቀረት የተናገሩት ምክንያት “ኢዴሐቅ ጦር የለውም” የሚል ነበር፤ ኢዴሐቅን ከሽግግር መንግሥቱ ምስረታ ኮንፍረንስ ሲያስቀሩ እንደምክንያት የተናገሩት ደግሞ “ኢዴሐቅ በጊዜያዊ መንግሥቱ ላይ ጦርነት አውጇል” የሚል ነው፡፡”
 አቶ መርሻ ዮሴፍ የኢዴሐቅ ሊቀመንበር እና የኢህአፓ ከፍተኛ የአመራር አባል (ኢትዮጵያን ሪቪው መጽሔት፣ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 1992)
*****
“በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ግጭት የለም፡፡ ግጭት አለ ከተባለ በትምክህተኞች ጭንቅላት ውስጥ ነው”
አቶ መለስ ዜናዊ፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እፎይታ መጽሔት “በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ግጭት ተፈጥሯል ይባላል” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ የተናገሩት (እፎይታ መጽሔት፤ ጥር 1990)
*****
“በእኛ ሀገር እውቀት ከስልጣን ይመነጫል”
 ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም፣ (የብራና ማህደር፣ ሚያዚያ 1985)
*****
“የኢትዮጵያን ባንዲራ እንኳንስ እኛ ግመሎቻችን ያውቋታል”
ሱልጣን ዓሊ ሚራህ፤ የአፋር ህዝብ መንፈሳዊ አባት (አፍሪካ ቀንድ መጽሔት፣ የካቲት 1985)
*****
“ከባድመ ወጣን ማለት ጸሀይ ጠፋች ማለት ነው፡፡ ጸሀይ ለዘላለሙ ጠለቀች ማለት ነው”
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ (የኤርትራ ሬድዮ፣ ህዳር 1991)
*****
“የዘመናት የህዝብ ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን የአዲስ አበባን ሬድዮ ጣቢያ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ተቆጣጥሮታል”
በቅጽል ስሙ ላውንቸር በሚል የሚታወቀው የኢህአዴግ ታጋይ (የኢትዮጵያ ሬድዮ፣ ግንቦት 20/1983) 
*****
“የኢህአዴግን ልብ እንኳን ሰው እግዚአብሔርም አያውቀውም፤ ሳይንስም አልደረሰበትም”
ዶ/ር መረራ ጉዲና (ጦቢያ መጽሔት፤ ህዳር 1992)
*****
“ኢትዮጵያዊ ለመሆን መደራደር እንፈልጋለን”
አቶ ሌንጮ ለታ ፣ በወቅቱ የኦነግ ም/ሊቀመንበር (ሳሌም መጽሔት፣ ነሐሴ 1984)
*****
“የግንቦት ሀያው ድል የመጨረሻዋን ጥይት በአዲስ አበባ ላይ የተኮሱት የኢህአዴግ ታጋዮች ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያዋን ጥይት በአሲምባ የተኮሱት የኢህአፓ ታጋዮች ጭምር ነው”
 አቶ ያሬድ ጥበቡ ፤ የኢህዴን መስራችና ሊቀመንበር የነበሩ (መስታወት መጽሔት ጥቅምት 1985)
*****
“ስዬ፣ ክንፈ እና መለስ በየተራው ወደኔ እየመጡ “እመን፤ አለበለዚያ ልጆችህን ፊትህ እንገድላቸዋለን” እያሉ ህሊናዬን ሲያስጨንቁት ምን ላድርግ?… ለልጆቼ ደህንነት ስል ያልሰራሁትን ሰራሁ ብዬ ከማመን በስተቀር ምንም ምርጫ አልነበረኝም”
     አቶ ታምራት ላይኔ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል ፍርድ ቤት ቀርበው ከተናገሩት (ጎህ መጽሔት ሚያዚያ 1993)፣
*****
“የሆነ ነፋስ ነው የሰጣችሁ እንጂ ሰርታችሁ ያመጣችሁት ውጤት አይደለም፡፡ ህዝቡን አሳስታችሁ ነው ይህቺን ታክል ያገኛችሁት፡፡ ቢሆንም አሁንም ያሸነፍነው እኛ ነን”
  አቶ በረከት ስምኦን፣ በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትርና የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ ኮሚቴ ኃላፊ የነበሩ፣ ተቃዋሚዎች በምርጫ-97 ያገኙትን ውጤት በማስመልከት ከተናገሩት (በበርካታ ፕሬሶች ላይ ታትሞ ነበር፣ ግንቦት 1997)
*****
“ኢህዴን (ብአዴን) የሕወሐት የአማርኛ ዲፓርትመንት ነው”
አቶ አብርሃም ያየህ (የብራና ማህደር፣ ሚያዚያ 1985)
*****
“እኛ ታሪክ ይቅርና ጦርነት መስራት እንችላለን”
በሽግግሩ ዘመን የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ (አባባሉ በብዙ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ቢታይም አቶ ስዬ እንዲህ ያሉበትን አጋጣሚ በትክክል ለማወቅ አልቻልኩም)
*****
“የኦሮሞ ህዝብ ግንድ ነው፡፡ ቅርንጫፍ እንጂ ግንድ አይገነጠልም”
  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ (ኢትኦጵ መጽሔት፤ መጋቢት 1996)
*****
“ያለምንም ማጋነን ለኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ነገር አድርገንለታል፡፡ የመሬት አዋጁን ያወጅነው እኛ ነን፡፡ ለሙስሊሙ ህዝብ የሃይማኖት በዓሉን በብሔራዊ በዓል ደረጃ አውጀንለታል፡፡ ለክርስቲያኑም ጥበቃ አድርገናል”
  የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ (ሳሌም መጽሔት፣ ጥር 1985)
*****
  “ኢትዮጵያ በታሪኳ ጦርነት አሸንፋ አታውቅም”
  አቶ ዳዊት ዮሐንስ ፣ የቀድሞ አፈ-ጉባኤ (ምኒልክ መጽሔት ፤  ታህሳስ 1992)
*****
 “ከእንግዲህ እግርህ ቢቆረጥስ ምንድነው? ማራቶን አትሮጥበት፡፡ አንተ በጊዜህ ለሀገርህ ሁሉንም አድርገሃል፡፡ ከአሁን በኋላ እግር  ብዙም ላያስፈልግህ ይችላል፡፡ ስለዚህ አንገትህን አትድፋ፡፡ ኮራ ነቃ በል”
ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ጥላሁን ገሰሰ እግሩን ከተቆረጠ በኋላ ስልክ ደውለው ሲያነጋግሩት (ኢትኦጵ ጋዜጣ፤ የካቲት 1997)
*****
“ይህ ያለቀለት ጨዋታ ነው፡፡ በቃ! አንድ መንግስት አዲስ አበባ ታቆማለህ፡፡ አንድ መንግሥት በአስመራ ታቆማለህ፡፡ ይህንን አምነን መቀበል አለብን፡፡ የኛ ሰው ትልቁ ችግር እውነት አምኖ ለመቀበል አለመቻል እና የሚያምንበትን በግልጽ አለመናገር ነው፡፡ እኛ ግን የኤርትራ ጥያቄ በዚሁ መልኩ እንደሚፈታ ግልጽ ሆነን እንናገራለን”
አቶ ተፈራ ዋልዋ በዋሽንግተን ዲሲ ለተሰበሰቡ ኢትዮጵያዊያን (አባባሉ የተሰማው ኢህአዴግ ስልጣን ከመያዙ በፊት በአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ በ1982 ባሰራጨው አንድ ዝግጅት ነው፡፡ እኔ እዚህ የጻፍኩት ግን ከኢትኦጵ መጽሔት የመስከረም 1997 እትም ወስጄው ነው)
*****

Friday, September 13, 2013

Ali Shabbo’s Search for his Beloved


-----------------
Written by: Mohammed Ahmed (Mohammed Qophee)
Perforomed by: Ali Shabbo
Date: 1986
--------------
Ali Shaboo lost the whereabouts of his beloved accidentally. He started to seek her through the entire Hararghe region. And finally he found her in my hometown, Galamso. Here is how he expressed the story of the search for his beloved in a beautiful song (the poem is in Afaan Oromoo. The words in parenthesis are the approximate English translations).
------------
Diimtuu too bareedduu tannin yaadu halkuu (My beautiful beloved the one I miss all nights)
Obsu waa hindandayuu bikka isin jirtuu (I can’t be patient of thinking her whereabouts)
Hamman deemee arku (Until I go and get her)
Teeyso isidhaa hinbeyne bikka itti argamtu (I don’t know the address where she can be found)
Mee nin iyyaafadha oliifi gadittuu (Let me move in the ups and downs to look for her)
Barbaadu waa hindhabu Hararguma haataatu (If she is in Hararge, it is likely that I can get her)
------------
Dirree Dhawaas bu’ee mana gaggaafadhe (I went to Dire Dawa and asked her residence)
Tanin shakke cufa suuta akheekadhe (I watched carefully the ones I suspected of her)
Dhiiroo barbaada isii oow’i waan nagodhe (But I gained nothing except the heat of the desert)  
------------
 Jijjiga Hindabartu kharaa Gursum khana (She might not pass Jijjiga and the way up to Gursum)
  Xuuxxisaa dhagayeetin itti-fufe amna (On that proposition I continued my journey)
Way garaa jalalaa laalaa laala gowwomina (Really love has misled me by taking me there)  
------------
Kharaa baddaa Khanaa hindhabamtu Laata (She might be found up in the highlands)
Je’e numan dhaqe ani Gaara Mul’ataa (Saying that I went to Gara Mul’ata and the hills)
Arkuu waa hindandeenyee waan isii fakkaataa (But never did I see the like of her)
------------

Oborraa fi Ciroo hunda kehysa dhaqe (I really traveled in Oborra and Ciroo)
Miilaa fi makinaan barbaadeetin dhabe (But I couldn’t get her after a search on foot and by trucks)
Argu koo waa hin oolu je’etin of sobe (I wasn’t frustrated, and I said to myself rather “I will get her”)
------------
Sa eedaan qalbiin tuni wahayyuma beyti (Indeed my heart knew what was going to happen)
Baddeeysa ol kunnaan khate gammachutti (When I passed Baddeessa, it (my hart) was full of delights)
Jaalalleen tiyya tun intala Habrootii (For my beloved was found to be a native of Habro)
------------
Jaalallen gar meeqaan barbaadaan of rakkee (My beloved whose search had caused me these troubles)
Tanin deemee dhabe baakkan itti shakkee (The one whom I couldn’t get from the places I suspected)
 Walkkaa magaalaa Galamsottiin arke (I found her in the center of Galamso town)
--------------
Arkadhe qal’o too diimtuu too bareedduu (I got my beloved, the beautiful and the tall)
Isii barnootarra kharaa gala deemtu (When she is returning to home from school)
 Gamdeen bahaa mee ree dheebuu tootuu (Let me be happy now, let me quench my thirst in her)
--------
Regards to Ali Shabbo for immortalizing my hometown in his beautiful speech.

Afendi Muteki
September 14/2013
--------

“ዓሊ ሸቦ” እና “ፍለጋው”


ጸሓፊ፡- አፈንዲ ሙተቂ
----------
ባልሳሳት ዘመኑ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 1978 ይመስለኛል፡፡ በዚሁ ዓመት ነበር አንድ አንጋፋ አርቲስት አስደናቂ ዜማውን የለቀቀው፡፡ ይህ ሰው ፍቅረኛው ስለጠፋችበት በዘፈኑ እየተመራ በእግር በፈረስ ይፈልጋት ጀመር፡፡ በቆላውና በደጋው ሁሉ ሲንከራተትላት ከረመ፡፡ በመጨረሻም አጥቷት ልቡ እንደተሰበረ ወደቤቱ ሊገባ ሲል በአንድ ከተማ ውስጥ አገኛትና በደስታ ፈነጠዘ፡፡ ከዚያም የልቡን አደረሰ፡፡
   ለመሆኑ እርሱ ማን ነው? ጉዞውን እንዴት ፈጸመው? እስቲ አብረን እንየው
  *****  *****  *****
   ዓሊ ሸቦን ለኦሮምኛ ተናጋሪዎች ለማስተዋወቅ አልቃጣም፡፡ አማርኛ ከሚናገሩት ውስጥ ግን እርሱን የማያውቁት እንደሚበዙ ይታወቀኛል፡፡ ስለዚህ ትንሽ ማብራሪያ ቢጤ እነሆ!
 
“ዓሊ ቢራን ለሙዚቃ እድገትህ አርአያ የሆነህ ማን ነው?” ብላችሁ ብትጠይቁት “ዓሊ ሸቦ” በማለት ነው የሚመልስላችሁ፡፡ ትንሹ ዓሊ (ቢራ) ትልቁን ዓሊ (ሸቦ) ስላየ ነው ወደ ከያኒነት የገባው፡፡ ጊታር ከመጫወት ጀምሮ በህዝብ ፊት ቆሞ እስከ መዝፈን ያሉትን እውቀቶች ሁሉ የቀሰመው ከዓሊ ሸቦ ነው፡፡

   በርግጥም ዓሊ ሸቦ በጣም አንጋፋ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እድሜው ወደ ሰባ ገደማ እንደሆነ ይገመታል፡፡ በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ በድሬዳዋ ከተማ “አፍረን ቀሎ” የሚባለውን የኪነት ቡድን ከመሰረቱትና በቡድኑ አባልነት ከተመዘገቡት የመጀመሪያቹ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ወደ ስልሳ ዓመታት በሚጠጋው የሙዚቃ ህይወቱ የተጫወታቸው ዘፈኖች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ከነርሱ ውስጥ “ዱምቡሼ ገላ”፣ “አማሌሌ”፣ “ኢስፖርቲ” (ስፖርት)፣ “ሹፌራ”፤ “ቢዮ አደሬ” ወዘተ… ሊጠቀሱ ይችላሉ (የዓሊ ሸቦን “ዱምቡሼ ገላ” ለማየት ይህንን ሊንክ “ነካ” አድርጉት http://www.youtube.com/watch?v=WRb7ze724ww )፡፡






   ከዓሊ ሸቦ ኋላ የተነሱት እነ ዓሊ ቢራ፣ ሂሜ ዩሱፍ፣ ማህዲ ጃፖን፤ ሀመልማል አባተ፣ ወዘተ.. የርሱን ዘፈን ተጫውተዋል፡፡ የሶማሊያዋ ፋጡማ ቃሲምም “ሜ ማሉፊን ኦፊቱ በራ” የሚለውን የዓሊ ሸቦ ዜማ ባማረ ሁኔታ ተጫውተዋለች፡፡ የሱዳኑ መሐመድ ወርዲ “ሱድፋ” የሚባለውን ዘፈኑን ከዓሊ ሸቦ የኦሮምኛ ግጥም ጋር እየቀላቀለው ዘፍኖታል፡፡ በሌላ በኩል ዓሊ ሸቦ በጊታር ተጫዋችነቱ የበርካታ ከያኒያንን ዘፈን በሙዚቃ አጅቧል፡፡ የነ አደም ሐሩን፣ ሐሎ፣ ዳዌ፣ አልማዝ ተፈራና ከዲር ሰዒድን የድሮ ካሴቶች ስትከፍቱ ከውስጡ የምትሰሙትን ጊታር የሚጫወተው ዓሊ ሸቦ ነው፡፡
    
ስለዓሊ ሸቦ ይህንን ያህል ካልኳችሁ ይበቃል፡፡ አሁን ወደ ዋናው ጉዳይ እንለፍ፡፡
    *****  *****  *****
ከመግቢያዬ እንዳልኩት ዓሊ ሸቦ ወዳጁ ጠፋችበት፡፡ እናም በ1978 በለቀቀው ዜማው እንዲህ ሲል ፍለጋውን ጀመረ (በቅንፍ ውስጥ ያለው ተቀራራቢ የአማርኛ ትርጉም ነው)፡፡

 Diimtuu too bareedduu tannin yaadu halkuu (የኔ ቀይ ዳማ ጉብል ሁሌ እምናፍቃት)
Obsu waa hindandayuu bikka isin jirtuu (እንዲህ ጠፍታብኝስ እኔስ አልታገሳት)
Hamman deemee arku ( ካለችበት ፈልጌ እስከማገኛት)

ትንሽ ወረድ ብሎም እንዲህ በማለት ጨመረበት፡፡
Teeyso isidhaa hinbeyne bikka itti argamtu (አድራሻዋን አላውቅ የተደበቀችበትን)
Mee nin iyyaafadha oliifi gadittuu (እኔስ ላስሳት ነው ሄጄ ታቹን ላዩን)
Barbaadu waa hindhabu Haraguma haataatu (ከሀረርጌ ምድር አገኛት እንደሆን)

  ታዲያ ዓሊ ፍለጋውን ከየት የጀመረ ይመስላችኋል? ከሀረር ነው፡፡ በጥንታዊቷ የአባድር ከተማ ላይ ከትሞ ነው እንዲህ በማለት ለፍለጋዋ መቁረጡን ያሰማው፡፡ ከዚያስ ወዴት ቀጠለ? እንዲህ ይለናል፡፡
 Dirree Dhawaas bu’ee mana gaggaafadhe (ድሬ ዳዋ ወርጄ ጠያይቄ አድራሻዋን)
Tanin shakke cufa suuta akheekadhe (በጥንቃቄ አይቼ እርሷ ትሆን ያልኳቸውን)
Dhiiroo barbaada isii oow’i waan nagodhe (ወበቅ ብቻ ተረፈኝ ወይ እኔን ወይ እኔን)

   ዓሊ ፍለጋውን በተስፋ ከድሬ ዳዋ መጀመሩ ልክ ነበር፡፡ በርግጥም ድሬ ከምስራቁ ክፍል ልዩ ልዩ መንደሮች የተሰባሰቡ ሰዎች መኖሪያ ናት፡፡ የዚያ ዘመን ወጣት በድሬ የተጧጧፈው የኮንትሮባንድ ንግድ ስለሚያስጎመጀው እንደምንም ብሎ በከተማዋ ላይ  ከትሞ እየሸቀለ ኑሮውን መሙላት ይፈልጋል፡፡ በአነስተኛ ከተሞች የከበረው ነጋዴ የመጨረሻው ዓላማው ድሬዳዋ ገብቶ ስሙን እነ ሐሰን ፎርሳ፣ ባሻንፈር፣ ሐምዳኢል፣ ሙሐመድ አብዱላሂ ኦግሰዴን ከመሳሰሉ የዘመኑ ዲታዎች ተርታ ማሰለፍ ነው፡፡ በድሬ ዘመድ ያላቸው ኮረዳዎችም “ቫኬሽን”ን እያሳበቡ ከቤተሰቦቻቸው ያፈተልኩና ክረምቱን በዚያች ውብ ከተማ ለማሳለፍ ወደዚያው ያቀናሉ፡፡ ታዳጊዎችም የሐሺሚን ሓላዋና ባቅላዋ በዝናው ስለሚያዉቁት እዚያ ሄደው ካልበሉት የሚረኩ አይመስላቸውም፡፡ ስለዚህ ቤተሰቦቻቸው ወደ ድሬዳዋ የሚሄዱ ከናንተ ጋር ካልሄድን ብለው ያስቸግራሉ፡፡

   በአንጻሩ ደግሞ ከሀረርጌ ወደ ሌሎች ቦታዎች መጥፋት የሚፈልግ ሰው ለመነሻው ድሬዳዋን ነው የሚመርጣት፡፡ ምክንያቱም በባቡር ወደ ጅቡቲ፣ በአውሮፕላን ወደ አዲስ አበባና ወደ ሌላም ቦታ ሊጠፋ ይችላልና፡፡ የሀገር አቋራጭ አውቶቡስም ቢሆንም በብዛት ከድሬዳዋ ነበር የሚነሳው፡፡ ለዚህ ለዚህ ድሬ በጣም ምቹ ነበረች፡፡

    በዚህ ስሌት መሰረት ነው እንግዲህ ዓሊ ሸቦ ፍቅረኛውን ለማሰስ ወደ ድሬ የወረደው፡፡ ከዚያም ሄዶ ፈለጋት! አስፈለጋት፡፡ የጠረጠራቸውን ቦታዎች ሁሉ ፈተሸ፡፡ ነገር ግን ትርፉ የድሬ ዳዋ ሀሩርና ወበቅ ሆነና አረፈው፡፡ ከዚያስ ወዴት አመራ? እንዲህ ይለናል ዓሊ ሸቦ፡፡

  Jijjiga Hindabartu kharaa Gursum khana (ከጅጅጋስ አታልፍ ከዚያም ከጉርሱም)
  Xuuxxisaa dhagayeetin itti-fufe amna (እያልኩ በጥርጣሬ ተይዤ ብሄድም)
 Way garaa jalalaa laalaa laala gowwomina ( እዩት የኔን ፍቅር ሞኝነቴን ሲያስቀድም)

  አዎን! ልጅቷ ከድሬ ከጠፋች በቀጥታ ወደ ጅጅጋ ልታመራ ትችላለች ብሎ ማሰብ ደግ ነው፡፡ ጅጅጋ የድሬን ያህል ባትሆንም በንግድና በስራ ሰበብ ብዙ ሰው ይጎርፍባታል፡፡ ደግሞም ለሶማሊያ ድንበር ቅርብ ስለሆነች በሀገር ውስጥ መኖር ያስመረረው ሰው ወደርሷ  ይሄድና ለውጪ ጉዞው መንደርደሪያ ያደርጋታል፡፡

   ዓሊ ሸቦም ፍቅረኛው ከሀገሬ ሳትጠፋብኝ ቶሎ ልድረስባት ብሎ  ወደዚያ በማቅናቱ ጥሩ መላ ዘይዷል፡፡ ነገር ግን ትርፉ ድካም ብቻ ሆነበትና ሆደ ባሻነቱን አባባሰበት፡፡ “ለመጽናኛዬ ወደ ጉርሱም ጎራ ብዬ ልፈልጋለት” ቢልም አልተሳካለትም፡፡ ታዲያ እንዲያ ለፍቶ ቢያጣት ጊዜ ምነው አይከፋ? ማልቀስ እንኳ ሲያንሰው ነው! ግን ምን በጀው? ወዴትስ ይሂድ? እንዲህ በማለት ይናገረዋል፡፡

 Kharaa baddaa Khanaa hindhabamtu Laata (ከወደ ደጋው በኩልስ ምናልባት አትጠፋም)
Je’e numan dhaqe ani Gaara Mul’ataa (እያልኩኝ በጉጉት ጋራሙለታ ብወጣም)
Arkuu waa hindandeenyee waan isii fakkaataa (እርሷን የምትመስል ጭራሽ አልታየችም)

 አሁን ዓሊ ሸቦ በአዕምሮው ተደናበረ፡፡ “ምን ይውጠኛል?” ማለትን አመጣ፡፡ ስለዚህ ጀርባውን አዙሮ ሸመጠጠ፡፡ መቼም “ፍቅረኛዬ ከሀረርጌ ውስጥ አትውጣ እንጂ ፈልጌ አላጣትም” ብሎ የለ? ስለዚህ ጀርባውን ሰጥቶ ያለፋቸውን ቦታዎች ማሰስ ነበረበት፡፡ በዚህም መሰረት ነው እንግዲህ ወደ ደጋማው የጋራሙለታ አውራጃ የወጣው፡፡ ነገር ግን በለስ ሊቀናው አልቻለም፡፡ እርሷን የምትመስል ሴት በጭራሽ አልታየችውም፡፡ በመሆኑም ለፍቶ መና ሆኖ ተመለሰ (እርሱ ባይገልጸውም የግራዋ ብርድ በሀይለኛው እንደጠለዘው ይታየኛል)፡፡
    *****  *****  *****
   ዓሊ ትንፋሽ ወስዶ እንደመቆዘም አለ፡፡ ፍቅረኛው የት ገባችበት? ሰማይ ላይ ወጣች? ወይንስ ወደ ምድር ሰረገች? ብቻ አሁንም መንገዱን አላቆመም፡፡ እናም እንዲህ አለ፡፡

Oborraa fi Ciroo hunda kehysa dhaqe (ኦቦራና ጭሮን በአካል አሰስኩት)
Miilaa fi makinaan barbaadeetin dhabe (በእግር በመኪና ሁሉን አዳረስኩት)
Argu koo waa hin oolu je’etin of sobe ( “ጭራሽ አላጣትም” ለሆዴ እያልኩት)

 ከጋራ ሙለታ አውራጃ ያጣትን ፍቅረኛውን ለማግኘት ፍጥነት ጨመረ፡፡ ወደ ምዕራብ ገስግሶ “ኦቦራ” (ወበራ) እና ጭሮን (ጨርጨርን) በፍለጋ አዳረሰ፡፡ ነገር ግን ሊያገኛት አልቻለም፡፡ እንዲያውም እርሷን ሳያገኛት የሀረርጌ ምድር ሊያልቅበት ሆነ፡፡ ቢሆንም ተስፋ አልቆረጠም፡፡ ከዚያስ ምን ተከተለ? እንዲህ በማለት ያስረዳል፡፡

Sa eedaan qalbiin tuni wahayyuma beyti ( ለካስ ይህቺ ቀልቤ የፊቱን ትገምታለች)
Baddeeysa ol kunnaan khate gammachutti (በዴሳን ሳልፈው በደስታ ተብከነከነች)
Jaalalleen tiyya tun intala Habrootii (ፍቅረኛዬ ለካንስ የሀብሮ ልጅ ነች)

    አዎን! ዋናው ተስፋ አለመቁረጥ ነው፡፡ ችግር መከራውን ከታገሱት ያሰቡትን ያሳካሉ፡፡ ተስፋን ይዞ ሲባዝን የከረመው ዓሊ ሸቦም ድካሙን ሁሉ ቻለው፡፡ እናም ከውስጡ የተስፋ እንጥፍጣፊ ሳያልቅ የደስታው መዓዛ አወደው፡፡ ከጭሮ ታጥፎ በዴሳን እልፍ እንዳለ ፍቅረኛው ከሩቅ ሸተተችው፡፡ ለካስ ውቃቢው ነው ዝም ብሎ ፈልግ ያሰኘው እንጂ ልጅቱ ቀድሞውንም ቢሆን አልጠፋችበትም? እንደተፈጠረች እትብቷ ከተቀበረባት ቦታ ሆና ትጠብቀው ነበር፡፡ “የት?” ብትሉ “ሀብሮ” ነው መልሱ!

  የዓሊ ሸቦ ፍቅረኛ የሀብሮ ልጅ ሆና ተገኘች፡፡ ታዲያ “ሀብሮ” ሰፊ አውራጃ ነው እንጂ አንድ ከተማ ወይንም መንደር አይደለም፡፡ ከቁኒ እስከ ባሌ ጠረፍ ድረስ ያለው ተራራማ ምድር ሁሉ የሚካተትበት ክልል ነው፡፡ ስለዚህ የልጅቱ ትክክለኛ አድራሻ መታወቅ አለበት፡፡ ዓሊ ሸቦ የመጨረሻውን ውጤት እንዲህ በማለት ያበስረናል፡፡

 Jaalallen gar meeqaan barbaadaan of rakkee (ስንት ሀገር በፍለጋ ያዳረስኩላት ፍቅረኛዬን)
Tanin deemee dhabe baakkan itti shakkee (ከሁሉም ቦታዎች ያጣኋት ጉብልዬን)
 Walkkaa magaalaa Galamsottiin arke (ገለምሶ መሀል ላይ አገኘኋት ወዳጄን)

 እንዲህ ነው ዓሊ ሸቦ! ብራቮ ዓሊ ሸቦ! እርሱ ከቆላ ደጋ የተንከራተተላት ጉብል የገለምሶ ልጅ ሆና ተገኘች! የወንዜ ልጅ! ግዳዩም በድል ተጠናቀቀ! ዓሌ ሸቦ በሐሴት ባህር ዋኘ፡፡ ነፍሲያውም በደስታ ረካች! በመጨረሻም ዓሊ እንዲህ አለና አጠቃለለ፡፡

 Arkadhe qal’o too diimtuu too bareedduu (አገኘሁ የኔን አለንጋ ያላት የደስ ደስ)
Isii barnootarra kharaa gala deemtu (ከትምህርት ቤት ወደ ቤቷ ስትመለስ)
 Gamdeen bahaa mee ree dheebuu tootuu (ዛሬ ጥማቴን ልወጣው የልቤ እንዲደርስ)

    *****  *****  *****
አንድ የሚነደኝ ነገር ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? በሸዋ ከተሞች (አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ቢሾፍቱ ወዘተ..) “የገለምሶ ልጅ ነኝ” ከተባለ በሳቅ የሚያውካኩ ሰዎች አሉ፡፡ ምክንያቱ ለምን ይመስላችኋል? አንዳንድ “ውሪ ውሪ” ነጋዴዎች የከተማዬን ስም ከዚያ ዘመነኛ “ቅጠል” ጋር በማያያዛቸው ነው፡፡ በመሆኑም ገለምሶ ሲባል ብዙዎቹ የሚታያቸው ያ ጫት የሚባለው “ጨረንጉላ” ቅጠል ነው፡፡ ደግሞ እኮ የሚያሳዝነው ቅጠሉ ከዚያ አይደለም የሚጫነው፡፡ አብዛኛው “ከራ ዱለቻ”፤ “ዴፎ”፣ “ቢዮ”፤ “ሚሊሎ” እና “ዳሎ” ከሚባሉ ትንንሽ የገጠር ከተሞች ነው የሚጫነው፡፡ ነጋዴዎቹ ጫቱ “ዳሎ” ወይንም “ሚሊሎ” ቢባል የማይታወቅ ሰለመሰላቸው ነው በከተማዬ ስም የጠሩት፡፡ እነዚህ ከይሲዎች! ጂንኒ ጀቡቲ ሁላ!

 እርግጥ ጫት በገለምሶም አለ፡፡ ግን ብዙዎች እንደሚያስቡት ገለምሶ በጫት የናወዘች ከተማ አይደለችም፡፡ የዛሬን አያድርገውና ዓሊ ሸቦን እንዲህ በፍለጋ ያንከራተተች “ቀሽቲ” ከተማ ነበረች፡፡ በሀረርጌ ምድር ከሀረርና ከጉርሱም (ፉኛን ቢራ) በስተቀር በእድሜ የሚቀድማት ከተማ የለም፡፡ አሁን እነ “በዘበዛ” አደከሟት እንጂ፡፡ ግድ የለም! አንድ ቀን ትነሳለች፡፡ አንድ ቀን ገለምሶም፣ ሀረርም፤ ድሬዳዋም፣ አዲስ አበባም፣ ኢትዮጵያም ሁሉም ይነሳሉ፡፡ ዋናው ተስፋ አለመቁረጥ ነው፡፡ 
    *****  *****  *****
አሁን ወደ ወጋችን እንመለስ፡፡

  ዓሊ ሸቦ እንዴት ይህንን ዘፈን ሊዘፍን ቻለ? ከጀርባው ታሪክ አለው፡፡ መሐመድ አሕመድ (መሐመድ ቆጴ) የሚባል የዚያ ዘመን ታዋቂ ጋዜጠኛ የከተማችንን ጉብል ወደዳት፡፡ ሆኖም ፍቅሩ በምን ይውጣለት? በምን ያቅርባት?
  ምናልባት በዘፈን ብጠራት እሺ ትለኝ ይሆናል ብሎ ይህንን ድርሰት ጻፈላት፡፡ ዓሊ ሸቦም ተጫወተው፡፡ ግን ልጅቷና መሐመድ ቆጴ ለጥቂት ተላለፉ፡፡ መሐመድ በዘመኑ ደንብ መሰረት የልጅቷን ቤተሰቦች ለጋብቻ ሊጠይቃቸው ሲሰናዳ አንድ የአዲስ አበባ ሰው ቀደመውና ወሰዳት፡፡ ግን ገለምሶና የዓሊ ሸቦ ዘፈን እንደተጣመሩ ቀሩ፡፡

በመጨረሻም!
የዘፈኑን ግጥሞች በደንብ አያችኋቸው?… ሁሉም ባለ ሶስት መስመር ናቸው… በዚያ ዘመን በአማርኛም ሆነ በኦሮምኛ እንደዚህ ይገጠም ነበር፡፡ የዚያ ዘመን ደራሲዎች እንዲህ እየደረሱ ሰውን አጃዒብ ያስብሉ ነበር፡፡ ይህም ዘፈን የመሐመድ ቆጴን ችሎታ ካገነኑት ስራዎች መካከል አንዱ ሆኖ እስከ አሁን ድረስ ይዘከራል፡፡
   በነገራችን ላይ ሙሐመድ ቆጴን አወቃችሁት? ሐመልማል አባተ የምትዘፍናቸውን የኦሮምኛ ዘፈኖች በሙሉ የገጠመው ደራሲ ነው፡፡ መሐመድ አሁንም በህይወት አለ፡፡
----
አፈንዲ ሙተቂ
መስከረም 3/2006
 
Afendi Muteki is a researcher of ethnography and history of the peoples of east Ethiopia. He is an author of “Harar Gey”, an ethnography book about the historical city of Harar. You can read some of his articles on his facebook page and his blog.