Wednesday, August 28, 2013

ዓሊ ቢራ፣ የሸዋሉል መንግሥቱ እና “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ”


ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-------
ዛሬ ስለምን የማወጋችሁ ይመስላችኋል? ስለ“ፈስ” ነው የምንጨዋወተው፡፡ አዎን ስለ “ፈስ” ነው! ስለርሱ መጻፍ አይቻልም እንዴ? ስለርሱ ብንወያይ ነውረኛ እንሆናለን? የፈለጋችሁን በሉኝ! ስለ “ፈስ” ልጽፍ አሐዱ ብያለሁ፡፡ የጀመርኩትንም ሳልጨርስ አላቆመም፡፡
  
  ደግነቱ ስለሚገማ “ፈስ” አይደለም የማወጋችሁ (ስለዚህ አፍንጫችሁን አትያዙ! ቂቂቂቂቂ….)፡፡ ስለማይገማ “ፈስ” ነው የምጽፍላችሁ፡፡ እንዲያውም ይህ “ፈስ” ባለመልካም መዓዛ ነው፡፡ ሽታው እንደ ሉባንጃ (ሊባንጃው) እና እንደ “ሊባን ፎህ” መዓዛ ያውዳል፡፡
  
   ወዳጆቼ! እየዘባረቅኩኝ አይደለም፡፡ እውነት ነው፡፡ መዓዛው እንደ “እጣን” የሚያውድ ፈስ አለ፡፡ እንዲህ አይነቱን “ፈስ” የሚለቅ ሰው የሚበላው ምግብ በ“ቱራበል ሚስክ” የታሸ፣ በ“አንበር” የዋጀ፣ የፓሪስ ሽቶ የተርከፈከፈበት ወዘተ… ሳይሆን ይቀራል ግን?    
   
   ምንም አትጠራጠሩ! መዓዛማውን “ፈስ” የሚለቀው ሰውዬ እንደኛው ዓይነት ምግብ ነው የሚበላው፡፡ እንደኛው ውሃ ነው የሚጠጣው፡፡ እንደኛው አትክልትና ፍራፍሬ ይመገባል፡፡ ታዲያ “ፈሱ”ን ባለመዓዛ የሚያደርገው ምን ይሆን? እስቲ አብረን እንየው፡፡
  *****  *****  *****
  መለያየት ህመም ነው፡፡ ትልቅ ስቃይ ነው፡፡ ከምትወዱት ወዳጅና ዘመድ መለየት ደግሞ የሞት ታናሽ ወንድም ነው፡፡ አብሮ አደግ ጓደኛችሁን ወይም የምትወዱትን የቤት እመቤታችሁን በህይወት እያላችሁ ከተለያችኋቸው ስቃይና መከራው በቁም ይገድላችኋል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን ወዳጆችና ዘመዶቻችሁን በምን ቋንቋ ነው የምትገልጹት? በሌላ አነጋገር ለርሱ/ለርሷ ያላችሁን ገደብ የለሽ ፍቅር እንዴት ብላችሁ ነው የምታስረዱት?፡
   
   የናንተን እንጃ! ለዚህ ጽሑፍ መሰረት የሆነውን ትውፊት ያፈለቁት የሀረርጌ ኦሮሞ ልጃገረዶች ግን ለእኩያቸው ያላቸውን ፍቅር ሲገልጹ “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” ነው የሚሉት፡፡ ምን ማለት መሰላችሁ? “ውዴ/ጓዴ! አንቺ ባለእጣን መዓዛ ፈስ” እንደማለት ነው፡፡ በሙሉ ዐረፍተ ነገር ሲጻፍ ደግሞ “አንቺ የኔ ውድ ጓደኛዬ፣ እህቴ፣ ነፍሴ! ሌላው ቆርቶ ፈስሽ እኮ ለኔ እንደ እጣን ነው” እንደማለት ይሆናል፡፡
   
    ጥቅሉን ሐረግ ስንዝረዝረው ፍቺው የትየለሌ ነው የሚሆንብን፡፡ ለአሁኑ ግን “የኔ ውድ ባልንጀራዬ! አንቺ አብሮ አደጌ! የኔና ያንቺ መውደድ እኮ ገደብ የለውም፡፡ የመውደዳችን ጥልቀት ጥላቻን ከመሀከላችን ሰርዞታል፡፡ ሌላው ነገር ይቅርና ሰዎች ይገማል ብለው አፍንጫቸውን የሚይዙለት “ፈስ” በኔና ባንቺ መሀል ቢከሰት እንደ ሽቶና እንደ እጣን ነው የምንቆጥረው፤ ፍቅሬ! ሄዴ! ውዴ! እወድሻለሁ…” ወዘተ… እያልን ልንፈስረው (ልንፈታው) እንችላለን፡፡

   “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” እያሉ ለጓደኛቸው ፍቅራቸውን የሚገልጹት የሀረርጌ ኦሮሞ ኮረዳዎች ናቸው- ከላይ እንደገለጽኩት፡፡ ይሁንና ኮረዳዎቹ በ“ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” አንጀቱን የሚበሉትና ልቡን የሚያብሰለስሉት ሰው ወንድ አይደለም፡፡ ሴት አብሮ አደግ  ጓደኛቸውን ነው እንዲህ የሚፈታተኑት፡፡ ይህን ግን ለሁልጊዜ እንዳይመስላችሁ፡፡ ለአንድ ቀን ብቻ የሚቆይ ትእይንት ነው፡፡ ይኸውም ባልንጀራቸው በምታገባበት ዕለት ነው፡፡
  
  በዚህ ዕለት ጓደኛቸው ከነርሱ ተነጥላ ከባሏ ጋር መኖር ትጀምራለች፡፡ በዚህ ዕለት በልጅነቷ አብሯት አፈር እየፈጩ የተጫወቱ፣ ወንዝ ሄደው ውሃ የቀዱ፣ ጋራ ወጥተው እንጨት የቆረጡና በታዛ ስር ስፌድ የሰፉ ጓደኞቿን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ትሰናበታለች፡፡ “የእገሌ ልጅ” መባሏ ቀርቶ “የእገሌ ሚስት” እየተባለች መጠራት ትጀምራለች፡፡ ጓደኞቿም ከርሷ ጋር እንዳሻቸው የሚሆኑበት እድል ለወደፊቱ ተመልሶ እንደማይመጣ የሚያረጋግጡት በዚህ እለት ነው፡፡ ስለዚህ በዚህች ታሪካዊ ዕለት የመልካሙን ጊዜ ፍጻሜ  እያማረሩ በእንባ ይሸኟታል፡፡ እነዚህ ኮረዳዎች ለጓደኛቸው የነበራቸውን ፍቅር ለመግለጽና የወዳጅነታቸውን ግዝፈት ለማሳየት ከ“ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” የተሻለ ሐረግ የላቸውም፡፡ ይህንን ሐረግ እየደጋገሙ በመምዘዝ “በኔና ባንቺ መሀል መጥፎ ነገር የለም፤ አለ ቢባል እንኳ እኔ ሁሉንም በጎ አድርጌ ነው የምመለከተው” እያሉ ይሰናበቷታል፡፡ 
 
*****  *****  *****
እዚህ ዘንድ አንድ አስገራሚ ነገር ላጫውታችሁ፡፡

“ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” የኦሮምኛ ሐረግ ነው ብያችኋለሁ፡፡ በቀጥተኛ አገላለጽ “ያንቺ ፈስ ለኔ እንደ እጣን ነው እኮ” የሚል ፍቺ እንዳለውም ተናግሬአለሁ፡፡ ታዲያ “በኦሮሞ ባህል እንዲህ ተብሎ ይዘፈናልን?” የሚል ጥያቄ ሊቀርብልኝ ይችላል፡፡ መልሱ “አይቻልም” ነው፡፡ በአማርኛው ዘይቤ “ፈስ መጣብኝ” ወይንም “ፈሴን ለቀቅኩት” የሚሉት አነጋገሮች “ነውር” ተደርገው እንደሚታዩት ሁሉ በኦሮሞ ባህልም “ፈሴን ፈሳሁት” የሚለው አነጋገር የጨዋ ደንብ አይደለም፡፡ የኦሮሞ ባህል እንዲህ አይነቱን ንግግር “ሰፉ” (taboo) ይለዋል፡፡ “ሰፉ” የሆነ አነጋገር ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ቀርቶ በቤት እንኳ ይከለከላል፡፡ ይሁንና የሀረርጌ ኮረዶች በግልጽ “ሐደሶ ሊባነታ” እያሉ ይዘፍናሉ! ለዚያውም በሰርግ ቤት!! ማን ፈቅዶላቸው ነው ግን?
    
   ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ኮረዶቹ (ልጃገረዶቹ) የተጠቀሙበት ቃል የኦሮምኛው “ዹፉ” አይደለም (በአማርኛ “ፈስ” ማለት ነው፤ “መፍሳት” ማለትም ይሆናል)፡፡ “ፈስ”ን ለመግለጽ የገባው ቃል የዐረብኛው “ሐደስ” ነው፡፡ በሀረርጌ ኦሮሞ ባህል በህዝብ ፊት ወይንም በአደባባይ ቢጠሩ እንደ ነውር የሚቆጠሩ ነገሮችን ሳንሸማቀቅ ለመግለጽ ከፈለግን በዐረብኛ ስማቸው ነው የምንጠራቸው፡፡ ለምሳሌ “የወንድ ብልት” ለማለት ካሻን “ዘከር” እንላለን፡፡ የሴት ብልትንም “ሐሸፋ” ብለን ብንጠራው እንደ ነውር አይቆጠርብንም፡፡ ሽንት ቤት ለማለትም “ኸላ” ማለት ይቻላል፡፡ ሰገራንም በኦሮምኛ ስሙ ሳይሆን በዐረብኛው ስም “ቦውሊ” በማለት እንጠራዋለን፡፡ (የባውሎጂ አስተማሪዎቻችን የሰው ልጅ የመራቢያ አካላትን በአማርኛ ለመግለጽ እያፈሩ፤ በእንግሊዝኛ ግን ያለምንም ፍርሃት “Penis”, “Vagina”, “Urethra”, “Testicle”, እያሉ የሚጠሩበትን ብሂል አስታውሱ)፡፡

 *****  *****  *****
  ወደ “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” እንመለስ፡፡ “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” አንድ ሐረግ ብቻ ነው ያለው፡፡ ነገር ግን በሰርግ ቤት “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” ብቻውን አይባልም፡፡ እርሱን የሚያጅቡ ሌሎች ግጥሞች ታክለውበት በቡድን የሚዘፈን ዜማ ሆኗል፡፡
    
“ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” እያሉ መዝፈኑን ማን እንደጀመረው አይታወቅም፡፡ የዘፈኑ ግጥሞችም ከቦታ ቦታ ይለያያሉ፡፡ ዜማውም ሊለያይ ይችላል፡፡ ነገር ግን አዝማቹ ምንጊዜም ቢሆን አንድ አይነት ነው፡፡ እርሱም ባለሁለት መስመር ነው፡፡ እንዲህ ይሄዳል፡፡

    “ዮቢ ዮቢ ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ
     ወይ ነገየቲ ናን ጄኢ ሂሪዮ አማነታ”

     ግጥሙን ከነነፍሱ ወደ አማርኛ መመለስ በጣም ይከብዳል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ሊባል ይችላል፡፡
 
“ውዴ ጓዴ የሌለብሽ እንከን
  ያንቺ “ሐደስ” እኮ ነው የኔ እጣን
 ደህና ሁኚ በይኝ ውዴ አደራሽን”
 (“ሐደስ”ን ሳንፈታው እንዳለ ብንወስደው ይሻላል)

ይህ ምትሐታዊው “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” በሀረርጌ ገጠሮች ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡ እጅግ ውብ ጣዕም ባለው ዜማ ተቀምሮ ለኢትዮጵያ ህዝብ በካሴት ቀርቧል፡፡ ለዚያውም ከ30 ዓመታት በፊት! የሚገርመው ታዲያ ያኔ “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” እያለ የዘፈነው ሴት አይደለም፡፡ አንጋፋው አርቲስት ዶ/ር ዓሊ ቢራ ነው! ይህ ትንግርት እንዴት ሊፈጠር ቻለ?
    
    መልሱን ለማወቅ ካሻችሁ ከሁለት ቀናት በፊት (ሰኞ ነሐሴ 19/2005) በጻፍኩት ጽሑፍ ስራዋን በመጠኑ ያስተዋወቅኳችሁን ጋዜጠኛና ደራሲ የሸዋሉል መንግሥቱን የግዴታ ማንሳት ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ”ን ዓሊ ቢራ በዘፈነው መልኩ አቀናብራ ዘፈን እንዲሆን ያደረገችው እርሷ ናትና!
 
   የሸዋሉል መንግሥቱ የሀረርጌ ተወላጅ ናት፡፡ በምስራቁ የኦሮሞ ባህል ውስጥ ነው ያደገችው፡፡ በሀረርጌ ገጠሮች ሴቶች “ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ”ን ሲዘፍኑ አይታለች፡፡ እነዚያ ኮረዳዎች ጓደኛቸው በትዳር ስትለያቸው “እስከ ወዲያኛው ተለያየን” እያሉ በእንባ እንደሚሸኟት ታውቃለች፡፡ ዘፈኑን ለዓሊ ቢራ የሰጠችበትን መነሻ ለጊዜው በትክክል ባናውቀውም ድርሰቱን ስትጽፈው የነዚያ ኮረዳዎች እንባ እየታያትና የመለያየትን ክፉ እጣ እያሰበች እንደሆነ ለመረዳት አይከብደንም፡፡ በዚህም የመለያየትን አስከፊነት በሚገባ ለመግለጽ ችላለች፡፡ ለዚህ ቀላሉ አብነት በዘፈኑ ግጥም ውስጥ የሚታየው የእንጉርጉሮ ሀቅታና የሐዘን ድባብ ነው፡፡ እስቲ ሙሉ ግጥሙን ከአማርኛው ትርጉም ጋር ልጻፍላችሁ (በነገራችን ላይ የሸዋሉል ባለ ሁለት መስመሩን አዝማች ይበልጥ በማስፋት ባለ አራት መስመር አድርገዋለች፤ ስለዚህ ቀጥዬ የምጽፍላችሁ ባህላዊውን ግጥም ሳይሆን እርሷ የጻፈችውን ባለ አራት መስመሩን ግጥም ነው)፡፡
--------
አዝማቹ

Way yoobi yoobi yoobi hadasoo libaanta (ውዴ ጓዴ ባለ መዓዛማው “ሐደስ”)
Way yoobi yoobi bal’oo hiriyoo imaanta (ውዴ ጓዴ አደራችን አይገሰስ)
Wa nagayatti nan je’i hiriyoo ta dhaammata (እስቲ ለስንብትሽ ደህና ሁን በይኝ)
Way eenyu eenyu eenyu hiriyoo nayaadata  (አንቺ ከሄድሽማ ማን ነው የሚያስታውሰኝ)
Hiriyoo nagaafata (ማን ነው የሚጠይቀኝ)
----------
Guyyaan naaf hindhihu halkan naaf hinbarihu (አይነጋልኝም ሌቱ ቀኑም አይመሽልኝ)
Koottu mee yaa boontuu simalee naaf hintahu (እስቲ ነይ የኔ ውድ ያላንቺም አይሆንልኝ)
Si laalu si hin’argu siyaamu hin awwaatu (በዐይኔ አላይሽም ብጠራሽም አትሰሚኝ)
Naduraa fagaatte iddoon ati jirtu (ያለሽበት ቦታ እንደዚህ ርቆኝ)
Osonin si eegu nin seena ninbaha (አንቺን እያየሁ እገባና እወጣለሁ)
Yaadni kee narakke ani akkamin taha (ናፍቆትሽ አስጨነቀኝ እንዴት ነው የምሆነው?)
   
 *****  *****  *****
ዓሊ ቢራ ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 የቅዳሜ ጨዋታ ፕሮግራም ከመዓዛ ብሩ ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ ስለዘፈኑና ስለደራሲዋ ማውሳቱ ትዝ ይለኛል፡፡ ነገር ግን ያኔ እርሱ የጠቀሳት የግጥሙ ደራሲ የሸዋሉል መንግሥቱ መሆኗን ልብ አላልኩትም፡፡ ነገሩን በቅርብ ጊዜ ባደረግኩት ምርመራ ነው የደረስኩበት፡፡ ያቺ ውድ ደራሲና ጋዜጠኛ ከዓሊ ቢራ ጋር ብቻ ሳይሆን ከበርካቶች ጋር በመሆን ዘመን አይሽሬ የጥበብ ስራዎችን ሰርታለች፡፡ ይሁንና በዘመነ ቀይ ሽብር የመኢሶን አባል ሆና በመገኘቷ የጥይት እራት ሆነች፡፡ የርሷን ሞት ተከትሎ የተነዛው የአንድ ወገን ወሬም የጥበብ ስራዋን ሸፈነው፡፡ ይህ ትውልድ ግን ለጥበብ ውሎዋ ተገቢውን እውቅና የመስጠት ሀገራዊ ግዴታ አለበት፡፡ ስራዋን ማውሳትና ድንቅ ብዕሯን ማወደስ አለበት፡፡ እንደዚያ ካደረግን የዛሬዎቹ ጠቢባንም ለነገው መዘክራቸው ዋስትና አገኙ ማለት ነው፡፡ ታሪክም ትክክለኛ ሚናውን የሚጫወተው ያኔ ነው፡፡ 
------

አሁን አበቃሁ፡፡ ከላይ በመግቢያዬ ስለዚያ ነገር (“ፈስ”) ሳወራ አብሽቄአችሁ ከሆነ በይቅርታ እለፉኝ፡፡ ግን እኮ አጨራረሴ ጥሩ ነው! አይደለም እንዴ? ጥሩ ነው ካላችሁ ይሁን! ጥሩ ካልሆነም ለወደፊቱ እናሻሽላለን፡፡

 ለማንኛውም በወዳጅነታችን እንሰንብት!  
 አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 22/2005

Sunday, August 25, 2013

“የሸዋሉል መንግሥቱ” እና የጥላሁን ገሠሠ “Akkam Nagumaa”




ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----------
   አሁንም ወደ ዘፈን ልወስዳችሁ ነው፡፡ ስለወጋየው ደግነቱ “አርኬ ሁማ” ሳወጋችሁ እንደተናገርኩት በአንድ ዘመን በኢትዮጵያ ደራሲያን ሲጻፉ የነበሩት ዘፈኖች “ዘፈን” ተብለው ብቻ የሚታለፉ አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ በመልዕክታቸው ሀያልነት፤ ከፊሎቹ ደግሞ በዜማና ግጥማቸው ህብርነትና የረቀቀ መስተጋብር ዘመን አይሽሬ የሚባሉ ዓይነት ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ በሁለተኛው ዘርፍ ከሚመደቡት ዘመን አይሽሬ ዘፈኖች መካከል አንዱን አስቃኛችኋለሁ፡፡
   ዘፈኑ “አከም ነጉማ” ይሰኛል፡፡ ታዲያ ይህንን ዘፈን “ዘፈን” በመሆኑ ብቻ ልዳስሰው የተነሳሁ እንዳይመስላችሁ፡፡ ከጀርባው ያለውን አስገራሚ ታሪክ ላካፍላችሁ በመሻቴ ነው ለቅኝቴ የመረጥኩት (እንጂ እኔ በበኩሌ በአሁኑ ጊዜ ለዘፈን ብዙም “ሀጃ” የለኝም)፡፡
  *****  *****  *****
   የዘፈኑ ርዕስ “Akkam Nagumaa” ነው-ከላይ እንደገለጽኩት፡፡ በኦሮምኛ “እንዴት ነሽ ሰላም ነሽ” እንደማለት ነው፡፡ ዘፋኙ አንጋፋው ኮከብ ጥላሁን ገሠሠ ነው፡፡ በኔ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያላችሁ ሰዎች  (ከ30 ዓመት በላይ የሆናችሁ) ዘፈኑን በደንብ እንደምታስታውሱት ይታወቀኛል፡፡ ከኔ የምታንሱትም ብትሆኑ ጥላሁን በ1987 በለቀቀው አልበም ውስጥ በድጋሚ በዘፈነው ጊዜ እንደ አዲስ አጣጥማችሁታል (ለዘፈን ባይተዋር ካልሆናችሁ በቀር)፡፡
   “አከም ነጉማ” የፍቅር ዘፈን ነው፡፡ ጥላሁን ከአጠገቡ የተለየችውን አፍቃሪውን ነው “እንዴት ነሽ? ነሽ አማን ነሽ?” እያለ የሩቅ ሰላምታ የሚያቀርብላት፡፡ በዘፈኑ ውስጥ በናፍቆት ብስልስል ብሎ እንደተቃጠለላት ያወሳል፡፡ “እንቅልፍ አጥቻለሁ ቶሎ ነይልኝ” እያለም ይለማምናታል፡፡ እስቲ የዘፈኑን ግጥም ከአማርኛ ትርጓሜው ጋር ልጋብዛችሁ (ቃል በቃል ለመፍታት ቢከብድም እንደሚሆን አድርጌ ጽፌዋለሁ)፡፡
------
አዝማቹ
Akkam nagumaa Fayyuumaa (እንዴት? ነሽ አማን ነሽ? ደህና ነሽልኝ?)
Hiriyaa hinqabuu kophumaa (ሌላ ጓደኛ የለኝም እኔ ብቻዬን ነኝ)
Dhuftee na laaltus gaarumaa (እጅግ መልካም ነበር መጥተሸ ብታይኝ)
Akkam nagumaa fayyumaa (እንዴት? ነሽ አማን ነሽ? ደህና ነሽልኝ?)
----------
Eessattin si arga garamin harkisaa (የት ነው የማገኝሽ ወዴትስ ልጓዘው?)
Mee nama naaf dhaami bakki jirtu eessa (እስቲ ሰው ላኪብኝ ቦታሽን ልወቀው)  
Yaa damme yaa dammee yaa dammee bulbulaa (የኔ ማር የኔ ማር የኔ ወለላ ማር )
Ani hirriiba dhabe suman yaadaa bulaa (እንቅልፍ አጥቻለሁ ካንቺ ሓሳብ በቀር የለኝም አዳር)
---------
Namni na ilaalee karaa na ceesisaa (ሰዎች ያዩኝና መንገድ ያሻግሩኛል)
Gidiraan jaalalaa sihi na feesisaa (የፍቅር ውቃቢው አንቺን ያሰኘኛል)
Garaan nurakinnaan sabbataan hidhannee (ሆድ ቢያስቸግር እንኳ በመቀነት ያስሩታል)
Ijaa ammo akkam goona tan ilaaltee hin obsine (አይታ የማትታገሰውን ዐይን በምን ያባብሏታል?)
--------
Bakka ati jirtu qalbiin koo na yaadee (ያለሽበትን ቦታ በልቤ እያሰብኩት)
Numan ciisa malee hirriibni na dide (ተጋደምኩት እንጂ ምኑን ነው የተኛሁት) 
Nagaatti, nagaatti nagaatti jiraadhu (በሰላም በአማን በደህና ኑሪልኝ)
Guyyaa tokko dhufee hamman sidhungadhuu (አንድ ቀን መጥቼ ስሜሽ እስኪወጣልኝ)
------
ዘፈኑን ከነዜማው መስማት የሚፈልግ ካለ ይህንን የዩቲዩብ ሊንክ ይከተል፡፡
http://www.youtube.com/watch?v=QNfu_1TEQXk
------
  ይህ “አከም ነጉማ” የተሰኘው ዘፈን “የጠላሽ ይጠላ ብድሩ ይድረሰው” በሚለው የጥላሁን አልበም ላይ ነው የሚገኘው፡፡ በካሴት የታተመበት ጊዜ በ1973/1974 ይመስለኛል፡፡ ዘፈኑ በተለቀቀበት ጊዜ በሙዚቃ ያጀበውን ባንድ የማህሙድ አህመድን “እንቺ ልቤ እኮ ነው-ስንቅሽ ይሁን ያዥው” ያጀበው ባንድ እንደሆነ በትክክል ያስታውቃል፡፡ በመሆኑም ባንዱ በዘመኑ ገናና የነበረው አይቤክስ ባንድ ነው ማለት ነው፡፡ ዘፈኑ በ1973/74 ቢለቀቅም እስከ ሰማኒያዎቹ መግቢያ ድረስ ይሰማ ነበር፡፡ እኔም እርሱን በደንብ ለመስማት የታደልኩት በዚሁ ምክንያት ነው፡፡

 “አከም ነጉማ”ን በፊት ሳውቀው እንደ ማንም ተራ ዘፈን ነበር የምመለከተው፡፡ ክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ ባረፈበት ዕለት የአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ የኦሮምኛ ፕሮግራም ለቃለ-ምልልስ የጋበዘው አርቲስት ዶ/ር ዓሊ ቢራ “ከጥላሁን ዜማዎች መካከል የትኛውን ታስበልጣለህ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦለት “አከም ነጉማ” የሚል ምላሽ ከሰጠ በኋላ ግን በስስት ዐይን አየው ጀመር፡፡ ይሁንና ዘፈኑን ጠለቅ ብዬ የመመርመርና እንደ ቅርስ የማየት አባዜ የመጣብኝ ባለፈው የመስከረም ወር ነው፡፡
    
   በወቅቱ (መስከረም/2005) ዩቲዩብ በሚባለው ዝነኛ የኢንተርኔት ቻናል ቆየት ያሉ ቪዲዮዎችን እበረብር ነበር፡፡ በተለይ በዚያ ወር የኮሎኔል መንግሥቱን መጽሐፍ አንብቤ ስለነበረ የሳቸውን ንግግሮች የያዙ ቪዲዮዎችን ዳውንሎድ ለማድረግ ከፍተኛ ፍተሻ አደርግ ነበር፡፡ ታዲያ በመንጌ ቪዲዮዎች መካከል በተሸጎጠ አንድ ፋይል ላይ “Tilahun Gessesse’s Akkam Neguma” የሚል ርዕስ በማየቴ ተደነቅኩና ከፈትኩት፡፡ ዘፈኑን ከመስማቴ በፊት ግን ስለዘፈኑ በተጻፈ መጠነኛ ማብራሪያ ውስጥ “Written by Yeshewalul Mengistu”  የሚል ሐረግ ታየኝና አድናቆቴ ይበልጥ ጨመረ፡፡ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ይህንን መረጃ ባለማወቄም በእጅጉ አዘንኩ፡፡
  *****  *****  *****
   ይገርማል! ታሪካችን ይገርማል! የታሪክ አጻጻፋችንም ይገርማል፡፡ የምንጠላውን ሰው የሰይጣን ቁራጭ እያደረግን የአጋንንት መልክና የጋንጩር ቁመና እንሰጠዋለን፡፡ የምንወደውንም ሰው የመንግሥተ ሰማያት ሙሽራ እናስመስለውና ከመላእክት ተርታ እናሰልፈዋለን፡፡ በዚህ መሀል መታወቅ የነበረበት ሐቅ ይደበቅና አድናቆትና ጥላቻ የታሪክ አጸቆች ሆነው ቁጭ ይላሉ፡፡ ይሁንና ዛሬ የተደበቀው ሐቅ ትክክለኛ ጊዜውን ጠብቆ አንገቱን ቀና ያደርጋል፡፡ ያኔ ተረትን በታሪክ ቦታ ያነገሡ የጥላቻ ደቀ-መዛሙርት አንገታቸውን ይደፋሉ፡፡ እውነት ኮራ ብላ መራመድ ትጀምራለች፡፡፡፡

   “አከም ነጉማ”ን በውብ ብዕሩ ከሽኖ ለሀገር ቅርስነት ያበቃው ደራሲም የነዚህ የጥላቻ ደቀ-መዛሙርት የጥቃት ሰለባ ሆኖ ታሪኩ ሲበላሽበት ኖሯል፡፡ ሀገርና ትውልድ ሲያጠፋ እንጂ ለሀገር አንዳች ጠቃሚ ነገር ጠብ እንዳላደረገ ሲጻፍበት ሰንብቷል፡፡ ሆኖም በአንድ ወቅት የተነሳው የጥላቻ አቧራ ብንን ብሎ ሲጠፋለት ደራሲው እጅግ መልካም የሆኑ ቁምነገሮች እንደነበሩት ታሪክ ይመሰክርለት ይዟል፡፡ የዚያ ደራሲ ስም የሸዋሉል መንግሥቱ ይባላል፡፡ ደራሲውን በወንዴ ጾታ ስጠራው ግን ወንድ እንዳይመስላችሁ፡፡ “ሴት” ናት፡፡ 

 “የሸዋሉል መንግሥቱ” የሚለውን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት “አጥፍቶ መጥፋት” በሚለው የሙሉጌታ ሉሌ ድርሰት ውስጥ ይመስለኛል፡፡ በማስከተልም በባቢሌ ቶላ “የትውልድ እልቂት”፣ በክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” እና በሌሎችም ኢህአፓ-ቀመስ ድርሰቶች.. ውስጥ ስሙን አይቼዋለሁ፡፡ በዚህ ስም የምትጠራው ሴት በየመጻሕፍቱ ውስጥ ጨካኝ፣ አረመኔ፣ ገዳይ፣ ገራፊ፣ ዘራፊ፣ ለወጣት የማትራራ ወዘተ… በሚሉ ቃላት ተገልጻለች፡፡ በተለይ አንደኛው መጽሐፍ “እንደ ወንድ የታጠቀ ስኳድ እየመራች ከየቤቱ ወጣቶችን እያደነች የምትገድልና የምትገርፍ የሴት አረመኔ” ብሎ እንደገለጻት እስከ አሁን ድረስ ይታወሰኛል (በዚያ ዘመን ካለርሷ በስተቀር እንዲያ አይነት ጭካኔ የፈጸመች ሴት አልነበረችም ለማለት ይመስላል)፡፡

  የሸዋሉል የኖረችው በዘመነ ቀይ ሽብር ነው-ከአያያዜ እንደምትረዱት፡፡ ይህቺ ሴት በ1969/1970 በኢህአፓ ገዳይ ስኳዶች “ሰባራ ባቡር” በሚባለው ሰፈር ከነበረው ቤቷ በራፍ ላይ ተገድላለች፡፡ ኢህአፓዎች የግድያዋን ምክንያት ሲያስረዱ “በንጹሐን ደም እጇን ያጨቀየች ቀንደኛ የመኢሶን ገራፊ እና የገዳይ ጓድ መሪ ነበረች” ነው የሚሉት፡፡ ሴትዮዋ የኢትዮጵያ ሬድዮ ጋዜጠኛ እና የፕሮግራም መሪ ሆና ሳለ እንዲያ ዓይነት ወራዳ ተግባር ውስጥ የገባችበትን ምክንያት በትክክል መረዳት ቢከብደኝም በኢህአፓ አባላትና ደጋፊዎች የተጻፈውን ገለጻ የማስተባብልበት መንገድ ስላልነበረኝ “ታሪኩ እውነት ነው” በማለት ተቀብየው ኖሬአለሁ፡፡ ስለርሷ በጎውን የሚናገሩ ጽሁፎችንና ቃለ ምልልሶችን አልፎ አልፎ ባነብም ሙያዋንና ችሎታዋን በዝርዝር ያስረዳኝ ሰው ስላልነበር በጨካኝነቷና በገራፊነቷ መዝግቤአት ቆይቻለሁ፡፡ “የአከም ነጉማ” ደራሲ እርሷ መሆኗን ከተረዳሁበት ዕለት ጀምሮ ግን አቋሜን ሙሉ በሙሉ ለመቀየር ተገድጃለሁ፡፡
 
  አዎን! የሸዋሉል ከዕድሜዋ በፊት የተቀጨች ባለ ልዩ ችሎታ እመቤት ነበረች፡፡ ከጥላሁን “አከም ነጉማ” ሌላ በርካታ የኦሮምኛ እና የአማርኛ ዘፈኖች ግጥምና ዜማ ደራሲ ናት፡፡ ለምሳሌም በቅርብ ጊዜ ካገኘሁት መረጃ እንደተረዳሁት “ወይ ዮቢ ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” የሚለውን የዓሊ ቢራ ዘፈን የደረሰችው እርሷ ናት፡፡ የሸዋሉል በጋዜጠኝነቱም ቢሆን ወደር አልነበራትም፡፡ አድናቂዋ እና የሙያ ባለደረባዋ የነበረው አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማ ኢትኦጵ ከሚባል መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ “ትንታግ” በሚል ቃል ገልጾአት እንደነበር ይታወሰኛል (በወቅቱ የርሱ ቃለ ምልልስ ዘርዘር ያለ ስላልነበር ስለርሷ በጎውን እንዳስብ ሊያነሳሳኝ አልቻለም እንጂ)፡፡  ነገር ግን የዚያ ዘመን የደም ትርኢት ይህችን የመሰለች ውብ የኪነት እመቤት ምንጭቅ አደርጎ በላት፡፡ ሚስኪን!
    
   ስለሸዋሉል እውነተኛ ታሪክ ለመመርመር ጉዞ ጀምሬአለሁ፡፡ በተለይ በርሷ ስራዎች ዙሪያ አንድ መጣጥፍ የማጠናቀር ሃሳብ አለኝ፡፡ ሴትዮዋ ኢህአፓዎች እንደሚሉት ገራፊ እና ገዳይ ከሆነች እርሱንም ለወደፊቱ ላስነብባችሁ ቃል እገባለሁ፡፡ ይሁንና ይህ አስቀያሚ ታሪኳ (በእውነትም እንደዚያ አይነት ታሪክ ካላት) መልካም ታሪኳን በምንም መልኩ ሊያስቀረው እንደማይችል መታወቅ አለበት፡፡ ስለርሷ ገራፊነት ስትነግሩን የኖራችሁ ወገኖችም የሸዋሉል “አከም ነጉማ”ን የጻፈችበት ውብ ብዕርና ምትሃታዊውን ዜማ ያፈለቀችበት ውብ አዕምሮ እንደነበራት ልታወጉን ወኔው ይኑራችሁ፡፡ እንዲያ ካልሆነ እውነት ለመናገራችሁ አናምናችሁም፡፡
   
   እኔ ጸሓፊው ከሁለቱም ወገን አይደለሁም፡፡ የኢህአፓም ሆነ የመኢሶን አድናቂ አይደለሁም፡፡ በመሆኑም የኢህአፓዋን ወይዘሮ ዳሮ ነጋሽን “ነፍሰ ጡሯ ሰማዕት” እያልኩ የማሞግስበትና የመኢሶኗን የሸዋሉል መንግሥቱን “ዮዲት ጉዲት ናት” ብዬ የምራገምበት ምክንያት የለም፡፡ ለኔ ቀይ ሽብርም ሆነ ነጭ ሽብር ውጉዝ የሆነ የታሪክ እዳ ነው፡፡ ያንን እዳ ማወራረድ ያለበት ግን ያኛው ትውልድ ራሱ እንጂ ይህኛው ትውልድ አይደለም፡፡ ከያኔው ጥላቻ ጋር የሰዎችን ስብዕና እያጎደፉ መበከል በዚህ ትውልድ መቀጠል የለበትም፡፡ ውቢቷ የብዕር ገበሬና ጠንካራ ጋዜጠኛ የነበረችው የሸዋሉል መንግሥቱም በታሪክ ተገቢ ስፋራዋ ሊሰጣት ይገባል፡፡
  
 “አከም ነጉማ ፈዩማ
   ሂሪያ ሂንቀቡ ኮጱማ
   ዱፍቴ ነላልቱስ ጋሩማ
   አከም ነጉማ ፈዩማ”
   ------
ሰላም ሁኑልኝ
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 19/2005



Saturday, August 24, 2013

የኒያላ እና የግሥላ ካርቶን ንግድ (1983)


ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----------
ወቅቱ የደርግ መንግሥት ፍጻሜ ዋዜማ ነው፡፡ ዕለተ ማክሰኞ፡፡ ገለምሶ እንደ ሁል ጊዜዋ የማክሰኞ ገበያተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ነበረች፡፡ እኔም “አው ሰኢድ” ከሚባለው ሰፈር ካለው የአባቴ መኖሪያ (ድሮ የታወቀ ሱቅ ነበር) ወርጄ ወደ መኖሪያ ቤታችን እየተመለስኩ ነው፡፡ ታዲያ “ኒብራ” ከሚባለው የከተማችን አውራ ጎዳና ላይ ያልጠበቅኩት ነገር ገጠመኝ፡፡
 
  “ናሲሮ ሰኢዶ” የሚባለው አብሮ አደግ ጓደኛዬ በየሱቁ እየገባ “የኒያላ ወይም የግሥላ ካርቶን አላችሁ?” እያለ ይጠይቃል፡፡ በእጁ ከሶስት ያላነሱ ካርቶኖችን ይዞ ሌላ ካርቶን መጠየቁ ትንሽ ገረሜታን ፈጠረብኝ፡፡ ምክንያቱም ካርቶን ከአዲስ አበባና ከድሬ ዳዋ የሚመጡ ዕቃዎች ታሽገውበት ወደኛ ከተማ (ገለምሶ) ከመጣ በኋላ አገልግሎቱን እንዳበቃ ነው የሚቆጠረው፡፡ ወደ ሌላ አካባቢ የሚሄድ ጭነት (ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቡና፣ እህል ወዘተ…) የሚታሸገው በጆንያ እንጂ በካርቶን አልነበረም፡፡ ባዶውን ካርቶን የሚፈልጉት “ኩሊ” የሚባሉት የቀን ሰራተኞች አሊያም የቤታቸውን ግማሽ ከፍለው የጥናት ክፍል ሊሰሩበት የሚፈልጉ ተማሪዎች (በተለይ ወደ ሀይስኩል የገቡ)፤ ወይም በካርቶኖ ጊዜያዊ ኮርኒስ ለመስራት የሚፈልጉ አንዳንድ አባወራዎች ናቸው፡፡ “ናሲሮ” ግን ከሶስቱም አልነበረም (ልጁ በወቅቱ ቆንጆ የሆነ የጥናት ቤት ነበረው)፡፡ በዚያ ላይ በእጁ የተመነዘረ ረብጣ ብር ይዟል፡፡ እናም ነገሩን ከርሱ ጠይቄ መረዳት አማረኝና “ለምንድነው ካርቶን የምትገዛው?” አልኩት፡፡
“በጣም ይፈለጋል፤ ወደ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ተወስዶ ይሸጣል”
“ባዶ ካርቶን?”
“አዎን”
“በስንት ነው የምትገዛው?”
“የአንዱ ዋጋ አምስት ብር ነው”
“አምስት ብር ሙሉ?”
“አዎን”
“ሁሉም ዓይነት ካርቶን ይሆናል?”
“አይሆንም፤ የኒያላና የግሥላ ሲጋራዎች ብቻ ነው የሚፈለገው”

ናሲሮ በስራው እንዳግዘው ጠየቀኝ፡፡ “ስንት ትሰጠኛለህ?” አልኩት፡፡ አራት ብር ሊሰጠኝ ቃል ገባልኝ፡፡ እኔም ግብዣውን በደስታ ተቀበልኩት (አራት ብር ዶሮ ከተገዛለት በኋላ እንኳ አንድ ብር ያህል የሚተርፍለት ገንዘብ መሆኑን እያስታወሳችሁ)፡፡
ከናሲሮ ጋር በ“ኒብራ” ጎዳና አንድ ክንፍ ላይ ያሉትን ሱቆች አዳረስን፡፡ አሁን በትክክል የማላስታውሰውን ያህል የኒያላና የግሥላ ካርቶኖችንም ገዛን፡፡ ወደ አስር ሰዓት ገደማም “ፎቶ ማወርዲ” ከሚባለው ፎቶ ቤት አጠገብ ወደሚገኝ መጋዘን ወሰድናቸው፡፡ ከዚያም አራት ብሬን ይዤ ወደ ማክሰኞ ገደማ ላፍ አልኩ፡፡ ዘይቱናና ሸንኮራ እየበላሁ ከናስሮ ጋር የሰራሁትን ገድል ለጓደኞቼ እየቀደድኩላቸው ከቆየሁ በኋላ መሸ፡፡
  *****  *****  *****
በማግስቱ ትምህርት ቤት ሄጄ ስመለስ ከተማው “የኒያላ ካርቶን ያላችሁ….የግሥላ ካርቶን ሽልጡልን” በሚሉ ደላላዎች ተወረሮ አገኘሁት፡፡ “ምን መጣ?” አልኩኝ ለራሴ፡፡ “የሲጋራ ካርቶን ምን ይሰራበታል? ይህንን ያህል ይፈለጋል ማለት ነው?” እያልኩ አሰላሰልኩ፡፡ ነገሩ ይበልጥ የገረመኝ የመግዣ ዋጋው አስር ብር መግባቱን ስሰማ ነው፡፡
“ናሲሮ አታለለኝ ማለት ነው? ለምንድነው የደበቀኝ? እኔ አራት ብሬን ብቻ ከሰጠኝ ከዋጋው ጉዳይ የለኝ! ዋጋውን ለሌላ ሰው እንዳልናገርበት ጠርጥሮኛል ልበል?” እያልኩ በጓደኛዬ አድራጎት ስለፈላሰፍ አንዱ ደላላ ዋጋው በአንድ ቀን ከእጥፍ እንደጨመረ አስረዳኝ፡፡
“እንዴ! ባዶ ካርቶን?”
“አዎን”
“ምን ይሰራበታል ግን?”
“እኔ እንጃ! በጣም ይፈለጋል”

ነገሩ ሀገሬውን በሙሉ ነበር ያስደመመው፡፡ ታዲያ የዕሮብለቱ ሲገርመኝ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዋጋው በእጥፍ ጨመረ፡፡ ባዶ ካርቶን በሀያ ብር! ምክንያቱ ግን ለማንም ግልጽ አልነበረም፡፡

በዚህን ጊዜ ነው ከተሜው በሙሉ ካርቶንን ከያለበት ማሰስ የጀመረው፡፡ “ኩሊዎች” ለንጣፍ የሚጠቀሙበትን አሮጌ ካርቶን ለገበያ አወጡ፡፡ ተማሪዎች ከፍራሽ ስር የሚያነጥፉትን የእርጥበትና የአዋራ መከላከያ ካርቶን እያወጡ የሳምንት በርጫ መግዣ አደረጉት፡፡ ወሬው በየሰፈሩ ተዛመተ፡፡ የጎረምሳና የጎልማሳው የመወያያ ርዕስ “የኒያላ ካርቶን” እና “የግሥላ ካርቶን” ሆነ፡፡

ከጥቂት ቀናት በኋላ የካርቶን መግዣ ዋጋው ሀምሳ ብር ደረሰ፡፡ ካርቶንን እንደ ኮርኒስ የሚጠቀመው ቤተሰብ “ኮርኒስ በአፍንጫዬ ይውጣ” እያለ የቤቱን የጣሪያውን መከለያ ፈነቃቀለው፡፡ ዋጋው ወደ ስድሳና ሰባ ብር ሲያሻቅብ የካርቶን ግድግዳዎች ተደረመሱ፡፡ መቶ ብር ሲገባማ በርካታ ነጋዴዎች ቋሚ የካርቶን ገዥዎችና ጫኞች ሆኑ፡፡ ደላሎች እስከ ገጠር እየዘለቁ በየቤቱ የተደበቁትን የኒያላና የግሥላ ካርቶኖች እየገዙ በከፍተኛ ዋጋ ለነጋዴዎች ያቀርቡ ጀመር፡፡

ዋጋው እስከ መቶ ሀያ ብር ደረሰ… ገበያው ጦፈ፡፡ ምድርና ሰው ሁሉ “ካርቶን….ካርቶን” እያለ ቃላት የመላለስ ገባ ይመላለስ ገባ፡፡ የእናቶቸ የቡና ወሬ ካርቶን ሆነ፡፡ ወሬው ከከተማዋ አልፎ በየገጠሩ ተዛመተ፡፡ ጥቂት ነጋዴዎች በካርቶን ንግድ እስከ መቶ ሺህ ብር የሚደርስ ትርፍ እንደዛቁበት ይወራ ጀመር፡፡
  *****  *****  *****
ይህ ኩነት ከሁለት ወራት በላይ የቆየ አይመስለኝም (ምናልባት ሶስት ወር ያህል ቆይቶ ይሆናል)፡፡ ከሚያዚያ ወር መግቢያ በኋላ የከተማችን ነዋሪዎች የመወያያ አጀንዳ ተቀይሮ ከሰሜን ወደ መሀል ሀገር እየገፋ በመጣው የጦርነት ዜና ላይ ሆነ፡፡ የካርቶን ገበያ ሙሉ በሙሉ ባይደርቅም እጅግ በጣም እየቀዘዘ ሄደ፡፡ በሚያዚያ ማብቂያ ገደማ ከነአካቴው ጠፋ፡፡ ከዚያ ወዲህ ስለርሱ ያነሳ ሰው የለም፡፡

 “ስንቶች በዚህ ንግድ ከበሩ? ስንቶች በኪሳራ ተሸመደመዱ?” የሚለው እስከ አሁን ድረስ በትክክል የማይታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ መልስ ያልተገኘለት ጥያቄ ግን “የኒያላ እና የግሥላ ካርቶኖች እስከ መቶ ሀያ ብር በሚደርስ ሂሣብ የተቸበቸቡበት ምክንያት ምንድነው?” የሚለው ነው፡፡
 
   ለዚህ ጥያቄ የሚሆን ትክክለኛ ምላሽ እስከ አሁን አላገኘሁም፡፡ የተወሰኑ ሰዎች “በወቅቱ በምስራቅ ኢትዮጵያ በኮንትሮባንድ የሚገቡትን ሲጋራዎች በግሥላና በኒያላ ካርቶኖች እየደበቁ ወደ አዲስ አበባ ለማስተላለፍ ጥረት በሚደረግበት ጊዜ የካርቶኖቹ ፍላጎት ጨመረ፡፡ በድሬዳዋ አካባቢ ካሉት ገበያዎች የተገዙት የኮንትሮባንዲስቶቹን ፍላጎት ማሟላት አልቻሉም፡፡ ስለዚህም ነው ገበያው እስከ ገለምሶና መቻራ ድረስ የዘለቀው” ብለውኛል፡፡ እንዲያ ከሆነ በውጪ የተመረቱ ሲጃራዎችን እንደ ሀገር ውስጥ ሲጋራ በማድረግ  የፋይናንስ ፖሊሶች አይን እንዳያርፋበቸው ለማድረግ ተችሎ ነበር ማለት ነው፡፡ ግን ሲጃራው በብዛት ወደ አዲስ አበባ ሲጎርፍ የፋይናንስ ፖሊሶቹ በቀላሉ ይነቁ አልነበረም እንዴ? ወይስ ፋይናንሶችን በሙስና በመሸበብ ነበር የሚታለፈው?
 አንድ ሰው ግን “የሀገር ውስጥ ሲጋራዎች በድብቅ ኤክስፖርት ይደረጉ ነበር፤ ለዚህም ነው የካርቶን ንግድ የተጀመረው” ብሎኛል፡፡ ይህኛውን አባባል በምክንያትነት መቀበል የሚቻል ይመስላል፤ ምክንያቱም በዘመኑ አንዳንድ የመንግሥት ባለስልጣናት ከነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር እንደዚህ አይነቱን ንግድ ያካሄዱ እንደነበረ በስፋት ሲነገር ኖሯልና፡፡ ነገር ግን በዚህ አንጻር ሲኬድም “የሲጋራ ፋብሪካው ሲጋራ የሚያመርተው ያለ ካርቶን ነው እንዴ?” ከሚል ሙግት መፋጠጥ ግድ ይላል፡፡

    በበኩሌ እርግጠኛውን ነገር አልደረስኩበትም-ከላይ እንደጠቀስኩት፡፡ ወደፊት የምደርስበትን ጀባ እንደምላችሁ ቃል ልግባላችሁና የኔን ፈንታ በዚሁ ላብቃ፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ነገሩን የምታውቁ ጓዶቻችን ያላችሁን መረጃ እንድታካፍሉን በአክብሮት እንጠይቃችኋለን፡፡ ሰላም!
  አፈንዲ ሙተቂ