ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----------
አሁንም ወደ ዘፈን ልወስዳችሁ ነው፡፡ ስለወጋየው ደግነቱ “አርኬ ሁማ” ሳወጋችሁ እንደተናገርኩት በአንድ ዘመን በኢትዮጵያ ደራሲያን ሲጻፉ የነበሩት ዘፈኖች “ዘፈን” ተብለው ብቻ የሚታለፉ አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ በመልዕክታቸው ሀያልነት፤ ከፊሎቹ ደግሞ በዜማና ግጥማቸው ህብርነትና የረቀቀ መስተጋብር ዘመን አይሽሬ የሚባሉ ዓይነት ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ በሁለተኛው ዘርፍ ከሚመደቡት ዘመን አይሽሬ ዘፈኖች መካከል አንዱን አስቃኛችኋለሁ፡፡
ዘፈኑ “አከም ነጉማ” ይሰኛል፡፡ ታዲያ ይህንን ዘፈን “ዘፈን” በመሆኑ ብቻ ልዳስሰው የተነሳሁ እንዳይመስላችሁ፡፡ ከጀርባው ያለውን አስገራሚ ታሪክ ላካፍላችሁ በመሻቴ ነው ለቅኝቴ የመረጥኩት (እንጂ እኔ በበኩሌ በአሁኑ ጊዜ ለዘፈን ብዙም “ሀጃ” የለኝም)፡፡
***** *****
*****
የዘፈኑ ርዕስ “Akkam Nagumaa” ነው-ከላይ እንደገለጽኩት፡፡
በኦሮምኛ “እንዴት ነሽ ሰላም ነሽ” እንደማለት ነው፡፡ ዘፋኙ አንጋፋው ኮከብ ጥላሁን ገሠሠ ነው፡፡ በኔ የዕድሜ ክልል ውስጥ
ያላችሁ ሰዎች (ከ30 ዓመት በላይ የሆናችሁ) ዘፈኑን በደንብ
እንደምታስታውሱት ይታወቀኛል፡፡ ከኔ የምታንሱትም ብትሆኑ ጥላሁን በ1987 በለቀቀው አልበም ውስጥ በድጋሚ በዘፈነው ጊዜ እንደ
አዲስ አጣጥማችሁታል (ለዘፈን ባይተዋር ካልሆናችሁ በቀር)፡፡ “አከም ነጉማ” የፍቅር ዘፈን ነው፡፡ ጥላሁን ከአጠገቡ የተለየችውን አፍቃሪውን ነው “እንዴት ነሽ? ነሽ አማን ነሽ?” እያለ የሩቅ ሰላምታ የሚያቀርብላት፡፡ በዘፈኑ ውስጥ በናፍቆት ብስልስል ብሎ እንደተቃጠለላት ያወሳል፡፡ “እንቅልፍ አጥቻለሁ ቶሎ ነይልኝ” እያለም ይለማምናታል፡፡ እስቲ የዘፈኑን ግጥም ከአማርኛ ትርጓሜው ጋር ልጋብዛችሁ (ቃል በቃል ለመፍታት ቢከብድም እንደሚሆን አድርጌ ጽፌዋለሁ)፡፡
------
አዝማቹ
Akkam nagumaa Fayyuumaa (እንዴት?
ነሽ አማን ነሽ? ደህና ነሽልኝ?) Hiriyaa hinqabuu kophumaa (ሌላ ጓደኛ የለኝም እኔ ብቻዬን ነኝ)
Dhuftee na laaltus gaarumaa (እጅግ መልካም ነበር መጥተሸ ብታይኝ)
Akkam nagumaa fayyumaa (እንዴት? ነሽ አማን ነሽ? ደህና ነሽልኝ?)
----------
Eessattin si arga garamin harkisaa (የት ነው የማገኝሽ ወዴትስ ልጓዘው?)
Mee nama naaf dhaami bakki jirtu eessa (እስቲ ሰው ላኪብኝ ቦታሽን ልወቀው)
Yaa damme yaa dammee yaa dammee bulbulaa (የኔ ማር የኔ ማር የኔ ወለላ ማር )
Ani hirriiba dhabe suman yaadaa bulaa (እንቅልፍ አጥቻለሁ ካንቺ ሓሳብ በቀር የለኝም አዳር)
---------
Namni na ilaalee karaa na ceesisaa (ሰዎች ያዩኝና መንገድ ያሻግሩኛል)
Gidiraan jaalalaa sihi na feesisaa (የፍቅር ውቃቢው አንቺን ያሰኘኛል)
Garaan nurakinnaan sabbataan hidhannee (ሆድ ቢያስቸግር እንኳ በመቀነት ያስሩታል)
Ijaa ammo akkam goona tan ilaaltee hin obsine (አይታ የማትታገሰውን ዐይን በምን ያባብሏታል?)
--------
Bakka ati jirtu qalbiin koo na yaadee (ያለሽበትን ቦታ በልቤ እያሰብኩት)
Numan ciisa malee hirriibni na dide (ተጋደምኩት እንጂ ምኑን ነው የተኛሁት)
Nagaatti, nagaatti nagaatti jiraadhu (በሰላም በአማን በደህና ኑሪልኝ)
Guyyaa tokko dhufee hamman sidhungadhuu (አንድ ቀን መጥቼ ስሜሽ እስኪወጣልኝ)
------
ዘፈኑን ከነዜማው መስማት የሚፈልግ ካለ ይህንን የዩቲዩብ ሊንክ ይከተል፡፡
http://www.youtube.com/watch?v=QNfu_1TEQXk
------
ይህ “አከም ነጉማ” የተሰኘው ዘፈን “የጠላሽ ይጠላ ብድሩ ይድረሰው” በሚለው የጥላሁን አልበም ላይ ነው የሚገኘው፡፡ በካሴት የታተመበት ጊዜ በ1973/1974 ይመስለኛል፡፡ ዘፈኑ በተለቀቀበት ጊዜ በሙዚቃ ያጀበውን ባንድ የማህሙድ አህመድን “እንቺ ልቤ እኮ ነው-ስንቅሽ ይሁን ያዥው” ያጀበው ባንድ እንደሆነ በትክክል ያስታውቃል፡፡ በመሆኑም ባንዱ በዘመኑ ገናና የነበረው አይቤክስ ባንድ ነው ማለት ነው፡፡ ዘፈኑ በ1973/74 ቢለቀቅም እስከ ሰማኒያዎቹ መግቢያ ድረስ ይሰማ ነበር፡፡ እኔም እርሱን በደንብ ለመስማት የታደልኩት በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
“አከም ነጉማ”ን በፊት ሳውቀው እንደ ማንም ተራ ዘፈን ነበር የምመለከተው፡፡ ክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ ባረፈበት ዕለት የአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ የኦሮምኛ ፕሮግራም ለቃለ-ምልልስ የጋበዘው አርቲስት ዶ/ር ዓሊ ቢራ “ከጥላሁን ዜማዎች መካከል የትኛውን ታስበልጣለህ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦለት “አከም ነጉማ” የሚል ምላሽ ከሰጠ በኋላ ግን በስስት ዐይን አየው ጀመር፡፡ ይሁንና ዘፈኑን ጠለቅ ብዬ የመመርመርና እንደ ቅርስ የማየት አባዜ የመጣብኝ ባለፈው የመስከረም ወር ነው፡፡
በወቅቱ (መስከረም/2005) ዩቲዩብ በሚባለው ዝነኛ የኢንተርኔት ቻናል ቆየት ያሉ ቪዲዮዎችን እበረብር ነበር፡፡ በተለይ በዚያ ወር የኮሎኔል መንግሥቱን መጽሐፍ አንብቤ ስለነበረ የሳቸውን ንግግሮች የያዙ ቪዲዮዎችን ዳውንሎድ ለማድረግ ከፍተኛ ፍተሻ አደርግ ነበር፡፡ ታዲያ በመንጌ ቪዲዮዎች መካከል በተሸጎጠ አንድ ፋይል ላይ “Tilahun Gessesse’s Akkam Neguma” የሚል ርዕስ በማየቴ ተደነቅኩና ከፈትኩት፡፡ ዘፈኑን ከመስማቴ በፊት ግን ስለዘፈኑ በተጻፈ መጠነኛ ማብራሪያ ውስጥ “Written by Yeshewalul Mengistu” የሚል ሐረግ ታየኝና አድናቆቴ ይበልጥ ጨመረ፡፡ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ይህንን መረጃ ባለማወቄም በእጅጉ አዘንኩ፡፡
***** *****
*****
ይገርማል! ታሪካችን ይገርማል!
የታሪክ አጻጻፋችንም ይገርማል፡፡ የምንጠላውን ሰው የሰይጣን ቁራጭ እያደረግን የአጋንንት መልክና የጋንጩር ቁመና እንሰጠዋለን፡፡
የምንወደውንም ሰው የመንግሥተ ሰማያት ሙሽራ እናስመስለውና ከመላእክት ተርታ እናሰልፈዋለን፡፡ በዚህ መሀል መታወቅ የነበረበት ሐቅ
ይደበቅና አድናቆትና ጥላቻ የታሪክ አጸቆች ሆነው ቁጭ ይላሉ፡፡ ይሁንና ዛሬ የተደበቀው ሐቅ ትክክለኛ ጊዜውን ጠብቆ አንገቱን ቀና
ያደርጋል፡፡ ያኔ ተረትን በታሪክ ቦታ ያነገሡ የጥላቻ ደቀ-መዛሙርት አንገታቸውን ይደፋሉ፡፡ እውነት ኮራ ብላ መራመድ ትጀምራለች፡፡፡፡“አከም ነጉማ”ን በውብ ብዕሩ ከሽኖ ለሀገር ቅርስነት ያበቃው ደራሲም የነዚህ የጥላቻ ደቀ-መዛሙርት የጥቃት ሰለባ ሆኖ ታሪኩ ሲበላሽበት ኖሯል፡፡ ሀገርና ትውልድ ሲያጠፋ እንጂ ለሀገር አንዳች ጠቃሚ ነገር ጠብ እንዳላደረገ ሲጻፍበት ሰንብቷል፡፡ ሆኖም በአንድ ወቅት የተነሳው የጥላቻ አቧራ ብንን ብሎ ሲጠፋለት ደራሲው እጅግ መልካም የሆኑ ቁምነገሮች እንደነበሩት ታሪክ ይመሰክርለት ይዟል፡፡ የዚያ ደራሲ ስም የሸዋሉል መንግሥቱ ይባላል፡፡ ደራሲውን በወንዴ ጾታ ስጠራው ግን ወንድ እንዳይመስላችሁ፡፡ “ሴት” ናት፡፡
“የሸዋሉል መንግሥቱ” የሚለውን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት “አጥፍቶ መጥፋት” በሚለው የሙሉጌታ ሉሌ ድርሰት ውስጥ ይመስለኛል፡፡ በማስከተልም በባቢሌ ቶላ “የትውልድ እልቂት”፣ በክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” እና በሌሎችም ኢህአፓ-ቀመስ ድርሰቶች.. ውስጥ ስሙን አይቼዋለሁ፡፡ በዚህ ስም የምትጠራው ሴት በየመጻሕፍቱ ውስጥ ጨካኝ፣ አረመኔ፣ ገዳይ፣ ገራፊ፣ ዘራፊ፣ ለወጣት የማትራራ ወዘተ… በሚሉ ቃላት ተገልጻለች፡፡ በተለይ አንደኛው መጽሐፍ “እንደ ወንድ የታጠቀ ስኳድ እየመራች ከየቤቱ ወጣቶችን እያደነች የምትገድልና የምትገርፍ የሴት አረመኔ” ብሎ እንደገለጻት እስከ አሁን ድረስ ይታወሰኛል (በዚያ ዘመን ካለርሷ በስተቀር እንዲያ አይነት ጭካኔ የፈጸመች ሴት አልነበረችም ለማለት ይመስላል)፡፡
የሸዋሉል የኖረችው በዘመነ ቀይ ሽብር ነው-ከአያያዜ እንደምትረዱት፡፡ ይህቺ ሴት በ1969/1970 በኢህአፓ ገዳይ ስኳዶች “ሰባራ ባቡር” በሚባለው ሰፈር ከነበረው ቤቷ በራፍ ላይ ተገድላለች፡፡ ኢህአፓዎች የግድያዋን ምክንያት ሲያስረዱ “በንጹሐን ደም እጇን ያጨቀየች ቀንደኛ የመኢሶን ገራፊ እና የገዳይ ጓድ መሪ ነበረች” ነው የሚሉት፡፡ ሴትዮዋ የኢትዮጵያ ሬድዮ ጋዜጠኛ እና የፕሮግራም መሪ ሆና ሳለ እንዲያ ዓይነት ወራዳ ተግባር ውስጥ የገባችበትን ምክንያት በትክክል መረዳት ቢከብደኝም በኢህአፓ አባላትና ደጋፊዎች የተጻፈውን ገለጻ የማስተባብልበት መንገድ ስላልነበረኝ “ታሪኩ እውነት ነው” በማለት ተቀብየው ኖሬአለሁ፡፡ ስለርሷ በጎውን የሚናገሩ ጽሁፎችንና ቃለ ምልልሶችን አልፎ አልፎ ባነብም ሙያዋንና ችሎታዋን በዝርዝር ያስረዳኝ ሰው ስላልነበር በጨካኝነቷና በገራፊነቷ መዝግቤአት ቆይቻለሁ፡፡ “የአከም ነጉማ” ደራሲ እርሷ መሆኗን ከተረዳሁበት ዕለት ጀምሮ ግን አቋሜን ሙሉ በሙሉ ለመቀየር ተገድጃለሁ፡፡
አዎን! የሸዋሉል ከዕድሜዋ በፊት የተቀጨች ባለ ልዩ ችሎታ እመቤት ነበረች፡፡ ከጥላሁን “አከም ነጉማ” ሌላ በርካታ የኦሮምኛ እና የአማርኛ ዘፈኖች ግጥምና ዜማ ደራሲ ናት፡፡ ለምሳሌም በቅርብ ጊዜ ካገኘሁት መረጃ እንደተረዳሁት “ወይ ዮቢ ዮቢ ሐደሶ ሊባነታ” የሚለውን የዓሊ ቢራ ዘፈን የደረሰችው እርሷ ናት፡፡ የሸዋሉል በጋዜጠኝነቱም ቢሆን ወደር አልነበራትም፡፡ አድናቂዋ እና የሙያ ባለደረባዋ የነበረው አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማ ኢትኦጵ ከሚባል መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ “ትንታግ” በሚል ቃል ገልጾአት እንደነበር ይታወሰኛል (በወቅቱ የርሱ ቃለ ምልልስ ዘርዘር ያለ ስላልነበር ስለርሷ በጎውን እንዳስብ ሊያነሳሳኝ አልቻለም እንጂ)፡፡ ነገር ግን የዚያ ዘመን የደም ትርኢት ይህችን የመሰለች ውብ የኪነት እመቤት ምንጭቅ አደርጎ በላት፡፡ ሚስኪን!
ስለሸዋሉል እውነተኛ ታሪክ ለመመርመር ጉዞ ጀምሬአለሁ፡፡ በተለይ በርሷ ስራዎች ዙሪያ አንድ መጣጥፍ የማጠናቀር ሃሳብ አለኝ፡፡ ሴትዮዋ ኢህአፓዎች እንደሚሉት ገራፊ እና ገዳይ ከሆነች እርሱንም ለወደፊቱ ላስነብባችሁ ቃል እገባለሁ፡፡ ይሁንና ይህ አስቀያሚ ታሪኳ (በእውነትም እንደዚያ አይነት ታሪክ ካላት) መልካም ታሪኳን በምንም መልኩ ሊያስቀረው እንደማይችል መታወቅ አለበት፡፡ ስለርሷ ገራፊነት ስትነግሩን የኖራችሁ ወገኖችም የሸዋሉል “አከም ነጉማ”ን የጻፈችበት ውብ ብዕርና ምትሃታዊውን ዜማ ያፈለቀችበት ውብ አዕምሮ እንደነበራት ልታወጉን ወኔው ይኑራችሁ፡፡ እንዲያ ካልሆነ እውነት ለመናገራችሁ አናምናችሁም፡፡
እኔ ጸሓፊው ከሁለቱም ወገን አይደለሁም፡፡ የኢህአፓም ሆነ የመኢሶን አድናቂ አይደለሁም፡፡ በመሆኑም የኢህአፓዋን ወይዘሮ ዳሮ ነጋሽን “ነፍሰ ጡሯ ሰማዕት” እያልኩ የማሞግስበትና የመኢሶኗን የሸዋሉል መንግሥቱን “ዮዲት ጉዲት ናት” ብዬ የምራገምበት ምክንያት የለም፡፡ ለኔ ቀይ ሽብርም ሆነ ነጭ ሽብር ውጉዝ የሆነ የታሪክ እዳ ነው፡፡ ያንን እዳ ማወራረድ ያለበት ግን ያኛው ትውልድ ራሱ እንጂ ይህኛው ትውልድ አይደለም፡፡ ከያኔው ጥላቻ ጋር የሰዎችን ስብዕና እያጎደፉ መበከል በዚህ ትውልድ መቀጠል የለበትም፡፡ ውቢቷ የብዕር ገበሬና ጠንካራ ጋዜጠኛ የነበረችው የሸዋሉል መንግሥቱም በታሪክ ተገቢ ስፋራዋ ሊሰጣት ይገባል፡፡
“አከም ነጉማ ፈዩማ
ሂሪያ ሂንቀቡ ኮጱማ
ዱፍቴ ነላልቱስ ጋሩማ
አከም ነጉማ ፈዩማ”
------
ሰላም ሁኑልኝ
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 19/2005