የወፍ በረር ዳሰሳ - በአፈንዲ ሙተቂ
--------------------------
የመጽሐፉ ርዕስ፡ “ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች፡ የጭቆናና የትግል ታሪክ”
ደራሲ፡ አሕመዲን ጀበል
የገጽ ብዛት፡ 272
ዋጋ፡ 45.00 ብር
የታተመበት ዘመን፡ የካቲት 2003
--------------------------------------
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ በውጪ ምሁራን በሰፊው
ተጽፏል። አቡ ፈድሉላህ አል-ዑመሪ እና ሙሐመድ አል-መቅሪዚን የመሳሰሉ የዐረብ ጸሐፍት ስለኢትዮጵያ ሙስሊሞች የኑሮ ዘይቤና የሱልጣኔታዊ
መንግሥታት ታሪክ መጻፍ የጀመሩት ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነው። ኤንሪኮ ቼሩሊ፣ ጆን ስፔንሰር ትሪሚንግሀም፣ ኢዋልድ ዋግነር፣
ኡልሪች ብራውኬምፐር እና ሌሎችም የአውሮጳ ጸሐፍት በዚህ ርዕስ ዙሪያ በርካታ መጻሕፍትንና ጥናታዊ ጽሁፎችን አበርክተዋል። ይሁንና
የጉዳዩ ባለቤት የሆኑት የኢትዮጵያ ሙስሊም ምሁራን ታሪካቸውንና ማንነታቸውን በመጻፉ ረገድ የነበራቸው አስተዋጽኦ አነስተኛ ነው።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎቹ ፕሮፌሰር ሁሴን አሕመድ እና ፕሮፌሰር አሕመድ ዘከሪያ እንዲሁም የአትላንታ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ሙሐመድ
ሐሰንን የመሳሰሉ ምሁራን የሚችሉትን ያህል ከማድረግ አልተቆጠቡም። ሆኖም የነኝህ ምሁራን ጽሁፎች በአብዛኛው በውጪ ሀገራት የታተሙ
በመሆናቸው በውጪ ሀገር ከሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን በስተቀር በሀገር ቤት ለሚኖሩት አንባቢያን በቀላሉ የማይገኙ ሆነው ቆይተዋል።
በሀገር ውስጥ ያሉ ሙስሊም ምሁራን የኢትዮጵያ
ሙስሊሞችን ታሪክ በመጻፉ ላይ ዝምታን አብዝተው ቆይተዋል። በተለይ በሀገርኛ ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ ወዘተ…) የሚጻፉ መጻሕፍት
አልነበሩም ለማለት ይቻላል። ከፈረንጆቹ 2000 ዓ.ል. ወዲህ ግን ዝምታው እየተሰበረ ነው። በጣም ጥሩ ጥሩ ስራዎችን እያየን ነው።
ከነዚህ መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው “ሐበሻን የማቅናት ዘመቻ” የሚባለው ባለ ሁለት ቅጽ መጽሐፍ ነው። ይህ መጽሐፍ የኢማም አሕመድ
ኢብራሂም አል-ጛዚ ዜና መዋዕል የሆነው “ፉቱሑል ሐበሽ” በሀረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አማካኝነት ከዐረብኛ ወደ አማርኛ ቋንቋ የተተረጎመበት
ነው። በ1997 ዓ.ል. ደግሞ የወለኔው ሼኽ ዑመር በሽር ከዛሬ 100 ዓመታት በፊት በዐረብኛ የጻፉት መጽሐፍ “ጥሮነ-የኢትዮጵያ
ቀደምትና ታላላቅ ዑለማ ታሪክ” በሚል ርዕስ ተተርጉሞ ቀርቦልናል። አቶ ተሾመ ብርሃኑ ከማልም በ2000 ዓ.ል. “ኢማም አሕመድ
ኢብራሂም” የተሰኘ ወጥ ስራ አቅርበውልናል። እነዚህ ሶስት ስራዎች በፈር-ቀዳጅነታቸውም ሆነ የማናውቃቸውን ሀቆች በማሳወቁ ረገድ
የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ጸሐፍቱ (ተርጓሚዎቹ) እና አሳታሚዎቹ በእጅጉ ሊመሰገኑ ይገባል። ይሁንና የተጠቀሱት
ስራዎች በተወሰኑ ሰዎች ስብዕና ላይ ያተኮሩ ግለ-ታሪኮች (biographical works) በመሆናቸው ከመጠነ ሰፊው የኢትዮጵያ
ሙስሊሞች ታሪክ ጋር ሲመዘኑ “አባይን በጭልፋ” ያህል ነው የሚሆኑት።
በየካቲት ወር 2005 ግን በበርካታ ኢትዮጵያዊ
የመጻሕፍት ወዳጆች ዘንድ መነጋገሪያ ሊሆን የበቃ የታሪክ መጽሐፍ ብቅ አለ። ጸሐፊው አሕመዲን ጀበል ይባላል። የመጽሐፉ ርዕስ “ኢትዮጵያዊያን
ሙስሊሞች፡ የጭቆናና የትግል ታሪክ” ይሰኛል። የዚህ መጽሐፍ ፋና ወጊነት በሁለት መልኩ ሊታይ ይችላል። አንደኛ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን
የአንድ ሺህ ዓመታት ታሪክ በአማርኛ ቋንቋ የሚተርክ የመጀመሪያ መጽሐፍ ነው። ሁለተኛ በተመሳሳይ አውደ ርዕስ (subject) ምሁራዊ
ፈር ሳይለቅ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፈ የመጀመሪያ መጽሐፍ ነው።
“ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች፡ የጭቆናና የትግል ታሪክ”
ከ615 እስከ 1700 ዓ.ል የነበረውን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ ይተርካል። ይህም እስልምና ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ
የአውሳ ሱልጣኔት እስከ ወደቀበት ዘመን ድረስ መሆኑ ነው። አሕመዲን ጀበል መጽሐፉን ለመጻፍ ከፍተኛ ጥናት አካሂዷል። የዐረብና
የአውሮጳ ጸሐፍት በርዕሰ ነገሩ ዙሪያ የደረሷቸውን በርካታ መጻሕፍትና ጥናታዊ ጽሁፎችን በጥልቀት መርምሯል። የሀገራችን ቀደምት
ዑለማ የጻፏቸውን ያልታተሙ ሰነዶች ደጋግሞ ፈትሿል። የአፈ-ታሪክ መረጃዎችን በሰፊው አሰባስቧል። በአርኪኦሎጂ ቁፋሮ የተገኙ ስፍራዎችንና
እንደ ሀረር እና ኢፋት ያሉ ቀደምት ኢስላማዊ የስልጣኔ አምባዎችን በአካል ጎብኝቷል። በዚህ ሁሉ ልፋትና ምርምር ያገኘውን ውጤት
ነው በመጽሐፍ መልክ አሳትሞ ያቀረበልን።
አሕመዲን ጀበል መጽሐፉን የጻፈበት ዘይቤ የሚያመረቃ
ነው። የብዕር አጣጣሉ ለተራ አንባቢም ሆነ ለከፍተኛ ምሁራን የሚመች ነው። የጸሐፊውን ስልት እንደ ስነ ጽሁፍ ባለሙያ ሆነን ስንመዝነው
“ኢ-መደበኛ” እና “መደበኛ” የመጣጥፍ አጻጻፍ በሚባሉት ዘይቤዎች መካከል ያለ ሆኖ ነው የምናገኘው። ጸሐፊው የሀገራችን የታሪክ
መጻሕፍት ልዩ መታወቂያ እየሆነ የመጣውን የመደበኛነት ዘይቤ ሙሉ በሙሉ አልለቀቀም። ሆኖም በነዚያ መጻሕፍት የሚታየውን ጠንከር
ያለ የአጻጻፍ ወግ አጥባቂነት አይከተልም። በዐረፍተ ነገር አወቃቀሩም ሆነ በሚጠቀማቸው ቃላት ከመደበኛው አጻጻፍ ላይ ችክ አይልም።
ደረቅና ከበድ ያሉ ቃላትን ከማብዛትም ተቆጥቧል። በመሆኑም አንባቢው የመጽሐፉን 245 ገጾች በሙሉ በትልቅ ተመስጦ ነው የሚያነባቸው።
ይህ ግልጽ እንዲሆንላችሁ ካሻችሁ የአሕመዲንን መጽሐፍ በቅርብ ዘመናት ከወጡ ታሪክ-ነክ መጻሕፍት (በአማርኛ የተጻፉ) ጋር ማወዳደሩ
ይበቃችኋል። እነዚህ መጻሕፍት በትልቅ ልፋት የተዘጋጁ ሆነው ሳለ በአጻጻፋቸው ከሚከተሉት ድርቅ ያለ የወግ አጥባቂነት ባህሪ የተነሳ
የአንባቢውን ቀልብ ብዙም ሲማርኩ አይታዩም። ደራሲ አሕመዲን ጀበል ይህንን ጉልህ የሆነ የአጻጻፍ ድክመት በማጤን ሁሉንም አንባቢ
የሚማርክ ዘይቤ ወደ መምረጡ ያዘነበለ ይመስላል። በመሆኑም በጸሐፊው የተመረጠው ስልት በመጽሐፉ የተካተተውን ታሪክ ያህል አንባቢውን
ሊማርክ ችሏል። ለዚህም ይመስለኛል መጽሐፉ በጥቂት ወራት ውስጥ ሶስት ጊዜ ያህል ለመታተም የበቃው። ከዚህ አኳያ ሲታይ አሕመዲን
በመጽሐፉ ሊያስተምረው ከፈለገው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ በተጨማሪ ወደፊት ስለ ታሪክ መጻፍ የሚፈልጉ ጸሐፍት መከተል ያለባቸውን
አቅጣጫ አሳይቶአቸዋል ብሎ መደምደም ይቻላል። በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ማለት እንዲህ ነው!
***** ***** *****
ደራሲው
የተጠቀመው የአጻጻፍ ስልት በጣም ሸጋ ነው-ከላይ እንደተገለጸው። ሆኖም ጸሐፊው ትኩረቱን ለአጻጻፉ ብቻ አላደረገውም። የታሪክ መጻሕፍት
የሚጻፉበትን ምሁራዊ ፈርጅ ከሞላ ጎደል ጠብቋል። መረጃዎችን ያገኘባቸውን ምንጮች በቅንፍ እና በግርጌ ማስታወሻዎች ይጠቁማል። ትረካዎቹን
በፎቶግራፍ እያስደገፈ የበለጠ ለማብራራት ሞክሯል። የመጽሐፉ የአርትኦት ስራም በበሰለ ሁኔታ ተከናውኗል (አልፎ አልፎ የፊደላት
ስህተት ቢታዩበትም እንኳ)። ፊደላቱ ለዐይን ማራኪ ከመሆናቸውም በላይ ጤናማ እይታ ላለው ማንኛውም ሰው ጉልህ ሆነው ይታያሉ።
መጽሐፉ በይዘቱም ቢሆን ማለፊያ ነው። እስልምና ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ዘመን
ጀምሮ መነገር ያለባቸው አንኳር የሆኑ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪካዊ ክንዋኔዎች ተዳስሰዋል። ከሸዋ ሱልጣኔት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች
የመሰረቷቸው ታዋቂ የአካባቢና ሀገር አቀፍ መንግሥታት ታሪክ በመልክ በመልኩ ቀርበዋል። እንዲሁም ከመኽዙሚ ነገሥታት ጀምሮ የወላስማ፣
የአዳል እና አውሳ ስርወ መንግሥታት ታሪኮች ተዳስሰዋል። በምስራቅ፣
በደቡብና በመካከለኛው ኢትዮጵያ አብበው የነበሩት ሰባቱ የኢፋት፣ የደራ፣ የሀዲያ፣ የዳዋሮ፣ የባሊ፣ የአረባባኒ እና የሻርኻ እስላማዊ
ሱልጣኔቶች አነሳስ፣ እድገትና የመጨረሻ ውድቀታቸው አጠር አጠር ባለ መልኩ ተተርኳል። በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ ውስጥ ሰፊ ስምና
ዝና ተክለው ያለፉት ኢማም አሕመድ ኢብራሂም አል-ጛዚን የመሳሰሉ መሪዎች ስብዕና በተገቢ ሁኔታ ተፈትሿል። በአጠቃላይ ከ615 ዓ.ል.
እስከ 1750 ዓ.ል ድረስ ያለው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪካዊ ጉዞ ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ተተርኳል። ደራሲው እነዚህን ታሪኮች ሲተርክልን
በአንዳንድ መጻሕፍት ውስጥ ገኖ የሚታየውን የትረካዎች ተቃርኖ ለመከላከል ብርቱ ጥንቃቄ ያደረገ ይመስላል። ስለዚህ መጽሐፉን ጀምረን
እሰከምናጠናቅቀው ድረስ ልባችን በታሪክ ፈረስ ወደ ጥንታዊው ዘመን ይበርራል። 272 ገጽ እየጣፈጠን ነው የሚያልቀው።
***** *****
*****
“ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች” በእውነቱ የሚደነቅ ስራ ነው። ደራሲው የአንድ
ሺህ ዓመት ታሪካችንን በ45 ብር ብቻ በቀላል አማርኛ እንድናውቀው ስላደረገን መቼም የማንረሳው ባለውለታችን አድርገን ነው የምንወስደው።
ለወደፊቱም በምርምር የተደገፈ እጅግ የተሻለ ስራ እንዲያስነብበን እንጠብቃለን። ታዲያ ደራሲው ወደፊት ሊያሻሽላቸው የሚገባቸውን
አንዳንድ ህጸጾች ሳንጠቁም ብናልፍ አድናቆታችን ፈሩን ይለቅና “መጽሐፉ ሙሉ በሙሉ ፍጹም ነው” የሚል የዘመድና የወዳጅ ሆይ ሆይታ
ይመስልብናል። ስለዚህ የመጽሐፉን ይዘት ወደፊት በስፋት እዳስሰዋለሁ። ይህንን ግምገማ ከማጠናቀቄ በፊት ግን በፊት ሽፋኑ ላይ የሚታዩትንና ለኔ ያልጣሙኝን
ሶስት ነጥቦች ጠቆም ላድርግ።
“ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች” የሚለው ትልቅ ርዕስ የመጽሐፉን ይዘት በበቂ
ሁኔታ ይገልጻል። ከርሱ ስር ያለው “የጭቆናና የትግል ታሪክ” የሚለው አነስተኛ ርዕስ ግን ከመጽሐፉ ይዘት ጋር አለመጣጠን ይታይበታል።
መጽሐፉን ያነበበ ማንኛውም ሰው በቀላሉ እንደሚገነዘበው ደራሲው ያቀረበልን ታሪክ የጭቆናና የትግል ታሪክ ብቻ አይደለም። ንግዱ፣
እደ ጥበቡ፣ የከተማ ግንባታው፣ የመንግስት አስተዳደሩ፣ የተፈጥሮ ሐብቱ ወዘተ.. የተቻለውን ያህል ተዳስሰዋል። “የጭቆናና የትግል
ታሪክ” የሚለው ንዑስ ርዕስ ከእነኝህ ዘርፎች ጋር በተዘዋዋሪ ካልሆነ በስተቀር የቀጥታ ተዛምዶ የለውም። ስለዚህ አሕመዲን ከሚቀጥሉት
እትሞች ላይ ይህንን ንዑስ ርዕስ ማንሳት ይጠበቅበታል።
ሁለተኛው
ነጥብ ደግሞ ሞቃዲሾ ያለው የኢማም አሕመድ ኢብራሂም ሀውልት በሽፋኑ ላይ መካተቱ ነው። የኢማም አሕመድ ታሪክ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች
ታሪክ አካል ነው። ሆኖም የሞቃዲሾው ሀውልት ጄኔራል ዚያድ ባሬ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ለፕሮፓጋንዳ ያሰራው ከመሆኑ ውጪ ከኢማም
አሕመድም ታሪክም ሆነ ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጋር አንዳች ተዛምዶ የለውም። ደግሞም የሀውልቱ ትርጓሜ ኢማም አሕመድ ሶማሊያዊ እንጂ
ኢትዮጵያዊ አይደለም የሚል ነው። ዚያድ በሬ በ1969 ኢትዮጵያን ሲወር ሀውልቱንና የኢማሙን ታሪክ እንደ ቅስቀሳ መሳሪያ በሰፊው
ተጠቅሞበታል። በዚህም ኢማሙ የኛ እንጂ የናንተ አይደለም የሚል የታሪክ ሽሚያ አካሂዷል። ታዲያ አሕመዲን ጀበል ይህንን የመሰለ
ደባ ከጀርባው ያነገበውን ሀውልት በፊት ገጹ ላይ ማሳየት ነበረበት? በፍጹም አልነበረበትም! ከርሱ ይልቅ ኢማሙ ዋና ከተማውን የቆረቆረበት
የደምቢያ ጎራ፣ ወይንም የመጀመሪያውን ታላቅ ድል ያጣጣመበትን የሽምብራ ኩሬ ሜዳ፣ ወይ ደግሞ ኢማሙ የሞተበትን የዘንተራ በር በሽፋኑ
ላይ ቢያትም ኖሮ ምንኛ ያምርበት ነበር!? ስለዚህ አሕመዲን ጀበል ወደፊት በሚታተሙት መጻሕፍቱ ሽፋን ላይ ከታሪካችን ጋር አግባብነት
የሌላቸውን ስዕሎች ባያሳየን መልካም ነው እላለሁ።
ሶስተኛው
መጽሐፉ የታጠረበት የጊዜ ክልል ነው። ደራሲው በዚህኛው ቅጽ (ቅጽ አንድ) ከ615-1700 ያለውን ታሪክ ነው የጻፍኩት ብሎናል።
ከዚያ ወዲህ ያሉት 300 ዓመታት ብቻ ናቸው። እነዚህ ዓመታት ከበፊቱ 1100 ዓመታት በእጅጉ ያንሳሉ። በነዚህ የኋለኞቹ ክፍለ
ዘመናት የተከናወኑት ድርጊቶችም በቀደሙት ዘመናት ከተከናወኑት አንጻር ሲታዩ በአነስተኛ ሚዛን ላይ የሚቀመጡ ናቸው። ለምሳሌ ኢማም
ማሕፉዝ፣ ኢማም አሕመድና አሚር ኑር ሙጃሂድ በፊተኛው ዘመን የነበሩ ታላላቅ መሪዎቻችን ነበሩ። በኋለኞቹ ክፍለ ዘመናት የታየ ማንኛውም
ሙስሊም ኢትዮጵያዊ መሪ ከነዚያ ሶስት መሪዎች ጋር በጭራሽ አይወዳደርም።
የኋለኞቹ መሪዎች ያካሄዷቸው ዘመቻዎች አንድ ላይ ቢደመሩ አሚር ኑር ሙጃሂድ ብቻውን ከፈጸማቸው ዘመቻዎች ጋር አይተካከሉም። ታዲያ
አሕመዲን ለ1100 ዓመታት 250 ገጾች ያሉት አንድ ቅጽ መድቦ ለ300 ዓመታትም በተመሳሳይ መልኩ ሌላ ቅጽ መመደቡ አግባብ ነው?
አይመስለኝም። እንደኔ ከሆነ የመጀመሪያው ቅጽ ከዘመነ ነጃሺ ጀምሮ እስከ ኢማም አሕመድ መነሳት ድረስ ያለውን ታሪክ ቢዘግብና ሁለተኛው
ቅጽ ከኢማም አሕመድ መወለድ ወዲህ ያሉትን የ500 ዓመታት ታሪካችንን ቢተርክ እጅግ የተዋጣለት ይሆን ነበር። ስለዚህ አሕመዲን
ሚዛናዊ መስሎ ላልታየኝ ለዚህ የዘመናት አከፋፈል ማብራሪያ እንዲሰጠን
ይጠበቅበታል።
***** *****
*****
ባጠቃላይ
“ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች፣ የጭቆናና የትግል ታሪክ” ብዙሀኑ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪካቸውን በራሳቸው ቋንቋ እንዲያነቡና እንዲያጠኑ
አብይ ምዕራፍ ከፍቷል። ጸሐፊዎቻችንም በርዕሰ ጉዳዩ ላይ እንዴት መጻፍ እንዳለባቸው በቂ ግንዛቤ የሰጣቸው ይመስለኛል። በዚህ ድርሰት
ፋና ወጊነት ሌሎች ጸሐፍትም ተቀስቅሰው ያሉንን የታሪክ ማስረጃዎችና ማስተማሪያ መጻሕፍት እንዲያበራክቱልን እንጠብቃቸዋለን። ፈጣሪ
ለውዱ ጸሐፊያችን ለአሕመዲን ጀበል እድሜና ጤና ሰጥቶት ሌሎች ስራዎቹንም እንድናጣጥም ያድርገን! ሰላም
አፈንዲ ሙተቂ
አዲስ
አበባ