Friday, February 24, 2023

ሼኽ ሙሐመድ ረሻድን ስናስታውሳቸው

ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ

----
ሼኽ ሙሐመድ ረሻድ ከቢር አብዱላሂ የተወለዱት በቀድሞው የሀረርጌ ክፍለ ሀገር፣ ጨርጨር አውራጃ፣ ጉባ ቆርቻ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው የለገ አርባ (Laga Arbaa) ቀበሌ ነው። የእስልምና ትምህርታቸውንም በወላጅ አባታቸውና በሌሎች ታዋቂ የሀረርጌ ዑለማ (መምህራን) ስር ተከታትለዋል። ከዚያም 1950ዎቹ ውስጥ ሀገር ለቀው በዐረቢያና በሀገረ ሶሪያ በተለያዩ መምህራን ስር ለዓመታት ተምረዋል። በመጨረሻም ወደ ታዋቂው የአል-አዝሀር ዩኒቨርሲቲ በመግባት በእስላማዊ ስነ-መለኮትና የሸሪዓ ህግ የማስትሬት ዲግሪ ይዘዋል። በአፋን ኦሮሞ (ኦሮምኛ) እና በሶማሊኛ ቋንቋዎች ላይ ባደረጉት ምርምርም የዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል።




/ ሼኽ ሙሐመድ ረሻድ በመምህርነትና በቃዲነት በሱዑዲ ዐረቢያና በሶማሊያ ለረጅም ዓመታት ሰርተዋል። በዚህ ስራ ላይ እያሉም 1970ዎቹ አጋማሽ ላይ ቅዱስ ቁርኣንን ወደ አፋን ኦሮሞ (ኦሮምኛ) ተርጉመዋል። ይሁንና ይህ ብዙ የለፉበት የትርጉም ስራ የህትመት ብርሃን ለማየት የበቃው እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 1995 .. ነው። ህትመቱ ሊዘገይ የቻለው አሳታሚው የንጉስ ፈህድ የቅዱስ ቁርኣን ተቋም (King Fahd Qur’an Complex) በመጽሀፍ መልክ ከታተመው ስራ በፊት በኦዲዮ ካሴት የተዘጋጀውን የቁርኣን ትርጉም ለማሰራጨት ስለወሰነ ነው። ይህኛው የሼኽ ሙሀመድ ረሻድ የትርጉም ስራ 1984 (... 1992) በሚሊዮኖች በሚቆጠር ኮፒ ታትሞ ተሰራጭቷል።
------
ሼኽ ሙሐመድ ረሻድ የሚታወቁበት ትልቁ ገድል አሁን በስራ ላይ የሚገኘው የአፋን ኦሮሞ አጻጻፍ ስርዓትን መፍጠራቸው ነው፡፡ እንደሚታወቀው ኦሮምኛ በዚህ ዘመን የሚጻፈው በላቲን ፊደላት ነው፡፡ ኦሮምኛን በላቲን ፊደላት መጻፍ የጀመሩት 1840ዎቹ ወደ ሀገራችን መጥተው የነበሩት የአውሮጳ ሚሲዮናዊያንና ሀገር አሳሾች ነበሩ፡፡ ነገር ግን አውሮጳዊያኑ ኦሮምኛን ሲጽፉ ወጥ የሆነ የአጻጻፍ ስርዓት አልተጠቀሙም፡፡ ጀርመናዊያን የራሳቸውን ቋንቋ በሚጽፉበት ስልት ነበር ኦሮምኛን ለመጻፍ የሞከሩት (ለምሳሌ ለመጻፍ “tsch” እያሉ አራት ፊደላትን ይጠቀሙ ነበር)፡፡ እንግሊዛዊያንም ኦሮምኛን ሲጽፉ የራሳቸውን የጽሑፍ ፈለግ ይከተሉ ነበር፡፡ የፈረንሳዮች አጻጻፍ ደግሞ ከሁለቱም ከበድ ይላል፡፡ በመሆኑም ለረጅም ዘመናትአፋን ኦሮሞወጥ የሆነ የአጻጻፍ ስርዓት አልነበረውም፡፡


ሼኽ ሙሐመድ ረሻድ ይህ ጉዳይ ለረጅም ጊዜ ያሳስባቸው ነበር፡፡ በመሆኑም ለአፋን ኦሮሞ ወጥ የሆነ የአጻጻፍ ስርዓት ለመፍጠር ምርምር ማድረግ ጀመሩ፡፡ በምርምራቸው ያካተቱት በቅርብ የሚያውቋቸውን ሦሥት የፊደል ገበታዎችን ነው፡፡ እነርሱም የሳባ፣ የዐረብኛ እና የላቲን ገበታዎች ናቸው፡፡ በነዚህ የፊደል ገበታዎች ለኦሮምኛ መጻፊያነት ቢውሉ ያላቸውን ፋይዳም ሆነ የሚኖራቸውን እንከን በጥልቀት ካጠኑ በኋላየተሻለ አማራጭ እስኪገኝ ድረስ ለጊዜው ለአፋን ኦሮሞ መጻፊያነት የሚመረጠው የላቲን የፊደል ገበታ ነውከሚል መደምደሚያ ላይ ደረሱ። በዚሁ መሰረትም ዛሬ ኦሮምኛ የሚጻፍበትን Qubee Afaan Oromoo (የኦሮምኛ ቋንቋ ሆሄያት) በስራ ላይ አዋሉ።


እዚህ ላይ የተወሰኑ ምልከታዎችን መጠቆም እፈልጋለሁ። አንዳንድ ሰዎች ኦሮምኛ በላቲን ፊደላት የሚጻፍበትን ስርዓት በፖለቲካ አሻጥር የተወሰነ ውሳኔ አድርገው ሲተቹት እሰማለሁ። እነዚህ ሰዎች የላቲን ፊደልን ለኦሮምኛ መጻፊያነት የመረጡት ለሳባ ፊደል ጥላቻ ያላቸው ሰዎች ናቸው ይላሉ፡፡ ይሁንና ነገሩ በምርምር የተደረሰበት እንጂ በጥላቻ የተወሰነ አይደለም፡፡


ሼኽ ሙሐመድ ረሻድ የፊደል ገበታውን ለመፍጠር ሙከራ ሲያደርጉ ያለሙት ግብ ሁሉንም የኦሮምኛ ድምጾችና እርባታዎቻቸውን የሚወክል የፊደል ገበታ መምረጥ ነው። ለምሳሌ ኦሮምኛ በሳባ የፊደል ገበታ ሲጻፍ” (a) የተሰኘውን ተነባቢ ድምጽ መወከል አይቻልም (ተነባቢውእንጂ አናባቢውበአማርኛም ሆነ በትግርኛ ውስጥ እንደሌለ ልብ በሉ፤ በአማርኛም ሆነ በትግርኛ የመጀመሪያው ግዕዝ አናባቢነው)፡፡ ይህንን ድምጽ እንወክላለን ቢባል እንኳ በንባብ ጊዜ ሰዎች እንደነው የሚያነቡት፡፡ አናባቢው እንደከተነበበ ደግሞ የቃላትና የዐረፍተ ነገሮች ፍቺ በጣም ይዛባል፡፡ በተለይም ብዙ የኦሮምኛ ቃላት በተነባቢ ደረጃ እየተመሳሰሉ በአናባቢ ብቻ ይለያያሉ፡፡ እነዚህ ቃላት በተገቢው ድምጸት ካልተነበቡ ትርጉማቸው መቀየሩ አይቀሬ ነው፡፡ ሁለት አብነቶችን ልስጣችሁ፡፡


በኦሮምኛ Mala ከተባለመላ” (ዘዴ) ማለት ነው፡፡ “Malaa” ከተባለ ግንመግልነው፡፡ “Mallaa” ሲባል ደግሞ ጉንጭ ማለት ነው፡፡ “Maala?” ሲባል ደግሞ “የከብት ዳልጋ” ማለት ነው፡፡ እነዚህ አራት ቃላት በሳባ ፊደላት ሲጻፉ ይመሳሰላሉ፡፡ በሌላ በኩል በኦሮምኛ “aada” ሲባልማቃሰትማለት ነው፡፡ “aadaa” ከተባለ ደግሞባህልእንደማለት ነው፡፡ “adda” ደግሞግንባርነው፡፡ እነዚህም ሦሥት ቃላት በሳባ ፊደላት ሲጻፉ ይመሳሰላሉ፡፡ በመሆኑም አንባቢያን የቃላቱን ትርጉም በማያሻማ ሁኔታ ለመረዳት ይቸግራቸዋል፡፡ ኦሮምኛ በዐረብኛ ፊደላት ሲጻፍም በአናባቢ ምክንያት የሚመጣው ችግር ጎልቶ ይታያል (ለምሳሌ ዐረብኛ ሶስት አጭር አናባቢዎች እና ሶስት ረጅም አናባቢዎች ብቻ ነው ያሉት፡፡ ኦሮምኛ ግን አምስት አጭር አናባቢዎችና አምስት ረጅም አናባቢዎች ነው ያሉት)፡፡


የኦሮምኛ ስነ-ጽሑፍ በጅምር ላይ ያለ በመሆኑ ቋንቋውን ለማሳደግ ከተፈለገ አንባቢያን በቋንቋው የተጻፉ ጽሑፎችን ፈጥነው የሚረዱበት የአጻጻፍ ስርዓት ያስፈልገዋል፡፡ የሳባ እና የዐረብኛ ፊደላትን ለኦሮምኛ መጻፊያነት መጠቀሙ ግን ከላይ ከተገለጹትና ከሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ጋር ያፋጥጣል፡፡ ኦሮምኛ በላቲን የፊደል ገበታ ሲጻፍ ግን እነዚህ ችግሮች የሉም፡፡ በዚህ መሰረት ነው እንግዲህ ሼኽ ሙሐመድ ረሻድ የላቲን ገበታን ለኦሮምኛ መጻፊያነት የመረጡት፡፡ ከዚህ ውጪ ውሳኔው በሳባ ፊደል ጥላቻ ተብሎ የተደረገ ነው ማለት አንዳች ሐቅ የለበትም፡፡ ሼኽ ሙሐመድ ረሻድ ውሳኔውን በስሜት የወሰኑት ቢሆን ኖሮ የላቲን የፊደል ገበታን ከዐረብኛው የፊደል ገበታ ባለስቀደሙት ነበር፡፡
----
ሼኽ ሙሐመድ ረሻድ ከቅዱስ ቁርኣን በተጨማሪ በርካታ የዐረብኛ ድርሳናትን በኦሮምኛ ቋንቋ ተርጉመዋል። የኦሮምኛ-ዐረብኛ እና የኦሮምኛ-ሶማሊኛ መዝገበ ቃላትንም አዘጋጅተዋል። ሼኽ ሙሐመድ ረሻድ ከመምህርነትና ከተርጓሚነት ሌላ በጋዜጠኝነት፣ በደራሲነትና በገጣሚነት በእጅጉ ይጠቀሳሉ።


ሼኽ ሙሐመድ ረሻድ ወደ ሀገር ተመልሰው በአዳማና ድሬዳዋ ከተማ ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ ግንቦት 17/2005 አርፈዋል። አላህ ይርሐማቸው። የበጎ ስራቸውን ዋጋ በጀንነት ይክፈላቸው፡፡
***** ***** *****
አፈንዲ ሙተቂ
መጀመሪያ ሰኔ 11/2005 ተጻፈ፡፡
እንደገና ተሻሽሎ ሰኔ 21/2007 ተጻፈ፡፡

ሀረር


ሀረር