Wednesday, January 19, 2022

ኑሆ ጎበና እና ትዝታዎቼ

ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ

------

ልጅ ነበርኩ፡፡ ዓመቱ በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1977 ይመስለኛል፡፡ እንደሚታወቀው 1970ዎቹ ዓመታት በገለምሶም ሆነ በሌሎች የሀገራችን ከተሞች ሰርግ በሚሰረግበት ወቅት ዳንስ የመደነስ ፋሽን በሰፊው ተስፋፍቶ ነበር፡፡ በጊዜው ለማስደነሻ የሚመረጡት ዘፈኖች ደግሞ የአውሮጳ እና የአሜሪካ የዲስኮ እና ፖፕ ሙዚቃዎች ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ የተለየ ነገር ቢኖር ህንዳዊው አክተር ሚቱን ቻክራቦርቲ (ጂሚ) በተወነበት Disco Dancer የተሰኘ ፊልም ላይ ያሉት ዘፈኖች በአንድ ላይ የተሰበሰቡበት ካሴት ከሌሎች ዘፈኖች እኩል ይደነስበት የነበረ መሆኑ ነው፡፡

 

ከላይ በጠቀስኩት ዓመት በከተማችን በተከወነ አንድ ሰርግ ላይ ግን የተለየ ነገር ነበር የታየው፡፡ ተጋቢዎቹ ሸምሰዲን ሙሐመድ እና አዚዛ አሚን ይባላሉ፡፡ በጊዜው ህጻናት የነበርነው ደቃቃዎች ወደ ሰርግ ቤት እንሄድ የነበረው ወጣቶች በዲስኮ ሙዚቃ እና በጂሚ ዘፈኖች ብሬክ ዳንስ እና ትዊስት ሲደንሱ ለማየት ነበር፡፡ በሸምሱ እና አዚዛ ሰርግ ላይ ግን ዲስኮ ሙዚቃ አልተከፈተም፡፡ ብሬክ ዳንስ የሚደንስም አልነበረም፡፡ በቤቱ ሳምንቱን በሙሉ የሚከፈተው ሙዚቃ የኦሮምኛ ዘፈን ሲሆን ዳንሱም ቀዝቀዝ ያለ ውዝዋዜ ነበር፡፡ የዳንሱ ፕሮግራም የሚጀመረው ጸሐይ በረድ በምትልበት ወቅት (ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ) ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ታዳሚው ሁሉ በርጫ እያደረገ ይጫወታል፤ ይዝናናል፤ ሙሽሮቹን ያጫውታል፡፡

 

በዚያ ሰርግ ቤት በሁለት ካሴቶች ላይ ያሉ ሁለት ዘፈኖች በጣም ጎልተው ይሰሙ እንደነበረ በደንብ አስታውሳለሁ፡፡ ታዲያ ካሴቶቹ በተመሳሳይ ሰዓት አይከፈቱም፡፡ አንደኛው ካሴት ቀዝቃዛው ዳንስ በሚጀመርበት ወቅት ነበር የሚከፈተው፡፡ ከሁለቱ ተመራጭ ዘፈኖች መካከል አንደኛው ያለው በዚህ ካሴት ላይ ነበር፡፡ የዚያ ዘፈን ተጫዋች ያሲን አሕመድ የሚባለው አንጋፋ የኦሮምኛ ድምጻዊ መሆኑን ከጊዜ በኋላ አውቄአለሁ፡፡ የዘፈኑ አዝማችም የሚከተለው ነው፡፡

 

Yaadaan na rakkisaa

Garaan na dhiphisaa

Intala lookoo san

Gurbayyoo shaggaa san

Mee wal nubarsiisa

 

ሁለተኛው ካሴት የሚከፈተው ወጣቶች ተሰብሰበው በርጫ እያደረጉ ከሙሽሮች ጋር በሚጨዋወቱበት ወቅት ነው፡፡ ይሁንና ረፋድ ላይ ወደ ሰርግ ቤቱ በምንሄድበትም ወቅት በቤቱ የሚከፈተው ይኸው ካሴት ነው፡፡ እንግዲህ ከላይ ካልኳችሁ ተመራጭ ዘፈኖች ሌላኛው የሚገኘው በዚህ ካሴት ላይ ነበር፡፡ የሰርጉን ዐውድ ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረውም በዚህ ካሴት ላይ ያለው ተወዳጅ ዘፈን ነው፡፡ ወጣት ሴቶችና ወንዶች የዘፈኑን ግጥሞች በቃላቸው ይዘውት ካሴቱ በማይከፈትበት ወቅት ጭምር ይዘፍኑታል፡፡ እያደር ዘፈኑ በከተማዋ በጣም ገንኖ ወጣቱም ሆነ ታዳጊው በሄደበት ሁሉ ይጫወተው ነበር፡፡ ታዲያ ያኔ ህጻናት የሆንነው የዘፈኑን ግጥሞች መያዝ ስላቃተን ስንጫወተው እንሰባብረው ነበር፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ (1979 ገደማ ይመስለኛል) የሬድዮ ደንበኛ መሆን ስጀምር ግን አዝማቹን መለየት ችያለሁ፡፡ የዘፈኑ አዝማች የሚከተለው ነው፡፡

 

Away way way

Namuu sijaallaa saboontuu to

Namuu sijaallaa way haga malee

Koottu mee walgarraa

 

አሁንም ልብ በሉ! በዚያ ዓመት የዘፈኑን አዝማች ነው ያወቅኩት እንጂ የዘፋኙን ማንነት አልለየሁም፡፡ የአርቲስቱን ሰም ለማወቅ ተጨማሪ ሁለት ዓመት ወስዶበኛል፡፡ ይህ የተከሰተው ደግሞ በከተማ ሳይሆን በገጠር ነው፡፡ 1981 አባቴ የተወለደበትን በልበሌቲ የሚባል መንደር ለማየት ሄጄ ነው የአርቲስቱ ማንነት የተነገረኝ፡፡ ለዚህ ምክንያት የሆነው ደግሞ በዘመኑ ከሀረር ሬድዮ ጣቢያ ይተላለፉ የነበሩ ፕሮግራሞችን ይከታተል የነበረው ያዕሱብ ሼኽ ሙሐመድ ረሺድ የሚባለው አጎቴ (የአባቴ ወንደም) ነው፡፡ የዘፋኙ ስም ማን ነው? እርሱን ቆየት ብዬ አወጋችችኋለሁ፡፡ አሁን ግን ወደ መነሻዬ ልመልሳችሁ!

 

ከላይ ስጽፍ የሸምሱ እና የአዚዛ ሰርግ 1977 የተካሄደ ይመስለኛል ብያለሁ አይደለምን? ይገርማል፡፡ ዘፈኑ የወጣበት ዓመት ሰርግ ከተሰረገበት ወቅት ከአንድ ዓመት በላይ እንደማይበልጥ የሚያረጋግጥ ማስረጃ አግኝቼአለሁ፡፡ ዘፈን የወጣበትን ዓመት የተናገረው ደግሞ ሌላ ሰው ሳይሆን ዘፋኙ ራሱ ነው፡፡ እንዲህ ስል ግን ዘፋኙን በአካል አግኝቼው ቃለ-መጠይቅ አድርጌለት ያገኘሁትን መረጃ እየነገርኳችሁ አይምሰላችሁ፡፡ ዘፋኙ በተዘዋዋሪ መንገድ ነው ዓመቱን ያሳወቀን፡፡

 

ለማለት የፈለግኩት ገብቶአችኋል? አርቲስቱ ዘፈኖቹን የሰራበትን ዓመት እና ካሴቱ የተቀረጸበትን ቦታ የተናገረበት ድምጽ ነው በአጋጣሚ እኔ ዘንድ የመጣው፡፡ ይህ ድምጽ ድሮ በምናውቀው ካሴት ላይ አይሰማም፡፡ 1999 በአንዱ ቀን ግን ፉአድ ሀምዛ የሚባል የገለምሶ ልጅ ካሴቱን አምጥቶ አስደመጠኝ፡፡ በዚያ ካሴት ላይ አርቲስቱ ዘፈኖቹን ተጫውቶ ካጠናቀቀ በኋላ ድምጹን ከፍ አድርጎ ክቡራት እና ክቡራን አድማጮች፡ እኔ የሰማችኋቸውን ዘፈኖች ያቀረብኩላችሁ የሀገራችሁ ልጅ እገሌ እባላላሁ፡፡ ይህ ካሴት የተሰራው እንደ አውሮጳ አቆጣጠር 1984 ሲሆን ስፍራው በጅቡቲ ከተማ ነው ብሎ ይናገራል፡፡ ዓመቱ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ሲቀየር 1976 ወይንም 1977 ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ ካሴት ላይ አርቲስቱ ራሱን ያስተዋወቀበትን ድምጽ ከሰማሁ በኋላ ዘፈን በአቶ ሸምሱ እና በወይዘሮ አዚዛ ሰርግ ላይ ተደጋግሞ የተደመጠው በጊዜው አዲስ ስለነበረ መሆኑን ተረድቻለሁ።




-----

አዎን!

የዚያ ውብ ዘፈን ተጫዋች ትናንት ምሽት በሞት የተለየን ተወዳጁ ድምጻዊ ኑሆ ጎበና ነው፡፡ ኑሆ ጎበናንም በስም ያወቅኩት ያዕሱብ በሚባለው አጎቴ አማካኝነት ነው፡፡ ይሁንና አጎቴ የዘፋኙን ማንነት ሲነግረኝ ኑሕ ሙሐመድ ይባላል ነበር ያለኝ፡፡ በኋላ ላይ አባቴም ይህንኑ ነው ያረጋገጠልኝ፡፡ ድሮ ኑሕ ሙሐመድ እያልን የምንጠራው አርቲስት ኑሆ ጎበና መታወቅ የጀመረው በደርግ ውድቀት ማግስት ነው፡፡ ሆኖም ከዚህ መጠነኛ የስም ልዩነት ጀርባ ሌላ የተወሳሰበ ታሪክ የለም፡፡ ያለው እውነታ በአጭሩ እንደሚከተለው ሊገለጽ ይችላል፡፡


ኑሕ ሙሐመድ በልጅነት ጓደኞቹ እና በድሬ ዳዋ ተወላጆች ዘንድ ኑሆ በሚል የቁልምጫ ስም ነው የሚጠራው፡፡ እርሱም የካናዳ ነዋሪ ከሆነ በኋላ የቁልምጫ ስሙን እንደ መድረክ ስም (Stage name) ሲጠቀምበት ኖሯል፡፡ ጎበና ደግሞ የአያቱ ስም ነው፡፡ በካናዳ ሀገር ፓስፖርት ላይ ስሙ የተጻፈው Nuh Mohammed Gobana ተብሎ ነው፡፡ እንደምታውቁት ፈረንጆች በአሰራራቸው የአባትን ስም ይዘልሉትና Surname የሚሉትን ሶስተኛ ስም ከሁሉ በላይ ያገንኑታል። በመሆኑም አርቲስቱ የውጪዎቹን ልማድ በመከተል ከስሙ ውስጥ የአባቱን ስም ይዘለዋል፡፡ ከመድረክ ስሙ ጋር የአያቱን ስም በማያያዝ Nuho Gobana እያለ ራሱን ይጠራል፡፡ እኛም በዚሁ ስሙ ስንጠራው ኖረናል፡፡

 

አርቲስት ኑሕ ሙሐመድ (ኑሆ ጎበና) በእርግጥም በድሬ ዳዋ ከተማ የተወለደ ፈናን እና ቀሽቲ ነው፡፡ እናቱ ፋጡማ አደም ትባላለች፡፡ አባቱ ሼኽ ሙሐመድ ጎበና ይባላሉ፡፡ ሼኽ ሙሐመድ በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ፣ በባሌ ዞን፣ በጊኒር ከተማ አካባቢ ነበር የተወለዱት፡፡ 1940ዎቹ የእስልምናን ትምህርት ሊያጠኑ ወደ ሀረርጌ መጡ፡፡ ከትምህርታቸው መጠናቀቅ በኋላ ኢጃዛ ሲቀበሉ በድሬ ዳዋ ከትመው ማስተማር ጀመሩ፡፡ በዚያች የበረሃዋ ንግሥት በምትባል ከተማ ትዳር መሥርተው ሲኖሩ ኑሕ የሚባል ልጃቸውን 1950 ገደማ ወለዱ፡፡

------

ከሼኽ ሙሐመድ ጎበና አብራክ የተወለደው ኑሆ በአባቱ ፈለግ አልተጓዘም፡፡ እርሱን የጠራው ሌላ የጥበብ ጥሪ ነው፡፡ በተጠራበት መንገድ ሲጓዝ ደግሞ ድንቅ አርቲስት ወጥቶታል፡፡ የመጀመሪያ ካሴቱን ካወጣበት ጊዜ ጀምሮ በብዙ አድናቂዎቹ በፍቅር ሲደመጥ ኖሯል፡፡

 

ኑሆ የሙዚቃ ስራውን የጀመረው በተወለደባት የድሬ ዳዋ ከተማ ነው፡፡ በድሬ እያለ የቀበሌ ኪነት ቡድን አባል በመሆን በተለያዩ የሀረርጌ ከተሞች ስራውን አቅርቧል፡፡ በዚያ ዘመን የተጫወታቸው ዘፈኖች በሀረር ሬድዮ ጣቢያ ተቀርጸው የነበሩ ሲሆን አንደኛው ዘፈኑ በተለየ ሁኔታ በሬድዮ ጣቢያው የመዝናኛ ክፍለ ጊዜ ተደጋግሞ ይቀርብ እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ ታዲያ የያኔው ኑሆ ድምጽ በኋለኛው ዘመን ከምናውቀው ድምጹ ወፈር ይላል፡፡ ያንን ዘፈን ብትሰሙት የኑሆ ድምጽ መሆኑን ለማመን ይከብዳችኋል፡፡

 

ኑሆ ጎበና በሙዚቃው ነጥሮ የወጣውና የሙዚቃ መሣሪያ መጫወትን የለመደው በጅቡቲ ነው፡፡ በዚያ ሀገር ሳለ ከተጫወታቸው ዘፈኖቹ መካከል Biyya too haadha too እና Yaa Biyya too gaarii የሚሉት በቀዝቃዛ ስልት የተጫወታቸው ዜማዎች በዘመነ ደርግ በሀረርና በአዲስ አበባው ሬድዮ ጣቢያዎች በአፋን ኦሮሞ ፕሮግራም ተደጋግመው ይሰሙ ነበር፡፡ አርቲስቱ የሠራቸው የመጀመሪያዎቹ ሶስት ካሴቶች የተቀረጹት 1974 እስከ 1980 ድረስ በኖረባቸው ጅቡቲ እና ሳዑዲ ዐረቢያ ነው ፡፡

 

ይሁን እንጂ ኑሆ በዘፈኖቹ አድማጩን በሙሉ ቁጭ ብድግ ማድረግ የጀመረው እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር 1980 ወደ ካናዳ ተሻግሮ የቶሮንቶ ከተማ ነዋሪ ከሆነ በኋላ ነው፡፡ በዚያ ሀገር ሳለ ነው ድምጹ እንደ ማረሻ ተስሎ በዘፈኖቹ ማስገምገም እና ማግሳትን የተካነው፡፡ ብዙዎች ኑሆን ከሱዳኑ ታዋቂ ድምጻዊ ሰይድ ኸሊፋ ጋር ማመሳሰል የጀመሩት ከቶሮንቶ የለቀቃቸውን አልበሞች ከሰሙለት በኋላ ነው፡፡ አርቲስቱ ከሀረርጌ ባሻገር በሌሎች የኦሮሚያ ዞኖች እና በአጎራባች ክልሎች መታወቅ የጀመረው የጥበብ አፍቃሪዎች ከቶሮንቶ የለቀቃቸውን ሥራዎቹን ካጣጣሙለት ወዲህ ነው፡፡

 

ኑሆ በሙዚቃ ሕይወቱ ከአርባ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በዚህ ረጅም ጊዜ ውስጥ አስራ አንድ ካሴቶችን (አልበሞችን) ሰርቷል፡፡ ይሁንና እኔ አፈንዲ ሙተቂ አርቲስቱ ያሳተማቸውን አልበሞች በሙሉ በአንድ ሚዛን ላይ አላስቀምጣቸውም፡፡ በኔ እይታ 1982 እስከ 1984 መጨረሻ ድረስ ባለው ጊዜ የወጡት ሶስት አልበሞቹ የምንጊዜም ምርጥ ስራዎቹ መሆናቸውን አምናለሁ፡፡ እነዚህም 1982 የወጣው Ara Guyyaan ka Oromooti የተሰኘ አልበም፣ 1984 የተለቀቀው Isin waamti Harmeen የሚባል አልበም እና 1984 መጨረሻ ላይ በቢልቂሳ ሙዚቃ ቤት አሳታሚነት የተለቀቀው Alaabaa Oromiyaa የተሰኘ አልበም ናቸው፡፡ እነዚህ አልበሞች በግጥም፣ በዜማ፣ በሙዚቃ ቅንብር፣ በሜሎዲ፣ በድምጽ፣ በቀረጻ እና በሚያስተላልፏቸው መልእክቶች ይህ ቀረሽ የማይባሉ ናቸው፡፡

-----

አፈንዲ ሙተቂ

ጥር 11/2014

በድሬ ዳዋ ከተማ ተጻፈ፡፡

-----

©Afendi Muteki, January 2022

------

የቴሌግራም ቻነሌ የሚከተለው ነው።

You may join my telegram channel here.

https://t.me/afandishaHarar