Friday, March 8, 2019

የተቃውሞው መነሻ ከመሠረቱ


-----
ጸሐፊ: አፈንዲ ሙተቂ
----
የአዲስ አበባ መስተዳድር በከተማዋ ዙሪያ ባለው የኦሮሚያ ልዩ ዞን ቀበሌዎች ውስጥ የሰራቸው ኮንዶሚኒየም ቤቶች ባለቤቶችን በእጣ መወሰኑን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ዙሪያ ብዙዎች ያላቸው ግንዛቤ በጣም የተሳሳተ ነው። ስለሆነም የተቃውሞውን መነሻ እና በኦሮሞ ህዝብ በኩል እየተባለ ያለውን ነገር በድጋሚ ዘርዘር አድርጎ ማሳየቱ ተገቢ ይመስለኛል።
የተቃውሞው መነሻዎች የሚከተሉት ናቸው።
1 ቤቶቹ የተሰሩት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው። መሬቱ አሁንም ድረስ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው ያለው። ሆኖም በመሬቱ ላይ መወሰን ያለበት የኦሮሚያ ክልል ድምጽ ታፍኗል። በዚህ ሁኔታ ወደ ቤት እደላ መሄዱ ህጋዊ መሠረት የለውም።
2 ቤቶቹ የተሰሩበት መሬት ከኦሮሞ አርሶ አደሮች በግዴታ የተነጠቀ ነው። አርሶ አደሮቹ የት እንደደረሱ ተጠይቀው አይታወቅም። እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ለአንዳንዶቹ አርሶ አደሮች ለመሬቱ በካሬ ሜትር 2 ብር ለግጦሽ በካሬ ሜትር 1.35 ሳንቲም ብቻ እየተከፈላቸው ነው ከይዞታቸው የተፈናቀሉት። በዚህ ስሌት መሠረት አንድ ሄክታር (10000 ካሬ ሜትር) ያርስ የነበረ ገበሬ በድምሩ 40000 ብር ብቻ ይሰጠው ነበር ማለት ነው። የእነዚህ አርሶ አደሮች ብዛት በመቶ ሺዎች ይቆጠራል። ሁላቸውም ምትክ መሬት የላቸውም። ሁላቸውም ከግብርና በስተቀር ሌላ ሙያ የማያውቁ በመሆናቸው የተሰጣቸው አነስተኛ ብር የትም ሳይደርሳቸው እያለቀባቸው ተበታትነዋል።
3 ቤቶቹ የተሰሩት በ2014 እና በ2015 የኦሮሞ ህዝብ ትልቁን የተቃውሞ ትግል እንዲጀምር ምክንያት በሆነውና ወያኔ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የዘር ማፅዳት ወንጀል ሊሰራበት ባቀደው "ማስተር ፕላን" መሰረት ነው። ማስተር ፕላኑ ቆሟል ቢባልም በእርሱ ላይ በመመርኮዝ የተሰሩት ግንባታዎች አሁንም ድረስ አሉ።
4 ቤቶቹን የሰራው የፌዴራል መንግስቱ የስራና የከተማ ልማት ሚኒስቴር እንጂ የአዲስ አበባ መስተዳድር አይደለም። መስተዳድሩ በቤቶቹ እጣ ፈንታ ላይ የመወሰን ስልጣን የለውም።
5 ቤቶቹን የማከፋፈል አጀንዳ ከሶስት ወር በፊት ሲቀሰቀስ ችግር እንዳይፈጠር ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተነግሮአቸዋል። በተለይ በአራት ነገር ላይ ጥልቀት ያለው ጥናት እንዲደረግ ተናግረን ነበር።
ሀ/ ማስተር ፕላኑ እና እርሱን ተከትሎ የመጣው ተቃውሞ ያስከተለው ክልል አቀፍና ሀገር አቀፍ ቀውስ
ለ/ በቤቶቹ ግንባታ ሳቢያ በኦሮሞ አርሶ አደሮች ላይ የደረሰው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳትና ውድመት
ሐ/ በኦሮሚያ ክልል የተገነባን ቤት በሌላ ክልል ለሚኖር ህዝብ መስጠቱ ያለውን ፖለቲካዊ እድምታ
መ/ ቤቶቹ ያለ በቂ ጥናት በችኮላ መከፋፈላቸው በህዝቦች መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ሊያስከትለው የሚችለው አሉታዊ ችግር
6: የአዲስ አበባ መስተዳድር በራሱ ወጪ የሰራቸውና ለማንም ያልተከፋፈሉ በርካታ የኮንዶሚኒየም ቤቶች አሉት። እነርሱን ለነዋሪዎች ማከፋፈል እየቻለ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች የሚነሱባቸውን ቤቶች ለማከፋፈል መነሳቱ በመስተዳድሩ ውስጥ ሆን ብሎ ጠብ ለመጫር የሚንቀሳቀስ ቡድን ያለ እያስመሰለ ነው።
7 ከሁሉ በላይ አሁን ያለው መስተዳድር የህጋዊነት ጥያቄ የሚነሳበት ነው። መስተዳድሩ በህዝብ ምርጫ ያልተሾመ ጊዜያዊ የሽግግር ጊዜ አስተዳደር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህንን በግልፅ ነግረውናል። በሁለተኛ ደረጃ ለመስተዳድሩ የተሰጠው ጊዜ አንድ ዓመት ብቻ ነው። እንደሚታወቀው በህጉ መሠረት የአዲስ አበባ መስተዳድር ምክር ቤት ምርጫ አምና መደረግ አለበት። ይሁን እንጂ አምና ሀገሪቱ የገባችበትን ቀውስ በመንተራስ ምርጫው በአንድ ዓመት እንዲራዘም ተጠይቆ ህዝቡም ፈቃደኝነቱን ገልጿል።
እንግዲህ የአዲስ ከተማ መስተዳድር በቀሩት ትንሽ ወራት ዋነኛ ሰራው መሆን የነበረበት ምርጫውን ማካሄድ ነው። ይሁን እንጂ የመስተዳድሩ አካላት እርሱን ማሰቡን ትተው በህግ ከተሰጣቸው ስልጣን በላይ በመሄድ ይህንን ከባድ መዘዝ ሊያስከትል የሚችል የቤቶች እደላ ጉዳይ ለማስፈፀም ተንቀሳቅሰዋል። ስለዚህም ነው የኦሮሞ ህዝብ በአንድ ድምፅ እየጮኸ ያለው።
-----
የመፍትሔ ሐሳብ
በችግሩ ላይ መግባባት ከተቻለ በመፍትሔውም ላይ መግባባት ይቻላል። የመፍትሔ ሐሳቡም ከላይ በቁጥር 5 ስር በተቀመጡት አቅጣጫዎች እንዲፈለግ ማድረግ ነው። በአጭሩ የኦሮሞ ህዝብ "ቤት ወደ ማከፋፈሉ ከመግባታችሁ በፊት በቂ ጥናት አድርጋችሁ ሁሉንም ወገኖች ሊያስማማ የሚችል መፍትሔ አምጡ" እያለ ነው። ይህንን ሳይፈፅሙ ወደ ቤቶች እደላ መግባት ህገ ወጡ ማስተር ፕላን እንዲተገበር መፍቀድ ማለት ነው። ስለዚህ የሚመለከታቸው አካላት የህዝቡን ድምፅ መስማት አለባቸው።
-----
ሼር ቢደረግ መልካም ነው።
Share godhaa waliif dabarsaa..