Saturday, January 27, 2018

“ቡኻራ” እና “ቡኻሪ”


ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
------
“ቡኻራ” በዛሬው ዘመን “ኡዝቤኪስታን” በሚባለው ሀገር የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ ይህቺ ከተማ በጥንታዊነታቸው ከሚጠቀሱት የዓለማችን ከተሞችም ትመደባለች፡፡ ከተማዋ ጥንታዊት በመሆኗም ብዙዎችን አፍርታለች፡፡ ታዲያ በእቅፏ ተወልደው ካደጉት ሰዎች ሁሉ ስማቸው በጣም ገንኖ የሚታይ አንድ ሰው አለ፡፡


  የዚህ ሰው የልደት ስም ሙሐመድ ኢብን ዒስማኢል ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ የሚታወቀው ግን “ቡኻሪ” ወይንም አል-ቡኻሪ በተሰኘው ስም ነው፡፡ የሁለቱም ፍቺ የቡኻራው ሰውዬ እንደማለት ነው፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ “የቡኻራው ሰውዬ” የሚታወቅበትን ዋነኛ ስራ እና የቡኻራን ተጠቃሽ ገጽታዎች በጥቂቱ እንቃኛለን፡፡
-----
አል-ቡኻሪ በርግጥም በኡዝቤኪስታኗ የቡኻራ ከተማ ነው የተወለዱት፡፡ ትምህርታቸውን አሐዱ ብለው መማር የጀመሩትም በዚህችው የልደት ቀዬአቸው ነው፡፡ በጉርስምና ዘመናቸው ግን የዕውቀት ጥማታቸው በጣም ጨመረ፡፡ በመሆኑም በዘመኑ የነበሩትን የዒልም መዲናዎች ማሰስ ጀመሩ፡፡ ወደ ኒሻፑር፣ መካ፣ መዲና፣ አል-ፉስጣጥ (ግብጽ) ጠብሪዝ፣ በስራ፣ ኩፋ፣ በግዳድ፣ ደማስቆ፣ ወዘተ እየሄዱ እንደ አሕመድ ኢብን ሀንበልን በመሳሰሉት ስመ-ገና ሊቃውንት ስር እውቀትን ተመገቡ፡፡
  አል-ቡኻሪ በትምህርታቸው ላይ እያሉ የነቢዩን (ሰዐወ) ሐዲሶች በአንድ መጽሐፍ የማጠናቀር ጉጉት አደረባቸው፡፡ በዚህም መሠረት ከካይሮ እስከ ሜርቭ (ቱርክሜኒስታን) ድረስ እየሄዱ በሰው አንደበት የሚነገሩትን ሐዲሶች መሰብሰብ ጀመሩ፡፡ ከአስራ ስድስት ዓመታት አድካሚ ጥረት በኋላም በነቢዩ (ሰዐወ) ስም የሚነገሩ 600,000 ሐዲሶችን ሰበሰቡ፡፡
  “አል-ቡኻሪ” ከዚያ ለጥቆም የተለያዩ መመዘኛዎችን በማስቀመጥ የሰበሰቧቸውን ሐዲሶች እውነተኛነት በጥልቀት ፈተሹ፡፡ ከሰበሰቧቸው ሐዲሶች መካከል አብዛኞቹ ከአጠራጣሪ ምንጮች የተገኙ መሆናቸውን ተረዱ፡፡ 7275 የሚሆኑት ግን መቶ በመቶ አስተማማኝ (ሰሐሕ) እንደሆኑ ደመደሙ፡፡ በዚህ መደምደሚያ መሠረትም የማይሻር ክብርና ሞገስ ያስገኘላቸውን ጃሚዑል ሰሒሕ (በብዙዎች ዘንድ በሚታወቅበት ስሙ ሰሒሕ አል-ቡኻሪ) የተሰኘ ዝነኛ የሐዲስ መጽሐፍ አጠናቀሩ፡፡ ለዚህ ድካማቸው ከሙስሊም ዓለም “ኢማም” የተሰኘውን ማዕረግ አገኙ፡፡
  አዎን! ኢማም ቡኻሪ የአላህ ፈቃድ ሆኖ ለኛ ያበረከቱት ትልቁ ገጸ-በረከት “ሰሒሕ አል-ቡኻሪ” ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በእስልምና ሊቃውንት ዘንድ ከሐዲስ መጻሕፍት ሁሉ የመጀመሪያ ደረጃ ተሰጥቶታል፡፡ በእስልምና ደንብ ከቅዱስ ቁርኣን በማስከተል ዋነኛ የስነ-መለኮትና የሸሪዓ ህግጋት ምንጭ ተደርጎ የሚወሰደው እርሱ ነው፡፡
  በኢማም ቡኻሪ የተጠናቀረው “ሰሒሕ አል-ቡኻሪ” ተደናቂ የሆነበት አንደኛው ምክንያት “ቡኻሪ” ሐዲሶቹን ያገኙባቸውን ሰዎችና ሐዲሱ ከነቢዩ (ሰዐወ) ሲወርድ ሲዋረድ የመጣበትን ሐረግ (በዐረብኛ ስሙ “ሰነድ”) በተመለከተ የተሟላ መረጃ የያዘውን “ታሪኽ አል-ከቢር” የተሰኘ መጻፍ ለማጠናቀር መቻላቸው ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በቅድሚያ እያንዳንዱ ሰሒሕ ሐዲስ በነቢዩ (ሰዐወ) አንደበት የተነገረበትን ቦታና ጊዜ፣ እንዲሁም ሐዲሱ ከሰሐባ ትውልድ በኋላ በተከታታይ በመጡ ትውልዶች እየተወራረሰ እስከ ቡኻሪ ዘመን የደረሰበትን “የዘገባ ሐረግ” (Chain of Transmission) ያሳያል፡፡ በማስከተል ደግሞ በእያንዳንዱ የዘገባ ሐረግ ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች የልደት ቦታ፣ ጎሳ፣ የዕውቀት ደረጃ፣ የኢማን ሁኔታ፣ ስለእስልምና የነበረው አመለካከት፣ የጤና ሁኔታ፣ ሰውዬው በማኅበረሰቡ ዘንድ የነበረው ተኣማኒነት ወዘተ… በዝርዝር ተመዘግቧል፡፡
  ኢማም ቡኻሪ አንድን ሐዲስ “ሰሒሕ” (authentic) በማለት የሚመዘግቡት በዘገባው ሐረግ ውስጥ የተጠቀሱት ግለሰቦች በሁሉም መለኪያዎች “positive” የሚል ምስክርነት ካገኙ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ አንዱን ሐዲስ ያስተላለፈ ሰው እብለት ያልታየበት (የማይዋሽ) መሆኑ ተረጋግጦ ሳለ ሰውዬው የአዕምሮ ጤና እንዳልነበረው የሚጠቅስ መረጃ ከተገኘበት ቡኻሪ ሐዲሱን ውድቅ ያደረጉት ነበር፡፡
   በሌላ በኩል ደግሞ በአንዱ የዘገባ ሐረግ (ሰነድ) ውስጥ የተጠቀሰው ሰው በጣም ጃጅቶ የሚናገረውን መለየትና ሰገራውን መቆጣጠር ባልቻለበት ዕድሜው ሐዲሱን አውርቶት ከሆነም ሐዲሱ በቡኻሪ መመዘኛ ውድቅ ይደረግ ነበር፡፡ ሰውዬው ሐዲሱን ያወራበት የተለየ የፖለቲካ ተልዕኮ ያለው መሆኑ ከታወቀም ቡኻሪ ለሐዲሱ “ሰሒሕ” የሚለውን ደረጃ ይነፍጉታል (ለምሳሌ “የፖለቲካ ስልጣን በዓሊና በፋጢማ ዝሪያዎች ብቻ መያዝ አለበት” የሚሉት በርካታ የሺዓ ሐዲሶች በቡኻሪ መጽሐፍ ላይ ያልተመዘገቡት ሐዲሶቹ ፖለቲካዊ ግብ ባላቸው ሰዎች የተወሩ ፈጠራዎች መሆናቸው ስለታወቀ ነው)፡፡ ከእንደዚህ ዓይነት ጉድለቶች በጠሩ ሰዎች አንደበት የተላለፉ ሐዲስ ብቻ ናቸው በቡኻሪ መጽሐፍ ውስጥ “ሰሒሕ” ተብለው የተመዘገቡት፡፡
---
ከላይ እንደገለጽኩት “ሰሒሕ አል-ቡኻሪ” ከቅዱስ ቁርኣን ቀጥሎ ሁለተኛው የእስልምና ህግጋት ምንጭ ነው፡፡ ይሁን እንጂ መጽሐፉ በይዘቱ ሸሪዓዊ ብቻ አይደለም፡፡ የነቢዩ ሙሐመድን (ሰዐወ) እና የቀደምት ባልደቦቻቸውን የህይወት ታሪክ በተመለከተም ዋነኛ የሰነድ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል፡፡ እስልምና በቀዳሚዎቹ ዓመታት የተተገበረበትን አኳኋን መረዳት በሚፈልጉ ተመራማሪዎች ዘንድም የመጀመሪያ ደረጃ የታሪክ ምንጭ ሆኖ ይወሰዳል፡፡
   ኢማም ቡኻሪ ከጃሚዑ-ሰሒሕ (ሰሒሕ አል-ቡኻሪ) በተጨማሪ በርካታ መጻሕፍትን ጽፈዋል፡፡ የበርካታ ታላላቅ ዑለማ አስተማሪም ነበሩ፡፡ ከተማሪዎቻቸው መካከልም አንዱ ሰሒሕ ሙስሊም የተሰኘውን ታዋቂ የሐዲስ መጽሐፍ ያጠናቀሩት ሙስሊም ኢብን ሐጃጅ ናቸው፡፡ አል-ቡኻሪ በመጨረሻ የህይወት ዘመናቸው ወደ ተወለዱባት የቡኻራ ከተማ ተመልሰው መኖር ጀመሩ፡፡ ይሁንና በዘመኑ ከነበረው የቡኻራ ገዥ ጋር ስላልተስማሙ ኸርታንክ ወደተባለች ከተማ ሄዱ፡፡ እዚያ ጥቂት ከኖሩ በኋላም በስልሳ ዓመታቸው አረፉ፡፡ አላሕ ይርሐማቸው፡፡ መልካም ስራቸውን ይቀበላቸው፡፡
---
አል-ቡኻሪን ያፈራችው ቡኻራ በመካከለኛው እስያ ቀደምት ከሆኑት ሁለት ከተሞች አንዷ ናት (ሌላኛዋ ሰመርቀንድ ናት)፡፡ በዓለም ታሪክ ውስጥ የሐር መንገድ (Silk Road) እየተባለ የሚጠራው የንግድ መስመር ከሚያቋርጣቸው ዋና ዋና ከተሞች መካከልም አንዷ ነበረች፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላ 709 የኡመያድ ኸሊፋዎች ግዛት አካል ስትሆን ነዋሪዎቿ እስልምናን ተቀብለዋል፡፡
  ቡኻራ ለረጅም ዘመናት የእስልምና የትምህርትና የባህል ማዕከል በመሆን ነው የምትታወቀው፡፡ በዚህ ረጅም ዘመኗ የተገነቡላት በርካታ መስጊዶችና መድረሳዎች አሏት፡፡ ከነርሱም መካከል አንዳንዶቹ በኸሊፋ ሐሩን አል-ረሺድ ዘመን የተሰሩ ናቸው፡፡ ይህም ከዛሬ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ዓመታት በፊት ማለት ነው፡፡ በነዚህ ጥንታዊ ግንባታዎች ላይ የሚታየው ውበት በመካከለኛው ዘመን የነበረውን እስላማዊ የኪነ-ህንጻ ጥበብን (Islamic Architecture) ይወክላል፡፡ እነዚህ ቅርሶች በደንብ መጠበቅ ያለባቸው መሆኑን ለማስገንዘብ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) ቅርሶቹ የሚገኙበትን የቡኻራ ከተማን ጥንታዊ ክፍል (Old Quarter) በዓለም ቅርስነት መዝግቦታል፡፡
----
አፈንዲ ሙተቂ
መጀመሪያ ህዳር 2/2007 በገለምሶ ከተማ ተጻፈ፡፡
እንደገና ተሻሽሎ ጥር 19/2010 በሸገር ተጻፈ፡፡


Monday, January 22, 2018

አልኸዋሪዝሚ- የአልጄብራ አባት





ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ

------
እነሆ ስለሒሳብና ስለ እውቁ የሒሳብ ጀግና በጥቂቱ ልናወጋችሁ ነው፡፡ ጀግናችን ፎቶግራፍ ከተፈጠረበት ዘመን አስቀድሞ የኖረ በመሆኑ ፎቶውን ልናሳያችሁ አንችልም መቼስ!. በምስሉ ላይ የምትመለከቱት የሒሳቡ ጀግና የተወለደበት 1200 ዓመት ሲከበር ታላቋ የሶቪየት ህብረት ያሳተመችውን  የመታሰቢያ ቴምበር ነው፡፡ ሰውየውን ከሶቪየቶች ጋራ ምን አገናኘው? ከወደታች እንመጣበታለን፡፡ አሁን ወጋችንን በመሰረታዊ ጉዳዮች እንጀምር፡፡
          *****
  እስቲ ከዜሮ ጀምሩና በቅደም ተከተል የሚመጡትን ቁጥሮች ጻፉ፡፡ 1 2 3 .. አስር ስትደርሱ ሌላ ቁጥር ለማግኘት አትችሉም አይደል? አዎን! አስር ለማለት ከፈለጋችሁ አንድና ዜሮን ጎን ለጎን በማድረግ ትጽፋላችሁ፡፡ ሌሎቹንም ቁጥሮች ለመጻፍ ከፈለጋችሁ በነዚህ ቁጥሮች ትጠቀማላችሁ፡፡

   በጥንት ዘመን ግን እንዲህ ዓይነት ነገር አልነበረም፡፡ የጥንት ግብጻዊያን ይገለገሉበት በነበረው የሄሮግሊፍ (hieroglyphic) አጻጻፍ ሁሉንም ነገር በተለየ ምስል ስለሚመስሉ የሚጠቀሙባቸው ቁጥሮች ብዛትም ማለቂያ አልነበረውም፡፡ ሮማዊያን በበኩላቸው ፊደልን እንደ ቁጥር ሲጠቀሙ ነው የኖሩት፡፡ ይህኛው የቁጥር ዘዴም ወጥ የሆነ ቀመር ስለሌለው ትልልቅ ቁጥሮችን ለመጻፍ ይቅርና በመቶና በአንድ ሺህ መካከል ያሉ ቁጥሮችን እንኳ ሳይደናግሩ ሊጽፉበት ይከብዳል፡፡ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ያሉ የቁጥር ዘዴዎችም (numeration systems) ተመሳሳይ ጉድለቶች አሏቸው፡፡ በመሆኑም ከጭንቀት ለመገላገል የሚፈልግ ሰው በመግቢያዬ ወደጠቀስኩት የአቆጣጠር ዘዴ መመለሱ የግድ ነው፡፡

  ይህ ዘዴ የሂንዱ-ዐረብ የቁጥር ዘዴ (Indo-Arabic Numeration System) ይባላል:: ከስያሜው እንደምትረዱት ህንድ ዐረቢያ በጋራ በመሆን ለዓለም ህዝብ ያበረከቱት ታላቅ ገጸ-በረከት ነው፡፡ የቁጥሮቹ መሰረት የሆኑት ምልክቶች የተወጠኑት ከክርስቶት ልደት በፊት በሀገረ-ህንድ ነው፡፡ እነዚያ ምልክቶችም 1-እስከ 9 ያሉትን ቁጥሮች ብቻ የሚወክሉ ነበሩ፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመጀመሪያው ምእተ- ዓመት ምልክቶቹ ከህንድ ተሻግረው ወደ ፋርስ፣ ግብጽ፣ ሜሶጶጣሚያ፣ ሶሪያና ዐረቢያ ገቡ፡፡ በነዚህ ሀገራት የሂሳብ ሊቃውንትና በነጋዴዎች እጅ ሲሸከረከሩም ቆዩ፡፡ 800 .. ገደማ ግን አንድ ሰው ከባግዳድ ተነሳና ምልክቶቹን በማሻሻል አሁን ያሉትን ቁጥሮች አስገኘ፡፡

 ታዲያ ይህ ሰው ቁጥሮችን በማስገኘቱ ብቻ አላበቃም፡፡ ከዚያ በፊት የማይታወቁ የሂሳብ ጽንሰ-ሐሳቦችንም ለዓለም አስተዋውቋል፡፡ ከነዚያ ጽንሰ-ሐሳቦች መካከል የመጀመሪያው the concept of Zero” ይባላል፡፡ ሰውዬው ዘጠኙ ቁጥሮች በትክክል ሊሰሩ የሚችሉት ዜሮ ከታከለችባቸው ብቻ መሆኑ ገብቶታል፡፡ በዚህም መሰረት ዜሮን በራሱ በመፈልሰፍ በአስሩ ቁጥሮች ሁሉንም ዐይነት ህልቅ (number) ለመጻፍ እንደሚቻል አሳይቷል፡፡ በተጨማሪም በቁጥሮቹ በትክክል ለመጠቀም ከተፈለገ የሂሳቡ ዓምድ አስር (base ten) መሆን እንዳለበት አስገንዘቧል (ከዚያ በፊት ሂሳቡ ወጥ ዓምድ አልነበረውም፡፡ ግሪኮች አስራ ሁለትን ወይንም ደርዘን ነበር እንደ ዓምድ የሚጠቀሙት፡፡ ለባቢሎኒያ እና ለአሶሪያ ሰዎች ደግሞ የሂሳቡ ዓምድ ስድሳ ቁጥር ነበረ)፡፡
          *****
ለጥንት ሰዎች ሂሳብ ማለት ሁለት ነገር ነው፡፡ አንደኛው በየቀኑ ነገሮችንና የምንደምርበት፣ የምንቀንስበት፣ የምናባዛበትና የምንቀንስበት መሰረታዊው የሂሳብ ዘርፍ ነው፡፡ ይህም አርቲሜቲክ ይባላል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ስፋት፣ ርዝመት፣ ወርድ፣ መጠነ ዙሪያ፣ ቁመት ወዘተ የመሳሰሉትን ለመስፈር የምንጠቀምበት ጂኦሜትሪ ነው፡፡

 ታዲያ ከላይ የጠቀስነው የባግዳዱ ሰውዬ ከሁለቱ የሂሳብ ዘርፎች ወጣ በማለት መመራመር ጀመረ፡፡ የምርምሩን ውጤትም ሒሳቡል ጀብር ወል-ሙቃበላ በሚል ርዕስ አሳተመ፡፡ መጽሐፉ በልዩ ልዩ ምሁራን እጅ ሲገባም ጥንት ያልነበሩ የሂሳብ ስልቶችን፣ ስሌቶችንና ዘዴዎችን አጭቆ የያዘ አዲስ የሂሳብ ዘርፍ እንደፈጠረ ታወቀለት፡፡ በመሆኑም አዲሱ የሒሳብ ዘርፍ በመጽሐፉ ስም ሒሳቡል-ጀብር ተብሎ ተሰየመ፡፡ መጽሐፉ ወደ ላቲን ሲተረጎም ደግሞ ስያሜው አልጄብራ ተብሎ ተቀየረ፡፡
          *****
የሒሳብ ሊቅ ሙሐመድ ኢብን ሙሳ ይባላል፡፡ የተወለደውና አብዛኛውን ዘመኑን ያሳለፈው በአሁኗ የኢራቅ መዲና በባግዳድ ውስጥ ነው፡፡ ይሁንና ወላጆቹ ኸዋሪዝም ከምትባለው የመካከለኛው እስያ ክፍለ ሀገር (በአሁኗ ኡዝቤኪስታን ውስጥ የምትገኝ) ወደ ባግዳድ የመጡ በመሆናቸው ራሱን ሲጠራ አል-ኸዋሪዝሚ በሚል ቅጥያ በስሙ ላይ ይጨምር  ነበር፡፡ የዓለም ህዝብም እርሱን በደንብ የሚያውቀው  በተጸውኦ ስሙ ሳይሆን በዚሁ ቅጥያ ነው፡፡ የሒሳብ ሊቃውንት በበኩላቸው ስራዎቹ ዘወትር ይታወሱ ዘንድ አልጎሪዝም (algorithm) የተባለውን የስሌት ዘዴ በስሙ ሰይመውለታል፡፡

 አል-ኸዋሪዝሚ በመላው ዓለም የተከበረ ምሁር ነው፡፡ በዓለም ታሪክ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ ናቸው ከሚባሉት 100 ሳይንቲስቶች መካከልም ስሙ አለ፡፡ በዚህም የተነሳ እርሱ የተወለደባት ኢራቅ፣ ለተወሰነ ጊዜ የኖረባት ኢራን እና ወላጆቹ የተገኙባት ኡዝቤኪስታን የኔ ነው በሚል ይወዛገቡበታል፡፡ እንግዲህ የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት በምስሉ ላይ የምትመለከቱትን የመታሰቢያ ቴምብር ያሳተመችው አል-ኸዋሪዝሚ የኔ ነው በሚል መነሻ ነው (ኡዝቤኪስታን 1924 እስከ 1991 የሶቪየት ህብረት አካል እንደነበረች አስታውሱ)፡፡
  
ቢሆንም አል-ኸዋሪዝሚን የአንድ ሀገር ብሄራዊ ጀግና ብቻ አድርጎ ማየቱ ለዚህ ዘመን ሰው አይስማማም፡፡ ስራው መላውን ዓለም ያዳረሰ በመሆኑ የሁሉም ህዝቦች ብሄራዊ ሀብት ተደርጎ ቢታይ ነው የሚመረጠው፡፡
  -----
አፈንዲ ሙተቂ
ህዳር 8/2007
በገለምሶ ከተማ ተጻፈ፡፡
---