(አፈንዲ ሙተቂ)
----
ወደ ዱባይ በመጣሁ በሁለተኛው ሳምንት ይመስለኛል። እኔና ባለቤቴ "ኮርኒች" ከሚባለው የቱሪስቶችና የዋናተኞች መናኸሪያ በሚገኝ ካፍቴሪያ ላይ ተሰየምን። ወዲያውኑ አንድ ልጅ እግር አስተናጋጅ እየተጣደፈ መጣ።
"ዐላ ኺድማቲኩም ሰይዳቲ" አለን በዐረብኛ። "ልታዘዛችሁ ዝግጁ ነኝ" ማለቱ ነው። ባለቤቴ ጭማቂ አዘዘች። እኔ ሳንድዊች መብላት አምሮኝ ስለነበረ "ሳንዱች መውጁድ?" አልኩት ("ሳንድዊች አላችሁ እንዴ" እንደማለት ነው)። "ኤይዋ መውጉድ" በማለት መለሰልኝ!! ልጁ ግብጻዊ እንደሆነ ገባኝና "አንት ሚን መስር?" አልኩት። "ኤይዋ! አነ ሚን መስር" (አዎ! ከግብጽ ነኝ!) ብሎኝ የታዘዘውን ሊያመጣ ሄደ። ያ ልጅ በጣም የሚጣደፍ ከመሆኑ የተነሳ ግብጻዊ መሆኑን እንዴት እንዳወቅኩ አልጠየቀኝም። ቢሆንም ፎርሙላውን ለናንተ ልጻፈው።
ከዐረብኛ በርካታ ዘዬዎች መካከል የግብጹ ዘዬ በአንድ ነገር ይለያል። ይኸውም "ጀ" የሚባል ድምጽ የሌለው መሆኑ ነው። በዋናው የአል-ፉስሐ ዐረብኛ (Classical Arabic) የተጻፈና "ጀ" የሚል ድምጽ ያለበት ቃል በግብጾች ዘዬ በ"ገ" ድምጸት ነው የሚነበበው። ለዚህም ነው ግብጾች ታዋቂ መሪያቸውን "ጀማል ዐብዱናስር" በማለት ፈንታ "ገማል ዐብዱናስር" እያሉ የሚጠሩት። ያ ግብጻዊ ወጣትም "መውጁድ" በማለት ፈንታ "መውጉድ" ብሎ የመለሰልኝ ለዚሁ ነው (ይህ "ጀ"ን ወደ "ገ" የመቀየር አካሄድ ለቅዱስ ቁርአን ብቻ አይሰራም። በቁርአን ምንባብ ወቅት ሁሉም ፊደል በትክክለኛው ድምጽ መነበብ አለበት)።
በሌላ ምሽት በዚያው ስፍራ በእግር እየተንሸራሸርን ነበር። ያ ግብጻዊ ወጣት ወደ አስፋልቱ ወጥቶ በመንገዱ ላይ የሚያልፈውን ሰው ሁሉ "ጥሩ እራት! ከጥሩ መስተንግዶ ጋር! ወደኛ ሬስቶራንት ይግቡ" እያለ ይለማመጣል። በመሃሉ አንድ ቆነን ያለ ወፍራም ወጣት "ወደዚያ ሂድልን ባክህ!! መንገዱን ትዘጋብናለህ እንዴ!!" በማለት ገፍትሮት አለፈ። ግብጻዊውም "አረ ባክህ ተወን! ለራስህ መለይካ እየመሰልክ ትረማመዳለህ፥ እኛም ሰርተን ይለፍልን እንጂ" እያለ ለፈለፈ።
ታዲያ አንድ ነገር ውልብ አለብኝ። በልቤ "በዚህ ግብጻዊ ላይ ሙድ መያዝ አለብኝ" አልኩ። እናም ተጠጋሁትና "ኸሊ ያ ጋሊ! ሃዳ መጅኑን" አልኩት (ወዳጄ ተወው! ይሄ እኮ እብድ ነው" እንደማለት ነው)። ታዲያ ልጁም በሰውዬው አድራጎት ቅጥል ብሎ ኖሮ ጠንከር ባለ አነጋገር "ኤይዋ ሃዳ መግኑን" አለኝ። ባሰብኩት መንገድ ስለመለሰልኝ ከልቤ ሳቅኩ። እርሱም ከጣሪያ በላይ እያንባረቀ ከኔ ጋር ሳቅ። ( እኔ የሳቅኩት "መጅኑን" የሚለውን ቃል በግብጻዊው ስልት "መግኑን" ብሎ ስለተናገረው ነው። እርሱ ግን በዚያ አውደልዳይ መንገደኛ የሳቅኩ ነበር የመሰለው)።
ግብጻዊው አቀራረቤ ስላማረው ነው መሰለኝ የመጣሁበትን ሀገር ጠየቀኝ። ከኢትዮጵያ መሆኔን ነገርኩት። እርሱም ለመሸኛ የሚሆነኝን ንግግር እንዲህ በማለት አሸከመኝ!
"ኢትዮጵያ በለድ ገሚል"
እኔም ደግሜ ሳቅ አከናነብኩት። እርሱም በሃይለኛው ከኔ ጋር ሳቀ!!
(ሚስኪን!! እርሱ እኮ "ኢትዮጵያ ቆንጆ ሀገር ናት" እያለኝ ነበር። እኔ ግን "ጀ"ን ወደ "ገ" ቀይሮት ሲናገረው ልስማው ብዬ ነበር ያዋራሁት። አላህ ይቅር ይበለኝ እንግዲህ!!)
----
"አንተ ስለ ሰው አነጋገር ምን አሳሳበህ?" ትሉኝ ይሆናል። በኢትኖግራፊ ምርምር ውስጥ ስትገቡ እንዲህ ነው የሚያደርጋችሁ። ስለሰዎች አነጋገር፣ የቃላትና የዐረፍተ ነገር አሰካክ፣ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ ጌጣጌጦች፣ የጸጉር አሰራር፣ ልዩ ልዩ ልማዶች ወዘተ በሰፊው ለማወቅ ትጨነቃላችሁ። ታዲያ ይህ አመልና አምሮት ያለጊዜውና ያለቦታው መዋል የለበትም። ተወዳጁ ገጣሚ ጀላሉዲን ሩሚ ይህንኑ በአንድ ወግ አጫውቶን ነበር።
ሰውዬው የነህዊ (ሰዋስው) መምህር ናቸው። ማንኛውም ሰው የሰዋስው ህግን ጠብቆ ያናግረኝ ባይ ነበሩ። በአነጋገሩ ስህተት የፈጸመውን ሁሉ "ያንተ ሰዋስው ችግር አለበት" ይሉት ነበር። ታዲያ እኚህ ሰውዬ በአንድ ሰፈር ሲያቋርጡ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ። እዚያ ሆነው ቢጣሩ ማንም ሊደርስላቸው አልቻልም። ወደ ውሃው ለመስጠም ሲቃረቡ ግን በመንገዱ በማለፍ ላይ የነበረ ገበሬ በድንገት ድምጻቸውን ሰምቶ ሊረዳቸው መጣ። መምህሩ ነፍሳቸውን በማዳን ፈንታ የገበሬው አነጋገር አስጨነቃቸው። እናም "ወዳጄ! ስትናገር እኮ የሰዋስው ህግ ጥሰኻል" አሉት።
"ደግ ነው እንግዲህ!" አለ ገበሬው፡ "ሰዋስው ተምሬ እስክመጣ ድረስ እዚሁ ይቆዩኝ!"
ከእንደዚህ ዓይነቱ ይሰውረን!! መልካም ጊዜ ለሁላችሁም ተመኝተናል!!
-----
አፈንዲ ሙተቂ
ዱባይ፥ የተባበሩት ዐረብ ኢማራት
January 13/2017