ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
“ሀረር ጌይ” በተሰኘው መጽሐፌ ውስጥ “ሀረር
የባግዳድ እህት ናት” የሚል የረጅም ጊዜ ልማድ እንዳለ አጫውአችኋለሁ፡፡ ይህም አመለካከት የመጣው ሁለቱ ከተሞች የሚመሳሰሉ በመሆናቸው
ነው፡፡ ከተሞቹን ከሚያመሳስሏቸው የህይወት ዘርፎች መካከል አንዱ እምቅ የስነ-ቃል ሀብታቸው ነው፡፡ ከነዚህ የስነ-ቃል ሀብቶች
ቀዳሚ ሆኖ የሚጠቀሰው ተረት ነው፡፡ የባግዳድ ተረቶችን በ“አንድ ሺህ አንድ ሌሊት” በኩል አንብበናቸዋል፡፡ የሀረር ተረቶች ግን
በመጽሐፍ ያልተሰበሰቡ በመሆናቸው ከብዙኃኑ አንባቢ ዘንድ ሊደርሱ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ እነርሱንም በመጽሐፍ የሚሰበስብ የብዕር ጀግና
ያስፈልገናል፡፡
በዚህ ጽሑፍ ሁለት የሀረር ተረቶችን አጋራችኋለሁ፡፡
ሁለቱንም ተረቶች በልጅነቴ የማውቃቸው ቢሆንም በሀረር ከተማ ቆይታዬ በአዲስ መልክ ሰምቼአቸዋለሁ፡፡
የሓኪም ጋራ መሰንጠቅ
በጥንት ዘመን ሀረር በድርቅ ተመታች፡፡ በድርቁ
ሳቢያም ምንጮቿና ወንዞቿ ደረቁ፡፡ አንድ “ኤላ” (የውሃ ጉድጓድ) ግን በተአምራዊ መንገድ ከመጥፋት ተረፈ፡፡ ይሁንና መገኛው ያልታወቀ
ትልቅ ዘንዶ ከጉድጓዱ አፋፍ ተቀምጦ “ኤላው የኔ ነው” በማለቱ ከኤላው ውሃ መቅዳት አስቸጋሪ ሆነ፡፡ የሀረር ህዝብ ከኤላው ውሃ
መቅዳት ከፈለገ በየዓመቱ አንዲት ቆንጆ ወጣት መገበር እንዳለበት ዘንዶው በአዋጅ አስታወቀ፡፡ የመጠጥ ውሃ ማግኘት የቸገረው የሀረር
ህዝብም አማራጭ ሲያጣ ለዘንዶው በመገበር ከኤላው ውሃ ለመቅዳት ተገደደ፡፡
ለዘንዶው የምትሰጠው ልጅ በእጣ ነው የምትወሰነው፡፡
እጣው የሚወጣበት ሁኔታ ግን ፍትሐዊ አልነበረም፡፡ የሀብታምና የባለስልጣናት ልጆች በስውር ዘዴ ከእጣው ውጪ እንዲሆኑ ይደረግና
የድሃ ልጆች ብቻ እየተመረጡ ለዘንዶው ይሰጣሉ፡፡ ድሆቹ ይህንን በደል ቢያውቁትም ከሀብታሞቹ ጋር መፎካከር ስለማይችሉ ልጆቻቸውን
ለዘንዶው እየገበሩ እምባቸውን መርጨት ግዴታ ሆነባቸው፡፡
ታዲያ በአንድ ዓመት ልጅ የመገበሩ እጣ የደረሰው
ለአንዲት “ተቂይ” (አላህን የምትፈራ) ሴት ነው፡፡ ያቺ ሴት አንዲት ልጅ ብቻ ነበራት፡፡ ልጅቷንም ያገኘችው በስተእርጅና ሲሆን
ባለቤቷ ከልጅቷ መወለድ በኋላ ሞቶባታል፡፡ በመሆኑም ሴትዮዋ አንድዬ ልጇን እንደ እናትና እንደ አባት ሆና ነው ያሳደገቻት፡፡ እንግዲህ እነዚያ እጣ አውጪዎች ሴትዮዋ በስተእርጅና ያገኛትንና በድህነት ያሳደጋችትን
ያቺኑ ልጅ ለዘንዶው እንድትገብር ነው የፈረዱት፡፡
ይሁንና ሴትዮዋ ልጇን ለዘንዶው አላስረክብም አለች፡፡ የሰፈሯ ሰዎች “እምቢ
ካልሽ እኮ ዘንዶው አንቺንም ጨምሮ ይበላሻል” እያሉ ቢያስፈራሯትም ሴትዮዋ ወይ ፍንክች በማለት በቃሏ ጸናች፡፡ ሰዎቹም “በቃ!
ውርድ ከራሳችን!! ዘንዶው ቢበላሽ ተጠያቂ አይደለንም” በማለት ብቻዋን ተዋት፡፡ ወደ ዘንዶው ሄደውም ስለሴትዮዋ እምቢተኝነት ነገሩት፡፡
ከዚያም በየቤታቸው ሆነው ተከታዩን ነገር መጠባበቅ ጀመሩ፡፡ ሴትዮዋም ልጇን ከምታስረክብበት ዕለት በፊት ባለው ምሽት የዘንዶውን
ጭካኔና የእጣ አውጪዎቹን አሻጥር እያነሳች ፈጣሪዋን ስትለምን አደረች፡፡ በማግስቱም ከቤቷ ቁጭ ብላ ዘንዶው የሚያመጣውን መቅሰፍት
መጠባበቅ ጀመረች፡፡
ሴትዮዋ ልጇን የምታስረክበው ከጧቱ በሶስት ሰዓት ገደማ የነበረ ቢሆንም ዘንዶው
በሰዓቱ ግብሩን አላገኘም፡፡ በዚህም የተናደደው ዘንዶ ሴትዮዋን ከነልጅቷ ሊውጣት እጅግ በሚያስፈራ ግርማ ወደ ቤቷ መጓዝ ጀመረ፡፡
የሰፈሩ ሰዎችም “ሊበላት ነው፤ ሴትዮዋ አለቀላት!” እያሉ በአድናቆትና በተመስጦ ትርዒቱን ይመለከቱ ገቡ፡፡
ዘንዶው አቧራውን እያቦነነ ከሴትዮዋ ቤት አጠገብ
ደረሰ፡፡ ሴትዮዋንም ሊውጣት መንደርደር ጀመረ፡፡ ፍላጎቱን ከመፈጸሙ በፊት ግን ፈጣሪ ውጥኑን አከሸፈበት!! እጅግ ግዙፍ የሆነ
ንስር (አሞራ) ከሀረር በስተሰሜን አቅጣጫ በመምጣት ዘንዶውን ከመሬት ላይ “ላጥ” አድርጎ አነሳው፡፡ ንስሩ ዘንዶውን ወደ ሰማይ
በማውጣት ላይ ሳለም የዘንዶው ጭራ ሀረርን በደቡብ በኩል የከበበውን የሀኪም ጋራን በሁለት ቦታ ከፈለው፡፡
ያ ከይሲ ዘንዶ ፈጣሪዋን የምትፈራው ሴትዮ ባደረገችው ጸሎት ተወገደ፡፡ በሀረር
ከተማ ላይ የተጣለው ልጅን የመገበር ግዴታም ለዘልዓለሙ ተነሳ!! ይሁንና ያኔ በዘንዶው ጭራ የተከፈሉት ሁለቱ የሐኪም ጋራ ኮረብቶች
በአንድ ላይ ሳይመለሱ እስከዚህ ዘመን ድረስ ዘለቁ፡፡
አሚር ሆይ! አንተ “ኸይሩ”ን ብቻ አስብ፤ “ለሸሩ” ባለቤት አለውና!!
------
በጥንት ዘመን አንድ ቅን ሰውዬ በሀረር ከተማ ይኖር ነበር፡፡ ይህ ሰው ሁለት ልጆች
ነበሩት፡፡ የመጀመሪያው ልጁ ርህሩህና የዋህ የነበረ ሲሆን ሁለተኛው ልጁ ግን ተንኮል እየፈጠረ ሰዎችን ማሞኘትና መሳቅ ይወድ ነበረ፡፡
አባትዬው ትንሹን ልጅ ቢመክረው አልሰማ እያለ አስቸገረው፡፡ ስለዚህ በትንሹ ልጅ ተስፋ የቆረጠው አባት ዘወትር ትልቁን ልጅ እየጠራው
“ልጄ ሆይ! አንተ ደጉን ብቻ አስብ፡፡ ለተንኮል ባለቤት አለውና” የሚል ምክር ይሰጠው ነበር፡፡ አባት በዚህም ሳያበቃ ለትልቁ
ልጅ “ዓሊ ኸይሮ” (ቅን አሳቢው ዓሊ) የሚል ቅጽል አወጣለት፡፡ ትንሽየውን ግን “ዓሊ ሸርሮ” (ተንኮለኛው ዓሊ) በማለት ሰየመው፡፡
ከጊዜ በኋላ አባት
የአዱኛውን ዓለም ተሰናበተ፡፡ በዚህም የተነሳ ልጆቹ ተቸገሩ፡፡ ኑሮ በጣም ከበዳቸው፡፡ በመሆኑም ወደ ሀረሩ አሚር ሄደው በችግር
መቆራመዳቸውን ነገሩት፡፡ አሚሩ በአጋጣሚ የቤተ መንግሥት ከብቶችን የሚጠብቅ ሰው ይፈልግ ነበርና ወንድማማቾቹ ለእረኝነት እንዲቀጠሩ
ጠየቃቸው፡፡ ወንድማማቾቹ ለስራው የሚሰጣቸውን ምንዳ ሲጠይቁት ከሚበሉት ምግብና ከሚለብሱት ልብስ በተጨማሪ በዓመቱ መጨረሻ ላይ
አንዲት ጊደር እንደሚያገኙ አሳወቃቸው፡፡ ወንድማማቾቹም ከአሚሩ የቀረበላቸውን ጥያቄ በደስታ ተቀበሉትና ስራቸውን ጀመሩ፡፡
ወንድማማቾቹ በመቶዎች የሚቆጠሩትን የአሚሩን ከብቶች “አው-ሓኪም”፣ “አቦከር”
እና “ሸድዳ ዋ መድዳ” ወደሚባሉት ተራሮች እያሰማሩ በትጋት ማገዱን ተያያዙት፡፡ ስራቸውን በደህና ሁኔታ እያከናወኑ ዓመቱን አገባደዱት፡፡
የዓመቱ መጨረሻ እየተቃረበ ሲመጣ ግን የ“አሊ ሸርሮ” ልብ በግለኝነት መመታት ጀመረች፡፡ ለምንዳ የምትሰጣቸውን ጊደር ጉዳይ ሲያስብ
አዕምሮው በስስት ተወጠረ፡፡ በመሆኑም “ወንድሜን ገድዬው ጊደሪቱን የግሌ ማድረግ አለብኝ” በማለት ወሰነ፡፡ እቅዱንም በአው ሓኪም
ተራራ ላይ ለመፈጸም ቆረጠ፡፡
ወንድማማቾቹ ከብቶቹን ወደ “ሓኪም” ተራራ በወሰዱበት በአንደኛው ቀን “አሊ ሸርሮ”
ለወንድሙ “አንተ ከዚህ ሆነህ ከብቶቹን ጠብቅ፤ እኔ ተራራው ላይ ወጥቼ ለምለም ሳር እንዳለ ልይና ልመስ” አለው፡፡ “አሊ ኸይሮ”ም
በቀረበለት ሃሳብ ተስማምቶ ከብቶቹን ለብቻው መጠበቅ ጀመረ፡፡ “አሊ ሸርሮ” ከተራራው ላይ እንደ ወጣ ትልቅ ድንጋይ አንቀሳቅሶ
ወንድሙ ወዳለበት አቅጣጫ ቁልቁል ለቀቀው፡፡ ድንጋዩ ከተራራው ላይ እየተንከባለለ ወረደ፡፡ ከ“አሊ ኸይሮ” አጠገብ ሲደርስ ግን
ወደ ወርቅነት ተቀየረ፡፡ “አሊ ኸይሮ” በዚህ ተአምር ተገረመ፡፡ “ወደ ወርቅነት የተቀየረው ድንጋይ እኔና ወንድሜ ሀብታም እንድንሆን
ዘንድ ከአላህ የተሰጠን ነው” በማለት በደስታ ፈጣሪውን አመሰገነ፡፡ የተፈጠረውንም ተአምር ለወንድሙ ለመንገር በጉጉት ይጠባበቅ
ጀመር፡፡
“አሊ ሸርሮ” በበኩሉ
“አሊ ኸይሮ በድንጋይ በመገደሉ “ጊደሪቱ የኔ ብቸኛ ሀብት ትሆናለች” እያለ በደስታ ከተራራው ወረደ፡፡ ወንድሙ ወደነበረበት ቦታ
ሲደርስ ግን ያልጠበቀውን ነገር አየ፡፡ “ይህ ወርቅ ከየት ነው የመጣው?” በማለትም ወንድሙን ጠየቀው፡፡ አሊ ኸይሮም “አንድ ትልቅ
ድንጋይ ከተራራው ላይ እየተንከባለለ መጥቶ እኔ ጋ ሲደርስ ይህንን ወርቅ ሆነ” በማለት መለሰለት፡፡ “አሊ ሸርሮም “ድንጋዩ የተንከባለለው
ከስሩ የነበረውን ለምለም ሳር ለማየት ብዬ ስላንቀሳቀስኩት ነው፤ እዚህ ደርሶ ወደ ወርቅ ከተቀየረ እኔም የራሴ ወርቅ ሊኖረኝ ይገባል፡፡
ስለዚህ አንተም በተራህ ወደ ተራራው ውጣና ሌላ ድንጋይ አንከባልልኝ” አለው፡፡
“አሊ ኸይሮ”ም ከወንድሙ የሰማውን ሳይጠራጠር ወደ ተራራው ወጥቶ ትልቅ ድንጋይ
አነሳና “አሊ ሸርሮ” ወደነበረበት አቅጣጫ አንከባለለው፡፡ ይሁንና ድንጋዩ ወደ ወርቅነት ሳይቀየር “አሊ ሸርሮ”ን ጭፍልቅ አድርጎ
ገደለው፡፡ “አሊ ኸይሮ” ከተራራው ወርዶ ወንድሙ ወደነበረበት ስፍራ ሲሄድ ወንድሙ ሞቶ አገኘው፡፡ በዚህም በጣም ደነገጠ፡፡ ወደ
ሀረሩ አሚር ሄዶም የተከሰተውን ሁሉ አንድ በአንድ ነገረው፡፡ ሆኖም አሚሩ ሊያምነው አልቻለም፡፡ “ወንድምህን ራስህ ነህ የገደልከው”
በማለትም ከሰሰው፡፡ በመሆኑም “ነፍስ ያጠፋ ሰው ይገደል” በሚለው የሀረር ከተማ ጥንታዊ ህግ መሰረት በድንጋይ ተጨፍልቆ እንዲሞት
ተፈረደበት፡፡
“አሊ ኸይሮ”ም ፍርዱ ሊፈጸምበት ወደ “ሐኪም” ተራራ ግርጌ ተወሰደ፡፡ ከተራራው
ላይ ትልቅ ድንጋይ ተንዶ ቁልቁል ተወረወረበት፡፡ ይሁንና ድንጋዩ “አሊ ኸይሮ” አጠገብ ሲደርስ እንደገና ወርቅ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡
የቅጣቱን አፈጻጻም ለማየት በስፍራው ተሰብስቦ የነበረው የሀረር ህዝብም በተፈጠረው ነገር በጣም ተገረመ፡፡ “ይህ ተአምር ልጁ ወንድሙን
እንዳልገደለ በሐቅ ይመሰክራል” በማለትም ደመደመ፡፡ የሀረሩ አሚር በበኩሉ “የዓሊ ኸይሮ”ን ተአምር ሲያይ “በህይወቴ ስፈልገው
የነበረውን ሐቀኛ ሰው ዛሬ አገኘሁት” የሚል ቃል ተናገረ፡፡ “አሊ ኸይሮ”ንም የዙፋኑ ወራሽ በማድረግ ሾመው፡፡
-----
ወደ ሀረር ከተማ ከመጣችሁ “Amiroo! Kheyruma yaadi,
Sharriin abbuma eeydii” የሚል አባባል ትሰማላችሁ፡፡ “አሚር ሆይ! አንተ ኸይሩን ብቻ አስብ፤ ለሸርሩ ባለቤት አለውና”
እንደማለት ነው፡፡ ከአባባሉ ጀርባ ብዙ ታሪኮች ይነገራሉ፡፡ ከነዚያ ታሪኮች መካከል አንዱ ከላይ የቀረበው ተረት ነው፡፡
በተረቱ እንደተገለጸው
ተንኮለኛ ሰው በለስ የቀናው መስሎት ብዙ የሸር ትብታቦችን ሊተበትብ ይችላል፡፡ ይሁንና እንደዚህ ዓይነቱ ሰው አጓጉል ሆኖ ነው
የሚቀረው፡፡ የማታ ማታ ራሱ በሸረበው የተንኮል ድር መታሰሩ የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህ በህይወት እያለ ደግ ደጉን ብቻ አስብ!!
ለተንኮሉ ባለቤት አለውና!!
በድጋሚ Amiroo kheyruma yaadi, Sharriin abuma eeydi ብለናል፡፡
----
አፈንዲ ሙተቂ
ጥቅምት 20/2007
-----
The writer, Afendi Muteki,
is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of
East Ethiopia. You may like his facebook
page and stay in touch with his articles and analysis: Just click the following
link to go to his page.
አፈንዲ ሙተቂ
ጥቅምት 8/2007
ሀረር-ምስራቅ ኢትዮጵያ