Sunday, September 21, 2014

መሐመድ ወርዲ- ዘመን የማይሽረው አርቲስት

ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
                                                       
----
 እነሆ ነፍስ የሆነውን አርቲስት ልናነሳው ወደድን!! ተወዳጅ፣ ጥበበኛ፣ ባለ ተሰጥኦ ከያኒ!! እውነተኛ የሙዚቃ ቀማሪ! ሱዳን ያፈራችው የምንጊዜም ጌጥ!! ከካይሮ እስከ ዑጋንዳ፣ ከጅቡቲ እስከ ማሊ ምንጊዜም እንደተወደደ ያለ የጥበብ ዋርካ!! ሙሐመድ ወርዲ!!

  “ወርዲ” ማለት ለሱዳኖች ንጉሥ እንደማለት ነው፡፡ እኛም ከአንጋፋ አርቲስቶቻችን ነጥለን አናየውም፡፡ በድሮ ጊዜ ወርዲን በፍቅር ሰምተነዋል፡፡ ዛሬም ወርዲን በመደጋገም እየሰማነው ነው፡፡
*****
ወርዲ ከልቡ ዘፋኝ ነው፡፡ ዘፈኖቹ ከኛ ጋር ከመዛመዳቸው የተነሳ እኛን እኛን ይሸታሉ፡፡ በርካታ ዜማዎቹ እኛ የምንጊዜም ምርጦች አድርገን ለምንወዳቸው ታዋቂ ዘፈኖቻችን መነሻ ለመሆንም በቅተዋል፡፡ ለምሳሌ አንጋፋው ድምጻዊ ጥላሁን ገሠሠ ያዜመውን “አንቺ ከቶ ግድየለሽም”ን ውሰዱት፡፡

አንቺ ከቶ ግድ የለሽም
ስለፍቅር አይገባሽም
ሁሉን ነገር እረስተሽው
ችላ ብለሽ ስለተውሽው
ቻልኩት ፍቅር ለብቻዬ፡፡

አዎን! ዛሬም ድረስ የዚህ ዜማ ተወዳጅነት አልቀነሰም፡፡ ለዚህ ዜማ መሰረቱ የሙሐመድ ወርዲ “አነ ዐርፈክ ያ ፉአዲ” ነው፡፡ ሙሐመድ ወርዲ ዘፈኑን ሲያዜመው እንዲህ ነበር ያለው፡፡

“አነ ዐርፈክ ያ ፉአዲ
ጠል ዐዛበክ ዋ ሱሃዲ
ዋ ሽጃያ አነ ዐዛቢ”

ታዲያ ሙሐመድ ወርዲ የተጫወተውን ዜማ ጋሽ ጥላሁን ወደ አማርኛ የመለሰው እንዲሁ በጋጠወጥነት አይምሰላችሁ፡፡ በነገሩ ውስጥ  የወርዲ ሙሉ ቡራኬ አለበት፡፡ በቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ዘመን የካርቱም መንገድ ለኛ አርቲስቶች የውሃ መንገድ ነበረ፡፡ ለሱዳኖችም ከዋዲ ሃልፋ ይልቅ ሸገር ነበር የምትቀርባቸው፡፡ እናም በዚህ ምልልስ መሀል የኛዎቹ አንጋፋዎች (ጥላሁን ገሠሠ፣ ምኒልክ ወስናቸው፣ አለማየሁ እሸቴ፣ ዓሊ ሸቦ፣ ዓሊ ቢራ ወዘተ..) እና የሱዳኖቹ አንጋፋ አርቲስቶች (አሕመድ አል-ሙስጠፋ፣ ሰይድ ኸሊፋ፣ ሙሐመድ ወርዲ፣ አብዱልከሪም አል-ካብሊ፣ አብዱል ዓዚዝ አል-ሙባረክ ወዘተ…) የአንድ ቤተሰብ ልጆች ሆነው ነበር፡፡ ሱዳኖቹ ያዜሙትን የኛዎቹ ወደ አማርኛ፣ ኦሮምኛና ሶማሊኛ እየመለሱ ይጫወቱታል፡፡ የኛንም ዘፈኖች ሱዳኖች በቋንቋቸው እየተረጎሙ ይዘፍኑታል፡፡ አንዳንዴ ዕድል ሲገጥማቸው ሁለቱም ዘፋኞች አንዱን ዜማ በአንድ መድረክ ላይ በየቋንቋቸው ይጫወቱታል፡፡ በዚህ ስሌት መሰረት ነው እንግዲህ የሙሐመድ ወርዲ “አነ ዐርፈክ ያ ፉአዲ” ወደ አማርኛ የተመለሰው፡፡

አዎን!! እነ ጋሽ ጥላሁን እንደ አሁኖቹ ዘፋኞች (አንዳንዶቹን ማለቴ ነው) የሱዳንና የፈረንጅ ዜማን ወደ አማርኛ እየገለበጡ “የራሴ ድርሰት ነው”  ብለው ሊያሞኙን አይከጅሉም፡፡ ዋናው አርቲስት ባለበት ጭምር እየዘፈኑ ያሳዩትና “እንዴት ነው! አበላሽቼብህ ይሆን?” በማለት ምክርና እገዛ ይጠይቁታል፡፡ ሱዳናዊው አርቲስትም በሰማው ነገር ላይ የራሱን አስተያየት ይሰጣል፡፡ የኛዎቹም ከሱዳናዊያኑ አርቲስቶች የሚሰጣቸውን አስተያየት ተንተርሰው እጅግ የተሻለ ስራ ይሰሩና ህዝቡን እንካችሁ ይሉታል፡፡ ለዚያም ነበር ስራው የሚዋጣላቸውና ዘመን ተሻጋሪ የሚሆንላቸው፡፡

በዚህ ስሌት ወደኛ ቋንቋዎች ከተቀየሩት ተወዳጅ የሱዳን ዜማዎች መካከል የጥላሁን ገሠሠ “እዩዋት ስትናፍቀኝ” (ሰይድ ኸሊፋና ኢብራሂም አውድ በጋራ ከዘፈኑት ዘፈን የተወሰደ)፣ የአሰፋ አባተ “ሸግዬ ሸጊቱ” (ከአሕመድ አል-ሙስጠፋ “ሐቢቢ በኪቱ” የተወሰደ)፣ የምንሊክ ወስናቸው “ስኳር” (ከአብዱልከሪም አል-ካብሊ “ሱከር” የተወሰደ) የዓሊ ቢራ “ኦፊ ረፋ ቡልታ” (ከሙሐመድ ወርዲ “ያ ኑረል-ዐይን” የተወሰደ) ይጠቀሳሉ፡፡
                                                                          *****
    በርካታ የሀገራችን የሙዚቃ ወዳጆች ከመሐመድ ወርዲ ዜማዎች መካከል ለ“ገመር ቦባ” እና ለ“ቲስዐተ ዐሸር ሰና” (ብዙዎች የሚያውቁት  “ሰበርታ” በሚለው ስም ነው) ልዩ ፍቅር አላቸው፡፡ ሆኖም ሱዳኖች በአንደኛ ደረጃ የሚያሰልፏቸው ሌሎች በርካታ የወርዲ ዜማዎች አሉ፡፡ በተለይም “ሱድፋ”፣ “ቃሲ ቀልበክ”፣ “አልሀወል አወል”፣ “አነ ማ በንሳክ”፣  “አንናስ አል-ጊያፋ”፣ “ሐረምተ አድ-ዱንያ”፣ “ያ ኑረል ዐይን”፣ “ሸተል ዘማ”፣ “አል-ሙርሳል” የመሳሰሉት ከምርጥ የወርዲ ዜማዎች መካከል ይሰለፋሉ፡፡ እኔ በግሌ በጣም ከምወዳቸው የሱዳን ዜማዎች መካከልም አንዱ የሙሐመድ ወርዲ “አዚብኒ ወተፈነን” ነው፡፡

ዐዚብኒ ወዚድ ዐዘባ ዩምኪን ገልቢ ይግሳዚይክ
ዜይመን ሳኒ ገልበክ ዩምኪን ገልቢ ይግሳዚክ፡፡
አዚብኒ ወተፈነን ፊ አልዋን ዐዛቢ
ማ ቲምሳሕ ዲሙዒ ማ ቲርሐም ሸባቢ፡፡
ኸሊኒ ፊሹጁኒ ዩምኪን ገልቢ ይክሳዚይክ
ዜይ መንሳኒ ገልበክ ዩምኪን ገልቢ ይክሳዚይክ፡፡

ወርዲ በዚህ ዘፈን ለወዳጁ “ልብሽ ጨክኖብኝ ፍቅርሽ አቃጥሎ እየጨረሰኝ ነው፤ መጥተሸ እምባዬን የማታብሺልኝ ልበ-ደረቅ ነሽ” የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው የፈለገው፡፡ ወርዲ ይህንን ዜማ የዛሬ 20 ዓመት ገደማ በአዲስ አበባ ስታዲየም እጅግ ባማረ ሁኔታ የተጫወተው ሲሆን የሀገራችን አድናቂዎችም በጋለ ስሜት ተቀብለውታል ( ቪዲዮውን በሚከተለው ሊንክ ላይ ተመልከቱት፡፡  https://www.youtube.com/watch?v=WkegFEEwjjM&feature=related
                                                                          *****
ታዲያ የወርዲ ፍቅረኛ በ“አዚብኒ-ወተፈነን” ውስጥ እንደተገለጸው በጭካኔዋ አልዘለቀችም፡፡ ወርዲ በጉንጮቹ ላይ የሚያፈሰው እምባ አሳዝኖአት ከፍቅር በረከቱ ልታቀምሰው መጥታለታለች፡፡ ወርዲም ፍቅረኛውን ያገኘበትን ቀን “የቀኖች ሁሉ ረጢብ፣ እጅግ በጣም ገዳም፣ የምኞቴን ያሳካሁበት ቀን መጥቶልኛል” በማለት ገልጾታል፡፡
“ሱድፋ” የሚለውን የሙሐመድ ወርዲን ዘፈን እናውቀው የለ?.. በዚያ ዘፈን ውስጥ ወርዲ ለወዳጁ ያለውን ፍቅር ብቻ ሳይሆን ከናፈቁት ወዳጅ ጋር መገናኘቱ የሚሰጠውን ደስታ በተዋቡ ቃላት ገልጾታል፡፡ እኔ በበኩሌ እጅግ በጣም የምወደው የወርዲ ዘፈን ይኸው ሱድፋ ነው፡፡ እነሆ የሱድፋን ሙሉ ግጥም ተጋበዙልኝ፡

ሱድፋ… ሱድፋ
ሱድፈ ወ አጅመል ሱድፈነ የውም ላቄታ
አስዓድ የውም የውሚል ሐዬታ
ኑረ ዐይነያ አያም ሓቤታ

ይህ አዝማቹ ነው እንግዲህ፡፡ “ሱድፋ” ማለት አስገራሚ ዕድል ማለት ነው (በእንግሊዝኛ fortunate የሚለው ቃል ይቀርበዋል)፡፡ ተከታዮቹ ግጥሞች የሚከተሉት ናቸው፡፡

አን-ነዘራት በሪዓ ገመም ዘውፍጀል ኸጀል
አልበሰማት ተበዊ ዘይ ኑረል ዐመል
ወጅሂክ ቤን መዛህሪክ ዘይ በድሪ-ክ-ከመል
ወሽሻመክ ኺዴድክ ዘይ ጠዕመል ኹበል
ተስኪር ገልቢ
ወተሽዒል ሑቢ
ኢሽሀክ ረብቢ
አነ በህ ዋ
-----
ማ ቃዲር አጉል ሊክ አን ሑብቢል ከቢር
ወስፉ ዓለይያ ቃሲ መዓዪሽ ፊ-ድ-ደሚር
ቀድረል ከውን ተኩልሉሁ አክበር ቤ ከቲር
ማሊክኒ ሙሐዪይርኒ ሹፍከል ቢል ኣሲር
አስአሊ ቀልቢ
ኢኪኒ ዪቅደር
ኢሽራሕ ሑቢ
አነ ሙሕታር
------
ሱድፈ ዑዩኑ ሻፈክ ሌይሊ ባቂ ይነዊር
ያ አይያም ረቢዒ ዑምሪ መዓኪ አዝሐር
ፊሃ አጥ-ጤይር ይገኒ ሚን አል-ሓኒ ዪዝከር
ቀልቢ ፈራሸ ሐውሊ ወኢንቲ ሸባቢከ አኽደር
ያ መበሒብቢ
ባዕቡድ ሑብቢክ
አለሻን ሑብቢክ
ሩሒ ፈዳክ
*****
ለመሆኑ መሐመድ ወርዲ ማን ነው?

  ሙሉ ስሙ ሙሐመድ ዑስማን ሳሊሕ ወርዲ ነው፡፡ እርሱ ግን “ሙሐመድ ወርዲ” ወይንም በአጭሩ በቤተሰቡ ስም “ወርዲ” ተብሎ ነው የሚታወቀው፡፡ የተወለደው እ.ኤ.አ. በ1932 “ዋዲ ሀልፋ” በተሰኘው ሰሜናዊው የሱዳን ክፍለ ሀገር፣ “ሱወርዳ” በተባለች ትንሽዬ የገጠር መንደር ውስጥ ነው፡፡ እናቱ የኑቢያ ተወላጅ ስትሆን አባቱ ዐረብ ነው፡፡

ወርዲ የሙት ልጅ ነው፡፡ ሁለቱንም ወላጆቹን በልጅነቱ ነው ያጣው፡፡ በመሆኑም በዘመዶቹ ጥበቃ ስር ሆኖ ነው ያደገው፡፡ ትምህርቱን በዋዲ ሀልፋ እና በካርቱም ተከታትሏል፡፡ የተወለደበትን ሀገር እስከ 1956 በመምህርነት ሙያ ካገለገለ በኋላ በወቅቱ ይሞካክራቸው የነበሩት ዘፈኖች በኦምዱርማን ሬድዮ ጣቢያ ተቀርጸው በመተላለፋቸው በህዝብ ልብ ውስጥ ገባ፡፡ ያገኘው የሞራል ድጋፍ ማነሳሻ ስለሆነው መምህርነቱን ትቶ የአርቲስትነቱን ጎራ ተቀላቀለ፡፡ ከዚያም ሱዳኖች ከሚያፈቅሯቸው ቁንጮ ዘፋኞቻቸው አንዱ ለመሆን በቃ፡፡
 
    ወርዲ በህይወቱ የተረጋጋ ኑሮ አልኖረም፡፡ በሱዳን የተለዋወጡት መንግሥታት በተቃዋሚነት እየፈረጁት አንገላተውታል፡፡ በመሆኑም ለሀያ ዓመታት ያህል በካይሮና በለንደን ነው የኖረው፡፡ በ2002 ግን ወደ ሀገሩ በክብር ተመልሷል፡፡ ወርዲ በሙዚቃው ዕድገት ላደረገው አስተዋጽኦ ከካርቱም ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሸልሟል፡፡ ከልዩ ልዩ የአውሮጳ፣ አፍሪቃና እስያ ሀገራትም ሽልማቶችን ተቀብሏል፡፡
 መሐመድ ወርዲ በመጨረሻዎቹ ዓመታት በደረሰበት የጤና መታወክ ሁለት ኩላሊቶቹ ከጥቅም ውጪ ሆነው ነበር፡፡ ይኸው የኩላሊት ህመም ፋታ ነስቶት በየካቲት ወር 2012 ከዚህች ዓለም አሰናብቶታል፡፡
*****
ከመግቢያዬ እንደገለጽኩት የሀገራችን የሙዚቃ አፍቃሪዎች በጣም የሚወዱት የመሐመድ ወርዲ ዘፈን “ሰበርታ” ነው፡፡ እኔም “ሱድፋ”ን ከሁሉም እንደማስበልጥ ገልጫለሁ፡፡ በሱዳኖች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነው የመሐመድ ወርዲ ዜማ ግን “ገመር ቦባ” ነው፡፡ ሱዳኖች እ.ኤ.አ. በ2000 ባደረጉት ምርጫ “አል-ገመር ቦባ” የተሰኘው ዘፈን የክፍለ ዘመኑ ምርጥ “ነጠላ ዜማ” ተብሎ ተመርጧል፡፡እኔም ገመር ቦባን በድምጽ (ኦድዮ) ልጋብዛችሁና ላብቃ፡፡

ቦባ ዐሌክ ተጊል… ቦባ ዐሌክ ተጊል
አል-ገመር ቦባ ዐሌይክ ተጊል፡፡
አስ-ሰጊሩን አል-ማ-ከቢር
አር-ሪጌበት-ጊዛዛት አሲር
አስኑን በርራጊን የሺል
አል-ዑዩን መሥለል ፈናጂል
ቢንተ-ሱዳን አሲል
ያ ገመር ቦባ ዐሌክ ተጊል፡፡

(ገመር ቦባን በዚህ ሊንክ ላይ ይስሙት https://archive.org/details/MohammedWardi-AlQamarBoeba )
------
አፈንዲ ሙተቂ
መጀመሪያ ታሕሳስ 6/2006 ተጻፈ፡፡
እንደገና ተሻሽሎ መስከረም 9/2007 ተጻፈ፡፡
---
The writer, Afendi Muteki, is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia.
 You may like his facebook page and stay in touch with his articles and analysis: Just click this link to go to his facebook page.



Monday, September 15, 2014

የኤርትራ ህልም!

ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
----------                                               
ኤርትራ ዛሬ ራሷን የቻለች ሀገር ናት፡፡ ትናንት ግን የኛው አካል ነበረች፡፡ አጼ ኃይለ ሥላሤ ብልጥ የሆኑ መስሎአቸው ለሁላችንም አስፈላጊ የነበረውን የፌዴሬሽን ፎርሙላ ሰረዙትና ህዝቡን አስቀየሙት፡፡ ደርግ ደግሞ የራሳችንን ህዝብ እንደ ባዕድ እየቆጠረ በመትረየስ አጨደው፡፡ በታንክ ደመሰሰው፡፡ በዚህም የተነሳ ወጣቱ “አደይ ኤሪቲሪያ”ን እየዘመረ ወደ ባርካና ሳህል ነጎደ፡፡ ራሱን አደራጅቶ ጀብሃና ሻዕቢያ ሆኖ መጣ፡፡ ውጤቱም 1983 ላይ ታየ፡፡
  
   የደርግና የኃይለ ሥላሤ መንግሥታት ያደረጓቸው ነገሮች ሲገርሙን በጣም ግራ የሚያጋባው ሶስተኛው መንግሥታችን መጣ፡፡ ይህ የኛ መንግሥት “የተበላሸውን ሁሉ አስተካክለን አብረን መኖር እንችላለን” ብሎ መከራከር ሲገባው ጭራሹኑ “ኤርትራ ካልተገነጠለች ኢትዮጵያ ሰላም አታገኝም” ባይ ሆኖ ተገኘ፡፡ ክፍለ ሀገሩ “ሓርነት ወጣ” ከተባለ በኋላ ደግሞ መንግሥቱ ከሚከተለው ግልጽነት የጎደለው አሰራር የተነሳ በ1990 ሺዎችን ያረገፈ ግዙፍ ጦርነት ተቀሰቀሰ፡፡ ከአንድ ምንጭ የተቀዱ ህዝቦች ተጋደሉ፡፡ እነሆ ዛሬም ድረስ ነገሩ ሳይለይለት በጨለማ ውስጥ ነው ያለነው፡፡
                                                               
   እኛ ግን ተስፋ አንቆርጥም! በአያያዝ ጉድለት የተለየንን ወገናችንን መመለስ እንፈልጋለን፡፡ ህዝቡ ለጊዜው ሪፈረንደም አድርጎ ነጻነቱን ማወጁን እናደግፋለን፡፡ ቢሆንም ህልም አይከለከለምና አንድ ቀን ተቀራርበን በጋራ ስለመስራት እንወያይ ይሆናል ብለን እናልማለን፡፡ የኛ ልጆች ደግሞ በኮንፌዴሬሽን ስለመስራት ያስቡ ይሆናል፡፡ የልጅ ልጆቻችን በፈቃደኝነት ስለመዋሃድ ያስቡ ይሆናል፡፡ በዚያን ጊዜም አሁን የምንመኘው በአንድነት ውብ የመሆን ሚስጢራችን ይመለስልናል ብለን እንመኛለን፡፡ ምን ይታወቃል? ለፈጣሪ የሚሳነው ነገር የለም፡፡

ወገኖቼ ደጉን ነው የተመኘሁት፡፡ በቅን ልቦና በርትተን ከጸለይንና ከኛ የሚጠበቀውን ካደረግን ሁሉንም የሚችለው ፈጣሪ ህልማችንን እውነት ያደርግልናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
-------
   ምን እንደጣለብኝ እንጃ! ያንን ምድር እጅግ ሲበዛ እወደዋለሁ፡፡ እኔ ለተወለድኩበትና አብዛኛውን ዕድሜዬን ለጨረስኩበት የምስራቅ ኢትዮጵያ ክልል ጎረቤት ከሆነችው ሶማሊያ ይልቅ በ1600 ኪ.ሜ. የምትርቀው አስመራ ናት የምትናፍቀኝ፡፡ ስለሶማሊያ የተጻፈ መጽሐፍ ማንበብ ብዙም አይማርከኝም፡፡ ስለ ኤርትራ የተጻፈ መጽሐፍ ካጋጠመኝ ግን ሳላየው አላልፍም (ይህ ግን ሶማሊያን ከመጥላት እንደማይቆጠርብኝ ተስፋ አደርጋለሁ)፡፡

    ታዲያ በርካቶቻችሁም እንደኔው ትመስሉኛላችሁ፡፡ ለምሳሌ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ሲታተም የቆየው የቤኒ አምሩን ወጣት የሚያሳየው ፖስተር ዛሬም ድረስ ከኛ ጋር ተሳስሮ ነው ያለው፡፡ አሁንም ድረስ በበርካታ ስፍራዎች ተለጥፎ አይቼዋለሁ፡፡ በፌስቡክም እርሱን እንደ ፕሮፋይል ፒክቸር የሚጠቀም ኢትዮጵያዊ ሞልቷል፡፡ በሌላ በኩል የኤርትራን ሙዚቃ የሚያዳምጡ ሰዎች በሽ ናቸው፡፡ ደራሲ መሐመድ ሳልማን መቐለ ሄዶ ያየው ነገር ቢያስገርመው “በኤርትራ ሙዚቃ የምትጨፍር ከተማ” የሚል አስደናቂ ወግ ጽፎ እውነቱን አስረድቶናል፡፡ መንግሥታት ቢጣሉ እንኳ ህዝቦች ምንጊዜም እንደሚነፋፈቁ ከዚህ በላይ የሚያስረዳ ዋቢ ያለ አይመስለኝም፡፡
--------
     ማርታ ሀይሉን አስታወሳችኋት? አዎን! ማርታን “ብራ… ነው… ብራ ነው”፤ “አዘዞ”፤ “ሎጋ ..ና እናውጋ” በተሰኙት ዘፈኖቿ እናውቃታለን፡፡ ከማርታ ዘፈኖች ዘወትር ቀልቤን ይገዛ የነበረው ግን የትግርኛ ዜማዋ ነው፡፡ አዝማቹ እንዲህ ይመስለኛል፡፡

 ካብ አስመራ ድንገት ርእዮ
ምጽዋ ገባሁ ልበይ ሕብዮ፡፡

እንተርጉመው እንዴ?… ግድ የለም ማርታ ራሷ እንዲህ እያለች በአማርኛ ተርጉማዋለች፡፡

“ከአስመራ ድንገት አይቼው
ምጽዋ ገባሁ ልቤን ሰጥቼው”፡፡

     አዎን! ትናንት የኛ ናት ስንላት ለነበረችው ኤርትራ ነው እንዲህ የዘመርንላት፡፡ ዛሬም ብንዘምርላት እንከበራለን እንጂ አንወቀስም፡፡ ምክንያቱም በመንግሥት ደረጃ ነው የተለያየነው፡፡ ሁለት ፓስፖርት እንዲኖረን ነው የተደረግነው፡፡ ሁለታችንም ግን አንድ ህዝቦች ነን፡፡ በደምም ሆነ በባህል በጣም የተዋሃድን የአንድ መሬት ብቃዮች ነን፡፡ ሁለታችንም የተዋብን የሴምና የኩሽ ህዝቦች ውቅር ነን፡፡ እንደኛ የሚያምር ህዝብ በትኛውም ዓለም የለም፡፡ የጀበና ቡና፣ ዶሮ ወጥ፣ ድፎ ዳቦ፣ የስጋ ፍትፍት፣ አምባሻ፣ ወዘተ…. ሁለታችን  ዘንድ ብቻ ነው ያለው፡፡
-----
    በርግጥ እላችኋለሁ፡፡  በምንባብና በወሬ እንጂ በአካል የማላውቃት ኤርትራ ትናፍቀኛለች! ያ በታሪክ ምዕራፎች “ምድሪ ባህረ ነጋሽ” እየተባለ ሲጠራ የኖረው ጀግና መሬትና ህዝብ ይናፍቀኛል፡፡ ያ የሰሜኑ በረኛ እያልን ስንመካበት የነበረው ህዝባችን ይናፍቃል፡፡

እውነትም ኤርትራ ! የዳማት ታሪክ ውቅር! የመጠራ አብያተ መንግሥታት ከርስ! የሀውልቲ ፍርስራሾች ቀብር! የአዱሊስና የዙላ ወደቦች መዘክር! የሱዋኪምና የዳህላክ ሱልጣኖች ደብር!

ኤርትራ የአብረሃ ደቦጭ ሀገር! የሞገሥ አስገዶም ሀገር! የዘርዓይ ደረስ ሀገር! የሎሬንዞ ታዕዛዝ ሀገር! የደጃች ሀረጎት ሀገር! በአይበገሬ ጀግንነታቸው ድፍን አፍሪቃን ያኮሩ አርበኞች የበቀሉበት ምድር!

ኤርትራ የበረከት መንግሥተ አብ ሀገር! የፀሐይቱ ባራኪ ሀገር! የአብረሃም አፈወርቂ ሀገር! የአሕመድ ሼኽ ሀገር! የሄለን መለስ ሀገር! የየማነ ባሪያው ሀገር! የሄለን ጳውሎስ ሀገር! በስርቅርቅ ድምጻቸው የሰውን ልብ እየሰረሰሩ የመግባት ሀይል ያላቸው የጥበብ ከዋክብት የወጡበት መንደር!

ኤርትራ የፊያሜታ ጊላይ ሀገር! የስዕላይ በራኺ ሀገር! የኦቦይ ተኽሌ ሀገር! የተክላይ ዘድንግል ሀገር! የሆቴል ፓራዲዞ ሀገር! የዕቁባይ ሲላ ሀገር! የምንወደው ደራሲያችን በዓሉ ግርማ በ“ኦሮማይ” መጽሐፉ እንደ ፊልም ግልጥልጥ አድርጎ እየተረከልን ዝንተ-ዓለም እንድንወዳት ያደረገን የቀይ ኮከብ ትዝታ ወመዘክር!

ኤርትራ የፊዮሪ ሀገር! የሳባ ሀገር! የማርቲና ሀገር! የብርኽቲ ሀገር! ፊያሜታ ጊላይን የመሳሰሉ “ሽኮሪናዎች”ን ያበቀለች ውብ የውቦች እመቤት!
-----
  ኤርትራን ስንጠራ በቅድሚያ ወደ አዕምሮአችን የምትመጣው አስመራ ናት፡፡ የአስመራ ናፍቆት ይገድላል፡፡ አስመሪና፣ አስመሪቲ፣ አቲ ጽብቕቲ!…

ውይ ስታምር! “ቀሽቲ” እኮ ናት፡፡ ያኔ በልጅ አዕምሮአችን በዘምባባ ጥላዋ ተሸክፋ በፖስትካርድ ስትቀርብልን “የኛ ውቢት” እያልን እንመጻደቅባት ነበር፡፡ እንቆቅልሽ ስንጫወትና መልሱ ጠፍቶን “ሀገር ስጠኝ” ስንባል እርሷን ለመስጠት እንሰስት ነበር፡፡ ጠያቂውም የዋዘ ስላልሆነ “አስመራ” ካላልነው ለጠየቀን ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ አይነግረንም ነበር፡፡ ከማናውቃቸው “ዋሽንግተን” እና ሮማ ይልቅ አስመራ ነበር የምትበልጥብን፡፡ በትምህርት ቤት መዝሙራችንም እንዲህ እንል ነበር፡፡

ኦኬ ኦኬ ኦኬ ስራ
ሰላም ሰላም ወደ አስመራ
አዲስ አስተማሪ ከጃፓን የመጣ
ማስተማሩን ትቶ በቦክስ የሚማታ
አናግረኝና አናግርሃለሁ
በአሜሪካ ሽጉጥ አዳፍንሃለሁ፡፡
አማርኛም አልችል ትግርኛም አልሰማ
ሰተት ብዬ ልግባ አስመራ ከተማ፡፡

ግጥሙ “አንታራም” የሚሉት የህጻናት ጨዋታ ዓይነት ነው፡፡ ነገር ግን አስመራ ከልባችን እንዳትጠፋ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ዛሬም በልባችን ነግሳለች አስመሪና!
 ----
አስመሪና! እቲ ሽኮሪና! ሰሜናይት ጽብቕቲ! በዓሉ ግርማ ላንቺ ክብር የጻፈው ትዝ ይልሻል? እስቲ እናስታውሰው!

አስመሪና አስመራዬ
ካብ ሐንቲ ንግሥቲ ይበልፅ መልክእኪ
አማአድዬ ክርእየኪ ከሎኹ ኽአ
አብ ኢደይ ዘሎ ነገር ይወድቕ፡፡

(አስመራ አስመራዬ)
(ከአንድ ንግሥት ይበልጣል መልክሽ)
(በሩቅ ሲያይሽ በውበቷ ስለተማረሽ)
በእጄ ያለ ነገር ሳይታወቀኝ ይወድቃል)
------
  ጸጸራት፤ ፎርቶ፣ ሐዝሐዝ፣ አርበእተ አስመራ፣ እምባጋሊያኖ፣ ኮምቢሽታቶ፣ አዲ ጓእዳድ፣ ቃኘው፣ ማይተመናይ፣ ሰምበላይ፣ ጎዳይፍ፣  ገጀረት፣ ወዘተ… በጽሑፍ የማውቃቸው የአስመራ ሰፈሮች ናቸው፡፡ አንድ ቀን በሆነልኝና ባየኋቸው እያልኩ አልማሁ፡፡  እነዚህ አስገራሚ የአስመሪና ሰፈሮች ብዙ ባለታሪኮችን አብቅለዋል፡፡ ብዙዎች ገድላቸው እየተደጋገመ ሲነገርላቸው እሰማለሁ፤ አነባለሁ፡፡ ለኛ ቅርብ የነበረ አንድ ውድ ልጅ እየተረሳ በመሆኑ ግን አዝኛለሁ፡፡
 
     አማኑኤል እያሱ ይባላል! አስታወሳችሁት አይደል? አዎን! አማኑኤል በኛ ዕድሜ ዘመን ኢትዮጵያ ዋንጫ መብላት እንደምትችል ያስመሰከረው የታላቁ የ1980 የእግር ኳስ ቡድናችን ቋሚ ተሰላፊ ነበረ፡፡ የማሊያ ቁጥሩ 2 ይመስለኛል፡፡ አማኑኤል የያኔው ቡድናችን ባደረጋቸው ሁሉም ጨዋታዎች ተሰልፏል፡፡ ቡድኑ ዋንጫውን ሲበላም ከጓደኞቹ ጋር ቤተመንግሥት ድረስ ተጋብዞ ተሸልሟል፡፡ አማኑኤልን ያስገኘው ከዚያ ዘመን ዝነኛ ቡድኖቻችን መካከል አንዱ የነበረው የኤርትራ ጫማ ቡድን ነው፡፡ ይህ ቡድን የኤርትራ አንደኛ ዲቪዚዮን ዋንጫን በተደጋጋሚ ያሸነፈ ነው፡፡
 
    አማኑኤል እያሱ በኢትዮጵያ ትቅደም አንደኛ ደረጃ ዋንጫም ለኤርትራ ክፍለ ሀገር ምርጥ ቡድንም ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ ባልሳሳት የ1981 የኢትዮጵያ ዋንጫን ያሸነፈው እነ አማኑኤል የነበሩበት የኤርትራ ክፍለ ሀገር ቡድን ነው፡፡ የአማኑኤል እያሱን ወሬ ለመጨረሻ ጊዜ ያነበብኩት በ1988 ለወዳጅነት ጨዋታ አዲስ አበባ መምጣቱን በማስመልከት በርካታ የግል ጋዜጦች ቃለ-መጠይቅ ባደረጉለት ጊዜ ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ መረጃው የለኝም፡፡ እስቲ የአስመራ ልጆች ወሬው ካላችሁ ስለአማኑኤል እያሱ አንድ ነገር በሉን፡፡
-----------------
አሁን ወደ ምዕራብ ኤርትራ ተሻግረናል! ባርካና ጋሽ የሚባሉት ቆላማ አውራጃዎች እዚህ ነው ያሉት፡፡ አቆርዳት፣ ተሰነይ፣ አሊጊደር፣ ኡምሐጀር፣ ባሬንቱ የተሰኙት ከተሞች በቆላው ምድር ውስጥ ተዘርግተዋል፡፡ ኩናማ፣ ናራ እና ቤጃ የሚባሉት ብሄረሰቦች እዚህ ነው የሚኖሩት፡፡ የአካባቢው ዋነኛው ህዝብ ግን ለኛ በጣም ቅርብ የሆነውን ሳቂታውን የቤኒ አምር ወጣት ያስገኘው የትግረ ህዝብ ነው፡፡

  የትግረ ህዝብ በውስጡ በርካታ ጎሳዎች አሉት፡፡ ከሁሉም የሚበረክተው ግን የቤኒ አምር ጎሳ ነው፡፡ ህዝቡ የሚነጋገርበት የትግረ ቋንቋ ከሴማዊ ቤተሰብ ነው የሚመደበው፡፡ ለዚህ ቋንቋ በጣም የሚቀርበው በደጋው ኤርትራና በኛዋ የትግራይ ክልል የሚነገረው ትግርኛ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ቋንቋዎች ከጥንታዊው የግዕዝ ቋንቋ ነው የተወለዱት፡፡ የትግረ ቋንቋን ከ35 በመቶ የማያንሰው የኤርትራ ህዝብ ይናገረዋል፡፡ “ትግረ” ከኤርትራ ሌላ በሱዳንም (ከሰላ አካባቢ) በስፋት ይነገራል፡፡

ትግረና ትግርኛ በጣም ከመመሳሰላቸው የተነሳ እንግዳ ለሆነ ሰው አንድ ዓይነት ቋንቋዎች ሊመስሉት ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም ለትግርኛ ተናጋሪዎች የትግረ ቋንቋን መልመድ በጣም ቀላል ነው ይባላል፡፡ የትግረ ተናጋሪም ትግርኛን በቶሎ መልመድ ይቀለዋል፡፡ በመሆኑም ከጠቅላላው የኤርትራ ህዝብ 50% የሚሆነው ሁለቱንም ቋንቋዎች መናገር ይችላል (ይህ ቁጥር ትግርኛ ብቻ የሚናገሩትን፣ ወይንም “ትግረ” ብቻ የሚናገሩትን አይጨምርም)፡፡

 ምዕራባዊው ቆላ ኤርትራዊያን በጣም የሚያደንቋቸውን እንደ ሃሚድ ኢድሪስ አዋቴ፣ ሙሐመድ ኢድሪስ እና ኢድሪስ ገላውዴዎስን ያፈራ መሬት ነው፡፡ በዚህ ሰሞን ልቤን ያሸፈተው የትግረ ልጅ ግን “አሕመድ ሼክ” ነው፡፡ አሕመድ ሼክን አወቃችሁት አይደል? አዎን! “ባቡሬይ”፣ “ኢላ ሰርጎ” ወዘተ.. እያለ በማይጠገበው የትግረ ምት የሚያዜመው ተወዳጅ ድምጻዊ ነው፡፡ አንድ ኤርትራዊ ወዳጃችን “ኤላ ሰርጎ”ን ሲፈታልን `ከጀርባው ፌሎሶፊ አለው” ነው ያለኝ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡
 
   የትግረ ሴት ለምትወደው አንድ ሰው (ለባሏ) እንጂ ለማንም ጸጉሯን አትገልጠውም፡፡ ስለዚህ ጉብሊቷን ልጅ የወደደው አሕመድ ሼክ በተዋቡ ግጥሞች እያወደሳት ዘፈነላትና ፍቅሩ ልቧ ውስጥ ዘልቆ መግባቱን ለማረጋገጥ ጸጉሯን ማየት ጀመረ፡፡ እርሷም ግጥሞቹን ከሰማችለት በኋላ ጸጉሯን ገልጣ አሳየችው፡፡ ድል አድራጊው ወዲ ሼክም ይዟት በረረ፡፡ “ኤላ ሰርጎ! ኤላ ሰርጎ” እያለ ነጎደ!
------
ሰሜን ኤርትራ!

ተወዳጇ የከረን ከተማ እዚህ ነው ያለችው! የሀረርጌዋ የድሬ ዳዋ ከተማ መንትያ እህት የምትመስለው ውቢቷ የሰሜን ፈርጥ! በቪዲዮ አይቻት ውበቷን አደነቅኩላት! አበቦቹ! ቤቶቹ! መንገዶቹ ሁሉም ውብ ናቸው፡፡ ከትግራይ የተገኘው ዝነኛው ብርሃነ ሃይለ አንድ ላይ በነበርነበት ዘመን ለከረኗ ጉብል እንዲህ ብሎላታል፡፡

ሸው በሊ ብለነይ ብለነይ
ዝለሊ ብለነይ ብለነይ
አሊሊ ብለነይ ብለነይ
አቲ ጓል ከረነይ ብለነይ

አዎን! ቢለን ከከረን ከተማ ጋር ስሙ የሚጠቀስ ብሄረሰብ ነው፡፡ ቋንቋው ከኛው የአገው ቋንቋ ጋር አንድ ዐይነት ነው፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ነው አንባቢ ሊመራመር የሚገባው፡፡ በወሎና በጎጃም የሚኖረው አገው ምን ሊያደርግ እዚያ ሄደ?… መቼ ነው እዚያ የሄደው?… መላምት ከመዘብዘብ በስተቀር ማንም ሰው ይህንን እንቆቅልሽ በሚያመረቃ ሁኔታ ሊፈታው አልቻለም፡፡ ኤርትራና እኛ አንድ ነን የሚያሰኘኝ እንዲህ ዓይነት ተጨባጭ ማስረጃ ስላለን ነው፡፡
  
  ቢለን ውብ ባህል ያለው ህዝብ ነው፡፡ በዚህ ህዝብ ባህል መሰረት ሴቶቹ ካገቡ በኋላ ጸጉራቸውን መሰተር ግድ ነው፡፡ ህዝቡ የቢለን ቋንቋ ተናጋሪ ቢሆንም የትግረ ቋንቋንም ይጠቀማል፡፡ ትግርኛም በስፋት ይነገራል፡፡ በጣም ታዋቂ የሆነው የቢለን ተወላጅ “ዑመር እዛዝ” ነው፡፡ የጀብሃ ጦር ከመፍረክረኩ በፊት የሁለተኛው ዞን አዛዥ እንደነበረ ከዚህ በፊት ጽፌ ነበር፡፡

  ከከረን ሽቅብ ወደ ሰሜን ስናመራ ታሪካዊቷ አፋቤት አለች፡፡ ጄኔራል ታሪኩ አይኔ የሚመራው ናደው እዝ እዚህ ነበር የሰፈረው፡፡ የቀይ ኮከብ ዘመቻ ዋና አምባም ይህ ነበር፡፡ ከአፋቤት ወደ ሰሜን ስንበር ንዳዳማውና አስቸጋሪው የሳህል መሬት አለ፡፡ በሳህል እምብርት ላይ የኤርትራ ገንዘብ መጠሪያ ለመሆን የበቃችው “ናቅፋ” አለች፡፡ በዓሉ ግርማ እንደተረከልን ከሆነ ሳህል ማለት እሳት ነው፡፡ ነገር ግን ሰዎች ይኖሩበታል፡፡ ከብቶች ይሰማሩበታል፡፡ ተክልም ይበቅልበታል፡፡ እዚህ አካባቢ በብዛት የሚኖረው ህዝብ “ረሺዳ” ይባላል (አንዳንዶች “ራሻይዳ” ይሉታል፤ ስህተት ነው፤ ትክክለኛው አጠራር “ረሺዳ” ነው)፡፡

  የ“ረሺዳ” ህዝብ ከሌላው የኤርትራ ህዝብ የሚለይበት በርካታ ነገሮች አሉት፡፡ ለምሳሌ ይህ ህዝብ ከሳዑዲ ዐረቢያ ተነስቶ ወደ ኤርትራ የገባው በቅርብ ዘመን (በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ) ነው፡፡ በዚያ ወቅት የአሁኗ ሳዑዲ ዐረቢያ አልነበረችም፡፡ ሀገሩ ሁሉ በጎሳዎች የተከፋፈለ በረሃማ ምድር ነበር፡፡ ከነዚህ ጎሳዎች አንዱ አል-ረሺድ ይባላል፡፡ ይህ የአል-ረሺድ ህዝብ የአካባቢው የበላይ እንዲሆን በኦቶማን ቱርክ ተወሰነ፡፡ አብዛኛው ህዝብም ለነርሱ አደረ፡፡ “አል-ሱዑድ” የሚባለው ቤተሰብ ግን “አሻፈረኝ” አለ፡፡ “ራሴ በረሃውን ጠቅልዬ መግዛት ስችል ለምን በአል-ረሺድ ጎሳ የበላይነት አድራለሁ” በማለት አንገራገረ፡፡ በሁለቱ መካከል ጠብ ተነሳ፡፡ በመጀመሪያው ላይ የአል-ረሺድ ጎሳ አሸነፈ፡፡ አል-ሱዑዲዎች ወደ ኢራቅ ሸሹ፡፡

   ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን የአል-ሱዑድ ቤተሰብ በእንግሊዞች ደጋፊነት ራሱን አጠናክሮ መጣ፡፡ በአል-ረሺድ ጎሳ ላይም ድልን ተቀዳጀ፡፡ በዚህም የተነሳ የዐረቢያ በረሃ ለአል-ረሺድ ጎሳ አባላት ሲኦል ሆነ፡፡ ረሺዳዎች እየተያዙ በጅምላ ታረዱ፡፡ ንብረታቸው ተዘረፈ፡፡ በፊት ይረዳቸው የነበረው የቱርኮች መንግሥት በራሱ ችግር በመወጠሩ ምንም ሊያደርግላቸው አልቻለም፡፡ በመሆኑም ከእልቂቱ ለመዳን ሲሉ ባህር እያቋረጡ ወደ አፍሪቃ ምድር ተሰደዱ፡፡ በሱዳንና በኤርትራ መኖሪያቸውን ቀለሱ፡፡

እንግዲህ ረሺዳዎች ከዘር ማጥፋት ወንጀል ለመሸሽ ወደ ኤርትራ የመጡ ተፈናቃዮች ናቸው ማለት ነው፡፡ በኤርትራ ውስጥ ንጹህ የዐረብ ዝሪያ የሚባሉት እነርሱ ናቸው፡፡ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውም ዐረብኛ ነው፡፡ በዚህ ህዝብ ባህል መሰረት ለአካለ መጠን የደረሰች ማንኛዋም ሴት ፊቷንም ሆነ ጸጉሯን መሸፈን ግዴታዋ ነው፡፡ በዓሉ ግርማ በኦሮማይ ውስጥ ሲተርክልን “ማንኛውም የረሺዳ ባል የሚስቱን ፊት ገልጦ የሚያይበትን ሰው አይፈልግም” በማለት የተናገረውም የባህላቸው አንድ አካል ነው፡፡
-------
አሁን ወደ ምስራቅ ኤርትራ ተሻግረናል፡፡ ብርኽቲ የሆነችው ምጽዋ እዚህ ነው ያለችው፡፡ ብርሃነ ሃይለ “ሸው በሊ ብለነይ” የተሰኘውን ዘፈን ሲቀጥል ምጽዋን እንዲህ ይላታል፡፡

“አብ ዋሊድ ማሳዋ
ኩለ ሊየን ሒልዋ”
 
   ትርጉሙን በትክክል ባላውቀውም “የምጽዋ ልጆች ሁሉም ጣፋጭ ናቸው” የሚል መልዕክት እንዳዘለ ይገባኛል፡፡ የምጽዋ ልጆች ቆንጆ ናቸው ተብሎ እየተደጋገመ ተነግሮላቸዋል፡፡ ከወደብ ከተማ የተገኙ በመሆናቸው ዓለም አቀፍ ስልጣኔና ልዩ ልዩ ባህሎች በነርሱ ላይ ሲነፍስ ይታያል፡፡

  ምጽዋ በጣም ውብ ናት፡፡ በተለይም ኪነ-ህንጻዋ ብዙ ተብሎለታል፡፡ ከዑስማናዊያን ቱርኮች ዘመን ጀምሮ ብዙ ገዥዎች ሲፈራረቁባት የነበረች መሆኗ በከተማዋ የሚታየውን ኪነ-ህንጻ እንዳሳመረው ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
  
ኤርትራዊያን ምጽዋን ይወዷታል፡፡ እኛም እንወዳታለን፡፡ ነገር ግን ወደዚያ ለመድረስ የሚሻ ሰው እንደ እሳት የሚፋጀውን ሙቀቷን መቻል አለበት-ከተማዋ በዓለም ላይ ከፍተኛ ሙቀት ካላቸው ስፍራቸው አንዷ ናትና፡፡ የዚህች ከተማ ህዝብ ኑሮውን ከአየር ጸባዩ ጋር እንዲጣጣም አድርጎ ቀይሶታል፡፡ በመሆኑም አብዛኛው የንግድ እንቅስቃሴ የሚከናወነው ከምሽት እስከ እኩለ ሌሊት ባለው ጊዜ ነው፡፡ ታዲያ ከተማዋ ለዘወትር እንደጋለች አትቀርም፡፡ በዓመት ሁለት ጊዜ ሙቀቱ ጋብ ይልና ጤናማው አየር ይነፍስባታል፡፡ ይህም ከጥር-የካቲት ባለው ጊዜ እና በሀምሌ ወር ነው፡፡ በነዚህ ወራት ከተማዋን የሚጎበኘው ቱሪስት በጣም ይጨምራል፡፡ በቀድሞው ዘመን ቀዳማዊ ኃይለሥላሤም ከተማዋን ለመጎብኘት የሚመጡት በነዚህ ወራት ነው (እርሳቸው ያሰሩት ቤተ-መንግሥት እስከ አሁን ድረስ አለ)፡፡

     ምጽዋ በወደብነት አገልግሎት መስጠት የጀመረችበት ዘመን በትክክል አይታወቅም፡፡ የታሪክ ምሁራን እንደሚሉት ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በአካባቢው ከተማ ቀመስ ሰፈራ ነበር፡፡ ይሁንና እስከ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ እንደ ወደብ ሲያገለግሉ የነበሩት ከምጽዋ አጠገብ የነበሩት ጥንታዊያኑ “ዙላ” እና “አዱሊስ” ነበሩ፡፡ የምጽዋ ተፈላጊነት ጉልህ ሆኖ የተከሰተው የባህር መደቡ በ1508 በዑሥማናዊያን ቱርኮች (Ottoman Turks) በተያዘበት ወቅት ነው፡፡ ከቱርኮቹ በማስከተልም ግብጾችና የኢጣሊያ ወራሪዎች ተፈራርቀውባታል፡፡

   ኢትዮጵያና ኤርትራ በፌዴሬሽን ከተዋሃዱ በኋላ ምጽዋ ከፍተኛ እመርታ ማሳየት ጀምራ ነበር፡፡ ከ1970ዎቹ መግቢያ ጀምሮ ግን የጦርነት ቀጣና ሆነች፡፡ የሻዕቢያ ሀይሎችና የኢትዮጵያ ሰራዊት ከፍተኛ እልቂት የተፈጸመባቸውን ጦርነቶች አካሂደውባታል፡፡ በተለይም በ1982 (እ.ኤ.አ. 1990) በተካሄደው ጦርነት ከሁለቱም ወገን በአስር ሺህ የሚቆጠር ሰራዊት መርገፉን ሁኔታውን በቅርበት የተከታተሉ ወገኖችና የዐይን ምስክሮች ገልጸዋል (የሀምሳ አለቃ ታደሰ ቴሌ ሳልባኖን “አይ ምጽዋ” አስታውሱት)፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያምም “ለከፍተኛ ሽንፈትና ኪሳራ የዳረገን ውድቀት ያጋጠመን በምጽዋ ነው” በማለት ተናግረዋል፡፡

የድሮው ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) የአሁኑ “ህዝባዊ ግንባር ንዴሞክራሲን ንፍትሒን” (ህግዴፍ) ምጽዋን የተቆጣጠረበትን ዘመቻ “ኦፕሬሽን ፈንቅል” በማለት ይጠራዋል፡፡ ምጽዋ የተያዘችበት ዕለትም (የካቲት 20) በየዓመቱ ይከበራል፡፡ በርካታ ህዝብ ወደ ምጽዋ ከሚጎርፉባቸው ዕለታት መካከልም አንዱ ይህ “የኦፕሬሽን ፈንቅል” መታሰቢያ የሚከበርበት ቀን ነው፡፡

ምጽዋ የብዙ ህዝቦች መኖሪያ ናት፡፡ ዋነኞቹ ነዋሪዎች ግን የአሳውርታ፣ ሳሆ፤ እና አፋር ብሄረሰቦች ተወላጆች ናቸው፡፡ በከተማዋ በዋናነት የሚነገረው ቋንቋ ዐረብኛ ነው፡፡ የሻዕቢያ መስራች ተብሎ የሚታወቀው ዑሥማን ሳልህ ሳቤ የተወለደው በምጽዋ አጠገብ ካለችው ሂርጊጎ የተባለች አነስተኛ መንደር ነው፡፡ ኢብራሂም አፋ፣ ረመዳን መሐመድ ኑር እና ዓሊ ሰዒድ አብደላን የመሳሰሉት የህግሓኤ (ሻዕቢያ) እውቅ ኮማንደሮችም የምጽዋ ልጆች ናቸው፡፡ 

  ከምጽዋ ወደብ ዝቅ ብሎ ጥንታዊቷ የአዱሊስ ወደብ ትገኛለች፡፡ ይህች የወደብ ከተማ ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ የተጓዦች መግቢያና መውጪያ ነበረች፡፡ የጥንቱ ሮማዊያንና ግሪኮችም በደንብ ያውቋታል፡፡ አጼ ካሌብ ወደ ደቡብ ዐረቢያ ሲዘምት ወታደሮቹን በመርከብ ያስጫነው ከዚህች የወደብ ከተማ ነው፡፡ በሀገራቸው ከፍተኛ በደል ያጋጠማቸው የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ተከታዮች ከጥቃቱ ለመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በአዱሊስ በኩል ነበር ያለፉት፡፡ ሌላም ብዙ ታሪክ ተስተናግዶአል-በአዱሊስ፡፡
---------
ከምጽዋ ወደ መሀል ኤርትራ ለመጓዝ መንገዱን ስንጀምር በቅድሚያ የምናገኘው የሳሆ ህዝብን ነው፡፡ ይህ ህዝብ በስተደቡብ በኩል ከሚጎራበተው የአፋር ህዝብ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የኢኮኖሚ መሰረት አለው፡፡ ሁለቱም በከብት እርባታ ነው የሚተዳደሩት፡፡ ሁለቱም ኩሻዊ ቋንቋ ነው የሚናገሩት፡፡ በአለባበስ ግን ሳሆን ከአፋር በቀላሉ መለየት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የሳሆ ተወላጅ የሆነ ሰው አፋሮች የሚታጠቁትን “ጊሌ” የሚባለውን ረጅም ቢላዋ አይታጠቅም፡፡ የሳሆ ሰው የሚያሸርጠው ሽርጥም ከአፋር ሽርጥ ረዘም ይላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሳሆ ብዙ ጊዜ ከእጁ ጦር አያጣም፡፡ ታዲያ የሳሆ ቋንቋ በትግራይ ክልል ምስራቃዊ ዞን የሚኖረው የኢሮብ ህዝብ ከሚናገረው ቋንቋ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ኢሮብና ሳሆ የሚለያዩት በሚከተሉት እምነትና በኢኮኖሚ መሰረታቸው ነው፡፡ ሳሆ ሙሉ በሙሉ የእስልምና እምነት ተከታይ ነው፡፡ ኢሮብ ግን በአብዛኛው ክርስቲያን ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የሚበዙትም ካቶሊኮች ናቸው፡፡ በሌላም በኩል የኢሮብ ህዝብ አራሽ ገበሬ ይበዛዋል፡፡ ከላይ እንደተገለጸው የሳሆ ህዝብ በከብት እርባታ ነው የሚተዳደረው፡፡

ሳሆን ስናልፍ ደግሞ ትግርኛ ተናጋሪው ህዝብ በስፋት የሚኖርባቸውን የአከለ ጉዛይ፣ ሰራዬ እና ሐማሴን አውራጃዎችን እናገኛቸዋለን፡፡ በኤርትራ ውስጥ ካሉት ብሄረሰቦች መካከል ብዙ ቁጥር ያለው (50 % የሚሆነው) ይህ ትግርኛ ተናጋሪ ህዝብ ነው፡፡ ይህ ህዝብ በባህሉም ሆነ በቋንቋው ከኛው የትግራይ ህዝብ ጋር ይመሳሰላል፡፡ ህዝቡ በአብዛኛው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ መሆኑም ከትግራይ ህዝብ ጋር ያመሳስለዋል፡፡ ይሁንና ቋንቋው ባለፉት በርካታ ዘመናት ከጣሊያንኛ፣ ከዐረብኛ እና ከትግረ ቋንቋዎች ጋር በመወራረሱ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚነገረው ትግርኛ የተለየ ዘዬ ሊሆን በቅቷል፡፡

አጅግ በርካታ የሆኑ የኤርትራ ከተሞች ያሉት በዚህ ክልል ነው፡፡ ጊንዳዕ፣ ሐሙሲት፣ ሰገነይቲ፣ ደቀምሐረ፣ መንደፈራ (አዲ ዑግሪ)፣ አዲኳላ፣ ሰንዓፈ፣ ደባሩዋ ወዘተ… እዚህ ነው የሚገኙት፡፡ በመሀከላቸው ደግሞ አስመራ ጉብ ብላ ትታያለች፡፡ ከከተሞቹ መካከል የሚበዙት በጣሊያን ዘመን የተቆረቆሩ ናቸው፡፡ በሰራዬና በአከለ ጉዛይ አውራጃ ውስጥ ግን የጥንቱ የአክሱም ዘመነ መንግሥት ታዋቂ ከተሞች የነበሩትን እንደ “ሀውልቲ” እና “መጠራ” የመሳሰሉ መንደሮችን ማግኘት ይቻላል፡፡ በነዚህ ከተሞች ፍርስራሽ ስር ገና ያልተነካ ድልብ የአርኪዮሎጂ ሀብት አለ፡፡ ወደፊት ቆፈረን የምናወጣቸውን ማቴሪያሎች የህዝቦቻችንን አንድነት የሚመሰክሩ ቋሚ ቅርሶች አድርገን ልጆቻችንን እናስተምራለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ 
-------
ኤርትራን በኢትኖግራፊ ጉዞ እንዲህ ቃኝተናታል፡፡ ነገር ግን በዚሁ አናበቃም፡፡ ወደፊትም በተሻለ ዝግጅት ተመልሰን እንዘይራታለን፡፡ ለአሁኑ በዚሁ ይብቃን!!
ሰላም!!
-----
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 30/2006
-----
The writer, Afendi Muteki, is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia. You may follow him on his facebook page. Just click this link