ጥንቅር፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
“ኢዴሐቅን ከለንደኑ ኮንፈረንስ ለማስቀረት የተናገሩት ምክንያት “ኢዴሐቅ ጦር
የለውም” የሚል ነበር፤ ኢዴሐቅን ከሽግግር መንግሥቱ ምስረታ ኮንፍረንስ ሲያስቀሩ እንደምክንያት የተናገሩት ደግሞ “ኢዴሐቅ በጊዜያዊ
መንግሥቱ ላይ ጦርነት አውጇል” የሚል ነው፡፡”
አቶ መርሻ ዮሴፍ የኢዴሐቅ ሊቀመንበር እና የኢህአፓ ከፍተኛ የአመራር አባል
(ኢትዮጵያን ሪቪው መጽሔት፣ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 1992)
*****
“በኢትዮጵያና በኤርትራ
መካከል ግጭት የለም፡፡ ግጭት አለ ከተባለ በትምክህተኞች ጭንቅላት ውስጥ ነው”
አቶ መለስ ዜናዊ፣ የኢፌዴሪ
ጠቅላይ ሚኒስትር እፎይታ መጽሔት “በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ግጭት ተፈጥሯል ይባላል” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ የተናገሩት (እፎይታ
መጽሔት፤ ጥር 1990)
*****
“በእኛ ሀገር እውቀት
ከስልጣን ይመነጫል”
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም፣ (የብራና ማህደር፣ ሚያዚያ 1985)
*****
“የኢትዮጵያን ባንዲራ እንኳንስ እኛ ግመሎቻችን ያውቋታል”
ሱልጣን ዓሊ ሚራህ፤ የአፋር ህዝብ መንፈሳዊ አባት (አፍሪካ ቀንድ
መጽሔት፣ የካቲት 1985)
*****
“ከባድመ ወጣን ማለት ጸሀይ ጠፋች ማለት ነው፡፡ ጸሀይ ለዘላለሙ
ጠለቀች ማለት ነው”
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ (የኤርትራ ሬድዮ፣ ህዳር
1991)
*****
“የዘመናት የህዝብ ብሶት
የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን የአዲስ አበባን ሬድዮ ጣቢያ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ተቆጣጥሮታል”
በቅጽል ስሙ ላውንቸር
በሚል የሚታወቀው የኢህአዴግ ታጋይ (የኢትዮጵያ ሬድዮ፣ ግንቦት 20/1983)
*****
“የኢህአዴግን ልብ እንኳን
ሰው እግዚአብሔርም አያውቀውም፤ ሳይንስም አልደረሰበትም”
ዶ/ር መረራ ጉዲና
(ጦቢያ መጽሔት፤ ህዳር 1992)
*****
“ኢትዮጵያዊ ለመሆን
መደራደር እንፈልጋለን”
አቶ ሌንጮ ለታ ፣ በወቅቱ
የኦነግ ም/ሊቀመንበር (ሳሌም መጽሔት፣ ነሐሴ 1984)
*****
“የግንቦት ሀያው ድል
የመጨረሻዋን ጥይት በአዲስ አበባ ላይ የተኮሱት የኢህአዴግ ታጋዮች ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያዋን ጥይት በአሲምባ የተኮሱት የኢህአፓ
ታጋዮች ጭምር ነው”
አቶ ያሬድ ጥበቡ ፤ የኢህዴን መስራችና ሊቀመንበር የነበሩ (መስታወት መጽሔት
ጥቅምት 1985)
*****
“ስዬ፣ ክንፈ እና መለስ
በየተራው ወደኔ እየመጡ “እመን፤ አለበለዚያ ልጆችህን ፊትህ እንገድላቸዋለን” እያሉ ህሊናዬን ሲያስጨንቁት ምን ላድርግ?… ለልጆቼ
ደህንነት ስል ያልሰራሁትን ሰራሁ ብዬ ከማመን በስተቀር ምንም ምርጫ አልነበረኝም”
አቶ ታምራት
ላይኔ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል ፍርድ ቤት ቀርበው ከተናገሩት (ጎህ መጽሔት ሚያዚያ 1993)፣
*****
“የሆነ ነፋስ ነው የሰጣችሁ
እንጂ ሰርታችሁ ያመጣችሁት ውጤት አይደለም፡፡ ህዝቡን አሳስታችሁ ነው ይህቺን ታክል ያገኛችሁት፡፡ ቢሆንም አሁንም ያሸነፍነው እኛ
ነን”
አቶ በረከት ስምኦን፣ በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትርና የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ
ኮሚቴ ኃላፊ የነበሩ፣ ተቃዋሚዎች በምርጫ-97 ያገኙትን ውጤት በማስመልከት ከተናገሩት (በበርካታ ፕሬሶች ላይ ታትሞ ነበር፣ ግንቦት
1997)
*****
“ኢህዴን (ብአዴን) የሕወሐት የአማርኛ ዲፓርትመንት ነው”
አቶ አብርሃም ያየህ (የብራና ማህደር፣ ሚያዚያ 1985)
*****
“እኛ ታሪክ ይቅርና
ጦርነት መስራት እንችላለን”
በሽግግሩ ዘመን የመከላከያ
ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ (አባባሉ በብዙ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ቢታይም አቶ ስዬ እንዲህ ያሉበትን አጋጣሚ በትክክል
ለማወቅ አልቻልኩም)
*****
“የኦሮሞ ህዝብ ግንድ
ነው፡፡ ቅርንጫፍ እንጂ ግንድ አይገነጠልም”
አቶ ቡልቻ ደመቅሳ (ኢትኦጵ መጽሔት፤ መጋቢት 1996)
*****
“ያለምንም ማጋነን ለኢትዮጵያ
ህዝብ ብዙ ነገር አድርገንለታል፡፡ የመሬት አዋጁን ያወጅነው እኛ ነን፡፡ ለሙስሊሙ ህዝብ የሃይማኖት በዓሉን በብሔራዊ በዓል ደረጃ
አውጀንለታል፡፡ ለክርስቲያኑም ጥበቃ አድርገናል”
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ (ሳሌም መጽሔት፣
ጥር 1985)
*****
“ኢትዮጵያ በታሪኳ ጦርነት አሸንፋ አታውቅም”
አቶ ዳዊት ዮሐንስ ፣ የቀድሞ አፈ-ጉባኤ (ምኒልክ መጽሔት ፤ ታህሳስ 1992)
*****
“ከእንግዲህ እግርህ ቢቆረጥስ ምንድነው? ማራቶን አትሮጥበት፡፡ አንተ በጊዜህ
ለሀገርህ ሁሉንም አድርገሃል፡፡ ከአሁን በኋላ እግር ብዙም ላያስፈልግህ
ይችላል፡፡ ስለዚህ አንገትህን አትድፋ፡፡ ኮራ ነቃ በል”
ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለ
ማሪያም ጥላሁን ገሰሰ እግሩን ከተቆረጠ በኋላ ስልክ ደውለው ሲያነጋግሩት (ኢትኦጵ ጋዜጣ፤ የካቲት 1997)
*****
“ይህ ያለቀለት ጨዋታ ነው፡፡ በቃ! አንድ መንግስት አዲስ አበባ
ታቆማለህ፡፡ አንድ መንግሥት በአስመራ ታቆማለህ፡፡ ይህንን አምነን መቀበል አለብን፡፡ የኛ ሰው ትልቁ ችግር እውነት አምኖ ለመቀበል
አለመቻል እና የሚያምንበትን በግልጽ አለመናገር ነው፡፡ እኛ ግን የኤርትራ ጥያቄ በዚሁ መልኩ እንደሚፈታ ግልጽ ሆነን እንናገራለን”
አቶ ተፈራ ዋልዋ በዋሽንግተን
ዲሲ ለተሰበሰቡ ኢትዮጵያዊያን (አባባሉ የተሰማው ኢህአዴግ ስልጣን ከመያዙ በፊት በአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ በ1982 ባሰራጨው አንድ
ዝግጅት ነው፡፡ እኔ እዚህ የጻፍኩት ግን ከኢትኦጵ መጽሔት የመስከረም 1997 እትም ወስጄው ነው)
*****