Sunday, January 21, 2018

ስለ“አዳል” በጥቂቱ




(አፈንዲ ሙተቂ)
------
በመካከለኛው የታሪክ ዘመን (Medieval Era) ኢትዮጵያን፣ ኤርትራን፣ ጅቡቲን፣ ሶማሊላንድን እና ሶማሊያን በሚያቅፈው የአፍሪቃ ቀንድ ቀጣና የተለያየ ቅርጽና አወቃቀር የነበራቸው መንግሥታት ተመሥርተዋል፡፡ ከነዚያ መንግሥታት መካከል ከአስር የማያንሱት የሙስሊም ሱልጣኔቶች ነበሩ፡፡ ከሱልጣኔቶቹ መካከል ስሙ በጣም ገንኖ የነበረውና በአፍሪቃ ቀንድ ሕዝቦች ታሪክ፣ ጂኦ-ፖለቲካ እና የህዝቦች ስብጥር ላይ መጠነ-ሰፊ አሻራ ትቶ ያለፈው ደግሞ ዋና ከተማውን በዘይላ እና በሀረር ያደረገው የአዳል ሱልጣኔት ነው። እንግዲህ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈው የዚያ ሱልጣኔታዊ መንግሥት ታሪክ ነው፡፡
               
የአዳል ሱልጣኔት ታሪክ ከሌሎች ታሪኮች ጋር ተዳብሎ ሲጻፍ ተመልክተናል፡፡ ይሁን እንጂ ሙሉ ትኩረታቸውን በሱልጣኔቱ ታሪክ፣ ጥንታዊ ባህል፣ ትውፊቶችና ቅሪቶች ላይ ያደረጉ መጻሕፍት በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የአዳል ሱልጣኔትን ታሪክ በተናጥል ለመጻፍ የጣሩት ከሶስት የማይበልጡ ደራሲዎች ብቻ ናቸው (ዝርዝሩ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ በሰፊው ቀርቧል)፡፡

   እነዚህ ጥቂት ሥራዎች የአዳል ሱልጣኔትን ታሪክ በማሳወቅ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ ነገር ግን ድርሰቶቹ ብዙኃኑ የሀገራችን ተደራሲ በማያነበው የዐረብኛ ቋንቋ ነው የተጻፉት፡፡ በሁለተኛ ደረጃም መጻሕፍቱ በቀላሉ ተፈልገው የሚገኙ አይደሉም፡፡ እንግዲህ የአዳል ሱልጣኔትን ታሪክ በተናጥል እንድጽፈው ያነሳሳኝ ቀዳሚ ነጥብ በዘርፉ ያሉን ድርሰቶች ውስን መሆናቸውና እስከ አሁን የተጻፉትም ከታሪኩ ባለቤቶች ዘንድ በሰፊው አለመድረሳቸው ነው፡፡

    በሌላ በኩል ከላይ የተጠቀሱት መጻሕፍትም ሆኑ ሌሎች ድርሰቶች ያልዳሰሷቸው የሱልጣኔቱን ታሪክ የሚመለከቱ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሱልጣኔቱ የተመሠረተበት ታሪካዊ ዳራ (historical background) በጽሑፍ ምንጮች በደንብ አልተፈተሸም፡፡ ለአዳል ሱልጣኔት ምሥረታ መንስኤ የሆኑ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችም በወጉ አልተዳሰሱም፡፡ እንደዚሁም ደግሞ በርካታ ጸሐፍት ሱልጣኔቱ በተማከለባቸው ግዛቶች የሚኖሩት ህዝቦች የሚናገሯቸውን ትውፊቶች በጽሑፍ ከሚታወቀው ታሪክ አንጻር ለመመዘን ሲጥሩ አይታዩም፡፡ ይህንን መጽሐፍ እንድጽፍ የቀሰቀሰኝ ሁለተኛ ነጥብም ከአዳል ታሪክ ጋር መነሳት ያለባቸው በርካታ አንኳር ጉዳዮች ከግራና ከቀኝ በደንብ አለመዳሰሳቸው፣ እንደዚሁ ደግሞ በጽሑፍ ምንጮች ያልተወሱና የአዳል ሱልጣኔት ታሪክ ግንዛቤአችንን ሊያጎለብቱ የሚችሉ ርካታ ጉዳዮች መኖራቸው ነው፡፡  

  በሶስተኛ ደረጃ መወሳት ያለበት በሱልጣኔቱ ታሪክ አጻጻፍ ላይ የሚታየው ከፍተኛ ጉድለት ነው፡፡ የተለያዩ ደራሲዎች ስለሱልጣኔቱ ታሪክ የጻፏቸው ዘገባዎች በአብዛኛው ወገናዊነት ያጠቃቸዋል፡፡ ወገናዊ ካልሆኑት ጸሐፊዎች መካከል ደግሞ አንዳንዶቹ ታሪካዊ መረጃዎችን በአግባቡ አያሰፍሩም፡፡ አንዳንዶቹ ደራሲዎችም የሰበሰቧቸውን የቃልና የጽሑፍ መረጃዎችን በደንብ አይተነትኑም፡፡ የአዳልን ታሪክ ለማጥናት ያነሳሳኝ ሳልሳይ ነጥብም በሱልጣኔቱ ታሪክ አጻጻፍ፣ የመረጃ ትንታኔ እና የታሪክ ምዝገባና አስተምህሮ ዐውዶች (historiography) ላይ የሚታዩት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ናቸው፡፡

  እነዚህንና ሌሎችንም አስፈላጊ ነጥቦች እንደ መነሻ በማድረግ በሱልጣኔቱ ታሪክ ላይ ያተኮረ ጥናት በተለያዩ ዘዴዎችና በልዩ ልዩ አካባቢዎች ሳከናውን ከቆየሁ በኋላ ይህንን መጽሐፍ አዘጋጅቼአለሁ፡፡
***** 
   አሁን የምታነቡት መጽሐፍ ለብቻው ከላይ የዘረዘርኳቸውን ክፍተቶች ያሟላል ብዬ ለመናገር አልደፍርም፡፡ በአዳል ሱልጣኔት ታሪክ አጻጻፍ ላይ የሚታዩት ዘርፈ-ብዙ ችግሮች በዚህ መጽሐፍ ብቻ ይቀረፋሉ የሚል እሳቤም የለኝም፡፡ ቢሆንም የሱልጣኔቱን ታሪክ በማጥናት መሰል ሥራዎችን ለማሳተም ለሚፈልጉ ወገኖች እንደ አቅጣጫ ጠቋሚ ሊያገለግል ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡

የዚህን መጽሐፍ ይዘት በጥቅሉ እንደሚከተለው ማቅረብ ይቻላል፡፡

·       መጽሐፉ ስድስት ክፍሎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ክፍል ክፍል ጥናቱ የተካሄደበትን ጊዜ እና ዘዴ፣ ለጥናቱ ያገለገሉትን ዋነኛ የመረጃ ምንጮች፣ ደራሲው የተጠቀማቸውን የመረጃ ትንተና እና የማስረጃ ምዘና ስልቶች፣ መጽሐፉ የተቀናበረበትን መንገድና አንባቢያን በንባባቸው ወቅት ሊገነዘቧቸው የሚገቡ መመሪያዎችን ይዘረዝራል፡፡

·       ሁለተኛው ክፍል ለአዳል ሱልጣኔት ምሥረታ መንስኤ በሆኑ ኩነቶችና የሱልጣኔቱ መነሻ በነበሩት ቀደምት  መስተዳድሮች ታሪክ ላይ ያተኩራል፡፡ በዚህም መሠረት በቅድሚያ እስልምና በኢትዮጵያና በአፍሪቃ ቀንድ የተስፋፋበትና እስላማዊ መስተዳደሮች የተመሠረቱባቸው ሂደቶች ተዳስሰዋል፡፡ በማስከተል ደግሞ በሀገራችንም ሆነ በአፍሪቃ ቀንድ ቀጣና ስም ተክለው ያለፉት የሸዋ-መኽዙሚ ሱልጣኔት ታሪክ እና የኢፋት-ወላስማ ሱልጣኔት ታሪክ በሰፊው ቀርበዋል፡፡

·       ሶስተኛው ክፍል የአዳል ሱልጣኔት ከተመሠረተበት ዘመን ጀምሮ የተለመደው የሱልጣኔቱ የአመራር ዘይቤ በ1492 ገደማ እስከተለወጠበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ታሪክ ይዳስሳል፡፡ በተለይም በአዳል-ወላስማ ሱልጣኖችና በኢትዮጵያ ሰለሞናዊ ዐፄዎች መንግሥት መካከል የተካሄደው ትንቅንቅ በስፋት የቀረበው በዚህኛው ክፍል ነው፡፡ ከዚህ ሌላም በዚህኛው ክፍል የአዳል ሱልጣኔት መሬት፣ ህዝብ፣ የግዛት ወሰን፣ አውራጃዎችና ግዛቶች፣ ከተሞች፣ የሱልጣኔቱ የአስተዳደር ሁኔታና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም ከርሱ ጋር በተጻራራሪነት የቆመው የኢትዮጵያ ሰለሞናዊ ዐፄዎች መንግሥት የስልጣን ተዋረድ፣ የአስተዳደር አወቃቀርና የአገዛዝ ፍልስፍና፣ የጦር ኃይል፣ ኢኮኖሚ (በተለይም የመሬት ስሪት)፣ የሃይማኖት ተዋስኦ፣ የውጪ ግንኙነቶች ወዘተ… ተዳስሰዋል፡፡

·       አራተኛው ክፍል ከ1492 ጀምሮ ኢማም አሕመድ ኢብራሂም የአዳልን መራሄ መንግሥትነት ስልጣን ሙሉ በሙሉ እስከተቆጣጠረበት ጊዜ ድረስ በነበረው የሱልጣኔቱ ታሪክ ላይ ያተኩራል፡፡ ይህ ክፍል ከሌሎቹ የሚለየው በክፍሉ የቀረበው ትረካ በአዳል የጦርና የፖለቲካ መሪዎች (አሚር ማሕፉዝ፣ ገራድ አቡን፣ ኢማም አሕመድ እና ሱልጣን አቡበከር) ዙሪያ የተዋቀረ በመሆኑ ነው፡፡

·       ክፍል አምስት የመጽሐፉ መደምደሚያ የተጻፈበትና የአዳል ሱልጣኔት ታሪክን በበለጠ ሁኔታ አሟልቶ በሰነድ ለማስቀመጥ መከናወን ያለባቸው ሥራዎች የተጠቆሙበት ነው፡፡ በጥናቱ ሂደት ድጋፋቸውን ለለገሱ ግለሰቦችና ተቋማት ምስጋና የቀረበውም በዚህኛው ክፍል ነው፡፡

·       ክፍል ስድስት የተለያዩ አባሪዎች፣ የዋቢ ሰነዶች ዝርዝር እና የመጽሐፉ መጠቁም (index) የተካተቱበት ነው፡፡ ከመጽሐፉ አባሪዎች መካከል ሁለቱ በጥንት ዘመን በዐረብኛ ቋንቋ የተጻፉትና ብዙዎች (እኔን ጨምሮ) ለዓመታት ሊያገኟቸው ሲቸገሩባቸው የነበሩት “የመኽዙሚ ሱልጣኖች ዜና መዋዕል” እና “የወላስማ ሱልጣኖች ዜና መዋዕል” የሚባሉት የታሪክ ሰነዶች ናቸው፡፡ ተመራማሪዎችና የሱልጣኔቱን ታሪክ ለማጥናት የሚሹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሰነዶቹን በቀላሉ ያገኟቸው ዘንድ በተጻፉበት የዐረብኛ ቋንቋ ታትመዋል፡፡
----
ታሪክን የማጥናት አጋጣሚ የተፈጠረልኝ በ2001 ዓ.ል. የጥንታዊቷ የሀረር ከተማ ነዋሪ ለመሆን በመብቃቴ ነው፡፡ የአዳል ሱልጣኔትን ታሪክ የማጥናት ልዩ ፍላጎት ያሳደሩብኝ ግን የሰሜን ምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራትንና የህዝቦቻቸውን ታሪክና አንትሮፖሎጂ በሰፊው የጻፉት የዶ/ር ኤንሪኮ ቼሩሊ እና የፕሮፌሰር ኡልሪች ብራውኬምፐር ሥራዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም መጽሐፉ ለነዚህ ምሁራን መታሰቢያ እንዲሆን ተበርክቷል፡፡

ይህ መጽሐፍ በአዳል ሱልጣኔት ታሪክ ዙሪያ ልጽፋቸው ካሰብኳቸው ድርሰቶች መካከል የመጀመሪያው ነው፡፡ የርሱ ቀጣይ የሆነው ሁለተኛ መጽሐፍም ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ የኅትመት ጊዜውን እየጠበቀ ይገኛል፡፡ ወቅቱን ባላውቅም በቅርቡ ወደ አንባቢያን አደርሰዋለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። የመጽሐፉን ሶስተኛ ክፍል ለማዘጋጀት የሚደረገው እንቅስቃሴም ተጀምሯል፡፡ እርሱንም በቅርብ ጊዜያት ለማጠናቀቅ እሞክራለሁ፡፡ ለሁሉም ፈጣሪያችን ዕድሜና ጤና ይስጠን! አሚን!
  
አፈንዲ ሙተቂ                              
ሀረር፣ ምሥራቅ ኢትዮጵያ
ሀምሌ 2009 ዓ.ል.
---------
ü መጽሐፉ በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች ይገኛል፡፡ የመጽሐፉ ዋና አከፋፋይ አዲስ አበባ ለገሀር አካባቢ የሚገኘው ጃዕፈር መጻሕፍት መደብር ነው (ስልክ ቁጥሩ 0911-12 53 24 ነው)፡፡
ü የአንዱ መጽሐፍ መሸጫ ዋጋ 130 ብር ነው (በውጭ ሀገራት 30 ዶላር ነው)፡፡




Wednesday, January 17, 2018

የገለምሶው መምሬ ይፍሩ ወጎች

ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
ክርስቲያን ወንድሞቻችን የጥምቀት በዓልን በሚያከብሩበት ዋዜማ ላይ እንገኛለን፡፡ ከዚህ ቀደም በዓሉ በመጣ ቁጥር ትዝ የሚሉኝን መምሬ ሙላቱን የተመለከተ ትዝታዬን አካፍዬአችሁ ነበር፡፡ በዛሬው እለት ደግሞ በከተማችን ቀደምት አዛውንት ዘወትር የሚታወሱትን መምሬ ይፍሩን ላስተዋውቃችሁ ፈቀድኩ፡፡
----       
መምሬ ይፍሩ በሸዋ ክፍለ ሀገር ነበር የተወለዱት፡፡ በ1940ዎቹ የቀድሞው የጨርጨር አውራጃ (የአሁኑ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን) በአዲስ ሁኔታ ሲደራጅ የሀብሮ ወረዳ አጥቢያ ዳኛ ሆነው ወደ ገለምሶ መጡ፡፡ መምሬ ወደ ገለምሶ በመጡበት ዘመን ህዝቡ በፍትሕ እጦት በከፍተኛ ሁኔታ ይማረር ነበር፡፡ መምሬው ህዝቡ በተነገፈው ፍትሕ በጣም አዘኑ፡፡ በመሆኑም ለማንም ሳይወግኑና ፍርድ ሳያዛቡ የዳኝነት ስራቸውን ለመስራት ወሰኑ፡፡

በዘመኑ በመላው ኢትዮጵያ በጣም ይበደል የነበረው ጭሰኛው ገበሬ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም መምሬ ይፍሩ ጭሰኛው አርሶ አደር ምርቱንና ጉልበቱን የሚበዘብዙትን ባላባቶች በፍርድ ቤት እንዲፋረዳቸው አደፋፈሩት፡፡ ባላባቶች በጭሰኞቻቸው እንዳይከሰሱ ለመከላከል ተብሎ የተዘረጋውንና “በፍርድ ቤት የሚያስዘው ቋሚ ንብረት የሌለው ሰው ክስ መመሥረት አይችልም” የሚል ይዘት የነበረውን የዘልማድ አሰራር በመነቃቀል አስወገዱትና ጭሰኛው ባላባቶችን እንዲፋለማቸው መንገዱን ከፈቱለት፡፡

መምሬ ይፍሩ ለክስና ለምስክርነት የሚመጡትንም የሩቅ ሀገር ሰዎች በራሳቸው ቤት እየመገቡ ያሳድሯቸው ነበር ይባላል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በጭሰኞቹ ገላ ላይ በሚያዩት የነተበ ጨርቅ ያዝኑና የተለያዩ አልባሳትን ገዝተው ያለብሷቸው ነበር፡፡ ከሩቅ የመጡ ባለጉዳዮችን በቀጠሮ ከማጉላላትም ይቆጡ እንደነበረም ይነገራል፡፡

የዘመኑ ባላባቶች በመምሬ ይፍሩ አድራጎት በጣም ነበር የተደናገጡት፡፡ በመሆኑም “ይህ ሰውዬ ጭሰኞቻችን በኛ ላይ እንዲፈነጩ እያደረጋቸው ነው” የሚል ክስ በጭሮ (አሰበ ተፈሪ) እና በሀረር ለሚገኙት የበላዮቻቸው አቅርበዋል፡፡ ይሁንና መምሬው የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት እየጠቀሱ ባለስልጣኖቹ እንዲገሰጹ አድርገዋቸዋል፡፡ ከዚህም አልፎ የዘመኑ የሀረርጌ ጠቅላይ ግዛት ሹማምንት መምሬ ይፍሩ ፍትሕን ለማስፈን ያደረጉትን ጥረት በአዎንታዊነቱ በመውሰድ የወረዳ ገዥነት ሹመት እንደሰጧቸው ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡

መምሬ ይፍሩ ከመንግሥት የተሰጣቸውንም መሬት ከፋፍለው ለጭሰኞች ያስረከቡት ከባላባቶቹ በተለየ መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ የመሬት ከበርቴዎቹ እንደሚያደርጉት አርሶ አደሩ ካመረተው ምርት 75% በመሻማት ፈንታ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ምርቱን ከጭሰኛው ጋር እኩል ይካፈሉ ነበር፡፡ ታዲያ ይህንን ከማድረጋቸው በፊት ከጠቅላላው ምርት ገበሬው ለዓመት የሚሆነውን ቀለብ እንዲወስድ ይፈቅዱለታል፡፡ ገበሬው ከሚፍለው ግብርም ግማሹን ይከፍሉለታል፡፡

መምሬው እንደ ዘመኑ ባለባቶች ጭሰኛው የጉልበት ስራ እንዲሰራላቸውም አያስገድዱም፡፡ በዚህ ፈንታ ገበሬዎች የእርሻ ስራቸውን አጠንክረው እንዲሰሩ ይገፋፉአቸው ነበር፡፡ በህይወት ዘመናቸው መጨረሻ ገደማም አራት ጋሻ ከሚሆን መሬታቸው ከአምስት ሄክታር ያልበለጠውን ብቻ አስቀርተው ሌላውን ለጭሰኞች፣ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለመስጊድና ለታዋቂ የሙስሊም ዑለማ ሰጥተዋል፡፡
------         
መምሬ ይፍሩ በሃይማኖት ረገድ ያላቸው እይታም በብዙዎች ዘንድ ተደንቆላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ሙስሊሞች መስጊድ በሚሰሩበት ጊዜ የገንዘብ መዋጮ በማድረግ ይደግፏቸዋል፡፡ ከመንግሥት መሬትም ለአጣናና ለወራጅ የሚሆን ዛፍ እንዲወስዱ ይፈቅዱላቸው ነበር፡፡ በርሳቸው ድርጊት ልቡ ይነካ የነበረው ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በበኩሉ በተለያዩ ጊዜያት ብድሩን በመመለስ ተባብሮአቸዋል፡፡ ለምሳሌ መምሬ ይፍሩ ኮሚቴ አዋቅረው “ደረኩ” እና “ቦኬ” በሚባሉት ከተሞች ቤተ ክርስቲያን ባስገነቡበት ወቅት በርካታ ሙስሊሞች ለግንባታው የገንዘብ ድጋፍ አድርገው ነበር (ወላጅ አባቴ ለደረኩ ቤተክርስቲያን ግንባታ 200 ብር ለግሷል፡፡ የያኔው ሁለት መቶ ብር በመግዛት አቅሙ ከአሁኑ ሃያ ሺህ ብር እንደሚበልጥ ልብ በሉ)፡፡ በነገራችን ላይ “ደረኩ” እና “ቦኬ” የሚባሉትን ከተሞች የቆረቆሩት መምሬ ይፍሩ ራሳቸው ናቸው፡፡
-----
ስለመምሬ ይፍሩ የሚነገሩ አንዳንድ ወጎች “ideal” የሚባሉ ዓይነት በመሆናቸው “እውን በዚያ ዘመን ይህ ተፈጽሞ ነበርን?” ያሰኛሉ፡፡ ለምሳሌ መምሬ ይፍሩ የዐረብኛውን ቅዱስ ቁርኣን ማንበብ እንደሚችሉ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቁርኣን መማርና ማስተማር የሀይማኖቱን መሠረቶች ከመረዳት ባሻገር ፊደልን የማጥናት አካል እንደሆነ ያምኑ ነበር ይባላል፡፡ ስለዚህ ለርሳቸው የተማረ ሰው ማለት መደበኛ ትምህርትና የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ያጠናው ብቻ ሳይሆን የእስልምና የእውቀት ዘርፎችን ያጠናው ጭምር ነው፡፡

መምሬ ይፍሩ የመንግሥት ስራቸውን በሚሰሩበት ወቅት በቤተ ክርስቲያን የሚሰጡትን አገልግሎት አላቋረጡም፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በትርፍ ጊዜአቸው ህፃናትን ፊደል ያስጠኑ ነበር፡፡ በህይወታቸው መጨረሻ ላይ ደግሞ በገለምሶ ከተማ ምሥራቃዊ ጫፍ ላይ በሚገኘው ቤታቸው አጠገብ ያሰሩትን አንድ ክፍል የጸሎት ቤት ለዚሁ አገልግሎት በመመደብ ብዙ ህፃናት “ሀ ሁ”ን እንዲያጠኑ ረድተዋቸዋል (ለረጅም ጊዜ በዚህ ቤት ህፃናትን ፊደል ያስተማሩት “ጋሽ ሸዋንግዛው” የሚባሉትና በኛ ዘመን በጡረታ ላይ የነበሩት የድሮ መምህር ነበሩ፡፡ እርሳቸውም ህፃናትን በነፃ ያስተምሩ እንደመሆናቸው ውለታቸው የማይዘነጋ ነው)፡፡

በነገራችን ላይ እኔ ጸሐፊው የአማርኛን ፊደል ማጥናት የጀመርኩት መምሬ ይፍሩ ባሰሩት ጸሎት ቤት ነበር (በዘመኑ “ቄስ ትምህርት ቤት” ብለን ነበር የምንጠራው)፡፡ በርካታ የሙስሊም ልጆችም ጠዋት የቁርአን ትምህርታቸውን ከተማሩ በኋላ ከሰዓት የአማርኛ ፊደል ለማጥናት ወደ ቄስ ትምህርት ቤት ይሄዱ ነበር፡፡ ይሁንና ትምህርት ቤቱ ከመኖሪያ ቤታችን ባለው ርቀትና በመንገዱ ላይ የሚጫወቱ ህፃናት በሚያሳርፉብን ምት ወዲያውኑ ነበር የተማረርኩት፡፡ በመሆኑም በአስራ አምስት ቀኔ ትምህርቱን አቋርጬ ወጣሁና በመድረሳዬ ብቻ ተወሰንኩ፡፡
----
መምሬ ይፍሩ እኔ ከመወለዴ በፊት ነው ያረፉት፡፡ በዚያ ዘመን ሀገሪቱን ይገዛ የነበረው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ መንግሥት በኦፊሴል በሚከተለው ፖሊሲና በሚፈጽማቸው ተግባራት ከርሳቸው ጋር ይራራቃል፡፡ የወቅቱ መንግሥት በጊዜ ነቅቶ እርሳቸው ያንፀባረቁትን ተራማጅነት በግማሹ እንኳ ቢከተል ኖሮ ሀገራችን ዛሬ በተሻለ ደረጃ ላይ በተገኘች ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ ለሁሉም ብዙዎች በጫቷ ብቻ የሚያውቋት ገለምሶ መምሬ ይፍሩን የመሰሉ አርቆ አስተዋይ ስብዕናዎች ታሪክ የሰሩባት መድረክ እንደሆነች እወቁልን እላችኋለሁ፡፡
----
አፈንዲ ሙተቂ
ጥር 9/2010
በሸገር ተጻፈ፡፡


Monday, January 15, 2018

መረራ ጉዲናን ሳስታውሰው



ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
በ1988 የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና (ESLCE) እንደወሰድኩ ነው፡፡ ዕለቱ ከሚያዚያ ወር መአልት አንዱ መሆኑ ይታወሰኛል፡፡ በዚያች ዕለት የጀርመን ድምጽ ራድዮ ከቀደሙት የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለየ ዓላማን ያነገበ ድርጅት መቋቋሙን ዘገበ፡፡ የፓርቲው መስራች የሆኑት ግለሰብ የተናገሩትንም ቀንጨብ አድርጎ አስደመጠን፡፡  በጉዳዩ ዙሪያ ሐሳባቸውን የሰጡ ግለሰቦች “አዲሱን ድርጅት የመሠረቱት ግለሰብ ለኦሮሞ ህዝብም ሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች አዲስ ራዕይ ያላቸው ናቸው” ማለታቸውንም ሰማን፡፡
በዚያች ዕለት ድምጻቸውን የሰማናቸው ግለሰብ የያኔው ረ/ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ የአሁኑ ዶክተር መረራ ጉዲና ነበሩ፡፡ እርሳቸው የመሠረቱት ድርጅት ደግሞ “የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረስ” ይባል ነበር (ከ1998 ወዲህ “ኦህኮ” ተብሎ ነበር፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት ደግሞ የቀድሞው ኦፌዴን እና “ኦህኮ” አንድ ላይ ተዋህደው “ኦፌኮ” የሚባል ድርጅት ፈጥረዋል)፡፡
በዕለቱ በተላለፈው የሬድዮ ዘገባ ዶ/ር መረራ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ነገር “መገንጠል ከኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ጋር አይሄድም፤ የኦሮሞ ህዝብ በስፋቱና በብዛቱ ልክ በኢትዮጵያ ፖለቲካና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ውስጥ ሁነኛ ስፍራ እንዲኖረው መታገል ነው የሚሻለው” የሚል ነበር፡፡ ይህ የዶ/ር መረራ የፖለቲካ አስተርዮ በርካታ ደጋፊ ያፈረላቸውን ያህል ብዙ ተቃዋሚዎችም አስነስቶባቸዋል፡፡ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በ1990 እስኪቀሰቀስ ድረስም ለፖለቲካ የቀረቡ የሀገራችን ዜጎች የሚራኮቱበትና የሚቆራቆሱበት ዋነኛ አጀንዳም እርሱ ነው፡፡ በወቅቱ ከፍተኛ አንባቢ የነበራቸው የግል ጋዜጦችና መጽሔቶችም ለዶ/ር መረራ ከፍተኛ ሽፋን ይሰጧቸው ነበር፡፡
በዚያ ወቅት ዶ/ር መረራ ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠማቸው ከኦሮሞ ሊሂቃን እና መገንጠልን ከሚደግፉ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደነበረ ይታወቃል፡፡ በዘመኑ የኦሮሞን የፖለቲካ መድረክ (Spectrum) ተቆጣጥሮት የነበረው “የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል” የሚለው አማራጭ ነበር፡፡ ስለሆነም ከዚህ የተለየ አማራጭ ይዞ ወደ ኦሮሞ ፖለቲካ በሚቀላቀል ግለሰብም ሆነ ድርጅት ላይ ተቃውሞ ይቀርብበት ነበር፡፡ በሂደት ግን በዶ/ር መረራ የተቋቋመው ፓርቲ የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር ከመታገል ውጪ ሌላ አጀንዳ እንደሌለው በርካቶች ተረድተዋል፡፡ ዶ/ር መረራ የለኮሱት ርእዮት ለኦሮሞ ህዝብ መቅረብ ካለባቸው አማራጮች ቀዳሚው እንደሆነም ተገንዝበዋል፡፡
----------                                         
አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ዶ/ር መረራ ጉዲናን በመልክ ያወቃቸው የ1992 ሀገር አቀፍ ምርጫን በማስመልከት የተዘጋጀው የፓርቲዎች ክርክር ተቀድቶ በቴሌቪዥን ሲተላለፍ ነው፡፡ ክርክሩ በሁለት ወቅቶች (በታሕሳስና ሚያዚያ 1992) ነበር የተካሄደው፡፡ ዶ/ር መረራ አይረሴ (classic) ሆነው የተመዘገቡላቸውን “የሚበላውን ያጣ ህዝብ መሪዎቹን ይበላል” እና “የኢህአዴግን ልብ እንኳን ሰው እግዚአብሄርም አያውቀውም” የተሰኙ ታዋቂ አባባሎችን የተናገሩት በነዚያ የክርክር መድረኮች ላይ ነበር፡፡
በኔ እይታ ዶ/ር መረራ እጅግ ውጤታማና ማራኪ ክርክር ያካሄዱት ያኔ ነው፡፡ በተለይም ዶ/ር መረራ በሚያዚያ-1992 በተካሄደው ክርክር ያሳዩት ብቃት የተለየ ነው፡፡ በውይይቱ ወቅት የገዥውን ፓርቲ ጥፋቶችና ድክመቶች እየነቀሱ በማውጣትም ሆነ የራሳቸው ፓርቲ የሚያራምደውን ዓላማ በማብራራት ረገድ ከሁሉም ተከራካሪዎች በልጠው ታይተዋል፡፡ በንግግራቸው መሀል የሚወረውሯቸው ቀልዶችና ሽሙጦችም ከመሬት ጠብ የማይሉ ነበሩ፡፡ በጥቂቱ ብናስታውሳቸው አይከፋም፡፡
በሚያዚያ-92 በተካሄደው ክርክር ገዥውን ፓርቲ ወክለው የተገኙት ወይዘሮ ገነት ዘውዴ ለአርባ ደቂቃ ያህል “ኢህአዴግ ያስገኛቸው የልማት ውጤቶች” የሚል ይዘት ያለውን ንግግር አቀረቡ፡፡ ከርሳቸው በማስከተልም የመናገሩ ተራ የዶ/ር መረራ ጉዲና ሆነ፡፡ ታዲያ ዶ/ር ንግግራቸውን የጀመሩት እንዲህ ነበር፡፡
“አፄ ኃይለ-ሥላሴ ‘የምንወደውና የሚወደን ህዝባችን’ እያሉ የኢትዮጵያን ዕድገት በ40 ዓመት ወደ ኋላ ጎተቱት፡፡ ደርግ ደግሞ ‘አስራ ሰባት የትግልና የድል ዓመታት’ እያለ ኢትዮጵያን ከሶስት ደሀ የዓለም አገሮች አንዷ አደረጋት፡፡ ኢህአዴግም በተራው “አንጸባራቂ የልማት ድሎች” እያለን ኢትዮጵያን የዓለም ቁጥር አንድ ደሀ ሀገር አደረጋት”
(በአዳራሹ የነበረው የክርክሩ ታዳሚ ሳቀ፡፡ ዶ/ር መረራም ፈገግ አሉ፡፡ ትንፋሽ ከወሰዱ በኋላ ደግሞ ንግግራቸውን እንዲህ በማለት ቀጠሉ)

“ቢሆንም ኢህአዴግ የወሰደው እርምጃ ደግ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም “ቀኝ ኋላ ዙር” በተባለ ጊዜ በኢኮኖሚያችን ከዓለም አንደኛ እንሆናለን”
(አዳራሹ በድጋሚ በሳቅ ተናወጠ፡፡ ክርክሩን በዳኝነት ይመሩ የነበሩት ዶ/ር ገብሩ መርሻ እና በሀገር ሽማግሌነት የተጋበዙት ደራሲ ማሞ ውድነህ ጭምር ይስቁ እንደነበረ አስታውሳለሁ)፡፡
-------
ዶ/ር መረራ በዚያ የክርክር መድረክ ላይ አጽንኦት የሰጡት አንዱ ጉዳይ “ብሄራዊ እርቅ” ነው፡፡ በወቅቱ የነበሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብሄራዊ እርቅን የሚደግፉ ሲሆን እርቁን የሚገፋው ኢህአዴግ ብቻ ነበር፡፡ ይህንኑ በማስመልከት ዶ/ር መረራ በክርክሩ ላይ የሚከተለውን ተናግረዋል፡፡

“አንድ የኦሮሞ ህዝብ ተረት “Waraabeessi balleessaa isaa waan beekuuf jecha halkan dukkana deema” ይላል፡፡ “ጅብ ያጠፋውን ነገር ስለሚያውቅ በጭለማ ይጓዛል” ማለት ነው፡፡ ኢህአዴግም የብሄራዊ እርቅ ጥሪን የሚገፋው ያጠፋውን ስለሚያውቅ ነው፡፡
(ሌላ ሳቅ አዳራሹን ደበላለቀው፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና የተናገሩት የኦሮምኛ ተረትም በሳምንቱ የወጡት ጋዜጦች ዐቢይ ርእስ ለመሆን በቃ)፡፡
-------
በዚያ የECA አዳራሽ “ተቃዋሚዎች የሰነዘሩትን ሐሳብ እንዲሞግቱ” በሚል የኢህአዴግ ትልልቅ ካድሬዎች ለአምስት ደቂቃ ያህል እንዲናገሩ ይፈቀድላቸው ነበር፡፡ ከነዚያ ካድሬዎች መካከልም አንዳንዶቹ ስሜታዊ ይሆኑና የተቃዋሚ መሪዎችን በኃይለ-ቃል እስከ መወረፍ ይደርሱ ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ ፈርጅ የተከወነ አንድ ነገር ዘወትር አይረሳኝም፡፡ እንዲህ ነው፡፡

ኦህዴድን ወክለው በአስረጅነት ከተገኙት ባለስልጣናት አንዱ የነበረው አቶ ዮናታን ዲቢሳ “ድርጅታችን ያስገኘው የልማት ውጤት” ያለውን መረጃ ስሜታዊ በሆነ መልኩ አቀረበ፡፡ በማስከተልም “ረ/ፕሮፌሰር መረራን የመሳሰሉ ሰዎች ግን ኦህዴድን እንደተለጣፊ ድርጅት ነው የሚያዩት” የሚል ክስ ሰነዘረ፡፡ ዶ/ር መረራም ለአቶ ዮናታን መልስ ሲሰጡ እንዲህ በማለት ጀመሩ፡፡
“እኔ የኦሮሞን ልጅ ተለጣፊ ብዬ አላውቅም፡፡ ምናልባት አቶ ዮናታን ኦነግ የሚላቸውን ነገር ይዘው ይመስለኛል በዚህ የሚከሱኝ”
በማስከተልም ዶ/ር መረራ ለአቶ ዮናታን የሚከተለውን ምላሽ ሰጡ፡፡
“ቢሆንም ግን የኦህዴድ ሰዎች ምስጋና አታብዙ! እባካችሁ ከአቶ ሐሰን ዓሊ ተማሩ!! እንደምታውቁት ከሐሰን ዓሊ በላይ እኔ ነኝ ያለ የኦህዴድ ካድሬና የስርዓቱ ደጋፊ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ወደ አሜሪካ ኮብልሎ “እንኳንስ ህዝቡ እኔ ራሴ ነፃነት አልነበረኝም” እያለ ነው፡፡ ስለዚህ ለነገው መንገዳችሁ ስትሉ ምስጋና አታብዙ”

ዶ/ር መረራ ይህንን ተናግረው ዓመት እንኳ ሳይሞላ ነበር አቶ ዮናታን ዲቢሳ መኮብለሉ የተሰማው፡፡ በሚያዚያ 1992 በተዘጋጀው የክርክር መድረክ ላይ በልበ ሙሉነት ሀገር ሲያስተዳድር እንደነበረ ለማስረገጥ ያልጣረውን ያህል ባለፉት 16 ዓመታት ግን “የኦህዴድ ገመና” ያለውን ሁሉ ሲዘከዝክ ከርሟል፡፡ ዶ/ር መረራ በመድረኩ ላይ የሰጡት መልስ አንቅቶት ከሀገር ጠፍቶ ይሆን? ምክንያቱ አልታወቀም፡፡ አጋጣሚው ግን የሚረሳ አይደለም፡፡
------
ዶ/ር መረራ በምርጫ-97 ወቅት በተካሄዱት ክርክሮችም ከፍተኛ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ ዶክተሩ በነዚያ መድረኮች ላይ ካሳዩት ገቢሮች መካከል ብዙዎች የሚያስታውሱት ከአባዱላ ገመዳ ጋር ያደረጉትን ፍጥጫ ነው፡፡ ዶ/ር መረራ በመድረኩ ላይ መናገር የጀመሩት አባዱላን እንዲህ በመተረብ ነበር፡፡

“አቶ አባዱላ! መቼም “ጄኔራል” የሚል ማዕረግ ነበርዎት፡፡ ያ ማዕረግ ከብዙ ልፋት በኋላ የተሰጥዎት ስለሆነ መከበር አለበት፡፡ ስለዚህ ጄኔራል ብዬ ብጠራዎት እንዳይከፋዎት”
(ሁሉም ተከራካሪ ሳቀ፡፡ በጣም የሳቁት ደግሞ አባዱላ ገመዳ ራሳቸው ናቸው)፡፡

በዚህ መድረክ ላይ አባዱላ ገመዳ “በዶ/ር መረራ የሚመራው “ኦብኮ” የቀድሞ ስርዓት ናፋቂዎች ተላላኪ ነው” የሚል ክስ አቅርበው ነበር፡፡ ታዲያ ዶ/ር መረራ መልሱ አልከበዳቸውም፡፡ ወዲያውኑ ነበር የመልስ ምታቸውን እንዲህ በማለት የወረወሩት፡፡
“አባዱላ ገመዳ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ከየት ወደየት የሚል መጽሐፋቸውን ሲጽፉ የኔን መጻሕፍትና በመጽሔቶች ላይ የወጡትን ጽሑፎቼን ከሰላሳ ጊዜ በላይ እንደ ምንጭ ጠቅሰዋል፤ አሁን ደግሞ ተላላኪ ነህ ይሉኛል፤ ተላላኪ ከሆንኩ ጽሑፎቼን በምንጭነት ሲጠቀሙ እንዴት እምነት ሊጥሉብኝ ቻሉ? ይህ ሊገባኝ አልቻለም”
(ሳቅ እንደገና ትንሹን አዳራሽ ሞላው፡፡ በነገራችን ላይ ቅንጅትን ከወከሉት ተከራካሪዎች አንዱ የነበሩት አቶ ሙሐመድ ዓሊ እዚሁ ፌስቡክ ላይ ስላሉ አሁን በጻፍኩት ላይ ማስተካከያ ሊሰጡን ይችላሉ፡፡ እኔ የጻፍኩት በአዕምሮዬ የማስታውሰውን ብቻ ነው)
 -------
መረራ ጉዲና በሚያስተምርበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለአራት ዓመታት (ከ1989-1992) ነበርኩ፡፡ ይሁንና በነዚያ ዓመታት ለአንድም ቀን እንኳ አይቼው አላውቅም፡፡ ከዚያ በኋላም እርሱን በአካል ያየሁት ለሶስት ወይንም ለአራት ጊዜ ብቻ ቢሆን ነው፡፡ በማስሚዲያና በፕሬስ ግን ዘወትር እከታተለዋለሁ፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ድምጹን የሰማሁትና በቪዲዮም ያየሁት በአምናው ክረምት እርሱ፣ ጌታቸው ረዳ፣ ነጃት ሀምዛ እና ፍጹም ብርሃነ በአል-ጀዚራ ቴሌቪዠን ለክርክር በቀረቡበት ጊዜ ነው፡፡ በቀደሙት ዓመታት መጽሐፎቹንና መጣጥፎቹን አንብቤአቸው ነበር፡፡ ስለስብእናውና ስለግላዊ ህይወቱ በደንብ የተረዳሁት ግን በ2006 የታተመውን ግለ-ታሪኩን ሳነብ ነው፡፡
በዚህ ዓመት (2009) መግቢያ ላይ ዶ/ር መረራ በሽብርተኝነት ተጠርጥረሀል ተብሎ መታሰሩ ይታወሳል፡፡ በብዙሀኑ የሀገራችን ዜጎችም ሆነ በዓለም አቀፍ ተቋማት “አፋኝና ጨቋኝ” ተብሎ የተወገዘውን የጸረ-ሽብር ህግ ያጣቀሰ ክስም ተከፍቶበታል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ እጆቹ በካቴና ታስሮ ልብ በሚሰብር ሁኔታ ወደ ፍርድ ቤት ሲወሰድ የሚያሳይ ፎቶግራፍ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወር ነበር፡፡
አንዳንዶች “ፎቶው በሐሰት የተሰራ ነው” እያሉ ነው፡፡ ይሁንና ዋናው ነገር ፎቶው አይደለም፡፡ እጅግ በጣም ልብ የሚያደማው ዋነኛ ነገር ከአበባ የወጣትነት ዘመኑ ስምንት ዓመታትን በከርቸሌና በማዕከላዊ ምርመራ ያሳለፈው፣ ደርግ ከወደቀ በኋላም የሚበዛ ጊዜውን ለህዝብ መብት መከበር ሲታገል የነበረው፣ በዩኒቨርሲቲው በሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በማስተማር የአባትነት ኃላፊነቱን የተወጣው፣ በዚህች ሀገር የተቃውሞ ፖለቲካን በሰለጠነ መንገድ ማካሄድን ሲያስተምር የቆየውና ይህ የተቃውሞ ፖለቲካ ባህል ስር እንዲሰድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው ዶ/ር መረራን የመሰለ ጎምቱ ምሁር በመጦሪያው ወቅት “አሸባሪ” ተብሎ ወደ እስር ቤት መወርወሩ ነው፡፡
የዶ/ር መረራ እጣ ፈንታ ያሳዝናል፡፡ በጣም ያስጨንቃል፡፡ ሰዎች የተለየ የፖለቲካ አመለካከት በመያዛቸውና ለሀገርና ለህዝብ የማይበጁ አዝማሚያዎችን በመቃወማቸው ብቻ እንደ ጠላትና ሽብርተኛ ሲፈረጁ ማየት ሁላችንንም ያሳስበናል፡፡ ባለፉት 26 ዓመታት በዚሁ መንገድ ስንጓዝ ከርመናል፡፡ ገዥው ፓርቲው “በጥልቀት ታድሻለሁ” በሚልበት በዚህ ወቅት ቀዳሚው ትኩረቱ ዜጎች ያለ አንዳች ስጋትና ፍርሐት የሚኖሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት መሆን ነበረበት፡፡
አሁንም ድምጻችንን ደግመን እናሰማለን!! ዶ/ር መረራን ጨምሮ በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ በየወህኒ ቤቱ የታሰሩት ዜጎቻን ይፈቱልን!! አላግባብ የታሰሩ የፖለቲካ መሪዎች ይፈቱልን!! አላግባብ የታሰሩት የህዝበ-ሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ይፈቱልን!! አላግባብ የታሰሩት ጋዜጠኞች ይፈቱልን!! አላግባብ የታሰሩት ተማሪዎች ይፈቱልን! “ሽብርተኛ” እየተባሉ አላግባብ የታሰሩት ሙስሊም ወጣቶች ይፈቱልን! ሁሉም ዜጋ በሀገሩ ላይ ያለ ፍርሐት የሚኖርበት ሁኔታ ይፈጠርልን!! የሰዎችን ነፃነት የሚተበትቡትና ሀገሪቱን በዓለም ዙሪያ መሳለቂያ እያደረጉ ያሉት “የጸረ-ሽብር ህግ”ን የመሳሰሉ አፋኝ አዋጆች ይወገዱልን!!
አላህ ሀገራችንና ህዝቦቻችን በሰላምና በፍቅር ያኑርልን! አሚን!! 
----
አፈንዲ ሙተቂ
ሀምሌ 25/2009

በአዳማ ከተማ ተጻፈ፡፡

Sunday, January 14, 2018

“ቡሩጁል ሱልጣን”ን በጨረፍታ


ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
----
በጥር ወር 2004 “ሀረር ጌይ” የተሰኘው መጽሐፌ በታተመበት ሰሞን ነው፡፡ አንድ ሰውዬ (ዘመድ ቢጤ ነው) “አፈንዲ! እኔ የምልህን ስማኝ!! አንድ ሁለት ፍሬ ይዘህ ከቢር እገሌ ጋ ሄደህ፣ ቀይ ዶሮ አሳርደህ እርሳቸው የገድ ኪታባቸውን እንዲቀሩበት ብታደርግ ውጤቱን በቶሎ ታየዋለህ” አለኝ፡፡ ከልቤ ሳቅኩኝ፡፡ “እፍረትም አያውቅ እንዴ ይሄ በዘበዛ?” በማለትም ተገረምኩኝ፡፡ እናም “ሲያምርህ ይቀራታል እንጂ. አላደርገውም” ብዬ አባረርኩት፡፡

   የአጋጣሚ ነገር ሆነና የመጽሐፉ ሽያጭ በመጀመሪያዎቹ ወራት በጣም ተንቀረፈፈ፡፡ ሰውዬውም በድጋሚ መጥቶብኝ “አይ አንተ ልጅ!.. አየህ መጽሐፍህ ገበያ እንዴት እንዳጣ!” ሲለኝ ጊዜ “አቦ ተወን ወደዚያ! ቢፈልግ ቤቴ ውስጥ እንደተቆለፈበት አይጥና አይጠ-መጎጥ ይብላው” አልኩትና በድጋሚ ጃስ አልኩት፡፡ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን የሽያጩ መንቀርፈፍ ከነከነኝና የዳሰሳ ጥናት አካሄድኩ፡፡ ችግሩንም ደረስኩበት፡፡ የችግሩ ምንጭም ሰብዓዊ ነበር እንጂ “የከቢር እገሌ ዛር ስለተቀየመኝ” አይደለም፡፡ ለምሳሌ “የኢትኖግራፊ ወጎች” የሚለውና በመጽሐፉ ሽፋን ላይ ያለው መለስተኛ ርእስ በአንባቢያን ዘንድ ግርታን ፈጥሮ ነበር፡፡ መጽሐፉን ያነበቡት ላላነበቡት ሰዎች ስለይዘቱ ሲያስረዱ ግን ሁኔታዎች እየተስተካከሉ ሄዱ፡፡ የልፋታችንን ዋጋ መመለስም ጀመርን!!
------
በቅርቡ “አዳል”ን ሳሳትምም ያንን ዘመዳችንን አስታወስኩት፡፡ ያ ሰውየ አሁንም አልተሻለውም፡፡ እንደለመደው “ፍየል ገዝተን፣ ቅጠል ዘንጥፈን እገሌ ጋ እንሂድ” ባይ ነው (ፈጣሪ ብርሃኑን ያብራለትና)፡፡ እርግጥ ከርሱ የሚብሱና እነ ኦፋ ዳኜን ከፈጣሪ በማስበለጥ ነፍሳቸውን ሊሰጧቸው የሚከጅሉ ድኩማን አሉ፡፡ “አባባ ታምራት ገለታ” እንደ ኩርኩር ሲነዳቸው የነበሩ “አሪፍ ነን” ባይ ወተቴዎች ባሉበት ሀገር ውስጥ እንደምንኖርም አልዘነጋንም፡፡ “ስኒ አስገልብጠህ ፈለጉን አስነብብ” ከሚሉት አንስቶ “ቡሩጁል ሱልጣን” አስደግመህ በኪስህ ውስጥ አድርገው” እያሉ የሚነዘንዙ በዘበዛዎችም ሞልተዋል (ነዑዙቢላህ)!! ሁሉንም መታዘብ ነው እንግዲህ!! “ዓለም ቲያትር ናት” አለ ያ ሼክስፒር!!
   ኧረ እንዲያውም ሌላውን ወደ ጎን እናድርግና ስለ“ቡሩጁል ሱልጣን” ትንሽ እንጨዋወት!! ይሄ “ቡሩጁል ሱልጣን” ከሁሉም የከበደው “ሲሕር” ነው ይባላል፡፡ “ሳሒሮቹ” ድግምቱን ሲሰሩ በመጀመሪያ የአንተንና የእናትህን ስም ይወስዳሉ (የእናት ስም የሚወሰደው “የአንድ ሰው ትክክለኛ እናቱ እንጂ ትክክለኛ አባቱ አይታወቅም” የሚለውን ጥንታዊ እሳቤ በመንተራሰስ ነው)፡፡ ከዚያም በስሞቹ ውስጥ ያሉት ሆሄያት በጥንታዊው ዐረብኛ ይሰራበት በነበረው የ“አብጀድ” የፊደል ገበታ ላይ ያላቸውን ክብደት አስልተው ይደምሩታል (እዚህ ጋ አንድ ነገር ልብ በሉ!! ፊደላቱ በአብጀድ ቅደም ተከተል ተድርድረው የተለያየ ክብደት የተሰጣቸው በመሠረቱ ለጥንቆላና ለመተት ስራ ሲባል አይደለም፡፡ በድሮ ዘመን ነገሮችንና ክስተቶችን በፊደላቱ ክብደት ልክ መሰየም በጣም ስለሚወደድ ነው ይህ ልማድ የተፈጠረው፡፡ ለምሳሌ “ሀረር” ሲባል “405” እንደማለት ነው፡፡ ዝርዝሩን “ሀረር ጌይ” በተሰኘው መጽሐፌ በሰፊው ገልጬዋለሁ)፡፡
   በማስከተልም ሳሒሮቹ “ሀዛ ቡሩጁል ሱልጣኑን ወል-ሀመሉን ወል-ሚርሪዙን” እያሉ ህብረ-ቃሉን ይደጋግሙታል፡፡ በመጨረሻም የፊደላቱን መጠሪያ በመለዋወጥ እኛ “ቢልቂሳ” የምንላትን ጂንኒ ይጠሩባታል (ለምሳሌ “ሲን” የሚባለውን የዐረብኛ ፊደል ሲጠሩት “ኺጥ” ይላሉ፤ “ሷድ”ን ደግሞ “ቃድ” ይሉታል፣ “ዋው”ን ደግሞ “ዋር” ይሉታል፡፡ “ካፍ”ንም “ራፍ” ይሉታል ወዘተ…)፡፡ ይህንን ሁሉ ደረጃ አልፎ የሚታሰረው መተትና የሚሠራው ድግምት በታንክና በቢ-ኤም እንኳ አይፈራርስም ይባላል፡፡ እነ እገሌ ሀብታም የሆኑትም በርሱ ነው ይባል ነበር (ዋ!! እኛ ሲባል የሰማነውን ነው የጻፍነው)፡፡
   ታዲያ በዛሬው ዘመን “ኢሉሚናቲ”ን በመሳሰሉ ተረቶች የሚያምን በርካታ የሩቅ መንገደኛ መኖሩ ቢያስገርመኝ “ይሄንን ወፈ-ሰማይ አጩሌ በቡሩጁል ሱልጣን እያቀዣበርኩ በዘበዛ ላድርገው እንዴ?” አሰኝቶኝ ነበር!! (በሹክሹክታ አንድ ሚስጢር እናጫውታችሁ! ባሎቻችሁ አርፎ አልቀመጥ ያላችሁ ሴቶች!! እንኳን ደስ አላችሁ!! ለዚህ ፍቱን መድኃኒቱ ይኸውላችው!! ቡሩጁል ሱልጣንን በወረቀት ላይ አስደግማችሁ በሰውዬአችሁ ሙንታታ ውስጥ ጣሉለት!! ሰውዬአችሁ ሌላ ሴት ባሰበ ጊዜ “ነገርዬው” ኩንታል ሙሉ ጅልቦ እንደተሸከመ “ሀምማል” ተዝለፍልፎ ይወድቃል ይባላል!! ዘዴው ውጤታማ ነው አሉ ሚስጢሩን ያጫወቱኝ ሰዎች! ስስስሽሽሽሽ…! ሚስጢር ነው እንግዲህ)!!
----                           
አፈንዲ ሙተቂ   
ሀምሌ 2009

በአዳማ ከተማ ተጻፈ፡፡

Saturday, January 13, 2018

የገለምሶው ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብን በጨረፍታ

                                     
ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
---
በከተማችን ነዋሪዎችና በሌሎች አካባቢዎችም ዘንድ በጣም የሚከበሩት ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ በትናንትናው እለት አርፈዋል፡፡ ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ ዕድሜአቸው ወደ መቶ ዓመት ሆኖአቸው ነበር፡፡ አላህ ዕድሜ ሰጥቶአቸው ብዙ ማየት ቢችሉም የሄዱት ተመልሰው ወደማይመጡበት ዓለም ነውና እርሳቸውን በማጣታችን መሪር ሐዘን ተሰምቶናል፡፡

ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ በአንድ ዘመን በገለምሶና በመላው የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ፈክተው ይታዩ ከነበሩት እነ ሼኽ ሙሐመድ ጡልላብ (ጪሮ)፣ ሼኽ ሙሐመድ ረሺድ ሼኽ ቢላል (ጭረቲ)፣ ሐጂ ዑመር አርቦዬ (ደረኩ)፣ ሼኽ ኒብራስ ሙሐመድ (አሰቦት)፣ ሼኽ አሕመድ ሼኽ አቡበከር (ቡሶይቱ)፣ ሙፍቲ ሓጂ ዑስማን (ገርቢ ጎባ)፣ ሼኽ ሐሰን አነኖ፣ ሼኽ ሻቶ ሚኦ (ጉባ ቆርቻ)፣ ሼኽ ሙሐመድ ጀልዲ (ሂርና) የመሳሰሉትን ታላላቅ ዑለማ ያፈራው ወርቃማው ትውልድ አባል ነበሩ፡፡ ከነዚያ ዑለማ መካከል እስከ ለታሪክ ተርፈው ረጅም ዓመት መኖር የቻሉት እርሳቸውና የገለምሶው ሼኽ ሙሐመድ ሲራጅ ብቻ ናቸው፡፡ እርሳቸው አሁን አርፈዋል፡፡ ሼኽ ሙሐመድ ሲራጅ ብቻ ቀርተዋል (ዕድሜአቸውን ያርዝመውና)፡፡
*****
ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ የተጸውኦ ስማቸው “ሙሐመድ ሐቢብ” ነው፡፡ ሸሪፍ” ደግሞ የማዕረግ ስማቸው ነው፡፡ እኝህ ዓሊም እንደ ሌሎች ዑለማ ሼኽ ተብለው ያልተጠሩት በትውልዳቸው ሸሪፍ በመሆናቸው ነው (ሸሪፍ የዘር ሐረጋቸው ከነቢዩ ሙሐመድ (..) ቤተሰብ ለሚዘዝ ሰዎች የሚሰጥ ማዕረግ ነው፤ አንዳንድ ጊዜም “ሰይድ” ይባላሉ፤ ከነቢዩ ቤተሰብ የተወለዱ መሆናቸው የሚነገርላቸው ጎልማሶችና ዑለማ በአብዛኛው “ሸሪፍ” እየተባሉ ነው የሚጠሩት)፡፡

ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ የተወለዱት በቀድሞው የጨርጨር አውራጃ (በአሁኑ ምዕራብ ሀረርጌ ዞን) በዶባ ወረዳ፣ ቢዮ ኸራባ በሚባለው መንደር ነው፡፡ ይሁን እንጂ የዕድሜአቸውን ግማሽ ያህል የኖሩት ሎዴ በተሰኘውና በገለምሶ ከተማ ዳርቻ ላይ ባለው መንደር ነው (መንደሩ ከከተማው ሶስት ኪሎሜትር ያህል ወጣ ብሎ ይገኛል)፡፡ ሸሪፍ ሙሐመድ በዚህ የሎዴ መንደር የከተሙት 1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው፡፡
------
ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ በመምህርነት፣ በአባትነት እና በሀገር ሽማግሌነት ህዝቡን ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ታዲያ እኝህ ዓሊም ከሌሎች የገለምሶ ዑለማ በበለጠ ሁኔታ የሚታወሱበትና ስማቸውን የተከሉበት አንድ ቁምነገር አለ፡፡ ይኸውም ዘጠና ዘጠኙን የአላህ ስሞች (አስማኡላሂል ሑስና) እየጠሩ ዚክር ማድረግን ለአካባቢያችን ህዝብ በስፋት ያስተዋወቁ መሆናቸው ነው፡፡

የሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ ደረሳ ሆኖ አስማኡል ሑስና ያልሓፈዘ (በቃሉ ያልያዘ) የለም ለማለት ይቻላል፡፡ “ሐርፍ” መቁጠር (ፊደል ማጥናት) ከጀመረው ህፃን አንስቶ ኪታብ እስከሚቀራው ደረሳ ያለው የሸሪፍ ሙሐመድ ተማሪ “እስቲ የአላህ ስሞችን ቁጠርልኝ” ብትሉት አንድ በአንድ ይነግራችኋል፡፡ እሳቸው ከኖሩበት መንደር ነዋሪዎች መካከልም ብዙዎች አስማኡል ሑስናን በቃላቸው ይዘዋል፡፡

 ታዲያ ይህ የሸሪፍ ሙሐመድ አስማኡል ሑስና አብዮት በሒፍዝ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ደረሳዎቻቸው በልዩ ልዩ ወቅቶች የሚያዜሟቸው ዚክሪዎችም አስማኡል ሑስና መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ እነዚህ ዚክሮች በድቤ ታጅበው በዜማ የሚዘከሩ በመሆናቸው “መንዙማ” ይባሉ ይሆናል፡፡ በአካባቢያችን ልማድ መሠረት ግን “አስማኣ” ወይንም “አስማኡል ሑስና” ነው የሚባሉት፡፡

በኛ ዘንድ መንዙማ የሚባለው በግጥም እየተቀኘ የሚጻፈው ውዳሴ ነው፡፡ የሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ “ዚክሪ” ግን ከአላህ ስሞች በስተቀር ሌላ ግጥም የለውም፡፡ ሸሪፍ ሙሐመድ የሚገጥሙት አዝማቹን ብቻ ነው፡፡ ተከታዮቹ ግጥሞች ደግሞ ዘጠና ዘጠኙ የአላህ ስሞች ናቸው፡፡ እስቲ ለወግ ያህል ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ ዜማና አዝማች እያወጡላቸው ያቀናበሩዋቸውን አንዳንድ የአስማኣ ዚክሪዎችን ላካፍላችሁ፡፡
------
አንዱ የሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ ዚክሪ የሚከተለው አዝማች አለው(ተቀራራቢ ትርጉሙ በቅንፍ ውስጥ የተጻፈው ነው)፡፡

አላህ ቀሲሙን ዳኢሙ (አንተ የምትረዝቀው ሁሌም የምትኖረው አላህ ሆይ)
አላህ ቀሲሙን ዳኢሙ (አንተ የምትረዝቀው ሁሌም የምትኖረው አላህ ሆይ)
ሱብሓነከ ቃኢሙ (ከጉድለት ሁሉ የጠራኽ ነህ አንተ ዘወትር ያለኸው)

ጀመዓው ድቤ እየመታና በአንድ ሼኽ እየተመራ ይህንን ዚክሪ እየደጋገመ ያዜማል፡፡ በዚህ በኩል የሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ ዚክሪዎች በሌሎች አካባቢዎች ከምታውቋቸው መንዙማዎች ልዩነት የላቸውም፡፡ ሼኹ ዚክሪውን ሲመራው ግን የአላህ ስሞችን እንደሚከተለው ይጠራቸዋል፡፡

ራሕማን ረሒም አላህ (ጀመዓው አላህ ቀሲሙን ዳኢሙ እያለ ይቀበላል)
ደያኑን ቡርሓን አላህ (አሁንም ጀመዓው አላህ ቀሲሙን ዳኢሙ ይላል)
አወሉን አኺር አላህ 
ወሊዩን ከቢር አላህ
 (ሼኹ የመጨረሻዎቹን ሁለት ግጥሞች በአንድ ላይ ስለሚላቸው ጀመዓው በጸጥታ ያሳልፋል)፡፡

ሼኹ ይህንን ተናግሮ ፋታ ሲወስድ ጀመዓው እንደገና አላህ ቀሲሙን ዳኢሙ ይዘምራል፡፡ ከዚያም ሼኹ ሌሎች የአላህ ስሞችን ይጠራል፡፡ ጀመዓው እንደገና አላህ ቀሲሙን ዳኢሙ ያዜማል፡፡ እንደገና ሼኹ ሌሎች የአላህ ስሞችን ይጠራል፡፡ እንዲህ እንዲህ እየተባለ ሼኹ ሁሉንም የአላህ ስሞች ጠርቶ እስኪያበቃ ድረስ ዚክሪው ይሄዳል፡፡

ታዲያ ሼኹ ሁሉንም የአላህ ስሞች ጠርቶ ገቢሩን የሚዘጋው በነቢዩ ሙሐመድ ላይ ሰለዋት በማውረድ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ለሁሉም ዚክሪዎች የሚያገለግለው አንድ ባለ አራት መስመር ግጥም ነው፡፡ ግጥሙ እንዲህ ይሄዳል፡፡

መዐ-ስ-ሰላሚላህ መዐ-ስ-ሰላሚላህ (ከአላህ ሰላም ጋር፣ ከአላህ ሰላም ጋር)
ዐላ ሙሐመዲን ወ ኸይሩ ኸልቂላህ (የፍጡራን ሁሉ በላጭ በሆነው ሙሐመድ ላይ በሚወርደው)
ወል አህሊ ወሳህቢ ወማ ፊ ዲኒላህ (በቤተዘመዶቹ፣ በባልደረቦቹና በአላህ ዲን ውስጥ ባለው ሰው ሁሉ)
ዐላ ሙሐመዲን ወኩሊ ጁንዲላህ (በሙሐመድ እና በአላህ ሰራዊትም ላይ)

*****
ሸሪፍ ሙሐመድ “አስማኣዎቹ”ን በየጊዜው ነው የሚያወጡት፡፡ እነርሱን በቃል መያዝ ደግሞ በጣም ቀላል ነው፡፡ በሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ ከተደረሱት ዝነኛ የአስማኣ ዚክሮች መካከል የሚከተሉትን ማስታወስ ይቻላል፡፡

1.  ሐስቡነላህ ወኒዕመል ወኪሉ
ሐስቡነላህ ወኒዕመል ወኪሉ
ኒዕመል መውላ ወኒዕመ-ንነሲሩ

2.  ቢስሚላሂ ራሕማኒ-ረሒም
አልሐምዱሊላህ ወሱብሓነላህ
ረብቢ ሰልሊ ዐላ ሙሐመድ

3.  አላሁ አላህ አላሁ አላህ
ሱብሓነከ ያ ሳቲረል ዑዩብ
ጋፊረ ዙኑብ

4.  አላሁ አላሁ ሚንከል መደዱ
አላሁ አላሁ ሚንከል መደዱ
ጀማል ከውኒ አንተል አሐዱ

5.  አላሁ አላህ ያ አላህ
ራሕማን ያ ረሒም
ኢርሐምና ወል-ሙስሊሚና
በርሩ ያ ከሪም

*****
ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ በአንድ ወቅት የደረሱት “አስማኣ” በህብረተሰቡ ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ አስማኣ የሚከተለው አዝማች ነበረው፡፡ 

አላሁ አላህ አላህ ዘልፈረጂ
በሺር ረብበና ቢል ቢል-ኢማን ኩለል ፈረንጂ
የአማርኛ ትርጉሙ እንደሚከተለው ሊሆን ይችላል፡፡

አንተ የፈረጃ ባለቤት የሆንከው አላህ ሆይ
ፈረንጆችን ሁሉ በኢማን አብስራቸው (ኢማን ሙላባቸው)፡፡

ሸሪፍ ሙሐመድ ይህንን ዚክሪ ለምን እንደጻፉ ሲጠየቁ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡
እነኝህ ፈረንጆች ኢማን ባይኖራቸውም አብዛኞቹ ደግ ናቸው፡፡ የሚሰሩት ነገርም ደግ ነው፡፡ ከአውሮፕላን እስከ መኪና፣ ከመርከብ እስከ ባቡር የተሰሩት በእነርሱ ነው፡፡ እነርሱ በሰሯቸው መጓጓዣዎች ነው ወደ ሐጂ የምንሄደው፡፡ የምግብ ማብሰያ ቡታጋዝና ማታ የምናበራውን ፋኖስ የፈለሰፉት እነርሱ ናቸው፡፡ ሰዎች የሚለብሷቸው አልባሳትም በአብዛኛው በነርሱ የሚሰራው፡፡ ሌላው ይቅርና ድርቅ ሀገራችንን በሚያጠቃበት ወቅት የእርዳታ እህል የሚመጸውቱን እነርሱ ናቸው፡፡ በመሆኑም ነው እነዚህ ደጋግ ፈረንጆች ኢማን ኖሯቸው አላህ ጀንነት እንዲሰጣቸው የተመኘሁት” 
    
*****
እኝህ ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብ አስማኣን ከመቀመር በተጨማሪ የሚታወቁባቸው አስገራሚ ጸባዮችም ነበራቸው፡፡ ለምሳሌ ጉዳይ ሲይዛቸው ከመንደራቸው እስከ ገለምሶ የሚመጡት በእግር ነው፡፡ የመልስ ጉዞውንም የሚያደርጉት በእግር ነው፡፡ በመንገዱ ላይ የሚዘዋወሩ መኪናዎች ሲቆሙላቸው በጭራሽ አይሳፈሩም፡፡ በእጃቸውም እንደ ሽማግሌ ከዘራ አይዙም፡፡ በተጨማሪም በሐድራቸው ከመቶ ከማያንሱ ደረሳዎቻቸውና ልጆቻቸው ጋር እየኖሩ አንድም ሰው በጉዞአቸው እንዲያጅባቸው አይፈቅዱም፡፡ ይህ በብዙ ሼኾች ዘንድ ያላየሁት ጸባያቸው ነው፡፡

ሸሪፍ ሙሐመድ ሐቢብን ለመጨረሻ ጊዜ ያየኋቸው የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ነበር፡፡ አንድ ቀን ተመልሼ የሕይወት ታሪካቸውን በስፋት አጠናለሁ የሚል ሐሳብ ነበረኝ፡፡ ነገር ግን ሐሳቤ ሳይሞላልኝ እርሳቸው ቀድመውኝ ወደ አኺራ ሄዱ፡፡ አላህ በጀንነት ያብሽራቸው፡፡ መልካም ስራቸውን ይቀበላቸው፡፡
------
አፈንዲ ሙተቂ
መጀመሪያ ሐምሌ 10/2006 በገለምሶ ከተማ ተጻፈ፡፡
እንደገና ተሻሽሎ ጥር 5/2010 በሸገር ተጻፈ፡፡