Pages

Tuesday, December 28, 2021

 

የአድአው ጥቁር አፈር

------

ዝክረ ተስፋዬ ገብረአብ (ክፍል አንድ)

-----

ጸሐፊ: አፈንዲ ሙተቂ

-----

እውቁ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ሃያሲ፣ ገጣሚና ተርጓሚ ተስፋዬ ገብረአብ ከትናንት ወዲያ ዐርብ ታህሳስ 15/2014 አርፏል። ሰውዬው በሕይወት በኖረባቸው አመታት በጎራ የተከፈሉ አውጋዦች እና አድናቂዎች በከረረ ሁኔታ ሲነታረኩበት የነበረ ከመሆኑ የተነሳ ትክክለኛ ታሪኩ ተደብቆ በሰዎች ምናብ የተፈጠረ ጥላው ብቻ እንደ ግለ-ታሪኩ ሲነገር የኖረ ነው። ታዲያ በህይወት ያለን አድናቂዎቹና ወዳጆቹ እውነተኛ ማንነቱን የማውሳት ግዴታ አለብን። ከኛ የሚጠበቀውን ለማሟላት ስንልም ከብዙ በጥቂቱ ልንዘክረው ነው።

------

ተስፋዬ ገብረአብ "የጋዜጠኛው ማስታወሻ" በተሰኘ ድርሰቱ ውስጥ "የአድኣ ጥቁር አፈር ያበቀለኝ ነኝ" ይላል። አድኣ በቀድሞው የኤረር እና ከረዩ አውራጃ ምዕራባዊ ክፍል የሚገኝ ወረዳ ነው። የአድኣ አፈር በእርግጥም ጥቁር ነው። በአድኣ አፈር ላይ የተዘራ እህል በረካ አለው ይባላል። መሬቱ በጣም ለም ከመሆኑ የተነሳ እህል ከተዘራበት እጥፍ በእጥፍ ሆኖ ነው ምርቱን የሚሰጠው። የአድኣ ጥቁር አፈር የዘሩትን ሁሉ መልሶ የሚሰጥ ነው። በመሆኑም የአካባቢው የቱለማ ኦሮሞዎች ሲመራረቁ "እንደ አድኣ ጥቁር አፈር ይባርክህ" ይላሉ። ተስፋዬም የእነርሱን አባባል ወስዶ ነው ለራሱ መጠሪያ ያደረገው።

የአድአ ወረዳ ዋና ከተማ "ቢሾፍቱ" (ደብረ ዘይት) ናት። ከቢሾፍቱ አጥቢያዎች አንዱ "ቀጂማ" ይባላል። አንዳንዶች አጥቢያውን በአካባቢው ካለው የጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ጋር በማያያዝ "ቀጂማ-ጊዮርጊስ" ይሉታል። ተስፋዬም ይህንን አጠራር ሲጠቀም አንብበነዋል። ይሁንና ሰፈሩ በአብዛኛው የሚታወቀው "አርመን ሰፈር" በሚል መጠሪያ ነው። ይህም በአካባቢው መኖሪያቸውን ቀልሰው ይኖሩ በነበሩት የአርሜኒያ ዜጎች ስም የተሰጠ ስያሜው ነው።

የተስፋዬ አባት የሆኑት አቶ ገብረአብ ሀብተጽዮን 1950ዎቹ መግቢያ ላይ ከኤርትራዋ የመንደፈራ ከተማ ተነስተው በቢሾፍቱ ከተማ ሰፈሩ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ የተስፋዬ እናት የሆኑት ወይዘሮ መዓዛ ገበረወልድም ባለቤታቸውን ተከትለው ወደ ቢሾፍቱ መጥተው አብረዋቸው ይኖሩ ጀመር። አቶ ገብረአብም የአርመን ዜጎች ይዞታ በሆነ የአካባቢው እርሻ ላይ በዘበኝነት ተቀጠሩ።

አቶ ገብረአብ ሀብተጽዮን በአርመን ሰፈር ሲኖሩ ብዙ ልጆችን ወልደዋል። ከእነርሱም አንዱ ተስፋዬ ገብረአብ ነው። ተስፋዬ (ተስፍሽ) ለወላጆቹ አራተኛ ልጅ ሲሆን የተወለደው ነሐሴ 1960 ነው። በልጅነቱ ከዕድሜ እኩዮቹ ጋር ሆኖ ቢሾፍቱን ተደስቶባታል። ጨፍሮባታል። ከቢሾፍቱ ከተማ ባሻገርም በተፈጥሮ በተዋበው የአድአ ወረዳ ጋራና ሸንተረር፣ ተራራና ሸለቆ፣ ወንዞችና ሐይቆች እየተዟዟረ ከጓደኞቹ ጋር ቦርቋል። ከእረኞች ጋር ከብት እየጠበቀ በዘፈናቸው ተደስቷል። ከኦሮሞ ገበሬዎች ጋር በኢሬቻና በአርፋሳ "ዋቃ ጉራቻ" ለምኗል። የወላጆቹ እምነት የሆነውን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትናን የሚያውቀውን ያህል የኦሮሞን ባህልና ትውፊትም አድጎበታል።

ተስፋዬ ገብረአብ በኋላ ላይ ወደ ደራሲነት ሲሸጋገር "ወርቃማው ዘመን" ብሎ የሚጠራውን የልጅነት ሕይወቱን እያጣፈጠና እያሳመረ በብዙ መጣጥፎቹ ተርኮልናል። የተስፋዬ ገብረአብ ብዕር ሃይል፣ የትረካ ክህሎትና የጽሑፍ አወራረድ ጎልቶ የሚታየውም የልጅነት ህይወቱን በሚተርክበት ጊዜ ነው። ብዙዎችም በልጅነት ዘመኑ ላይ ባጠነጠኑት ትረካዎቹ ተመስጠው "የአፍሪቃ ቀንድ ማክሲም ጎርኪ" ብለውታል። እኔም (አፈንዲ ሙተቂ) በአንድ ወቅት "ለምን ፖለቲካ ነክ ጽሑፎችን ቀንሰህ ስለልጅነት ዘመንህ በብዛት አትጽፍልንም?" ብዬው ነበር። እርሱም በሃሳቤ ተስማምቶ በልጅነት ዘመኑ ላይ ብቻ ያጠነጠነ መጽሐፍ ሊጽፍ ቀጠሮ ይዟል። ነገር ግን ውሳኔውን ተፈጻሚ ሳያደርግ እውነተኛው የሞት ቀጠሮ መጥቶ ወደ ሁለተኛው ዓለም ወስዶታል። ቢሆንም የመጽሐፉ ረቂቅ የሚገኝ ከሆነ ካለበት ፈልገን የህትመት ብርሃን ልናሳየው ይገባል።

-------

ተስፋዬ ገብረአብ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስኪገባ ድረስ ከወላጆቹ ዘንድ ኖሯል። ወላጆቹ ሲያርፉ ግን በዚያው የቢሾፍቱ ከተማዋ አግብታ ትኖር ከነበረችው ታላቅ እህቱ ዘንድ ተጠግቷል። በትምህርቱ የደረጃ ተማሪ ባይሆንም ከአንደኛ እስከ አስረኛ ከሚወጡት መካከል ነው። በዚያው ልክ ከልጅነቱ ጀምሮ ገደብ የሌለው የማንበብ ፍቅር ተጠናውቶት ነበር። ከንባቡ ጎን ለጎን ደግሞ ግጥሞችንና አጫጭር ታሪኮችን ይጽፋል።

በዚያው ወቅት አቶ እውነቱ የሚባሉት የአየር ሃይል ሆቴል ባለቤት ልጆቻቸውን እንዲያስጠናላቸው ቀጥረውት ለኪሱ መደጎሚያ የሚሆን ገንዘብ ይሰጡት ነበር። እኒህ የተከበሩ ሰው ለወጣቱ ተስፋዬ ገብረአብ ቤተ መጻሕፍታቸውን ክፍት አድርገውለት በእርሳቸው ቤት ብዙ መጻሕፍትን ለማንበብ እንደበቃ ተስፍሽ "የደራሲው ማስታወሻ" በሚል ርእስ በጻፈው መጽሐፍ ተርኮልናል።

ተስፋዬ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መልቀቂያ ፈተና ያገኘው ውጤት ለኮሌጅ የሚያበቃው አልነበረም። በዚህም የተነሳ ከታላቅ እህቱ ጋር ተጋጨ። ከእህቱ ግሰጻ ለመሸሽ ሲልም ወደ ድሬ ዳዋ በባቡር እየሄዱ የሳልባጅ ልብስ አምጥተው ከሚሸጡት ነጋዴዎች አንዱ ለመሆን ሞክረ። ይሁንና የሰውዬው ቀልብ ለንባብና ለጽሑፍ እንጂ ለንግድ አልመች አለች። በንግዱ ከስሮ በጥቂት ወራት ውስጥ ከስራው ውጪ ሆነ።

ተስፋዬ የንባብ ሱሰኛ እንደመሆኑ ከጽሑፍ ጋር የተገናኘ ስራ ለመስራት ይመኝ ነበር። በተለይም የበዓሉ ግርማ እና የብርሃኑ ዘርይሁንን ስራዎች በጣም ያፈቅራቸው ስለነበረ እንደ እነርሱ ደራሲና እና ጋዜጠኛ የመሆን ምኞት ነበረው። 1979 ጀምሮም ለኢትዮጵያ ሬድዮ፣ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እና ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ጽሑፎችን ይልክ ጀመር። ሆኖም ከጥቂቶቹ በቀር ብዙዎቹ ጽሑፎች ለንባብና ለአየር አልበቁለትም። ቢሆንም ተስፋ አልቆረጠም። በጽናትና በትእግስት ማንበቡንም አላቋረጠም። በኋላ ላይ ደግሞ የንባብ ጥማቱ ስለጠነከረበት መጽሐፎቹን በሻንጣ ተሸክሞ ይዞር ነበር።

እያደር ደግሞ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች ታዩ። ተስፋዬ የሚያቀርባቸው የተለያዩ ጽሑፎች በሬድዮ እና በጋዜጣ አልፎ አልፎ ይቀርቡ ጀመር። ይህም ከስነ-ጽሑፍ ዓለም እንዳይርቅ ረድቶታል።




------

እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 1981 ነው።

የተስፋዬ ገብረአብን የህይወት ጉዞ ሙሉ በሙሉ የቀየረው አጋጣሚ የተከሰተው በዚህ ዓመት ነበር። በዚያ ዘመን ዘወትር እሁድ፣ ጠዋት 4:30-500 ባለው ጊዜ የኢትዮጵያ ድምጽ ብሄራዊ አገልግሎት የሚባለው "የጦር ሃይሎች የሬድዮ ፕሮግራም" የተባለ ዝግጅት ያስተላልፍ ነበር። ተስፋዬ ገብረአብም ለዚህ ፕሮግራም ጽሑፎችን እየላከ በአዘጋጆቹ ተደንቆለታል። በየሳምንቱ እሁድ ጠዋት ሲመጣም በአራት ሰዓት ተኩል ላይ ሬድዮ ካለበት እየሄደ የእርሱ ጽሑፍ መተላለፉን ይከታተል ነበር።

ታዲያ በአንደኛዋ እሁድ ጠዋት ተስፋዬ የሬድዮ ፕሮግራሙን ሲያደምጥ የመከላከያ ሚኒስቴር በግንባር ያለውን ጦር ሞራል የሚያጎለብቱ፣ በጽሑፋቸው ሰራዊቱን የሚቀሰቅሱ እና የጦሩን ውሎ ከግንባር የሚዘግቡ ወጣቶችን መልምሎ በመኮንንነት ለማሰልጠንና ለመቅጠር እንደሚፈልግ ማስታወቂያ ያስነግራል። ይህ ማስታወቂያ በተስፋዬ ልብ ውስጥ ብሩህ ተስፋን ሲፈነጥቅ ተሰማው። በተለይም ማስታወቂያው እርሱ የሚፈልጋቸውን ሁለት ነገሮች ያሟላ በመሆኑ በቸልታ ሊያልፈው አልፈቀደም። አንደኛ፣ ተስፋዬ ስራ ፈላጊ ነበር። በወቅቱ ለተቀጣሪ መኮንኖቹ የሚከፈለው ደመወዝ ሶስት መቶ ብር ነው። ይህም በያኔው ኑሮ ከፍተኛ ገቢ ነው። በተለይም በቢሾፍቱ ከተማ ሶስት መቶ ብር አንድ ላም ይገዛ ነበር (ላቋርጣችሁና! በገለምሶ ከተማ ደግሞ እኔ ራሴ 1984 መጨረሻ ላይ አንድ ኮርማ በሬ ሽጥ ተብዬ 620 ብር ሸጬዋለሁ) በሌላ በኩል በማስታወቂያው የተነገረው ስራ ተስፋዬ ከልቡ ሲመኝ ለነበረው የጋዜጠኝነትና የስነ-ጽሑፍ ሙያ በር ከፋች የሚሆን ዓይነት ነው።

ተስፋዬ ገብረአብ በማግስቱ ወደ ፊንፊኔ በርሮ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ተመዘገበ። ከተመዝጋቢዎቹ መካከል የተሻሉት ተለይተው በእጩ መኮንንነት ወደ "ሁርሶ ጦር ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት" ተላኩ። አዳዲሶቹ ምልምሎች ስልጠናቸውን አጠናቅቀው 1982 አጋማሽ ላይ በምክትል የመቶ አለቃ ማዕረግ ተመረቁ። ብዙም ሳይቆይ ሁላቸውም ወደ ኤርትራ፣ ትግራይ፣ ጎንደር፣ ወለጋ፣ ሀረርጌ እና ኦጋዴን ተላኩ።

ምክትል የመቶ አለቃ ተስፋዬ ገብረአብ እና ሃያ የሚሆኑት ጓዶቹ የተመደቡት በጎንደር ክፍለ ሀገር፣ ጋይንት አውራጃ የነበረውን 603 ኮር እንቅስቃሴ እንዲዘግቡ እና የፕሮፓጋንዳ ጽሑፍ እንዲያዘጋጁ ነበር። ይሁንና የአንድ ወር ደመወዝ እንኳ ሳይቀበሉ በታላቁ የደብረ ታቦር ውጊያ ላይ ከያኔው የኢህአዴግ ሰራዊት ጋር ፍልሚያ ገጠሙ። በውጊያው ከሁለቱም ወገን ብዙዎች አለቁ። የኢትዮጵያ ሠራዊት አዛዦች በሂሊኮፕተርና በጂፕ አመለጡ። ተስፋዬ ገብረአብ ደግሞ የኢህአዴግ ጦር በተኮሰው መትረየስ ግራ እጁ ላይ ክፉኛ ተመትቶ ህሊናውን ሳተና ከአንድ ገደል ስር ገባ። ከነበረበት የሰመመን ዓለም ሲባንን ራሱን የወያኔ ምርኮኛ ሆኖ አገኘው።

-----

አዎን! የተስፋዬና የወያኔ ትውውቅ የጀመረው በዚህ መንገድ ነው። ተስፍሽ ለኢትዮጵያ ሊዋጋና የጦሩን ውሎ ሊዘግብ ወደ ጎንደር ዘምቶ ነው በወያኔ የተማረከው። ከዚያ በፊት ከህወሓት ጋር ፈጽሞ አይተዋወቅም። ከህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) ጋር የተዋወቀው ደግሞ ከዚህ በጣም ዘግይቶ ነው። ተስፋዬ ከመነሻው ጀምሮ የወያኔ እና የሻዕቢያ የውስጥ አርበኛ እንደነበረ አድርገው የሚተርኩልን ሁሉ በጩኸትና በግርግር ብዛት ውሸትን ወደ እውነት ለመቀየር የሚውተረተሩ ገገማዎች ከመሆናቸው ውጪ ስለእርሱ የሚያውቁት አንድም ሚስጢር የለም። እውነትን የምትሹ ከሆነ እውነቱ ይህ ነው።

-----

ተስፋዬ ገብረአብ በወያኔዎች ሲማረክ ኢህአዴጎች ተራ ወታደር ነበር የመሰላቸው። ሰራዊቱን እንዲቀሰቅስና የጦር ሜዳ ውሎዎችን እንዲዘግብ የተቀጠረ መስመራዊ መኮንን መሆኑን ሲያውቁ ግን ሊጠቀሙበት ፈለጉ። በዚህም ቁስሉን በአፋጣኝ አክመውለት የኢህአዴግ ሬድዮ ጣቢያ ከነበረበት ሀገረ-ሰላም የተባለ የትግራይ የገጠር ቀበሌ ላኩት። ከዚያስ ምን ተከሰተ?

በክፍል ሁለት እናየዋለን።

(ይቀጥላል)

-----

አፈንዲ ሙተቂ

ታህሳስ 17/2014

ሀረር-ምሥራቅ ኢትዮጵያ

------

©Afendi Muteki, December 27/2021

-----

የቴሌግራም ቻነሌ የሚከተለው ነው።

You may join my telegram channel here.

https://t.me/afandishaHarar